ተክለሚካኤል አበበ (ኦታዋ-ካናዳ)

በረራው ተሰረዘ፡ እኛም ተደናገጥን

የዩኤስ አየር መንገድ ስልከኛ ሰው ደውሎ ያስቀመጠውን “የበረራ መስመር 7744 ስለተሰረዘ በሚከተለው ስልክ ቁጥር ደውሉና ማስተካከያ አድርጉ” የሚለውን መልእክትስሰማ ክው አልኩኝ። ለበረራው የቀረው ከሶስት ሰዓት ያነሰ ነው። ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ከተማሪዎቹ ጋር ያለውን ጣጣ ጠቅለል አድርጎ ወደጥያራ ጣቢያ ለመንዳት የሚያሟሙቅበት ሰዓት ነው። የዚያን ቀን ከሰዓት በኋላ የማስረክበውን ወረቀት ለመጨረስ ደፋ ቀና ስል ስልክ ጥሪዎች እንዳይረብሹኝ ብየ ስልኬን አጥፍቼው ስለነበር፡መልእክቶቼን ለመስማት ስከፍተው ዘግይቼ ነው ያንን የ “በረራ ተሰርዟል” መልእክት የሰማሁት። ተረበሽን።

 

ምክንያቱም ሌላኛው ተጋባዥ እንግዳ ታማኝ በየነም እንዲሁ፡ ያሜሪካ ፓስፖርት ይዞ እንዳይገላግለን ነገር፡ አስራምናምን አመት የስደተኞች የመጓጓዣ ሰነድ ይዞ ሲንገታገት፤ ለእድሳት ልኮት ስላልተመለሰ ለቅዳሜው የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ እንደማይገኝ ስላረዳን ነው በዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በረራ መሰረዝ የደነገጥነው።

 

ኦኬ አሁን ለመበሳጨት ግዜ የለም። ስለዚህ ተረጋጋሁ። ወደ ዩኤስ አየርመንገድ ስልክ ደወልኩ። በእንግሊዘኛ ከንፈር እየመጠጡ፡ በዚያን ቀን በምድረ ፔንስልቫኒያ፡ እንዲሁም በምድረ አሜሪካ በነበረው አውሎ ነፋስና ተው-ናደው ምክንያት (ቶርኔዶ የሚለውን ቃል ተው ናደው ብዬዋለሁ) ምክንያት በረራው እንደተሰረዘ ነግረውኝ፡ ሊያደርጉልኝ የሚችሉት ነገር ቢኖር በጠዋቱ በረራ ብቻ ማሳፈር እንደሆነ አስረዱኝ። ግን ነገስ? ነገስ ምን ዋስትና አለ? ቢሰረዘስ? ደግሞስ የነገ አርቡ የካናዳ ስብሰባስ ምን ይደረጋል? ከሁለት ያጣ እንዳንሆን፡ ወደስራ ባልደረቦቼ ስልክ ከመደወሌና ከማማከሬ በፊት፡ የበነጋታውን በረራ እንዲይዝልኝ አደረግኩት። እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ሀሙስ ከሰዓት ነው። የኦታዋ ዋናው የገንዘብ ማሰባሰቢያና የውይይት ዝግጅታችን ቅዳሜ ቢሆንም፡ አርብ ቀኑን ሙሉ የተለያዩ ዝግጅቶች አሉን። ስለዚህ ሲሆን ሲሆን ሀሙስ ማታ፡ ያለበለዚያ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ፡ በምንም ተአምር፡ ቢያንስ አርብ ጠዋት እዚህ ካናዳ መግባት አለበት።

 

