እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)

ቻይና ሰራሽ እስክሪብቶዬን ከገዛኹት ሁለት ቀናት እንኳን አላስቆጠርኹም። ገና ከወዲሁ እየተቆራረጠ ግን ትዕግስቴን እየተፈታተነው ነው። በዘመኑ የአራዳዎች ዘይቤ «ሙዴ» ሊበላሽ አፋፍ ላይ እየተንገዳገደ ነው።

 

በሌላ በኩል፣ የአምባሳደር ቡዝ ቃለ-ምልልስ አለብኝ። ለሁለተኛ ሳምንት መዝለቁ ምቾት አልሰጠኝም። አቦ! ስንት የሚፃፍለት ነገር እያለ! ስለሚሊኒየሙ ግድብ ምን ተነካ? የእኔንም ሆነ የብዙ ሰዎችን ስሜት እየኮረኮረ ያለ ጉዳይ ነው። ኢሕአዴግ ብቻውን እየጋለበው ነው፤ እያተረፈበትም ነው። ቅዳሜና እሁድ በአሜሪካ ስለተደረጉት ፀረ-ኢሕአዴግ ሰላማዊ ሰልፎች አንዲት ጦማር ብሰንቅ ነፍሴ በደስታ ትውተረተር ነበር። የብዕሬ ቱሩፋት የሚሊዮኖችን የታፈነ ስሜትም ትኮረኩር ነበር ብዬ አስባለኹ።

 

የገራገር መሳዩ አምባሳደር ቃለ-ምልልስ የሞተ ጉዳይ መስሎ እየታየኝ ነው። ችግሩ፣ ብዕሬን እንዳላጥፍ የገታው ቁጭት በውስጤ መብከንከኑ ነው።

 

አምባሳደር ቡዝን በግል አግኝቼ ለማነጋገር ዕድሉን አላገኘኹም። በባሕልና በትምህርት ላይ ማተኮርን እንደሚመርጡ እሰማለኹ። ማለፊያ ነው እኔ ከሁለቱም የለኹበትም። በስም እንደሚያውቁኝ ግን የማምናቸው ወዳጆቻቸው ነግረውኛል። እውነት ከሆነ፣ በጨረፍታ ያውቁኛል ማለት ነው።

 

ከእሳቸው በፊት ከነበሩት ያማማቶ ጋር በተደጋጋሚ ተወያይቻለኹ። እንዲያውም፣ አንድ ግዜ እኔንና ባለቤቴን መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ጋብዘውን ነበር፤ እግዜር ያክብራቸውና። ከሕግ ውጭ የጋዜጣ ፍቃድ ተከተከልን ብዬ ስሞታ ብጤም አጫውቻቸዋለኹ፤ ሕግ እንዲከበር እንዲማለዱን በመማፀን። ከልብ አዝነው ሲያዳምጡኝ አስታውሳለኹ። በኋላ ላይ ግን፣ መልስ ነፈጉኝ።

 

የአሜሪካ ብሔራዊ ፀጥታ (National Security) አስተማማኝ አጋር በሆነው ኢሕአዴግና የሞራልና የመርህ ስበት ባላቸው ሰለባዎቹ መካከል ሚዛን ጠብቆ መጓዝ፣ ለአሜሪካ ዲፕሎማቶች ቀላል ያልሆነ ፈተና ነው። ያማማቶን ተረድቻቸዋለኹ። ስለዚህም፣ ገፍቼ አልሄድኹም። «አትምጣብን» መባል አላስፈለገኝም። ምልክቶቹ ከበቂ በላይ ነበሩ ለእኔ፤ ባለስስ ቆዳው የሀበሻ ልጅ።

 

ስለቡዝ ስፅፍ ይሄ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጀመሪያውን የሞነጫጨርዃት በእንግሊዝኛ ነበር። መረጃ ሳፈላልግ የኢንተርኔት ካፌዎች ሲሳይ ሆኜ ከርሜ ነበር። ውጤቱ በመጠኑም ቢሆን እንዳውቃቸው ያበቃኝ መስሎኝ ነበር።

 

ቃለምልልሳቸውን ካነበብኹኝ በኋላ ግን፣ የማውቃቸው በጣም በትንሹ እንደሆነ ተሰምቶኛል። በመካከላችን ገደል እንዳለም ተረድቻለኹ።

 

እንደብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን፣ ሀገሬ ለዲሞክራሲ ዝግጁ ነች ብዬ አምናለኹ። እውን እንዲሆን በብዕሬ ታግያለኹ። እየታገልኹም ነው፤ እነጋናን፣ ማሊን፣ ቦትስዋናን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት አርአያ አድርጌ። ወደአውሮፓና አሜሪካ መመልከት አላስፈለገኝም።

 

አምባሳደር ቡዝ ደግሞ፣ «ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች የምታደርገውን እንቅስቃሴ ብንደግፍ ይሻላል» ብለዋል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ቃለ-ምልልስ። «ኢትዮጵያ እዚያ ደረጃ ላይ ስትደርስ፣ እድገቱ በራሱ አሜሪካ ወደምትፈልገው ዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንድታመራ ያግዛታል» በማለትም ደምድመዋል።

 

እኝህን ቡዝ የተዋወቅዃቸው በአውራአምባ ታይምስ ጋዜጣ በኩል ነው። ኢንተርኔት ላይ ያገኘኋቸው ቡዝ፣ እንዲህ አይነት እምነት እንዳላቸው ፍንጭ አይሰጡም። የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ቀርበው የአምባሳደርነት ሹመታቸውን ለማፅደቅ የምስክርነት ቃል ሲያሰሙም፣ በሀገራት ነፍስ ወከፍ ገቢና በመድብለ ፓርቲ ስርዓት መካከል ቁርኝት አለ ብለው አልተከራከሩም። አዲስ አበባ ላይ እንደ ድንገት የዘረገፉት ዱብዕዳ ነው።

 

አምባሳደር ቡዝ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በሁለት የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በአምባሳደርነት የተሰየሙት በላይቤሪያ ነበር፤ በ1997 ዓ.ም። ድኅረ ቻርልስ ቴለር ላይቤሪያ ዲሞክራሲያዊ ሀገር ሆናለች፤ በአሜሪካ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ። ቡዝ በላይቤሪያ በቆዩባቸው ሶስት ዓመታት ዲሞክራሲ ስር ሲሰድና ሲጎለብት ለማየት ታድለዋል። ላይቤሪያ ግን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የምትመደብ አይደለችም። ዲሞክራሲ እንዲያብብ የጠየቀው የአምባገነኑ ቻርልስ ቴለር መወገድ፣ የቀሪዎቹ ፖለቲካ ድርጅቶች ቁርጠኝነትና የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ናቸው።

 

ከላይቤሪያ ወደ ዛምቢያ ነበር ያመሩት። ይቺም የአፍሪቃ ሀገር የመካከለኛ ገቢ ባለቤት አይደለችም። የተመሰከረላት ደሃ ሀገር ናት። ዲሞክራሲ ግን ለምልሞባታል። የፖለቲካ ድርጅቶች ስልጣን ተቀባብለውባታል። ቡዝ የቅርብ ምስክር ሆነው ለሶስት ዓመታት ኖረውባታል።

 

ታዲያ፣ እንዴት ነው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ዲሞክራሲና የሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ የተቆላለፈባቸው? Enlighten us, sir!!

 

ብልፅግናንና ዲሞክራሲን በማዛመድ ቡዝ የመጀመሪያው አይደሉም። የእሳቤው ምንጭ ፕሮፌሰር ጆሽዋ ሙራቪችክ ይባላሉ። ሕይወታቸውን ያሳለፉት በባለ ብዙ ፈርጅ ምርምር ተጠምደው ነው። ስማቸው የተጠራው ግን፣ ሀብትንና ዲሞክራሲን በአስተሳሰሩበት ሰፋ ያለ ጥናታቸው ነው። ብዙ ተከታይም አፍርተውበታል። እኔ እስከገባኝ ድረስ፣ ቡዝ አንዱ መሆናቸው ነው።

 

ከቀሪዎቹ ተከታዮቻቸው መካከል የሚመደቡት ፕሮፌሰር ስቲቨን ክሌስነር በበኩላቸው፣ ነፍስ ወከፍ ገቢያቸው 6000 ዶላር ያልደረሱ ሀገራት ለዲሞክራሲ አልደረሱም ብለው ይከራከራሉ። የሙራቪችክ ተከታዮች፣ አነሰም በዛም ብለው አልተከራከሯቸውም፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ።

