ግርማ ካሣ (ቺካጎ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

“ኢትዮጵያውያንን እስከሆንን ድረስ ትግራይ መሬታችን ነው። ኦሮሚያ መሬታችን ነው። ደቡብ ና ሶማሊያ መሬታችን ነው። አፋርም መሬታችን ነው። ለነርሱም ትግራይ መሬታቸው ነው። አማራም ትግራይ መሬቱ ነው። ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ማመን አለብን። ከዚህ ውጭ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶችን እንደጠላት ለማስፈራሪት መጠቀም የሥልጣን እድሜን ማራዘሚያ እንደሆነ መታወቅ አለበት። አሁንም በሰላምዊ ትግል ካመኑትና ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብረን መሥራት እንቀጥላለን።” - አቶ ገብሩ አሥራት

“ኢትዮጵያ እኮ የኢህአዲግ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የእኛም ናት” - አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

“ኢትዮጵያችን” - ዶ/ር መራራ ጉዲና

አቶ ስየ አብርሃና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራውን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መቀላቀላቸውን በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። አስተያየቶቹ በጥቅሉ ብንመለከታቸው በሦስት ምድብ የሚከፈሉ ናቸው። የመጀመሪያው ምድብ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ስሜት ያንጸባርቃል ብዬ የማስበው፣ በአቶ ስየ አብርሃና በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ውሳኔ የተደሰቱ ኢትዮጵያውያን አስተያየቶችን የያዘ ምድብ ነው።

 

ሁለተኛው ምድብ አቶ ስየና ዶ/ር ነጋሶ የቀድሞ የኢህአዲግ ባለሥልጣናት ከመሆናቸው የተነሳ የአንድነት ፓርቲን መቀላቀላቸው ያላስደሰታቸው ወገኖች አስተያየቶችን የያዘ ምድብ ነው። በዚህ ምድብ ያሉ የተቃውሞ አስተያየቶች በብዛት በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ፣ በጠራ አዕምሮ ታስበውና ተወጥነው የወጡ ተቃውሞዎች ሳይሆኑ ከግለሰባዊ ስሜትና ከቂም በቀል መንፈሥ የመነጩ ተቃውሞዎች ናቸው። “እነ አቶ ስየ ከዚህ በፊት የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት የነበሩ ጊዜ ላጠፉት ጥፋቶች ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል። ወንጀለኞች ናቸውና እንዴት የአንድነት ፓርቲ እነርሱን ይቀበላል” ይላሉ።

 

እርግጥ ነው አቶ ስየም ሆኑ ዶ/ር ነጋሶ የኢህአዲግ ባለሥልጣናት እንደመሆናቸው ኢህአዲግ ላጠፋው ጥፋቶች እነርሱም ተጠያቂዎች ናቸው። ነገር ግን ከኢህአዲግ አመራሮች ጋር ባሏቸው ልዩነቶች ምክንያት ኢህአዲግን ጥለው ወጥተዋል። ባለሥልጣን ሆኖ በመቀጠል፣ ሕሊናቸውን ሽጠው መኖር ሲችሉም ኢህአዲግ የሚያራምዳቸውን አንዳንድ ፖሊሲዎች በመቃወማቸው እነርሱም የኢህአዲግ በትር ደርሶባቸው እንደነበረ የሚታወስ ነው።

 

በኢህአዲግነታቸው ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወንጀል ሠሩ ከተባለ ደግሞ እንደማንም ዜጋ ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም።

 

የአንድነት ፓርቲ በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እንዲኖር የሚታገል ድርጅት ነው። የሕግ የበላይነት ስንል አንድ ሰው ነፃ በሆነ ፍርድ ቤት ተከሶ፣ እራሱን በነፃነት የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት ፍርድ ቤት ወንጀለኛ እስኪለው ድረስ ወንጀለኛ አይደለም። (innocent until proven guilty)። ስለዚህ አቶ ስየንም ሆነ ዶ/ር ነጋሶን በግላቸው ወንጀለኛ ናቸው ብሎ አሁን መፍረድ ትልቅ ስህተት ነው።

