ፍቅሩ ይበልጣል

ሰሞኑን በሀገራችን ፖለቲካ ለሁለተኛ ጊዜ የህዝብን ቅስም የሚሰብር ድርጊት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በአንድ ወቅት የህዝብን የጋለ ስሜት አነሳስቶ የነበረውና ወደ ድል ሊያሸጋግረው ነበረው የቀድሞው ቅንጅት፣ በአመራር ላይ ባሉ ግለሰቦች አሳፋሪ የሆነ ድክመት ባልታሰበና ህዝብና ደጋፊ ባልጠበቀው ሁኔታ መንገድ ስቶ ተንኮታኩቶ ወደቀ። ያንን የወዳደቀ ስብርባሪውን አንስተው፣ ጠግነው፣ የተሰበረውን የህዝብ ልብ መልሰን ቀድሞ ወደነበረው አመኔታ እንመልሰዋለን በማለት የተነሱ ጥቂት አመራሮች እንደገና በማንሰራራት የቅንጅት ወራሽ የሆነውን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ በሚል ስያሜ በመመስረትና ልበ ሙሉዋን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በመሪነት በመምረጥ ትግሉን ለመቀጠል ለህዝብ ቃል ገቡ።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቃሊቲ መወርወር መላውን ደጋፊዎቿን ያስደነገጠ ቢሆንም ለወ/ት ብርቱካንና የገዥውን ፓርቲ በደንብ ለሚያውቁ ሁሉ እንግዳ ክስተት አልነበረም። ገዥው ፓርቲ በምንም ይሁን በምን ትግሉን የሚያንኮላሽበትን መንገድ በመፈለግ ሌሊትና ቀን የማይተኛ በመሆኑ የብርቱካን መታሰር በስሌት ተደረገ ለመሆኑ ለማንም ግልፅ ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ግን ወ/ት ብርቱካን በእስር እየማቀቀች ባለችበት ሁኔታ ሌሎች አመራሮች የአመራሩን ሃላፊነቱን በመውሰድ መሠራት የሚገባቸው ብዙ ሥራዎች ሊኖሩ ሲገባ (ለምሳሌ ያህል በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ትግሎችና በውጭ ሀገራት አምባሳደሮች በኩል በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የብርቱካንን ማስፈታት ሂደትን ማፋጠን ሲገባቸው) በዛ ምትክ የእርስ በርስ ንትርክ በመፍጠር መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳይሰሩና ወ/ት ብርቱካንም በእስር ቤት እንድትረሳ የሚያደርግ የጭካኔ ተግባር ተከናውኗል። በድጋሚም ሊጠገን የነበረው የህዝብ አመኔታ በድጋሚ እየተሰበረ ነው።

 

የህዝብን ከፍተኛ ከበሬታ የተካኑት እነዚህ የፓርቲ አመራሮች፣ እውቀቱም ያላቸው፣ በመቻቻልና በመነጋገር በሠለጠነ መንገድ ችግራቸውን የፈታሉ ተብለው የሚታመንባቸው፣ አይነት ስብስብ በመሆኑ ይህ የተፈጠረው መለያየት በመነጋገር ይፈታል የሚል ተስፋ በመላው የአንድነት ደጋፊዎች ዘንድ ነበር እንጂ እንደዚህ አሳፊሪና አንገት የሚያስደፋ ደርጊት ይፈጠራል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ የትእይነቱ መሪ ተዋንያን ከስማቸው በፊት ከበድ ያሉ ግርማ ሞገስ ያለው መጠሪያ የተሸከሙት ፕሮፌሠሮችና ዶክተሮች መሆናቸው ነገሩን ይበልጥ አሳዛኝ እንዲሆን አድርጎታል። ባለፈው ሣምንት የተደረገው ድርጊት ለደጋፊዎች በጣም አሳፋሪ፣ የትግሉን መዳከም ለሚፈልጉ ለወያኔና የወያኔ ደጋፊዎች ደግሞ ታላቅ ድል የሆነበት ሣምንት ነበር።

