0.6% ያገኙት፣ ግን 99.4% ያገኘውን ህወሓትን ያሸነፉት ተቃዋሚዎች ናቸው

ናኦሚ በጋሻው ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

”ምርጫ” ተደረገ ይሉናል። እኛ ግን ጨዋታና ቀልድ ነው የተደረገው እንላለን። ከምርጫው በፊት ይሄንኑ ነበር የምንናገረው። ምርጫ የሚወሰነው በድምፅ ሰጪው ሳይሆን በቆጣሪው ነው ስንል ነበር። መድረኩ ”ተሸነፈ” እንደሚባል ጥርጣሬ አልነበረንም። እንደገመትነውም እንደ ዶር መርራ ጉዲና፣ ኢንጂነር ግዛቸው፣ አቶ አንዱዋለም፣ አቶ ስየ አብርሃ የመሳሰሉ አንጋፋና ተወዳጅ የፖለቲካ መሪዎች፣ ተሸነፉ እየተባልን ነው።

 

 

በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝባችን በረሃብ የተጠቃ ነው ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ደግሞ በቀን አንዴ ከበላ ትልቅ ነገር ነው። ። የኑሮ ውድነት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። አርባ በመቶ የአገራችን ባጀት የሚሸፍኑት ምእራባውያን ናቸው። የአገራችን ድንበር ለሱዳን እየተሸነሸነ ተሰጥቷል። የአዲስ አበባ ህዝብ ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ነው የነበረው። ውሃ የለም። በሶማሊያ የአሜሪካኖች ጥቅም ለማስጠበቅ (አቶ ስየ ኮንትራክትአውት እንዳሉት) የወገኖቻችንን ደም በከንቱ እንዲፈስ ተደርጓል። ሠላማዊና ተወዳጇ እህታችን የኢትዮጵያ አንሳ ሱኪያ በግፍና በጭካኔ ታስራለች።

 

ይሄን ሁሉ ያደረገውን፣ ዘረኛ፣ በትዕቢትና በጥጋብ የተሞላውን፣ በሙስና የተዘፈቀና አፋኝ አገዛዝ የሆነውን ነው እንግዲህ፣ በህዝብ ተመረጠ የሚሉን። ያውም ደግሞ፣ የምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ውጤት መሰረት በ99.4% ድምፅ ነው። (ከ7.3 ሚሊዮን ተቆጠሩ ከተባለው ድምፅ ህወሓት/ኢህአዲግ 6.8 ሚሊዮን ሲያገኝ ተቃዋሚዎች አራት መቶ ሺህ አካባቢ ብቻ አግኝተዋል)

 

የቃሌ የኢትዮጵያውያን መወያያ ፓልቶክ ክፍል አድሚኖች፣ በምርጫ ቀን ኢትዮጵያ የተለያዩ ወረዳዎች እየደወሉ ምርጫውን በተቀነበረ መልኩ ይዘግቡ ነበር። ብዙዎቻችን እንቅልፍ ሳይወስደን ከኢትዮጵያ የሚሰጡ ቃለ መጠይቆችን በቀጥታ የማዳመጥ እድል አግኝተናል። በተንቤን ወደ ሰማይ ጥይት ተተኩሷል። በባሌ ጎባ 28 የመድረክ ታዛቢዎች ታስረዋል። በገሞጎፋ አምልጠው ጫካ ውስጥ እስኪደበቁ ድረስ የመድረኩ ደጋፊዎች ተደብድብደዋል። በበርካታ ወረዳዎች ኮሮጆው ባዶ መሆኑንና የምርጫው ሁኔታ በትክክል መስተካከሉን ለመታዘብ የተመደቡት ታዛቢዎች ”በቃ አታስፈልጉም” ተብለው በምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ካርድ ተነጥቀው ተባረዋል።

 

የምርጫውን ሂደት የሚያካሂዱና የሚመዘግቡ፣ ቀለም በእጅ ላይ የሚቀቡ ..ከሁለት እስከ ሶስት የሚሆኑ የምርጫ ቦርድ ሰራተኞች አሉ። እነዚህ ያው የኢህአዲግ ሰራተኞች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። ”ህዝብ የመረጣቸው” በሚል ገዢው ፓርቲ በተጨማሪ አምስት የራሱን ካድሬዎች በያንዳንዱ ጣቢያ አስቀምጧል። ያ ብቻ አይደለም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲም የራሱ ታዛቢ ስለሚኖረው እንደ መድረኩም ኢህአዲግ አንድ ተጨማሪ ታዛቢ ነበረው። ልዩነቱ የመድረኩ ታዛቢዎች ድብደባ፣ እሥር ወከባ ሲደርስባቸው የኢህአዲግ ታዛቢዎች ግን አበል ላጥ ማድረጋቸው ነው። በአጠቃላይ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች በያንዳንዱ ጣቢያ የኢህአዲግ ጥቅም ለማስጠበቅ ተሰማርተው ነበር።

 

