ወልቃይት ፀገዴገለታው ከሩቅ ምስራቅ

ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደምትናፍቅ፤ ወልቃይትም ዘውጉን ናፈቀ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ደጋግመው ይናገሩ የነበሩት ስለ በግድ ምስለት ወይም በግድ እኔን መስለህ ኑር (forced cultural assimilation) ጉዳይ ነበር። እንደ አዲስ መገለጥ ነበር ይህን የሚሰብኩት። ህወሓት ገና ደርግን ሥልጣን ላይ ትንሽ ቆይቶ ሳያየው ወደ ጫካ ወሰደኝ የሚለው ጉዳይ ይሄው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በነሱ ቋንቋ “መጨፍለቅ … መዳጥ” ጉዳይ ነው ይላሉ። ይህ ማለት ቡድኖች ሳይወዱ በግድ አማራውን እንዲመስሉ ተደርጓል በሚል ነው። በነሱ ቋንቋ “አማራይዜሽን” ይሉታል። እንዴው አማራው እንዲህ ባለፉት ስርአቶች ከተመቸው ስለምን ሃይለስላሴን ታገለ? ስለምን የወሎ እናት በነ አሊ ሙሳ ልጆቿን ተቀማች? ስለምን ሸዋ አመፀ? ስለምን ጎጃም ተነሳ … ስለምን ጎንደር ታገለ … ለዚህ ጥያቄ ወያኔ መልስ የለውም።

እንግዲህ ህወሓት ይህን የአማራ የባህል የበላይነት አጠፋለሁ ሲል እንደሚታወቀው አብዛኛው ማለት ይቻላል የቡድኖች ባህሎች ኃይማኖታዊ ናቸው ወይም በኃይማኖት ተፅእኖ ስር የወደቁ ናቸውና የአማራን የብዙሃን ኃይማኖት መምታት ፈለገ። በዚህ መሰረት ኦርቶዶክስን መምታት አንዱ ዋና የትግል ስትራተጂው አድርጎ ነበር። ለዚህም ነው እነ አቶ መለስ በተለይም አቶ ስብሃት በግልጽ ቋንቋ አማራንና ኦርቶዶክስን መምታት አለብን ያስባላቸው። በርግጥም እንዳሰቡት ሥልጣን ሲይዙ ኦርቶዶክስን ለሁለት ከፈሉና ጳጳስ በጳጳስ ላይ ሾሙ። ለነገሩ ሙስሊሙም አልቀረለት ይሄውና ዛሬ መከራውን ያያል። አማራውንም በተለያየ መንገድ ሲያሰቃዩት አሉ።

ህወሓት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ስለዚሁ ስለ ባህል ምስለት ጉዳይ ብዙ የሰበከ ሲሆን ወያኔ ደጋግሞ በተለይ ኦሮሞውን በግድ የአማራ ስም አውጥተህ ራስህን ያገኘኸው ለዚህ ነው ይል ነበር። በቅርቡ ዶክተር ቴድሮስ የአንድ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ጓደኛቸው ስሙ ገላና የነበረ ኦሮሞ በደረሰበት ጫና ገላነው ተባለ ይሉናል። እውነቱን እግዜር ይወቅ። ግን የራሳቸው የቴድሮስ ስምስ መቼ ትግርኛ ነው። ግሪክ እኮ ነው መነሻው። እንደው በዚህ ደረጃ ወርዶ መወያየት ቢያሳፍርም ማለቴ ነው። የኔ የራሴ ስም ገለታው ነው። መነሻው ኦሮምኛ ነው። በኦሮምኛ ገለታ ነው ስሜ ማለቴ ነው። ምንም እንኳን ኦሮሞ ባልሆንም እኮራበታለሁ። ለነገሩ እነ ዶክተር ቴድሮስ ህወሓቶች ይህቺን የስም ነገር እያራገቡ የኦሮምያን አንጡራ ሀብት ሲበዘብዙ ቆይተው ዛሬ ይሄውና የኦሮሞ ህዝብ መሬት አንቀጥቅጥ አመጽ ላይ ነው። ዛሬ ዓለም ታዝቦ ለካ ህወሓትን ጫካ የወሰደው ጉዳይ የብሔሮች ማንነት ጉዳይ ሳይሆን፤ ለኢኮኖሚ ጉዳዮቹ ነው ተብሏል። ለማናቸውም እንግዲህ ወያኔ ሀገሪቱን በብሔር ፌደራሊዝም ማስተዳደሩን ቀጠለ። ልዩነት በጣም ሲራገብ አንድነት አቅሉን አጣ።

በርግጥ የበፊቷ ኢትዮጵያ በኃይል ነበርና የተመሰረተችው የባህል ሚዛኑ ችግር ነበረበት። የቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ፣ የባህል ማንነት ጉዳይ በተሻለ ሲስተም ሊተዳደር ይገባው ነበር። መጀመሪያ ላይ ወያኔ ይህን የብሔር ብሔረሰብ እኩልነት ሲዘምር አማራው ቅር አላለውም። ሁሉም ብሔሮች ደግፈዋል። ምክንያቱም ይህቺ ሀገር የሁላችን እንደመሆኗ ሁሉም ብሔሮች በእኩልነት ሊኖሩባት ይገባልና ነው። አለበለዚያ አንድ የተባበረች ጠንካራ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ልታምረን አይገባም። ሩቅ ማሰብ አለብን። መሪነት ይሄ ነው። ነገን የማያይ መሪ መሪ አይባልም።