 

ከላይ እንዳልነው ወንጀል ሠሩ ከተባለ ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል። እነርሱም በማናቸውም ጊዜ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ዝግጁ እንደሆኑ በይፋ ገልጸዋል። አድራሻቸውን እናውቀዋለን። ሸሽተው ሀገር ጥለው አልሄዱም። ስለሆነም መካሰሱንና መወነጃጀሉን ለባለሞያዎችና ለዳኞች ትተን በእርቅ በይቅርታ በመቀባበልና በአንድነትን ሀገራችንን የምናድንበት ጊዜ ነው ባይ ነን።

 

አንድ ጊዜ አንዲት ሴት አመነዘረች ብለው በድንጋይ ሊወግሯት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመጧት። “ስለዚች ሴት ምን ትላለህ?“ ብለው ጠየቁት። እርሱም ሴትየዋ አላጠፋችም ብሎ አልመለሰላቸው። ነገ ግን “ከናንተ ሐጢያት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውር“ አላቸው። ሕሊናቸው እየወቀሳቸው አንድ በአንድ የሴትየዋ ከሳሾች ስፍራውን ጥለው ሄዱ። ጌታም “እኔም አልፈርድብሽም። ዳግም ሐጢያት አትስሪ” ብሎ ምህረት አደረገላት።

 

ሰዎችን መክሰስና የሰዎችን ወንጀል መቁጠር ቀላል ነው። የኢህአፓ አባሎች ብዙ ዜጎችን ገድለዋል። መኢሶንም እንደዚሁ። መቼም በደኖንና አርባ ጉጉን የምናስታውስ ኦነግ ያደረገውን እናውቃለን። የደርግንማ እንተወው። አቶ ስየ አብርሃ እራሳቸው አባታቸውንና ሁለት ወንድሞቻቸውን ደርግ ገድሎባቸዋል። እንነጋገር ከተባለ፣ ሁላችንም ብንመረመር ወንጀል አያጣንም። የሰው ደም ያፈሰስን ብዙ አለን። ደም ያላፈሰስንም ብንሆንና ጥይት ባንተኩስም ሰዎች ሲገደሉ ዝም ማለታችን እራሱ ተጠያቂ ያደርገናል። እንነጋገር ከተባለ ብዙ ብዙ ማለት እንችላለን።

 

ነገ ግን ቢበቃን አይሻልም ውድ ኢትዮጵያውያን? ጣዕሙ እንዳለቀ ማስቲካ ያለፈውን ከምናኝክ በይቅርታ ያለፈው ታሪካችንን ወደኋላ ትተን፣ ከዚህ በፊት የተፈጠረው ደም መፋሰስ ወደፊት እንዳይፈጠር በፍቅር መያያዙ አይሻለንም?

 

በሦስተኛው ምድብ እንደ ሁለተኛው ምድብ የነ አቶ ስየን ድርጊት የሚቃወሙ አስተያየቶችን የያዘ ምድብ ነው። ምክንያታቸው ግን የተለየ ነው። በዚህ ሦስተኛው ምድብ ያሉ አስተያየቶች አፍቃሪ ኢህአዲጎችና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የሚያራገቡት አስተያየቶች ናቸው።

 

ድልወንበሩ ነጋ የሚባሉ አንድ አፍቃሪ ኢህአዲግ ሰው አቶ ስየ አብርሃ የአንድነት ፓርቲ አባል መሆን እንዳላስደሰታቸው አይጋ ፎረም ላይ በወጣው ጹሑፋቸው “ለምንድን ነው የትግራይ ኩሩ ልጅ ስየ አብርሃ፣ ለትግራይ በቀል ዓረና ጀርባ ሰጥቶ በምርጫ 97 ፀረ-ትግሬ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩትን የሚቀላቀለው?” ሲሉ ነበር ዘረኛ፣ ጠባብና የኋላ ቀር አመለካከታቸውን ለማንጸባረቅ የሞከሩት።

 