 

ሌላው ታላቅ ዜና ሆኖ የሰነበተውና አሁንም የአንድነቱን ጎራ ለሁለት ከፍሎት የሰነበተው፣ የአቶ ስየ አብርሃ እና የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወደ ፓርቲው ለመቀላቀል መወሰን ነበር። አንዳንዶች ውሳኔውን በመልካም ሲቀበሉት አንዳንዶች ደግሞ ግለሰቦቹ ከዚህ በፊት ከገዢው ፓርቲ ጋር በነበራቸው ንክኪ ምክንያትና በአመራር ላይ በነበሩበት ወቅት በህዝብ ላይ በፈጸሙት ግፍና ወንጀል ምክንያት አነድነትን መቀላቀል አይገባቸውም ሲሉ ተደምጠዋል። በተለይ አቶ ስየ አብርሃ ህዝብን ይቅርታ ላለማለት በተለያየ መድረኮች ባሳዩት የደነደነ ልብ ምክንያት ብዙዎች ደስተኛ አለመሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይሰማል። ዶ/ር ነጋሶ እንኳን በተደጋጋሚ የይቅርታ ድምፃቸውን ስላሰሙ ቅሬታውም በዛው መጠን ለዘብ ያለ ነው።

 

ከላይ የፃፍኩት በሙሉ በግሌ የዘገብኩትና ከብዙ ኢትዮጵያውያን ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ አጋጣሚ ስንወያይ የተገነዘብኩት የራሴ የግል አስተያየት ሲሆን የሁለቱ ግለሰቦችን ወደ አንድነት መቀላቀል በተመለከተ ይግቡ ወይም አይግቡ የሚለው ውሳኔ የኔም ሆነ በተለይ የማንም በዳያስፖራ ያለ ኢትዮጵያዊ የሚወስነው ሳይሆን፣ የትግሉ ነበልባል የሚያቃጥለው የኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔና በተለይ ደግሞ የፓርቲው አዲስ አባላትን የሚቀበልበት አሠራር በሕገ ደንቡ ውስጥ የተካተተው ዋነኛ ሊሆን ይገባዋል ባይ ነኝ። መስፈርቱን አስካሟሉ ድረስና አመራሩ እስካመነበት ድረስ ያሰራር ሒደት መሆኑን ተቀብለን ማንኛውም ፍላጎት ያለው ኢትዮጵያዊ አባል የመሆን መብት እስካለው ድረስ የነዚህም ግለሰቦች በዚሁ ሊካተት ይችላል።

 

ነገር ግን እነዚህ ሁለት በአሁኑ ወቀት የገዢው ፓርቲ የሚያካሂደውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቃወሙና በጊዜውም የመድረክ አባላት ሆነው የቆዩ ግለሰቦች በፖለቲካው መድረክ የሚኖራቸው አንድምታ በትንሹ የሚታይ ባይሆንም እንደውም አቀራረባቸው ግልፅ ከሆነና በሥራቸው ህዝብን ማሳመን ከቻሉ፣ አነድነትን መቀላቀላቸው ፓርቲውን ይበልጥ ያጠናክረዋል ብዬ እገምታለሁ።

 

ግን ጥያቄው የነዚህ ሰዎች መቀላቀል ለምን አሁን ሆነ?

የፓርቲው አመራሮች የተዘፈቁበትን የጭቅጭቅና፣ መድረክን እንቀላቀል ከተባለ ጊዜ ጀምሮ ጎልቶ የወጣውን የመከፋፈል እና የተያዘው እኔ የጳውሎስ ነኝ እኔ የኬፋ ነኝ አይነት ሁኔታ በመካከላቸው እያለ በቅጡ ያልፀዳ ቤት ውስጥ ዘው ብሎ መግባቱ እንደ እኔ እምነት ትክክል አይመስለኝም። ሲሆን አቶ ስየም ሆኑ ዶ/ር ነጋሶ በመድረክ ውስጥ በነበራቸው የማሰባሰብ ሥራ፣ የተለያዩ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ ተቻችለው አብረው እንዲሰሩ ባደረጉት ከፍተኛ ተግባር ቢቻል በሽማግሌነት በአንድነት ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብ አብርደውና አቻችለው አባል ለመሆንና ጥሩ ሥራ ለመሥራት ቢሞክሩ። አለበለዚያ ግን በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል ነውና ፓርቲውን ጭራሽ አዘቅት ውስጥ የሚጨምር መስሎ ይታየኛል እንጂ መፍትሔ የሚሆን አይመስለኝም።

