ግርማ ደገፋ ገዳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በ2006 (እኤአ) የኩባው ፊደል ካስትሮ “ሞቱ!” ሲባል፣ በማያሚ (ፍሎሪዳ) መንገዶች ላይ ዳንስና ጭፈራ ነበር የተከተለው። የመኪና ጡሩምባ፣ ጩኸት፣ ፉጨት፣ የላቲን ሙዚቃና ውዝዋዜዎች በአናት በአናቱ ሲንቆርቆሩ ነበር ሌሊቱ የነጋው። ፊደል ካስትሮ ፕሬዚዳንት ስለመሆናቸው ሳይሆን፣ ኩባዊ ሰው ስለመሆናቸው ብቻ እያሰቡ እንኳ ያዘኑ የሉም። ወደ ኢትዮጵያ ዞር ስንል፣ የኢሕአዴጉን ጠቅላይ ሚኒስትር አስመልክቶ፣ አንዳንድ ሚዲያ ላይ ያልወጡ የሚያስቁም የማያስቁም ወሬዎች አሉ።

አንደኛው ይህ ነው፦ “መለስ የታመመው ለሌላ ነገር ሳይሆን፣ አበበ ገላው የአሜሪካ መንግሥት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ስላስደነገጠው፣ ከአሜሪካ መንግሥት ካሳ ለመጠየቅ ነው።” … ሌላው ደግሞ “በአንድ አበበ እንዲህ በፍጥነት ከፈራረሰ፣ አሥር አበበዎች ቢሆኑ እንዴት ሊሆን ነው? … ገና ‘We need freedom …’ ብለው ሲጀምሩ፣ እንደ ጨው ቅልጥልጥ?”

 

ቴሌቪዥኑን፣ ራዲዮውን፣ ጋዜጣውን፣ ኢንተርኔንቱን፣ ስካይፒውን፣ ጉግልቶኩን እና ዲሹን በሙሉ በራሳቸው ቁጥጥር ሥር ያደረጉት፣ በቁጥጥራቸው ሥር ባደረጉት ሚዲያ የራሳቸውን ‘ኦ! እሳቸው እስማርት ናቸው!’ ፕሮፓጋንዳን ብቻ የሚለቁትና ዓለም በሚዲያ ጠላትነት የፈረጃቸው የኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትርና “የአፍሪካ ተወካይ” በጠና ታመዋል። በማይታመን ሁኔታ አሽመድምዶ ሥፍራው ካልታወቀ ቦታ ወርውሮ የጣላቸው በሽታ፣ ካንሰር ይሁን አበበ በግልጽ አልተነገረም። እንኳን አፍሪካን ሊወክሉ፣ ራሳቸውን ወክለውና እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ከእንቅልፋቸው ብንን ብለው፣ “እንቅልፍ በጣም ስለምወድ፣ ተኝቼ ነው” የሚባል ማስተባበያ ለመስጠት እንኳ አቅም አጥተዋል። ተበለጡ! ‘የአፍሪካ ተወካይ ነኝ! የክላይሜንት ጠበቃ ነኝ! ድኅነት አስወጋጅ ነኝ! እኔ ከሌለሁ ያፍሪካ ቀንድ ያልቅለታል!’ የሚባል ረጅም ጡሩንባ ዛሬ የለም። ኮፐንሃገን፣ ፕሪቶሪያ፣ ካምፕ ዴቪድ፣ ኦስሎ፣ ፓሪስ፣ በርሊን፣ ሎንዶንና የዓለም ከተማትን እየዞሩ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በስንት ብድር የሚመጡትን የኢትዮጵያን ሕዝብ አውሮፕላኖች ማንከራተት ቀረ። ስድብ ቀለቡ የሆነው የፓርላማ ሕንጻ ኡፈይ አለ። ለ21 አመታት በጭቆና ሥር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጊዜውም ቢሆን ጭንቀት ከማጅራቱ ላይ ቀነሰለት። ኃይለማሪያ ደሳለኝም ቀን ወጣላቸው። በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ባይሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይ ተገኙ። ቻይናም ሄዱ። ፈራ ተባም እያሉ መግለጫ መስጠትም ጀምረዋል።