እንግዲህ ወያኔ ወደ ሥልጣን ሲመጣ፤ የጎንደር፣ የወሎ፣ የሸዋ ህዝብ እየሰነቀ ነው የሸኘው። በተለይ ጎንደር ብዙ መከራ አይቷልና። በርግጥም በህወሓት ትግል ጊዜ ከታች የነበረው ተራው ታጋይ በእውነት በንጽህና ነበር ይታገሉ የነበሩት። እኔ በግሌ ያኔ ገና አዲስ አበባ ሳይገቡ ካደኩባት ከተማ ውስጥ ቀድመው ገብተው ነበርና የህወሓትን ታጋዮች አይቻለሁ። እነ ሃደራን፣ እነ አበባን፣ እነ ጎይቶምን፣ … መቼም አልረሳቸው። በንጽህና ደርግን ታግለዋል። አንድ ተጋዳላይ ባህርዩ ማርኮኝ ስለነበርና ተስፋ መስሎ ስለታየኝ ልብስ ሲያጥብ አይቼ ሱሪህን ካላጠብኩ ሞቼ እገኛለሁ ብየ አጠብኩ። ደስ አለኝ። ያቺን እናቴን እባክሽ ቡና አፍይና ጥሪያቸው እያልኩ ስንት ቀን አብረን ቡና ጠጣን። እሷም እግዜር ይስጣት ጠብ እርግፍ እያለች ታስተናግድልኝ ነበር። አባቴ ዛፍ እንዲሰጥ ለመንኩ። የሚያበስሉበት የቸገራቸው መስሎኝ ነው። በሽማግሌ ጎኑ እንጨት እየፈለጠ በጎረቤት ሰፍረው የነበሩ ወያኔዎችን አገዘ። እንቢ ሳይለኝ ያልኩትን አደረገልኝ። ወያኔዎቹ ቁምጣቸውንም ይሁን ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው ስለሚታጠቁ የተራቡ እየመሰለኝ ብዙ ቀን ተሳቀኩ። ቤተሰቦቼ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ቢኖራቸውና በእኔ በልጃቸው ስም ለወያኔዎቹ ቢለግሱልኝ ይሰማኝ የነበረው ደስታ ኃያል ነበር። ኋላ ላይ ከዚያች ከኛ ከተማ ወያኔዎች አፈገፈጉና 18ኛው ተራራው የተባለው ጦር ይመስለኛል (እርግጠኛ አይደለሁም) ከተማዋን መልሶ ያዘ።

ጨካኙ ደርግ ጎረቦቶቼን አጎቴን የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሬን ጥርግርግ አድርጎ በአንድ ጉድጓድ ረሸናቸው። ከዚያች ትንሽ ከተማ አስር ታዋቂ ሰው ሲጠፋ ሲረሸን ከተማዋ ባዶ የቀረች ያህል ይሰማል። ከወያኔ ጋር ተባብራችኋል፣ አብልታችሁ፣ አጠጥታችኋል ነው ክሱ። በዚህ ጊዜ አንዱ ሊረሸን የነበረው የኔ አባት ነበር። ደርግ እንደገና ከተማዋን ሲቆጣጠር አባቴ ታስሮ ነበር። ሊገደል ተወስኖ በታምር ተረፈ። ደርግን ድሮም እጠላው ነበር፤ አሁን አውሬ መስሎ ታየኝ። ሁዋላ ላይ ለትምህርት በሚል ወደ ሌላ ከፍ ያለች ከተማ እንድመጣ ተወሰነና መጣሁ። ቤሳቢስቲ ሳይኖረኝ በዚያች ሻል ያለች ከተማ ደረስኩ። ዕድሜ ለቀይ መስቀል በነሱ እርዳታ ነው በዚያ ትምህርት የጀመርኩት። እንደኔ ላሉ ተፈናቃዮች ቀይ መስቀል አባትና እናት ሆኖ አከረመን። ታዲያ በዚያ ከተማ እያለሁ የመጨረሻውን የደርግን ግፍ አይ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዶ ነበር መሰለኝ ወደ አንድ ፖለቲካ የሌለበት ኃይማኖታዊ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሄጄ በደርጉ ፖሊሶች ታሰርኩ። መታሰር ብቻ አይደለም ግርፍም ነበር። በመጀመሪያው ቀን ስንያዝ የመጣንበትን ተጠይቀን እኔ የመጣሁባት ከተማ ውስጥ አሁን ወያኔ ስላለ እንደምገደል ገምቼ ነበር። የኔና የጥቂት ሰዎች ጉዳይ ከወያኔ ሰላይነት ጋር ሊያያዝ ነው ማለት ነው። የፖሊስ አዛዡም ይህን ጠቆም አርገው ነበር። ታዲያ ስንገረፍ ትዝ የሚለኝ ሁለት ፖሊሶች አምስታችንን እየተፈራረቁ ይገርፉን ነበር። ለምን እንደሆነ አላውቅም አንዱ ፖሊስ እኔን ለብቻየ አውጥቶ ይደበድበኝ ጀምር።

