የሚታዘነውስ ለነ አቶ መለስ ዜናዊ ነው (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
የእህታችን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የጤና ሁኔታ ብዙዎቻችንን እያሳሰበና እያስጨነቀ እንደሆነ አስባለሁ። ሊያስጨንቀንና ሊያሳስበንም በርግጥ ይገባል። የርሷ ሕመም የእያንዳንዳችን ሕመም ነው። በርሷ ላይ የሚደርሰው በኛ እንደደረሰ ነው። እርሷ ስታቃስት እኛም እናቃስታለን። ከዚህ በፊት በአንድ ጽሑፌ እንደገለጽኩት፣ እኛም ዓላማዋን ዓላማችን አድርገን ይዘን የተነሳን “ብርቱካን ሚደቅሳዎች” ነን። አራት ኪሎ ያሉ ባለሥልጣናት አንዲቷን ብርቱካን ሚደቅሳ በአካል ቢያስሯትም በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ብርቱካን ሚደቅሳዎች ተወልደዋል።
በተለይም በዚህ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕመምን በምናስብበት ሣምንት፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰውን ስቃይ ሳስብ፣ በሥጋ ውስጤ ቢቆጣና ቢያዝንም፣ በመንፈሴ ግን ተጽናናሁ። ከሁሉም በላይ የሆነ፣ የተረሱትን የሚያስታወስ፣ የወደቁትን የሚያነሳ፣ ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለድሃ አደጎች የሚራራ፣ ትዕቢተኞችን የሚያዋርድ አምላክ እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ ሳስብ ልቤ በደስታ ተሞላ።
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት፣ አንድ ዓርብ ቀን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባላጠፋው ጥፋት፣ የሰው ልጆችን በሙሉ ከኃጢያት ለማዳን እንደ ወንበዴ ተቆጠረ። ይከተሉት የነበሩ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ሸሹ። ትላንት በሽተኞች ሲፈውስና ድንቅ ተዓምራት ሲያደርግ በሺዎች እንዳልተከተሉት ሁሉ፣ የዚያን ዓርብ ቀን ግን፣ ከጎኑ የሚቆም ጠፋ። ተጠማሁ ባለ ጊዜ ሆምጣጤ አጠጡት። የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ጫኑበት። ገረፉት። በሚስማር እጆቹንና እግሮቹን ወግተው ሰቀሉት። “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሳባክታኒ - አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ብሎ ጮኸ። ነፍሱን አሳልፎም ሰጠ። ፀሐይ ብርሃኗን መስጠት አቆመች። መሬት ተንቀጠቀጠች። የደመናው ጥቁረት ያስፈራና ያስደነግጥ ነበር። አዎ! የያኔዋ ዓርብ ቀን የኀዘንና የልቅሶ ቀን ነበረች።
ከሦስት ቀናት በኋላ መቃብር ፈንቅሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተነሳ። “ክርስቶስ ትንሣዔ ሙታን፣ ሞተ ይኬዶ ለሞት፣ ለእለ ውስጥ መቃብር፣ ወካቤ ሕይወት ዘለዓለም እረፍት” እንደተባለው ክርስቶስ ሞትን ድል ነሳ። ከሰማይ ብርሃን ተገለጠ። ደስታና ዝማሬ ሆነ።
ይህ የጌታ የትንሣዔ ዜና የሚያስተምረን አንድ ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር፣ እንደጨለመ እንደማይቀር ነው። ዛሬ ዓርብ በመሆኑ ጉልበተኞች፣ ክፉዎችና ጨካኞች ደም እያፈሰሱ ይሆናል። ዛሬ ዓርብ በመሆኑ ወንጀል ያልሠሩ፣ መልካም ያደረጉ፣ ፍቅርን ያስተማሩ ታስረዋል። ዛሬ ዓርብ በመሆኑ እነ ብርቱካን ሚደቅሳ በማንም ነፈሰ ገዳይ ላይ ያልደረሰ ግፍ እየደረሰባቸው ነው። ዛሬ ዓርብ በመሆኑ ፍርድ እየተዛባ ነው። ዛሬ በነ አቶ መለስና በነካድሬ ሽመልስ ከማል ውስጥ ያለ የጭካኔ፣ የውሸት፣ ሰይጣናዊ መንፈስ ያየለ የሚመስልበት ጊዜ ነው። ዛሬ ብዙዎቻችን እያለቅስን ያለንበት ጊዜ ነው።
ነገር ግን እንደ ጨለመ አይቀርም። እንዳለቀስን አንቀርም። እሁድ ይመጣል። ዛሬ ያስጨነቁን የሚጨነቁበት፤ ዛሬ ያስለቀሱን የሚያለቅሱበት ጊዜ ይመጣል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈወሳለች። ከሕፃን ልጇና ከአሮጊት እናቷ ጋር እንደገና በቤቷ ማዕድ ትቆርሳለች። እንደገናም ድምጿን እንሰማለን። የፍቅር፣ የሠላም፣ የይቅርታ፣ የወንድማማችነት መልዕክቶቿም ይደርሱናል። እንደ ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በላይዋ ደርባ በአካልና በጤና እናያታለን። ይህንን ደግሞ የሚያደርገው ሁሉን እየተመለከተ ያለው የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ነው። (እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው ደግሞ እግዚአብሔር የሚሠራው በሰዎች እንደሆነ ነው። እኛ ከዝምታ ወጥተን እግዚአብሔር ለሚወደው ፍትህ ለመቆም ስንነሳ ያኔ እግዚአብሔር በኛ ውስጥ ይሠራል)
