ስጋ ቆራጭ እንደ ጆሮ ቆራጭ የሚያስፈራበት ጊዜ መጣ!?
አቤ ቶክቻው (ከአዲስ አበባ)
ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ? በዛሬው ወሬያችን ርእስ ያደረግነውን ጉዳይ ከማውጋታችን በፊት እስቲ ሌሎቹን ጉዳዮች ትንሽ ትንሽ እናውጋቸው! እንዴት ነው ወዳጄ ኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ደረሰዎት እንዴ? እስቲ አዎ! ይበሉና ያስደስቱኝ። እውነቱን ለመናገር የዘንድሮው ኮንዶሚኒየም እጣ ደረሰኝ ብሎ ሲያወራ የሰማሁት አንድም ሰው እኮ የለም። ወይስ የኔ ወዳጆች በሙሉ ምዝገባው በነበረበት 97 አመተ ምህረት በስራ ተጠምደው የነበሩ ናቸው? የሆነ ሆኖ እጣው ከደረሰዎ እንኳን ደስ አለዎ!
ወዳጄ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ የቴሌ ኮሙኒኬሽን ሰራተኞች፤ መስሪያ ቤታቸው እንደ ክፉ አባት ሜዳ ላይ በትኗቸው ሲያበቃ ሰሞኑን ደግሞ አይዟችሁ ለማለት ደውሎላቸው ነበር አሉ። አንድ “ቴሌን ትርፋም ያደረኩት እኔ ነኝ” የሚል ወዳጄ መስሪያ ቤቱ “ካንሳፈፈው” በኋላ “አይዟችሁ” ለማለት ስልክ እንደተደወለለት ነግሮኝ ነበር። እኔም ድሮምኮ መንግስታችን ሆደ ሰፊ ነው ስራ ሊመልሳችሁ ነው። ብዬ ብለው “ሚሻለው እንደዚያ ነው አለበለዚያ እንደ ቱኒዚያው ወጣት ራሴን አቃጥዬ ከመሞት ውጭ ምርጫ የለኝም” አለኝ። እኔም ለንግግሩ አበስኩ ገበርኩ በል አንተ የሰይጣን ጆሮ አይስማ… ብዬ ገሰጽኩት። በሀሳቤም ይህች ዳርዳርታ!!! ስል ማንሰላሰል ጀመርኩ!
በማግስቱ የቴሌ ጉዳይ የሚመለከታቸው ዋና ሰውዬ “ተንሳፋፊ” ሰራተኞቹን ሰብስበው ወደስራቸው ለመመለስ ያላቸው ተስፋ ጠባብ ቢሆንም አደራጅተው ሌላ ስራ እንደሚፈጥሩላቸው ቃል ገቡላቸው! እኔ ይህንን ስሰማ እሰይ የኔ አዛኝ፣ እሰይ የኔ ቡቡ… ብዬ ሳንቆለጳጵሳቸው ያው ወዳጄ ስልክ ደወለልኝ፤ እኔም በል ወዳጄ ጋዝ ተራ መሄዱን ትተህ ተደራጅ1 ስል ምክሬን ለገስኩት፡ “እስቲ ተወኝ” አለኝ በሀዘን። ምነው? ብለው “ሰውየው ያለጋዝ አቃጠሉንኮ አልሰማህም እንዴ?” ብሎ በምላሻቸው ማዘኑን አወጋኝ። ነገሩ ክንክን ቢያደርገኝ እንድ ወዳጄን ቴሌ እስከዛሬ አንድም ቀን ከሰርኩ ሲል ሰምቸው አላውቅም ታዲያ ለምን ሰራተኞቹን ይቀንሳል? ብየ ብጠይቀው ምን እንደመለሰልኝ ያውቃሉ? “ሰራተኛ ለማባረር መክሰር ብቻ አይደለም ምክንያቱ” አለኝ። ታዲያ ካልከሰረ ሌላ ምን ምክንያት ይኖረዋል? ስለው “ሰክሮ ሊሆን ይችላል!” አለኝ። እውነት ግን ይቺ የሰራተኞች ሆድ ብሶት ጥሩ አይደለችም። እና መካሪዎች ሆይ ምከሩባት።
