ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ምርጫውን በተመለከተ ሀገር ቤት ያሉ ድርጅቶች የሚበጃቸውን እንደሚያውቁና በተለይም ውጭ ሀገር ያለን ብዙ ጫና ማብዛት እንደሌለብን የሚገልጽ ሃሳብ ከጥቂት ወራት በፊት፣ ጥቅምት 3 ቀን 2002 ዓ.ም. “ኢህአዲግ ብርቱካን ሚደቅሳን ለምን ይፈታታል?” በሚል አርዕስት በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ አቅርቤ ነበር።

 

“ምርጫው ሰባት ወራት ይቀሩታል። በመድረክ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች እንዲሁም መኢአድ በምርጫ እንሳተፋለን ወይም አንሳተፍም የሚሉ አስተያየቶችን ከመስጠት ተቆጥበው፣ ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጋራ እንዲሠሩ ያስፈልጋል። በምርጫው ወቅት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔት መሆኑ ግንዛቤ ላይ ከተደረሰ፣ ባለፈው የወረዳና የማሟያ ምርጫ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ያኔ በጋራ እራሳቸውን ከምርጫው ያገላሉ። በምርጫው መሳተፍ ጥቅም ካለው ደግሞ በጋራ ወደ ምርጫው ይገባሉ። ይህንን ውሳኔ በጊዜው እንዲወስኑ ለነርሱ እንተውላቸው።” ነበር ያልኩት።

 

ሦስት ወራት አለፉ። ብዙዎቻችን ተስፋ እንዳደረግነው ሳይሆን፣ መኢአድ ከኢዴፓ ጋርም በመሆን የሥነ ምግባር ሰነድ በመፈረም ምርጫውን እንደሚሳተፍ አረጋገጠ። ገዢው ፓርቲ በዚህ ሂደት ትልቅ ዓለም አቀፍ ድልን ተቀዳጀ። በዚህም ምክንያት ከምርጫው ራስን በማግለል፣ የ2002 የፊታችን ምርጫ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዳይኖረው ማድረግ የሚቻልበት እድል በጣም ጠቧል ማለት ይቻላል።

 

አንዳንዶቻችን ድርጅቶቹ ወደ ምርጫ በመሄዳቸው ልናዝን እንችላለን። እርግጥ ነው ከ97ቱ ምርጫ ጋር ቢነጻጸር የአሁኑ ምርጫ በምንም መስፈርትና ሚዛን ነጻ ነው ማለት አይቻልም። ነገር ግን እንደዚያም ቢሆን ወደ ምርጫ መግባቱና በምርጫ ዘመቻ ህዝብን ማስተባበሩ መልካም ነው ባይ ነኝ። ምርጫውን አለመሳተፍ የሚያመጠው ይሄ ነው የሚባል ጥቅም ያለ አይመስለኝም። ምርጫውን መሳተፍ ግን ከዚህ በታች ለማስረዳት እንደምሞክረው የህዝብ ጉልበት እንዲገለጥ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስችል ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

 

በአሜሪካ የተደረገውን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በተመለከተ ያለፈው ዓመት በኒውዮርክ ታይምስ ላይ የተጻፈ የሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን ታሪክ ማስታወስ እፈልጋለሁ። ታሪኩ እጅግ ልብ የሚነካና ትምህርት ሰጪ ታሪክ ነበር።

 

ከአርባ ስምንት ዓመታት በፊት እጅ ለእጅ ተያይዘው “መንፈስ ቅዱስ ምረጡ ሲለን እንመርጣለ! ኦ አምላካችን ሆይ! - እንመርጣለን መንፈስ ምረጡ ካለን” እያሉ በመዘመር ነበር ያኔ የሃያ አንድ ዓመትና የሰላሳ አራት ዓመት ወጣቶች የነበሩ፣ ሩታ ማይ ሃሪስና ማሚ ኔልሰን የሚባሉ ጥቁር አሜሪካውያን ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በአሜሪካን በጆርጂያ ክፍለ ሀገር አልበኒ በምትባል ከተማ በሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ለመምረጥ የተጓዙት።

 

እግዚአብሔር የሰጣቸውን የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብታቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው የአልበኒ ፖሊስ የምርጫ ካርድን ከመስጠት ይልቅ የዱላና የግፍ በትር አወረደባቸው። ሩታ ማት ሃሪስና ማሚ ኔልሰን ለመብታቸው በመቆማቸው ታሰሩ። ተሰቃዩ። ተንገላቱ። በዚያን ወቅት ዘረኛ ነጮችም በዚያ አካባቢ ኢኮኖሚውን ይቆጣጠሩ ስለነበረ፣ ጥቁሮች እንዲመርጡ ያስተባበሩ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ታጋዮችም ከሥራቸው ተባረሩ።