ትንሽ እስቲ ወደ ሂሳብ ልውሰዳችሁ። ዘጠኝን (የካደሬዎች ቁጥር) በአርባ ሰባት ሺህ (የምርጫ ጣቢያ) ስናባዛ አራት መቶ ሶስት ሺህ ካድሬዎች ተሰማርተው ነበር ማለት ነው። ለእያንዳንዱ ካድሬ በዚያን ቀን፣ ቢያንስ መቶ ብር አበል ተሰጠው ብንል ከአርባ ሚሊዮን ብር በላይ ህወሓት/ኢህአዲግ ገንዘብ አውጥቷል ማለት ነው።

 

በአንድ በኩል ያሳቀኝ በሌላ በኩል ያሳዘነኝና ያሳፈረኝ አንድ ነገር ላንሳላችሁ። የኢትዮጵያ ቴለቭዥን አቶ መለስ ዜናዊ አድዋ ለመምረጥ ሲሄዱ፣ በምርጫው ጣቢያ በርካታ እናቶቻችን በግራና በቀኝ ተሰልፍው ቆመዋል። ለምርጫ የመጡ ናቸው እንዳልል ከበሮ ይዘው ሲጨፍሩ ይታያሉ። ለሙሽራ እንደሚደረገው ከበሮ እየደለቁ፣ ዳንኪራ ይመቱ የነበሩት አቶ መለስን እንኳን ደህና መጡ ለማለት ነበር።

 

በመጀመሪያ ይህ አይነቱ ትርዒት የስነ ምግባር ደንቡን የጣሰ ሕገ ወጥ የሆነ ተግባር ነው። የምርጫ ቅስቀሳ የቆመው ሐሙስ ነው። አቶ መለስ ድምጻቸውን ለመስጠት በመጡበት ጊዜ ለወ/ት አረጋሽ ድምፅ ለመስጠት የሚፍልጉ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አያስቸግርም። ታዲያ አቶ መለስ ሊመርጡ ሲሉ የነበረው ሁካታ ሌላ መራጮችን ማወክ ተደረጎ አይቆጠረምን? አንድ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ከምርጫው በፊት ”ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ አይደለም” ማለታቸው በመቃወም ኢቲቪ ስቱዲዮ ድረስ በመሄድ ሲንጣጡ ነበር።

 

ታዲያ እኝህ ሰው አቶ መለስ በምርጫ ጣቢያ የስነ ምግባር ደንቡን በይፋ ገደል ሲከቱት ዝም ማለታቸው ምን ይበላል? (በነገራችን ላይ ኢንጂነር ግዛቸው ይቅርታ አደረጉ እያሉ የህወሓት ካድሬዎች እያወሩ ናቸው። ኢንጂነር ግዛቸው ቃላቸውን አለወጡም። ይቅርታ የጠየቁት ምርጫው ሳይጠናቀቅ አስተያየት በመስጠታቸው ነው እንጂ ምርጫው ፍጹም ኢዲሞክራሲያዊና ኢፍትሃዊ መሆኑን አሁንም በድጋሚ የሚያረጋግጡት ነው።)

 

ወደ አቶ መለስ ልመለስ። መቼም እርሳቸው ክራባታቸውን ጠበቅ፣ ጠበቅ እያደረጉ፤ ጸሃይ በሌለበት ቦታ ትልቅ ጥቁር የጸሐይ መነጽራቸውን አጥልቀው፣ ከነ ጎርደን ብራውንና ስቲቭን ሃርፐር ጎን ሲቆሙ እራሳቸውን እንደ አንድ ዴሞክራትና የሰለጠነ ሰው አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። በቅርቡ በእንግሊዝ አገር በተደረገው ምርጫ ጎርድረን ብራውን ድምፅ ሲሰጥ በቢቢሲ ተመልክቻለሁ። ሌሎች ሰዎች አብረው ድምፅ ለመስጠት ይገባሉ፣ ሰጥተው ይወጣሉ።

 

ግርግር የለም። በምርጫው ጣቢያ ዳንኪራ አላየንም። በአንድ ዲሞክራሲ አገር የድምፅ መስጫ ቦታ የተከበረ ነው።

 

የኛው ጉድ አቶ መለስ ግን እንኳን ዴሞክራት ሊሆኑ ቀርቶ ከአሥራ ዘጠኝ አመት በፊት የተኳቸውን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምን የማይተናነሱ አምባገነን ናቸው። ኮሎኔል መንግሥቱም ምርጫ አሸንፌያለሁ ብለው እኮ ነው የኢሕአዴሪ ፕሬዘዳንት የሆኑት። ድምጻቸውን ሲሰጡ ልክ በአድዋ ትላንትና እንደታየሁ ሁሉ፣ ያኔም በምርጫው ቦታ ሆታ ነበር። በመንግሥቱ ጊዜ አጃቢዎቹና ሆ ባዮቹ መለዮ ለባሾችና ካድሬዎን ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን አቶ መለስ ዜናዊ ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ፣ ችግርና መከራ የጠበሳቸውን ሠላም ወዳድ እናቶቻችንን ነው መጠቀሚያ ያደረጉት።

