ሙሉጌታ አሻግሬ
ማኅበር እየደገሰች ዘመድ የምትሰበስበዋ አክስቴ 'ሀገር የጋራ ነው ኃይማኖት የግል ነው' ትላለች። ይህን አባባል ለአክስቴ መስጠቴ አይደለም ሙስና እንዳይሆንብኝ። ህዝቡ ሁሉ እንደዛ ይላል። አክስቴ ምን ታድርግ መስመርና አብዮት የተባሉ ሰው ሰራሽ ጭራቆች ወንድሞቿን በልተውባታል።

 

ይህ አባባል በፖለቲካ ምክንያት እሳት እና ጭድ የሆኑ ቀሪ ዘመዶቿ የተለመደውን ንትርክ እንዳይጀምሩ የምትጠቀምበት ዘዴ ነው። እኔ ግን ስተረጉመው 'ዝምድና የጋራ ነው ፖለቲካ የግል ነው' ማለቷ ነበር። በአክስቴ እምነት ፖለቲካ ጥሩ አይደለም። ሞት ያስከትላል።

ግን ኃይማኖትና ፖለቲካ እውነት ለየቅል ናቸው? ይህን አስተያየት ለመፃፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ጀባ ያለኝ የስብከት ሊንክ ነው። ምንም እንኳን እንደአባባሉ ኃይማኖት የግል ሀገር የጋራ ቢሆንም የወያኔ ገዥ ቡድን ሀገርም የእነርሱ፤ ኃይማኖትም የእነርሱ እንደሆነ ህቅ እስኪለን ድረስ አሳይተውናል።


የእስልምና መሪዎች ሹመት በቀበሌ ምርጫ ካልሆነ ምኑን ኃይማኖት ሆነው ሊሉን ዳርዳር ያሉ የወያኔ ካድሬዎችን ታዝበናል። ማንን ፈርተው እንደተዉት ባይታወቅም 'የመጅሊስ ተመራጮች ምርጫ ቦርድ መመዝገብ አለባቸው' የሚል የደደቢት ቀጭን ትዕዛዝ ይተላለፋል ብዬም ጠብቄ ነበር። ኦርቶዶክሱንም ቢሆን ያልተመቻቸውን ሽረው፣ የተመቻቸውን ሾመው፣ ኽረ ወግ እየተናደ ነው ብለው ቅሬታ ያሰሙ አባቶችን ደብድበውና አስደብድበው ሲኖዶሱ የእነሱን መስመር የሚከተል እንዲሆን ሰርተዋል። በአደባባይ በመውጣት ሚዲያ በመጠቀምም የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰብረናል ብለዋል። ስለዚህ ፖለቲካ ከእኛ በላይ ለአሳር ያሉት የወያኔ ገዥ ቡድን አባላት ይህን ካደረጉ እና ከተናገሩ፤ የእኔ የተራው ዜጋ ሁለት መስመር አስተያየት ኃይማኖት እና ፖለቲካን እንደማታቀላቅል እጅግ እርግጠኛ ነኝ።

ስብከቱ ከአንድ ሰዓት በላይ ነው። ትዕግስቴ አፍንጫዬ ላይ እንደሆነ የሚያውቀው ወዳጄ ግን አደራ ጨርሰህ እንድትሰማው ብሎ መክሮኝ ነበር፤ አይገርምም አንዴ አይደለም ደግሜ ሰማሁት። በዚህ አስተያየት ውስጥ የኃይማኖት ክፍሉን ለኃይማኖቱ ተከታዮች በመተው ወቅታዊ የሀገሪቱን ችግር የተመለከተውን ብቻ ለማሳየት እሞክራለሁ። የሰባኪውን ማንነትም ሆነ የኃይማኖትን ጉዳዮች ሳልነካካ ማለት ነው። የወዳጄም ትልቁ ፍላጎት ይህ ነው።

ሰባኪው ይናገራል። በጥንቱ መጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ የኢትዮጵያን የዛሬ መከራ እና ችግር ይተረትረዋል። ወጣትነት፣ ስደት፣ ሙስና፣ አድልዎ፣ ተጠያቂነት ምንም አልቀረውም። ሰባኪው የቤተክርስትያኗን አንደበት የሸበበውን በረዶ ሰብሮታል። ልክ 'ICE Breaker' እንደሚባለው ማለት ነው። ይህ መጀመሪያው ነው፤ አምናለሁ በርካቶች ሊከተሉ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። አሸባሪ ተብሎ ክስ ካልተመዘዘበት በቀር። ግን ደጋግሞ 'መናገር ካለብኝ እናገራለሁ፣ አልፈራም' ይላል ሰባኪው።