ዲባቶ ብርሀኑ ጋር ደወልኩ። አያነሳም። መልእክት ተውኩ። ጠበቅኩት መልሶ አይደውልም። አሁንም ደወልኩ። አሁንም አያነሳም። ከዚያ በሶስተኛው አነሳው። “ምንድነው የምሰማው መልእክት ባካህ” አለኝ? የሆነውን ነገርኩት። ለዚህ ዝግጅት መሳካት ዋንኛውን ሚና የተጫወቱት የኦታዋ ሰዋችን ለአርብ እለት ሁለት ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት ብዙ ስለደከሙ፡ ዲባቶ ብርሀኑ ራሱ የጧቱን ስብሰባ መቅረቱን አልፈቀደውም። ሁለተኛ ደግሞ እሱም “ነገስ ቢሰረዝ ምን ይወጠናል? ታማኝም እኔም ብንቀር ዲዛስተር ነው የሚሆነው” ስለዚህ? ስለዚህማ፡ “It may sound crazy፤ ግን በመኪና ምንያህል ይፈጃል?” አለኝ። “ከዚህ በፊት ወደ ቶሮንቶ ስነዳ አንድ ስድስት ሰዓት ነው የፈጀብኝ።” “እኔ እንጃ፡ እንግዲህ ቶሮንቶ ራሱ ከኛ ከኦታዋ ወደ አራት ሰዓት ይፈጃል። ግን የግድ ቶሮንቶን አልፈህ ስለማትመጣ፡ ምልባት ኦታዋ አንድ ስምንት ሰኣት ሊፈጅብህ ይችላል። “በቃ፡ እኔ መኪና እከራያለሁ፡ እየነዳሁ እመጣለሁ፡ ከደከመኝም መንገድ ላይ አርፋለሁ። ለጠዋቱ ስብሰባ ግን መድረስ አለበኝ፡ በቃ እየነዳሁ እመጣለሁ።” ገላገለኝ። ገላገለን። ብሬ ገላግሌ ነው። ሌሊቱን ከስምንት ሰዓት በላይ ሲነዳ አድሮ በፈረንጅ ሰዓት ከጠዋቱ 2 ሰዓት ኦታዋ ገባ። ብርሀኑ ነጋ። አይመችም?

http://ethiopiazare.com/the-news/latest/1-latest-news/1705-ottawa-news

 

አርብ፡ ክርክር፡ ሳንድዊችና ንግግር

አርብ ቀኑን ከተያዙለት ሁለት ስብሰባዎች አንዱን በድል አጠናቀቀ። በተለይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የተካሄደው አንደኛው ስብሰባ የተሳካ ነበር። አርብ ማታ ላይ 50 ከሚሆኑ በአካባቢው ከሚኖሩ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በነበረን ውይይት ላይ፡ ስለነበረው የቀን ውሎ ሲያወሳን ነው የማታው ስብሰባ የተጀመረው። ቀን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ሲያናግራቸው፡ አብረውት የገቡት ሰዎች እስኪገርማቸው ድረስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ሰዎች ከአምባገነኖች ጋር ያላቸውን ፖሊሲያቸውን እንዲቀይሩ፡ ያለበለዚያ ግን ነገሮች ሳያስቡትና ሳይዘጋጁበት እንደቱኒዚያና እንደ ግብጽ፡ እንደየመንና እንደሊቢያ ድንገት እንደሚመጡባቸው በድፍረትና በልበሙሉነት እንደነገራቸው ነገሩን። ምእራባውያን በአምባገነን አገራት የሚካሄደውን ነገር ሁሉ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ፡ ነገር ግን ፖሊሲያቸው መሰረት ካደረጋቸው ሶስት የተዛቡ ግምቶች የተነሳ አሁንም ወደፊትም እስካሁን በሚጓዙበት የተሳሳተ መንገድ እንደሚቀጥል፡ ይልቁንስ ኢትዮጵያዊያን በምንም መልኩ ምእራባዊአንን መሰረት እንዳያደርጉ፡ አስረድቷል።

 

እንደ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ገለጻ አንዱ የምእራባዊያን የተሳሳተ ግምት፡ የአፍሪካውያን ታሪክና ባህል ለዴሞክራሲ የማይመች፡ የምእራባዊያን ባህል ግን የሚመች ስለሆነ፡ አፍሪካውአን ዲሞክራሲ እንደማይገባቸው፡ ሁለተኛ ምእራባዊያን፡ በደሀ አገራት ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሰው ልጅ የተወሰነ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለት እንደሚያምኑ፡ ለምሳሌ አንዳንድ ምሁራን ዴሞክራሲን ለማስፈን፡ የአመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ ስድስት ሺህ ዶላር መሆን አለበት እንደሚሉ፡ እስከዚያው ግን አፍሪካዊያን ሆዳቸውን ብቻ ይሙሉ አይነት አስተሳሰብ እንደሚያራምዱ፡ ሶስተኛው (ሶስተኛውን ረሳሁት) አስረዳ። በዚህም ይሁን በቀጣዩ ውይይት ላይ ብዙ ወርቃማ ሀሳቦች ተነስተው ስለነበር፡ እኔ ራሴ በሀሳቦቹ ከመመሰጤ የተነሳ ማስታወሻም በቅጡ መያዝ አልቻልኩም።

