ይድረስ ለተከበሩ አቶ መለስ ዜናዊ

ተጻፈ ከግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ምድረ አሜሪካ - ቺካጎ

በቅድሚያ ባሉበት ቦታ ለርስዎና ለቤተሰብዎ ሠላምታዬ ይድረስዎ!

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አምላክ ሆኖ ሳለ እኛን ለማዳን ወደዚች ምድር መጣ። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ወንድ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተወልዶ ሰው ሆነ። በምድር በሚመላለስበት ጊዜ እራሱን ሲጠራ ”የሰው ልጅ” ብሎ ነበር የሚጠራው። በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅትም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና አንዱ ደቀ መዝሙሩን ሲያለቅሱ አይቶ፣ እናቱን ”አንቺ ሴት እንሆ ልጅሽ” ነበር ያላት።

 

እራሱን የ”ሰው ልጅ” እናቱን ደግሞ ”ሴት” ብሎ ሲጠራ ምን ያህል ሰው መሆን በእግዚብሄር ዘንድ ትልቅ ማዕረግ ክብር ያለው እንደሆነ የሚያሳይ ነው። አንድ ሰው የአካል ጉዳተኛ ወይንም ሊሆን ይችላል። ገንዘብ የሌለው ድሃ ሊሆን ይችላል። ብዙ ስህተቶችና ወንጀሎች ከዚህ በፊት ሰርቶ ሊሆን ይችላል። ትግሬ ወይንም አማራ ወይንም ኦሮሞ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ከዚህ በፊት ጉዳት ስላደረሰብን የምንጠላው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ያ ሰው በስብእናው የተከበረ ነው። ያ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው።

 

በመሆኑም በአንቱታ ስጠራዎትና አክብሮት ስሰጥዎት በሰሩት መልካም ሥራና ተግባራት እንዳልሆነ ይወቁልኝ። የሚሰሩት በርካታ ሥራዎችን አጥብቄ የምቃወማቸውና የማወግዛቸው ናቸው። አክብሮቴ የመነጨው የሰው ልጅ በመሆንዎ እና በኢትዮጵያዊነትዎ ነው። እርስዎን ባላከብር እራሴን እንዳላከበርኩ ስለምቆጥር ነው።

 

ከሰላሳ አምስት ዓመታት በፊት በቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ጊዜ ኢትዮጵያውያን እንደ ከብት መተራረዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የሰው ክቡርነት ጠፍቶ ነበር። ወንድምና ወንድም አንዱ ኢሕአፓ ሆኖ ሌላው መኢሶን ሆኖ ተገዳድለዋል። አባት በልጅ ላይ፣ ልጅ በአባት ላይ ተነስቷል። ትንሽ የሃሳብ ልዩነት ከተነሳ ነፍጥ መምዝዝ ነበር የሚቀናው።

 

እርስዎም ከዚያ ትውልድ በመሆንዎ፣ አሁንም የማርክሲዝምና የዘረኝነት አስተሳሰብ አይምሮዎትን ስለበረዘው ነው መስለኝ ሰውን የማክበር ሁኔታ አይታይብዎትም። የያኔው ፖለቲካ የግትርነት ፖለቲካ ነበር። ያያነው ፖለቲካ ተቃዋሚን እንደጠላት የማየት ፖለቲካ ነበር። አሁንም እርስዎ የሚገኙት በዚያ ፖለቲካ ውስጥ ይመስለኛል። መልካም እንዲያደርጉ የሚነግርዎትን እግዚአብሔር ሲፈጥርዎት በውስጥዎ ያስቀመጠውን የሕሊናዎትን ድምጽ ከማዳመጥ ይልቅ፣ በውስጥዎ እንዲገባ የፈቀዱለት፣ የበቀል፣ የፍራቻ፣ ሰውን ያለመተማመን፣ የጥላቻ መንፈስን እያዳመጡ ለራስዎም ለቤተሰብዎም ለሀገርዎትም የሚጎዳ ነገር ሲሰሩ ነው እያየን ያለነው።

 

ከዚህ በፊት በርካታ ግልጽ ደብዳቤዎችን ጽፌልዎታለሁ። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መውቀስ ብቻ ሳይሆን መልካም ሲሰሩም መመስገን እንዳለብዎት አምናለሁ። ለዚህም ተከራክሬያለሁ። በተለይም በአገሪቷ ያለው ኢንፍራስትራክቸርን በመቀየር አኳያ መንግሥትዎ ብዙ ጠቃሚና አስደሳች ተግብራትን መፈጸሙ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ አውቃለሁ። በቅርቡ የአባይን ውሃ በመጠቀም አንጻር የግብጽ ጫናን በመናቅ ኢትዮጵያ ፊርማዋን ማስፈሯ አኩርቶኛል።