አንድ የምናገረው አለ አልኩት ጮክ ብየ። በግርፉ መሃል።

“ምንድን ነው!” አለኝ። በሚያቧርቅ ድምጽ። ኮፍያው ተጣሟል አልቦታል።

ፋታ የሰጠኝ ስለ ወያኔ የምለው ያለ መስሎት ይመስለኛል። እኔ ግን እንዲህ አልኩት፤

“አስራ ስምንት ዓመት አልሞላኝም እኮ!” አልኩት።

እውነቱን ለመናገር አስራ ስምንት ዓመት ይሙላኝ አይሙላኝ ይለፈኝ ጠንቅቄ አላውቅም። የልደት ካርድም የለኝም። ስለ ዕድሜ እኛ አካባቢ ብዙ ትኩረት የለም። ለፖሊሱ ያንን ያልኩበት ዋናው አጀንዳየ ግን አንድም ቢያንስ ድብደባውን እንዲተወኝ … አለ አይደለም እንዲያዝንልኝ ነበር። አሰነዛዘሩ እስክሞት የሚቀጥል መስሎኝ ነው። መዘየዴ ነበር። ሌላው ደግሞ ለሕግ ይገዙ እንደሆን ብየም ነበር። ያ ፖሊስ የሳቀው ሳቅ ከህሊናየ አይጠፋም። እስኪችል ደበደበኝ። ይህን በመጠየቄ እጥፍ ዱላ ተቀበልኩ። ያ ፖሊስ በሕግ ላይ ነበር የሳቀውና ውስጤ እንደ ብረት ሆነ። በእግሩ ስር ሲወቃኝ ልታገለው እስካስብ ኃይል ተሰማኝ። በቃ ለውጥን ሰብዓዊነትን ከልብ ለሀገሬ የተመኘሁላት ያን ቀን ጨለማ እስር ቤት እያለሁ ምሽት ላይ ነበር ልበል። ለወደፊት በዚህ ጭለማ ላይ ሻማ በርታ ብርሃኑ ጨለማውን አስወግዶ በምናብ አየሁ። አብሮኝ ለታሰረው ሹክ አልኩት። ሻማ በርቶ ይህ ጭለማ በብርሃን ተሸንፎ አየሁ አልኩት። በድብደባ የሞተውን እግሩን እያሸ ሲስቅ ይሰማኛል። በነገራችን ላይ በዚያች በትንሽ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ ሁለት በእግር ብረት የታሰሩ ወያኔዎችን አገኘሁ። እንዲሁ ስናንሾካሹክ አደርን። ያሳዝናሉ። የሚጠብቃቸው ነገር የፍርድ ሂደት ሳይሆን የሜጀር ጄነራል ከፈለው ይብዛን ወይም ከዛ በታች ያለ አዛዥ የሚሰጠውን የግድያ ትዕዛዝ ብቻ ነው። መጨረሻ ላይ እኔ በዋስ ስወጣ እዚህ አካባቢ ዘመድ ካላችሁ ላኩኝ ስንቅ እንዲያመጣላችሁ ብየ ሹክ ብላቸው ምንም ሰው የለንም አሉኝ። በኋላም አብዮታዊ ርምጃ እንደተወሰደባቸው ሰማሁ። ወደ ኋላ እንዳልመልሳችሁ እንጂ፤ በዚያች ባደኩባት ከተማ አንድ የደርግ መኮንን ውሃ በኮዳ እንድቀዳ ያዘኛል። እየሮጥኩ ሄጄ በዚያች በኮዳው ውሃ ይዤ መጣሁ። ስመለስ አንድ ዘግናኝ ነገር ገጠመኝ። ይህ ወታደር የሆነ አንድ ገበሬ ከፊቱ አቁሞ ያናግራል። ያ ገበሬ ቃል የለውም። በርግጠኝነት በእውቀት ላይ የተደገፈ የወያኔ ደጋፊ አይደለም። ወያኔ አብልቶ አጠጥቶ ቢገኝም። ምክርና ቁጣ ለዚህ ገበሬ ከበቂ በላይ ነው። ወታደሩ የወንበዴ ቅጥረኛ እያለ ያዋርደዋል። እኔ ደግሞ ያቺን ውሃ ሙሉ ኮዳ እንደዘረጋሁ ነው። ጥቂት ከንፈሩን ነከሰና ሽጉጡን ላጥ አርጎ ግንባሩን አለው። ለብዙ ቀን የዚያ የገበሬ ሁኔታ ሲያሳዝነኝ ነበር። ብዙ ሰው ሞቶ አይቻለሁ፤ እንደዛ ገበሬ ያሳዘነኝ ግን የለም።

ወደ ወያኔዎቹ ልመለስና፤ በውነት እነዚያ የትግራይ ልጆች ሐቀኞች ነበሩና ማርከውኝ ነበር። ይህን የግል ሕይወቴን ሁሉ የማወራችሁ ሌላም ዜጋ ወያኔን እንደኔው ተስፋ አድርጎ አስቦ ነበር ብየ ስላመንኩ ነው። ታዲያ የነዚያን የዋህ ወያኔዎች ሁኔታ አይቼ ተስፋ ብሰንቅም የነሳሞራ፣ የነ ገብሩ፣ የነ አባይ ጉዳይ በርግጥ አሳስቦኝ ነበር። አዲስ አበባ ላይ ያቺን ትልቅ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድሩ ማሰባቸው በጣም አሳስቦኝ ነበር። ከነበራቸው እውቀት አንጻር ማለቴ ነው። ከነበራቸው ሎጂክ አንጻር ማለቴ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ጄነራል የሆነው ሳሞራ እኔ ተልዕኮየ ህዝብን ነፃ ማውጣት ነውዕ ከዚያ ወደ ግል ኑሮየ … ብሎ ነበር። ይሄ ትንሽ ረፍት ሰጥቶኝ ነበር። በርግጥ እነዚህ ታጋዮች ታግለው ታግለው የልጅነት ጊዜያቸውን በረሃ በልቶት ኢትዮጵያ ዝም ብላ አትበተንም። የካሳ ዘመን ልትደግስላቸው እንደሚገባ በሚችሉት ሀገራቸውን ሊያገለግሉ እንደሚገባ አምን ነበር። እኔና ከነዚህ ታጋዮች መሃል አንዱ ለሥራ ውድድር ቀርበን ለሱ አፈርማቲቭ አክሽን ተብሎ አድቫንቴጅ ቢሰጠውና እኔ ሌላ ዕድል ብጠብቅ ቅር አይለኝም ነበር። ይህ ግን አልሆነም። እንደገቡ ምሁር የተባለውን በባትሪ እየፈለጉ ከነሱ በእውቀት ያንሳል የሚሉትን እየፈለጉ ኢትዮጵያን በመልካም አስተዳደር እጦት ይቀጡ ጀመር።

እነዚያ ብዙ ንፁህ የህወሓት ታጋዮች መስዋዕትነት ከፍለው ለእኩልነት ይታገሉ እንጂ፤ እነመለስ ከመነሻው በነዚህ ሰዎች ሬሳ ላይ ሌላ አጀንዳ ነበራቸው። ይሄው አጀንዳ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ታየ።

ጎንደር እኮ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያ የሁላችን ነች፣ አምባገነንነት ይውደም ባለ ነው ልጆቹን ያጣው። የጎንደር እናት እንዲህ ስትል ሙሾ አውርዳ አልነበር?

መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም

የዛሬን ማርልን ሁለተኛ አልወልድም።

በርግጥም የጎንደር ወጣቶች የሞቱትና የተሰደዱት ለብሔሮች እኩልነት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ነው። ታዲያ እንዲህ በደርግ የተጎዳ ጎንደር ህወሓት ወደ ክልሉ ስትገባ የብሔርተኝነቱ ስሜት ስላልነበረ፤ እነዚህ ወያኔዎች ወገኖቻችን ናቸውና እስቲ እነሱ ከበረቱልን ይህን አረመኔ ደርግ ይጣሉት፣ እኩልነትን ያመጣሉ በሚል፤ ስንቅ እያቀበለ፣ እየደገፈ ነበር የሸኛቸው። ጎጃም ለወሎ፣ ወሎ ለሸዋ እያቀበላቸው ነው አዲስ አበባ የገቡት። እንደውም በአንድ ቦታ እንዲህ ተዘፍኖ ነበር። ዘፋኙ ሰው ልጆቹን ሁሉ በግድ ለብሔራዊ ውትድርና ገብሮ የመረረው ገበሬ ነበር።

ምንሽር ልገዛ በሬየን ሳስማማ

ወያኔ ደረሰች በነጠላ ጫማ

በርግጥ ለውጥ የተራበ ህዝብ አንዳንዴ አይመዝንምና ስለወያኔ የፖለቲካ ተፈጥሮ ሳይመራመር ደጋግፎ አዲስ አበባ አስገባ። ብዙ ሳይቆይ ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በሁዋላ ያንኑ ሲያበላው የነበረውን እጅ መንከስ ጀመረ። እነዚህ ሰዎች ለብሔር እኩልነት ሳይሆን የመጡት ለዘረፋ ነው ተባለ። ከሃያ ዓመት በኋላ ወጣቱን ሥራ ፈት አደረጉት። አምራቹን ተንከራታች ስደተኛ አደረጉትና ሲመረው እንዲህ ሲል ዘመረ። ዝማሬው ያስደነግጣል።

ና ና መንግሥቱ ና ና

ና ና መንግየ ና ና …

ያሳዝናል።

ትናንት ወያኔ ደረሰች በነጠላ ጫማ ይል የነበረ ህዝብ ዛሬ ያንን ያስለቀሰውን መንግሥቱን እንደገና ናና መንግሥቱ ናና … እያለ ሲዘፍን እንደማየት የሚያሳዝን ኧረ ለመሆኑ ምን ነገር አለ? ይህ ህዝብ ወደ ኋላ ያስመኘው ምን ያህል ቢበደል ነው? ምን ያህል ሆድ ቢብሰው … ምን ያህል ቢመረው ነው? ምን ያህልስ ቢርበው ቢከፋው ነው? የሚለው ነገር እስከ ሃቹ ያስደምማል።

ሕብረተሰቡን ከምንም በላይ የጎዳው ስነ ልቦናዊው ጉዳይም ነው በርግጥ። በዚያች ሀገር የአንድ ብሔርን የበላይነት ለማምጣት የሚሞክረው ወያኔ ይህ ጉዳይ ለህዝቡ አልተዋጠለትም። ህዝቡ ዕለት ዕለት ይህ ስሜት እያበሳጨው እያናደደው ሲመጣ ይታያል። ሃጎስ፣ አበበ፣ ገለታ፣ ሜቶ ጎረቤት ሆነው ሲኖሩ ዛሬ ሃጎስ ህወሓት ሥልጣኑን ተቆጣጥሯልና የበላይነት ለማሳየት ቢንጠራራ በርግጥም ሌሎቹን ያሳብዳል። አበበም ሆነ ገለታ ወይም ሜቶ አንዱ ባንዱ ላይ መንጠራራት ካማራቸው ኢትዮጵያ አለቀላት። የብሔር ፖለቲካ ችግር ይሄው ነው እንግዲህ። ወያኔ የዘራውን የዘር ፖለቲካ ሰብል አጨዳ ላይ ነንና ጎበዝ እንጠንቀቅ።

ወደ ዋናው ርዕሴ ልመለስና እንዴው የኢኮኖሚውን የዴሞክራሲውን ጉዳይ ሁሉ እንተወውና ቢያንስ ይሄ ሞቼለታለሁ የሚለው የብሔሮች ማንነት ጉዳይ እንዴት ነው? ብለን ስንጠይቅ ህወሓት በአደባባይ ምስለትን ይርገም እንጂ በጓዳው ግን የሆነ ነገር ቀብሮ ይኖራል። የወልቃይቶች የማንነት ጉዳይ …