 

“99 ፐርሰንት አግኝተናል፤ ብሄር ብሄረሰቦች እንዲሁም ሕዝቦች ‘ጠብ እርግፍ እስኪሉ ድረስ’ ይወዱናል” ሲባል እንዳልነበር ሁሉ፤ ኢሕአዴግ የሳቸውን እውነተኛ ሕመም “ጠብ እርግፍ እስኪሉ” ድረስ ለሚወዷቸው ሕዝቦች መናገር ተስኖታል። አንዴ “ጀርመን” አንዴ “ብራሰልስ ነው ያሉት፤ አልታመሙም፤ ውሸት ነው፤ እሳቸውን በሽታ ንክችም አያደርጋቸውም፤ የተቃዋሚዎች ቱልቱላ ነው፤ በመልካም ጤንነት ላይ ነው የሚገኙት” ሲባል ተቆየ። አሁን ደግሞ፣ “አነስተኛ በሽታ ናት። እንደ ማንኛውም ሰው “ሰው” በመሆናቸው መደበኛ የሕክምና ምርመራ ለማድረግ ነው” የሚባሉ ምክንያቶች ቀጠሉ። “የሥራ ጫና ስላለባቸው ለ21 ዓመታት እረፍት ወስደው አያውቁም!” የሚባለው ደግሞ አንኳሩ ነው። እረፍት እንዳይወስዱ ማን ከለከላቸው? የብዙ ሀገራት መሪዎች’ኮ ዓመታዊ እረፍታቸውን ወስደው ሀይቅ ውስጥ ሲዋኙ ያታያሉ። ብስክሌት ይነዳሉ። ኳስ ይጫወታሉ። ለበዓል ጊዜ ቤተመንግሥታቸው ውስጥ ተራውን ዜጋ ይጋብዛሉ። ቡና ይጠጣሉ። ዶሮ ይበላሉ። ሰው ስለሆኑ ከልጅነት አብሮ አደጎቻቸው ጋር ስለልጅነታቸው ይጫወታሉ። 21 ዓመት በታንክ ታጥረው አልኖሩም። እንደ የጸረሽብርተኛው ሕግ፣ እሱንም ለምንድ ነው ቃል በቃል፣ ኮማ ሳይቀር፣ የማይተረጉሙት?

 

“አልሞቱም፤ ይንቀሳቀሳሉ፤ ይነከላወሳሉ፤ የሐኪም እረፍት ተሰጥቷቸው ነው፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ አውሮፓ ድረስ ሄደው ጠይቀዋቸዋል፤ ሚስታቸውም ፓርላማ ውስጥ ለመገኘት የቻሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት ጥሩ ደረጃ ላይ ስላለ ነው” የሚባል ጊዜው የረፈደበት ሽወዳም እየተደረደረ ነው። በ1997 ዓ.ም ሕዝብ እረፍት ሰጥቷቸው ለማረፍ ያልወደዱ፣ እንዲያውም እረፍት የሰጣቸውን ሕዝብ በመትረየስ የረፈረፈ ሥርዓት መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አንድ አውሮፓዊ ዶክተር ትንሽ ወረቅት ላይ በቢክ እስከሪብቶ የሐኪም እረፍት ሰጥቷቸው፣ ሲያርፉ! … ፐ! ሕዝቡን እንዴት አታለሉት!

