ይድረስ ለውድ ብርቱካን! (ኩችዬ)
ይድረስ ለውድ ብርቱካን!
ቃሊቲ እስር ቤት - አዲስ አበባ
June 7 2009
ኩችዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / www.kuchiye.blogspot.com
“ታውቅ ይሆን?” እያልኩ አወጣና አወርዳለሁ። “የስንቱን ህሊና እንደነካች ታውቀው ይሆን?” እላለሁ።
የሰሞኗ ጀንበር የምትጠልቀው የሁለተኛ ልጄን መወለድ ሳሰላስል ነው። ታዲያ ከየት መጣ የማልለው ጭንቀት በድንገት ይወረኛል። ጭንቀቱ ስለልጆቼ እንጂ ስለኔ እንዳይመስልሽ። “እኔ የማውቃትንና ያደግሁባትን ኢትዮጵያ፤ በማይነጥፍ የፍቅር እስትንፋስ ኮትኩቶ ያሳደገኝን ቀዬ፤ ይሰማኝ የነበረውን ልበ-ሙሉነትና ብሩህ ተስፋ፤ በበቂ የማይወሳለትን የወገኔን ጨዋነትና የመቻቻል ባህል፤ … ልጆቼ የነዚህ ቅርሶች ባለቤት የመሆን ዕድል ይገጥማቸው ይሆን?” እያልኩ ነው የምጨነቀው።
ከአጉል ውዳሴ አይቆጠርብኝ እንጂ ምንኛ ስሜቴን እንደነካሽው ላሳውቅሽ እፈልጋለሁ። ከቃሊቲ እስር ቤት በጥር ወር 2006 ገደማ የፃፍሽውን ደብዳቤና አሁን በታህሳስ 2008 እንደገና ወደ እስር ሊወረውሩሽ ሲዘጋጁ “ቃሌ!” በሚል ርዕስ ለህዝብሽ የሰጠሽውን ምስክርነት ደጋግሜ አነበውና ስሜቴ ሲታደስ አየዋለሁ። አልፎ አልፎም ይሁን እንጂ ዓለማችን ጠንካራ መንፈሥ ኖሯቸው የተስፋ ራዕይ በሚናኙ ሰዎች መታደሏን አስታውሼ እጽናናለሁ። ስለጠንካራ መንፈስሽና ስለ ተስፋ ሰጭነትሽ ከልብ አመሰግንሻለሁ።
ውድ ብርቱካን!
ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የወላጆቻችንን ቅስም ሰብረው ለስደት ኑሮ ዳረጓቸው። አሁን ደግሞ ህዝባችንን በጎሣና በኃይማኖት ለመከፋፈል የሚረጨው መርዝ የምንተነፍሰውን አየር እየበከለው ይገኛል። ለዚህ ነው ያሁኑም ትውልድ ስደተኛ እየሆነ የመጣው። አየሽ! የአምባገነኖች ተግባር ርኩስ ነው የሚባለው ተቀናቃኞቻቸውን በመፍጀታቸውና በማፈናቸው ብቻ አይደለም። ከዚያ ባላነሰ የሚጎዱን መጭው ትውልድ የተስፋ ባለቤት እንዳይሆን በሚያካሂዱት የሥነ-ልቦና ጦርነት ነው።
“ዲሞክራሲንና በሥነ-ምግባር የታነጹ መሪዎችን መሻት መብታችን ነው!” ማለትን ካቆምን፤ ተፈጥሯዊና ሕገመንግሥታዊ መብታችንን ከእጃችን ሊመነጭቁ ሲመጡ “ወግዱ አናስነካም!” ማለትን ካልለመድን፤ ያኔ ነው የሽንፈትም ሽንፈት የሚሆንብን። ለዚህም ነው ያንች “ወግዱ!” እና “መብቴን አላስነካም!” ለሁላችን ምሣሌ የሆነው።
ኢህአዲግ ሊያሳምነን የሚጥረው ኢትዮጵያ ከዚህ የተሻለች መሆን እንደማትችል ነው። የተሻለ ዲሞክራሲ፣ የተሻለ ፍትህ፣ የተሻለ አስተዳደር፣ … ሊኖር እንደማይችል። የሚመራንን ፓርቲ ስንመርጥና ለዲሞክራሲ ዝግጁ መሆናችንን ስናስመሰክር የዲሞክራሲን ጎዳና ፈጽሞ ይዘጋዋል። የጎሣ ፖለቲካ እንዳላመቸው ሲረዳ የኃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶችን ያስፋፋል። ይሁን እንጂ ኢህአዲግ ራሱ የማይስተው አንድ ዕውነታ አለ። የሚቆጣጠራቸውን የእርሻ መሬቶች፣ የፋይናንስና የንግድ ድርጅቶች፣ ትልቅ ደመወዝ ከፋይነቱንና ወታደራዊ ኃይሉን የጭቆናና የማባበያ መሣሪያ ባያደርግ ኖሮ ለአንድ ጀንበር ሥልጣን ላይ እንደማይቆይ ያውቃል። በህዝባዊ ፍቅር ተከልሎ በሁለት እግሩ የቆመ መንግሥት እንዳልሆነ ያውቀዋል። ባለሥልጣኑም፣ ካድሬውም፣ ሠራዊቱም በውስጣቸው ይህን ያውቃሉ።
ውድ ብርቱካን!
ኢህአዲግ በጥፋት ጎዳና መጓዙን አቁሞ የህዝብና ለህዝብ የሚያደርገውን ጎዳና ቢመርጥ የሁላችንም ምኞት ነው። የኛው መንገድ የአንድነት፣ የዲሞክራሲ፣ የመብት፣ የእኩልነትና የዕርቅ ስለሆነ በፍቅርና በተስፋ ተሞልቷል። ለሰው ልጅ ከተስፋ የሚበልጥ ቁምነገር የለምና ተስፋን ምርኩዛችን እስካደረግን የነገው ሕይወታችን ከዛሬው የተሻለ እንደሚሆን አንጠራጠርም።
የተስፋን የአንድነትንና የጥንካሬን ካባ ስላላበሽን ለውለታሽ መጠን የለውም። በቅርቡ ከእስር ወጥተሽ የጀመርሽውን የአዲስ ትውልድ አደራ እንድትወጭ፤ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ጉዞ አብረሽን እንድትጓዥ እንፀልያለን። የኔዎቹ ሁለቱ እንዲሁም ያንችዋ “ሐሌ” እጅግ መልካም የሆነች ኢትዮጵያ ትኖራቸዋለች።
ኩችዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / www.kuchiye.blogspot.com