በመሰረቱ የወልቃይቶች የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አልገነነም ነበር። ለምን? ቢባል አንደኛ አማራው አብዛኛው አማራ ማለት ነው ከብሔርተኝነት ጋር የተጋጨ ስለነበረና የወያኔን የብሔር ፌደራሊዝም በህሊናው መቀበል ስለተሳነው የወልቃይቱ አማራ የሄደ የሄደ ሳይመስለው እንዲሁ ቆየ። ይህ የብሔር ፌደራሊዝም ሲፈጠርም አማራ አልተካተተም ነበር። የሚሆነውን ሁሉ ዝም ብሎ ከዳር ቆሞ ያይ ነበር። ኋላ ሁኔታው ስላላማረው ላለው መንግሥትና ላለው ሲስተም እውቅና (legitimacy) አልሰጠም ነበር። ይህ ሁኔታም የወልቃይትን ጥያቄ አጉልቶ እንዳያይ አድርጎት ቆይቷል። ይሁን እንጂ በመሃል ወልቃይት መጮህ ጀመረ። ጨዋታው በየቤትህ እደር ሆኖ ሃያ አምስት ዓመት ሲቆይ ጊዜ ወልቃይት መንጋው ናፈቀው። ትግራይ ወደ መንጋው ሲገባ ሌላውም ማንነትህ ተጠብቋል ተብሎ የብሔር ፖለቲካው ሲጦፍ ወልቃይትም ዘውጉን ናፈቀ። ማንነቱ … የሚኮራበት … ያ … አማራነቱ መጣበት …። እናም በአካባቢው ያሉትን የትግራይ ሰዎች እያየ ይሄው አጨፋፈሩ የኔን አይመስልም፣ ይሄው በአል ሲካድም እንደኔ አይደለም፣ ይሄው ሠርግና ምላሻችን ይለያያል … ያለ ቤቴ ነው ያለሁት … አለ። ሴቷ የወልቃይት አማራ ደግሞ ልዩነት ፈልጋ የኔ ጸጉርና የሷ ፀጉር አያያዝ አይመሳሰልም … እንለያያለን … ወዘተ … ማለት ተጀመረ። ይህ ነገር በርግጥ ከጥላቻ አይደለም። እነዚህ ሁለት ብሔሮች ይጋባሉ። ይሁን እንጂ የፖለቲካው መስመር በየቤትህ እደር ሆኖ የወልቃይቱ አማራ ማንነቱ ሳያውቀው እየተነነ የመጣ መሰለውና ደነገጠ። አንድ ትልቅ ክህደት ሊፈጽም መሰለው። በርግጥ ከፍ ሲል እንዳልኩት ሸዋው፣ ጎጃሙ፣ ጎንደሩ፣ ወሎውና በያለበት ያለው አማራ ሁኔታውን ዝም ብሎ ማየቱ ያንን የወልቃይት ዘውጉን መዘንጋቱ ሳይሆን እስቲ ወይ ጊዜ ይፈታዋል እስከዚያው ያው ሀገሩ ነው በሚል ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ብዙው አማራ ወያኔ የብሔሮችን እኩልነት አመጣበታለሁ ያለውን የልዩነት ፖለቲካ እየረገመ ስለሆነ ያለው የወልቃይቶች የማንነት መጨፍለቅ ጉዳይ ትኩረት ሳያገኝ እንሆ 25 ዓመት ቆየ። ይሁን እንጂ አሁን አሁንስ ወልቃይት ትግራይ ውስጥ ባይተዋርነት ተሰማው …። ለምን ተሰማው? ብንል ከትግራይ ህዝብ ጋር በሚኖረው ኑሮ ሳይሆን ዘረኛ የሆነው ህወሓት የሚያደርስበት ስነ ልቡናዊ ጫና ነው። ዛሬ ዛሬ ግን ወልቃይት ሰሚ አገኘ። በርግጥ ትኩር ብለን ካየነው ከማንነት ጋር በተያያዘ በዚህ መንግሥት እንደ ወልቃይት የተጎዳ የለም። የዴሞክራሲ መብቶች ችግሮችን ሁላችን የምንጋራ ሆኖ ነገር ግን ወልቃይት በማንነት ጉዳይ በጣም ተጎድቷል።

እንዴት? ማለት ጥሩ ነው። በሚከተሉት ምክንያቶች ቀድሞ ከነበረውም የምስለት ግፎች የወልቃይት በጣም ይከፋል።

አንደኛው ምስለቱ በራሱ ብቻ ሳይሆን የከፋው በግድ መሆኑና ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ በግድ የሆነ ምስለት በብሔር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ከባቢ ውስጥ መሆኑ ነው። በአንድ ሀገር ጥላ ስር ባለ ማንነት ስር የሚደረግ ምስለት በአንጻራዊነት የሚሻል ሲሆን የብሔር ፖለቲካ በነፈሰበት ሀገር አንድ ቡድን ያለ መንጋው ሲገኝ ቢጨንቀው ስለምን ይፈረድበታል? ሆዱ ቢባባና የተረሳ ቢመስለው ስለምን ይፈረድበታል? አንዱ የወልቃይትን ስነ ልቡና ያደቀቀው ነገር ጨዋታው በየቤትህ እደር ሆኖ ወልቃይት የሚኮራበት የዘውግ ቤት እያለው ለምን ትግራይ ውስጥ ይሸጉጡኛል የሚለው ነው። ልብ የሚነካ አሳዛኝ ነገር ነው። ማንም ብሔርና ግለሰብ ይህን የወልቃይትን ጉዳይ በሚገባ ሊረዳው ይገባል። ሌላው የወልቃይትን ግፍ የሚያገዝፈው ጉዳይ ደግሞ ይህ በግድ እኔን ምሰል የሚል ነገር ዛሬ ዘመን ላይ መፈጸሙ ነው። የማንነት ፖለቲካ ተቀባይነት ባይኖረውም ነገር ግን በግድ የመለየት ፖለቲካው ከመጣ በሁዋላ ዜጎች ስለማንነት በሚገባ ያጠናሉ። ማይክሮ የነበሩ ማንነቶችን ሁሉ በማይክሮስኮፕ እያዩ ልዩነትን እየነቀሱ እያወጡ ያገዝፏቸዋል። ልዩነትን ይፈልጋሉ። በዚህ ላይ እውቀታቸው ይጨምራል። ታዲያ እንዲህ በዚህ ዘመን አንድን ቡድን በኃይል መስሎ እንዲኖር ለማድረግ መሞከር የዚያን ማኅበረሰብ ስብራት እንዲገዝፍ ያደርገዋል። ከዴሞክራሲያዊ መብቶችም በላይ የወልቃይት ስነ ልቡና ተጎድቷልና ይህን ጉዳት ኢትዮጵያውያን ሊረዱለት ይገባል።

የወልቃይት ጥያቄ ንጹህ የማንነት ጥያቄ ነው። አንድ ነገር መገንዘብ ያለብን ወልቃይት ወደ ዘውጋችን መልሱን ሲል ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ስለተነካና በዚህ በኩል አማራ ክልል ስለሚሻል አይደለም። አማራ ክልልም ሄድክ ኦሮሚያ ወይም ደቡብ ወይም ሌላ ክልል በአንድም በሌላም መንገድ ገዢው ያው ህወሓት ነው። የወልቃይት ህዝብ ይህንን ያውቃል። ይሁን እንጂ ጥያቄው የዘውግ ጥያቄ ነው። ተመቸውም አልተመቸው ወደ ቤቱ መመለስ ይፈልጋል። በቋንቋው በባህሉ እየኖረ በሌላ በኩል ደግሞ ዴሞክራሲ ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ ከሌሎች ብሔሮች ጋር የወልቃይት ህዝብ የብሔር ፖለቲካንና የከፋፍለህ ግዛውን ሥርዓት ሊታገል ይፈልጋል። የወልቃይት ህዝብ የሚታገለው ብሔራዊ አንድነቱም ዘውጋዊ ማንነቱም ተጠብቀው ሳይጋጩ የሚያኖርለትን ሲስተም ለማምጣት ነው። ይሄ መታወቅ አለበት። የአንድ ዴሞክራቲክ መንግሥት ኃላፊነት እነዚህን ሁለት ዋና ዋና ማንነቶች መጠበቅ ነው።

