እኔ አላውቅም ፈራሁ ጁሃር
ሄኖክ የሺጥላ
የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 483 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉ-አባ-ቦራ (Eloo The father of Holstein Friesian) ኢልባቡር ከተማ በሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ስኩዌር ሜትር ይዞታ ላይ ሥራውን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1993 ማከናወን የጀመረ ትልቅ የቢራ ማምረቻ ድርጅት ነው። ኢሊባቡር መልካም ምድራዊ አቀማመጡም ሆነ ምድራዊ ልምላሜው፣ እንደ በቆሎ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ የቅባት እህሎች፣ ማር፣ ከነ ቦራ ደሞ ወተት፣ ቅቤ እና ወዘተ የሚዘራባት፤ የሚታጨድባት፤ የሚቆረጥባት፤ የሚታለብባት ሀገር እንድትሆን አድርጉዋታል።
ኢሊባቡርን የጽሑፌ መንደርደሪያ አደረኩ እንጂ ዋናው ነጥቤ እሱ አይደለም። ዛሬ መናገር ወይም መጻፍ የፈለኩት ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲያሳይ ወኪል የሆነውን የበደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ (boycotting) በመላው ኢትዮጵያ ይደረግ ዘንድ አንዳንድ ግለሰቦች የጀመሩትን ነገር ሰምቼ፤ ለምን በደሌን፤ ለምን ቴዲን የሚል ጥያቄ ለሚጠይቁ፤ መልስ የሚመስለኝን ለመተየብ፤ ከተቻለም ለማሳየት መመኮር በመሻቴ ነው።
ቴዲ አፍሮ በቅርቡ በጋዜጣ ላይ ስለ አድዋ ድል በሰጠው አስተያየት የተቆጡ፤ የተቀየሙ ግለሰቦች፤ ቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው ብሎ ንጉሥ ምኒልክን፤ ከዛም በላይ የአድዋ ድልን በመዘከሩ የተበሳጩ የሕብረተሰብ አካሎች፤ ቴዲ አፍሮ ከዚህ ቀደም ጃ ያስተሰርያል ብሎ በመዝፈኑ ቂም የቁዋጠሩ ሰዎች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን በ1936 የኢጣልያንን የተለከለከለ የኬሚካል መሳሪያ መጠቀምን በመቃወማቸው፤ ኢትዮጵያን የዩናትድ ኔሽን አባል በማድረጋቸው፤ ቅራኔዎችን አብርደው ያፍሪካን ሕብረት በመመስረታቸው፤ ለነዚህ ጉልህ አስተዋጽኦቻቸው በመዝፈኑ፤ ለነዚህ ለተጠቀሱት መልካም ሥራቸው መታሰቢያ የጭንቅላቱ ውጤት የሆነውን ሙዚቃ በማበርከቱ፤ ቴዲ አፍሮ፤ አቀንቃኝ እና አዝማሪ፤ ገጣሚና ሰዓሊ፤ ሃያሲና ደራሲ፤ ፀሐፊ ተውኔቱና ብላታው፤ አፉን በለጎመበት ዘመን፤ በብዕሩ የታሪክ ጋሻ፤ በግጥሙ ለቆሰለ ታሪክ ማገገሚያ፤ በዘፈኖቹ (ከማሊ ሱፊዎች ባልተናነሰ መልኩ) የነብስን ክር እየተጫነ ያላስለቀሰው፤ ያላስተከዘው፤ ሰው እንደሌለ የገባቸው ሰዎች፤ በይበልጥም የአድዋ ድል፤ የጥቁር አንበሳዎች ድል መሆኑን ያሳየበት በመሆኑ እና ይህም የሚያማቸው ሰዎች፤ ዛሬ በደሌ ቢራ ቴዲ አፍሮን ስፖንሰር ስላደረገ፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ ጠርተዋል። አሁን ቴዲ አፍሮን አብዶ በረንዳ (የጫት ማከፋፈያ በረንዳ ነው) ቢሆን ስፖንሰር ያረገው ምን ሊሉ ነበር።። ባረገው እና የተከታዮቻቸውን መልስ ባየን። አንድ ጊዜ ቆይ ጠብቁኝ ሳቄ መጣብኝ ያለው ተናጋሪ ማን ነበር።
አዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም (ጥቁር ሰው) የብዙዎቹን እትዮጵያዊያኖች ድምፅ ያስገኘለትን ያህል፤ ንጉሥ ምኒልክ በድሎናል፤ ጡታችንን ቆርጦዋል፤ ወዘተ ወዘተርፈ ለሚሉት ደሞ፤ ከምኒልክ መፈጠር፤ ከታሪክ አንቀጽነቱና አኩሪ ገድሉ ጋር የጀመሩትን እጹብ ጸብ ውሃ የሚደፋበት በመሆኑ፤ ጠላት ሊያፈራበት እንደሚችል መገመት ብዙም አይዳግትም። እናም 'ነዚህ ሰዎች ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት አድማ እናድርግ እያሉ ነው። ልክ ናቸው፤ ህዝብ በጥላቻም በቢራም ሰክሮ እንዴት ይሆናል፤ ባንዱ ብቻ ይበቃልና።
በነገራችን ላይ ይህንን አድማ ለማስመታት ከሚራወጡት እና ከሚሯሯጡት ሰዎች መሃከል አንዱ ጁሃር መሐመድ መሆኑን ሰምቼ አፍሬ ጥፍሬ ውስጥ ልገባ ነበር። ባንድ ወቅት ይሄ ወጣት ፖለቲከኛ ስለ ራሱ ሲናገር "እኔ እናቴ መንዜና የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነች አባቴ ደሞ ኦሮሞና ሙስሊም ነው፤ ታዲያ ከኔ በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ምንነት አለ ወይ" ብሎ ነበር። መልሱ ሊሆን ይሚችለው ጁሃርዬ በውነትም የለም፤ እንዳንተው አቶ መለስም እኮ የተላቀቀ ነገርን ማጣበቅ የሚችል (ኡሁ የሆነ) (UHU ... glue) ደም ነበራቸው፤ ግን ደሙ ሳይሆን የደሙ ባህሪ ነው ወሳኙ ነገር። የተሸከምነው ደም ሳይሆን በውስጣችን ያፋፋነው ስብዕና ነው ማንነት፤ ማንነት ሥራ ነው እንጂ አንተ እንዳልከው የ-ኢ-ተጎራባች ዘር ደም ውህደት (ኬሚስትሪ ውጤት አይደለም)፤ ክርስቶስ (ኤሳው ... አለይሁ ሰላም) በ-በረት ተወለደ ብለን እናምናለን፤ ግን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በ-በረት መወለዱ ሳይሆን ሰው ሆኖ ሲኖር ያደረገውን ነገር ነው የምናስበው፤ ስለ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ.) አንድ ሙስሊም ሲያስብ ስለዘራቸው ሳይሆን ስለሥራቸው ነው የሚያስበው ብዬ አስባለሁ። ባንድ ወቅት ይሄው ሰው፤ ፹ ከ፻ የሚሆነው የሀገሬ እስላም ኦሮሞ ነው፤ እናም የኦሮሞ ህዝብን ኢምፓወር ማድረግ፤ እስልምናን ኢምፓወር እንደማረግ ነው አለን፤ ለመስማት አይደል የተፈጠርነው እናም ሰማነው፤ ባሜጃ አለን ዝም ብለን ሰማነው፤ ቀጥሎም ኢትዮጵያ አውቶ ኦፍ ኦሮሚያ አለን እሱንም ሰማነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ አውት ኦፍ ኦሮሚያን ወደ ፈርንጅኛ ስቀዳው (the child give birth of her mother) አይመስላችሁም? ለመተርጎም የተገደድኩት የመጀመሪያው ራሱ እንግሊዘኛ መሆኑን ስለ-ተጠራጠርኩ ነው። ለነገሩ ስታንፈርድና ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ እኮ መፈክር አያስተምሩም።