 

አንደኛው የስብሰባ ቦታ ግን ስብሰባው የተጠራው ዘግይቶ ስለነበር ብዙ ሰው አልመጣም ነበር። አንዲት በአባይ ወንዝ ላይ መሰለኝ የዶክትሬት ድግሪዋን የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ሴት ግን ነበረች። እና ስለአባይ አነሳች። እዚህ አካባቢ ስላደገች፡ ብዙም የኢትዮጵያን ፖለቲካ የምታውቅ አይነት ነገር አትመስለንም። “መለስ እስከዛሬ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች ያልሞከሩትን አባይን የመገንባት ህልም እውን ሊያደርግ የተነሳ መሪ ነውና ሊመሰገን ይገባዋል” ብላ ተነሳች። ብርሀኑን አላወቀችዉም። እንዳጋጣሚ ሆኖ ደግሞ በኋላ ላይ በቅዳሜው ዋንኛው ስብሰባ ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ፡ ለየት ባለ መልኩ ተነስቷል። ለምንድነው ተቃዋሚዎች ሁሉንም የምትቃወሙት፡ ለምሳሌ የአባይን ግንባታ ለምን አትደግፉም? አይነት ጥያቄ። ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ስለአባይ በደንብ ያውቃል። ለነገሩ ስለአባይ ብቻ አይደለም፡ ስለኢህአዴግም ያውቃል። እንዲያውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥናት ተቋም ውስጥ ሲሰራ አባይን ጥናት አድርገውበታል። እናም ህወሀት ኢህአዴግ በምንም አይነት መልኩ እንኩዋንስ ለአባይ አይነት የ80 ቢሊዮን ብር ግንባታ ሊታመን ይቅርና፡ የደርግ ጅምሮች ስለሆኑ ብቻ፡ የጣና በለሳና የአልዌሮን ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንዴት አድርጎ ፈነቃቅሎ ከስራ ውጭ እንዳደረጋቸው፡ ከምንም በላይ ግን ለእድገትም ይሁን ለልማት ዋንኛ መሰረት የሆነውን የሰውን ልጅ እንዴት አድርጎ እንደሚጨቁንና በምንም መልኩ ሊታመን እንደማይችል ነገራቸው። አብራራላቸው። ብርሀኑ ሲናገር አንጀት ያርሳል። ዛሬ በተለያየ መስክ ይሰለፉ እንጂ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ብርሀኑ ነጋና እንደ ልደቱ ልደቱ አያሌው ያለ አብራራው አልተፈጠረም። ወደ ብርሀኑ ልመልሳችሁ።

 