ሌላው የወልቃይትን ጥያቄ ያመረረውና ያከበደው ጉዳይ የህወሓት የፖለቲካ እምነት ነው። በብሔር ፖለቲካ እምነት መሰረት ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለው ነገር የፍልስፍና መሰረቱ ምንድን ነው? ካልን ዘውጎች በራሳቸው ልጆች ሲመሩ አስተዳደሩ ትጋትንና ርህራሄን ይጨምራል፣ ተግባቦት ይጨምራል ከሚል ነው። እኔ በግሌ አላምንበትም። ታዲያ እንግዲህ እንዲህ አይነት አመለካከት ባለው የፖለቲካ ድርጅት ስር ድንገት የሌላ ዘውግ አባል ሆኖ መገኘት በርግጥም ይጨንቃል። በርግጥም ባይተዋርነት ይሰማል።

የጨነቀው የወልቃይት ህዝብ በየማኅበራዊ አጋጣሚው የሆድ የሆዱን ሹክ ማለቱ አይቀርም። እንዴው ለመሆኑ ለምን ፈለጉን …?

ትግርኛ ስለምንሞክር …

እንዴ? አንዳንድ ክልሎች ቋንቋቸው አማርኛ ሆኖ የለም እንዴ?። አንድ ቋንቋ መናገር ብቻውን በአንድ ክልል ውስጥ እንድትሆን አያስፈርድብህም። ዐረብኛ ስለምንናገር ነገ ሱዳን ተነስቶ ይህ አካባቢ የኔ ነበር ምልክቱ ህዝቡ ዐረብኛ መናገሩ ነው … ሊል ነው?

ወልቃይት እየተደመመ አሁንም ሹክ ይላል …።

ምን አልባትም እነዚህ ሰዎች ይህቺን ሀገር አምሰው አምሰው ኋላ መውጫ ቀዳዳ ሲጠፋባቸው ወደ መገንጠል ሊያመሩ ይችሉ ይሆን? ከተገነጠሉ ደግሞ የወልቃይት ለም መሬቶች አጓጉታቸዋለች ማለት ነው? የሰሊጥና የኑግ ምርት … ታላቋ ትግራይ የሚያሰኛቸው የዚህ የወልቃይት መጨመር ይሆን? ይላል ግራ የተጋባ ህዝብ ከዘውጉ ከመንጋው ተገንጥሎ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ያለ ወልቃይት …። በነገራችን ላይ ይሄ ታላቋ ትግራይ፣ ታላቋ አማራ፣ ታላቋ ኦሮሞ፣ ታላቋ ሲዳሞ … የሚባል ነገር እልም ያለ ቅዠት ነው። የቀን ቅዠት። ትግራይ አይደለችም ኤርትራ የባህር በር ይዛ፣ ለብቻየ ኖሪያለሁ ታሪክ አለኝ ላለችውም የሚበጅ አልሆነም። መገንጠል ማነስ እንጂ ምን ታላቅነት አለው?

ወደ ወልቃይት እንመለስና ወልቃይትን አሁን ግን ዓለም ይፈርደዋል። ጩኸቱ ከጸባዖት ገብቷል። ስለዚህ ስለ ክልል ጉዳይ ብዙ ሰው ሲጨነቅ እሰማለሁ። የትግራይ ክልል ተከዜ ነው። ከዚያ በመለስ በታሪክ ጎንደር ነው ይላሉ። በርግጥም በዚህ ላይ መቼም መከራከር አይቻልም። ይህ ሃቅ ነው። ህወሓት ድንጋዩን ዳቦ ነው ብሎ አፍጦ ስለሚከራከር ከሱ ጋር መከራከር ጊዜ መግደል ነው። ይሁን እንጂ ከህወሓት ቀድሞ ታጋዮች እንደውም ይህንን ወልቃይትን ወደ ትግራይ የመከለሉን ሥራ የሠሩት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ራሳቸው እንዲህ ነበር ያለት።

“ወልቃይት ወደ ትግራይ እንዲገባ የተደረገው ወደ ሱዳን መውጫ ለማግኘት ነው” (ዶክተር አረጋዊ በርሄ)

“የትግራይ ወሰን የተከዜ ወንዝ ነው” (ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም)

“የጎንደር እና ትግራይ ግዛቶች የሚያዋስነው ተከዜ ወንዝ ነው” (አቶ አሰገደ ገብረሥላሴ)

”የወልቃይት ህዝብ የዘር ማጥፋት እና ግዛት ማካለል የተጀመረው በ1970ዎች ነው። ህወሓቶች ወልቃይቶችን ወደ ትግራይ ልትጠቃለሉ ነው ሲሏቸው ህዝቡ እምቢ በማለቱ ከዚያን ጀምሮ የኃይል ርምጃ እየተወሰደ ወልቃይትም በግድ የትግራይ ሆነ” (አቶ ገብረመድኅን አርኣያ)

“ወልቃይት ወደ ትግራይ ሲካለል ከሱዳን ጋር ለመገናኘት ስለነበር የህዝብን ፍላጎት አልጠበቀም። በመሆኑም የህዝብ ምርጫ ሊከበር ይገባል” (አቶ ግደይ ዘርአጽዮን)