ወያኔ ድሮም በኃይማኖት ጣልቃ የመግባት ምስጢር መንግሥተ ሰማያት አሊያም ጀነት የመግባት ፍላጎት አሳስቦት አይደለም። ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ያውቀዋል። ኢትዮጵያዊው በኃይማኖቱ ሥነምግባርን ብቻ ሳይሆን መስዋዕትነትም የተማረ ህዝብ ነው። ስለዚህ ወያኔ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ትላልቅ የሚባሉ ኃይማኖቶችን ወደራሱ መንገድ መጠምዘዝ ነበረበት። ህዝቡ የኃይማኖት አባቶችን፣ የእምነት ተቋማቱን ያዳምጣል። ከልቡ። ስለዚህ ወያኔ በዚያ በኩል ሊመጣ የሚችለውን 'የሥልጣን አደጋ' ለመከላከል የዘየደው ዘዴ የኃይማኖት ቁንጮዎችን ማወየን አሊያም መቆጣጠር ነበር።

እንደስብከቱ ግን ኃይማኖትን በአግባቡ ለማምለክ ሀገርና ማንነት ያስፈልጋል የሚል ግልጽ መልዕክት ተላልፏል። አትዝረፉ። ኽረ ሙስና ይብቃ። ተጠያቂነት ወዴት ነሽ? እያለ ሰባኪው ይጠይቃል። በቃ፣ በቃ፣ ይበቃል። ይላል ሰባኪው። ወያኔዎች በዚህ መልኩ ከተረዱት ትምህርት ይወስዳሉ። እራሳቸውንም ከጥፋት መልሰው ህዝቡን ማዳመጥ ይጀምራሉ። ይህን መልዕክት የትምክህተኞች እና ያለፈ ሥርዓት ናፋቂዎች ነው ብለው የተለመደውን ነጠላ ዜማ ከለቀቁ ግን ከእግራቸው ስር ያለው መሬት እየተሰነጠቀ መሆኑን ለመረዳት እንደረፈደባቸው ያሳያል።

ህዝቡ በኃይማኖት በኩል ማጉረምረም ከጀመረ ... ኦሮማይ።

ሰባኪው በክሊፑ ከ18፡00 እስከ 19፡15 ደቂቃ ላይ ስደትን እየነገረን ለሚደርሰው ግፍ እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ተጠያቂ የለም ይለናል። ከ28፡33 እስከ 29፡35 ስለ ኢትዮጵያውያኖች ጀግኖች፤ ስላልተዘመረላቸው የኢትዮጵያ እንቁ ጀግኖች ይጠይቃል። ይናገራል። የእኛ ጀግኖች ብዙ እንደሠሩ ግን እንደተደበቁ ያስታውሰናል።

ከ42፡20 ጀምሮ ስለ ኢትዮጵያ ጥቁር ህዝብ ማንነት ይናገራል። የኦርቶዶክስን አከርካሪ መስበር ኢትዮጵያን ለመስበር መሞከር እንደሆነ በማስረጃ ይተነትናል። ቤተክርስቲያኗ ትምህርት ቤት፣ የሕክምና ቤት፣ የፍርድ ቤት እንደነበረች ይነግረናል። አከርካሪዋ መሰበር ሳይሆን መመስገን ይገባታል ይለናል።

ከ46፡50 ጀምሮ ስለ ሞራል፣ ስለ ሀገር ተረካቢነት ይጠይቃል። ሙስና ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት መንደሯን በስፋት እንደሠራች በግልጽ ይነግረናል። ህዝቡን እርስ በእርስ የማበላላት ፕሮግራም የኢትዮጵያን የወደፊት ማንነት ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ በመጠየቅ፤ መብላት እና መበላላት መወገድ አለበት ይላል። አጽንኦት በመስጠት።

ከ58፡30 ጀምሮ ሰባኪው ይመለስና ወደማንነታችን እንመለስ ይለናል። ወደ እውነት እንምጣ ይለናል። እምቢ፣ እምቢ እንበል ይለናል፤ ኢትዮጵያውያኖች ነንና። ኢትዮጵያውያኖች ነንና ነውር የሆነውን ትተን ወደክብራችን እንመለስ ይለናል።

ከ1፡00፡50 ጀምሮ ስለነፃነት አባቶች፣ ከባርነት ላወጡን አርበኞች ክብርና ምስጋናውን ያቀርባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
ሙሉጌታ አሻግሬ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!