ወያኔ መሞቻውን፤ እኛ መሰንበቻውን
ይገረም አለሙ
"ወያኔ የራሱን መቃብር እየቆፈረ ሞቱን ሲያፋጥን፤ ተቃዋሚዎች ገንገንዘው ሳጥን ለመክተትም ሆነ ከቀብር ስፍራ አድርሰው አፈር ለመመለስ የሚችሉ አልሆኑም"
እኔ ከምኑም የለሁበት ተቀዋሚም ደጋፊም አይደለሁም በሚል ጭንብል ተሸፍኖ የሚኖረው ክፍል ሲቀር ሌላው በሁለቱ ጎራ ይመደባል። በወያኔ ጎራ ያለው ወገን ለአባልነትም ይሁን ለደጋፊነት ያበቃው ምክንያት ምንም ይሁን ባለው አቅም በሚችለው መንገድ የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም ያስችላል ብሎ ያመነበትን ይሠራል። እንደውም አንዳንዱ ያለ ወያኔ መኖር እንደማይቻል ራሱን አሳምኖ ሞቴን ከወያኔ ጋራ ያለ ነው የሚመስለው። በዚህ ጎራ የተሰለፉ ሰዎች ሆነ ብለው አቅደው ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ናፍቀው የወያኔን ዕድሜ በሚያሳጥር ተግባር ላይ አይሰማሩም። የውስጥ አርበኞች ካልሆኑ በስተቀር።
በአንጻሩ በተቃውሞው ጎራ ያለው ወገን ለተቀዋሚነት የበቃበት ምክንያትና እንዴትነት የመለያየቱን ያህል ተግባሩም የዛኑ ያህል የተለያየ ነው። ይህም በመሆኑ መቋሰል መጓተቱን፤ መወነጃጀል ጣት መቀሳሰሩን ወደ ጎን አስቀምጦ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ለወያኔ ዕድሜ ማጠር መሥራት አልቻለም። ይህም በመሆኑ ወያኔ በጥንካሬው ሳይሆን በድክመቱ፣ በእውኑ ሳይሆን በሙቱ ሲገዛ ኖሯል፤ አሁንም እየገዛ ነው ምን አልባትም ወደፊትም! (መበስበሳቸውን ከነገሩን በኋላ በእኛ ድክመት ሕይወት ዘርተው ስንት ዓመት ገዙን?)
ከወያኔ ጎራ የተሰለፉት ሥልጣን ሽተውም ይሁን በዘር ተስበው፤ ስኳር ልሰውም ይሁን መሬት ብናገኝ ብለው፤ አያያዙን አይተህ ወደሚያደላው ብለው መስሎ ተመሳስሎ መኖርን መርጠውም ይሁን ብቻ ባሉበት በተሰለፉበት ለወያኔ ይበጃል ያሉትን በተናጠልም ይሁን በመተባበር ሲሠሩ፤ እኛ ለተያያዝነው ትግል ይበጃል የምንለውን ምን ሠራን ብለን ራሳችንን ከመጠየቅ ይልቅ እነሱን ማውገዙ በእጅጉ ይቀለናል። ዓላማው ምንም ይሁን ምን ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመስለው ተባብሮ በራሱም ተጠናክሮ በጽናት የሚሠራ ይደነቃል። ዓላማየ የሚለውን ያውም በቃል ሲነገር የተቀደሰ ዓላማ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የማይጣጣር የማይተባበር መወገዝ መወቀስ ካለበት እርሱ ነው።
የተቃውሞው ጎራ ዥንጉርጉርነት በራሱ አልሞ አቅዶና ታግሎ ውጤት ማምጣት አይደለም ጊዜ የሚፈጥራቸውን አጋጣሚዎች ለመጠቀም እንኳን የማይችል አድርጎታል። በመሆኑም ወያኔ ለሥልጣኔ ማቆያ ይበጀኛል እያለ በሚፈጽመው ኢ-ሰብዓዊ፣ ኢ-ሕጋዊና ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ በሆነ ተግባሩ በየግዜው ከህዝብ እየተጣላ መሞቻውን ሲያፋጥን በአንጻሩ ተቀዋሚው መሰንበቻውን ያመቻችለታል። (የወያኔን ዕድሜ የሚያራዝም ተግባር ይፈጽማል።)
