መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) ሰኔ 2000 ዓ.ም.

በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ላይ ስለ ችጋር በተናገርኹት ላይ አንድ ስሙን የማላስታውሰው ሰው፣ ዛሬ ያለውን የገጠሩን ህዝብ የጥጋብ ኹኔታ ባለማወቄ አዝኖልኝ መልስ ሰጥቶ ነበር። ሰሞኑን በውጭ ቴሌቪዥኖች ከትግራይ እስከ ቦረና የተከሠተውን ችጋር በሚያሣቅቅ ኹኔታ ሲያሳዩን ነበር። ይህን በምጽፍበት ጊዜ ትግራይ ውስጥ ህዝቡ በቤተ ክርስቲያን ተሰብስቦ እግዚኦ እያለ ነው። አለማወቅ የሚባለው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚባለውን ከሆነ ጸሐፊው ትክክል ነበር። ነገር ግን ችጋርን እና ሞትን መደበቅ በጣም አስቸጋሪ ነውና እያየነው ነው፤ ላስተዋለ ችጋር ያባረራቸውን በአዲስ አበባ መንገዶችም ላይ ያያቸዋል። ይህንን ለማንሣት የተገደድሁት «እየሮጡ የሚታጠቁት ፖለቲከኞችና የትም የማያደርሰው መንገዳቸው» በሚል በአቶ ጌታቸው ረዳ የተጻፈውን ሳነብ በጣም የሚቀራረብ ሀሳብና አስተሳሰብ ስላገኘሁበት ነው።

 

በዚሁ ልጀምር፤ ጽሑፉ ፖለቲከኞቹ የማያወቁት በማለት «የብዙ ሚሊዮኖች ሕይወት ግንዛቤ ፍላጎትና ተስፋ በመሠረቱ ተቀይሮአል፤» ይላል። ይህ አባባል ፖለቲከኞቹ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን በወጉ አያዳምጡትም ከማለት በቀር የሚያስተላልፈው እውነት እምብዛም ነው፤በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህንን መቀበሉ በጣም አስቸጋሪ ነው። ጽሑፉ ገዢውን ፓርቲ ለመካብና የተቀናቃኝ ጎራውን ለማጥላላት የሚያንጸባርቀውን አስተሳሰብ ሲገፋበት ፖለቲከኞቹ «ባለው ላይ ለማከል … ሳይሆን ለመተካት» የቆረጡ ናቸው ይላል፤ ጥሩ ሃሳብ ይመስላል። ግን ሁለት እግሮች ሊኖሩት ሲገባ አንድም የለውም፣ አንዱ እግር «ባለው» የተባለው ምን ምንን እንደሚያካትትና ብቃቱ ምን ያህል እንደሆነ ማሳወቅ ነበረበት፤ሁለተኛው እግር ፖለቲከኞቹ እንደሚሉትም ቢሆን የሚተካው ምን እንደሆነ አልተገለጸም። ሁለት ስውር መነሻዎችን ይዞ መንደርደር ያስቸግራል፤ ስለዚህ ምንድን ነው የተባለው ስንል በወታደር ቋንቋ «ባለህበት ሂድ!» ብቻ ይሆናል።

 

ለፖለቲከኞቹ የከረረ ውግዘት አለበት፤ አገርንና ህዝብን እንደቋሚ ቤተ ሙከራ ይጠቀሙበታል፤ ይላል። ይህ ውግዘት ከመጠን ያለፈና በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በጣም የተዳከመውን የተቀናቃኝ ቡድኖች ጎራ ጭራሹኑ ለመግደል የታለመ ይመስላል። ለማን እንደሚጠቅም አላውቅም። ኩነኔው አደገኛ ነው።

 

ጽሑፉ የኢትዮጵያን ባህል ተመርኩዞ ቢነሣ አንዳንዶቹን ችግሮች ምናልባት በበለጠ ለማስረዳት የሚቻል ይሆን ነበር። ጽሑፉ ውስጥ አንዳንድ የማይካዱ እውነቶች አሉበት፣ ሜዳው ሲመች የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ፖለቲከኞች የሚሆኑና እንቅፋት ሲያዩ ወይም ሲመታቸው ሰበብ እየፈለጉ ከመድረኩ የሚወጡ አሉ፤ የራስ-ደጃዝማችን ባህል ወርሰው ሌላውን እንደሎሌ የሚመለከቱ አሉ፤ፖለቲካ የህዝብ ጉዳይ መሆኑን ሳይገነዘቡ በድብብቆሽና በሴራ የግል ታማኝ ደጋፊዎቻቸውን ለማበርከት የሚጥሩ አሉ፤ ይህ ሁሉ በገዢው ፓርቲ ውስጥም የሚታይ ነው። ይህ ሁሉ የባህል ተጽእኖ የሚያመጣው ችግር ነው። ሁላችንም የተማረ፣ ያልተማረ፣ ፈረንጅ አገር የኖረ፣ ከመንደሩ ያልወጣ፣ሀብታም፣ ደሀ፣ገዢዎች፣ ተገዢዎች ከባህል የአገዛዝ ተጽእኖ ገና አልወጣንም፤ ሥልጣን ምንድን ነው? በእኛ ባህል ሥልጣን ጎራዴ ነው፣ ሥልጣን ጠመንጃ ነው፣ሥልጣን አለንጋ ነው፤ ባጭሩ ሥልጣን ማስፈራትና ማርበድበድ ነው። በማናቸውም ዓይነት የአገዛዝ ሥርዓት ሥልጣን ማለት ይህ ነው። ለምን እንዲህ ሆነ? በባህሉ መሠረት ሥልጣን የሚወርደው ከላይ ነው፣ ነገሥታቱ እንዲመቻቸው የሥልጣን ምንጭ እግዚአብሔር ነው ብለው ራሳቸውን ወኪል አደረጉ። ከዚያ ጫና ገና አልተላቀቅንም።

