ክንፉ አሰፋ

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢ.ቲ.ቪ.) ለሳምንት ያህል አንድ ማስታወቂያ እየደጋገመ ማሰማት ጀመረ። 'አኬልዳማ’ የተባለ ልዩ የፊልም ዝግጅት። በአኬልዳማ ማስታወቂያ ፊልሙን ከ13 አመት በታች ያሉ ህጻናት እንዳይመለከቱት ጥብቅ ማስጠንቀቅያም አለለበት። ማስታወቂያውን ከዚህ በፊት ከነበሩት ለየት የሚያደርገው ይህ የማስፈራርያ ማስተንቀቅያው ነው። በማስታወቂያው ውስጥ የአርቲስት ደበበ እሸቱ ምስልም ይታያል።

 

በዚህ 'ልዩ' ዝግጅት አርቲስት ደበበ እሸቱ የሚተውንበት ከሆነ ከቀድሞዎቹ የፈጠራ ስራዎች ሁሉ የተሻለ ድራማ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ደበበ ድራማን የተካነበት የጥበብ ሰው ነው። የድራማው ደራሲ ደበበን አስቀድሞ እንደተዋንያን ይጨው ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። የፊልሙ ዲያሬክተር ደግሞ ደበበን ሊያገኘው የሚችው በዚህ መንገድ ብቻ መሆኑ ግልጽ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚተውኑ የህወሃት ድራማዎችን የሚከታተል ማንም ሰው ይህንን ቅንብር የሚያጣው አይመስለኝም።

 

'አኬልዳማ’ - ከአስራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ይሁዳ ክርስቶስን በሰላሳ ዲናር ከሸጠው በኋላ በዲናሩ አንዲት ቋት መሬት ይገዛል። ይሁዳ የኋላ ኋላ በሰራው ስራ እጅግ ይጸጸትና በዛችው ስፍራ ራሱን ሰቅሎ ይሞታል። ያ መሬትም አኬልዳማ ተባለ። ከዚያም የድሆች እና የመጤዎች መቀበርያ ስፍራ ሆነ። ትርጓሜውም የደም መሬት ማለት ነው።

 

እንግዲህ ይህንን ታሪክ በአእምሯችን ይዘን ነው የአኬልዳማን ድራማ በኢ.ቲ.ቪ. ለማየት ስንጠባበቅ የነበረው።

 

የንጹሃን ዜጎችን ደም በከንቱ ያፈሰሱ፤ ምድሪቷን በደም ያጠቡ የአደገኛ አሸባሪዎች ጥልቅ የሆነ ሚስጥር ሲፈነዳ፤ ህጻናት እንዳያዩት የተከለከሉበትን የአዲሲቷን የደም ምድር እልቂት ምን እንደሚመስል በጉጉት መጠበቃችን አልቀረም።

 

ቀኑም ደርሶ አዲሱን የኢ.ቲ.ቪ. ድራማ ተመለከትን።

 

በፊልሙ ውስጥ ከሚታዩት መሃል የመስፍን አማንን ስም እና ፎቶ ስላየሁ ለመስፍን ደወልኩለትና ዝግጅቱን እንዲመለከት ነገርኩት።

 

“ባክህ አላይም” ሲል መለሰልኝ።

 

“ለምን?”

 

“አልሰማህም እንዴ? ፊልሙ ከ13 አመት በታች ላሉ ብቻ ነው የተፈቀደው።” አለኝ መልሶ።

 

የመስፍን አገላለጽ አሳቀኝ እና ስልኩን ዘግቼ ፕሮግራሙን ማየት ቀጠልኩ።

 

