የኢዴአፓ የቀውስ ፖለቲካ (ቃልኪዳን አምባቸው)
ቃልኪዳን አምባቸው
ኢዴአፓ-መድኅን በቀውስ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቁን የሚያሳዩ በቂ አስረጂዎች አሉ። ፓርቲው ውሉ ጠፍቶበታል። በአንድ በኩል የገዥው ፓርቲ ዕድገት አብሳሪ መሆንን ይሻል። የኢህአዴግን መጠንከር፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት፣ በመጪው ምርጫ አሸናፊ እንደሚሆንና ሌሎችንም የምንሰማው ከኢህአዴግ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሳይሆን ከኢዴአፓ-መድኅን የፓርቲዎች የግምገማና የልኬት ቤተ-ሙከራ ነው። ኢዴአፓ-መድኅን ይህን ቢያደርግ በእርግጥ ከልካይ የለበትም።
በአንፃሩ ደግሞ ተቃዋሚዎች መፍረክረካቸውን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አወንታዊ ሚና መጫወት የሚችል የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ያለመኖሩን፣ ተቃዋሚዎች በመጪው ምርጫ ሊያሸንፉ እንደማይችሉም ሆነ በደፈናው የተቃዋሚዎችን ጉድለትና ድክመት፣ በመራር መግለጫዎች ሲያዥጎደጉድ የምንሠማው ራሱን የተቃዋሚዎች እንደራሴ አድርጎ ከሾመው ኢዴአፓ-መድኅን ነው። ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ፓርቲው ውሉ ጠፍቶበታል የሚያሰኘው።
የኢዴአፓ-መድኅን የቀውስ መዘውር በዚህ ብቻ አይገደብም፤ በኢዴአፓ-መድኅን የልኬት ቤተ-ሙከራ የተገመገመው የኢትዮጵያ ህዝብም ”አሉታዊ ሚና …” ያለው በሚል ተፈርጇል። ”ሕገ-መንግሥቱ በብዙ መልኩ ጥሩ ሆኖ ተገኝቷል …” የሚለው የኢዴአፓ-መድኅን የምርምርና የጥናት ግምገማ በአንድ ጉዳይ ላይ ግን ያብጠለጥለዋል፤ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሥልጣን ገደብ ወይም ለምን ያህል ጊዜ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደሚችሉ መወሰን ነበረበት ይለናል። ከኢዴአፓ-መድኅን የመሪነት ዙፋን ነቅነቅ ማለትን ለማይደፍሩት ለአቶ ልደቱ አያሌው፣ ፓርቲው መላ መምታት እንዳለበት ግን ግምገማው አልተወያየበትም። በእርግጥ ኋላ ላይ ፓርቲው ለተዘፈቀበት የቀውስ ፓለቲካ ዋነኛው ምክንያት የከፊል አመራሮቹ ግላዊ ቀውስ መሆኑን የምንሞግተው ቢሆንም፤ አቶ ልደቱ ”ሥልጣን ይልቀቁ” ማለትን እንጂ ሥልጣን ልልቀቅ የማይሉ የአሮጌው ሥርዓት አራማጅ እንጂ የለውጥ ሐዋርያ አለመሆናቸውን መገንዘብ ብዙ አይቸግርም።
የኢዴአፓ-መድኅን አመራሮች በፓርቲው ላይ አስተያየት የሚጽፍ ጋዜጠኛ፣ የፓርቲው ተቀናቃኝ አድርገው መፈረጃቸው የተለመደና የዚሁ የቀውስ ፖለቲካ ውጤት በመሆኑ ባይደንቅም፣ የኢዴአፓን የቀውስ ፖለቲካ መዘውሮች አብጠርጥረን ለመመልከት እንሞክር። አመራሩ እንደሚሉት ጥላቻ ሳይሆን፣ ፓርቲው ቀድሞ ወደነበረበት አወንታዊ ሚና መመለስ እንዲችል እንዲሁም አሁን ፓርቲው የሚያወጣቸውን አፍራሽ መግለጫዎች መልሶ እንዲቃኝና ሌሎች ወጣት አባላት ፓርቲያቸውን እንዲፈትሹ አስተያየት ለማጋራት ነው።
ተቃዋሚዎችን የመቃወም አባዜ
ኢዴአፓ-መድኅን ተቃዋሚዎችን በጅምላ ይወርፋል። የተቃዋሚዎችን ደካማነትና ውድቀት ይለፍፋል፤ ለምን? አንድ የኢዴአፓ-መድኅን አመራር በዚሁ ድረ ገጽ ተቃዋሚዎችን የመገምገም ኃላፊነት አለብን የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። በተቃዋሚዎች ላይ ጥላቻ መቀስቀስ ይቻላል ወይ? በተለያዩ ጋዜጦች በተለይም የአቶ ልደቱን የፓርቲ ስም ነጥለው እየጠሩ፣ በማንአለብኝነት የፓርቲ አመራሮችን ስም እየጠቀሱ በማናናቅ መናገርና በጅምላ ተቃዋሚዎችን ደካማ ናቸው፣ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም፣ በመጪው ምርጫ ተቃዋሚዎች ሊያሸንፉ አይችሉም የሚሉ መግለጫዎችን ማዥጐድጎድ እንደምን ጥላቻ አይሆንም?