 

አንድ ነገር እርግጥ ነው፤ አምባገነን መሪ ሕመሙ እንኳ ተደብቆለት እንዲቆይ ነው ፍላጎቱ። ከታመመበት በሽታ እንዴት ሊድን እንደሚችል ሳይሆን የአልጋ ቁራኛም ሆኖም ሥልጣኑን እንዴት ሊያቆይ እንደሚችል ነው የሚያስበው። የት እንደሚታከም፣ መች ሄዶ መች እንደሚመለስ አይታወቅም። ከስልጣን መጀመሪያ እስከ ሥልጣን መጨረሻ ድረስ ሁሉም ነገር ታፍኖለት ይያዛል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆስፒታል ሲገቡ፣ ሕዝቡ ያውቃል። ለምንና የትኛው ሆስፒታል እንደገቡ፥ ሥልጣኑን ለጊዜው ለማን እንደሰጡ፣ መች ከሆስፒታል እንደሚወጡና ሥራቸውን መች እንደሚጀምሩ ይነገራል። ጆርጅ ቡሽ፣ ቤተስዳ (ሜሪላንድ) ከሚገኘው የባሕር ኃይል ሆስፒታል ለመደበኛ ጤና ምርመራ ሲገቡ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ዲክ ቼይኒ በልብ ሕመማቸው ምክንያት ጆርጅ ዋሺንግተን ሆስፒታልን ሲጎበኙ፣ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለሕዝብ ይነገር ነበር። የቬኑዜላው ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝ፣ ለካንሰር ሕክምና ሶስት ጊዜ ሃቫና (ኩባ) ሲመላለሱ፣ እየሳቁም እያለቀሱም ለሕዝባቸው ነግረዋል። ጸጉራቸውን ሁሉ ተላጭተው ቬኑዜላዊ ሰውና በሽተኛ ለመሆናቸው ለሕዝባቸው አሳይተዋል። ከመገናኛ ብዙህ አልራቁም። ለሕክምና ሲሄዱና ጨርሰው ሲመጡ የደረሱበትን ሁኔታ፣ መሉ በሙሉ ባይሆንም፣ እንደ ሀገር መሪነታቸው የሚናገሩትን ሲናገሩ ተሰምቷል። ‘ሕመሙ የኔ ብቻ ነው! ማንም አያገባውም! ሥልጣኔን እንዳላጣ በሚስጥር ይዤዋለሁ!’ አላሉም። ወይም አላስባሉም። የቀድሞው የራሽያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሟቹ ቦሪስ የልሲንም፣ ለቀዶ ጥገና ሕክምና ሆስፒታ ሊገቡ ሲሉ፣ የሀገሪቱን የኑክሌር ቁልፍ ለምክትላቸው ሲሰጡ በመገናኛ ብዙሃን ታይተዋል።

 

የኢሕአዲጉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከታመሙ በድብቅ የትም እንዲጣሉ የፈቀዱ በመሆናቸው፣ ስለአድራሻቸው “ጠብ እርግፍ እስኪሉ” የሚወዷቸው ሕዝቦች እንዲያውቁ አልተፈለገም። ምስጢር የሆነው፣ አቶ በረከት እንዳሉት የኢሕአዴግ ባሕሪ ሆኖ ሳይሆን፣ ከአምባገነን መሪዎች ፍልስፍና አንዱ በመሆኑ ነው። አምባገነኖች “ታመሙ!” መባልና ጡረታ መውጣት አይፈልጉም። የተኙበትን ሆስፒታልና የበሽታቸውን ዓይነት ሕዝብ እንዲያውቅ ምርጫቸው አይደለም። በሰውነታቸው ላይ የሚታየውን የበሽታ ምልክት ሁሉ ክደው ሲደነፉ ነው የሚከርሙት። ‘እንዴት ሆኖ በሽታ ይይዘኛል! ሲ.አይ.ኤ. ነው የሚያስወራው!’ የተለመደ ሆኗል። በያዛቸው በሽታ ምክንያት ከስተውና ተጣመው እየሄዱ፣ ‘ሙሉ ጤነኛ ነኝ’ ብለው የሚሸመጥጡ ሸምጣጮች ናቸው። ምክንያቱም ሥልጣናቸውን የሚቀሙ ይመስላቸዋል። ከተቀሙ ደግሞ ምን እንደሚጠብቃቸው አስቀድመው ያውቃሉ። ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ በኩል፣ ፍትህ የሚፈልጉ፣ ልጆቻቸውን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ በስናይፐር ጠመንጃ የተመነተፉ ብዙ ወላጆች አሉ። ጠመንጃ ስለሌላቸው በኢትዮጵያ ፍትህ የሚነግስበትን ጊዜ ብቻ ነው በሃዘን ተኮራምተው የሚጠብቁት። ጥቁር ልብሳቸውን አንድ ቀን የሚገፍላቸው ሥርዓት እንደሚመጣ ያውቃሉ። የፈለጉትን ያህል ቢቀጠቅጡት እውነት በፍጹም ሊሞት እንደማይችል አሳምረው ይረዳሉና!