እንደኢህአዴግ ያለ ማንም የለም፡

መለስ ሌሎች የኢትዮጵያ መሪዎች ያልሰሩትን ሊሰራ ነው ሲባል ግን ሌላም ነገር ትዝ አለውና አነሳ። ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ። በምርጫ 2005 ክርክር ላይ ነው። እሱ ቅንጅትን ወክሎ፡ ካሱ ኢላላ ደግሞ ሕወሀትኢህአዴግን ወክለው ክርክር ቀርበዋል። እና ካሱ ኢላላ፡ “እንደኢህአዴግ ያለ ማንም የለም፡ ኢህአዴግ ማንም ኢትዮጵያ መሪ ያላደረጋቸውን ነገሮች ሰርቷል። ኢህአዴግ ለዚህች አገር የዋለው ውለታማ ስፍር ቁጥር የለውም። ለምሳሌ ኢህአዴግ ሞባይል ስልክ አስገብቷል” ሲል ተናገረ። ብርሀኑ ከትከት ብሎ ሳቀና፡ “ካሱ፡ ምኒሊክ ሊያስገባልህ ትፈልጋለህ እንዴ? በል ንገረኝ እንጂ ካሱ ኢላላ፡ ታዲያ ሞባይል ስልክ አጼ ምኒሊክ እንዲያስገቡልህ ትፈልግ ኖሯል እንዴ?” አለው። ተንቀሳቃሽ ስልክ የተፈጠረው ወይም በአለምም ላይ የተስፋፋው በኢህአዴግ ዘመን ስለነበርና ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ስላለ ሞባይል ስልክ አስገባ። እንጂ ኢህአዴግ በችሎታው የፈጠረው ነገር አይደለም። ስለዚህ አያስገርምም። እንደዚያማ ከሆነ ባቡርና ሆስፒታል፡ መኪናና ትምህርት ቤት የገነቡት አጼ ምኒልክ ምን ሊሉ ነው? አይነት ነገር። መንግስቱ ሀይለማሪያም ባለቀለም ቴሌቪዥን አስገባሁ ሲሉ ታየኝ እኮ።

 

የመገናኛ ብዙሀን ጥማቴ የሚጸናብን እንዲህ ያሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት አስቂኝ ነገሮችን ስሰማና ሳስብ ነው። ሳስበው ሳስበው፡ ሕወሀት ኢህአዴግን በሬዲዮና ቴሌቪዥን ተረባ ብቻ የምንጥለው ሁሉ ይመስለኛል። ከዚህ ቀደምም በ2000ው ምርጫ የኢህአዴግ ሚኒስትር ሙላቱ ተሾመ ያሉትን አጫውቻቸችኋለሁ። አንድኛው የተቃዋሚ ተከራካሪ ኢትዮጵያ በድህነት ከአለም መጨረሻ ንች ሲላቸው፡ እኚህ ሰው እጃቸውን አውጥተው፡ “ማስተካከያ አለኝ፡ እርማት፡ ኢትዮጵያ ከመቶ ሰባ አገራት 167ኛ ነች፤ እንጂ መጨረሻ አይደለችም” ያሉት ነገር ትዝ አለኝ። ይሄ የምላችሁ በሰዓቱ በቀጥታ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ የነበረ ነገር ነው። ሙላቱ ተሾመም በወቅቱ የኢኮኖሚ ምክትል ሚኒስትር ነበሩ። በሰዓቱ አዳራሹ ውስጥ የነበረው ሰው በጣም መሳቁ ትዝ ይለኛል፡ እኛም በየቤታችን መሳቃችን ትዝ ይለኛል። እንዲህ ያለውን መሳቂያና መሳለቂያ ለመቀነስ ነው የቀጥታውን የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ያጠፉት። ዲባቶ ብርሀኑ የአርብ ቀን ውሎውን ሲያጠናቅቅም፡ ባጠቃላይ፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር የነበረው ውሎ መልካም እንደነበር፡ ነገር ግን፡ የውጪው ኢትዮጵያዊ ህዝብ ዋና ሚና የሚሰጠው መልእክት ስለሆነ፡ በውጭ መንግስታት ሳይተማመን፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይዞህ አብረን ነን፤ በዘርና በሀይማኖት አትከፋፈል፤ በርታ ብሎ የሚያስተላልፈው መልእክት ነው ብሏል።

 

ጉዳዩ ምን ነበር? ምንስ ሰራን? ምንስ አወራን?

