ግርማ ካሳ

በሕዝብና በሀገር ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የሀገሪቷ መሪ ህዝቡን የመምራትና የማረጋጋት ኃላፊነት አለባቸው። ሳዑዲዎች በኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ግፍ በፈጸሙ ጊዜ፣ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ከመምራት ይልቅ ዝምታን መርጠው፣ አንዴ በካታር፣ ሌላ ጊዜ በፖላንድ ሲሽከረከሩ እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ነው። "ጠ/ሚኒስትሩ የት ነው ያሉት?" የሚል ጥያቄና ትችት እየጠነከረ በመጣ ጊዜ፣ ከሣምንታት በኋላ ብቅ አሉ። በኢቲቪ ቃለ መጠይቅም አደረጉ።

 

የአቶ ኃይለማሪያም ቃለ መጠይቅ ግን ብዙ አልተመቸኝም። የወገኖቻችንን ቁስልና ሕመም፣ የኢትዮጵያም ውርደት የተሰማቸው አይመስሉም። በሳዑዲ ያሉ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከወራት በፊት ሁኔታዎችን ኢሕአዴግ አመቻችቶ፣ የተመለሱት ግን በመቶ የሚቆጠሩ ብቻ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ኃይለማሪያም፣ "ስደተኞ በጊዜው ቢመለሱ ኖሮ ችግሩ አይወሳሰብም ነበር" ሲሉ፣ ለተፈጠረው ችግር በዋናነት ተጠያቂ ያደረጉት የተጎዱ ወገኖቻችን ነው። አንዳችም በሳዑዲ የተደረገውን ግፍ የማውገዝም ሆነ የመቃወም ነገር አላሰሙም። ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም እንዳደረጉት፣ ስደተኞችን ሄዶ መጎብኘቱንማ ረሱት። እንደውም "ይሄ የተፈጠረው ችግር ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት በምንም ሁኔታ አያደፈርሰውም" ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከዚያ በፊት "በሳዑዲ ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን" ያሉትን፣ በይፋ ነው የቀለበሱት።

አንድ ወቅት የአፍሪካና ጥቁር ሕዝብ ኩራት እንዳልነበርን፣ አሁን እንደዚህ መዋረዳችን ያሳዝናል። አንድ ወቅት እንደ ጃንሆይ ምኒልክ፣ ጀግናው አጼ ዮሐንስ፣ አንበሳው መይሳው ካሳ የመሳሰሉ፣ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር የቆሙ፣ የውጭ ኃይላትን ተጽዕኖ የተቋቋሙ፣ ኩሩ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች እንዳልነበሩን፣ አሁን ያሉት መሪዎቻችን የዐረቦችን ሰንደል ጫማ ሲልሱ ማየት በርግጥ ልብን የሚያደማ ነው።

ሳዑዲዎች፣ በኢትዮጵያ እንደፈለጉ እየገቡና እየወጡ፣ ሰፊ መሬት ተሰጥቷቸው የፈለጉት እያረሱ፣ በአፈራችን ያመረቱትን ደግሞ በቀጥታ ወደ ሀገራቸው በመላክ ኢትዮጵያን እየበዘበዙ ያሉ ናቸው። ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን ኢትዮጵያ ለዐረቦች እየሆነች ነው።

ለምሳሌ በጋምቤላ የሆነውን እንመልከት። በዚያ የሚኖሩ ነዋሪዎች በኃይል እንዲፈናቀሉ ተደርጎ፣ በዚያ ያለው ለም መሬት ተመንጥሮ፣ ለውጭ ሀገር ዜጎች መሬት እየተቸበቸበ ነው። አሥር ሺህ ሔክታር መሬት፣ ለሳዑዲዎች የሩዝ ምርት የተሰጠበትን ስምምነት የያዘ፣ በአቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመራው፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ ይፋ ያደረገውን እና በግብርና ሚኒስቴርና በሳዑዲዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት የያዘ የሚከተለውን ሰነድ እንመልከት፦ 

በዚህ ስምምነት መሰረት፣ 10 ሺህ ሔክታር የሚሆን መሬት ሳዑዲዎች ለ50 ዓመታት እንዲጠቀሙ ተሰጧቸዋል። አንድ ሔክታር ሁለት የእግር ካስ ሜዳን ያክላል። ለአንድ ሔክታር ወይንም ሁለት የእግር ኳስ ሜዳ፣ አምሳ ዓመት ተጠቅመው ሳዑዲዎች የሚከፍሉት 30 ብር ወይንም 1.7 ዶላር ብቻ ነው። በዓመት ሲሰላ 0.0348 የዶላር ሣንቲም (በኢትዮጵያ 60 ሣንቲም) በሔክታር ይሆናል። በሌላ መልኩ ሂሳቡን ላስቀምጠው። 57 የእግር ኳስ ሜዳ የሚሆን መሬት፣ ሳዑዲዎች አርሰው፣ ከዚያም የሚገኘውን ምርት ሰብስበውና ወደ ሀገራቸው ልከው፣ የሚከፍሉት፣ በዓመት አንድ ዶላር ብቻ ነው። እንግዲህ የሀገሬ ሕዝብ ፍረድ!!!!!!!