ከሁሉ በላይ የወልቃይት ህዝብ ሲጠየቅ ይደነቃል። ምስክር በማቅረቡ ራሱ ይገርመዋል። በእንበል ገበያ ሆነን እንድ ሰው አቶ አባይ ፀሐዬን አንተ ትግሬ አይደለህም የሌላ ብሔር ሰው ነህ ብሎ ቢከራከር፤ አቶ አባይና በውል የሚያውቋቸው ሰዎች ምን ይላሉ? የወልቃይት የአማራነት ጥያቄ በዚህ ደረጃ የሚታይ ነው። ይሁን እንጂ ህወሓት አንድ ነገር አለው። አንድን የፈጠራ ውሸት ብዙ ጊዜ ደጋግመህ እውነት ነው፣ እውነት ነው፣ እውነት ነው … ካልክ በህዝብ ላይ የሚፈጥረው ስነ ልቡናዊ ጫና አለ አንድም ያሳምናል ቢያንስ ቢያንስ ግን ግራ ያጋባል ይላሉ። ይሄ የማይቀየር የወያኔ የህዝብ ግንኙነት የፍልስፍና መሰረት ነው። በርግጥ ይህ ነገር ሳያዋጣቸው አልቀረም። አይቀይሩትም። የጥንድ ቁጥሩ የእድገት ፕሮፓጋንዳ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት ሰፍኗል የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሰፍኗል … ፕሮፓጋንዳዎች መሰረት በዚሁ የህዝብ ግንኙነት ፍልስፍና መሰረታቸው ላይ የቆመ ነው።

ወልቃይትን ያስጨነቀው ዋና ጉዳይ ወሰኑ ተከዜ ነው ምናምን ሳይሆን የማንነቱ ጉዳይ ነው። ጨዋታው የብሔር ፖለቲካና ፌደራሊዝም በመሆኑና፤ እኔ ደግሞ ያለ ዘውጌ በመገኘቴ ለማንነቴ ችግር ፈጥሯል ነው የሚለው ወልቃይት። ፍትሃዊ ጥያቄ ነው። ወልቃይት እንደው የዴሞክራሲውንና የልማቱን ጉዳይ ተዉትና ሥርዓቱ ወይም ሲስተሙ ለማንነቴ አደጋ ፈጠረ ነው የሚለው። ትክክለኛ ጥያቄ ነው።

የወሰኑ ጉዳያ ብዙ ስሜት አይሰጠኝም። ይህ ከማንነት ጋር የተያያዘ ወሰን በአዲስ ኪዳን መፍረሱ ስለማይቀር። የአማራ ህዝብ ወሰኑ ሞያሌ፣ ኢሉባቦር እስከ ኦጋዴን ነው፣ የትግራይ ህዝብ ወሰኑ ተከዜ ሳይሆን ኦጋዴን፣ ሞያሌ፣ ኢሉባቦር ባራቱም ማዕዘናት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ወሰኑ ሳንጃ ቋራ እስከ ኦጋዴን እስከ ትግራይ ድረስ ነው። የደቡብ ህዝብ ወሰኑ ጠገዴ ኦጋዴን አማራ ትግራይ ጫፍ ድረስ ነው። አፋሩ፣ ሐረሪው፣ ጋምቤላው፣ ቤንሻንጉል ጉሙዙ፣ ኦጋዴኑ ሁሉ ድንበሩ ባራቱም ማዕዘን ነው። ይህ ነው ድንበራችን። አባቶቻችን ያስተማሩን ድንበር የሚባለው ነገር ይሄ ነው። በየቀበሌው የተገኘ ወንዝና ቦይ ሁሉ ድንበር አይባልም። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃል ወደፊት ድንበር መኖር የለበትም። ሁለት ሀገር ሆነውም ድንበር አያስፈልጋቸውም። አፍሪካውያን ዛሬ እየተራመዱ ነው። ማንም አፍሪካዊ የትም ሀገር ያለ ቪዛ ሊሄዱ ነው።

አሁን ያለው የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ሲሆን ማንነቱ ዘውጉ ውስጥ ተጠብቆ እንዲኖር ብዙ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ለማድረግ ወደሚያስችለው ክልል መሄድ አለበት። ማንነቱ ሲነካ የሚወድ የለም። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ተነስቶ ሆ ብሎ የሚታገለውን የወልቃይትን ህዝብ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊደግፉት ይገባል። ለወደፊት ግን ጎበዝ ሀገራችን አዲስ ኪዳን ውስጥ መግባት አለባት። እነዚህ ሰዎች ለኤፈርት ሀብት ሲሉ ሀገሪቱን ከባድ ችግር ውስጥ ዘፍቀዋታል።

ሀገራችን ማኅበራዊ ጉዳዮቿንና ይህን የፖለቲካ ጉዳዮቿን ሳይጋጩ የምታስኬድበትን አዲስ ሥርዓት መከተል አለብን። ማኅበራዊ ጉዳይን ከፖለቲካ ማላተም ሀገርን ያፈርሳል። ኢኮኖሚን ይጎዳል። እነዚህ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ ማኅበራዊ ጉዳይና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደየ ባህርያቸው በዴሞክራሲ መርኆዎች መተዳደር አለባቸው። በተለይ አሁን በዚህ ሁኔታ ውስጥ የቆየች ሀገር ያለባትን ዙሪያ መለስ ችግር የሚፈታላት አዲስ ቃል ኪዳን ውስጥ መግባት ብቻ ነው። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ ሌላ ውይይት ለማድረግ ጽሁፍ ተዘጋጅቷል። ለአሁኑ መብቶቻችንን ለማስከበር ሁላችን በአንድነት እንነሳ። እንደ አንድ ዜጋ ወንድም በተለይ ወጣቱን እማፀናለሁ።