ዶ/ር ብርሀኑ ነጋና ታማኝ በየነን የጋበዝንበት ዋንኛ ምክንያት ለኢትዮጵያ ናተላይ (ሳተላይት የሚለውን ቃል በ”ናተላይ” ተክቼው ነው) ቴሌቪዥን ገንዘብ ለማሰባበሰብ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን ሰዎች ይሄንን ያህል ሺህ ኪሎሜትሮች አጓጉዘን፡ ቀናቸውን በልተን፡ ከልጆቻቸውና ከስራቸው ነጥቀን ስናበቃ፡ ሰዉን መቶ መቶ ሀምሳ ሀምሳ ብር አምጣ ብቻ ብለን በዚያ እንድንለያይ አልነበረም እቅዳችን። ይልቅስ በተገኘው አጋጣሚ ከነዚሁ ታዋቂ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመጫወትም ነበር እንጂ። ስለዚህም አርብ ማታና ቅዳሜ ቀኑን ሙሉ፡ በተለያዩ ሰፋፊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን አድርገናል። ስለነበረው ጠቅላላ ግዜ አንዳንድ አስተያየቶችን እሰጣለሁ። ከዚያ በፊት ግን በሁለቱም ቀን የተነሱትን ዋና ዋነ ነጥቦችና ከዲባቶ ብርሀኑ ነጋም በኩል የተሰጡትን አስተያየቶች እንቃኛለን።

 

በኦታዋ ከተማ በሚያዘጋጀው ሳንድዊች በተከታታይ ተወዳጅነትንና አንደኝነትን በሚያገኘው ጉኒስ ያበሻ ሳንድዊች ቤት ነው በመጀመሪያው ቀን የተሰባሰብነው። ወደ አርባ የምንሆን ኢትዮጵያዊያን ዶ/ር ብርሀኑን ከበን፡ በጥያቄና በአስተያየት እናሰቃየው ነበር። አርብም ቅዳሜም በተደጋጋሚ ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ የህብረት ምስረታና የግንቦት ሰባት ከጸረ-አንድነት ሀይሎች ጋር የያዘው ፍቅር ጥያቄ ነው። “እናንተ ባንድ በኩል ከአንድነት ሀይሎችና ድርጅቶች ጋር ሳትሰሩ በሌላ በኩል ግን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ካሰፈሰፉ ሀይሎች ጋር ለመስራት ተሰናድታችኋል። ለምሳሌ ከኦነግና ከኦብነግ ጋር በቅርቡ አብራችሁ ታይታችኋል። ይሄ እንዴት ይሆናል?” ይላል ደግሞ ተደጋግሞ የሚነሳው ጥያቄ። ዶ/ር ብርሀኑ ሊያብራራ ሞከረ።

 

አንደኛ ነገር የአንድነት ሀይሎች ያው የአንድነት ሀይል ስለሆኑና በኢትዮጵያ ስም ስለተሰባሰቡ፡ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይንም በኢትዮጵያዊነታችን ተገፍተናል የሚሉትንና የሚያስቸግሩትን ወደ አንድነት ካመጣን የተቀሩትን የአንድነት ሀይሎች ለመሰብሰብ ቀላል ስለሆነ ከአስቸጋሪው ስራ እንጀምር ብለን ነው ከኦነግና ከኦብነግ ጋር ንግግር የጀመርነው። ሁለተኛ ምንም አይነት ህብረት አልመሰረትንም። እንደው አትላንታም አንድ መድረክ ላይ ታየን፡ ኦነጉም ተነስቶ እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ከናንተ ያነስኩ አይደለሁም አለ፤ ስለዚህ ያ ሊያስደስት ይገባል እንጂ ለምን እንዲህ አረጋችሁ የሚያሰኝ አይደለም። ሶስተኛ፡ የግድ አንድ ህብረትም መመስረት የለበትም። ወይንም ሁሉንም ማሰባሰብ ላንችልም እንችላለን። እስከዚአው ግን በአንድነት ያመነ መሰባሰብ ይችላል፡ የግድ እኛን መጠበቅና የኛን ህብረት ማግኘት የለበትም። “እኔ እንደሚመስለኝ” አለ፡ ዲባቶ፡ “አንዳንድ ድርጅቶች የተተዉ ወይንም የተዘነጉ እየመሰላቸው እኛ ተረሳን አይነት ስጋት እየተሰማቸው ነው ተቃውሞ የሚያበዙት፡ ምንም ቢሆን ግን በዚያ ተዘነጋን ምክንያት ብቻ ለጥቃትና እኛ የመሰረትነውን ህብረት ለማውገዝ መነሳት አግባብ አይደለም” ሲል አምርሮ ተናገረ።

 