ወዳጄ… ይህንን ያህል ከተንደረደርን እስኪ ወደ ዋናው ርእሳችን እንግባ! ልብ ብለው እንደሆነ እንጃ እንጅ “ጮማ” ስጋ እኮ ተረት ወደመሆን እየተቃረበች ነው። ልክ አባቶቻችን በደህናው ጊዜ እያሉ እንደሚያወጉን አይነት ተረቶች።
አባቶቻችን በርካታ የጥጋብ ጊዜያት አሳልፈዋል እኮ። ታዲያ እኛስ በርካታ የጥጋብ ወሬዎችን በመስማት አሳልፈን የለም እንዴ!። እርግጥ የአባቶቻችን ጥጋብ ተኮር ወሬዎች እየተጋነኑ እና እያደር ሲመጡ ተረት ሆነዋል። በአንድ ወቅት ከአባቶች አንዱ የሆኑት በደህናው ጊዜ ስለነበረው ጠጅ የሚከተለውን አውግተውናል። ከልጆች አንዱ የሆንኩት እኔ ደግሞ እርሳቸው የነገሩኝን እነግራችሁ ዘንድ እነሆ…
“በዛን ጊዜ የነበረው ጠጅ በውስጡ የነበረው ማር ለአንዱ ብርሌ አንድ አንድ ሰራዊት ንብ ያዘጋጀው ነበር የሚመስለው። እንዳውም አንዳንዴ ከማሩ መብዛት የተነሳ ለብርሌ አዲስ የሆነ ጠጭ ሲጠጣው ከንፈሩ አካባቢ ጠጁ ሲነካው ማሩ እንደማስቲሽ አጣብቆት መናገር ይሳነው ነበር።” አሉን። እኛም ጨዋታ ወዶ ማጋነን ጠልቶ አይቻልምና ይሁን ብለን ሰማን። ቀጠሉ… “የጠጁ አወፋፈሩስ…! አንዳንዴማ ጠጁ ከመወፈሩ የተነሳ እንደዳቦ ቆሎ በመቀስ ነበር የምንቆርጠው። ምን ዋጋ አለው… እንዲህ ያለው ጊዜ መጣ!” ሲሉ እያማረሩ ያለፈውን ጊዜ ያወጉናል።
አሁን በቅርቡ በኛ ጊዜ ደግሞ… አረ ምን በኛ ጊዜ ብቻ በልጆቻችን ጊዜ እንጂ… እረ ከአንድ ወር በፊት… ያኔ ስጋ… ከስጋ ደግሞ ጮማ! የተባለ… ያማረ… አላፊ አግዳሚውን ለጉምዠት የዳረገ… ስጋ በየልኳንዳ ቤቱ ደጃፍ ይታይ ነበር። (ነበር! የምትለዋን እንድገማት… ነበር!) ደግሞም ምን መታየት ብቻ አቅም ያላቸው ወዳጆቻችን ከማየትም አልፈው ሄደው ቆርጠውት… ደሞም በልተውት… ጮማ ቆርጠን ይሉን ነበር። እኛም ራሳችን እቁብ በደረሰን ጊዜ… እየሄድን “የመጣው ይምጣ!” ብለን አይደፈሬን እንደፍረው ነበር። አሁንስ…?
አሁንማ እነሆ “ጸሀይ ወጣ” በእቁብ ዘመናችን አንዴ ብቻ ስንጎበኘው የነበረ ጮማ ባመቸን ጊዜ ሄደን “ከዚህ ቁረጥልኝ… ከዚህ አድርግልኝ” ለማለት እንችል ዘንድ አዋጅ ወጣ! እነሆ እናንት ስጋ የራቃችሁ… ጮማ ትቆርጡ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው ብለን ከያለንበት ተጠራርተን ወደ ልኳንዳ ቤት ለመሄድ ተነሳን። ምን ዋጋ አለው። በፊት በየልኳንዳ ቤቶች ደጃፍ ስናልፍ ስናገድም እናየው የነበረ ጮማ ከዋጋ ተመኑ ኋላ ድራሹ ጠፍታል። ምን እሱ ብቻ ዛሬ በየልኳንዳ ቤቶቻችን ሻኛ የለ፣ ዳቢት የለ፣ ነብሮ የለ… ብቻ ባጠቃላይ የተሰቀለው ስጋ ሁሉ ስም አልባ ነው።