ፊልሙን እንደጨረስኩም መስፍን ያለኝ ነበር ትክክል መሆኑን ተገነዘብኩ። መላው ኢትዮጵያዊ ኢ.ቲ.ቪ. የሚናገረውን ሁሉ ገልብጦ በተቃራኒው ነው የሚተረጉመው። “ኢ.ቲ.ቪ. እውነት የሚናገረው ሰዓት ብቻ ነው!” ያለኝ ትዝ አለኝ። በርግጥ የዝግጅቱ መልእክት ከ13 አመት በታች ያለ ህጻን ልጅን እንኳን የማያሳምን በመሆኑ አዋቂዎች ላይ ከሚያሾፉ ይልቅ ህጻናትን ሊያታልሉበት ይችሉ ይሆናል።

 

ባጭሩ በ ኢ.ቲ.ቪ. እንዲህ ያለ አሳፋሪ ነገር ስናይ የመጀመርያው ባይሆንም ይህ ግን እጅግ በጣም ወርዷል። የሃገር እና የህዝብ ሃብት ለእንደዚህ አይነት አሳፋሪ የፈጠራ ስራ መባከኑ ሊያስቆጨንም ይገባል።

 

ለነገሩ ኢ.ቲ.ቪ.ን የሚያየውም የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ኢ.ቲ.ቪ.ን ማየት ካቆመ ሰነባብቷል። ህዝቡ ዛሬ ሌላ አማራጭ ስላገኘ ብቻ አይደለም ቴለቪዥኑን እርግፍ አድርጎ የተወው። አብዛኛው ህዝብ በኢቲቪ የሚቀርቡ ፕሮግራሞችን እያየ ይበሳጫል። 90 በመቶ የሚሆነው ዝግጅት ትምህርት የማይሰጥና ተመልካቹን የሚንቅ ፕሮፓጋንዳ ነው። አንዳንዶችን ደግሞ ያዝናናቸዋል። እኔም ኢቲቪን እያዩ ከሚዝናኑ ሰዎች ክፍል እመደባለሁ። የሚያስቁኝ እና ዘና የሚያደርጉኝ ታዲያ ድራማዎቹ ወይንም የሚቀርቡት የሙዚቃ ትዕይንቶች አይደሉም። የዜና እና “ዶክመንተሪ” ዝግጅቶች እንጂ።

 

አንድ የምሽቱ 2 ሰዓት ዜና እወጃ ላይ የቀረበ ዜና እንዲህ ይላል"

 

“... የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች ለህዳሴው ቦንድ መግዣ የእለት ቁርሳቸውን ለገሱ ...”

 

የህጻናቱ ተወካይም በቴሌቪዥኑ ቀርቦ ህጻናቱ ተሰብሰበው ያወጡትን መግለጫ እንዲያነብ ተደረገ፤

 

“እኛ የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች የዛሬ ቁርሳችንን ለህዳሴው ግድብ መስዋዕት አድርገናል። ...“

 

በእርግጥ በቲቪ የቀረበው የህጻናቱ ተወካይ ቁመቱ እና ገጽታው እንጂ አነጋገሩ የልጅ አይመስልምና አንዱ ታዛቢ፤

 

“ይህ ህጻን ልጅ ሳይሆን በምግብ እና በኑትሪሽን እጥረት የቀጨጨ አዋቂ ሰው ነው።” ሲል ተደምጧል።

 

በብሄራዊ ቴለቪዥን የሚቀርቡ እንደዚህ አይነት ፌዞች ብዙዎችን ቢያበሳጩ ሊደንቀን አይገባም። ይልቁንም የህወሃት መገናኛ ብዙሃን ዛሬ ዛሬ የቀልድ ማፍለቂያዎች እየሆኑም መጥተዋል። በቲቪው ፕሮግራሞች እና በዜናዎቹ ቀልድ እየፈጠሩ የሚዝናኑ ጥቂት አይባሉም።

 

“በሊቢያ ይህ እንደሚደርስ አውቀን ኮሎኔል ጋዳፊን አስቀድመን አስጠንቅቀን ነበር።” ይላል ሌላው ዘገባ።

 