በተለይ ለትግራይ ህዝብ አንዲት ነገር መናገር እሻለሁ። በውነት የትግራይ ህዝብ ሆይ ጸጋ በዝቶልሃል። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በጣም ሲጠነቀቅልህ አያለሁ። ፖለቲካው ወደ ዘር ጥላቻ የሚወስድ ሆኖ እንኳን ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ተጠንቅቀው ወያኔንና ትግራይን ለይተናል እያሉ ሲታገሉ ድፍን ሃያ አራት ዓመት አለፈ። ከትግራይ አንድ ተቃዋሚ ወጣት ብቅ ሲል ጭብጨባው ሌላ ነው። ራሱ ወያኔ ለፖለቲካ ትርፉ የሚጠቀምባቸው ሰዎች ትግራይ ለወያኔ እንዳደረ ይናገሩ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ አክብሮህ ተጠንቅቆልሃል። ወያኔ አለኝ የሚለው ማኅበራዊ መሰረት ትግራይ ነው። ታዲያ ለትግራይ ወጣቶች ያለኝ ምክር ምንድነው? ልክ እንደዚህ አንተም ይህን ግፈኛ ሥርዓት በቀጥታ በመቃወም አሳይ። የኦሮሞ ወገኖችህን ጥያቄ ከፍ አድርግ። የወልቃይትን ህዝብ ደግፍ። ይህ ድጋፍህ በሰልፍ ብቻ አይደለም የሚገለፀው። አብሮህ ለሚኖረው ኦሮሞ አብሮህ ለሚኖር አማራ የፍትህ ወገንተኝነትህን አሳይ። ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በድጋፍ አጨናንቅ። ወያኔ ተቃዋሚውን ለማጃጃል፣ ሕብረትን ለማፍረስና ለመጉዳት መጠቀሚያ ሊያደርግህ ሲሞክር እምቢኝ በማለትና ይህን አሳፋሪ የወያኔ የህዝብ ግንኙነት መረብ በመበጠስ ሀገርህን ታደግ። በተለይ በውጭ ሀገር የምትኖሩ የትግራይ ልጆች ወንድሞቼና እህቶቼ ወያኔን የሚቃወሙትን የፖለቲካ ሰዎች አክቲቪስቶች ባሉበት ስነ ልቡናቸውን በመጉዳት ሕብረታቸውን በማፍረስ በመካከላቸው ፍቅር ጠፍቶ እንዲጣሉ ትግሉ እንዳያድግ ለማድረግ እንደ ታማኝ መሣሪያ ሊጠቀምባችሁ ሲያስብ እምቢኝ በሉ እንደውም እያጋለጣችሁ ሀገራችሁን ታደጉ። እንዲህ አይነት በባህላችን የሌለ የወያኔ አፍራሽ ሥራ በእግዚአብሔር እጅም ያስቀጣል።

በቅርቡ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር አወጋ ነበር። እንዲህ አለኝ። የትግራይ ሰው እኮ ከ90 በመቶ በላይ ወያኔን ይደግፋል አለኝ። ይህ ሰው ይህን እንዴት ሊል ቻለ ብየ አሰብኩ። ይህን ያስባለው በአካባቢው ካሉ እሱ ከሚያውቃቸው ጥቂት የትግራይ ልጆች ጋር ተወያይቶ ሲደግፉ በማየቱ ሊሆን ይችላል። ወይም አንድ ወያኔ የተወሰኑ የትግራይ ሰዎችን ወደዚህ ሰው እየላከ ትግራይን እንዲጠላ እንዲያጠቃልል አድርገውት ሊሄን ይችላል። ይህንን የሱን ዓለም አጠቃሎ ነው ከዘጠና በመቶ በላይ የትግራይ ህዝብ ይደግፋል የሚለኝ። እኔ ደግሞ ለራሴ ማሰብ ጀመርኩ። ከማውቃቻው ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ውስጥ ሁሉም ማለት እችላለሁ ወያኔን ከልብ አይደግፉም ነበር። ከቅርቦቹ ማለቴ እንጂ ድርቅ ያሉ የወያኔ ደጋፊዎችንም አይቻለሁ። በቅርብ በተደጋጋሚ ያየኋቸው ግን ተጠቃሚም አይደሉም አደግፉምም። እንደውም አንዱ የትግራይ ልጅ ገና በፊት እንዲህ አለኝ።

ገለታው

አቤት

እንደው ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ሌላ ሀገር አላቸው ወይ? ሌላ ሀገር በድብቅ አስቀምጠው ነው ወይ ይህቺን ሀገራቸውን እንዲህ የሚጎዱት? አለኝ።

አላውቅም ብየ ተደምመን ተለያየን።

ምን ለማለት ነው? ሰው በአካባቢው ያለውን እየቆጠረ ስለሆነ ያለው የትግራይ ልጆች ይህንን ከግንዛቤ ቢያስገቡ ጥሩ ነው። ህወሓትን መደገፍ ከዴሞክራሲ መብት ጋር ስለማይገናኝ ነው ይህን የምለው። ሀገራችን እውነተኛ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ስትገባ ያኔ ሰው የፈለገውን ይደግፍ ይባላል። ወያኔ ሀገር አጥፊ ነው። አይማርም። ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኔ ደግሞ ትግራይን ይረዳው። እርስ በርስ መረዳት ነው ትልቁ ትግላችን። ወያኔ ምንም እንኳን ማኅበራዊ መሰረቴ ትግራይ ነው ቢልም ህወሓት የትግራይ አምባገነናዊ መሪ ነው። የትግራይ ህዝብ በዚህ አምባገነን ሥርዓት ስር እንዳለ መረዳት ተገቢ ነው። እንዲህ ስናደርግ እርስ በርስ መተማመን ይጨምራል። አይዞን ወገን በያለንበት። አይዞን ወልቃይት። ሁላችን በጋራ ትግላችን ኢትዮጵያችንን ወደ አዲስ ኪዳን እናመራና ዘረኝነት ይቆማል። ዴሞክራሲ ያብባል። የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገነባለን። ይህቺ አዲሲቱ ኢትዮጵያ በሁላችን የሁላችን ለሁላችን ትሆናለች። አማራውም ጎንደር የቀደሰውን ደባርቅ እንደተከተለ ትግሉ ይቀጥል። ኦሮሞው ጥያቄው ሳይመለስ አያርፍም። ደቡቡም ይነሳ! ሁላችን በጋራ እንታገል። የጋራ ትግል የጋራ ድልን ያመጣና ሀገራችንን ወደ ተሻለና የተረጋጋ ሥርዓት ይመራልናል። ይሄው ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አክባሪ ወንድማችሁ፣

ገለታው ከሩቅ ምስራቅ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