እና ዛሬ በደሌ መጣ እና ወንድሜ ጁሃር ሰማኒያ ከመቶ ካለው ሃሳብ ጋ ግንባር ለግንባር ተጋጨ (head on collusion) እናም ሁለት የሚጋጩ ነገሮችን እንግዲህ እናስተውላለን።
፩) መቼም ፹ ከመቶው እስላም ኦሮሞ ነው ብለኽን፤ አንተም በዘር ብቻ ሳይሆን በእምነትም ጭምር ጠበኽ፤ አልገባኝም ታዲያ እንዴት ነው፤ እነማን ቦይ ኮት እንዲያረጉልኽ ነው ጥሪውን ያቀረብከው፤ ፳ ፐርሰንቱ እስላም ያልሆነው ኦሮሞ? ደሞ ከ፹ ከመቶ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ውስጥም ቢሆን አዲስ የበደሌ አድመናኛ ማግኘት ይቸግራል ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም እነሱ ላንተ ሲሉ ሳይሆኑ ለዲናቸው ሲሉ ድሮም እንዲህ አይነቱን ነገር ይነኩት ነበር ብዬ አላስብም፤ በፍጽም አያደርጉትም። ታዲያ የማይጠጡ ሰዎችን ነው አድማ የጠራነው፤ ወይስ ሙሉ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ምሳሌ እንድትሆን ያደረገችህ የመንዜዋ እናትህን ዘመዶች፤ እኔ አላውቅም ፈራሁ ሄኖክ ነው ያለኝ የልጅነት ጉዋደኛዬ፤ ባንድ ትልቅ የውሃ ጉድጉዋድ ውስጥ እንሹለክ ስለው። እኔ አላውቅም ፈራሁ ጁሃር።
ዛሬ ጀርመን ያላትን ቅርጽ እንድትጠብቅ ወይም እንዲኖራት ያደረገው ኦቶ ቮን ቢስ ማርክ፤ የደም ትግል ውጤት ነው። ታዲያ ጀርመኖች በቢስ ማርክ ተናደው ፒሊሲነርን (የጀርመን ታዋቂ ቢራ ነው) ቦይ ኮት እናርግ አላሉም። በፈረንሣይ እንዲህ የሚባል ታሪክ አለ፤ በአሜሪካም፤ አረ ሆመር በጥንታዊያኖቹ የግሪክ ዘመን ስለነበረው ጦርነትም ጽፎዋል። ስለሥርዓቱ፤ ስለአገማምኖን እና የወንድሙ መንግሥት፤ ስለ ሄለናዊው ሥርዓት፤ ከዚያም በኋላ እነዳንቴ ስለጻፉት ስለዲቫይን ኮሜዲ፤ ፍሬድሪክ ዊልሃልም ኒቺ ስለተራቀቀበት የማኅበረሰብ ሥነልቦና፤ እነአልበርት ካሙ ስለጻፉለት የፈረንሣይ ማኅበረሰብ እና በየሥርዓቶቹ ውስጥ ስለነበረው ፍዳ፤ እነልዮ ቶሎስቶይ በሰላ ብዕራቸው ስለዘገቡት የሩሲያ የጭቆና ቦለቲካ፤ እነፓብሎ ፒካሶ ጉሬንሽያ ብለው ስለገለጹት የስፔን ከተማ ስለስንቱ ለዚህ ለወጣቱ ፖለቲከኛ እንንገረው?! እስኪ ባክህ ጁሃርዬ ገረፍ ገረፍ አርጋቸው፤ በቃ እንደውም ለዚህ ክረምት ለፐርሰናል ዲቨሎፕመንት ... ትመለከታቸው ዘንድ እጠይቅሃለሁ። (ማሳሰቢያ በአብዛኛው በአማራ ፀሐፊ አይደልም የተጻፉት፤ ቢሆኑም ደሞ አንተ አምሳ ፐርሰንት አማራ አይደለህ እንዴ? የምሬን እኮ ነው!)
በታሪክ ላይ ጥላሸት መቀባት በፍጹም ለማንም አይሳካም፤ ወደድንም ጠላንም፤ ጠቅልለን የምንጎርሰውን እንጀራ የፈጠሩት አባቶቻችን ናቸው፤ ለሆዳችን ያለን ቅርበት ለታሪካችንም ይኑረን። ቴዲ እንዳለው ክፉውን በክፉ ለመመለስ ማሰብ ሌላ ክፉነት ነው። ሁለቱ ደሞች እንደ ደም ይሰሩ፤ ያስቡ ዘንድ ሰው እንሁን።