በኢህአዲግ ውስጥ ችግር ፈጣሪ የሆኑት የአክራሪ ኃይሎች የፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ነው የሚባለው አይጋ ፎረም፣ የአቶ ድልወንበሩን ጽሑፍ ከማውጣቱ አንድ ቀን በፊት “ዛሬ ዶ/ር ነጋሶና አቶ ስየ የዓረና ትግራይንና የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄንና የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስን በማሳጣት ብዙም የማይታወቀውን የአንድነት ፓርቲ ለመቀላቀል ወስነዋል። አቶ ስየ አንድነትን መቀላቀላቸው ዓረና ትግራይ በርሳቸው ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ያሳያል” ሲል በአንድነት ፓርቲና በዓረና፣ ኦፌዲን፣ ኦህኮ መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር ሲፍጨረጨር ታዝበናል።

 

በመጀመሪያ ደረጃ በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት “ኢንተርሃምዌ” በማለትና ቅንጅት የትግራይ ወገኖቻችንን ለማጥፋት እንደተነሳ በማራገብ መሰረተ ቢስና አሳፋሪ ፕሮፖጋንዳ ሲረጩ የነበሩት እራሳቸው ኢህአዲጎች ነበሩ።

 

አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ፀረ-ትግሬ ወረቀቶች ተበትነው ነበረ። እነዚህን ወረቀቶች በአዲስ አበባ እየተሰራጩ መሆናቸውን የተገነዘቡ የቀድሞ የቅንጅት አመራር አባላት ይህ ወረቀት እነርሱ እንዳልጻፉትና አጥብቀው የሚያወግዙት መሆኑን የሚገልጽ መግለጫ ያወጣሉ። ኢህአዲግ ለሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና የኢትዮጵያ ራዲዮ መግለጫውን ለህዝብ እንዲያነብላቸው ቅንጅቶች ይጠይቃሉ። ነገር ግን መግለጫቸው ሳይነበብላችው ይቀራል።

 

ይህም የሚያሳየው ተበተነ የተባለው ወረቀት የመነጨው ከኢህአዲግ እንደነበረና ዓላማውም የትግራይ ወገኖቻችንን ከሌሎች ወንድሞቻቸው ለመለያየትና በፍርሃት ተሞልተው ወደዱም ጠሉም አገዝዙን እንዲደግፉ ለማድረግ ነበር።

 

እውነቱ ይሄ ሆኖ እያለ አቶ ድልወንበሩ በቅንጅት አካባቢ ፀረ-ትግሬ ቅስቀሳ ተደርጎ ነበር ማለታቸው፤ ሰውዬው ተራ የአገዛዙ ካድሬ መሆናቸውን ያሳያል። የሚጽፉትና የሚያራግቡትም ከእውነት የራቀና በጥላቻ ላይ ያተኮረ ጊዜው ያለፈበት ርካሽ ፕሮፖጋንዳ ነው።

 

አቶ ድልወንበሩና አይጋ በጻፉት ላይ ለማንሳት የምፈልገው ሌላም ነጥብ አለ። አቶ ድልወንበሩ የጻፉት ትክክል ነው እንበል። አቶ ድልወንበሩ በኢህአዲግ፣ መኢአድ፣ የአቶ ልደቱና የአቶ ጫሚሶ ቡድኖች ጋር በሼራተን የተደረገውን ስምምነት ይደግፋሉ። በዚህ ስምምነት ከአቶ መለስ በስተቀር ሁሉም የቅንጅት አባል የነበሩ ሰዎች ናቸው።

 

ታዲያ አቶ መለስ ዜናዊ ከቀድሞ ቅንጅታውያን ጋር በሼራተን ከተጨባበጡ አቶ ስየ አብርሃ ብርቱካን ሚደቅሳ ከምትመራው ፓርቲ ጋር አብረው ለመሥራት መወሰናቸው እንዴት ሆኖ ነው ፀረ-ትግሬ ውሳኔ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው? አቶ መለስ ሲያደርጉት ጣፋጭ፤ አቶ ስየ ሲያደርጉት መራራ የሚሆንበት ምክንያቱ ምንድን ነው?