 

የኩባ ስደተኞች በማያሚ ጎዳናዎች ላይ እንዳደረጉት ሁሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት እውነት ከሆነ፣ ኢትዮጵያውያን የሳቸውን ሞት በስናይፐር ከሞቱት አፍላ ኢትዮጵያዊ ታዳጊዎች ሞት አስበልጠው የሚያዩበት፣ አሳማኝ ወይ የማያሳምን ምክንያት የለም። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ21 ዓመታት የገዢነት ዘመን፣ ታዳጊ ሕጻናት “ባንክ ዘራፊ!” እየተባሉ በለጋ ዕድሜያቸው በጥይት እየተገሸለጡ ለዘላለም ተደፍተው በቀሩበት ምድር፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት፤ ለቤሰባቸው፣ ለአጋር ባለሥልጣናትና ‘እሳቸው ስማርት ናቸው’ ዘፈንን እየዘፈኑ ኢትዮጵያን ለሚዘርፉ ካልሆነ በቀር፣ ታዳጊ ልጆቻቸውን በግፍ ላጡ ወላጆችና የወላጆቻቸውን ሀዘን ለተጋሩ ዜጎች ምንም ማለት አይደለም። እምባ አይኖራቸውም። ጥቁር ልብስ የሚለብሱበትና ጸጉራቸውን የሚላጩበት ምክንያት ከየትም አይመጣም። “ወይኔ! ጠቅላይ ሚኒስትርዬ! እንደው እኔን ድፍት ያድርገኝ!” እያሉ የሚቆዝሙበት ሁኔታም አይታሰብም። ኢትዮጵያ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል በተሸለመችው ከኤርትራና ከሶማሊያ ጋር ባለው ያልተቋጨ ችግርና፣ በአምስት ዓመቱ የልማትና የእድገት መርሃ-ግብር ምክንያት ከምእራቡም ከምስራቁም አምጥተው በከመሩባት ብድር ሳቢያ፣ ለመሰባበር መሞከሯ የማይቀር ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ እስረኞች የታጎሩባቸው እስር ቤቶች በስፋት ተከፍተው ዜጎች ነጻ የሚወጡበ አጋጣሚ ይመጣ ይሆናል። ከሳቸው ሕመምና ሕልፈት በኋላ በጉልህ ሊጠበቅ የሚችለው ያ ብቻ ነው እንጂ ‘የአፍሪካ ተወካይ ነኝ! የክላይሜንት ጠበቃ ነኝ! ድኅነት አስወጋጅ ነኝ! እኔ ከሌለሁ ያፍሪካ ቀንድ ያልቅለታል!’ የሚባል የሰለቸ ፕሮፓጋንዳ አይደለም። እሱ ፍትህ በሚነግሥበት ሥርዓት ውስጥ ወንበር የለውም። ኢሕአዴግ እንደከፈታቸው ትምህርት ቤቶች፣ ‘ወንበር ስለሌለ የራሴን ድንጋይ ይዤ ልቀመጥ’ ማለትም አይሰራም።

 