ታዲያ ከዚህ የበለጠ ምን የሚያስቅ ነገር ይኖራል? የኮመዲ አርቲስቶች በኢ.ቲ.ቪ. ልማታዊ ቀልድ ብቻ እንዲቀልዱ በተደረገበት ሃገር በአሁኑ ሰዓት እንደፈንድሻ አያሳረረ ፈገግ እያሰኘን ያለው ኢ.ቲ.ቪ. መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

 

አንድ ግዜ በአጋጣሚ ኢ.ቲ.ቪ.ን ክፍቼ ስመለከት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለ ልዩ የሰርግ ስነ-ስርዓት ይታይ ነበር። ሰርጉን ልዩ ያደረገው ሙሽሮቹ በሊሞዚን ሳይሆን በትራክተር ተጭነው በከተማው ውስጥ ሲንሸራሸሩ መታያቸው ነበር። ሙሽሮቹ ለምን ይህንን እንደመረጡ ከጋዜጠኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤

 

“ሰርጋችንን በትራክተር ለማድረግ የተገደድነው ትራክተር የልማታች አጋር ስለሆነ ነው።” ነበር ያሉት።

 

ይህንን የተገነዘበ አንድ ህጻን ታዲያ “ያ ትራክተር ቀኑን ሙሉ በከተማው ውስጥ ሲዞር ከሚውል መሬት ቢያርስ ኖሮ ልማቱን ሊያግዝ ይችል ነበር።” ሲል በህጻን አእምሮው ትዝብቱን ገልጿል።

 

እንደዚህ አይነቱ የትራክተር ሰርግ በአንድ ብቻ ቆመ እንጂ ቢቀጥል ኖሮ የልማቱ ተረት-ተረት ቀርቶ በሃገሪቱ የነዳጅ ዋጋ ጣራ ላይ በደረሰ ነበር። ልብ በሉ ትራክተር በሌትር 3 ኪሎ ሜትር ነው የሚጓዘው።

 

ሰርግ በትራክተር ተደረገ፤ ስለልማት ተወራ.. ተዘፈነ። አመታት አለፉ። ነገር ግን የተባለው ልማት ከአፍ ሊያልፍ አልቻለም። ልማት የሚለው ላይ ለማደናገርያ “ትራንስፎርሜሽን” የሚል የእንግሊዝኛ ቃል መጨመረበት። ትራንስፎርሜሽኑም አመት አለፈው - ለውጥ ግን የለም። ስለዚህ የልማቱ ቀረርቶ በሌላ ጨዋታ መተካት አለበት። ሽብርተኝነት፤ አኬልዳማ …።

 

ኢ.ቲ.ቪ. በአኬልዳማ አዲስ ድራማ ሊነግረን የፈለገው ሽብርተኞቹ የትራንስፎርሜሽኑ (ለውጡ) እንቅፋቶች ሆኑብን ነው።

 

በእውነት ለመናገር ከድራማው ውስጥ ህጻናትን ሊያስፈራራ የሚችል አንዳች ነገር አለየሁም። በደራሲው ፈጠራ በድራማው መሪ ተዋንያ በግንቦት ሰባት የሽብር ሴራ የተገደሉ ሰዎችን አላሳዩንም። በሴራው የፈራረሰ የ ”ልማት አውታርም” በፊልሙ አልተካተተም። የቀረቡት ምስሎችም ሆኑ ንግግሮች በስውር ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃን በግልጽ የሰማናቸው እና የተመለከትናቸው ታሪኮች ናቸው።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመለስን ስርዓት በሁለገብ ትግል እናስወግዳለን አሉ፤ ኤልያስ ክፍሌ አስመራ ሄዶ መጣ ... በአዲሱ ዓመት ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል … ወዘተ የኤልያስን አስመራ መሄድ የሰሙት አሁን ነው እንዴ? ... ይህንን ነገር ነው ህጻናት እንዳይሰሙት የተባለው ወይንስ ጸሃይ የሞቀው የ1994ቱን የበደኖ እልቂት?