ብዙዎች በመልሱ ረክተዋል። ብዙዎችም አልረኩም። አንዳንዶች ያጉረመረሙም ነበሩ። እኔ ራሴም ባንዳንዱ መልስ አልረካሁም። የግድም መርካት የለብኝም። ዶ/ር ብርሀኑም በሚሰጠው መልስ የግድ ሁሉንም ማስደሰት የለበትም። በኔና በሌሎች ያልረኩ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ግን፡ እኔ አለመርካቴን በነጻነትና በግልጽ እናገራለሁ። አንዳንዶቹ ግን በግልጽ አይናገሩም። በነገራችን ላይ አንደኛው በዚህ የሁለት ቀን ዝግጅት ላይና ከዚያም በፊት ያስተዋልኩት አንዱ የኛ ትልቁ ችግር፡ የግልጽነት መጉደል። መቼም እነሱም አይወዱኝም፤ እኔም አላርፍ፡ ያው የተለመደውን ድርጅት እንደ ምሳሌ ልጠቅስ ነበር ግን ሌላ ጦርነት ከምጋብዝ ይቅርብኝ። የሆነ ሆነና፡ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ከሕብረት ምስረታ ጋር በተያያዘ የድርጅታቸውን ዋና ዋና መሰረታዊ ሀሳቦች ተናገረ። አንደኛ ማናቸውም ከነሱ ጋር ህብረት ለመመስረት የሚፈልግ ድርጅት ዴሞክራሲያዊ መሆን እናዳለበት። አንዳንዶቹ ድርጅቶች ዴሞክራሲ አያውቃቸውም። ስለዚህ ከነሱ ጋር ህብረት ልንመሰረት አይገባም አለ። ሁለተኛውን የግንቦት ሰባት ነጥብ ረሳሁት። ብዙ ድርጅቶች ስም ድርጅቶች ናቸው እንጂ፡ ምድር ላይ የረገጡና የሰው ሀይል ያላቸው የምር ድርጅቶች መሆን አለባቸው መሰለኝ።

 

ሌላው አብሮ ያነሳው ግን፡ አንዳንድ ተጨባጭ ችግሮች ስላሉባቸው መሆኑን ተናገረ። ለምሳሌ፡ ከኢህአፓ ጋር ሲደራደሩ፡ ከየትኛው ኢህአፓ ጋር ነው የሚደራደሩት። እንደምታውቁት ኢህአፓ ለሁለት ተከፍሏል። ከኦነግም ጋር እንደዚሁ። ከአንደኛው አንጃ ጋር ህብረት ቢመሰርቱ፡ ሌላኛው ወዲያውኑ ያወግዛቸዋል። ህብረት በመመስረቱ ሂደት ላይ እንደዚያ ያሉ ተጨባጭ ችግሮችም እንዳሉባቸው ተናገረ። ከዚያ ውጪ ግን፡ አንዳንድ ድርጅቶች ሁለት ሰዎች ብቻ ከፊት አስቀምጠው፡ ድርጅት ነን እያሉ የሚኖሩት ሁኔታም ችግር ነው። ለምሳሌ፡ ዲባቶ በየነ ወደ ስድስት ድርጅት አላቸው። የሁሉም ሊ/መ እሳቸው ናቸው። ስለዚህ ሕብረት ይመስረት ሲባል፡ ስድስት ድምጽ ይኑረኝ ይሉና ችግር ይፈጥራሉ። እነደዚያ ያሉ ችግሮችም አሉ። ለማንኛወም ማንም ድርጅት እንዳልተተወ፡ ይልቅስ ሁሉም በሂደት እንደሚካተቱ፡ እስከዚያው ግን ሁሉም የራሱን ህብረት በማጠናከር እንዲጓዝ መከረ።

 