በቀደም እለት አንዱ ኩስምን ያለ የኔ አይነት ሰው ስጋ ቆራጩ ፊት ቆሞ እያዘዘ ነበር። ( በነገራችን ላይ አሁን ባለንበት በዚህ ጊዜ ስጋ ቆራጭ ፊት መቆም በልጅነታችን ጆሮ ቆራጭ ፊት እንደመቆም የሚያስፈራውን ያህል እንደሚያስፈራ ለመናገር እወዳለሁ።) እናም ይህ ወዳጃችን ስጋት እየያዘውም ቢሆን ስጋ ቆራጩ ፊት ባለ በሌለ ድፍረቱ ቆሞ… “እስኪ ከታላቅም ከታናሽም” አድርግልኝ ብሎ አዘዘ። ስጋ ቆራጩም ኮስተር ብሎ “ታናሽ ታላቅ የለም” አለ። እሺ ምንድን ነው ያለው… ቢል በችግር ወደተጎሳቆለው ወዳጃችን በቢላው እየጠቆመ… “እኩያ ነው ያለው” አለውና አረፈው። እናልዎ ይሄ ከስጋ ተመኑ በፊት ወደ ልኳንዳ ቤት ደጃፍ ደርሶ የማያውቅ ወዳጃችን ዛሬ ገና የእርሙን ወደስጋ ቤት ቢሄድ የራሱን ስጋ ከማስገመት ውጭ ትርፍ አላገኘም እልዎታለሁ።
እውነት ግን ወዳጄ የዚህ የዋጋ ተመን ጉዳይ እንዴት ነው? ዋጋ ይቀንሱ ተብለው ስማቸው የተጠራ “መሰረታዊ” ሸቀታ ሸቀጦች በሙሉ እኮ ዋጋቸው ሳይሆን ራሳቸው ሸቀጦቹ ከገበያ እየተቀነሱ ነው። ለምሳሌ በሱቅ ውስጥ ስኳርን ማየት ብርቅ ሆኗል። ዛሬ ስኳር የምትገዛው እንደ ጅንአድ ከመሰሉ ድርጅቶች እና ከኢት ፍሩት ኮንቴነሮች ብቻ ካልሆነ በስተቀር እንደዋዛ ወጣ ብለው ከሱቅ የምትገዟት ነገር አልሆነችም። ወረፋውን ተቋቁሞ ከነ ኢት ፍሩት ስኳር የገዛ ሰው ራሱ ወደቤቱ ይዞ ሲመጣ በርካታ ሰዎች በአድናቆትና በጉምዥት ይመለከቱታል። ከዛም አልፎ በታክሲ ላይ ቦታ ሊለቀቅለት፣ በመንገድ ላይ “ልሸኝዎ ጋሼ?” ሊባልም ይችላል። ስኳር ብርቅ ነዋ!
ዘይትስ ብትሆን… በደህናው ጊዜ የጤና ባለሙያዎች በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ እያሉ ለጤናዎ አስጊ ነውና አጠገቡ እንዳይደርሱ እያሉ ሲያስጠነቅቁን የነበረው ዘይት ብቻ እኮ ነው በአዲሱ የገበያ ዋጋ እየተሸጠ ያለው። ሌላው ዛሬም እስከ አርባ ብር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጠ ነው። አሁንለታ አንድ ወዳጄ ይሄ “ለጤና ሀርድ” ነው የተባለውን የሚረጋ ዘይት ገዝቶ ባየው ተው ይሄ ጤና ላይ ችግር ያስከትላል ሲሉ ሰምቻለሁና ቢወደድም ያው ፈሳሹን እና የሀገር ውስጡን የኑግ ዘይት ይሻልሀል ስል መከርኩት። እሱቴ… ሊሰማኝ ነው! “ተወው እባክህ ያው ነው” አለኝ። እንዴት!? ብለው “ዋጋው ውድ የሆነውን ዘይትም ብገዛ በዋጋው የተነሳ የአእምሮዬ ጤና መታወኩ አይቀርም። ልዩነቱ የሀገሬ የኑግ ዘይት ገና ዋጋውን ስከፍል ነው ህመም የሚጀምረኝ ይሄኛው ግን ከበላሁት በኋላ ነው ህመሙ የሚመጣው ስለዚህ እኔ በልቶ መታመሙን መርጫለሁ። እንጂ ሁለቱም በሽታ ማስከተላቸው አይቀርም” ሲል በምሬት አወጋኝ።