 

እንግዲህ አሁን የተቀናቃኞች (ተቃዋሚ የሚለውን አልወደውም) ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መመሥረት ነው፤ በዴሞክራሲ የሥልጣን ምንጭ ህዝብ ነው፣ ስለዚህም እንደኢትዮጵያ ያለ አገር ውስጥ በመጀመሪያ ህዝቡን የሥልጣን ባለቤት ማድረግና አጠቃቀሙን ማስለመድ ያስፈልጋል። አለዚያ የሥልጣን ጥም ያለባቸው ሰዎች ለዴሞክራሲ የተደረገውን ትግል ለራሳቸው ምኞት መሣሪያ አድርገው ወደ አምባገነንነት ይለውጡታል፤ እኛም እያየን ነው፣ በብዙ አገሮችም ታይቶአል። ስለዚህም የፖለቲካ ቡድኖቹ የትግል ዋና ዓላማ ቡድናቸውን ወይም የቡድናቸውን መሪ ለማንገሥና ጠመንጃ ወይም አለንጋ ለማስጨበጥ መሆን የለበትም፣ በሠለጠኑት አገሮች ሁኔታው የተለየ ነው፤ ለምሳሌ አሁን በአሜሪካ በሚደረገው ውድድር ኦባማ ወይም ማኬን ያሸንፋል፣ ምን ማለት ነው? የኦባማ ወይም የማኬን የፖለቲካ እምነትና አስተሳሰብ አሜሪካንን ለአምስት ዓመታት ይገዛል ማለት ነው፤ ይህ የፖለቲካ እምነት የአሜሪካ እምነት ይሆናል፤ ታዲያ መረን አይለቀቅም፤ ምክር ቤቱ አለ፣ የዜና አውታሮች አሉ፣ የምሁራኑ መድረክ አለ፣ በነዚህ ሁሉ ተወጥሮ ለሚቀጥለው ምርጫም ማሰብ አለ።

 

በቀድሞው ቅንጅትና አሁን ደግሞ በአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትሕ ያለው አስተሳሰብ ግለሰቦችን ወይም ቡድኑን ለማንገሥና አፍአዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን በሁሉም ዘንድ ስለሥልጣን ሥር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ነው፤ አስቸጋሪ ነው፣ ለአስቸጋሪነቱ ዋና ምክንያት የባህላችን ተጽእኖ ነው፤ በመጀመሪያ ፖለቲከኞቹ ራሳቸውን መለወጥ እንደሚገባቸው አምናለሁ።

 

በሃያ አንደኛው ምዕተ-ዓመት እውቀት ለእኔ ብቻ የተሰጠ ነው ብሎ መገመት አለማወቅን ያመለክታል፤ «ሰዎቹ (ማለትም ፖለቲከኞች የተባሉትን ይመስለኛል) አዲሲትዋን ኢትዮጵያ በፍጹም አያውቁአትም፤» ማለት ድፍረቱ ቢያስደስትም ንቀቱ ያሳዝናል፤ ይህም ቢሆን የባህል ተጽእኖ አለበት፤ ጽሑፉ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ በቂ እውቀት (ማለት እውነት) ያለበት መሆኑን ለመመዘን ፖለቲከኞቹ «በየክልሉ፣ በየዞኑ፣ በየወረዳውና በየቀበሌው መዋቅርን መዘርጋት … ቆላ መውረድንና ደጋ መውጣትን» እንደሚያስፈልጋቸው ምክር መስጠቱ ይበቃል፤ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን የፖለቲካ ቡድኖቹን ብቻ ሳይሆን የህዝቡንም (ከተፈለገ የሕዝቦቹንም!) የፖለቲካ ስሜት ለማቀዝቀዝ ሳይሆን ለመደምሰስ የተቃጣው ሙከራ ነው። በፖለቲካ ቡድኖቹ ውስጥ ብዙ የሚያሳዝኑ እውነቶች መከሰታቸውን በበኩሌ እቀበላለሁ፤ ሆኖም ስሕተቶች ይታረማሉ፤ አስተሳሰብም ይቃናል፤ ስለዚህም የኢትዮጵያን ህዝብ ተስፋ አላጨልመውም። ኢትዮጵያ የተዓምር አገር ነች። 


 

(ፕ/ር መስፍን በጽሑፋቸው መግቢያ ላይ "እየሮጡ የሚታጠቁት ፖለቲከኞች እና የትም የማያደርሰው መንገዳቸው" በሚል ርዕስ ጌታቸው ረዳ የጻፉትን ጽሑፍ ጠቅሰዋል። ይህ ጽሑፍ የወጣው በሀገር ውስጥ በሚታተመው አዲስ ነገር ጋዜጣ የግንቦት 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ዕትም ላይ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ!) ሲሆን ምላሻቸውን የሰጡት እምቢልታ በተሰኘ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ነው። 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