 

ያኔ ጥቁሮች እንኳን ሊመረጡ፣ መምረጥ የማይችሉበት የጨለማ ዘመን ነበር። ያኔ መብት የሚረገጥበትና በደልና ግፍ የበዛበት ዘመን ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን “እግዚአብሔር የሰጠንና የራሳችን የሆነውን ማንም አይነጥቀንም። እኛም ሰዎች ነን። እኛም ሃሳብ አለን። እኛም ድምፃችን ይሰማ” ብለው፣ ድፍረት ወኔ መንፋሣዊ ጽናትና ፈሪሃ እግዚአብሐርን ተሞልተው ዘረኛውን የጆርጂያ አስተዳደር ተጋፈጡ።

 

የኒዎርክ ታይምሱ ዘጋቢ ኬሸን ሳክ፣ ከአንድ ዓመት በፊት እንደዘገበው ሩታ ሃሪስና ማሚ ኔልሰን ለፕሬዘዳንት ኦባማ ሲመርጡ ስድሳ ሰባትና ሰማኒያ ዓመት ሆኗቸው ነበር። በወጣትነታቸው ይዘምሩት የነበረውን የነፃነት መንፋሣዊ መዝሙር እየዘመሩ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ድምፃቸውን ለመስጠት ወደ አልበኒ ማዘጋጃ ቤት አቀኑ።

 

ከዚህ በፊት ለመመምረጥ በመምጣታቸው ተደብድበውና ቆሳስለው ተመለሱ። ያለፈው ዓመት ግን በደስታና በኩራት ድምፃቸውን ሰጡ። ያኔ ጥቁር ስለሆኑ መምረጥ ተከለከሉ። እነርሱ ባላመጡት እግዚአብሔር በሰጣቸው በሰውነታቸው ቀለም ምክንያት በደል ደረሰባቸው። ያለፈው ዓመት ግን የነርሱ አይነት ቀለም ያለውን ሰው ለመምረጥ በቁ። ያኔ ጥቁር መሆን ያስደበድብ ነበር። ያኔ ጥቁር መሆን ባርነት ነበር። አሁን ጥቁር አሜሪካዊ የዓለም ኃይል ሀገር የሆነችው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ለመሆን በቃ። ያኔ ትግሉ ለመምረጥ ነበር። አሁን መመረጥ ተቻለ።

 

ገዢው ፓርቲ ሁላችንም ተስፋ ቆርጠን ቤታችን እንድንቀመጥ ነው የሚፈልገው። በገንዘብና በጥቅም ድምጽ ለመግዛትና ድጋፍ ለማግኘት ሰፊ እንቅሳቃሴ እያደረገ ነው። ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን በጥቅማ ጥቅም የኢህአዲግ አባል አድርጓል። የኢህአዲግ አባል አንሆንም ያሉ ከሥራቸው በዘዴ እንዲወጡ ሲደረግ በነርሱ ምትክ የኢህአዲግ አባል በመሆናቸው ብቻ የተቀጠሩ ብዙ ናቸው። ለርሱ ሊሰሩለትና በምርጫ ወቅትም ሊመርጡለት የሚችሉ ግለሰቦችን በዚህ ረገድ ማብዛቱ አንዱና ትልቁ የኢህአዲግ ስትራቴጂ ነበር። ይሳካላት አይሳካለት ወደፊት የምናየው ይሆናል።

 

ሌላው ስትራቴጂው የተቀረነው ኢትዮጵያዊያንን ተስፋ ማስቆረጥ ነው። ለዚህም እኩይ አላማ፣ የሚያሳዝነው፣ በተለይም በውጭ ሀገር ያለን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አስተዋጾ እያደረግን መሆናችን ነው። ምርጫውን ኢህአዲግ ከወዲሁ እንዳሸነፈና መወዳደር እንደማያስፈልግ የምንናገር ጥቂቶች አይደለንም።

 

ኢህአዲግ የኢትዮጵያ ህዝብ ሌላ አማራጫ እንደሌለው በሚቆጣጠራቸው ሜዲያዎች በውሸት ለማሳየት በመሞከር፣ ሀገር ሊያስተዳደር የሚችል ብቸኛ አካል እርሱ እንደሆነ ለማሳመን ሲፍጨረጨር እየታየ ነው። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም። ኢህአዲግን ሊቀናቀን የሚችል አገረ ሰፊና ጠንካራ መሰረት ያለው አካል አለ። እርሱም የብርቱካን ሚደቅሳ ፓርቲን አንድነትን ያቀፈው መድረክ ነው።

