ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ

ሌተናል ጄኔራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ Photo – General Tsadkan during an interview with HornAffairs. Feb. 2015

መግቢያ

ከሃያ አምስት ዓመት ኢህአዴግ የደርግን መንግሥት በጦርነት አሸንፎ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡ ፖለቲካዊ ችግሮች በግልፅ ጎልተው መታየት ጀምረዋል። አሁን ገዥው ፖርቲና ፖርቲው የሚመራው መንግሥትም የችግሮቹን መኖር አምኖ ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መንገር ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህ ሁኔታ ለማንኛውም የሀገሩን ደህንነትና ሰላም፤ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ብልፅግና፤ ለሚመኝ ሀገር ወዳድ ዜጋ ያሳስባል። ከዚህ አንፃር የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው።

የትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ያኔ ሁኔታው በፈቀደው መሰረት በህዝብ ተሳትፎ ሕገ መንግሥት አፅድቀን በዚህ ሕገ መንግሥት እየተመራን መጓዝ ከጀመርን ሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥረናል። በነዚህ ያለፍንባቸው ዓመታት ብዙ የተመዘገቡ ድሎች ያሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መሰራት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮችም አሉ። በዚህ ፅሁፍ በዋናነት መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች በተለይ ደግሞ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ፣ የተረጋጋ ለኢኮኖምያዊ እድገትና ለማህበራዊ ብልፅግና የተመቻቸ እንዲሆን ለማስቻል የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ለአሸናፊ ፖለቲካዊ ኃይል እንዲተላለፍ ለማስቻል፣ አሁን የሚታየውን ያለመረጋጋት በፖለቲካው ስራ ምን ቢሰራ የተሻለ መረጋጋት ሊፈጠር ይችላል። በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳቤን ለማካፈል ነው።

ይህ አጭር ፅሁፍ ስድስት ክፍሎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ችግሮቹ ምንድን ናቸው መንስኤያቸው ምንድን ነው የሚለውን ጉዳይ ይዳሰሳል፣ ቀጥሎም ይህ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት እያደገ መጣ ወደየት ይወስደናል ያሉት አማራጮች ምንድን ናቸው የሚለው ሃሳብ ያነሳል፣ ከዚህ ቀጥሎ የትግራይ ህዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን ምን ዓይነት ቦታ ላይ ያስቀምጣል የሚለውን ጥያቄ በማንሳት አስተያየቴን አስቀምጣለሁ። ከዚህ በኋላ አሁን እያደገ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ የፀጥታ ኃይሎች በተለይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እጅን በማስገባት ሊፈታው ይችላል ወይ በሚል ጥያቄ ላይ ያለኝን አስተሳሰብ እገልፃለሁ፣ ቀጥሎም ከዚህ አሁን በግልፅ እየታየ ካለው ፖለቲካዊ ቀውስ እንዴት መውጣት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ የሚታየኝን ሃሳብ አቀርባለሁ። በመጨረሻም ማጠቃለያ ሃሳብ ይኖራል።

እንግዲህ በሃሳብ አቀራረቡ በግልፅ እንደሚታየው ይህ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንፍታው፣ ችግሩን ለመፍታት ደግሞ በኢህደአዴግና ድርጅቱ በሚመራቸው የመንግሥት ይሁን የፖርቲ መዋቅሮች ታጥረን በምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም። ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው መዋቅር በተጨማሪም ከየፖርቲና የመንግሥት መዋቅር ውጭ ያሉ ፖለቲካዊ ኃይሎችና ምልዓተ ህዝቡ በስፋትና በንቃት ሲሳተፍበት ነው በእርግጠኝነት ችግሩን መፍታት የሚቻለው ከሚል መነሻ ሃሳብ የሚነሳ ነው። ይህ ደግሞ በከፍተኛ የህዝቦች መስዋዕትነትና ተሳትፎ የፀደቀውን ሕገ መግስታችንን መሠረት አድርገን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፖለቲካዊ ኃይሎችም ያለምንም ተፅዕኖ ያልተገደበ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድርገው በመጨረሻም በገለልተኛ በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነፃ ዴሞክራዊያዊና ያለምንም ተፅዕኖ የተከናወነ ምርጫ መሆኑ ተረጋግጦ የተካሄደ ምርጫ የሚሰጠንን ውጤት ተቀብለን ለመጓዝ ቆርጠን ስንነሳ ነው በሚል አስተሳሰብ ላይ ያጠነጥናል። ይህ ፖለቲካዊ ሂደት ብዙ ስራና ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ ከአሁኑ መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ።

በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት በመጠቀምና ይህንኑ ያለመረጋጋት በማባባስ፣ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሄድ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለእነዚህ የውጭ ኃይሎች ለማገልገል በመወሰን የሚንቀሳቀሱ የሀገራችን ኃይሎችም አሉ። እነዚህ ኃይሎ በጋራ የሚፈጥሩትን ፓለቲካዊ ያለመረጋጋትና ከዛም ያለፈ ቀውስ መቋቋምና ማሸነፍ የምንችለው ሀገር ወዳድ የሆኑ ፖለቲካዊ ኃይሎች በሚያማማቸው ፖለቲካዊ መድረሻ ተገናኝተው በመጀመሪያ የሀገራችንን የራሳችንን ችግሮች ስናስወግድ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱን መነሻ በማድረግ ሊጀመር ይችላል ብዬ አምናለሁ። ይህ ቢሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች በቅንጅት በሀገራችን ሊፈጥሩት የሚፈልጉትን ቀውስ ማሸነፍ እንችላለን። አለበለዚያ ለእነዚህ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ካልፈጠርንላቸው ቀውሱን ለመፍታት እየተቸገርን እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ።

ሀገራችን ያለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ

ሀገራችን በአሁኑ ግዜ እጅግ ባልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው የሚል እምነት አለኝ። መንግሥት የሚያወጣቸው መግለጫዎችም ይህንኑ ያመላክታሉ። ሰፊ የመልካም አስተዳደር እጦት እንዳለ፣ በግልባጩም ብልሹ አስተዳደር በተለያዩ መንግሥታዊ መዋቅሮች እንደተስፋፋ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከፍተኛ እንደሆነ፣ የመንግሥት ገንዘብና ንብረት ብክነት በስፋት እንደሚታይ፣ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በግዝያቸው እንደማይጠናቀቁ ይህ ደግሞ ሀገሪቱን ለክፍተኛ ችግር እያጋለጣት እንደሆነ ይገለፃል። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች (የማንነት ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ ተተቃሚነት ጥያቄ፣ የፍትሕ መጓደልና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ወዘተ) በኦሮምያ፣ በደቡብ ህዝቦች፣ በአማራ፣ በትግራይ የህዝብ መነሳሳትና መንግሥት ጥያቄዎቹን እንዲፈታላቸው በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ ይገኛሉ።

በርግጥ እንደ ሀገራችን ያሉ ኋላ ቀር ሀገሮች የተደላደለ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት እንዲኖራቸው ብዙ ፈተናዎችንና መሰናክሎችን ማለፍና ቀላል ያልሆነ ግዜ መፍጀት እንደሚጠበቅባቸው ይታመናል። ምክንያቱም የሕብረተሰቡ ማህበረ ኢኮኖምያዊ የእድገት ደረጃ የሚያስቀምጠው የግድ መታለፍ ያለበት መሰናክሎች ስላሉ። ይህ የሀገራችን የዕድገት ደረጃ የሚያስቀምጥልን ተፅእኖ ተጨባጭ ተፅእኖ እንደሆነ አውቆ በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሁነን እየሰራን እንዳለን ታውቆ ካለንበት ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና ስትርቴጂዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ዋና መነሻ ሕገ መንግሥት ነው ብየ አምናለሁ።

ይህ ከላይ የተገለፀው ማህበረ ኢኮኖምያዊ የዕድገት ደረጃ የሚፈጥረው ተጨባጭ ተፅእኖ እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን ሁኔታ ያገናዘቡ በማነኛውም ደረጃ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ያኔ ሁኔታው የፈቀደው ህዝባዊ ተሳትፎ በተደረገበት መንገድ የፀደቀ ዴሞክራስያዊ ሕገ መንግሥት አለን። ይህ ሕገ መንግሥት ህዝቦች ፈቅደው እንዲመሩበት ያወጡት የሀገሪቱ የመጨረሻ ሕግ ነው። ሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ የሆነ የሀገራችን መንግሥት አወቃቀርና አሰራር፣ የግለሰብ ይሁን የቡዱን ሰብዓዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በሚገባ ያካትታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ተቀባይነት አግኝተዋል። ይህ በአዲስ መንፈስ ተፈጥሮ ለነበረው የመንግሥት ግንባታ (State Building) ጥሩ መነሻ ነበር።

ሕገ መንግሥቱ በህዝባዊ የትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብዮታዊና ዴሞክራስያዊ መንፈስ የተላበሰ ኢህአዴግ በሚመራው መንግሥት እንዲኖር የሚፈለገውን የመንግሥት አሰራርና ባህርይ መለክያ (Standard) ይሆናል ብለን ያስቀመጥነው የትጥቅ ትግሉ ድሎች መቋጫ ነበር እላለሁ። የኋ ኋላ ግን ኢህአዴግ ከሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች፣ በተለይ ደግሞ ኦነግ ጋር በቅንጅት ያስቀመጠውን የመንግሥትን አሰራርና ባህርይ መለክያ ይሆናል ያለውን መተግበር እያቃተው ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ መንገድ እየገባች ነው።

ከዛ በኋላ ያለው ሁኔታም ሲታይ በርካታ አዎንታዊ ዕድገቶች ተመዝግበዋል። ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ የሀገራችን ህዝቦች ከነችግሮቻቸውም ቢሆን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርን ልምድ አግኝተዋል። ከዚህ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ልምድ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርና መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ቢጠቀሙ የሚኖረውን ጠቀሜታ ማየት ጀምረዋል። ሕገ መንግሥቱ በተግባር ላይ ሲውል እንዲሁ በፁሁፍ እንደተቀመጠው አለመሆኑና አተገባበሩ ላይ ያለውን ጉድለቶችና ችግሮች አውቀዋል። በነዚህ ባለፉት ከሃያ በላይ ዓመታት ደግሞ በተሰራው ማህበረ ኢኮኖምያዊ ስራ ሕብረተሰቡ ስለመብቱ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ከነበረው በላይ የተሻለ ግንዛቤና ሕገ መንግሥቱ እንዲተገበር ዕውቀትና ፍላጎት አለው። በርካታ የተማረ የሰው ኃይል ተፈጥሮአል። በሀገርቱ የተዘረጋው የመንገዶች የመገናኛ አውታሮች ሕበረተሰቡ በቀላሉ እንዲገናኝ፣ እውቀቱና የሚያገኝው መረጃ የዳበረ እንዲሆንም አስችሎታል። ከዚህ ጋርም ከውጪው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነትም በበርካታ ገመዶች እየተተበተበ ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል። ይህ ማለት የግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ከነበረው ሁኔታ የበለጠ ነው ማለት ነው።

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በድምር ሲታይ የሕብረተሰቡ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያለው አስተሳሰብና ለመሳተፍ ያለው ፍላጎትና እውቀት ጨምሯል። በአጭር አነጋገር ዴሞክራስያዊ ሥርዓቱ እንዲሰፋ ይፈልጋል። ቢያንስ በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መንግሥት እነዚህን በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች የሚገድቡ አሰራሮችና መመርያዎች በማውጣት ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ እያጠበበው ይገኛል። ይህ ሁኔታ በሀገራችን ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ አንድ ትልቅ ምክንያት ነው።

በሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጣቸውን ስብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ አለመተግበርና፣ ይባስ ብሎም ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ እየጠበበ ለመሄድ ሁለት እርስበርሳቸው የሚደጋገፉ ምክንያቶች አሉ ብየ አምናለሁ። አንደኛው የፖለቲካ ሥርዓቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ወሳኝ ድርሻ ነው። እነዚህ በመደጋገፍ የስራ አስፈፃሚውን የመንግሥት ክፍል የውሳኔ ሰጪነት የኃይል ሚዛን ከሌሎች ክፍሎች የበለጠ እንዲያመዝን በዚህም የተጠያቂነት አሰራር እንዲቀጭጭ፣ ቀስ በቀስ ደግሞ ህዝብ መንግሥትን እንዲቆጣጠር እየተገባው የስራ አስፈፃሚው ህዝብን አስፈርቶ የፈለገውን እያደረገ የሚሄድበት ሁኔታ ተፍጥሯል። አሁን መንግሥት እየገባባቸው ላሉት የተለያዩ ችግሮች ምንጫቸው ይህ የገዢው ፓርቲና የስራ አስፈፃሚው አካል ገደብ የሌለው ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ሥልጣንና ኃይል ነው። እነዚህ በየተራ እንያቸው።