እንዲህ ዓይነት ክስተት የኢሕአዴጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ብቻ አይደለም የተከሰተው። ከኢሕአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁኔታ ጋር የመመሳሰል ጸባይ ያለው፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኡማሩ አዱ ሁኔታ አንዱ ነው። ማቹ ፕሬዚዳንት ከመሞታቸው በፊት የነበሩትን ጥቂት ጊዜያት ያሳለፉት፣ በሳኡዲ አረቢያ ሆስፒታል ነበር። የሳቸው በሕመም ምክንያት ከናይጄሪያ ፖለቲካና ከመንግሥት ኃላፊነታቸው መራቅ ያሳሰባቸው የናይጄሪያ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን፣ በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ናይጄሪያ በምክትል ፕሬዚዳንቱ እንድትተዳደር ሲወተውቱ፣ የሳቸው አጋሮች ደግሞ፣ “ኧረ! ምን ነካችሁ? አበዳችሁ እንዴ! ፕሬዚዳንቱ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው! መንግሥታቸውን ለመምራት ብቁ ናቸው! በቅርብ ቀን በተሟላ ጤንነት ከች ይላሉ! … ለተለመደው ምርመራ ነው እንጂ!” ይሉ ነበር።

 

ከሆስፒታል አልጋቸው ሆነው የሞት አፋፍን በግልጽና በቅርበት የሚመለከቱትን ታማሚ ፕሬዚዳንት ድምጽን ለአንዲት ደቂቃ ለምትሆን ጊዜ ከሳኡዲ አረቢያ ቀድተው፣ በዛች የአንዲት ደቂቃ ደካማና ሰላላ ድምጽ የናይጄሪያን ሕዝብ በማሞኘት ለመግዛት ሞክረዋል። ይሁንና፣ መዓት ምክንያት ፕሬዚዳንት ኡማሩ አዱን ከሞት አላተረፋቸውም። “እርስዎ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ስለሆኑ ሞት አይመለከቶትም!” አልተባሉም። ጓደኞቻቸው እንዳሉትም ወደ ናይጄሪያ ከች አሉ። የመጨረሻውን ቀናቸውንም እየጠበቁ ትንሽ ወራት ቆዩ። በመጨረሻም ይህቺን ዓለምና ‘የሕዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ የሚባለውን የፖለቲካ ድርጅታቸውን ጥለው፣ ባዶ እጃቸውን ተሰናበቱ። ፕሬዝዳንትነቱንም፣ ምክትላቸው የነበሩት ጉድለክ ጆናታን ወስዱት። ዛሬ ሁለት ዓመት ሞላቸው፤ የሚያስታውሳቸውም የለም። ይህቺ ምድር፣ እንኳን የሞተን አምባገነን መሪ፣ በእውነተኛ ምርጫ ሥልጣን ይዞ ሕዝቡን ካገለገለ በኋላ፣ በጡረታ የተገለለን የቀድሞ ዴሞክራት መሪን እንኳ ከሚድያ የፊት ገጽ ላይ በፍጥነት ጠርጋ የምታወጣ ከንቱ ናት! ክሊንተን፣ ብሌር፣ ቡሽ፣ ሳርኮዚ፣ እና ሌሎችንም ጡረተኞች ያስታውሱ።

 

እንደማጠቃለያ አንድ ነገር ልጨምር። “የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ተሸለሙ” ይሰማል። “የምእተ ዓመቱን ጎል አሳኩ። ኢትዮጵያ በጤና መስክ ብዙ ቁምነገሮችን አስመዘገበች” ይለፈለፋል። ብዙ ጉራዎችን ሚዲያው ያሰራጫል። ያንን የመሰለ የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ የሚሰራጭበትን ሀገር የሚመሩ ባለሥልጣናት፤ ሲታመሙ ሀገር ውስጥ አይታከሙም! ምክንያቱም በባዶ ፕሮፓጋንዳ ለመኖር የቆረጡ በመሆናቸው ሆስፒታሉን የከፈቱት ራዲዮና ቴሌቪዥኑ ውስጥ ነው። የነሱ አልጋዎች፣ ሐኪሞችና መድሐኒቶች ያሉት ከዚያ ነው። ሰርኪዉት ቦርዱ ላይ፣ ግማሾቹ ተጣብቀው ግማሾቹ ተንጠልጥለው ነው የሚጠብቋቸው።


ግርማ ደገፋ ገዳ

 

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