ይህን ብዬ አንድ ነጥብ ላንሳ። ሁኔታውን በተለየ ማዕዘን ካየነው ሊታዘን የሚገባው ማስተዋል አጥተው ግፍ እየፈጸሙ ላሉ ሰዎች እንደሆነ አስባለሁ። አላወቁትም እንጂ እነ አቶ መለስ እየተዋረዱና እየቀለሉ መምጣታቸው በገሃድ እየታየ ነው። ምናልባት ከውጭ ሀገር መንግሥታት በተገኘ እርዳታ መንገዶችና ግድቦች በመሠራታቸው ታሪክ በጥሩ ሊያስታውሰን ይችላል የሚል እንጭጭ አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል። አይደለም። ከታሪክ መማር ይቻላል። የግራዚያኒን አገዛዝ ኢትዮጵያውያን የምናስታውሰው በተሠሩ መንገዶችና ድልድዮች አይደለም። የካቲት 12 ቀን በጨረሳቸው ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንጂ። መንግሥቱ ኃይለማርያምን የምናስታወሰው በሠራው የባሮ ድልድይ አይደለም። ነገር ግን በረሸናቸውና ባስረሸናቸው በሺህ የሚቆጠሩ ንጹኀን ዜጎች እንጂ።
አቶ መለስ ደከምኩበት፣ ለፋሁበት የሚሉት ቢኖርም በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ አሁንም የቀጠለው ጭካኔያቸው፣ ሁሉ ነገር እንዲሸፈን አድርጎታል። የነበረችው ሌጋሲያቸው አንድም ትሁን ሁለት፣ ዜሮ ገብታለች። ከስረዋል፣ ተዋርደዋል። ወድቀዋል። ኮትና ክራቫት አድርገው በቴሌቭዥን ሲታዩ ሰው ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በሕዝብ የተናቁና የተጠሉ፣ ከሕዝብ ሸሽተው በፍርሃት ተደብቀው የሚኖሩ ሰው ሆነዋል። እንደ ሀገር መሪ ሳይሆን እንደ ነፈሰ ገዳይ እንደ ጨካኝ፣ እንደ ክፉ፣ እንደ ቂመኛ ነው እየታዩ ያሉት። ከዚህ የበለጠ ታዲያ ውርደት፣ ከዚህ የበለጠ የሚያሳዝን ነገር ምን አለ? የሚያሳዝነው ደግሞ አቶ መለስ ይሄን ሁሉ በራሳቸው ላይ ያመጡት እራሳቸው መሆናቸው ነው።
በቅርቡ የነ አቶ መለስ ዜናዊ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመለስ ከማል የተባሉ፣ የሕግ ትምህርት ተምሬአለሁ የሚሉ ሰው፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታመም ላይ የሰጡትን አስተያየት ሪፖርተር ላይ አነበብኩ። ወ/ት ብርቱካን እንደማንኛውም እስረኛ በማረሚያ ቤቱ ልታገኘው የሚገባ ማንኛውንም ጥቅሞች የማግኘት መብት እንዳላት፤ ነገር ግን ከሌሎች እስረኞች የተለየ ልዩ መብት ሊሰጣት እንደማይችል ነበር የገለጹት።
ሌሎች እስረኞችን ሊጠይቁ የመጡ ሁሉ ለአንድ ሰዓት ያህል፣ ከሰዓት በኋላ ያለ ገደብ መጠየቅ ይፈቀድላቸዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ጠዋት ለሰላሳ ደቂቃ በእናቷና በሕጻን ልጇ ከመጎብኘት በቀር ማንም ሌላ ሰው እንዲጎበኛት ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ የተከለከለች እሥረኛ ናት። የቱ ላይ ነው ታዲያ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደሌሎች እስረኞች የታየችበት ሁኔታ?
ሌሎች እስረኞች፣ ሴቶችን በጉልበት የደፈሩና ነፍስ ያጠፉ ሁሉ ሳይቀር፣ በእስር ቤት ውስጥ ሙሉ መብታቸው ሲጠበቅ፤ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ለስድስት ወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ተቀምጣ የሥነ-ልቦና ቶርቸር ሲደረግባት ቆይቷል። የቱ ላይ ነው ታዲያ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደ ሌሎች እስረኞች የታየችበት ሁኔታ?
እንደ አቶ ሽመለስ ከማል አይነቶቹ እውነትን እያወቁ የክፋትና የውሸት ተምሳሌት ሆነው በአደባባይ አፋቸውን ሲከፍቱ መስማት፣ እንደ ሰው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ የሚያሳፍር ነው። አቶ ሽመልስ በርግጥ ለራሳቸው ስብዕና ክብር የሌላቸው እንስሳ መሆናቸውን ነው በሚናገሩት ነገር በገሃድ እያሳዩን ያሉት። እንዲህ አይነቱ ሰዎች አላወቁትም እንጂ ፈረንጆች ሳይኮፓት የሚሏቸው በሽተኞች ናቸው። እግዚአብሔር ያስባቸው! - አሜን!!
ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!
እህታችንንም ቸሩ መድኃኒዓለም ባለችበት ቦታ ያበርታት!
ግርማ ካሣ
(This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
መጋቢት 20 ቀን 2002 ዓ.ም.