ፖለቲካዊ ሥርዓቱ

ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ስንነሳ የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ዋነኛ ችግር በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ያለው ግንኙነት ፈፅሞ ጠፍቶ ገዢው ፓርቲና መንግሥት አንድ ከመሆናቸው የሚመነጭ ነው። በተለያየ ግዜ በብዙዎች በሞያው ጠለቅ ያለ እውቀት ካላቸው ሊቃውንት እንደተገለፀውና በረጅም የሰው ልጆች ታሪክ እየተረጋገጠ የመጣው የመንግሥት አወቃቀር ልምድ እንደሚታወቀው መንግሥት ሦስት ትልልቅ ክፍሎች አሉት። የስራ አስፈፃሚው፣ የሕግ አውጪው እና የሕገ አተረጓጎም (አፈፃፀም) ሥርዓቱ ናቸው። እነዚህ አካላት የስራ ክፍፍላቸው፣ የሥልጣን ዳርቻቸው በግልፅ የታወቀ አንዱ አንደኛውን እየተቆጣጠረ ሕግ ባስቀመጠለት ገደብ ውስጥ ብቻ ሆኖ እየሰራ መሆኑ እየተያዩ የሚሰሩበት ሥርዓት እንዲኖር ነው ጥረት የሚያደርገው። የዳበረ ኢኮኖሚ ባላቸውና ይህንን ኢኮኖሚ መነሻ አድርገው ዴሞክራስያዊ ሥርዓታቸውን ረዘም ባለ ግዜ የገነቡ ሀገሮች ታሪክ እንደሚገልፀው የሥልጣን ክፍፍሉ ሥርዓት ከመንግሥት አካላት አልፎ በሕብረተሰቡም ውስጥ ይታያል። የፖለቲካ ኃይሉና የኢኮኖሚ ኃይሉ ተነፃፃሪ ነፃነት ኖሯቸው በዚህ ሥልጣን መሰረት የመንግሥቱ አወቃቀርም የተስተካከለበት አካሄድ እናስተውላለን።

ከነዚህ ከላይ የተገለፁት የመንግሥት አካላት የሕግ አውጪው ክፍል (ፓርላማ) በቀጥታ ከህዝብ የተመረጠ ስለሆነ የተለያዩ የሕብረተሰቡ አስተሳሰቦችንና ጥቅሞችን የሚወክል እንዲሆን ነው የሚጠበቀው። ይህ የሕግ አውጪው የመንግሥት ክፍል ዋናው ስራው ሕግ ማውጣትና የስራ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል መቆጣጠር ነው። የስራ አስፈፃሚው በመንግሥት ሥልጣን እና ሃብት የማዘዝ እና ስራዎችን እለት ተእለት የማስፈፀም ሥልጣን ስላለው ይህንን ሥልጣኑን ያለአግባብ የመጠቀም እድሉ የሰፋ ነው። የሕግ አውጪው አካል ህዝብ በውክልና የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም የስራ አስፈፃሚው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ በመውጣት የህዝቦችን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንዳይጥስና የሀገርን ጥቅም እንዳይጎዳ ይቆጣጠራል። አስፈላጊ ሲሆንም ይህንን የሚገድብ ሕግ ያወጣል።

ይህንን ስራ በታሰበው መንገድ ለመስራት እንዲያስችለው ደግሞ ለሕግ አውጪው ተጠሪ የሆኑ የተለያዩ አካላትን ያቋቁማል፤ ከነዚህም ውስጥ የሰብዓዊ መብት ኮሚሺን፣ የኦዲት ኮሚሽን፣ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሌሎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ አወቃቀር ከማንኛውም ፖርቲ ጋር መዋቅራዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው የማይፈልጉ አካላትም የዚህ የመንግሥት አካል ተጠሪዎች ይሆናሉ። እዚህ ውስጥ ለምሳሌ የፕሬዝዳንቱ መስሪያ ቤት፣ ሠራዊቱ፣ ቢሮክራሲውም በዚህ ይጠቃልላል። እነዚህ በድምር በእንግሊዝኛው አጠራር ስቴት (state) ተብሎ የሚታወቀውን ስያሜ ይይዛሉ። እዚህ ታሳቢ የሚሆነው ነገር ምንም እንኳን ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት የስራ አስፈፃሚውን የመንግሥት ክፍል በአንድ የምርጫ ዘመን የሚቆጣጠረው አንድ ፓርቲ ቢሆንም በሕግ አውጪው (ማለት በፓርላማው) ውስጥ ግን የብዙ ፓርቲዎች አስተሳሰቦች ውክልና ስለሚኖር የሕብረተሰቡን ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ይንፀባርቃል። በሕግ አውጪው የሚቋቋሙት ኮሚሽኖችም ይህንን ስብጥር ያንፀባርቃሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፤ ስለዚህ ስቴት በሚባለው ስያሜ ውስጥ ያሉት አካላት ብዙ ግዜ የሀገሪቱን ዘለቄታዊ ጥቅም ያስጠብቃሉ የሚላቸውን ፖሊሲዎችንና ስታራቴጂዎችን በማውጣት የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እንዲሆን በማስቻል በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ሕገ መንግሥቱን ጠብቀው ሲያሸንፉ ሥልጣን እንድይዙ፣ ሲሸነፉ ደግሞ ሥልጣኑን እንዲለቁ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛው ተግባሩ ይሆናል። የተረጋጋ ሰላማዊ ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት በቅጡ እንዲሰራ ማስቻል ዋነኛው ተግባሩ ስለሆነ አንድ በአንድ ወቅት አሸንፎ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ ለዘላለም በሥልጣን ላይ እንዲኖር ዋነኛ ስራውን አያደርግም።

ከዚህ ቀጥሎ የሀገሪቱን ሕግ ተከትሎ ባንድ ወቅት በምርጫ ተወዳድሮ ያሸነፈ አንድ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚውን ዋነኛ የሥልጣን ቦታውዎች ይቆጣጠራል። ይህ ሁኔታ ከሀገር ሀገር እንደ ሕገ መንግሥቱና እንደ ምርጫው ውጤት ሊለያይ ይችላል። አንድ የፖለቲካ ፖርቲ ብቻውን ሥልጣን የማይቆጣጠርበት ሁኔታ ከተፈጠረ ፖርቲዎች በቅንጅት ሥልጣን የሚጋሩበት ሁኔታ ሲመጣ የሥራ አስፈፃሚው የሥልጣን ክፍፍሉም በዚሁ መሠረት ይስተካከላል። በሀገራችን አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫ ያሸነፈ ኃይል የስራ አስፈፃሚውን የመንግሥት ክፍል ይቆጣጠራል። ይህ ፓርቲ በምርጫ ወቅት እሰራዋለሁ ያለውን ስራ ለህዝብ አቅርቦ በህዝብ ተመርጦ ለአምስት ዓመት እንዲያስተዳድር እድል የተሰጠው ፓርቲ ነው። የገባውን ቃል ለማስፈፀም እንዲመቸው የስራ አስፈፃሚውን የመንግሥት ክፍል ይቆጣጠራል። ከዚህ አልፎ ግን የሕግ አውጪውንና የሕገ መተርጎም (Judicial System) ሥርዓቱንም የሚቆጣጠር ወይም በሥራ አስፈፃሚው ጫና ውስጥ እንዲሰሩ የሚያስገድድ ከሆነ ሥርዓቱ ይፋለሳል። ይህ ለተወሰነ ግዜ ሀገር እንዲያስተዳድር በምርጫ ሥልጣን የተሰጠው የግዜው መስተዳድር ረዘም ላለ ግዜ እሱን እንዲቆጠጠሩ የተቋቋሙትን የሕግ አውጪውንና እሱ የሚመራቸው የተለያዩ ኮሚሽኖች፣ የሚቆጣጠር ከሆነ ሥልጣኑ ገደብ የለሽ ይሆናል።

ከሕግ አውጪው በተለየ መንገድ ደግሞ የሕግ አተረጓጎሙ ሥርዓት አለ። ይህ የስራ አስፈፃሚው አካል ከሕግና ከተፈቀደለት የሥልጣን ገደብ አልፎ ስህተት የፈፀመ እንደሆነ ህጉን ለመተርጎምና በዚህ መሠረትም ጥፋተኛውን ለመቅጣትና ለማረም ተብሎ የተቋቋመ የመንግሥት ክፍል ነው። በርግጥ የመንግሥትን ባለሥልጣናት ብቻ አይደለም የሚቀጣው፤ አሁን በምናነሳው ጉዳይ ግን ዋናው ትኩረታችን የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ሀገር ሕግን በመጣስ በህዝቦች፣ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ወንጀል መፈፀም የሚችሉት በሀገር ሃብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ስህተት ወይም ወንጀል የሚፈፅሙት የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ናቸው። ስለሆነም በሀገር ከፍተኛ ጥፋት የሚያመጣ ጥፋትን፤ የዳኝነት ሥርዓቱ ከስራ አስፈፃሚው ነፃ ሆኖ የስራ አስፈፃሚውን ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የዜጎችን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ሲጥሱ የህዝቦችን መብት ሲጋፉ ያገር ሃብት ሲዘርፉ ወይም ሲያባክኑ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከስራ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት።

አሁን በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ሥርዓትና አስተዳደር ከዚህ የተለየ ነው። የሕግ አውጪውን አንድ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል፤ ይህ ፓርቲ ደግሞ በዴሞክራስያዊ ማዕከላዊነት መርህ የሚመራ ነው። ይህ ማለት የፓርቲው አባላት በማነኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ካሉ የፓርቲውን ፖለቲካዊ አቋም ማራመድ፣ መፈፀም እና ማስፈፀም አለባቸው። (በግላቸው የማያምኑበት፣ የማይቀበሉት ነገር ቢሆንም) ከዚህ ስንነሳ መቶ በመቶ የሕግ አውጪውን የተቆጣጠረ ፓርቲ ለሕግ አውጪው ተጠሪ የሆኑቱን የተለያዩ ኮሚሽኖችንም ይቆጣጠራል። የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብና ጥቅሞች የሚንፀባረቁበትን የሚንሽራሸሩበትን ፓርላማ የአንድ ፓርቲ ድምፅ ብቻ የሚያስተጋባበት መድረክ ይሆናል። በአንድ ወቅት የተመረጠን የፖለቲካ ፓርቲ ያቋቋመውን የተወሰነ ግዜ መስተዳድር በሕጉ መሰረት እየሰራ መሆኑን መቆጣጠር ቀርቶ ዋናው የስቴት አሰራርና መዋቅር ለስራ አስፈፃሚው እንደሚመች ያደርግለታል ማለት ነው። በፖለቲካዊ ፓርቲ፣ በስቴትና በወቅቱ መስተዳድር ያለው የሥልጣን ክፍፍል፣ ቁጥጥር በሙሉ ይጠፉና ስራ አስፈፃሚው በፈለገው መንገድ ሁኔታዎች ይመቻቹለታል ማለት ነው። በሀገራችን ያለው ሁኔታ ይህ ነው።

ይህ ከላይ የተገለፀው ሁኔታ ኢህአዴግ ስራዬና፣ ፕሮግራሜ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ ያመጣሁት ውጤት ነው ይለናል። እዚህ ማለት የምፈልገው ኢህአዴግ ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመረጡ ቀስቅስ የሚለው የለም። ግን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ከሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች ጋር ሆኖ ይስራ። ይህንን የሚገድቡ የተለያዩ መመሪያዎችና አሰራሮችን ያስወግድ የመጫወቻ ሜዳውን ለሁሉም ለራሱም ጭምር እኩል እንዲሆን ያድርግ። ሌሎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመመሪያዎችና ህጎች አይገድባቸው። ህዝብ ላይ የተጫነውን በፀጥታ ኃይሎች አስፈራርቶ የማስተዳደር አካሄድ ይነሳና በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚፈጠረው ችግር ይወገድ። እንደ ማነኛውም ፓርቲ ኢህአዴግም የፖለቲካ ቅስቀሳውን ያካሂድ፣ በኋላም የምርጫውን ውጤት በፀጋ ይቀበልና ውጤቱን እንየው።

አሁን በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ሥልጣን ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ የሚሸጋገርበት ሁኔታ እጅግ በጣም ጠባብ የሆነበት በመሆኑም በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በዚህ አጭር ፁሁፍ በመንግሥት (state) በግዜው መስተዳድር (regime)እና በምርጫ አሸንፎ ለተወሰነ ግዜ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ (incumbent party) ምንነታቸውና በመሃከላቸው ያለውን ዝምድና በሰፊው ለመግለፅ አይመችም፤ ሆኖም በእነዚህ አካላት ያለው ግልፅ የሥልጣን ክፍፍል፣ የስራ ዝምድና ካልታወቀና ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ካልዋለ አሁን ሀገራችን ውስጥ የሚታየውን በሕገ መንግሥት እውቅና ያገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች ሲጣሱ የሚያስቆምና የሚቆጣጠር አካል ይጠፋል። ለተወሰነ ግዜ ሥልጣን የያዘው ፓርቲ በስራው ጥራት ተቀባይነት እያገኘ ዳግመኛ እየተመረጠ የሚሄድበት ሁኔታ ጠፍቶ ፓርቲው ባወጣቸው አዋጆችና መመርያዎች ፖለቲካዊ ምህዳሩን በማጥበብ ዕድሜውን የሚያራዝምበት ሁኔታ ይፈጠራል። የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በሥልጣን መባለግ፣ ሙስና በግልፅ መንግሥት በሚያምንበት ደረጃ ቢታወቅም ፓርቲው (የሥልጣን ግዜውን ለማራዘም ውስጠ ፓርቲ ቀውስ ተፈጥሮ እንዳይዳከም) በቁርጠኝነት አይዋጋቸውም። በአጠቃላይ አንድ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት እየዳበረ መሄዱ የግድ ተፈላጊ የሆነው የቁጥጥርና የተጠያቂነት ሥርዓት በተለያዩ የሕብረተሰብ ውክልና ያላቸው ፖለቲካዊ ተቋማት የማይደረግ ስለሆነ የአንድ ፓርቲ ስራ ተደርጎ ሰለሚወሰድ ለማረምም ለማስተካከልም አስቸጋሪ ሆኗል።