 

ነገር ግን ”ሰራን፣ አከናወንን” የሚሉትን ተግባራት በሙሉ የሚሸፍን እጅግ በጣም አስቀያሚና አሳዛኝ ተግባራትን መንግሥትዎ በስፋት ሲፈጽምም እያየን ነው። በርስዎና በመንግሥትዎ ላይ ሰዎች ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው ካደረጉትና በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል የኔም የርስዎም እህት የሆነቸው የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ጉዳይ ነው።

 

መጀመሪያ ሰሞን ብርቱካን ሚደቅሳ ስትታሰር ”በተራ ካድሬዎች የተሰራ ስህተት ነው፤ በቅርቡ ትፈታለች” የሚል ግምት ነበረኝ። ያ ሳይሆን ቀረ። ይግረም ተብሎ በጨለማ ቤት ውስጥ ለስድስት ወራት በግፍና በጭካኔ እንድትቀመጥ ተደረገ። ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ ተጥሶ ይች እህታችን የመጎብኘት መብቷ ተረገጠ። በጸና ታማ ሕክምና እያስፈለጋት፣ ከማረሚያ ቤት ውጭ ሐኪም እንዳያይት ተከለከለች። ይሄንን ሁሉ የጭካኔ ሥራ ያጡታል ብዬ አላስብም። ብዙዎች እርስዎ ባዘዙት መሰረት እንደተደረገ ይናገራሉ። ባይሆንም እንኳን እንደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነትዎ ይሄን ማስተካከል ይችሉ ነበር። ግን አላደረጉትም።

 

የተከበሩ አቶ መለስ፣

ይች ሴት ምንድን ነው ያደረገችዎት? የሰው ነፍስ አጠፋች? አመጽን ሰበከች? ጉቦ በላች? ምንድን ነው ወንጀሏ? ከዚህ በፊት በፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ላይ አሁን ደግሞ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እንደታየው ሰውን በማሰቃየት የሰውን ልቅሶና ሰቆቃ በማየት ለምን ይደሰታሉ? ለምን በውስጥዎት ላለው ክፉ መንፈስ ይታዘዛሉ? ለምን ለአንዳፍታ እንኳን ለሰው ልጆች ሃዘኔታ አይኖርዎትም?

 

የውጭ ሀገር ዜጎች ብርቱካን ሚደቅሳን እንድትፈታ ሲጠይቅዎት የአገራችን ሉዓላዊነትን እንደመድፈር አድርገው ይቆጥራሉ። ያሳዝናል። ከፈረንጆች ይልቅ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እርስዎ ነበሩ ለኢትዮጵያዊ ማሰብ የነበረብዎት። ነገር ግን ያ አልሆነም። (ደግሞ መንግሥትዎት የሚንቀሳቀስበትን አንድ ሶስተኛ ባጀት ከፈረንጆች በልመና በሚገኝ ድጎማ ሆኖ ”ፈረንጆች ለምን ተናገሩ ” ማለትዎት አስገራሚ ነው።)

 

ስለ ብርቱካን ሚደቅሳ አንድ ነገር በግልጽ ልንገርዎት። ብርቱካን ሚደቅሳ ማለት እኛ ሁላችንም ማለት ናት። በብርቱካን ላይ ያደረጉት ክፉ ተግባራት በኛ ላይ እንደተደረገ አድርገን ነው የምንቆጥረው። እርስዎን አስረው፣ እያሰቃዩ፣ በሰላም የሚቆዩ ከመሰልዎት በእጅጉ ተሳስተዋል። ምናልባት አብረዎት ባሉ ታማኝና ሕሊናቸውን የሸጡ የደህንነት ሰራተኞች ተማምነው ሊሆን ይችላል። አይሳሳቱ አቶ መለስ። ማንም ዋስትና ሊሰጥዎት አይችለም። ወደዱም አልወደዱም ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታለች። በርስዎም ላይ እየደረሰ ባለው ከፍተኛ የጤንነት መታወክና ጉዳት፣ እርስዎ የትም ሀገር ቢሄዱ እንደሚጠየቁ ማወቅ አለብዎት። ዋስትና ሊሰጥዎት የሚችለውና ወደፊት ከማንም ጋር በሰላም የሚያኖርዎት አሁን የሚያደርጉት መልካም ተግባር ነው።

 