ለምንድን ነው ሳዑዲዎች ወገኖቻችንን በግፍ እያባረሩ፣ ኢትዮጵያ ለነርሱ ገነት የምትሆነው? ለምንድን ነው የሳዑዲ ኢንቨስተሮች ከሀገር እንዲለቁ የማይደረገው? ለምንድን ነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖም እንዳሉት ተመጣጣኝ እርምጃ ሳዑዲዎች ላይ የማይወሰደው? ለምንድን ነው በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍ እንደ ቀላል ነገር ተወስዶ ለማረሳሳት የሚሞከረው? ከላይ ባስቀመጥኩት አሳዛኝ ሁኔታ ለሳዑዲዎች የተሰጡ በርካታ መሬቶች ላይ፣ ከሳዑዲዎች በግፍ የተባረሩ ወገኖቻችን እንዲያርሱና እንዲያመርቱ በማድረግ፣ ሳዑዲዎች ወደ ጂዳና ሪያድ ለምን አይሸኙም? ወይስ አራት ኪሎ ያሉ ባለሥልጣናት፣ ለአንድ ሔክታር 0.03 ሣንቲም ብቻ በዓመት ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲገባ በመስማማት፣ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ፣ በአቋራጭ፣ በስማቸው ወይንም በዘመዶቻቸው ስም፣ ውጭ ወዳሉ የባንክ አካውንቶች ያዞሩ ይሆን? ለዚህስ ይሆን በሀገራችን ታሪክ ማንም አዋርዶን በማያወቅ ሁኔታ ያዋረዱንን ዐረቦች ላለማስቀየም ደፋ ቀና የሚባለው? ለዚህስ ይሆን ሕዝቡ ሳዑዲዎችን ለመቃወም ሰልፍ ሲወጣ "ፀረ-ዐረብ ስሜት ያለው ሰልፍ ነው" በሚል ዜጎቻችን የሚደበደቡት?

እንግዲህ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለምትኖረው ኢትዮጵያዊ ወገኔ ጥያቄ አለኝ። እስከመቼ ነው እንዲህ አይነቱን ግፍ የምንታገሰው? እስከመቼ ነው በሀገራችን፣ በተወለድንባት፣ በቀያችን የምንዋረደው? እስከመቼ ነው ዐረቦች በእጅ አዙር ቅኝ የሚገዙን? "አትነሳም ወይ? አትነሳም ወይ? የግፍ አገዛዝ አይበቃህም ወይ?" እንደተባለው መቼ ይሆን ይህን የግፍ አገዛዝ በቃን የምንለው? መቼ ይሆን እኛ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊያን የምንሆነው?

እንግዲህ ጊዜው አሁን ነው! ከዚህ የበለጠ ውርደት፣ ከዚህ የበለጠ የቁም ሞት የለም። በየቀበሌያችን እንደራጅ። እንነጋገር። በሀገራችን ጉዳይ ላይ እንምከር። አዎ! ጥቂት ለጥቅማቸው ያደሩ ሰላይ ካድሬዎች ይኖራሉ። የኛን መነሳት ሲያዩ እነርሱም ወደኛ ይመጣሉ። በየክልሉ፣ በየዞኑ፣ በየወረዳው ሁሉም መነጋገር ከጀመረ፣ ሁሉም መጠየቅ ከጀመረ፣ ሁሉም ቀና ካለ፣ ያኔ የዚህ ግፈኛ አገዛዝ መጨረሻ ይሆናል። በምንም ተዓምር ጥቂቶች ሰማኒያ ሚሊዮን የምንሆነውን ሊቆጣጠሩ አይችሉም። የነርሱ ጥንካሬ የኛ መፍራት ነውና ፍርሃትን አውልቀን እንነሳ! አሁን ካልተነሳን መቼ? እኛ ካልተነሳን ማን? ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ጥይት ሳንተኩስ፣ የሠለጠን እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ከኛ የተለየ ምናልባትም ኢሕአዴግን የሚደግፉትንም በማሳመን እና በማቀፍ፣ ተያይዘን የኢትዮጵያን ትንሳዔ ማወጅ እንችላለን።
ግርማ ካሳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