ይህ ሁኔታ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ብቻ የሚመለከት አይደለም፤ ሌላ ፓርቲ ሥልጣን ቢይዝም መሰረታዊ አወቃቀሩ አሁን ካለበት ካልተለወጠ ይብስ እንደሆነንጂ አይሻሻልም። የአንድን ሀገር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማስተካከልና ዜጎችዋን የሚጠቅም፣ ዜጎቹ በየግዜው እየወደዱትና እየተደሰቱበት እንዲሄድ የማድረግ የረዥም ግዜ ስራ ቅን ሐሳብ ላለው አንድ ሰው ወይም እሚበጅህን እማውቅ እኔ ብቻ ነኝ ለሚል አንድ ፓርቲ የሚተው ጉዳይ አይደለም። ዜጎች በትግላቸው በየግዜው እያስተካከሉት፣ እንዲመቻቸው እያደረጉት የሚሰራ ጉዳይ ነው። በሀገርችንም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይገባም፤ አይችልምም።

ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ሥርዓታችን ጉዳይ ነው። አሁን ያለው የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ታሪካዊ አስተዳደጉ የዜጎች በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የሌለው መንግሥት በአጠቃላይ የስራ አስፈፃሚው ክፍል ደግሞ በተለይ የፈለገውንና ያመነበትን ለማድረግ የሚከለክለው የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው። ምንም እንኳን በቅርብ ግዜ የመንግሥት ግብር የመሰብሰብ አቅም እየተጠናከረ የመጣ ቢሆንም፤ የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ልማት ዝቅተኛ በመሆኑ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢም መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት በሀገሪቱ ስራ ለመስራት የሚያስፈልገውን ትልቁን ገንዘብ ከውጭ ሀገር (በእርዳታ ወይም በብድር አሁን ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መልክ) ነው እሚያገኘው። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ራሱ ከሚቆጣጠራቸው የልማት ድርጅቶችና ከሀገር ውስጥ ገቢ በሚያገኘው ነው እሚንቀሳቀሰው። ይህ ማለት መንግሥት ሰፊ የሆነ ኢኮኖምያዊ ነፃነት አለው ማለት ነው። ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በተወካዮቹ በኩል (በፓርላማ) አድርጎ ፖሊሲዎቸን በስራ አስፈፃሚው የመጫን ጡንቻው በጣም ደካማ ነው። የፖለቲካ ሥልጣን የያዘ ኃይል በሀገሪቱ ኢክኮኖምያዊ ሕይወትም ላይ ከፍተኛ ሥልጣን አለው። በሀገራችን ዋና አሰሪ መንግሥት ነው፤ የተለያዩ ኮንትራክቶችን የሚሰጠው፣ ትላልቅ ፕሮጅክቶችን የሚያከናውነው የስራ አስፈፃሚው ነው። የስራ አስፈፃሚው ከፈለገ ሃብታም ያደርግሃል አለበለዝያ ደግሞ በድህነት እንድትኖር ይፈርድብሃል። መንግሥት በዜጎች ኢኮኖምያዊ ሕይወት ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ተፅእኖ አለው። ይህ በየደረጃው ያለው የስራ አስፈፃሚው አካል ተግባር ላይ የሚያውለው ሥልጣን በዜጎች ሕይወት በፖለቲካዊ አቋማቸውም ጭምር ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው። በአድርባይነት ወደ ሥልጣን የሚወጣው አካል በቢልየኖች ላይ የሚወሰን ስለሚሆን የዜጎችን ሰርቶ የመጠቀም ጉዳይ በሱ ፍላጎት ስር ይወድቅና በላብና በጥረት ሳይሆን ሎሌነት የመጠቀምያ መሳሪያ ይሆናል።

ኑሮን አሸንፎ ለመቀጠል የፖለቲካ ጠባይን “አሳምሮ” የመንግሥትና የፓርቲ ባለሥልጣናት የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ጠባይ መያዝ በሌላ አነጋገር አድርባይ መሆንን ይጠይቃል። ለዚህ ሁሉ ተብሎ የፓርቲ አባል መሆንና ከፍተኛ ደጋፊ መስሎ መታየትም “አዋጪ” መንገድ ይሆናል። በፖለቲካዊም በኢኮኖምያዊም እንቅስቃሴ እንደፈለገ ማድረግ የሚችል አረ ተው ባይ የሌለው ፓርቲና መንግሥት በሀገራችን ነግሷል። በእንዲህ ዓይነት ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ሁኔታ በመንግሥት ባለሥልጣናትና ከነሱ ጋር የተጠጉ ተጠቃሚዎች ሙስና፣ በአቋራጭ ለመበልፀግ መሯሯጥ (ኪራይ ሰብሳቢነት የሚባለው) ብልሹ አስተዳደር መንገስ ባህርያዊ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ፍርሃት፣ አድርባይነት ቢያስከትል አይገርምም።

አሁን በዓለማችን በአጠቃላይ በሀገራችን ደግሞ በተለይ ሀገራት ሊከተሉት ስለሚገባ የኢኮኖሚ ፖሊሲና አቅጣጫዎች (Developmental state VS Neo-Liberal political economy) አስተሳሰብ ላይ ስነ ሃሳባዊ ክርክር በዚህ ፅሁፍ ለማድረግ አይመችም። ግን የNeo-Libral political economy አስተሳሰብ ለሀገራችን ይጠቅማል የሚል አስተሳሰብ እንደሌለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ። መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት በመጠበቅ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ግብር በመሰብሰብ ብቻ ታጥሮ ይቀመጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ለገበያ ብቻ ይተው የሚል አመለካከት የለኝም። እንደ ሀገራችን በመሰሉ በጣም ኋላቀርና ከፍተኛ ድህነት ባለበት ሀገር ብቻ ሳይሆን በጣም በበለፅጉት ሀገራትም መንግሥት በሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አለው። በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት ደግሞ ድርሻው ይጨምራል፤ ግን የመንግሥት በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያለው ድርሻ ለመወጣት ሲንቀሳቀስ በምን ዋጋ ነው የሚሰራው ነው ትልቁ ጥያቄ። የሚጠቅምህን እኔ አውቅልሃለሁ ስለዚህ የምሰራውን ዝም ብለህ ተቀበል ብለን ህዝብን አግልለን ነው የምንሰራው ወይስ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ አሳምነን ጥቅሙን አውቆ እየደገፈው መከፈል ያለበት መስዋእትነት ካለ ተቀብሎ እየከፈለ በሌላ አነጋገር ከሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ጋር ነው የምናካሂደው። የህዝብን ሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ገድለን ግን የስራ አስፈፃሚውን ጡንቻና ኪስ አሳብጠን በሌላ አገላለፅ ለሙስናና ለብልሹ አስተዳደር ምቹ ሁኔታ ፈጥረን ከዚህ የተነሳ ደግሞ በሀገራችን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ችግር ፈጥረን ነው ወይ የምንተገብረው? ነው ምርጫው።

አሁን እየሄድንበት ያለነው የመንግሥት በሀገር ኢኮኖምያዊ ግንባታ ላይ ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ዋጋ እሚያስከፍለን ይሆናል ብየ አምናለሁ። ይህንን የመንግሥት በኢኮኖምያዊ ግንባታ ላይ ያለው ሚና በሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ህዝብ እየተቀበለው እያመነበት በወከላቸው የህዝብ ተመራጮች በኩል ደግሞ እየተቆጣጠረው እና እየወሰነበት የሚካሄድ መሆን ይኖርበታል። አሁን ኢህአዴግ በተቆጣጠረው ፓርላማ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዳላመጣ ግልፅ ነው። የስራ አስፈፃሚው አካል የፈለገውን ነገር ከማድረግ የሚያግደው ተቆጣጣሪ አካል የለም።

ይህ በህዝብ ተቆጣጣሪነት የሚካሄድ የመንግሥት በኢኮኖምያዊ ሕይወት ያለው ሚና ተግባር ላይ ሲውል ግዜ የሚፈጅ ብዙ ውጣውረድና ህዝብን የማሳመን ስራ እንደሚፈልግ አንዳንዴም የስራ አስፈፃሚው ከፈለገው ውጪ ውሳኔዎች ሊወሰኑ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። ይህ ሀገር ከተረጋጋና ከተወሰነ ግዜ በኋላ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቀጣይነት ግለቱን እየጨመረ የሚያድግ ኢኮኖሚና ዴሞክራስያዊ ሥርዓት መገንባት ከፈለግን መከፈል ያለበት ዋጋ ነው።

በማጠቃለል፣ አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ የህዝብ አመኔታ በመንግሥት ላይ በጣም ዝቅተኛ የሆነበት፣ በህዝቦች መሃከል ያለው መቀራረብ እና መዋደድ የቀነሰበት፣ ጥላቻ እየበረታና በግልፅ እየተነገረ፣ የህዝቦች የእርስ በርስ መናቆር እንዳይመጣ የሚፈራበት ስለሆነም ውስጣዊ አንድነታችን በጣም የላላበት፣ የመንግሥት መዋቅር የመፈፀም አቅሙ ደካማ የሆነበት፤ ከዚህ የተነሳም ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት፣ በያካባቢው ፖለቲካዊ ችግሮች ሲነሱ በታጠቀ ኃይል (ፖሊስና መከላከያ) የሚፈታበት፣ ህዝቡ አሁን የሚታየው ችግር ይፈታል፣ አይፈታም፣ እንዴት ይፈታል እያለ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።

አሁን ወዳለንበት ሁኔታ እንዴት ገባን?

ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ገባን ብሎ ዕድገቱን ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ተገቢ ይመስለኛል። ከዚህ ተምረን ችግሩን ለመፍታት እንድንችል። ኢህአዴግ በመራው የትጥቅ ትግል እና ከዚያም በኋላ በነበሩት ጥቂት አመታት ፀረ ዴሞክራስያዊ የሆኑ አስተሳሰቦችንና ተግባሮች አልነበሩም ባልልም መሰረታዊ ባህሪው ግን ህዝባዊና ዴሞክራስያዊ ነበር የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ዴሞክራስያዊ ባህሪ መቋጫ በህዝብ ተሳትፎ የፀደቀው ሕገ መንግሥት ነው እላለሁ።

አንድ ለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት በሚጠይቅና በመሠረቱ አብዮታዊ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የታገለ የፖለቲካ ድርጅት እንዴት ፀረ ዲሞክራዊያዊ ይሆናል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በእኔ እምነት በውስጡ ፀረ ዴሞክራዊያዊ የሆኑ ባህርያትም የነበሩበት ግን በመሠረቱ ዴሞክራሲዊያ የነበረ የፖለቲካ ድርጅት በሂደት በየጊዜው በሚወስዳቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና እንቅስቃሴዎች እየተለወጠ ፀረ-ዴሞክራሲ እየሆነ ይመጣል ብዬ አምናለሁ። በተለያየ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቱን የሚፈታተኑ ትላልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በሚወስዳቸው አቋሞች ቀስ በቀስ የነበረበትን ቦታ እየለቀቀ ይሄዳል። ኢህአዴግም ውስጥ የሆነው ጉዳይ ይህ ነው እላለሁ። እንደኛ ሀገር በመሰሉ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ማህበር ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሀገሮች የዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ግንባታው ቅን አስተሳሰብና በጎ ፍላጎት ባላቸው ግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ አይሳካም። በህብረተሰቡ ያሉ የተለያዩ አስተሳሰብ፣ ፍላጎት ያላቸው በህብረተሰቡም የራሳቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ባላቸው ኃይሎች አስተሳሰባቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በተደራጀ መንገድ በግልፅ አቅርበው በሚያደርጉት ሰላማዊ ትግልና የዚህ ትግል ውጤት ሆኖ ነው የሚያድገው። ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው።

በአንድ ሀገር ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ስር እየሰደደ በቀጣይነት እያደገ እየተገነባ እንዲሄድ የሚፈልጉ መሪዎች፤ ፖርቲዎች፤ ይህንን ሁኔታ አውቀው ሊገነባ ለሚፈልገው የተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠርና ማመቻቸት ሲችሉ ነው። ግለሰቦች ወይም ፖርቲዎች ትክክለኛ የመሰላቸውን የእነሱን አስተሳሰብና ፍላጎት ብቻ ህብረተሰቡ ላይ በመጫን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አይችሉም። ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ህብረተሰቡ ላይ መሠረት ያላቸው በተገቢው መንገድ ከተመሩና ዕድል ከተሰጣቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ በተደላደለ መሠረት ለማስጀመር ይጠቅሙ የነበሩ ፖለቲካዊ ክስተቶች ተፈጥረው በተገቢው መንገድ ሳንጠቀምባቸው ቀርተን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን በመጉዳት ተፈተዋል። በዚህ ሂደትም ኢህአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ቀሰ በቀስ ፀረ ዴሞክራስያዊ ባህርያቱ እያደጉ መጡ እላለሁ። ለዚህ አስተዋፅኦ የዳረጉ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፤ እነሱን ሁሉን መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም። ግን የመንግሥት ሥልጣን ከተያዘ በኋላ የኢህአዴግን ዴሞክራስያዊነት እሚፈታተኑ ሦስት ትልልቅ ክንዋኔዎች ተፈፅመዋል። እነዚህም ክንዋኔዎች የተፈቱበት መንገድ የኢህአዴግን ፀረ ዴሞክራስያዊነት ያጎሉ ከዛም በላይ ተቋማዊ (Institutionalize) እንዲሆን ያስቻሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነሱም፤

