የዘር ፖለቲካን እናምክን! (አማኑዔል ዘሠላም)
አማኑዔል ዘሠላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ኢህአዲግ ስልጣን በጨበጠ በአሥራ ስድስት ወራቱ ነው ሀገሬን ለቅቄ የስደት ኑሮ የጀመርኩት። በማውቃቸው የአሥራ ስድስት ወራቱ የኢህአዲግና የኦነግ የጋራ አገዛዝ፣ የባንክ ሰራተኞች ያለምንም ርህራሄ ሲባረሩ፣ በበደኖና በአርባ ጉጉ “ነፍጠኞች” እየተባሉ ኢትዮጵያውያን በግፍና በጭካኔ ሲገደሉ አስታወሳለሁ። በድሬደዋ ከተማም ለሶስት ቀናት ተቀስቅሶ የነበረው የዘር ግጭት በዚያ ወቅት ነበር የተከሰተው።
ያኔ ኢህአዲግ ለሚያካሂደው የክልል ምርጫ በየቀበሌያችን መመዝገብ ነበረብን። ወደ ቀበሌዬ ልመዘገብ ሄድኩኝ። ስሜን ጠይቁኝና ነገርኳቸው። መዝገቡ ላይ ጻፉ። ብሔሬን ጠየቁኝ። “ኢትዮጵያዊ” አልኳቸው። “አይደለም፣ እርሱማ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን። ማለታችን አማራ ነህ፣ ኦሮሞ ….? “ ብለው ደግመው ጠየቁ። “እርሱን መመለስ አልችም። አላውቀውም።” አልኳቸው። “አባትህ ምንድናቸው ? “ አሉኝ። “አባቴ እርሱም አዲስ አበባ እንደተወለደ ነው የማውቀው። ዘሩን አላውቅም” አልኳቸው”። ሊመዘግቡኝ አልቻሉም። አማራ ወይንም ትግሬ ወይንም ኦሮሞ ወይንም አንዱን ዘር ካልመረጥኩኝ በኢትዮጵያዊነቴ የመምረጥ መብት እንደሌለኝ ተነገረኝ። ሳልመዘገብ ወደ ቤቴ ተመለስኩኝ።
ከአሥራ አራት ዓመት ስደት በኋላ ወደ ሀገሬ በተመለስኩኝ ጊዜ የተለወጠ ነገር እንደሌላ አስተዋልኩ። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መታወቂያው ላይ ዘሩን ካልጠቀሰ መታወቂያ አይሰጠውም። አንድ ሰው መታወቂያ ካላገኘ ማንነቱን የሚገልጽ ነገር የለውም ማለት ነው። በሌላ አባባል አንድ ሰው “ትግሬ ነኝ። ኦሮሞ ነኝ። አማራ ነኝ ..” ካላለ በኢትዮጵያ ውስጥ “ምንም” እንዳልሆነ ያሳያል።
አንድ በናዝሬት ተወልዶ ያደገ ወዳጄ የነገረኝን ታሪክ ላጫውታቹህ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይምረቃል። በናዝሬት የክልሉ አስተዳደር ውስጥ በተማረበት ሞያ፣ ለመሥራት ያመለክታል። ሁሉንም ነገር ካጠናቀቀ በኋላ ሊቀጠር እንደማይችል ይነገረዋል። ምክንያቱን ሲጠይቅ “ኦሮሞ ስላልሆንክ፣ በኦሮሚያ መቀጠር አትችልም” ነበር ያሉት። ሥራውን ለማግኘት “እኔ ኦሮሞ ነኝ” ብሎ ተከራከረ። “መታወቂያህ ላይ አማራ ነው የሚለው። አስለውጥ” አሉት። መታወቂያውን አስለወጠ። መታወቂያው ላይ አማራ የሚለውን ወደ ኦሮሞ አስቀየረ። ስራውን አገኘ። (ይህ ሰው ኦሮምኛም ስለሚናገርና ስለሚጽፍ በቀላሉ አማራን ወደ ኦሮሞ በመቀየር ተገላገለ። ግን አንድ ኦሮሞ ነኝ የሚል በኦሮሚያ ያደገ ሰው ቢሆን ኖሮ፣ ትምህርት ቤት በቁቤ ስለሚማር፣ ምናልባትም አማርኛ መጻፍ ሊከብደው ይችላል። በመሆኑም በሌላው ክልል ሥራ የማግኘቱ እድል ባዶ ይሆን ነበር)
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት በቀዳሚነት የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶት ማንጸባረቅና አገዛዞች የሚያራምዱትን ጎጂ ፖሊሲዎች በመቃወም ነበር የሚታወቁት።
አሁን ግን ከተቋማቱ የምናየው ተማሪዎች እርስ በርስ በዘር ላይ የተመሰረተ ግጭት ሲፈጥሩ ነው። በአለማያ (አሁን ሃረማያ ተብሏል) ፣ በባሀር ዳር፣ በጂማ እንዲሁም በበርካታ ተቋማት ብዙ ጊዜ በሴንጢ እስከመገዳደል የደረሰ የተማሪዎች ብጥብጥ እየተነሳ፣ የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ የገባበት ጊዜ ብዙ ነው። (እንግዲህ አስቡት በዚህ ሁሉ ግርግር “ጥሩ አካል” ሆኖ እየታየ ያለው የፌደራል ፖሊስ ነው።)
ውድ ወገኖቼ!