ለምርጫ ውድድር የሚፎካከር ተቃዋሚ ፓርቲን፣ እንደምን ሌላኛው ተፎካካሪው ደካማ ነው፣ ምርጫውን ማሸነፍ አይችልም እያለ በየሣምንቱ በፖለቲካ ግምገማ መንፈስ ጥላቻ ሊቀሰቅስበት ይችላል? የኢዴአፓ-መድኅን ተቃዋሚዎችን የማጥላላት ስትራቴጂ፣ ራሱን እንደ አንድ ተቃዋሚ ወይም እንደ ፓርቲ ድክመቱን አብጠርጥሮ ላለማውጣት የሚሸፍንበት ስልት አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። አመራሮቹ እንደ አመራር ፓርቲው ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ ምን ላይ አድርሰውታል? ፓርቲው በአባላት ቁጥር፣ ደጋፊዎችን በማበራከት ደረጃ፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት የፖለቲካ ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ ረገድም ሆነ ከኅብረተሰቡ ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠር ያለውን ራዕይ በማጋራት በኩል ምን ተግባር አከናውኗል? የተቀባይነት እና ተፅዕኖ የማሳደር አድማሱ በምን ያህል ካለፉት አራት ዓመታት አድጓል? የሚሉትንና ሌሎችንም መሠረታዊ ጉዳዮች በጥልቀት ፈትሾ፣ ያለበትን የአመራር ችግርም ሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም የመገምገም ሥራ ላለማከናወን፣ በጅምላ በተቃዋሚዎች ጀርባ ላይ አርባ ጅራፍ ያሳርፋል።
አለፍም ሲል ህዝቡ አሉታዊ በመሆኑ ወይም ተቃዋሚዎችን የሚያበረታታም ሆነ ገንቢ ሚና የሚጫወት ባለመሆኑ፣ የተቃዋሚዎች ፖለቲካ መቀዛቀዙን ያላክካል። ህዝብን መውቀስ አይቻልም፤ ህዝብንም መገምገም አያስኬድም፤ በጅምላ የተወናበደ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ካልሆነ ኢዴአፓ በምን መሥፈርት ህዝቡን ሊገመግም ይችላል? በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህዝብን እንዴት ተሳስተሃል፣ መሳሳትህን ደግሞ በእኛ ግምገማ ውጤት ነው ሊሉት ይችላሉ? ይህም ፓርቲው ራሱን በህዝብ ውስጥ ምን ያህል ስር መስደድ፣ አለመስደዱን ከመለካት ይልቅ ራስን የመደለል ተግባር ውስጥ እንደተዘፈቀ አመልካች ነው።
ኢዴአፓ የተቃዋሚዎችን ድክመትና ጥርጣሬ ማወቄ፣ ራሴን ለመለካት እንደ ውስጥ መረጃ እገለገልበታለሁ ቢል እንኳ፣ በየጋዜጣው የውረፋ መግለጫ ለማውጣት ሊገለገልበት አይችልም። ህዝብንም መፈረጅ ሆነ መውቀስ ኢዴአፓን የወረቀት ነብር ከማድረግ ውጪ ለምርጫ ኮሮጆ ፋይዳ አይኖረውም። ተያይዞ የመውረድ ቀቢፀ ተስፋም፣ የዳበረና የበሰለ የፖለቲካ ባህልን የሚያቆረቁዝ በመሆኑ ሊመከት ይገባል።
ህዝብ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ ዓለምን ባስደመመ ሥልጡን የፖለቲካ ንቃተ ኅሊና በነቂስ ወጥቶ ምርጫ አካሂዷል። ለዚህ ደግሞ የወረዳ 21ን ህዝብ የሞቀ ተሣትፎ እንደ አብነት እናንሳና ቢያንስ አቶ ልደቱ የህዝብን ተሣትፎ ”አሉታዊ” በሚል ድምዳሜ ሊፈርጁት አይገባም። ፓርላማ ላለመግባት ሲወስን ውሳኔውን ያለ ተቃውሞ ካፀደቁትና ውሳኔውን ካስተላለፉት አንዱ ራሳቸው አቶ ልደቱ ናቸው። ኢዴአፓም እንደ ፓርቲ የዕለቱን ውሳኔ አልቀበልም ብሎ፣ ዕለቱን አቋሙን የገለፀበት መድረክ የለም። ህዝቡን ጨለምተኛ የሚያደርገው እምን ላይ ነው?
ህዝብን ተሳስተሃል የሚለው ማን ነው?