 

ይህንንም ገዢው ፓርቲ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከመድረክ ምሥረታ ጀምሮ በመድረክ ላይ ያለ የሌለ ጥቃትን ሲዘነዝር ቆይቷል። ጥቃቅን ነገሮችን በመለጠጥና በማጣመም አንዱን የመድረክ አባል ድርጅት ከሌላ የመድረክ አባል ድርጅት ጋር ለማጋጫት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። (ለመረጃ ያህል እነኢትዮ ቻናልና ኢትዮጵያ ፈርስት ላለፉት ስድስት ሰባት ወራት ሲጽፉት የነበረውን ብቻ ማየት ይበቃል)

 

ለዚህ ነው ገዢው ፓርቲ፣ በመድረክ ውስጥ ትልቁ ድርጅት የሆነው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለመፍታት ፈቃደኛ ያልሆነው። ለዚህ ነው በመስቀል አደባባይ ወ/ት ብርትካን ሚደቅሳ እንድትፈታ የሚጠይቅ የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት እንዲደረግ አልፈቅድም ያለው። ለዚህ ነው የብርቱካን ሚደቅሳ ፎቶ ያለበት ኬኔቴራ አድርገው ኬኔተራውን ይሸጡ የነበሩ ወጣቶች የታሰሩት። ለዚህ ነው በደሴና በበርካታ የአገሪቷ ግዛቶች ብርቱካን እንድትፈታ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የፊርማ ማሰባሰብ እንዳያደርጉ የተከለከሉት። ለዚህ ነው በናዝሬት/አዳማ በኦሮምኛ ስብሰባው ካልተደረገ ብለው የአንድነትን ስብሰባ ኦህድዶች የረበሹት። ለዚህ ነው እነፕሮፌሰር መስፍን ሊያውቋቸው ያልቻሉ፣ በዝም አንልሞች ውስጥ የተሰገሰጉ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ አየር በሰፊው የሚያገኙ፣ ከድርጅቱ ከመባረራቸው በፊት የድርጅቱን ሚስጥር ያወጡ የነበሩ፣ በከፍተኛ ገንዘብ በኢህአዲግ የሚደገፉና መመሪያ ከአራት ኪሎ የሚቀበሉ ግለሰቦች፣ የአንድነት ፓርቲን ስብሰባ ሲበጠብጡና ሕገ ወጥ ውንብድና ሲፈጽሙ ፖሊስ ዝም ብሎ የሚመለከተው።(ለምን የፖሊሶቹ አለቆች ከበላይ የላኳቸው በመሆኑ)

 

እንግዲህ እውነታው ይሄ ነው። ገዢው ፓርቲ የአንድነት ፓርቲን እንዲሁም መድረክን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። አራት ነጥብ።

 

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ!

 

አንድ በጣም የሚያሳዝን ነገር አለ። ብዙ ጊዜ ኢህአዲግ እንድናስብ የሚፈልገውን ነገር ነው የምናስበው። ኢህአዲግ እንድንቀበል የሚፈልገው እንቀበላለን። እርሱም “ኢህአዲግ አሸንፏል፤ ያሸንፋል፤ ምርጫውን መሳተፍ ለከንቱ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ ነው። ይህ መቆም አለበት!!!! ይህ ሽንፈታዊና ጨለምተኛ አመለካከት ነው የሚል ጠንካራ እምነት ነው ያለኝ።

 

“ኢህአዲግ አያሸንፍም። ሊያሸንፍ አይችልም። ኢህአዲግ በህዝብ የተጠላ ነው። ህዝብ ተስፋ ሳይቆርጥ ከመረጠ በቀላሉ ሊወገድ ይችላል” የሚል ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። በህዝብ ጉልበት መተማመን አለብን። ጥያቄው ኢህአዲግ ሊያሸነፍ ይችላል ወይ የሚለ አይደለም። ኢህአዲግ ተሸናፊ ነው። ጥያቄው ህዝብ ተነስቷል ወይ? ህዝብ ይነሳል ወይ? የሚል ነው።

 

አንዳንዶች ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ እንዴት ምርጫ እንገባለን ይላሉ? በርግጥ ምርጫ አለመግባት ወ/ት ብርቱካንና ሌሎች የፖለቲካ እሥረኞችን የሚያስፈታ ከሆነ “ምርጫ አንግባ” የሚሉትን መቀላቀል ይቻል ይሆናል። ነገር ግን ምርጫ አለመግባት ብርቱካን ሚደቅሳን አያስፈታም። እንደውም “ብርቱካን ካልተፈታች ምርጫ አንገባም” በሚል ወደ ምርጫ እንዳንገባ ለማድረግም ሲልም ይሆናል ሆን ብሎ ወያኔ/ኢህአዲግ ብርቱካንን አልፈታም ያለው።