 

በርግጥ ፕሮግራሙን እንዲሰራ የተፈረደበት ጋዜጠኛ አቀራረጹ ለህጻናት ብቻ ሳይሆን ለአዋቂም አስፈሪ እንዲመስል ተደርጓል። ካሜራው ጋዜጠናውን አውሬ አስመስሎ አቅርቦታል። ከ13 አመት በታች ያሉ ህጻናት የዚህ ጋዜጠኛ ምስል ብቻ ሊያስፈራቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ፕሮግራሙ ለህጻናትም ቢሆን የሚያሳምን ታሪክ ሆኖ ሳይሆን ይልቁንም እንደ ቶም እና ጄሪ ፊልሞች እነሱን ዘና የሚያደርግ የፈጠራ ታሪክ በመሆኑ እንጂ። የቶም እና ጄሪ ፊልም የሚያዝናናው ከእውነታ የራቀና የማይመስል ነገር ስለሚሰሩ ነው።

 

የልማቱ፤ የትራንስፎርሜሽኑ እና የህዳሴው ወሬ ሰሞኑን ጋብ ያለ ይመስላል። እነዚህ ሁሉ ህወሃት ቀውስ ውስጥ ሲገባ የሚስባቸው ካርታዎች ነበሩ እንጂ በተግባር አላየናቸውም። 80 ቢሊዮን የተገመተው የህዳሴው ግድብ መዋጮም የሼክ አላሙዲን ተጨምሮበት 7 ቢሊዮን ብር ላይ ቆሟል። ለሽልማትና ለፉከራ ወጪ እየተደረገ ያለው ከዚሁ መዋጮ ከሆነም ሰባቱ ቢሊዮን እስክሁን ሳይጋመስ የቀረ አይመስልም። የአምስት አመቱ የልማት እና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አንድ ኢንች አልተንቀሳቀሰም። ከጅምሩ የተጠናበት እና የተመከረበት አይደለማ። ታዲያ ይህ ካርታ ሲበላ ሌላ ካርታ መውጣቱ ለእነ መለስ አዲስ ነገር አይደለም፤ - ሽብርተኝነት፤ አሁን ወሬው ሁሉ ሽብርተኝነት ነው።

 

በህቡዕ ሳይሆን በአደባባይ የሚሰሩትን ሰላማዊ ስራዎች እንደማስረጃነት እያቀረቡ ሽብር ይሉታል።

 

በእርግጥ እነመለስም የማይክዱት አንድ እውነታ አለ። እየመሩት ያለው ስርዓት ህዝባዊ መሰረት ስለሌለው እንዲሁ በብእር ብቻ ይሽበራል። ስርዓቱ ገና በነጻ አስተያየት ስለተሸበረ ብእርተኞችን በአሸባሪነት ፈረጃቸው። በሽብርተኝነት ስለተከሰሱት ወገኖች ተጠይቀው አቶ መለስ ለአሻንጉሊት ፓርላማቸው ሲናገሩ፤

 

... ይህንን የሽብርተኝነት አዋጅ የሚያወግዙ ካሉ ተሳስተዋል። ምክንያቱም አዋጁ ካደጉ ሃግሮች ህግ አንድ በአንድ ተገልብጦ የመጣ እንጂ እኛ የፈጠርነው አይደለም።" ነበር ያሉት።

 

ያው ከመከረኛ አመሪካ ወይንም ክእንግሊዝ ማለታቸው ነው። ከአንድ ሃገር የተገለበጠን ህግ በሌላ ሃገር ላይ ተግባራዊ ማድረግ አሳፋሪ ከመሆኑ ይልቅ እንደትልቅ ሞያ ተቆጥሮ ነው ለፓርላማው እየተነገረ ያለው። ያም ሆኖ የጸረ-ሽብር አዋጅ ካወጡ ሃገሮች ውስጥ አንዳቸውም ሃሳቡን በነጻ የገለጸን ወገንም ሆነ ባይተዋር ዜጋ አላሰሩም።