ለውጥ መሪውን ይወልዳል” የእለቱ የሚጠቀስ አባባል

ሌላ ጥያቄ ተጠየቀ? ዶ/ር ብርሀኑ። እንደው ግን አሁን ለውጥ ቢመጣ፡ በግብጽና በቱኒሲያ ጦር ሰራዊቱ አንድ ነበርና አገሪቱን ጠበቀ። በኢትዮጵያ ግን ማን ነው የሚተካው? መለስን ጥለን ሌላ መለስ ልናመጣ ነው? ማን ነው የሚመራውስ? ተብሎ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ይመጣል። ለውጡ ሲመጣ ትንሽ ክፍተት ይፈጠር ይሆናል። ነገር ግን “ለውጥ መሪውን ይፈጥራል” ብሎ የሚጠቀስ ንግግር ተናገረ። የህዝቡና የሰው ልጅ የተፈትሮ ጨዋነትም አለ እኮ። ህዝቡ ጨዋ ነው። በዚህ የለውጥ ሂደትና ጉዞ ውስጥ ሕዝቡ የፖለቲካ፡ የዘርና የሀይማኖት ልዩነቶቹን ሳያጎላና ትልቅ ቦታ ሳይሰጥ ነው መጓዝ ያለበት። ዓለም ተለዋውጧል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ቢመጣ ከዚህ በኋላ ሌላ መለስ ይመጣል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ከዚያ በተረፈ ግን፡ ሕዝቡም እላዩ ላይ የሚሸኑበትን እምቢኝ ማለት መልመድ አለበት። ማንም ይሁን ማን፡ ህዝቡ አምባገነናትን ማስታመም ማቆም አለበት። ከዚያ ወደ ኋላ ሄደና ምሳሌ ሰጠ። ጋሽ ሀይሉ።

 

ጋሽ ሀይሉ፤ አቶ ሀይሉ ሻውልን መሆኑ ነው፡ እንዴት እምቢኝ አትንኩኝ ብሎ እንዳስቸገራቸው፡ ህዝቡም ምን ያልህ እንዳባለጋቸው ተናገረ። እኔ ግን የሱ የዶ/ር ብርሀኑ አይነት ሰዎችም አስተዋጽኦ እንዳለበት ነገርኩት። ለምሳሌ ከአቶ ሀይሉ ሻውል ጋር የነበረውን ችግር ገና ከመጀመሪያ ፊት ለፊት አውጥተው ፍርጥርጥ አድርገው መናገር ሲገባቸው፡ እያስታመሙ ያባለጓቸው እራሳቸው እነብርሀኑ፡ እነብርቱካን እነ ግዛቸው እንደሆኑ ተናገርኩ። እኔ ተክሌ አንበሳው። ዶ/ር ብርሀኑ ነጋም ለማስረዳት ሞከረ፡ ያንን ቢያደርጉ ህዝቡ ይከፋፈል እንደነበረ ለማስረዳት ሞከረ። ነግር ግን በኋላም ህዝቡ መከፋፈሉ አልቀረለትም። እንደውም ቀድሞ አውቆት ቢሆን ኖሮ፡ ጉዳቱን መቀነስ ይቻል እንደነበር አስረዳሁ። ይሄ ሽፍንፍን አድርጎ፡ እንዳንከፋፈል እየተባለ የምንጓዘው ነገር ነውችግር የፈጠረው። ይሄ ራሱን የቻለ ሰፊ አተታ ይወጣዋልና፡ እዚህ ላይ ልቁረጠው።

 

እንደማጠቃለያ፡ እንደምክርም

በመጨረሻም ከኢሳት የተሳካ የገንዘብ ማሰባሰብና ከዲባቶ ብርሀኑ ነጋ ጋር ከተደረገው ውይይት የያዝኳቸው አንዳንድ ነጥቦችና የብርሀኑ ምክሮች የሚከተሉት ናቸው። “የኛ ነገር” አለ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋ፡ “የኛ ፖለቲካ ላለፉት ሀያ አመታት እንደ ክራብ ሆኗል” (ክራብን ጊናስ ብዬዋለሁ። ከቅርፊት ውስጥ እየተፈለቀቀ የሚበላ የባህር ውስጥ ፍጥረት፡ የአሳ ዝርያ ነው)። “ፈረንጆች አንድ ክራብ በርሜል ውስጥ ብታስቀምጥው እንዳይወጣ የሚጠብቅ ዘበኛ ማድረግ አለብህ፡ ሁለትና ከዚያ በላይ ካስቀመጥክ ግን ዘበኛ አያስፈልጋቸውም። ምክንያቱም አንዱ አንዱን እንዳይወጣ እየጎተተ፡ እርስ በርሳቸው ይጠባበቃሉና።” ክራብ አትሁኑ፡ አንሁን ነው ምክሩ። እንደ ብርሀኑና እንደ ግንቦት ሰባት አንድ ነገር ቃል የገባነውና በምንም አይነት መልኩ የማናደርገው ነገር ቢኖር ሌላውን ድርጅት መሳደብና መዘርጠጥ ነው። የፈለገውን ይበሉን ሌሎችን ድርጅቶች አንሰድብም። በምንም መለኩ። ደግሞ እንደማህበረሰብ፡ ራሳችንን መሸንገል የለብንም። ማውራት መቀነስም አለብን። ራሳችንን መመርመርም መጀመር አለብን። ወደውስጥ መመልከት መጀመር አለብን። እንጂ ሁልግዜ ችግራችንን በሌሎች ላይ ብቻ በማላከክ መኖር የለብንም።