 

ሌላው ደግሞ ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችበትንም አላማ መዘንጋት የለብንም። ብርቱካን ሚደቅሳ እጅ የምትሰጥ ሴት አይደለችም። ሜዳውን ለኢህአዲግ አንለቅም ነበር ያለችው። እርግጥ ነው ትግሉ ከባድ ነው። ግን ከወዲሁ እጅ መስጠት፣ ሜዳውን ለኢህአዲግ መልቀቅ የብርቱካን ሚደቅሳ ፖለቲካ አይደለም።

 

ምርጫውን ባለመሳተፍ ገዢው ፓርቲ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳያጋኝ ማድረግ ይቻላል የሚልም መከራከሪያ የሚያቀርቡም አሉ። ነገር ግን ይህ መከራከሪያ ብዙም የሚያስኬድ መከራከሪያ አይደለም። ወያኔ/ኢህአዲግ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ የተደረጉትን በርካታ ብሄራዊና የወረዳ ምርጫዎች ብንመለከታቸው ከዘጠና ሰባቱ ምርጫ በስተቀር በሁሉም ምርጫዎች ገዢው ፓርቲ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያጣ የተደረገበት ሁኔታ የለም።

 

ከሁለት አመታት በፊት የተደረገውን የክልል ምርጫ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን እንዲያገሉ እኔን ጨምሮ በርካቶች ግፊት አደረገን። ተቃዋሚዎች እራሳቸውን አገለሉ። ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ በላይ ብቻውን ተወዳድሮ ያሸነፈው ኢህአዲግ ሆነ። በምርጫ ዘጠና ሰባት መቶ በመቶ ቅንጅት ባሸነፈበት ኩማ ደመቅሳ በምርጫ አሸንፌያልሁ ብሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነ። ማን ተናገረ? የአሜሪካ መንግሥት ምን አደረገ? በዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ ዘንድ የተገኘ ለውጥ አለን? ተቃዋሚዎች ምርጫን ባለመሳተፋቸው ምንም ጥቅም አገኙ? መልሱን ለአንባቢያን እተዋለሁ።

 

ይልቅ የገዢው ፓርቲ ማንነት የተጋለጠውንና ተቀባይነቱ ክፉኛ እንዲጎዳ የተደረገው ተቃዋሚዎች በተሳተፉበት በዘጠና ሰባት ምርጫ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በሌላ አባባል ምርጫ መሳተፍ ነው እንደውም የበለጠ ህዝቡን ሊያንቀሳቀስ የሚችለውና የገዢው ፓርቲ ማንነት የበለጠ የማጋለጥ እድል የሚሰጠው።

 

ስለዚህም በዚህ በቀረችው ጥቂት የምርጫ ወቅት በ“ይቻላል” መንፈስ ተሞልተን በሰላማዊ መንገድ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ሁላችንም መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ጥቃቅን ነገራት ወደኋላ እንዲጎትቱን መፍቀድ የለብንም። የሌለና ያልተጨበጠ ነገር ላይ ተስፋ አድርገን ይህን የሀገራችንን አቅጣጫ ለመቀየር እድል የሚሰጥን ትልቅ አጋጣሚ ማበላሸቱ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው።

 

በአሜሪካን ሀገር ጥቁሮች እንዳይመርጡ ብዙ ተንኮል ይሰራ እንደነበረ አሁንም ህዝቡ ተስፋ ቆርጦ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይመጣና የአንድነት ፓርቲንም ሆነ መድረክን እንዳይመርጥ ብዙ ሸፍጥና የተንኮል ሥራ በአንድነት ፓርቲ ላይ እየተሰራ መሆኑን ተገንዝበን፣ ሳናወቅ በገዢው ፓርቲ ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ እመክራለሁ። ከሁሉም አቅጣጫዎች ረጋ ብለን እናስብ።

 

እንደጥቁር አሜሪካኖቹ “እንመርጣለን! አንድነትን እንመርጣለን! መድረክን እንመርጣለን! ኢትዮጵያዊነትን እንመርጣለን! ፍቅርን እንመርጣለን! እኩልነትን እንመርጣለን!” እያለን የኢህአዲግ ዘረኛ ሥርዓት እንዳበቃለት እናረጋግጥ።


ግርማ ካሣ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ጥር 15 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