 

አቶ ገብሩ አሥራት ድርጅታቸው ዓረና ትግራይ በመቀሌ ባደረገው የመጀመሪያ ህዝባዊ ስብሰባ ወቅት አንድ የማልረሳውና ልቤን የነካው ትልቅ አባባል ተናግረው ነበር። አቶ ገብሩ አሥራት በመስቀል አደባባይ በተደረገ አንድ ሠላማዊ ሰልፍ ከሌሎች የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በመሆን በዚያ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። ያኔ ያደረጉትን ንግግር በማስታወስ አንድ የኢህአዲግ ካድሬ “የትግራይ ጠላት ከሆኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተገኝተው ለምን ንግግር አሰሙ?” በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ገብሩ ሲመለሱ፤ “ኢትዮጵያውያን እስከሆንን ድረስ ትግራይ መሬታችን ነው። ኦሮሚያ መሬታችን ነው። ደቡብ እና ሶማሊያ መሬታችን ነው። አፋርም መሬታችን ነው። ለነርሱም ትግራይ መሬታቸው ነው። አማራም ትግራይ መሬቱ ነው። ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ማመን አለብን። ከዚህ ውጭ የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶችን እንደጠላት ለማስፈራሪያነት መጠቀም የሥልጣን ዕድሜን ማራዘሚያ እንደሆነ መታወቅ አለበት። አሁንም በሠላምዊ ትግል ካመኑትና ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብረን መሥራት እንቀጥላለን።” በማለት ድርጅታቸው ከሌሎች የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሠራና በኢትዮጵያ የመከፋፈል ፖለቲካ ቦታ እንደማይኖረው ነበር ያስረዱት።

 

ያኔ በመቀሌው ስብሰባ በአቶ ገብሩ አሥራት ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ነው አሁን በአቶ ስየ ላይ እየተሰነዘረ ያለው። ነገር ግን አቶ ስየ ከማንም የበለጠ በኢህአዲግ ውስጥ ያለውን የሚያውቁ እንደመሆናቸው በርሳቸው ላይ ለሚሰነዘረው መሰረተ ቢስ ጥቃቶች አቶ ገብሩ እንደመለሱት ሁሉ በቂ ምላሽ እንዳላቸው አልጠራጠርም።

 

አቶ ስየና አቶ ገብሩ እንዲሁም ሌሎች ከተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ለአንዲት ኢትዮጵያ፣ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባት፣ ለሠላም፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለመልካም አስተዳደር ለመሥራት መወሰናቸው ኢህአዲግ የትግራይን ህዝብ ከሌላው በመነጠል፣ የትግራይን ህዝብ በማስፈራራት ሲያገኝ የነበረውን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር፣ የትግራይን ህዝብ በእጅጉ የሚጠቅም፣ በወንድማማቾች መካከል ፍቅርንና መቀባበልን የሚያመጣ ትልቅ ክንዋኔ ነው።

 

በአድዋ፣ በጉንደት፣ በጉራ፣ … በአንድ ላይ ስንሆን የጋራ ጠላቶቻችንን አሸንፈናል። አሁንም ትግሬው፣ አማራው፣ ኦሮሞው፣ አፋሩ፣ … ሁሉም ወደ አንድነት ሲሰባሰብ ሀገር ታድጋለች። አንዱ ተበድሎ ሌላው አይጎዳም። ሁላችንም በጋራ እናድጋለን። አቶ ስየና ዶ/ር ነጋሶ የአንድነት ፓርቲን ሲቀላቀሉ፣ አቶ ገብሩ የመድረክ የህዝብ ግንኙነት፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና የመድረኩ ሊቀመንበር ሆነው ሲሠሩ ማየት ኢህአዲግ ይዞት የነበረው ትልቁ በዘር የመከፋፈል መሣሪያው ዋጋ ቢስ እንደሆነበት በግልጽ የሚያሳይ ነው።

 