ለስላሳስ ራሷ እንዴት እንዴት እያደረጋት እንደሆነ አይታችኋል? በካፌ ውስጥ ለስላሳ ያገኘ ሰው ቢንጎ እንዳሸነፈ ሰው ነው የሚቦርቀው። ባጠቃላይ የዋጋ ተመን የወጣላቸው ሸቀጣ ሸቀጦች በሙሉ ከገበያ እየጠፉ ይገኛሉ። ስማቹን ያልጠቀስኩት እነ ቢራ እንዳትቀየሙኝ። “ድሮ ሲጎነጩት የሚያሰክረው ቢራ ዘንድሮ ፍለጋው ነው የሚያሰክረው” እየተባላችሁ መሆኑን አልሸሽጋችሁም። ሩዝየ የኔ እናት፣ የክፉ ቀኔ አንችንም አልረሳሁሽም። ከጠፉት መካከል መሆንሽን ሰምቻለሁ! ብቻ ሁሉም የተተመኑት በሙሉ ሸሽተው የት እንደገቡ እንጃላቸው! ከሁሉ ግን የሚደንቀው ነጋዴዎቹ የተተመኑትን ሸቀጦች ልትገዙዋቸው ስትጠይቁ ኮስተር የሚሉት ነገር ነው። በአንዳንድ ሰፈሮችማ የዋጋ ተመን የወጣላቸውን ሸቀጦች ለመግዛት ከቤተሰቡ ደፈር ያለ ሰው እየተመረጠ መላክ ተጀምሯል አሉ።
በመጨረሻም 1
ግብጽ
መቼ ለታ የግብጹ ፕሬዚዳንት ጋሸ ሙባረክ በተቃውሞ እንደ ድግስ ጌሾ ደጅ ለተሰጣው ህዝባቸው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ በጉጉት ሲጠበቁ ሲጠበቁ… አሁንም በጣም ሲጠበቁ ቆይተው መጡ!
ህዝቡ ከአሁን አሁን ስልጣኔን ለሰፊው ህዝብ ለቅቄያለሁ! ብለው ይናገራሉ ብሎ ሲጠባበቃቸው እሳቸው ሆዬ እንደ ክፉ አጋንንት ደህና አስጠማቂ እንዳልገጠመው “አልለቅም” ሲሉ ለፍልፈዋል። ህዝቡም ሙባረክ የተጠናታቸው ርኩስ መንፈስ ስልጣን እንዲለቃቸው መጠየቁን ቀጠለ። ኡኡታውም ተቀጣጠለ! ከጁምአ ሰላት በኋላ የሙባረክ ርኩስ መንፈስ ህዝቡንም አላህንም መቋቋም አልቻለም “ለቀቅሁ…!” ብሎ ቤተመንግስቱን ብቻ ሳይሆን ካይሮን ሁላ ትቶ ቀይ ባህር ዳርቻ ወደምትገኘው የመዝናኛ ስፍራ “ሻርም አል ሼክ” አምርቷል። ህዝቡም አሁን ወደሚገባቸው ቦታ ሄዱ ለመዝናናት ከቤተመንግስቱ የተሻለ ቦታ ነውና! ብለዋቸዋል።
በመጨረሻም 2
ፍትህ ጋዜጣ
ፍትህ የተባለችው ጋዜጣ ወደ 35 በሚጠጉ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባታል። ክስ መመስረት ብቻ አይደለም አዘጋጇ ወደ አስር ሺህ ብር ለዋስትና ሰጥተው ባይለቀቁ ኖሮ እስሩም አይቀርላቸውም ነበር። ይህንን የሰማ አንድ ወዳጄ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ብሎ አስተያየት እንደሰጠ ያውቃሉ? “ክቡር አቃቤ ህጉ ይሄ ሁሉወንጄል እስኪሰራ ምን ይጠብቁ ነበር? ወይስ ውሃ ማቆር የተባለው ስልት አላዋጣ ሲል ክስ ማቆር ተጀመረ እንዴ?” ብሎኛል። እኔ ግን ያሳስበኝ የነበረው እነዚህ ሰዎች በሰላሳ አምስት አይነት “ወንጀሎች” ተከሰው ከሞት በታች ምን አይነት ቅጣት ይጠብቃቸው ይሆን? የሚለው ነበር።
ወዳጄ ይበሉ እስኪ ለዛሬ ይህችን ታህል ካወጋን ሰላም ያድርገንና ደግሞ ለሳምንት ሌላ እናወጋለን።
አማን አሰንብተን!
ምንጭ፦ አውራምባ ታይምስ (3ኛ ዓመት፤ ቁጥር 154)



