ባየነው ከፊንላንድ

በዚህ በኢንተርኔት ዘመን ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሚቀጥለው ቀን ምን ዓይነት ዜና እንደሚቀርብለት መገመት አይቸግረውም። በቅርቡ በAmerican Chronicle ላይ “Why Europe can not tolerate the existance of 'Ethiopia' “ በሚል ርዕስ በዶ/ር ሙሐመድ ሜጋሎማቲስ የተፃፈው ፅሁፍ '.. the gangster state 'Ethioipia' must be decomposed and broken down to ten pieces, and all the oppressed nations that have been held captive therein must be liberated.' ብሎ ይደመድማል። በርግጥ ከሌሎቹ ፅሁፎቹ እንደተራዳሁት ሰውዬው ፀረ-ኢትዮጵያ (እንደሱ አባባል ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እኛ ሰርቀነው ነው) ብቻ ሳይሆን ዘረኝነትንና ጥላቻን፣ ፀረ-ሠላምን የሚያስፋፋ ነው።

ይህ የተፃፈው በአንድ ቱርክ ነው። የምዕራቡም ሆነ የምስራቁ ሚድያ በፍፁም የእኛን ሠላምና ጥሩ የማይፈልግ ነው የሚመስለው። ቢቢሲ የምርጫ 97ን ጉዳይ ሲዘግብ የ77ቱን የረሃብ ቪዲዮ እያሳየ ነበር። እስቲ ይሁን፤ ቢቢሲንም እንተወው፣ የቱርኩንም ምሁር ሆነ ሌሎቹን የግል ጉዳይ ያላቸውን ለጊዜው ወደጎን እናድርጋቸው፤ መቼም ከጠላት አፍ ሙገሳ ማግኘት ይከብዳል። እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ግን ምን እየዘገብን ነው?

 

በርግጥ ሀገራችን ውስጥ ያለውን የወያኔ ግፍ፣ ድህነቱን፣ ችግሩን፣ ከሁሉም በላይ የመረጃ አፈናውን እናውቀዋለን፣ ኑረንበታልም። ለህዝቡ፣ በተለይም በስደት ለሚገኘው፣ ትክክለኛውን መረጃ ማቅረቡ ተገቢ ነው። አሁን አሁን ግን ከመጠን ሳያልፍ አልቀረም።

 

ምንም ወቅታዊ ሁኔታዋ የከፋ ቢሆንም እንኳ ኢትዮጵያ ሲዖል አይደለችም። ስላሉን ጥሩ ጎኖች ብዘረዝር አሰለቻችሁ ይሆናል (ጥሩ ነገር ሲደጋገም ይሰለቻል?) በስደት የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ግን ከእነዚህ ጥሩና ድንቅ ጎኖች አንዱን እንኩዋን ያልሰማው፣ ቀንና ማታ የቢቢሲንና የዶ/ር ሙሐመድን ዓይነት ሰቆቃወ-ኢትዮጵያ ወሬዎች የጠገበው ፈረንጅ ስለሀገራችንና ስለእኛ የሚሰጠንን አስተያየት ጠንቅቀን እናውቃለን። “ሀገራችሁ የሚበላ ነገር አለ?” ነበር ያለኝ አንድ ከወራት በፊት ያገኝሁት ፈረንጅ። በርግጥ ይህን ገፅታ ለመቀየር ብዙ ጊዜና ሥራ እንደሚጠይቅ ዕውን ነው።

 

ለዚህም የፖለቲካ ውይይት ማድረጉ፣ መረጃ ላልደደረሰው ወገን መረጃ ማድረሱ ባልከፋ ነበር። ነገር ግን አወቀንም ሆነ ሳናውቅ ድረገፆቻችንን የምናጨናንቅባቸው የሰቆቃ ወሬዎች ወሰናቸውን አልፈዋል፤ እኛ ራሳችን ስለሀገራችን ያለንን አመለካከትም ሳያዛቡት አይቀርም። አሁን አሁን መጥፎ ዜናዎች ካልሰማን ዜና ያልሰማን የማይመስለን፣ ምንጩንም የምንጠራጠርበት ሁኔታ ይታየኛል።

 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ክፉ ወሬ በዓለም ሁሉ ሞልቷል። ዜና ማሰራጫዎችም ይህን ይፈልጉታል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ትንሽ ቀበሌ የመጻሕፍት ክለብ ያቋቋሙና ምናልባትም የኛን ጥቂት እርዳታ የሚፈልጉ ታዳጊዎች ይኖራሉ፤ የሰፈራቸው ገላጣ ሜዳ ላይ ጥቂት ችግኞችን የተከሉ ወጣቶችም አይጠፉም፤ ብዙ መቶ ዓመታት ያስቆጠረ አንድ ቤተክርስቲያን ወይም መስጅድ ያሳደሱ መንደርተኞችም ይኖራሉ። በቅርቡ የተገኘ አዲስ ቅርስም አለ። ለኦሎምፒክ የሚዘጋጁ አትሌቶችም፣ ሌላም ሌላም። እጅግ ብዙ ጥቃቅን የሀገራችንን መልካም የሚያስታውሱን ዜናዎች ሊሆኑ የሚችሉ ክንውኖች አሉ። ለነገሩማ እዚህ የፈረንጅ ሀገር እየገነባንና በፖለቲካ እየተቧቀስን ወረቀት ላይ ከምንዝል “አዋቂዎች” ይልቅ ችግኝ የተከሉት፣ ቤተመጻሕፍት የከፈቱት፣ ቅርስ ያሳደሱት፣ ለሀገራችን ትንሽም ብትሆን የተሻለ ሰርተዋል።

 

መጥፎ ዜናዎቻችን ከሁሉም በላይ እየጎዱ ያሉት ስለሀገሩ ምንም የማያውቀውን ስደተኛ የድረገጽ-ኢንተርኔት ዘመን ወጣት ትውልድ ነው። እኛም ከነቢቢሲና ዶ/ር ሙሐመድ ጋር በመተባበር ስለ ሀገሩ ዕውቀት እያስጨበጥነው ነው። ታዲያ ማን ነው ነገ ኢትዮጵያ ሂዶ አንድ ድንጋይ አንስቶ ሀገር የሚያቀናው?

 

ወሬዬን ላጠቃልና፣ እባካችሁ! መረጃ ማስተላለፋችንና በፖለቲካ ላይ አትኩረን መጻፋችን ጥሩ፣ ግን ስለሀገራችንም በጎ ጎን እየፃፍን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሚዛናዊ ዜና እናቅርብ።

 

ዛሬ ለአንድም ሆነ ለሌላ ምክንያት የለጠፍናቸው ክፉ ወሬዎች ነገ ብዙ ጭንቅላቶችን ለውጠውና ከዛሬ ክፉ ወሬነታችው የባሰ ክፋት ይዘውብን እንዳይመጡ እናስብ።

 

አመሰግናለሁ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