 

በዚሁ አጋጣሚ ለአንድነት አመራሮች ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር የተከፋፈላችሁበትን ምክንያቶችና ጉዳዮች ቁጭ ብላችሁ ራሳችሁ እንሰራበታለን ብላችሁ ባወጣችሁት የፓርቲው ሕግና ደንብ መሠረት በሠለጠነ መንገድ በመወያየት ፈትታችሁ ይህንን የኑሮ ውድነትና ችግር ያደቀቀውን ወገናችንን በትንሹም ቢሆን የተስፋ ስንቅ ብታሰንቁት። አለዚያ እስከመቼ ድረስ በነፃነት የሚኖርበትን ያቺን ቀን ከመዳፉ እያወጣችሁ ታርቁበታላችሁ? ተስፋውንም ታሟጥጣላችሁ? ለወ/ት ብርቱካንና ለታሰረችበት ዓላማስ ያላችሁ አክብሮት ምን ያህል ነው?

 

አንድ ፓርቲያችሁንና በሥራችሁ ያለውን ውሱን ደጋፊ በቅጡ መምራት ሳትችሉ ሀገር ለመምራት የምታስቡትስ በምን ስሌት ነው? እርስ በርስ በመዘላለፍና በመናናቅ፣ እኔ ነኝ የበላይ ወይም የኔ ድምፅ ብቻ መሰማት አለበት አይነት አሰራር ከሆነ ለማስፈን የሚፈለገው ያንን መቼ አጣንና፣ በፊትም ነበረን አሁንም ያለን ይበቃናል።

 

በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለማችን አህጉራት የምንገኝ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ኢትዮጵያውያን፣ የድጋፍ ማሕበራት እና የሲቪክ መድረኮች፡ በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ የዚህን አይነት ውዝግበ ሲነሳ ወደ አንዱ ከመወገን ይልቅ ነገሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት የሚፈቱበትን መንገድ በመሻት የቆሙለት ዓላማ አንድ መሆኑን በማመን ነገር ግን በመካከላችው ያለው የአሠራር ልዩነት ብቻ መሆኑን አውቀን፣ ይህን ልዩነታቸውን ለመፍታት ማድረግ የሚገባንን ከማድረግ ወደሗላ ማለት እንደሌለብን። ሌላው ቢቀር የምናደርገው ድጎማም ካለ (የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ) ማዕቀብ በማድረግ ለገቡለት ዓላማና ለተስማሙበት ሕግና ደንብ ተገዥ ለማድረግ ካልገፋፋን እኛም ሀገር በማፈራረሱ ሥራ ተባባሪነታችንን እያሳየን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል።

 

ቢቻል ሁላችንንም በአንድነት ሊያየስተሳስረን የሚችል የአንድነት ሰንሰለት ቢኖረን በሀገራችን ለሚገነባው የዲሞክራሲ ዋስትና ሊኖረን ይችላል። አለበለዚያ ግን በየጊዜው የሚታየው የተቃዋሚ ቡድኖች መፍረክረክ አምባገነንነትን አስወግዶ ሕዝባዊ ሥርዓትን ይተካል ብሎ ማሰብ የማይገመት ነው። ነገሩ አንድ የሀገራችንን አባባል አለ ‘ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ’ …

 

ፍቅርና ሠላምን ያድለን! ቸር ይግጠመን!


ፍቅሩ ይበልጣል ነኝ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