ይድነቃቸው ከበደ Yedenekachew Kebedeይድነቃቸው ከበደ

"ሕዝቡ እኔ ማን እንደሆንሁ ይላል?" በማለት እየሱስ ክርስቶስ መረጃ ይጠይቃል፤ ደቀመዛምርቶችም ስለሱ የተባለውን አንድም ሳያስቀሩ ይነግሩታል። እሱም መልሱ እንዲህ ይላቸዋል "እናንተስ እኔ ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?" አላቸው። እነሱም መለሱለት። ሙሉ ታሪኩ ሉቃስ ም.9 ቁ.18 ላይ ይገኛል።

 

መረጃ አይናቅም አይደነቅም ማለት እንዲህ ነው። በመሰረቱ ክርስቶስ ሰዎች ስለሱ ምን እንዳሉ ብቻ ሳይሆን ምን እያሰብ እንደነበር የሚያውቅ አምላክ ነው። ግን መጠየቅ እና መመለስ ሃሳብን መግለጽ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ለዚህም ነው ክርስቶ እንደሰው በምድር በተመላለሰበት ወቅት መረጃ ይጠይቅ የነበረው፤ እሱም ስለራሱ መረጃ ይሰጥ የነበረው። እርግጥ ነው ክርስቶስ ይህን ሲጠይቅ የራሱ ምክንያት አለው።

በመሆኑም ሃሳብ መግለጽ ተፍጥራዊ መብት ነው ወደሚለው ዓለም አቀፍ ስምምነት በመደረሱ የመናገር ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት የዲሞክራሲ ዋና የድም ስር ነው የተባለው። ስለዚህም ተሰባስቦ መቃወም እንዲሁም መደገፍ፣ አንድ ሰው የሚመስለውን ሃሳብ በፈለገው መንገድ መግለጽ፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ መንግሥትን የመተቸት፣ በራስ ፍቃድ የመናገር እና ያለመናገር፣ በዓልንና ኃይማኖትን መከተልና ማስፋፋት፣ እንዲሁም ሕግ ለሁሉም የሚሠራ ስለመሆኑ መረጋገጥ እና የመሳሰሉት ሁሉ ተግባራዊ የሚሆነው ተአቅቦ ያልተደረገበት የመናገርና የመረጃ መብት ልውውጥ ተግባሪዊ ሲሆን ብቻ ነው።

ለመደርደሪያነት የዚህን ያኸል ከተባለ ወደ ዋናው ጉዳይ አስፈቅደን ሳይሆን ፈቅደን እንገባለን። ያነሳነው ሃሳብ "መረጃ" እንደመሆኑ መጠን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ተፍጥሯዊ መብታችን በፈለግነውና በፈቀድነው መንገድ እንገልፃለን። እኛ ስል ለመረጃ ነፃነት የቆምነው ሁላችንም ማለቴ ነው።

ሰው በመናገሩ እና በመፃፉ ብቻ ለእስር እና ለስደት የሚዳረግበት ሀገር በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ነገር ግን "ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የመግለጽ ነፃነት አለው"፤ የሚለው በኢትዮጵያ ሕገመንግሥቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል። በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በሕገመንግሥቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን፤ ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በሕገመንግሥቱ ተገልፆ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ሃሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ደረጃ ላይ ይገኛል። አልፎ ተርፎ በአስተሳሰብ ወይም በአመለካከት ላይ ተፅዕኖ እስከመፍጠር ተደርሷል። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ለሕግም ሆነ ለሞራል ተቃራኒ እንደመሆኑ መጠን የፈጀውን ፈጅቶ ወደነበረበት መመለሱ የማይቀር ሐቅ ነው። ነፃ ሃሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መጽሔቶች ምን ያህል አሉ? ያሉት ጋዜጦች እና መጽሔቶች እየደረሰባቸው ያለው ማስፈራሪያና ዛቻ ደረጃው ምን ያኽል ደርሷል የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አክራሪነትና ፅፈኝነት የሚያበረታቱና የሚያሰራጩ በማለት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለህዝቡ ተገቢውን መረጃ እያስተላለፉ ያሉ የሕትመት ውጤቶችን ከገበያ ለማውጣትና ፈርጆ ለመክሰስ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ሌላው ማሳያ ነው። ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣ በማሰር እና እንዲሰደዱ በማድረግ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በሁለተኝነት ደረጃ ላይ ትገኛለች። መንግሥትን ተችቶ የፃፈና ጽሑፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መጽሔት ጨምሮ ሁሉም ለእስር የሚዳረግበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዜጎች የሚኖሩት ግልፅ በሆነ የሃሳብ ልውውጥ ነው። የትኛውም አይነት ሃሳብ ከማንም ሊመጣ ይችላል፤ ቁም ነገሩ መሆን ያለበት የሚመጣው ሃሳብ የሚመከተው በምንድነው የሚለው ነው። ለነፃ ንግግር ችግር የተሻለው መንገድ የበለጠ ነፃ ንግግር ነው፤ በመናገር መብት ላይ የሚደረግ ማናቸውም ተፅዕኖ ሲውል ሲያድር በእያንዳንዱ ግለሰብ የመናገር መብት ላይ ስጋት ሊያስከትል ይችላል። ለዚህም ነው ወደነበረበት መመለሱ የማይቀር ነው ለማለት የሚያስደፍረው። ምክንያቱ ደግሞ ማንም ሰው በስጋት ውስጥ መኖርን ስለማይፈልግ ነው።