አንደኛ፥ ከኦነግ ጋር የነበረን ቅራኔ አፈታት

ሁለተኛ፥ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጠ ፓርቲ ቀውስ አፈታት

ሦስተኛ፥ የ1997 ዓ.ም ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የተፈታበት አግባብ ናቸው። እነዚህን አንድ በአንድ እንያቸው።

የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር በመሰረቱ በኢህአዴግና በኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) መካከል በተደረሰበት ስምምነት ፀደቀ፤ ጊዝያዊ የሽግ ግር መንግሥትም በዚህው ስምምነት መሰረት ተመሰረተ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በኢህአዴግና በኦነግ በተፈጠረው አለመግባባት ኦነግ ከመንግሥት ወጣ፣ ውግያዎቹም ተካሄዱ። በዚህ ሂደት ጥፋቱ የማን ነበር የሚለውን ጥያቄ ለታሪክ እንተወውና ይህ ክስተት ግን በኢትዮጵያ ሊመሰረት ይችል የነበረውን የኃይል ሚዛን መሰረት ያደረገ ውስጣዊ የቁጥጥርና የተጠያቂነትን አሰራር ለመመስረት የሚያስችል የነበረ እድል እንድናጣ በማድረግ የዴሞክራስያዊ ሥርዓት ግንባታውን ሂደት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቷል የሚል እምነት አለኝ። ኦነግ የራሱ ችግሮችና ስህተቶች የነበሩት ቢሆንም በወቅቱ ግን የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትና ስሜት የሚያንፀባርቅ የፖለቲካ ኃይል ነበር።

ከዚህ በላይ ደግሞ ከኢህአዴግና ይህ ድርጅት ከሚመራበት አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ እምነትና ባህል ወጣ ያለ በራሱ መንገድ የተፈጠረ ስለነበረም ኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን ስብስብ የመገዳደር (Challenge የማድረግ) አቅምም ፍላጎትም የነበረው ድርጅት ነበር። ይሁን እኒጂ ኦነግ ደግሞ ብቻውን ኢትዮጵያን እንደፈለገ ማድረግ የሚችል የፖለቲካ ኃይል አልነበረም። ይህ ሁኔታ በሚገባ ቢያዝ ኖሮ ጤናማ የሆነ የቁጥጥርና የተጠያቂነት ሥርዓት ለመገንባት፤ የስራ አስፈፃሚ የሆነው የመንግሥት አካልን የኃላፊነትና የተጠያቂነትን አሰራርን የምንቆጣጠርበት የፖለቲካ ሥርዓት የመመስረት ዕድሉ የሰፋ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ይህ አካሄድ ችግሮች አይኖርበትም ነበር ለማለት ሳይሆን የተፈጠረው ሁኔታ የተፈታበት መንገድ ግን ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ማጥበብ ላይ ቀላል ያልሆነ ድርሻ ነበረው እላለሁ።

ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅና በምርጫ የቆመ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ በፓርቲና በመንግሥት ምን ዓይነት ግንኙነት መኖር ይገባዋል የሚል ሃሳብ እየተብላላ እያለ ኤርትራ ወረረችን። ይህ ወረራ በኢህአዴግ ውስጥ በተለይ በህወሓት መታየት ጀምሮ የነበረውን የሃሳብ ልዩነት አጉልቶ አወጣው። ከኤርትራው ጦርነት በኋላ በ1993 ዓ.ም. በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈልና ይህ መከፋፈል የተፈታበት መንገድ ሌላ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ጥቑር ጠባሳ ያስቀመጠ ፖለቲካዊ ክስተት ነበር። የክፍፍሉ አጀንዳዎች ምንምን ነበሩ፣ የትኛው ወገን ትክክለኛ፣ የትኛውስ ስህተት ነበር የሚለው አሁንም ለታሪክ እተወዋለሁ። አጀንዳው ምን ይሁን ምን መከፋፈሉን ለመፍታት የተወሰደው እርምጃ የድርጅቱን ሕገ ደምብ የጣሰ፣ ድርጅት ፈረሰ በሚል ማስፈራርያ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሕይወትና አሰራርን በመጣስ ገደል ውስጥ የከተተ ክስተት ነበር። ጉዳዩ በህወሓት ውስጥ የነበሩ በፖለቲካው ከፍተኛ ሚዛን የነበራቸው ሰዎች ለምን ወጡ አይደለም። አወጣጣቸው የውስጠ-ፓርቲ ዴሞክራሲ ያልተከተለ፣ የተወሰነ ኃይል ሌላውን ክፍል ከውስጠ ፓርቲ አሰራር ውጪ የፀጥታ ኃይሎች ተጠቅሞ ያባረረበት አሰራር ነበር። ይህንን ተከትሎም ከፓርቲ ከወጡ ሰዎች ውስጥ በጣም በሚገርም ፍጥነት የሀገር ፓርላማ ተስብስቦ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩትን ሰዎች ወህኒ ቤት ለማሰርና እዛም ለማቆየት የሚያስችል ሕግ በአንድ ቀን ወጣ፤ በፍርድ ቤት በዋስ የተለቀቀው ስየ አፍታ ሳይቆይ ወደ እስር ቤት ተወረወረ።

ይህ ዕድሜያቸውን ሙሉ በትግል ያሳለፉ፣ በድርጅቱና በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ የነበሩ ትላልቅ ሰዎች ግማሹ ወደ ውህኒ ግማሽ ወደ መንገድ ተወረወረ። አንድ የፖለቲካ ድርጅት በውስጡ ራሱ ያስቀመጠውን የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራስያዊ አሰራር በምንም ምክንያት ይሁን ራሱ ካፈረሰ ከዛ በኋላ ማቆምያ የለውም። እነዚህ ከላይ የተገለፁት ሰዎች የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ በሚፈቅደው መሰረት መብታቸውን ያላስጠበቀና፣ ቢሳሳቱም ይህንን ችሎ በዴሞክራስያዊ መንገድ የማይፈታ ድርጅት ለተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ዴሞክራስያዊ መብት ያስጠብቃል ብሎ ማሰብ ለኔ ዘበት ነው የሆነብኝ።

በዚህ ክስተትም በተቀረው የፓርቲው አባልና ሰፊው ሕብረተሰብ ላይ ፍርሃትን ነው የለቀቀው። እነዚህ ሰዎችን ፀረ ዴሞክራስያዊ በሆነ መንገድ የቀጣ ድርጅት ለሌላው ታችኛው ካድሬና የመንግሥት ባለሥልጣን ምንም ደንታ ሊኖረው እንደማይችል በጣም ግልፅ የሆነ መልእክት ተላለፈ። ሰውን አስፈራርቶ መግዛት እንደ የመንግሥት ፖሊሲ ግልፅ ሆኖ ወጣ። ከማሕበራዊ ኑሮ ጋር ተያይዞ ከቦታቸው የተነሱት የህወሓትና የመንግሥት ባለሥልጣናት መጠየቅ ራሱ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትል ጥፋት ሆነ። ኧረ ይሄ ነገር አፈታቱ ትክክል አይደለም ጀግኖቻችን አላግባብ እያዋረዳቹህ እኛንም እንደህዝብ ሃፍረትና ፍርሃት እያላበሳቹሁን ነው ብለው ለጠየቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከባድ ማስጠንቀቅያ ደረሳቸው። ይህ ሁኔታ በህወሓት ላይ ብቻ የታጠረ አልነበረም፣ በተለይ በኦህዴድና በዴህዴን ኢዴሞክራስያዊ እርምጃው በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጠለ። በኢህአዴግ ውስጥ ለየት ያለ ሃሳብ ማቅረብ እንደ ነውር የሚታይበት ሁኔታ ተፈጠረ። ፍርሃትና ከዚሁ ከፈተኛ ፍርሃትና ሌሎች ፍላጎቶች የሚመነጭ አድርባይነት፤ (Opportunism) እና ሙስና በፓርቲው ካድሬ በሰፊው ተዛመተ።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የህወሓት/ኢህአዴግ ባህሪይ የነበረውና የድርጅቱን ዴምክራሲያዊ ባህርይ መጠበቅ ላይ ቀላል ያልሆነ አስተዋፅዖ የነበረው የጋራ አሰራር መርህ (collective Leadership) አንድ ሰው የፈለገውን በሚወስንበት አሰራር ተተካ። በፓርቲው ውስጥና በሠራዊት ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምረው በትግል የቆዩ ነባር ካድሬዎችና የሠራዊት አባላት የራሳቸው ስብእናና አቋም ያላቸው እየተመነጠሩ ተባረሩ ወይም ራሳቸውን አገለሉ። እንደኔ አመለካከት ይህ ክስተት ሌላው የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ገድል በመክተት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበበ ፖለቲካዊ ክስተት ነበር፤ አሁን ለደረስንበት ሁኔታም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።

በመቀጠልም ኢህአዴግ የውስጠ ፓርቲውን ችግር ፈትችያለሁ ባለበትና ለሕብረተሰቡም ለዓለም ህዝብም ዴሞክራስይዊ መልክ ለማሳየት በመፈለግ የ1997 ዓም ምርጫን ትንሽ ከፈት አደረገ። ሰፋፊ ክርክሮች ተደርገው ምርጫው ተካሄደ። በዚህ ምርጫ ተቃዋሚዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የድጋፍ መጠን አገኙ፤ በተለይ በርእሰ ከተማዋ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ አሸነፉ። ኢህአዴግ ያልጠበቀውና ያልተዘጋጀበት የፖለቲካ ክስተት ነበር፤ እጅግም ተደናገጠ። ተቋዋሚዎቹም የተስማሙበትና ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ስትራቴጂ የነበራቸው አይመስልም።

ተቃዋሚዎች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ሥልጣን በአጠቃላይ ለመቆጣጠር ፍላጎት በማሳየት በጠቅላላው ምርጫ አሸንፈናል አሉ። ትክክለኛ ቁጥሮቹን እኔ አላውቃቸውም ግን ኢህአዴግ በአመነበት ደረጃ እንኳን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ቢሳተፉ ምናልባት አሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የተለያ ይሆነ ነበር ብዬ አምናለሁ። አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ያለው ጫና በጣም ትልቅ ነው። ከዛ በተጨማሪም በፖርላማው ውስጥ እስከ ከ1/3 ድምፅ በላይ አግኝተዋል ተብሎ ታምኖበት ነበር። እነዚህ ሁለቱ ተደምረው በኢህአዴግ የሚመራው የሥራ አስፈፃሚ የፈለገውን ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በራሳቸው መንገድ የመጡ፤ የሕብረተሰቡ ድጋፍ ያላቸው ፖለቲካዊ ኃይሎች ስለነበሩ በሕግ አውጭው አካል የሚደረጉ ውይይቶች የተለያዩ ሃሳቦችንና አማራጮችን የሚያቀርቡ፣ ሕብረተሰቡ ይህንን እንዲያውቅ ለቀጣይ ምርጫ ደግሞ ቀላል ያልሆነ ትምህርት እንዲቀስም በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርግ ይረዳው ነበር። ውሳኔዎችም ካላቸው ጠቀሜታ እየተመዘኑ የሚወስኑበት ሁኔታ ይፈጥር ነበር። ይህ ክስተት በድርድር ቢፈታ ኖሮ ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀም ነበር ብዬ አምናለሁ።

ከዚህ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ መጥፎ ጠባሳ አለ። ይኸውም በምርጫ እኔ አሸንፊያለሁ እኔ አሸንፊያለሁ በሚል የተሟሟቀ ክርክር ውስጥ ቅንጅት በግልፅ በአደባባይ ዘረኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ማስፋፋት ጀመረ። ውስጥ ለውስጥ በተደራጁ ኃይሎችም ይህንን ፀረ የትግራይ ተወላጆች የሆነውን ዘመቻቸውን አስፋፋው ይህንን ዘረኛ አስተሳሰባቸውን በተገቢው መንገድ አላስተባበሉም። ኢህአዴግ ደግሞ ይህንን አድሃሪ ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ አስተጋባው ሊፈጁህ ነው። የሩዋንዳ ዓይነት መገዳደል ይከሰታል ማለት ጀመረ። ይህ ሁኔታ ሕብረተሰቡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በትክክለኛ መንገድ ሳይሆን የፖለቲካ ኃላፊዎች በሚፈልጉት መንገድ እንዲያይ አደረገው። ቢያንስ የትግራይ ተወላጅ የሆነውን አስደነገጠው። ይህ ለፀረ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ምሽጋቻውን ለማጠናከር ጠቀማቸው። ይህ መጥፎ የፖለቲካ ጨዋታ የፈጠረው ጠባሳ እስከ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ አልሻረም። አሁንም እንደመጠቀሚያ መሳሪያ ይነሳል።

በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ መቋቋም የቻለው በመቶዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት በመግደል ነው። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትም ወህኒ ወረዱ። በዚህ ሂደትም ሁለት ግልፅ የሆኑ መልእክቶች ተላለፉ። አንድ፥ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲሁ በቀላሉ በምርጫ አሸንፍያለሁ ስለተባለ እንደማይሰጥ። ሁለት፥ የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረው አመራር ሥልጣኑን በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ለመጋራት ያሸነፈን የፖለቲካ ኃይል በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ሳይሆን የፀጥታ ኃይሎችን ተጠቅሞ እንደሚያጠፋ ግልፅ ሆነ። የኢህአዴግ መንግሥት በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ብልጫና ይህ ብልጫ የሚያስገኝለትን የሕብረተሰብ ድጋፍ ሳይሆን የመንግሥት ሥልጣን በመቆጣጠሩ የሚያገኘው የፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ በሥልጣን መቆየት መወሰኑን ግልፅ አደረገ።

ይህ ክስተት በፓርቲው ብቻ ታጥሮ የነበረውን ፍርሃትና አድርባይነት ወደ ጠቅላላ ሕብረተሰቡ እንዲጋባ አደረገ። መንግሥትን በተለይ የፀጥታ ኃይሎችን ፈርቶ ተሸማቆ እነሱ መስማት የሚፈልጉትን እየተናገሩና እነሱን እያስደሰቱ መኖር “አዋጭ” የፖለቲካ ባህርይ ሆነ።ክዚህ እየተነሱም ኃላፊዎች የሚፈልጉትን የፖለቲካ አቋም፣ ቃላቶች ሳይቀይሩ አለቆችን ለማስደሰት መደጋገም ከፓርቲው አልፎ ወደ ሕብረተሰቡ በስፋት ገባ። ገዢውን ፓርቲ ፈርቶና “ፀባይን አሳምሮ” በአድርባይነት መኖር ዋነኛው የፖለቲካ “ጥበብ” ሆነ።

በመሆኑም ከላይ የተገለፁት ሁኔታዎች እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ራሱ የፖለቲካ ድርጅቱ በመሪነት ያፀደቀው ሕገ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ባልቻለበት ሁኔታና፣ ሕገ መንግሥቱን የሚገድቡ የተለያዩ ሕጎችን በማውጣትና በፀጥታ ኃይሉ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በኔ እምነት ጨቋኞች ህዝቡን ጨቁነን እንገዛለን የሚል ግልፅ የፖለቲካ ውሳኔ ወስነው የጭቆና ሥርዓት አይዘረጉም። በአህአዴግ ውስጥ ያለው ሁኔታ በንግግር እኛ እናውቅልሃለን ለህዝብ ጥቅም ቆመናል እየተባለ በተጨባጭ ሂደቱ ግን ህዝብን እያስፈራሩና እየጨቆኑ መግዛት ሆኗል።

ሆኖም ይህ ከላይ የተገለፀው ሁኔታ ረጅም መቆየት ስለማይችል ሕብረተሰቡ ከሚሸከምው በላይ ስለሆነበት የመንግሥት የስራ አስፈፃሚው አካል በሕብረተሰቡ ላይ የሚፈፅመው በደል ስለበዛበት፣ ከዚሁ ጋርም የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ግልፅ አቅጣጫዎች አለማየቱ ጋር ተቀላቅሎ የኢህአዴግ መንግሥት በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፍያለሁ ባለበት ማግስት በከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቢያንስ ችግሮቹ የሚገለፁበትን መልክ በማንሳት በግልፅ ችግር አለብኝ እንዲል አስገድዶታል። ከላይ ከተጠቀሰው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተነስቼ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሦስት ቢሆኖች (scenarios) ያሉ ይመስለኛል።

ቢሆኖች (Scenarios)

አንደኛ ቢሆን ሀገሪቱ ከውስጥ የህዝብ ጥያቄ በሚፈጠረው ብጥብጥ ምናልባት የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና የኃይል ጫና ተጨምሮበት መንግሥት መቆጣጠር ከሚችለው በላይ ሁኖ የመንግሥት መፈራረስና ሁከት መፍጠር ሊመጣ ይችላል። ይህ አማራጭ የመከስት እድሉ አነስተኛ እንኳን ቢሆን እንደ አንድ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ታይቶ እንዳይከሰት መስራት ያስፈልጋል። የመሆን እድሉ ግን ዜሮ አይደለም። ባላፈው በኦሮምያ ተፈጥሮ የነበረው የህዝብ አመፅ የመንግሥት መዋቅር ላይ በተለይ በክልሉ መንግሥታዊ መዋቅር ላይ ፈጥሮት የነበረ ጫና በጣም ከፍተኛ ነው። በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃገብነት ነው አመፁ የቆመው። አመፁ በስፋትም በግዜም ቢቀጥል ኖሮ በተጨማሪም ሌሎች ተጓዳኝ የህዝብ አመፆች ቢነሱ ኖሮ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ሊፈጠር ይችል የነበረው ችግር መገመት አይከብድም።

ሁለተኛ ቢሆን ረዘም ላለ ግዜ አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ መቆየት ነው። ይህ ከሁሉም አማራጮች የመሆን እድሉ የላቀ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ በጠቅላላ ይሁን በተወሰነ ክፍሉ መጠነኛ ለውጦችን በውስጡ በማድረግ በግልፅ ያመነበትን የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና ቴክኒካዊ፣ አስተዳደራዊ ትርጉም በመስጠት በዚህ ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለመፍታት በመሞከር የተወሰነ ግዜ የጣላቸው የስራ ኃላፊዎችን በማስወገድ ከቀውሲ ለመውጣት ግዜ ለመግዛት በመፈለግ የሚፈጠር ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ በተፈጥሮ ሊያደላበት የሚችል የመጀመርያ ምርጫው የሚሆን በመሆኑ የመከሰት ዕድሉ የሰፋ አማራጭ ነው። ይህ አማራጭም ችግሩን ለተወሰነ ግዜ ሊያዘገየው እንደሆነ እንጂ አይፈታውም።

ለተወሰነ ግዜ በማዘግየት ችግሩ ይበልጥ ስር እየሰደደ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውም እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል። በዚህ ግዜም በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ እየተባባሰ ከመሄዱም በላይ በመጨረሻም በጣም አውዳሚ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ለሚፈልጉ ኃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፍጥርላቸዋል። ስለሆንም ፈጥኖ የሚታየው የመፍትሔ አቅጣጫ የመሆን እድሉም የሰፋ አማራጭ ሆኖ ሳለ ለሀገሪቱ አሁን የሚያስከፍለው ዋጋ ይህን ኋላ በሚያስከትለው ነውጥ እጅግ የከፋው ነው። ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ የተመዘገቡትን ድሎች ጠራርጎ ያጠፋል። ሀገሪቱን ወደኋላ ይመልሳል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውም ምን ዓይነት ሥርዓት እንደሆነ መተንበይና መገመት አይቻልም። እነዚህ ሁለት አማራጮች በጊዜ ሊለያዩ ካልሆነ በስተቀር በጣም ተመሳሳይ ናቸው። በራሳቸው መንገድ የሚከሰቱም ስለሆኑ እንዳይከሰቱ ምን እናድርግ በሚለው ሃሳብ ላይ ካልሆነ በእነሱ ላይ ብዙ መናገር አይቻልም።

ሦስተኛ ቢሆን ሰላማዊ፣ ሥርዓት ያለው፣ በንቃት የሚመራ፣ ለውጥ መጀመር ነው። ይህ ማለት አሁን በሀገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳለ በማመን ይህንን ቀውስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለን በሰፊ የፖለቲካዊ ኃይሎችና የምልአተ ህዝቡ ተሳትፎ ለመፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ሂደት መጀመር ነው። ይህ አማራጭ ከላይ የተገለፁትን ሌሎች ቢሆኖች እንዳይከሰቱ ለማድርግ ያስችላል። በመሆኑም በሀገራችን የወደፊት እድል ያገባናል የምንል ዜጎች በሙሉ ተንቀሳቅሰን እውን እንዲሆን ማድረግ አለብን የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ፖለቲካዊ ሂደት ዓላማና እንዴት ሊፈፀም ይችላል የሚለውን ሃሳብ መጨረሻ ላይ እመለስበታለሁ።

የትግራይ ህዝብ

በሀገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስላለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ስናነሳ የትግራይን ህዝብ ለብቻ ነጥሎ ማንሳት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ተገቢ ጥያቄ ነው። እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ ራሱን ኢትዮጵያ ለምትባለው ሀገር መመስረትና በታርኳ ውስጥ በተለያዩ ውድቀቶችም ይሁን ድሎች ዋና ተዋናይ አድርጎ ነው የሚያስበው። ከዚህ ውጭ በሌላ መንገድ አያስብም። አሁንም ችግሮችን ስናነሳና መፍትሔ ስንፈልግ በዚህ በታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አስተሳስብ ውስጥ ሁነን ነው። የትግራይ ህዝብ ለብቻው የሚያስበው መፍትሔ አልነበረም፣ የለም። አሁን ባለው ከላይ የተገለፀው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ተነስተን መፍትሔ ስናፈላልግ የትግራይ ህዝብ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ራሱን እንዴት ያስቀምጣል? ለሚለው ጥያቄ መፍትሔ ሲፈለግ ለትግራይ ህዝብ ብቻ የተለየ ከዛ አንፃር ብቻ የተቃኘ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት ለማስፈን፣ ከዚህ ሥርዓትም እንደ ማነኛውም የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው።

የትግራይ ህዝብ ይህ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት ለማምጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ታግሎ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ነው። በመሆኑም እስካሁን ድረስ ይሁን ለወደፊትም ሥርዓቱን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ከማድረግ አንፃር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ህዝብ በዘለቄታው ጥቅሙ የሚከበርለት በሕገ መንግሥት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት ሲገነባ ስለሆነ።

አሁን በትግራይ ወጣቶችና ጉዳዩ ያሳስበናል ብለው የሚያምኑ የትግራይ ተወላጆች ቀደም ብሎ በተነሳው ጥያቄ ላይ ግልፅ የሆነ ሃሳብ የለም። በመሃል ሀገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ይንፀባረቃል። የትግራይ ህዝብ በሥርዓቱ እላፊ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል፣ ይታያል። ተጨባጭ ሁኔታው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። በርግጥ ሁኔታውን ህዝብን በማጣላት እንጠቀማለን ብለው የሚመኙ ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች ያራግቡታል። እነዚህን ኃይሎች ካሰቡትና ከተመኙት ውጭ ማሳመን አይቻልም። ግን ደግሞ ተጨባጭ የህዝቦች መራራቅ አለ። ይህ ለምን መጣ? እንዴት እንፍታው ብሎ ማሰብና መወያየት ተገቢ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ተወላጅ በመሆኔና ከዚህ ህዝብ ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች ሁኜ ስለታገልኩና ስላታገልኩ ሁኔታውን በተሻለ አውቀዋለሁ፤ ስለዚህ የሚታየኝ ሃሳብ የማቅረብና ቢያንስ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የሕብረተሰቡ አጀንዳ ሆኖ እንድንወያይበት፣ ሃሳብ እንድንለዋወጥበት ማድረግ ይገባል ብየ ስላመንኩበት ነው።

አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብ የሚኖረው ድርሻና የሚጫወተው ሚና ምን መሆን አለበት? የትግራይ ህዝብ የሥልጣን ዘመኑን በፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ የሚያራዝም በየግዜው ከህዝብ እየተነጠለና በህዝብ እየተጠላ የሚሄድን የፖለቲካ ሥርዓት ጠባቂና ተከላካይ ነው መሆን ያለበት? ወይስ ሌላ ምርጫ አለው? የትግራይ ህዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የሚወስደው የፖለቲካ አቋም ምን ይሁን? ብሎ መጠየቅ ይገባል። በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጥስ ፖለቲካዊ ሥርዓት ጠባቂ ተደርጎ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ ጠላት ተደርጎ ነው መታየት ያለበት ወይስ በዴሞክራሲና በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ፣ ለህዝቦች መብት መከበር ለትክክለኛ ፍትሕና ለፍትሃዊ ኢኮኖምያዊ ተጠቃሚነት በፊታውራሪነት የሚታገል ህዝብ ተደርጎ ነው መታየት ያለበት? ብለን እየጠየቅን መልሱን መፈለግ ይኖርብናል።

ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባቴ በፊት በህወሓት መሪነት የተካሄደው የትጥቅ ትግልና፣ ይህ ትግል ያስመዘገበው ድል ዴሞክራስያዊ፣ አብዮታዊና ትክክለኛ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ደርግን የመሰለ ፀረ ዴሞክራሲ አፋኝ መንግሥትን ታግሎ መጣል ዴሞክራስያዊም አብዮታዊም ነበር። ለጭቁን ህዝቦች መብት መረጋገጥ የተደረገ ትግል ዴሞክክራስያዊ ካልሆነ ዴሞክራስያዊነት ምን ሊሆን ነው። ስለሆነም በህወሓት መሪነት በተደረገው ትግል በተለያዩ ደረጃዎች በተራ ተዋጊም በከፍተኛ አዛዥነትም ቦታ ላይ ሆኜ መሳተፌ እኮራበታለሁ። እነዚያን ጀግኖች እየመሩ የእነሱን ጥረት እያስተባበሩ ለድል መብቃት በታሪክ መታደል ነው እላለሁ። ይህ ማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለፅኩት ህወሓት የአማልክት ስብስብ ነበር ስህተት አልነበረውም፣ ችግሮች አልነበሩም ማለቴ አይደለም። በድምር ሲታይ የደርግን ሥርዓት ለማሸነፍና ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ ዴሞክራስያዊና አብዩታዊ ባህሪው ከሁሉም በየግዜው ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች ያመዘነ የበለጠ ነበር። ስለሆነም ነው በአሸናፊነት የዘለቀው የሚል እምነት አለኝ።