 

ያም ሆነ ይህ ውጤቱ ያው ይፋ ሆኗል። አጼ መለስ ዜናዊ እንደ ሳዳም ሁሴን 99.4% በመቶ አሸናፊ ሆነው ለአምስት አመት ለመግዛት እየተዘጋጁ ነው። መድረኩም ሆነ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከ547 የፓርላማ መቀመጫዎች ወደ 20 ካገኙ፣ እንደሚባለው ትልቅ ነገር ነው። አቶ ተሾመ ቶጋ ጸሎታቸውም የተመለሰላቸው ይመስላል። አቶ ተመስገንና ዶር መራራን ለማስቆም ማይክሮፎኑን ማስቆም ላይኖርባቸው ነው። (አልፎ አልፎም ሳያስቡት አንዳንድ አቶ መለስ የማይወዱት አስተያየቶች ከተሰጡም ”እንደዚያ ሲናገር እንዴት ፈቀድክለት” የሚለው የአቶ መለስ የጓዳ ስድብም ትንሽ ሊቀንስላቸውም ይችላል)

 

ላለፉት አምሳ አመታት በእንግሊዝ በፈረንሳይና በአሜሪካ አሽናፊ የሆኑ ፓርቲዎች ከ70 በመቶ በላይ ድምፅ አግኝተው የሚያውቁ አይመስለኝም። እንደውም በእንግሊዝ በአሁኑ ጊዜ አሸናፊ ባለመኖሩ ጥምር መንግሥት ነው የተቋቋመው።

 

በሌላ በኩል የኢራቁ የቀድሞ ሳዳም ሁሴን እንዲሁም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ምርጫ ሲያደርጉ 99% ነበር አሸነፍን ያሉት። እንግዲህ የኛው ጉድ፣ አይጋዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ አንበሳው፣ የአስታዋይው፣ የሊቁ፣ የአፍሪካ መሪው፣ የዴሞክራቱ ፓርቲ 99.4% አሸናፊ ሆነ ሲባል፣ አቶ መለስን ከየትኛው ምድብ ነው የምንከታቸው? መልሱን ለአይጋ ፎረም፣ ለቤን ለነዋሸራ ላሉ አፍቃሪ ህወሓት/ኢህአዲጎች እተዋለሁ?

 

ሁለት ነጥቦችን በማስቀመጥ ላጠቃል። የመጀመሪያው አቶ መለስ ዜናዊ የመጨረሻ እድላቸውን እንዳበላሹ ነው። የኮሎኔል መንግሥቱ፣ የሳዳም ሁሴን እጣ እንደሚገጥማቸው ልንጠራጠር አይገባም። የህዝብን ልብ ያላገኘ አገዛዝ አወዳደቁ በጣም የከፋ ነው የሚሆነው። አቶ መለስ በአጭበርባሪነታቸው፣ በገዳይነታቸው፣ በጭካኔያቸው፣ በመሰሪነታቸው ለጊዜው ያሸነፉ ሊመስላቸው ይችላል። ለጊዜው ሕሊና የሸጡ ደጋፊዎቻቸውን የንቧ ምልክት ያለበትን ከኔተራ ለብሰው ዳንኪራ የመቱ ይሆናል። ነገር ግን የተሸነፉት፣ የተዋረዱት የቀለሉት እርሳቸው ናቸው።

 

በሁለተኛ ደረጃ ለመድረኩና ለመኢአድ አመራር አባላት፣ ለተወዳዳሪዎች፣ ለመድረኩ/መኢአድ ታዛቢዎችና ሠላማዊ በሆነ ትግል የአገራችንን አንድነት ለማስጠበቅ መስዋእትነት ለከፈለው ወገናችን ያለኝን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽ እወዳለሁ። እነዚህ ወገኖቻችን ወሬ አላወሩም። ሰርተው ያሳዩ ናቸው። ”ፓርላማ ሊገቡ ነው፣ ወያኔ ናቸው ወዘተረፈ …” እየተባሉ ህወሓት/ኢህአዲግ የሚያደርስባቸው መከራ ሳያንስ ተቃዋሚ ነን በሚሉ በተለይም በውጭ አገር ባሉ ብዙ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ያንን ሁሉ ችለው፣ አንድነታቸውን ጠብቀው፣ ህወሓት 99.4 አሸነፍኩ ብሎ እራሱን እንዲያዋርድና እንዲቀል አስደርገውታል። የጦር አይሮፕላን አስነስተውታል። (የመድረኩ አመራር አባላት በዚህ አጋጣሚ ሰው በላው የአቶ መለስ አገዛዝ መትረየሱን በህዝባችን ላይ እንዳይረጭ ህዝቡን ለማረጋጋት እያደረጉት ያለው ጥርት ማለፊያ ነው። በዚሁ ይቀጥሉበት።)


ናኦሚ በጋሻው

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ግንቦት 17 ቀን 2002 ዓ.ም. / ሜይ 25 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