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ ይሄ ነው። እኔ እንደማስበው የኢትዮጵያ ትልቁና ዋናው ችግር ይሄ ነው። ይህ ችግር የኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ያተኮረ ችግር ነው። ይህ ችግር በአስቸኳይ ምላሽ ካልተሰጠው ወደፊት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርም ላትኖረንም ትችላለች።
ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ፣ ለዚህ ትልቅ የሀገራችን ችግር መፍትሄ በማምጣት ዙሪያ መመስረት አለበት ብዬ አጥብቄ የማምነው። ለዚህም ነው በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ የብሔር ፖለቲካ ያራምዱ የነበሩትን፣ ወደ ሕብረ ብሔራዊነት እንዲመጡ በማድረግ ዙሩያ እያደረገ ያለውን ቁልፍ እንቅስቃሴ በጣም መሰረታዊ፣ እጅግ ጠቃሚና በስፋት ሊደግፈ የሚገባው አድርጌ የምወስደው።
የከንባታ ህዝቦች ኮንግረስ በብሔር ላይ የተመሰረተውን ድርጅታቸውን አፍርሰው የአንድነት ፓርቲን ተቀላቅለዋል። ሌሎችም የጎሳ ድርጅቶች በቅርቡ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ሥር፣ የአንድነት ፓርቲን እንደሚቀላቀሉ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች እያየን ነው።
የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባርን አስተሳሰብ ያራምዳሉ ተብለው ሲተቹ የነበሩት፣ ዶር ነጋሶ ጊዳዳ “ለኦሮሞውም ሆነ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚበጀው በአንድነትና በህብረ ብሔራዊነት መታገል ነው” ብለው የአንድነት ፓርቲ አባል፣ አልፎም የአመራር አባል ሆነዋል።
በ1991 የተከበሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየሱስ ብቸኛ ተቃዋሚ በነበሩበትና ቻርተሩ በጸደቀበት በአዲስ አበባ ኮንፍራንስ ላይ፣ ያኔ የህወሓት ተወካይ የነበሩት፣ አቶ ስዬ አብርሃ ፣ የብሔር ብሔረሰብ መብት እስከ መገንጠል የሚለውን ሲያብራሩ የማእዘን ድጋይ አድርገው ነበር ያቀረቡት።
አሁን አቶ ስዬ፣ የሁሉ ነገር መሰረት ወይንም የ”ማዕዘን ድንጋይ” አድርገው የሚወስዱት የግለሰቦችን ነፃነት ነው። በግለሰቦች ነፃነት ውስጥ የቡድን መብት ይከብራል ብለው የሚያምኑ ናቸው። “ኢትዮጵያውያን በዘርና በጎሳ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተሰባሰበን፣ ለሁሉም እኩል የሆነችን ኢትዮጵያ መገንባት አለብን” የሚል ጠንካራ አቋም በመያዛቸው፣ የብርቱካን ሚደቅሳን ፓርቲ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተቀላቅለዋል።
ከላይ እንደጠቀስኩት ሀገራችን አደጋ ላይ ናት። ሀገራችንን ማዳን ይጠበቅብናል። ሀገራችንን የምናድነው በዘርና በኃይማኖት በመከፋፈል፣ ያለፈውን በጥላቻ በማንሳት፣ የስድብና የውሸት ፖለቲካን በማስፋፋት፣ ምንም ሳንይዝ በዜሮ ድምር የዘራፍ ፖለትካ በመጠመድ፣ የሚገዙትን ህዝብ እያረዱ ያሉትን እንደ ሻእቢያ አይነቶቹ ላይ በመደገፍ አይደለም።
