መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)
መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር)- ግንቦት 2000
ስማቸው እንደሚያመለክተው፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከመንግሥት መዋቅር ውጭ ሆነው፣ ከመንግሥት ምንም ያህል እርዳታ ሳይፈልጉ፣ ራሳቸው ከየትም በሚሰበስቡት ገንዘብ በአገር ውስጥ የሚሠሩ ድርጅቶች ናቸው። የሚሠሩት ምንድን ነው? የሥራቸው ዓይነት በጣም የተለያየና ሰፊ ቢሆንም፣ በሁለት መመደብ የሚቻል ይመስለኛል። አንደኛው በሰብዓዊ ርኀራኄ ላይ የተመሠረተና የሰውን ልጆች መራራ ኑሮ በተቻለ መጠን ለመቀነስና ወደተሻለ መንገድ ለመምራት ነው። ሁለተኛ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሰው-ሠራሽ ቀውስ በደረሰ ጊዜ አስፈላጊውን እርዳታ ለተጎዱት ሰዎች ለማቅረብ ነው።
የተጠቀሱትን ሁለት ዋና ዓላማዎች፣ ተጠግተው ሌሎች የኃይማኖትም ይሁን ወይም የፖለቲካ ሥራዎች ይካሄዱ ይሆናል። የኃይማኖትንም ሆነ የፖለቲካ ተልዕኮን እንደ ዋና ዓላማዎች አድርገን ብንወስዳቸው፣ በራስ መተማመንና ነፃነት ባለበት ማኅበረሰብ እንደችግር አይወሰዱም፤ እያንዳንዱ ሰው ጥቅሙንና ጉዳቱን በነፃነቱ እያመዛዘነ ይቀርባል ወይም ይርቃል። እንግዲህ እያንዳንዱ ሰው ጥቅሙንና ጉዳቱን የመለየት ነፃነት እንዳይኖረው ካልተፈለገ በቀር፣ እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚጠሉበት ምክንያት የለም። ሌላው መከራከሪያ ነጥብ፣ እነዚህ ድርጅቶች ራሳችንን እንዳንችል ያደርጉናል የሚል ነው። ይህ ክርክር ባዶ ነው። ምንም ዓይነት እርዳታና ድጋፍ፣ ራስን ከመቻል ሊያግድ አይችልም፤ ራስን ከመቻል የሚያግደው ነፃነትን ማጣት ነው።
እስቲ እውነቱን ገልጠን እንየው፤ በደርግ ዘመን፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ክፉ ጥርጣሬ ነበር። በ1977 ዓ.ም. የደረሰውን አገር-አቀፍ ችጋር የደርግ አገዛዝ በምንም መንገድ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ስለዚህም በሩን ብርግድ አድርጎ ከፈተላቸው። ከባድ የጭነት መኪናዎች፣ ገንዘብና ምግብ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ሆኖ ችጋሩን በፍጥነት ለመግታት ተቻለ። ብዙም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቋቋሙ። እነዚህ ድርጅቶች ያደረጉት ትልቅ ነገር ከ1977 ወዲህ በገፍ ሰዎችን የሚጨርስ ችጋር እንዳይከሰት መርዳታቸው ነው። ከ1977 ወዲህ እስከዛሬ ያሉት ዓመታት፣ አብዛኛዎቹ ከባድ የእህል እጥረት የተከሰተባቸውና ከሁለት እስከ አሥር ሚልዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ለረሀብ የተጋለጡባቸው ናቸው። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ ከፋ የችጋር ደረጃ ሳንሸጋገር የቀረነው በነዚሁ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥረት ነው። ይህ እውነት ብቻ የድርጅቶቹን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት ጎልቶ ያሳያል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ጠቃሚነታቸውና አስፈላጊነታቸው ጎልቶ የሚታየው ኋላ-ቀርና በሁሉም ነገር ደሃ በሆኑ አገሮች ነው፤ ጠላት መስለው የሚታዩትም እንደነዚህ ባሉ ደሃ አገሮች ነው። አሁን በበርማ (ሚያንማር) የምናየው አገሩ ከባድ ዝናብ በተቀላቀለበት አውሎ ነፋስ፣ ከ78 000 ሰዎች በላይ ሞተው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን አጥተው ሲሰቃዩ አምባገነኑ አገዛዝ ከውጭ እርዳታ አልቀበልም በማለት፣ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ነው። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አምባገነኖች ከሕዝባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በቅራኔ የተወጠረ ነው። ከነሱ ቁጥጥር ውጭ፣ ከሕዝቡ ጋር የቀረበና የወዳጅነት ስሜትን የሚፈጥር ግንኙነት ሲፈጠር ሁልጊዜም ያጠራጥራቸዋል፤ ያስደነብራቸዋልም፤ በነሱ ላይ ለሚደረግ ተቃውሞም ሆነ ሴራ፣ በርን ይከፍታል ብለው ያምናሉ። ሁለተኛም ችሎታ ያላቸውን አገዛዙ የማይፈልጋቸውን ሰዎች ይስባሉ፤ ክፍያቸውም አንጀት የሚያርስ ነው፤ የሚነዱትም መኪና ድንቅ ነው፤ ይህ ሁሉ ቅናትንና ምቀኝነትን ይጋብዛል።
የአምባገነን አገዛዝ የሰዎችን ኑሮ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይፈልጋል፤ ቢቻለው ነፍሳቸውንም ለመቆጣጠር ይመኛል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ፣ ቀደም ሲል የጠቀስሁት የበርማ አገዛዝ ነው፤ ለሰው ሕይወት ደንታ ስለሌለው፤ በሩን ዘግቶ፣ የሞተው ሞቶ፣ የተረፈው ይበቃኛል የሚል ይመስላል። ይህንን የበርማ የጭካኔ አገዛዝ፣ ለሕዝብህ እዘንለትና እርዳታ እናቅርብለት ብለው ለመለመን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ፣ ወደዚያ አገር በመሄድ ላይ ናቸው። ጨካኝ የሚባለው የደርግ አገዛዝ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ እንድናምን ያስገድደናል።
ይህንን ሁሉ ካልን በኋላ ግን አንድ ዋና ነገር መጨመር አለብን፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የስለላና የማነቆ መረብ የለባቸውም ለማለት አይቻልም። ሁሉም በሰብዓዊ ርኅራኄ የተቀሰቀሱ አይደሉም፤ ይህንን ጉዳይ ዛሬ በኢትዮጵያ የአገዛዙን ሥልጣን የያዙት፣ በደንብ የሚያውቁት ይመስለኛል። ከዚያም በላይ ለጋሾቹ አገሮች የቅርብ ወዳጆቻቸው ናቸውና የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ያውቃሉ።
ለችግሩ መፍትሔ የሚሆነው ቆም ብሎ ማሰብ ነው። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ በድርጅቶቹ እርዳታ በመጠኑም ቢሆን፣ ጊዜያዊም ቢሆን፣ ችግሩ መቃለሉን መካድ አይቻልም፤ እንዲሁም ደግሞ በነዚህ ድርጅቶች በኩል ወደ አገር የሚገባው የውጭ ምንዛሬ፣ ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ድርጅቶቹ የሚታሙበት የገንዘብ ማባከንና የስለላውንና የማነቆውን መረብ፣ በሕጋዊ ሥርዓት ለመቆጣጠር የሚቻል ይመስለኛል። ምንጊዜም ለማናቸውም ችግር መፍትሔው ማሰር፣ መከልከልና ማገድ ሲሆን፣ የሚያመለክተው የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ማዳከሙን ነው። ውጤቱ የባሰና የከፋ ወደ ችጋር አፋፍ ገፍቶ፣ የሚያስጠጋ ደሀነት ይሆናል።
(ለፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ጽሑፍ መነሻ የሆነውንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስመልክቶ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ከተዘገቡ ዜናዎች ውስጥ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)