አይጋ ፎረም እንዲሁ በከንቱ በአንድ በኩል አንድነት በሌላ በኩል በዓረና/ኦህኮ/ኦፌዲን መካከል ልዩነት ለመፍጠር እያደረገ ያለው ከንቱ ጥረት በተመለከተ ትንሽ ብለን እናቆማለን።

 

አይጋ የአንድነት ፓርቲን “ብዙ የማይታወቅ” ሲል ፓርቲውን ለማንኳሸሽ መሞከሩ በጣም የሚያስቅ ነው። ፓርቲው ደጋፊዎቹና አባላቶች በየክልሉ እየታሰሩበትና እየተዋከቡበት የአገዛዙን በትር ተሸክሞና ችሎ ህዝብን አሁንም እያንቀሳቀሰ ያለ ጠንካራ ድርጅት ነው። ሰማኒያ አራት ጽ/ቤቶች ያሉት ሲሆን፤ በገጠር፣ በከተማ፣ በኦሮሞያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ ክልል፣ በአፋር በመላው ኢትዮጵያ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ያለው ድርጅት ነው።

 

ኢህአዲግ ፓርቲው ጠንካራ በመሆኑ ፈርቶና ሰግቶ ሊቀመንበሯን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሕገ-ወጥና ተልካሻ በሆነ ምክንያት በቃሊቲ እሥር ቤት እንድትታሰር ያደረገው ለምን እንደሆነ ጠንቅቆ የሚያውቀው አይጋ ፎረም፤ የአንድነት ፓርቲ በርግጥ ጠንካራ ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ከተደረገ ትግራይን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቷ ግዛት አሸናፊ እንደሚሆን ውስጡ ይገነዘበዋል ብለን እናስባለን።

 

ከዚህ በፊት የኢህአዲግ ከፍተኛ የሆኑ ባለሥልጣናትን አሳምኖና አነጋገሮ በኢትዮጵያዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በማሰለፍ የድርጅቱ አባላት እንዲሆኑ ማድረጉ፣ ተራርቀው የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች በአንድ ላይ መጥተው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በማወለብለብ ሀገር ለማዳን በመድረክ ሥር እንዲሠሩ ትልቅ ሚና መጫወቱ በርግጥ የአንድነት ፓርቲ ያለውን ጥንካሬ በጉልህ የሚያሳይ ነው።

 

የነአቶ ስየ አብርሃ ወደ አንድነት መግባት የአንድነት ፓርቲን ብቻ ሳይሆን መድረክንም የሚያጠናክር ነው። አንድነት ተጠናከረ ማለት፣ ዓረና/ኦህኮ/ኦፌዲን ተጠናከሩ ማለት ነው። በነዓረናና በአንድነት መካከል ምንም አይነት ችግር የለም። በመድረክ ውስጥ አብረው የሚሠሩ፣ አብረው የሚታገሉ፣ የሚተማመኑና አንድ ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ምናልባትም ወደፊት አንድ ግንባር ወይንም አንድ ፓርቲ ወደ መሆንም የሚሸጋገሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ አይጋዎችና መሰሎቻቸው ብዙም አትልፉ እንላለን።

 

ይልቅስ የምታራምዱት የጎሣ ፖለቲካ ያለፈበትና ያረጀበት መሆኑን ተገንዝባችሁ የኢትዮጵያውያንን ስሜትና ፍላጎት ባንጸባረቀ መልኩ የምትደግፉት ድርጅት እንዲንቀሳቀስ ግፊት ብታደርጉ መልካም ይሆናል። የችግሩ አካል ከመሆን የመፍትሔ አካል ትሆኑ ዘንድ እንመክራለን።

 

በሚቀጥለው ጽሑፍ የነአቶ ስየ አብርሃ አንድነትን መቀላቀልና የመድረክ ምሥረታ ምን ያህል በሀገራችን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልና ለምን ኢትዮጵያን በሚወዱ ኃይላት ሁሉ ሊደገፍ እንደሚገባው አንዳንድ ሃሳቦችን ለማሳየት እንሞክራለሁ።

 

እስከዚያው ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!


ግርማ ካሣ (ቺካጎ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ኅዳር 19 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