ሀገራችንን የምናድነው እውነትን በመነጋገር፣ በራሳችን ህዝብ በመተማመን፣ በፍቅር፣ ይቅር በመባባልና የሰለጠነ ፖለቲካን በማራመድ ነው። የአንድነት ፓርቲ እያደረገ ያለውም ይሄንኑ ነው።
በዳያስፖራ ያሉ፣ ጥቂት ነገር ግን ድምጻቸውን በጣም የሚያሰሙ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ቡድኖች በአንድ በኩል ከሻዕቢያ ጋር የሚሰሩ ቡድኖችን በጭፍን ይደግፋሉ። ትላንትና ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባርና ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ተፈጠሮ የነበረውንና አሁን የሞተውን፣ የኢትዮጵያ አንድነትን ያልተቀበለውንና ያላረጋገጠውን፣ ኤ.ኤ.ፍዲ (ትብብር ለነፃነትና ለዲሞክራሲ) ከመደገፍም አልፈው የሚቃዋወሙትን ሲያወግዙ የነበሩ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የአንድነት ፓርቲ ድንኳኑን በማስፋቱና እነ አቶ ስዬን በማስገባቱ ጠንካራ ተቃውሞ ሲሰነዝሩ ይሰማሉ። ከነዶር መራራ ጉዲና ጋር አብሮ በመሆን የተቋቋመውንና በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የጸና አቋም ያለውን መድረክን ይቃወማሉ።
የሚያስደስተው ነገር ቢኖር ግን የአንድነት ፓርቲና እንዲሁም መድረክ ከገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል የሚደርስበትን ጫና ችሎ፣ በሌላ በኩል ከላይ ባነሳኋቸው ከተቃዋሚ ወገን ነን በሚሉ የሚደርስበትን ታቃውሞ መክቶ ጠንካራ የፖለቲካ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል።
መድረኩ ውስጥ ባሉ ድርጅቶች ወይንም በመድረክ ስም በአዲስ አበባ፣ በአዋሳ፣ በሆሳእና፣ በባህር ዳር፣ በናዝሬት/አዳማ (ኢህአዲግ ቢበጠብጥብ ስብሰባው እንደተረገ ነው የምቆጥርው)፣ በመቀሌ፣ በሽሬ፣ በማይጨውና በአዲግራት ህዝባዊ ስብሰባዎች ተደርገዋል። በጂማ፣ በድረዴዋ፣ በጎንደር እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቷ ግዛቶች ህዝባዊ ስብሰባዎች በቅርብ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ማድረግ ያለበትን፣ የትግሉ ባለቤት የሆነውን ህዝብ የማደራጀትና ለመብቱ እንዲታገል የማንቃት ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
ይህም ሁላችንንም ሊያስደስትና ሊያበረታታ የሚገባ ነው። ይህ የአንድነት ፓርቲ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ ከተፈለገም ያላሰለሰ የእያንዳንዳችን ሙሉ ድጋፍ ፓርቲው ያስፈልገዋል።
ጎበዝ የሀገሬ ልጅ፣ ህዝባዊውን እንቅስቃሴ እንቀላቀል። በተለያዩ ምክንያቶች ከትግሉ የሸሸን ወደ ትግሉ እንመለስ። ተስፋ ቆርጠንና ያቀረቀርን ቀና እንበል። ዝምታን የመረጥን እንነሳ። ለልጅ ልጆቻችን የበለጸገችና አንድነቷ የተጠበቀን ኢትዮጵያ እናስረክብ!አሁን ካልተነሳ መቼ? እኛ ካልተነሳን ማን?
አማኑዔል ዘሠላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥር 12 ቀን 2002 ዓ.ም.