 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) የኢትዮጵያን አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ገምቷል፤ በ2001 ዓ.ም። ይሄንን ለ80 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ስናካፍለው፣ በነፍስ ወከፍ ወደ 365 ዶላር አካባቢ ይደርሳል። ደርግ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ሲወድቅ 120 ዶላር ነበር። በኤሊ ፍጥነት ነው እየተንፏቀቀ ያለው። 6000 ዶላር ወይም ደግሞ በአሃዝ ወዳልተገለፀው የአምባሳደር ቡዝ መካከለኛ ገቢ አካባቢ ድርሽ ለማለት ስንት ተጨማሪ ዓመታት እንደሚጠይቅ መገመቱን ለአንባቢ መተው እመርጣለኹ።

 

የአምባሳደር ቡዝን ግምት ግን በቀጥታ ከአንደበታቸው የመስማት አጉል ጉጉት አድሮብኛል። ወደዱም ጠሉም፣ ከእንግዲህ ያሉበት ድረስ ሄጄ ልፈልጋቸው ነው፤ አያሳፍሩኝም የሚል ብርቱ ተስፋ ሰንቄ።

 

ቡዝ፣ ምርጫውን አስመልክተውም አስተያየት ሰጥተዋል። በምላሻቸው ቢያንስ በእኔ ላይ የእግር እሳት እንደለቀቁብኝ ነው የቆጠርኹት። ለዚህ ባለሁለት ክፍል ዳሰሳም ዋነኛው ምክንያት ነው።

 

የቀረበላቸው ጥያቄ፣ «በ2002 ምርጫ ኢሕአዴግ 99.6 በመቶ (የምክር ቤት መቀመጫዎችን) ማሸነፉ ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃር እንዴት ይመለከቱታል!» የሚል ነው።

 

አምባሳደሩ ምላሽ ሲሰጡ፣ «ምርጫውን በተመለከተ በወቅቱ መግለጫ ሰጥተናል» ብለው ጀመሩ። ጥሩ። እኔም ብሆን ያለፈው ሳምንት አንስቼዋለኹ። አሜሪካ ኃላፊነቷን ተወጥታለች። ምንም የሚያከራክረን ነገር የለም። ጭብጡንም ማንሳት አለመፈለጋቸውን እረዳለኹ። ደጋግመው እንደሚሉን፣ ተጨቃጭቀው ምንም ከማይሰሩ፣ ተግባባተው ትንሽ ቢሰሩ ይሻላል።

 

ነገር ድብልቅልቁ የወጣው በሚቀጥለው አረፍተነገራቸው ነው። አምባሳደሩ ቀጠሉ፣ «የኢትዮጵያ ሕዝብ የምርጫውን ውጤት ተቀብሏል» አሉ። እደግመዋለኹ። «የኢትዮጵያ ሕዝብ የምርጫውን ውጤት ተቀብሏል!!»

 

እነዚህን ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብዃቸው ቅዳሜ ዕለት ከሌሊቱ 7 ሰዓት እንደነበር አስታውሳለኹ። ባለቤቴና ልጄ ተኝተዋል። እኔ ሳሎን ቁጭ ብዬ አነባለኹ። አንድ ግዜ አንብቤ ጋዜጣውን ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥኹት። ደክሞኝ ፊደሎች እየተዘበራረቁብኝ ይሆን? በረጅሙ ተነፈስኹኝ። ዓይኔን አሻሸኹ። ትንሽ ቆይቼም አረፍተ ነገሩን ለሁለተኛ ጊዜ ተመለከትኹት። እነዚያው ፊደሎች መልሰው አፈጠጡብኝ። ከእኔ በኩል ስህተት የለም። ከቡዝ አንደበት በትክክል የፈነጠቁ ቃላት ናቸው። ሳቅኹኝ፤ የቁጭት ሳቅ። የዛሬው ረዥም ቀን ነው። ይበቃል። አልጋዬ ውስጥ ገባሁ። እንቅልፍ ቶሎ አልወሰደኝም። ምላሽ ልፅፍላቸው የወሰንኹት ይሄኔ ነው።

 

በጠዋቱ ወደ ኢንተርኔት ካፌ አመራኹ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ድረ-ገፅ ከፈትኹ። ምርጫ 2002 በማስመልከት ያሰፈረውን ኦፊሴላዊ ግምገማ ለማግኘት ብዙም አላስቸገረኝም። በከፊል እንዲህ ይላል።

 

In a tally of the popular vote, 91.95% voted for EPRDF and affiliate parties, while only 8.05% voted for the opposition countrywide. Election Day was peaceful as 89% of registered voters cast ballots, but independent observation of the vote was severely limited. Only European Union and African Union observers were permitted, and they were restricted to the capital and barred from proximity to polling places..... Overall, the 2010 elections were not up to international standards because the environment conducive to free and fair elections was not in place.