“ህዝብን ተሳስተሃል የሚለው ማን ነው?” ለሚለው የዶለደመ ምላሽ ሰጥተው ለማለፍ የሞከሩት የኢዴአፓ አመራር፣ ከምን መነሻ ተሳስተሃል ሊባል እንደሚችል (Reference) አንፃር ሊነግሩን አልቻሉም። የአሜሪካ መንግሥት እንኳ ይገመግማል ኢዴአፓ ቢገመግም ምን ይደንቃል የሚለው አስተያየትም በራሱ የዘቀጠ አስተሳሰብ ውጤት ነው። የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ህዝብ ሊገመግም አይችልም። የአሜሪካ መንግሥት ከምርጫ ታዛቢዎች አስተያየት ተነስቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባለው የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ግንኙነት ዙሪያ አቋም ላይዝ ይችላል። እሱም አቋሙ ለራሱ እንጂ ለሉዓላዊቷ ሀገር ህዝብ አይደለም። ኢዴአፓ ህዝቡን ገምግሞ አሉታዊ ከሆነበት የሚወስደው እርምጃ ምንድነው? ህዝቡን አትምረጠኝ የሚል ውሳኔ ማሳለፍ ወይንስ በግርድፍ መግለጫ ማውጣት?
የአመራሮች የግል ቀውስና የኢዴአፓ የማጥላላት ፓለቲካ
በኢዴአፓ-መድኅን ፓርቲ የሚወጡ መግለጫዎችም ሆኑ አቋሞች፣ ከአመራሮቹ የግል አቋም ጋር የተደበላለቁ ሆነው ይታያሉ። የኢዴአፓ-መድኅን ወይንስ የአቶ ልደቱ? የአቶ ሙሼ ሰሙ ወይንስ የአቶ አብዱርሃማን የፖለቲካ አቋም ነው? የሚለውን ከፓርቲው አቋም ጋር ነጥሎ ማየት እያዳገት ነው። ይሄ ደግሞ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ከ”አረም እርሻ መጽሐፍ” አንስቶ አመራሮቹ እያመሳቀሉ የሚጠቀሙበት የተዛባ የፖለቲካ አካሄድ ነው።
የአመራሮቹ ተቀባይነት አጥተናል የሚል ሥጋት፣ ፓርቲው እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ በነደፈው አማራጭ ፖሊሲ ላይ ጥላ የሚያጠላ መሆን የለበትም። የግል ቀውስ በግለሰቡ የሚፈታ እንጂ ይዘነው የምንቀርበውን የፖለቲካ ፕሮግራም ህዝቡ አይዋጥለትም በሚል ድምዳሜ መቅጨት አግባብ አይሆንም። የግል ተቀባይነት የማጣት ሥጋትን ተንተርሶ ሁሉንም የማጥላላት አጀንዳን የፓርቲ አቋም ተደርጐ እንዲወስድ ጫና ማሳደርን ፓርቲው ሊያከሽፈው ይገባል። ሁሉንም እንደ አፍራሽ መመልከት ጤናማ አካሄድ አይደለም። የዚህ ዓይነቱ የግል የተቃወሰ አስተሳሰብ፣ በፓርቲው አጀንዳ ሆኖ ፓርቲው ሁሉን እያጥላላና እንደ አደናቃፊ እየተመለከተ ከተጓዘ የኋሊት እንጂ ወደፊት መራመድ አይቻልም።
የፓርቲው አባላት ፓርቲያቸውን የማጠናከር ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል። ኢዴአፓ-መድኅን እንደ ቀድሞው አወንታዊ ሚና የሚጫወት እንጂ የማውገዝ መግለጫ የማስተላለፍ አካሄድን መስበር ያስፈልጋል። ኢዴአፓ እንደምን በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት ይችላል? ኅብረተሰቡ ዘንድ ስር ለመስደድና የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ለማስተዋወቅ ምን፣ ምን ሥራዎች መሥራት አለብን? የህዝቡን ችግር የሚፈቱና ውጤታማ የሚያደርጉ ምን ዓይነት አማራጭ ፖሊሲዎችን መቅረጽ አለብን የሚል እውነተኛ ግምገማ በኢዴአፓ-መድኅን አባላት መደረግ አለበት።
”በስህተት ከመወደድ እውነተኛ ሆኖ መጠላት” ከሚል ትርጉም አልባ መፈክር፣ ህዝብን ያሳተፈ አሠራር ለመቀየስና ፓርቲውን ወደፊት የሚያራምዱ አመራሮችን የመሰየም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ወሳኙ የኢዴአፓ-መድኅን አባላት ናቸው። ተቃዋሚዎችን የሚያከብር፣ ገዥውን ፓርቲ የሚያከብር፣ ህዝብን ከፍ አድርጐ የሚያይ ጤናማ አካሄድ ለመከተል፣ አባላቱ አጀንዳውን የራሳቸው የማድረግ እንጂ የማጥላላት አታሞ መደለቂያ እንዲሆን ከመፍቀድ መታቀብ ይገባል።