 

ሌላው እኔ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያዊያን ስብሰባ ያስተዋልኩትና የምጨምረው ነገር ቢኖር፡ አንዳንድ ሰዎች ለሚጠይቁት ጥያቄ መልስ አዘጋጅተው መልሱን እያወቁት ነው የሚጠይቁት። እነሱ የሚፈልጉት መልስ ካልተመለሰላቸው ክርክር ያደርጉታል። አንዳንዶች ለማፋጠጥና ነጥብ ለማስመዝገብም የሚጠይቁና የሚከራከሩም አሉ። ጥያቄ ጥያቄ ነው። አስተያየትም አስተያየት ነው። እንጂ መልሱን የምናውቀው ከሆነ መጠየቅም የለብንም። ደግነቱ እንደ ብርሀኑ ያለ መልሰ ብዙ ሰው ገጥሞን እንጂ፡ ለማፋተጥና ነጥብ ለማስመዝገብ የተሰናዳን ሰዎች ብዙ ነበርን። በመጨረሻ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ግን፡ ያው ዲባቶ ብርሀኑ እንዳለው የወሬ ማህበረሰብ ሆነን አንዳንቀር እንጂ፡ እንዲህ ያሉመድረኮች መብዛት አለባቸው። ብርሀኑ ነጋ አይጠገብም። ከብዙ ሰዎች አስተያየት ሰማሁ። ሁሉም፤ ወይም አብዛኞቹ በመልሶቹ ረክተዋል። ንግግሩ ግልጽ ነው። ፍርጥ ያደርገዋል። አይፈልግም እንጂ፡ ኢትዮጵያን ቢመራ የሚገባው ሰው ነው።

 

አንደኛው ጠያቂና አስተያየት ሰጪ ሰው ወደኋላ መለሰውና፡ በምርጫ 2005 ጉዳይ እናንተንም ኢህአዴግንም እወቅሳለሁ አለው። ዶ/ር ብርሀኑ፡ አንገቱን ሰበር፡ ወደጠረጴዛው ደፋ፡ መነጽሩን ዝቅ አድርጎ በተመስጦ የሚመልሰው ነገር አለው። “ይሄኮ፡ አንዲት በማስገደድ የተደፈረችን ሴት፡ የተደፈርሽው እኮ ባደረግሽው ቀሚስ ምክንያት ነው። ቀሚስሽ ረዘም ቢል ኖሮ፡ አትደረፈሪም ነበር። ስለዚህ ያንቺ ጥፋት ነው እንደማለት ነው። ሰልፈኛ የገደለው፡ ሰልፈኛ ያሰረው፡ ምርጫውን ያጭበረበረው፡ ፓርላማም አንገባም አላልንም፡ ነገር ግን የወሰድከውን ውሰድና፡ ቢያንስ ለሚቀጥለው ምርጫ ግን ይሄ እንዳይደገም እንደራደር ስላልንና ስለታሰርን ነው የተደፈርነውንም የደፈረንንም እኩል የምትወነጅለው?” ብሬ ተናገረ። ብርሀኑ ስለመጣና ስላስተማረን፡ በሺህ ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል መጥተው ገንዘብ ያዋጡትን በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ስለሰጡን እናመሰግናለን።

ሚያዝያ መጨረሻ፡ 2011

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