በመሆኑም በሀገራችን እየከሰመ ያለው ሃሳብን በነፃ የመግልጽ እና መረጃ የማግኘት መብት በገዥው መንግሥት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረት ወደመሆን ደረጃ ተሸጋግሯል። ለዚህም እንደማሳያ ከሰሞኑ የህዝብ ሳይሆን የገዥው መንግሥት አንደበት በሆነው በኢቲቪ በተላለፈው የዘጋቢ ፊልም ግለሰቦችም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ ለኢሳት መረጃ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ምክር መሰል ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

ለዚህም እንደምክንያት የቀረበው ኢሳት የተባለው የመገናኛ ብዙኀን በሽብርተኛ ድርጅት የሚደገፍ ነው የሚል ምክንያት ነው። ኢቲቪ በኢህአዴግ እንደሚደገፍ ሁሉ ኢሳት በማንም ሊደገፍ ይችላል፤ ቁም ነገር ሆኖ መታየት ያለበት ኢቲቪም ሆነ ኢሳት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው። በተጨማሪ መልዕክቱ ለሕግም ሆነ ለሞራል ምን ያኽል ተቃራኒ ነው የሚለው ነው። በተጨማሪም ኢቲቪ እንዲሁም ኢሳት በሕግ መደመጥ እንዲሁም መሰማት የተከለከሉ የመገናኛ ብዙኀን ናቸው ወይ ተብሎ መጠየቅና መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ሃሳቦች ናቸው። ይሁን እንጂ ወደ መልሱ ስናመራ ኢቲቪ እንዲሁም ኢሳት በሕግ የተከለኩ አይደሉም፤ ዋንኛው እና አስፈላጊው ነገር ይሄ ነው ሌላው የሕጉ ደጋፊ ሃሳብ ነው።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ የሕግ ጉዳይ ሳይሆን የፍላጎት ምርጫ ነው የሚሆነው። የፈለጉትን መስማት እና ማዳመጥ እንዲሁም በፈለጉት የመገናኛ ብዙኀን መንገድ ሃሳብን መግለጽ እና መረጃን ማግኘት ግለሰብ ከሆነ እንደግለሰቡ፣ ተቋም እንደተቋም እንዲሁም ፓርቲ እንደ ፓርቲ የመምረጥ የራስ መብት ነው። ይህ ደግሞ አንዱ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው። በዚህም መሠረት ከኢቲቪ ኢሳት፣ ከአዲስ ዘመን አዲስ አድማስ የዘወትር ፍላጎታቸው ለሆነ፤ እንዲሁም በተመሳሳይ ከኢሳት ኢቲቪ፣ ከአዲስ አድማስ አዲስ ዘመን ለመረጡ ምርጫቸውን ማክበረ ነው።

ሌላው እና አሳሳቢ ሊሆን የሚገባው ሰው የመረጠውን መስማትና ማዳመጥ እንዲሁም ማንበብ መብቱ እንደጠጠበቀ ሆኖ፤ ግለሰበ ወይም ተቋም ሃሳቡን እንዴት የመግለጽ መብት እና ግዴታ አለበት የሚለው ነው። ይህን በተመለከተ ተቋም ወይም ግለሰብ ሃሳብን ወይም መረጃን በማንኛውም መንገድ የመግለጽ ሙሉ መብት በሕግ የተጠበቀ ነው። እንዲኹም የዚህ መብት ተቃራኒ የሆኑ ማናቸውም ነገሮች ተቀባይነት እንደሌላቸው በሕገመንግሥቱ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህም መሰረት በኢሳት ሆነ በማናቸውም የመገናኛ ብዙኀን ሃሳብን መግለጽ እና መረጃን መስጠጥ በራሱ ወንጀል ወይም ጥፋት አይደለም፤ ይህ የሆነው ደግሞ መብት ከመሆኑ አንፃር ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሃሳብን በመግለጽ እና መረጃን በመስጠት ዙሪያ ግዴታ ሊያመጣ የሚችለው ምንድነው የሚለው ነው። ግለሰቡ ወይንም ተቋሙ በግልጽ በሕግ የተከለከለ መረጃ ወይም ሃሳብ የገለፀ እንደሆነ ግዴታው ተጠያቂነትን ስለሚያመጣ በሕጉ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል። ይህ የሕግ ተጠያቂነት አድሏዊነት የሌለበት፣ ለሁሉም በሁሉም ቦታ እኩል የሚሠራ ነው። ይህም ማለት በሕግ የሚያስጠይቅ ንግግር በኢሳትም ሆነ በኢቲቪ እንዲሁም በቢቢሲ ያደረገ በሕግ ከመጠየቅ ንግግር ያደረገበት የብዙኀን መገኛኛ ሊታደገው አይችልም እንደማለት ነው።

በመሆኑም በኢሳት ሃሳብን መግለጽ እንዲሁም መረጃ መስጠት አልፈልግም ማለት መብት ነው። ነገር ግን በኢሳት ሃሳባችሁን አትግለፁ፣ መረጃም አትስጡ ማለት ከፍላጎት የመነጨ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የለየለት የእብሪት ተግባር ነው። እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ምኞት እና ተግባር የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፤ ተምሮ ያለመለወጥ ልክፍትም ጭምር ነው! በተለይ በመንግሥት ደረጃ ሲታሰብ እጅግ በጣም ያሳፍራል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