 

አቶ መለስ ይህንን አዋጅ ከባእዳን ሃገራት ከሚገለብጡ ይልቅ ካደጉ ሃገሮች የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ወይንም የፕሬስ አዋጅን ቢገለብጡና ቢተገብሩ ሃገሪቷን በጠቀሙ ነበር።

 

ፕሮፌሽናል የተባሉ የአለማችን አሸባሪዎች ላይ እንኳን እንዲህ የተጋነነ ነገር አልሰማንም። አለም አልቃሂዳም ሆን አልሻባብ ላይ ሲዘምት እንደዚህ አልጮኸም። እነ እስክንድር ነጋ ጦር አልመዘዙም። ስርዓቱንም በሃይል እንገልብጥ አላሉም። እውነታውን በብእራቸው ቁጭ አደርገው ስላሳዩና አካሄዱን አደገኛነት ስለጠቆሙ ብቻ ነው አሸባሪ ተብለው እስር ቤት የተወረወሩት።

 

በአኬልዳማ ትያትር ትወና ላይ ዋነኞቹ የመርህ ሰዎችን አለማየታችን ደግሞ ቅንብሩን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አስመስሎታል፤ እነ እስክንድር ና ውብሸት እነ ርእዮትንና አንዷለምን በቃለ-መጠይቁ የሉም። በመርህ ጥያቄ ላይ አይደራደሩም እና እነሱ ሊኖሩም እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ከዲያስፖራው የሚጠሩት አንዳንዶቹ የተከሰሱት በፓል-ቶክ ቅጽል ስሞቻቸው መሆኑ ደግሞ የህወሃትን የስለላ እና የደህንነት ብቃት ገደል ያስገባዋል። የ'ረቀቀው' የህወሃት ኢንተሊጀንስ ይህንን እንኳን ሳያጣራ ነው ክስ የመሰረተባቸው።

 

በሃገር ቤት ያሉ በሰላም የሚታገሉት ወገኖች ላይ የተመሰረተው ክስ ደግሞ ፍርሃት የወለደው እብደት ካልሆነ በስተቀር ከሽብርተኝነት ጋር የሚያያይዝ አንዳች ጉዳይ የለውም። አንድ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራቱ ምክንያት አባላቱ በሙሉ በሽብርተኝነት ተከስሰዋል። ሳላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑ ቀርቶ ሽብርተኝነት መባሉ፤ ሰዎቹን ምን ያህል እንቅልፍ እንደነሳቸው ያሳየናል። አዎ አለም ያደነቀው የፌስቡክ አብዮት ለነመለስ ዜናዊ በሽታ ነው። ሽብርተኝነት ነው።

 

ከአኬልዳማ ድራማ ያስገረማኝ ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ የተላለፈው መልእክት ብቻ ነው። አንዳርጋቸው ጽጌ አስመራ ላይ "ሽብርተኞችን" እያሰለጠነ የመንግስት ተቋማትን እና የህወሃት ባለስልጣናቱን ለማስገደል እየታገለ እንደሆነ ጠቆም አድርገዋል። ይህንን መልእክት ያስተላለፉት በስህተት ካልሆነ በስተቀር እነ በረከት የኢትዮጵያን ህዝብ ብሶት ገና እንዳልተረዱት ይጠቁመናል። ለሁለት አስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ በመሆን እያሰቃዩ ያሉት የወያኔ ባለስልጣናት ቢወገዱለት የኢትዮጵያ ህዝብ በደስታ እንድሚጨፍር እንኳን የገባቸው አይመስሉም። ምን ይታወቃል እነሱም እንደ ኮሎኔል ጋዳፊ ህዝቡ ይወደናል ብለው ያስቡ እኮ ይሆናል።

 

በዚህ ረገድ ታዲያ ለግንቦት ሰባት ነጻ ማስታወቂያ ሰርተውለታል።


ክንፉ አሰፋ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