 

በግምገማው 4 አንኳር ነጥቦች ተቀምጠዋል።

1. የምርጫ ካርድ ካወጣው ሕዝብ 89 በመቶ ድምፅ መስጠቱን፣

2. ድምፅ ከሰጡት መካከል 91.5 በመቶ ኢሕዴግን መምረጣቸውን፣ 8.05 በመቶ ብቻ ተቃዋሚዎችን መምረጣቸውን፣

3. ምርጫውን እንዲታዘቡ የተፈቀደላቸው የአውሮፓና የአፍሪካ ሕብረቶች ብቻ መሆናቸውን፤ የእነሱም እንቅስቃሴ ገደብ የተጣለበት መሆኑን (የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳይታዘብ ተከልክሏል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ)

4. የነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ድባብ ያልነበረ መሆኑ፣ ይህም ምርጫው የዓለም አቀፍ ደረጃ እንደማያሟላ ማድረጉን ተንትኗል።

እንግዲህ፣ እንደአሜሪካ መንግሥት ግምገማ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አልተደረገም፤ ቢያንስ በ2002 ዓ.ም።

 

ታዲያ፣ እንዴት ነው ነፃና ፍትሐዊ ያልሆነን ምርጫ ውጤት አንድ ሕዝብ ሊቀበል የሚችለው? የአሜሪካ ሕዝብ ነፃና ፍትሐዊ ያልሆነ ምርጫን ውጤት ይቀበላል ብለው አምባሳደር ቡዝ እንደማይከራከሩ መገመት አይቸግረኝም። የአሜሪካን ሕዝብ አውቀዋለኹ። ቅን ሕዝብ ነው። ጀግና ሕዝብ ነው። ለመብቱ የሚሞት ሕዝብ ነው። ስለፍትሕም የሚጨነቅ ሕዝብ ነው። በእነዚህ ነጥቦች ዙሪያ ከአምባሳደሩ ጋር ሙሉ ለሙሉ እንስማማለን።

 

የምንለያየው በኢትዮጵያዊያን ዙሪያ ነው። ኢትዮጵያውያን ነፃና ፍትሐዊ ያልሆነን ውጤት በምን ሂሳብ ሊቀበሉ እንደሚችሉ ፈፅሞ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። ፈሪ ስለሆኑ ይሆን? ያልሰለጠኑ ስለሆኑ ይሆን? ስለፍትሕ መጨነቅ የማይችሉ ስለሆኑ ይሆን? ወይስ እንደ ዲሞክራሲም ድህነትና የሞራል እሴቶችም የተሳሰሩ ናቸው? በደሃ ሀገሮች ፍትሕ የቀጨጨ ዋጋ ነው ያላት?

 

ከሁሉም በላይ ግን፣ ሕዝቡ ነፃና ፍትሐዊ ያልሆነውን ምርጫ ውጤት ስለመቀበሉ የአምባሳደሩ ማስረጃ ምንድንነው? የእሳቸው የግል አቋም ነው? ወይስ የመንግሥታቸው? መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው።

 

ብዙ ብዙ መሄድ እችላለኹ። ማቆምን ግን እመርጣለኹ። ይሄን መጣጥፍ በመለጠጥ እንዳላንዛዛው እየፈራኹ ነው።

 

ሃሳብ በማቅረብ ላጠቃልል። አምባሳደር ቡዝ የእኔን ምላሽ ብቻ መሰማት የለባቸውም። ከሌሎች ቢሰሙ ለእሳቸውም ሆነ ለመንግሥታቸው ይጠቅማል። ፃፉላቸው። ረዥም መሆን የለበትም። ሁለት ወይም ሶስት አረፍተነገሮች ይበቃሉ። በጥሩ እንግሊዝኛ መሆንም አያስፈልገውም። ቁም ነገሩ፣ ከተለያዩ ኢትዮጵያዊያን መስማታቸው ነው፤ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ።

 

አድራሻቸው፡-

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በእኔ በኩል፣ ሕዝብ የምርጫውን ውጤት አልተቀበለም። በኃይል የተጫነበት መሆኑ ግን እውነት ነው። በሁለቱ መካከል የቀንና የጨለማ ያህል ልዩነት አለ።

እውን አምባሳደር ቡዝ ይሄ ጠፍቷቸው ነውን?


ፀሐፊውን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