እንደ ተቀዋሚ ድርጅቶቹ ብዛት እንደ መሪዎቹ ማንነት ለታቃውሞ የተነሱበት ዓላማና ምክንያት ይለያያል። ነገር ግን በወርቃማ ቃላት የተሸፈነ ድብቅ አጀንዳ እስከሌለ ድረስ የወያኔን አንባገነናዊ አገዛዝ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ማስወገድና ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ማድረግ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ነው። (በድርጅት ደረጃ ከዚህ የተለየ የተጻፈና በአደባባይ የሚናገሩት ዓላማና ግብ የነበራቸው ዕድሜ አስተምሮአቸው መከራ መክሮአቸው ተመልሰዋል።)
በመሆኑም አደረጃጀታቸው ቢለያይ፤ የመረጡት የትግል ስልት ሊዛመድ የማይችል ቢሆን ከላይ በተጠቀሰው ግብ ተስማምተው ቢችሉ ተባብረው ካልሆነም ሁሉም በየራሱ የትግል ስልትና መንገድ ወደ ግቡ መጓዝ እንጂ አንዱ የሌላኛው እንቅፋት ሲብስም ጠላት ሆኖ መሰለፍ ፍቺ ያጣ እንቆቅልሽ ነው። ይህ እንቆቅልሽ የሆነ ተግባር ነው እንግዲህ ወያኔ መቃብሩን ሲቆፍር ተቀዋሚዎች ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት እንዲሆኑት ያደረገው።እናም ወያኔ መሞቻውን እኛ መሰንበቻውን እንሠራለን ለማለት ያበቃኝ።
ብዙ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ወቅታዊውን ሁኔታ እንመልከት። ከሁለት ዓመት በፊት ተቃውሞ አስነስቶ የብዙ ወጣቶችን የሕይወት መስዋዕትነት አስከፍሎ ለብዙ ወጣቶችም እስር እንግልትና ስደት ምክንያት ሆኖ ተግባራዊነቱ የቆመውን የኦሮሚያና የአዲስ አበባ አጎራባች ወረዳዎች የጋራ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እናደርገዋለን ለማደናቀፍ የሚሞክሩትንም ልክ እናስገባቸዋለን ብሎ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት ባሳየ መልኩ መናገር ዕድሜ ማሳጠሪያ እንጂ ማራዘሚያ ሊሆን አይችልም። ይህ ወያኔ ሞቱን የጠራበት የአቶ አባይ ፀሐዬ ንግግር ግን ለፖለቲከኞቹ የተገለጠላቸው ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባ ወጥቶ በጥይት መውደቅ ከጀመረ በኋላ ነው።
በኦሮምያ በአብዛኛዎቹ ዞኖች የታየው ግድያ፤ የግፍ ደብደባና የገፍ እስራት የተጠቀመበት አልተገኘም እንጂ ወያኔ መሞቻውን ያመቻቸበት ነበር። አቶ ጌታቸው ረዳ ህዝብን ጋኔን፣ ሰይጣን ጠንቋይ በማለት የተናገሩትም ሆነ የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሙክታር ከደር የወያኔው ገዳይ ቡድን በኦሮምያ ክልል ተሰማርቶ የፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ሁሉ ተገቢና ትክክል እንደነበረ ገልጸው፤ ይህን በማድረጋችሁ ትመሰገናላችሁ በማለት በመገናኛ ብዙኀን አማካኝነት ያስተላለፉት አድናቆትና ምስጋና ለወያኔ መሞቻው እንጂ መሰንበቻው ሊሆን የሚችል አልነበረም። እንዲህ አይነት ግራ ገብ ነገር ሲገጥማቸው ሟች ሞልቶ ነበር ገዳይ ጠፋ እንጂ ነው የሚሉት አበው።