የትግራይ ህዝብ የደርግን ጨቋኝ ሥርዓት ለመጣል ከፈተኛ ዋጋ ይክፈል እንጂ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እላፊ ጥቅም ለማግኘት አልተመኘም፤ በተጨባጭም አላገኘም። በፌዴራል መንግሥት በርከት ያሉና ወሳኝ የሚባሉ የሚኒስቴር ቦታዎች መያዝና በዚህ ሳብያ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ባላቸው ቅርበት የተወሰነ ጥቅም የሚያገኙ የትግራይ ተወላጆች ካሉ የትግራይ ህዝብ የእላፊ ጥቅም ማግኘት ማስረጃዎች ተደርገው መወሰድ አይችሉም። ይባስ ብሎ በራሱ ጥረት ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ በኢኮኖሚው ረገድ ደህና የተራመደውም በእነዚህ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተጠግተው ጥቅም ከሚያገኙት ጋር እየተደመረ እንዲታይ ስለዚህም የሌሎች ህዝቦችን አሉታዊ ስሜት ማነሻሻም እየሆነ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ያገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ስራውን ሰርቶ ሃብት አፍርቶ ለመኖር የሚፈልገውም የትግራይ ተወላጅ ቀላል ያልሆነ ስጋት ውስጥ ከቶታል፤ ይህ መሆን የሌለበት ጉዳይ ነው።

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች የተለየ እላፊ ጥቅም አልፈለገም ሲባል ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚሰጠው መብትና ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ስርቶ መበልፀግ ስብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች በሚገባ ተከብረውለት መኖር ደግሞ ማንም ሊከለክለውና ሊነጥቀው አይገባም፤ በእኩልነት በመፈቃቀድ ህዝቦች መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው ተከባብረው የሚኖርባት ሀገር እንድት ሆን ነው ያን ሁሉ ዋጋ የተከፈለው። ይህንን ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ሊጠብቀው ይገባል፤ ድርሻውን የሚነጥቀው ኃይል እንዲኖር አይፈቅድም።

ከላይ የተቀመጡት ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ በእኔ አመለካከትና እምነት የትግራይ ህዝብ የሰብዓዊና የፖለቲካዊ መብቶች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት በፍትሕ ላይ ለተመሰረተ የህዝብ መብት ጥበቃ፤ ይህንን መሰረት አድርጎ ለሚመጣ ኢኮኖምያዊ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት ለማምጣትና እነዚህን መብቶች ስፋትና ጥልቀት ኖሯቸው ተግባር ላይ እንዲውሉ የሚታገል መሆን አለበት እላለሁ። እነዚህ በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩ መብቶች ሳይሸራረፉ ሳይገደቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጊዜው ሲፈቅድ ደግሞ ስፋትም ጥልቀትም እንዲኖራቸው በመታገልና ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ ነው። እንደ ህዝቡ ጥቅሙ የሚከበረው። ከዚህ ውጭ ግን በተወሰነ ታሪካዊ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ ከሱ የፈለቁ መሪዎችን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል መንግሥታዊ መብቶችን የሚገድቡ ህጎችና መመሪያዎችን መደገፍ የለበትም እላለሁ።

እዚህ ላይ በርከት ባሉ የትግራያ ተወላጆች የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ። ይኸውም አሁን ባለው መንግሥት ላይ ያለንን “የበላይነት” ካጣን ጠቅላላ መብቶቻችን አንድናጣ መልሰን እንድንጨቆን አድልዎ እንዲፈፀምብን ቢደረግስ ምን ዋስትና አለን? የሚል ነው። ዋስትናችን በትግላችን ያገኘነው አሁንም ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነን እየታገልን የምንጠብቀው ሕገ-መንግሥታችን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ ማድረግ ነው። ሌላው ዋስትናችን ህዝቡ ራሱ ነው። የተወሰኑ የክልሉ ተወላጆች በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ወሳኝ በሚባሉ የሥልጣን ቦታዎች ላይ መቀመጥ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሕገ-መንግሥት የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቀውና ሊተገብረው የሚፈልገውን ያህል፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሐረሪ፣ የደቡብ እና ሌሎች ህዝቦች ሊጠብቁት እና ተግባር ላይ እንዲውል የማይፈልጉበት ምክንያት የለም። አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት የሚቃወሙ ኃይሎች እንዳሉ አውቃለሁ። ከነዚህ በላይ ግን ሕገ-መንግሥቱ ሲጸድቅ በነበረው አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ አለመተግበሩ የሚቃወሙ ይበዛሉ። ከዚህ የተነሳም ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ከዋለ ሕገ-መንግሥቱን የሚጠብቀው፣ የሚያዳብረው ኋይል ይበዛል ያሸንፋል። ይህንን ሕገ-መንግሥት መጠበቅ በሚል ሰበብ አሁን ያለውን ሥርዓት የመጠበቅ ሸክም ለምን በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ብቻ ይወድቃል?

እዚህ ሊነሳ የሚገባ አንድ ጉዳይ አሁን ያለው የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር መሠረት ያደረገ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሕገ-መንግሥቱ እራሱ በሚፈቅደው አሰራር ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። በሌላ አነጋገር አዲስ ሕገ-መንግሥት ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አሸናፊ ሊሆን ይችላል። ይህ የሕገ-መንግሥቱ አሰራር ተከትሎ ህዝቡን አሳምኖ በሰላማዊ መንገድ እስከተፈጸመ ድረስ የህዝብ ፍላጎት ነውና ተቀባይነት ማግኘት አለበት። አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት በህዝብ ዘንድ በፍቃደኛነት ተቀባይነት እንዲኖረው ይህንን ሕገ-መንግሥት የሚደግፉት ፖለቲካዊ ኃይሎች ሥራቸው ሰርተው በሰላማዊ መንገድ ካላሸነፉ ተሸንፈዋል ማለት ነው። ስለዚህ ህዝብ በመረጠው መንገድ ሥርዓቱ ይዘረጋል። እኔ ይህ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል የሚል እምነት የለኝም፣ ግን ደግሞ የሚበልጠው ህዝብ አምኖበት በፈቃደኝነት ተግባር ላይ የሚውል እንጂ በጸጥታ ኃይሎች እየተጠበቀ ተግባራዊ የሚሆን ሕገ-መንግሥት ሊኖረን አይገባም።

በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይ በቅርብ ቀናት ከብዙዎቹ ጓደኞቼ ጋር ስንወያይ፣ በአንድ የውይይት ወቅት ሃሳቡ ተነሳና “የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ባለው ግንኙነት፤ በተለይ አሁን ጠንክሮ መገኘት አለበት፣ የደከመ መስሎ መታየት የለበትም” የሚል ሃሳብ ቀረበና “ጠንክሮ መገኘት አለበት ማለት ምን ማለት ነው?” በሚለው ተወያየን። ይህ ነጥብ በሌሎችም ይንሳል ብየ ስለማስብ ያለኝን አመለካከት ልግለፅ።

ጠንክሮ መገኘት ማለት የመከላከያና የድህንነት ኃይል በመቆጣጠርና በማሰማራት ኢህአዴግና ይህ ድርጅት የሚመራው መንግሥት የሚወስነው ውሳኔ ህዝብ ወደደሞ ጠላም ተቀብሎ እንዲሄድ ለማድረግ መንቀሳቀስ ነው? ወይም በፌዴራል መንግሥት በንፅፅር ሲታይ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ ወሳኝ የተባሉትን የሥልጣን ቦታዎች በብዛት መቆጣጣጠር ማለት ነው? ከዚህ አልፎም በየሄዱበት በተገኘው አጋጣሚ ኃይል ያለን መሆናችንን ለማሳየት መሞከር ነው? በአጠቃላይ ከኢህአዴግ በፊት የነበሩ ገዢ መደቦች ሲያደርጉት የነበረውን ለመኮረጅ መሞከር ነው ጠንክሮ መገኘት ማለት? ምንድን ነው? እኔ የትግራይ ህዝብ በጠቅላላውም የኢትዮጵያ ህዝብ “እንዲጠነክሩ” እፈልጋለሁ፤ አጋጣሚውን ሳገኝም ለዚሁ እሰራለሁ። ለእኔ ጠንክሮ መገኘት ማለት ከሁሉ በላይ የተሻለ ተራማጅ ሕብረተሰብን፤ የተረጋጋ ሰላም የኢኮኖሚ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት፤ ዴሞክራስያዊ፤ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት፤ ለመመስረት የሚደረግ ጥረት ባለቤት በመሆን ለዚህ ዓላማ ግንባር ቀደም ተዋጊ መሆን ነው።

ከትክክለኛ ዓላማ የሚነሳ ይህ ትክክለኛ ዓላማና ፍትሃዊ በሕግ የሚገዛ ሥርዓት የሚፈጥረው ውስጣዊ አንድነት ነው ጥንካሬውን የሚፈጥረው። ክዚህ ቀደምም በትጥቅ ትግሉ ወቅትና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጥንካሬውን የፈጠረው ትክክለኛ ፖለቲካዊ አመለካከት ነው። በህዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት ተግባራዊነት ላይ የተመሰረተ እምነት ነው። ፖለቲካዊ ሥርዓቱን ለመከላከል ነው በታላቅ ጀግንነት የተዋጋው። ይህ ፖለቲካዊ እምነት ነው። ውስጣዊ ጥንካሬውና ጀግንነቱን የፈጠረው።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የዓፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ከትግራይ ህዝብ ጋር ሆነው በጋራ የተዋደቁት የተለየ ሚስጢር ስለነበረን አይደለም። ያኔ የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት እየተመራ ሲያራምደው የነበረ ትግል እነሱንም የሚመለከት መሆኑን በንግግር ሳይሆን በተግባር ስላዩት ነው። የትግራይ ህዝብም የሰው ልጅ ሊሸከመው ይችላል ወይ ተብሎ ሊጠየቅ የሚችል ግፍና ጭፍጨፋ ተሸክሞ ከባድ መስዋዕትነት ክፍሎ እንደ ህዝብ በከፍተኛ ጀግንነትና ቆራጥነት የተዋጋው ፖለቲካዊ ዓላማው ትክክለኛ መሆኑን በተግባር እያየው ስለሄደ ነው፤ ከተጨባጭ ተሞክሮም ይህንን ስላረጋገጠ ነው። ጥንካሬ ማለት ይህ ነው። በረጅምና መራራ ትግል የደርግ ሥርዓት መፈራረስ የጀመረው በመጨረሻም የደርግን ሥርዓት ሲያገለግል የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በአስር ሺዎች እጁን ሲሰጥ የነበረው እኛ የትግራይ ታጋዮች የተለየ ጀግንነት ስልነበረን እነሱ ደግሞ ፈሪዎች ስለነበሩ አይደለም፤ እነሱም ጀግኖች ነበሩ፣ ግን የቆሙለት ዓላማ ከዳቸው፣ የቆሙለትን ፖለቲካዊ ዓላማ አምነው መከላከል ተሳናቸው። ውስጣዊ ጥንካሬያቸው በየግላቸው መፍረስ ጀመረ። ሌሎችን ጨቁኖ በመግዛቱ ላይ በተመሠረተ ፖለቲካዊ ዓላማና በብልሹ አስተዳደር የሚመራ ሠራዊት ደግሞ ውስጣዊ ጥንካሬ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይህ ለማንኛውም የህዝብን ጥቅም ለማያስጠብቅ ሥርዓት ይሰራል፤ ለደርግ ብቻ የተሰጠ ስጦታ አልነበረም።

ሁለተኛው ጉዳይ እኛ ሀገራችንን በጠቅላላ ጠንካራ ለማድረግ ከዚህ ጋር አያይዘን ደግሞ የድርሻችን የሆነውን የትግራይ ህዝብ ጠንካራ ለማድረግ የምንችለው በዋናነት እዛው ትግራይ ውስጥ በሚሰራ ስራ ነው። በፌዴራል መንግሥት የሚኖረንን ድርሻ ከላይ የተገለፀውን ፖለቲካዊ ዓላማ (ማለትም በህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ የተመሰረተ አንድነት እንዲጠነክር፣ ሕገ መንግሥቱና ስብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችም ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የመንግሥት ተጠያቂነት እንዲጎለብት ፍትሕ የነገሰበት ሥርዓት እንዲሰፍን ውዘተ) እየታገልንና ይህንን ትግል ሳናኮላሽ ክዚህ ጎን ለጎን በትግራይ ውስጥ የሀገሪቱ ሕግና አቅማችን የፈቀደልንን ያህል ከላይ ከተገለፁት ፖለቲካዊ ስራዎች በተጨማሪ ኢኮኖምያዊ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት እንዲስፋፋ ሌት ተቀን መስራት ይኖርብናል። የትግራይ ክልል በህዝቡ ጥረትና ብቁ አመራር በመስጠት የኢኮኖምያዊ ዕድገትና ዴሞክራስያዊ ሥርዓት የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ እንዲሆን የትግራይ ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍልሏል። ይህ እንቅስቃሴ በትግራይ ላይ ብቻ ይደረግ ወይም ከሌሎች ክልሎች እላፊ ያግኝ አላልኩም፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት አቅማችንን አሟጠን እንጠቀም ነው እያልኩኝ ያለሁት፤ የኛ ድርሻ ይህ ነው። ሌሎቹም ድርሻቸውን በበኩላቸው ይወጡ፤ የዚህ ድምር ውጤት ሀገራችንን ጠንካራ ያደርጋታል።

አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን ሁኔታ አይገልፅም። የክልሉ ተወላጆች ሃብታቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው ለማልማት ሲፈልጉ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም። የትግራይ ክልል በመልካም አስተዳደር፣ በኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለክልሉ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የተመቸ መሆን ሲገባው፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚሁ የራቀ ነው። ትንሽ በትምህርት ገፋ ያደረገውና ሃብት ያከማቸው ክልሉን እየተወ አዲስ አበባ ላይ ነው ስራውን የሚሰራው። ይህ የትግራይን ህዝብ በቀጣይነት ደካማ እያደረገ የሚሄድ ነገር ነው። ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠር በመሃል ሀገር ያለው ኢኮኖምያዊ ዕድሎች (Opportunities) አስተዋፅኦ እንደሚያድርግ ይገባኛል። ይህ ኢኮኖምያዊ ዕድል ባለሃብቶችን የመሳብ ዓቅም እንዳለው ግልፅ ነው። ከዚሁ ጋር ግን በትግራይ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመፈጠሩ የሚሸሸው ባለሃብት ደግሞ ብዙ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ህወሓትና የክልሉ መስተዳድር እንዴት አድርገን ነው መግፋቱን ትተን መሳብ የምንችለው ብሎ ሌት ተቀን መጨነቅ አለበት። አሁን ላለው ሁኔታ መፈጠር ትልቁን ኃላፊነትና ድርሻ የሚወስደው አሁን ያለው የህወሓትና የክልሉ መስተዳደር ነው። የትግራይ ህዝብ በትግሉ ወቅት ይሁን ከዛ በኋላ ባፈራቸው ከሁሉም የላቀ እወቀት ችሎታና ይህንን ለመተግበር ቁርጠኝነት አላቸው ብሎ በሚያምንባቸውና በዴሞክራስያዊ መንገድ በሚመርጣቸው ሲፈልግም በሚያወርዳቸው ልጆቹ መመራት አለበት። ሁለተኛው ዋስትናችን ራሳችን ይህንን ስራ ስንሰራ ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ሚና

ከግንቦት 17-21 1993 እ.ኤ.አ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ላይ አንድ ትልቅ ሲምፖዚየም ተዘጋጅቶ ነበር። ይህ ሲንፖዚየም የመወያያ አጀንዳው በሚቀረጸው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄድ ነበር፣ ሲምፖዚየሙ “Symposium on the making of the new Ethiopian constitution” ተብሎ ነበር የተሰየመው። በአለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ዝና የተጎናጸፉ ሙሁራን ከተለያዩ ሀገራት መጥተው በዚህ የአራት ቀናት ሲምፖዚየም በጣም ጥልቀት ያላቸው ሀሳቦችን በተለያዩ መስኮች አቅርበዋል። በዚህ ሲምፖዚየም እኔም በኢትዮጵያ የሚመሰረተው ሠራዊት በተመለከተ ሃሳብ እንዳቀርብ ተጋብዤ ነበር። በስምፖዚየሙ ተገኝቼ ሐሳቡን አቅርብያለሁ። ይህ ፅሁፍ ሲቀርብ እንደ የግል አስተያየት ሆኖ ቢቀርብም በወቅቱ ከመለስ ጋር በስፋት ተወያይተንበታል። ይህ ማለት በፅሁፍ የቀረቡት ሃሳቦች አስራሩን ተከትለን የድርጅት አመራር ውሳኔ አልተሰጠበትም እንጂ የድርጅቱ የኢህአዴግን በሠራዊት ግንባታ ላይ የነበረውን መሠረታዊ አስተሳሰብ ያንፀባርቅ ነበር ማለት እችላለሁ። በኋላም በዚህ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደ መመሪያ ልንጠቀምባቸው ሞክረናል።

በሲምፖዚየሙ በቀረበው ጽሑፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀሳቦች ተሰንዝሯል። ያኔ አሁን Security Sector Reform /SSR/ እየተባለ የሚጠራውና እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው አስተሳሰብ ገና ሳይታወቅና ስምም ሳይወጣለት በመሰረቱ ይህ አስተሳሰብ የሚመራባቸው አንኳር አንኳር ሀሳቦችን ለሠራዊት ግንባታ ሂደት ልንመራባቸው እንደሚገባ አስቀምጠን ነበር። ሁሉንም እነዚህን አስተሳሰብ እዚህ መድገም አስፈላጊ አይደለም። በዛ ጽሑፍ እንደማጠቃለያ ሆኖ የተቀመጠ አንድ አረፍተ-ነገር ግን እዚህ መጥቀስ አሁን ሠራዊታችን እንደዛ ነው ያለው ወይ? ብሎ ለመጠየቅ ተገቢ ስለመስለኝ እጠቅሰዋለሁ። “We must create a citizen’s army. We must create a military which is loyal to and a servant of the people and which cannot be miss-directed to serve the interest of an elite or of those who might abuse their power. We must create an army which belongs to the people.” ያኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባችን ገና ሳይበከል እያለ ነው ያስቀመጥነው፣ አሁንስ ምን አይነት ሁኔታ ነው ያለው?

እንደእኛ የመሰለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሽግግር በሚደረግበት ኢኮኖሚው ኋላቀር የሆነና ብዙሃነት በበዛበት ሀገር የሚገነባ የሀገር መከላክያ ሠራዊት ለሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓቱ ግንባታ አጋዥ እንዲሆን ከተፈለገ ከማንኛውም የፓርቲ፣ የጎሳ፣ የኋይማኖትና የፖለቲካዊ ወገንተኛነት በጸዳ መልኩ ሥራው መስራት ይኖርበታል። ይህ መርህ ከተጣሰ እና ሠራዊቱ እንደተቋም በሚመሩት መሪዎች ወገንተኛ በሆነ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ከሆነ የዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ግንባታ ያሰናክላል ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውድቀትና ብተና ምክንያት ይሆናል።

የሀገር መከላኪያ ሠራዊት በሀገሪቱ በሚደረጉ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ ተጽዕኖውን የሚያሳርፍ ከሆነ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ ይሆናል። ለዚህ ነው የሠራዊት አጠቃላይ አቅም በስቪል መዋቅሩ ካሉት ሌሎች አካላት የበለጠ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት። የሠራዊት ቁጥር አስፈላጊ ከሆነ በላይ እንዳይበዛ፣ በጀቱ ከሀገሪቱ አቅም ተመጣጣኝ እንዲሆን፣ የገንዘብ አወጣጡ የደረጃው ቁጥጥር እንዲደረግበት በህዝብ በተመረጡ በሲቪል ባለሥልጣናት ሙሉ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ ወዘተ የሚደረገው።

እዚህ አንድ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ የሀገርን በኢንዱስትሪ ዕድገት ለማፋጠን የሚደረገው እንቅስቃሴ በዋናነት በጄኔራሎች የሚመራበት መንገድ አይገባኝም። በተለምዶ ሜቴክ እየተባለ የሚጠራው አደረጃጀት በሀገሪቱ ያሉትን የኃይል ማመንጫ፣ የስኳር ፋብሪካ፣ የባቡር ሃዲድ ስራዎች እንዲሰራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። እነዚህ ስራዎች ሀገር ውስጥ ቢሰሩ ጥሩ ነው። ግን ለምን በጄኔራሎቹ ቁጥጥር ስር ይሆናሉ? በሀገር መከላከያ ውስጥ የሚገኝ ቴክኒካል ብቃት ካለ ታንክን፣ አውሮፕላን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የመገናኛ መሳሪያዎችን ወዘተ ይጠግን ብቃት ካለውም ይፈብርክ። ከዚህ በላይ ብቃታቸው ተፈላጊ የሆኑ የሠራዊት አባላት ካሉም በሲቭል መዋቅሩ ውስጥ ገብተው ስራውን ይስሩ። ምንም እንኳን በሕግ ራሱን የቻለ አወቃቀር ያለው ቢሆንም አሁን ከሀገር መከላከያ ጋር ያለው ቁርኝት ግን አላስፈላጊ ነው እላለሁ።

ይህ ግዙፍ በጀት ያለው አደረጃጀት በሕግ አውጭው አካል ተጠያቂ እንዳይሆን የሀገር የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ እየተባለ የሚሸፋፈን ነገር እንዲኖረ ስለዚህም ተጠያቂነት የሌለው ብክነት እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ከዚህ በተጨማሪም ስራ በመስጠትና በመከላከል በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መቅረት ይችል የነበረ አላስፈላጊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል። ይህ በድምር ደግሞ የሀገር መከላከያው ተቋም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሕይወት ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖይጨምራል። እንደ መርህ ግን ወደ ተደላደለ ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት በሚደረግ ሽግግር የሀገር መከላከያ ኃይል በጠቅላላው በሕብረተሰቡ ያለውን አላስፈላጊ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም መቀነስ ነው መሆን ያለበት። አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ ይህንን መርህ የተከተለ አይደለም።

አንድ ሀገር ሉዓላዊነቱን ጠብቆ ህዝብ በመረጠው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ ያለምንም የውጭ ሀገር ኃይሎች ተጽእኖ እንዲመራ በማስቻል የሀገር መከላኪያ ሠራዊት እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ያህል ከዚህ በላይ መስመር አልፎ በሀገሪቱ ውስጣዊ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ጣልቃ እየገባ ተጽእኖ የሚያሳድርና ለመምራት የሚከጅል ከሆነ ደግሞ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ የኖረዋል። በሕገ-መንግሥት ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያለ ሀገር ይህንን ከሠራዊት ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ መቃወምና መቆጣጠር ይገባዋል። ይህ ካልሆነ በሥርዓቱና በአጠቃላይ የሀገሪቱ ቀጣይ ህልውና ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ አንዳንድ ዘረኛ የሆኑ አስተሳሰቦች ጎላ ብለው ሲነገሩና በሀገራችን የህዝቦች መነሳሳት ሲበራከት የትግራይ ተወላጆች፣ የጸጥታ ኋይሉ በአጠቃላይ፣ የመከላከያ ኃይሉ ደግሞ በተለይ እንደመከታ የማየት አዝማምያ ይደመጣል። በነሱ አነጋገር መከላክያ ተጠናክሮ የሀዝብ መነሳሳቱን እንዲቆጣጠርና አገሩን “እንዲያረጋጋ” ፍላጎታቸውን ይገልፃሉ። ይህ የተለየ የተሻለ አማራጭ የመፍትሔ ሀሳብ ከማጣትና በችግሩ ከመጨነቅ የሚመጣ ይመስልኛል፤ ግን ደግሞ ችግሩ ያባብስ እንደሆነ እንጂ አይፈታውም።

በመከላክያ ኃይል ጣልቃ ገብነት የሚጠበቅ የትግራይ ህዝብ መብት ይሁን ጥቅም የለም። ቀደም ብሎ የነበሩ ገዢ መደቦች የፈጸሙትን ስህተት ለመፈፀም ከቃጣን ደግሞ አንችለውም። እነሱን እንኳን ከትግራይ ህዝብ የበዛ ህዝብ፣ የበለጠ ሀብት፣ የተሻለ ተሞክሮ፣ የተሻለ የተማረ የሰው ኋይል ይዘው አልቻሉትም፣ ምክንያቱም አስተሳሰቡ አድሀሪ ስለሆነና ህዝብ ለመጨቆን የሚቃጣ ስለሆነ አይቆምም።

ከላይ የሚታዩት የሠራዊት አዛዞች የትግራይ ተወላጆች በርከት ብለው ቢታዩም ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ስብጥር ነው። በዚህ አካል ውስጥ ወገንተኛ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም ከተያዘ ራሱን ተቋሙን ከውስጥ ለማፍረስ እንደወሰነ መታወቅ አለበት። በተቋም ያሉት አባላት የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ልጆች ስለሆኑ በየብሔር ብሔረሰቦቻቸው ተከፋፍለው ተቋሙ ይፈረካከሳል። ይህ ደግሞ ሰበቡ እጅግ ከፍተኛ ነው። የሀገር መከላክያ ሠራዊት የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ጠብቆ አንድ ሀገር እንዲሰራ ከሚያስችሉት ተቋማት ዋናው ምሰሶ ነው። እዚህ ተቋም ውስጥ የሚመጣ መፈረካከስ ሀገሪቱ በሙሉ ይዞ ነው የሚፈረካክሰው። ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ዋነኛው የጥንቃቄ እርምጃ ደግሞ እንደ ተቋም ወደ ወገንተኛ ፖሊቲካ (የብሔር፣ የፓርቲ፣ የኋይማኖት ወዘተ) አለመግባት ነው። ሕገ-መንግሥታዊ ተልእኮውን ብቻ መፈጸም ነው። ስለዚህ የመከላክያ ኃይል በማጠናከርና በፖለቲካዊ ጫዋታ ውስጥ እንዲገባ ማሰብ በእሳት እንደመጫወት መሆኑ መታወቅ አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ ግን እንደው ድንገት ይህ ጉዳይ ተሳክቶ ሠራዊቱ ሀገሪቱን ለጥቂት ጊዜ ቢያረጋጋ፣ ውለታ ፈጽሚያለሁ የሚለው ሠራዊት ወይ እራሱ ንጉስ ይሆናል /ደርግ እንዳደረገው/ ወይም አንጋሽ ይሆንና የሀገሪቱ ፖሊቲካ ወታደሮቹ በሚፈልጉት መንገድ ያምሱታል። የፈለጉትን ይሰቅላሉ፣ ያልፈለጉትን ያወርዳሉ፤ በዚህ ሂደት ሀገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚባል ነገር ታጣለች። ወታደሮቹ እንደፈለጉ ይፈነጩባታል። ይህ ደግሞ አስርት አመታት ወደ ኋላ መመለስ ነው። ይህን የሚመኝ ንጹህ ህሊና ያለው ዜጋ ያለ አይመስለኝም።