ድንገት ”ከአሁን በኋላ ምንም ማድረግ አይቻልም” የሚል አስተሳሰብ ሊኖርዎት ይችላል። አሁንም ታሪክዎትን ማስተካከል ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ የልጅነት ጓደኞትንና፣ ”እንክርዳድ” ብለው የጠሯቸውን አቶ ስዬ አብርሃን መመልከት ይችላሉ። አቶ ስዬ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በየትም ቦታ ያለ ጠባቂ ይወጣሉ፣ ይገባሉ። እዚህ አሜሪካ ሀገር ለጉብኝት መጥተውም በነጻነት ነበር የተመላለሱት።

 

ሌላው ደግሞ በእርስዎ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርገው ተሹመው የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ (አሁን አሁን ጥሩ ስማቸውን አበላሹት እንጂ) ምን ያህል በአዲስ አበባ ሕዝብ ይወደዱ እንደነበረ የሚያስታወሱት ነው። አቶ አርከበ በታማኝነት ህዝብን በማገልገላቸውና በሰሩት ሥራ ህዝብ አከበራቸው። በዘጠና ሰባት ምርጫ የንቧን ምልክት ይዘው ተወዳደሩ እንጂ በሌላ ምልክት ቢወዳደሩ ኖሮ ለፓርላማ ተመራጭ ይሆኑ ነበር። እርስዎም፣ ያኔ አቶ አርከበ አሁን ደግሞ አቶ ስዬ እንዳደረጉት ከህዝብ ጋር የማይስማሙበት ምንም ምክንይት የለም። ወሳኙ እርስዎ ኖት።

 

የሚሰሙኝ ከሆነ አንዳንድ ጠቃሚ ሃሳቦችን ላቅርብልዎት፡

• ወ/ት ብርትካን ሚደቅሳን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ይፍቱ። በግፍ ለደረሰባት ካሳ ሊሰጣት ይገባል። ይህ አሁን እየወሰዱት ያለው የበቀል እርምጃ ነውር ነው። እርሷን እስካልፈቱ ድረስ በአሥር ሚሊዮኖች በሚቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጠብ ይኖርዎታል። ወ/ት ብርቱካን ታስራ ”ሰራን፣ ገነባን፣ አለማን” የሚሉትን ማንም አይዋጥለትም።

• ይህ የአሁኑ የ2002 ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ አይደለም። ከወዲሁ የለየለት ነገር ነው። ይህንን ታሪካዊ እድል አበላሽተውታል። እርስዎ የሚቆጣጠሩት ምርጫ ቦርድ የርስዎን ፓርቲ አሸናፊ አድርጎ ማወጁ አይቀሬ ነው። ነገር ግን ይህ ለርስዎ ማሸነፍ አይደለም። ይህ ትልቅ ሽንፈት ነው። ሰርቀው ስልጣን እንደሚይዙ፣ ህዝብ እንዳልመረጥዎት ሰው ሁሉ ያውቃል። በዚህ ሁኔታ በውሸት አጭበርብሮ አሸንፈኩ ማለቱ ታዲያ ትልቅ ሽንፈት አይደለምን?

 

ከምርጫው በኋላ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ወደ ማንፈልገው ደረጃ እንዳይሄድ፣ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲሉ፣ ከጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አስቸኳይ ድርድር በማድረግ፣ በሁለት ዓመት ውስጥ እንደገና ነጻና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ የሚደረግበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ እመክርዎታለሁ። ይሄንንም እንዲረዳ አንድ ጠንካራና ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋሙ ይበጃል። እስከዚያው ድረስ እርስዎ የአገሪቷ ርእሰ ብሄር ሆነው ቢቀጥሉ ችግር አይኖረኝም። በዚህ ሁኔታ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚመረጠው አካል ስልጣንዎትን የሚያስረክቡበት ሁኔታ በቀላሉ ይመቻቻል ማለት ነው። እርስዎ ስልጣን ከያዙ አሜሪካና እንግሊዝ አራተኛ መሪ ለውጠዋል። ጆርጅ ዋከር ቡሽ፣ ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አሁን ደግሞ ባራክ ኦባማ በአሜሪካ፣ ጆን ሜጀር፣ ቶኒ ብሌር ጎርደን ብራውን አሁን ደግሞ ዴቪድ ካሜሮን በእንግሊዝ፣ አቶ መለስ እርስዎም ቢበቃዎት አይሻልም?

 

እንግዲህ ለሁላችንም እግዚአብሔር ቸሩን ያሰማን። በምርጫ ሰበብ ንጹሃንን ለመግደል የተቀሰሩ ቀስቶች የተሰበሩ ይሁኑ! ለርስዎም ለቤተሰብዎም ለሀገርችን ህዝብ ሁሉ ሰላም ይሁን!


ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ምድረ አሜሪካ - ቺካጎ

ግንቦት 9 ቀን 2002 ዓ.ም

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!