የሱዳኖችን መሬት ድንበር አልፈው ሄደው የያዙ ሽፍቶች በማለት የሀገሩን ዜጎች ከመወንጀል አልፎ፤ የኢትዮጵያን መሬት የሱዳን ነው በማለት በአደባባይ ለመመስከር የተበቃው ከማን አለብኝነት ንቀት በመነጨ ቢሆንም፤ ይህ ሞቱን ሊያፋጥኑ ከሚችሉ በርካታ ተግባሮቹ አንዱ የሆነው ድርጊት ያደረሰበት ነገር አለመኖሩ ሲታይ በርግጥም የናቀን አይቶ ገምቶ ነው ያሰኛል። ያስናቁን ደግሞ በመግለጫ እንጂ በተግባር የማይታዩ ቁጥረ ብዙ ድርጅቶች ናቸው።
በሀገሪቱ በብዙ አቅጣጫ ፈንድቶ የወጣ ቁጣ በሚታይበት ወቅት አዲስ አበባ ዝም በማለቱ ለዓመታት ተግባራዊ ያላደረጉትን የመንገድ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ተግባራዊ እናደርጋለን ብለው የታክሲ ሾፌሮችን ለሥራ ማቆም አድማ የዳረጉበትን ድርጊት፤ ማንም ጤነኛ የወያኔ አባልና ደጋፊ ለዕድሜ ማራዘሚያ የተደረገ ነው ሊለው አይችልም። ዝም ያለውን ለመቆስቆስና ተቃውሞውን አዲስ አበባ ላይም ለማቀጣጠል የውስጥ አርበኞች የፈጸሙት ነው ከተባለ ሊያስማማን ይችላል። ነገር ግን በማንም ተፈጸመ በማን፤ ከሌሎች ድርጊቶች ጋር ተደማምሮ የወያኔን መሞቻ ሊያፋጥን የሚችል ድርጊት ነበር። በነበር ቀረ እንጂ።
በሀገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በወጪ የሚገኙት ፖለቲከኞች እነዚህና ሌሎች በርካታ ወያኔ ራሱ የፈጸማቸውን ሞቱን የሚያፋጥኑ ድርጊቶች ሊያነሳሱዋቸውና ሊያስተባብሩዋቸው ቀርቶ፤ እንደ ዓላማና አደረጃጀታቸው በየራሳቸው መንገድ ተንቀሳቅሰው ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ለመቅበር ያደረጉት ነገር ባለመኖሩ፤ እሱ ሞቱን ቢያፋጥነውም እነርሱ እስትንፋስ ሰጥተውት መሰንበት ችሏል። መሰንበቱን ሲያረጋግጥ ደግሞ ይቅርታ የሚባል የዕድሜ ማረዘሚያ መድኃኒት ራሱ ለራሱ አዝዞ እየወሰደ ይገኛል። ይህን ተከትሎም አንዳንዶቹ ፖለቲከኞች በእውናቸው ይሁን በሕልማቸው የታያቸው ባይታወቅም፤ ይቅርታ በተባለው እንክብል ወያኔ ሙሉ ፈውስ አግኝቶ ከደደቢት እምነቱ ይለወጣል ብለው ተስፋ እያደረጉ ነው።
ወያኔ ከላይ ለአብነት የተጠቀሱትን ጨምሮ ለሃያ አምስት ዓመታት በቃልም በተግባርም መሞቻውን የሚያፋጥኑ ድርጊቶች ፈጽሟል። በአንጻሩ ወያኔን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ለማንሳት ነው የምንታገለው የሚሉ ፖለቲከኞች ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ፓርቲ ሲያፈርሱ ሲገነቡ፤ እንደ አሜባ ራሳቸውን ሲያባዙ፤ ርስ በርስ ሲወነጃጀሉ፤ የጎንዮሽ ሲታገሉ፤ ወያኔን ታግለው የሚያሸንፉ አይደለም፤ ወያኔ የራሱን መቃብር እየቆፈረ ሞቱን ሲያፋጥን፤ ገንዘው ሳጥን ለመክተትም ሆነ ከቀብር ስፍራ አድርሰው አፈር ለመመለስ የሚችሉ ባለመሆናቸው፤ ወያኔ ነበረ አለ እስከ መቼ እንደሆነ ባይታወቅም ይኖራል። አሳዛኝ! አሳፋሪ!