በአጠቃላይ በጸጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚፈታ የፖሊቲካ ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። የጸጥታ ኃይሎች በተለይ የሀገር መከላክያ ሠራዊት ጥሩ ውጤት የሚያመጣው የትክክለኛ ፖሊቲካ ተቀጥያ፣ የትክክለኛ ፖሊቲካ ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲያገለግል ነው። በአጭሩ ሕገ-መንግሥቱ ያስቀመጠለትን ተልእኮ ሲፈጽም ብቻና ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት ተነግሮ ያደረ ጉዳይ ነው።

የመፍትሔ ሃሳቦች

ከላይ እንደተገለፀው ሀገራችን በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው። ይህ ቀውስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ፓለቲካዊ ሂደት በቅርብ ጊዜ ካልተጀመረ ሀገራችን እንደ አንድ ህልውናውና ሉዓላዊነቱን የጠበቀ ሀገር ለመቀጠል አዳጋች በሚሆንበት ሁኔታ ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ። የዚህ አሁን ሀገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ዋናው ምክንያት ደግሞ በትንሹ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች መተግበር አለመቻል ነው። መፍትሔውም ሰፊ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፍጠር መጀመር አለበት። በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባር ላይ በማዋል የሚጀመር ፖለቲካዊ ሂደት ዋና አላማው ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በማስፋት ህዝብ በመንግሥት ላይ ሊኖረው የሚገባውን የመቆጣጠር አቅም መጨመር፣ ተአማኒነት ያለው አስተዳደር ለመመስረትና፣ ከዚያም በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ጥልቀትና ስፋት እየጨመረ፣ እየጎላበት የሚሄድበትን መደላድል ማመቻቸት ይሆናል።

አሁን ሀገራችን ካለችበት ቀውስ ለመወጣት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ያለምንም መሸራረፍ ተግባር ላይ በማዋል ሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ያለምንም ተፅዕኖ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት መጀመር አለበት። ከዚህ በተጨማሪም ሕብረተሰቡ በሲቪክ ማህበራቱ ይህን በተናጠል በየግሉ በሚያደርገው ሰፊ ተሳትፎ፣ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ከፍ ማድረግ ይገባል። በሂደትም ህዝብ በመንግሥት አሰራር ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳድግበት፣ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በሚመሠረት ፖለቲካዊ ሥርዓትም ይበልጥ መተማመን የሚፈጠርበት፣ ቅሬታዎቹንና የሚያያቸውን ጉድለቶች ሳይሸማቀቅ የሚወያይበት፣ ከዚህ እየተነሳም መፍትሔ የሚያቀርብበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፍጠር አለበት። ከዚህ ጋር ጎን ለጎንም ህብረተሰቡ፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡን ከሚስማማውና የሀገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ይችላል ብሎ በሚያምንበት ፖለቲካዊ ፓርቲ ስር በእምነት የሚደራጅበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ይህ ሂደት በጊዜ እየተጠናከረ፣ ሰላማዊና ዴሞክራዊያዊ በሆነ አግባብ ችግሮችን በመፍታት ቀውሱን ማስወገድ የሚቻልበት ሁኔታ እየጎላ መምጣቱን የሚያይበት፣ በመሆኑም በሕብረተሰቡና በፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል መተማመን እየጠነከረ የሚሄድበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል።

በመጨረሻም ጊዜውንና ሕግን ጠብቆ በሚደረግ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ምልዓተ ህዝቡን ያሳተፈና ተአማኒነት ያላቸው ዓለም ዓቀፋዊ የምርጫ ታዛቢዎች የተሳተፉበት ምርጫ በማካሄድ ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ፓርቲ እንዲመረጥ ማስቻል ይገባል። የፖለቲካዊ ኃይሎችም በዚህ ሂደት የሚገኝን የምርጫ ውጤት በፀጋ የሚቀበልበት፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የሚስማሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።

ይህንን ሰፊ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ በመጨረሻም በሚቀጥለው የምርጫ ዘመን የሚቋጭ ፖለቲካዊ ሂደት ለማስፈፀም በሀገራችን ካሉት የተለያዩ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ተስማምተው የሚቋቋሙት ይህንን ሂደት የሚመራ መዋቅር መፈጠር አለበት። ይህ ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በመስማማት የሚፈጠር አላማው ከላይ የተገለፁትን ሁኔታዎች ማሳካት የሆነ አካል ከመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ተለይቶ ዋናው ስራው አሁን ያለውን ቀውስ በመፍታት ከላይ የተገለፀውን ምርጫ ማካሄድ ይሆናል። በዚህ ወቅት መንግሥታዊ መዋቅሩ የመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሳይስተጓጎል ሲደረግ እንደነበረው ስራውን ይቀጥላል። ይህ ሂደት የታለመለትን ግብ እንዲመታና በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በፍጥነት እስከ መጪው የምርጫ ግዜ ድረስ ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ።

እነዚህ ከላይ የተቀመጡትን አላማዎችና የመፍትሔ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከመናገርና ከመፃፍ የዘለለ በርካታ ተጨባጭ ስራዎች መሰራት እንዳባቸው ግልፅ ይመስለኛል። ይህንን ሰፊ ስራ በተለያዩ ሞያ (Discipline) ዕውቀት ያላቸው ሰዎች መጀመሪያ ሃሳቡን በአግባቡ አደራጅተው ቢያስቀምጡትና ከዚህ የተነሳ ዝርዝር ዕቅድ መጥቶለት ቢተግባር የበለጠ ውጤት ይኖረዋል። ይህ የሚታሰበው እንቅስቃሴ ገዥው ፖርቲና እሱ የሚመራው መንግሥትም ችግሮቹን በግልፅ እየተናገረና የመፍትሔ ፍላጎት ያለው መሆኑን እየገለፀ ስለሆነ በውስጡ ያሉትን ችግሮች (ችግሮቹን ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የማይቀበሉ ኃይሎች እንደሚኖሩ ግልፅ ስለሆነ) ፈትቶ የችግሩ መፍትሔ አካል ይሆናል ከሚል ይነሳል።

መፍትሔ ሃሳቦች አጠቃላይ ባህርይ ገዥው ፖርቲና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በጋር በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መብቶች በሙሉ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይሆናል። የተጠቀሰውን ሁኔታ ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት የሚለው ሃሳብ የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸው በሚያደርጉት ምክክር፣ መደራደር፣ ዝርዝር አካሄዱ የሚለወሰን ቢሆን ይመረጣል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ለመጠቆም ግን እንደገና መታየት ያለባቸው ህጎች ይኖራሉ። ለምሳሌ የምርጫ ሕግጋት፣ የሰላማዊ ሰልፍ፣ የሚድያ የፓርቲ ምዝገባ ወዘተ በጠቅላላ ህዝቡን አደራጅቶ በነፃ ሃሳቡን ገልፆ የፈለገውን የፖለቲካ ፖርቲ ተቀላቅሎ በፍላጎቱ እንዲመርጥ፣ ፖርቲዎቹም ሃሳባቸውን ተገቢው መንገድ በመንግሥት ሚዲያም ጭምር ያለ ተፅዕኖ እንዲገልፁ፣ ከሕግ አንፃር ሁኔታዎች ማመቻቸትና ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ፣

መልሶ መደራጀት ያለባቸው አካላት ይኖራሉ። ለምሳሌ የምርጫ ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የመንግሥት ሚድያ Board ወዘተ። የጠቅላላ እንቅስቃሴው ውጤት የሚለካው በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የመተማመን (confidence building) መንፈስ በመፍጠር ህብረተሰቡ በፖለቲካዊ ሂደት ትልቅ ተስፋ እንዲያሳድር በማደረግና በመጨረሻም ነፃ ዴሞክራሲያዊ መርጫ ተካሂዶ ውጤቱ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማስቻል ነው።

በዚህ ሂደት የፀጥታ ኃይሎች እንደሌሎቹ የመንግሥት የስራ አስፈፃሚ አካላት ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መግባት ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ዋናው ስራቸው የሀገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ኃይሎች በጋር መድረካቸው የተሰማሙበት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከማንኛውም የተጠቃ ኃይል (የመንግሥት ይሁን የፖለቲካ ኃይሎቹ) የሚያሰማሩት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ወይም የእንቅስቃሴውን ውጤት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ እንደቅስቃሴ መቆጣጠር አለባቸው።

ማጠቃለያ

በኔ አመለካከት ሀገራችን ለመፍታት አስቸጋሪ ወደሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ልትገባ ትችላለች። ከዚህም አልፎ እንደ አንድ ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀች ሀገር ለመቀጠል የማትችልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች ብዬ አስባለሁ። ይህንን ለማስቀረት የሚያስችል የመሰለኝ ሃሳብ አቅርብያለሁ፤ የኔ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክል የሚል አቋም የለኝም። ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ የመንደር ስድቡና አሉባልታውን አስቀርተን በጉዳዩ ላይ እንነጋገርበት የሚል ሃሳብ አለኝ። ችግር መኖሩ መንግሥት በግልፅ ያመነበት ስለሆነ ችግሩን መደበቅ አይቻልም። የችግሩ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይፈታሉ? በሚለው ሃሳብ ላይ ደግሞ የተለየ አስተሳሰብ ካለ (የመንግሥት የገዢው ፓርቲ ይሁን የሌላ የፖለቲካ ኃይል) እንስማው። በአጠቃላይ አሁን ሀገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያለ ፍርሃት ሙሉ ዴሞክራስያዊ መብታችንን ተጠቅመን እንወያይበት።

በእኔ አመለካከት ይህ አሁን የሚታየው ፖለቲካዊ ችግር ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ሁኔታው የሚነሳ ስለሆነ ሥርዓታዊ (Systemic) ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለሆነም ነው ኢህአዴግ ችግሩን እያየ እያወቀው እየተነጋገረበት እያለም ለመፍታት ያስቸገረው ብየ አምናለሁ። ለወደፊትም በገዢው ፓርቲ መዋቅርና ገዢው ፓርቲ በቀየሰውና በሚመራው የህዝብ እንቅስቃሴ ብቻ አይፈታም የምለው። ከገዢው ፓርቲ፣ ገዢው ፓርቲ ካዋቀረው መዋቅርና እሱ ከሚመራው የህዝብ እንቅስቃሴ በተጓዳኝና እኩል እንደሱ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው የሚያደርጉት ሰፊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተጨምሮበት ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ሁሉ መቋጫው ደግሞ ነፃ፣ ፍትሃዊና በገለልተኛ ዓለም ዓቀፍና ሀገራዊ ታዛቢዎች ይህ መሆኑ የተመሰከረለት ምርጫ በማካሄድ ህዝብ የመረጠውን መንግሥት ሲመሰረት ነው። ጉዳዩ ቀስ በቀስ እየተፈታ የሚሄድ ብዬ አምናለሁ። ህዝብ መንግሥትን በተለይ የስራ አስፈፃሚውን መቆጣጠር ሲችል ነው አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች የመፍትሔ መንገድ የሚበጀላቸው ብየ አምናለሁ።

ዴሞክራሲና ነፃ የህዝብ ምርጫ በአንድ ወቅት ሥልጣን ላይ ያለን ፓርቲ ፍላጎትና ምኞት ማሳክያ መሳርያዎች አይደሉም። ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት እፈልጋለሁ ብሎ ያመነ ፓርቲ ከዚህ ጋር አብሮ ሕገ ወጥ በሆነ የጉልበት መንገድ እኔን ብቻ እንጂ ሌላውን ፓርቲ እንዳትመርጥ ማለት የለበትም። ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራስያዊ ሥርዓት ሂደት ነው፤ ውጤት ደግሞ በህዝብ ፍላጎት የሚወሰን ነው። በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የዴሞክራስያዊ ሂደት ውጤት ማሸንፍም መሸነፍም መሆኑ አውቆ፣ አምኖ ተቀብሎ መሄድና በዚህ መንገድ መስራት አለበት። አንድ ፓርቲ “ዘላለም” በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚመኝ ከሆነ አስተማማኙ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት አይደለም።

**********

* ፀሐፊውን ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይችላሉ።

* ከዚህ ቀደም ከሌ/ጄ ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ጋር ያደረግናቸውን ቃለ-መጠይቆች እና ምላሾች ለማግኘት ይህን ሊንክ ይጫኑ፡- General Tsadkan GebreTinsae 

* ሌፍተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ነባር የህወሓት ታጋይና አመራር ሲሆኑ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማጆር ሹም ሆነው አገልግለዋል። በዓለም ዓቀፍ ፖሊሲና ትግበራ በማስተርስ ዲግሪ እና በቢዝነስ አድሚኒስተሬሽን በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል።

ምንጭ፡- ሆርን አፌርስ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