አብርሃም በየነ

የጎንደር አመጽ Protest in Gonder July 31, 2016

የጎንደሮች የመለከት ድምፅ ኢትዮጵያ ነች። የእምቢልታው መስተጋቦ ኢትዮጵያዊነት ነው። የጥሩምባው የክተት ጥሪ የአማራው ህዝብ የህልውና ጥያቄ ነው። ስለሆነም አማራ ለህላዌው፣ ኦሮሞ ለመብቱ፣ ጋምቤላ ለመሬቱ፣ አፋር ላንድነቱ በጠላቱ በወያኔ ላይ የተነስ ጥሪውን ተቀብሎ በጋራ እንዲያምጽ ነጋሪቱ ተጎሹሟል።

ስንሞትም ባንድ ላይ፣ ስንኖርም ባንድ ላይ እንጂ፤ ተነጣጥለን አያምርብንም ነው የጎንደሮች የክተት አዋጅ መስተጋቦው። እናም እንደ ቅጠል የሚረግፈው ኦሮሞ፣ የግፉ ጽዋ ሞልቶ የሚደፋው የጋምቤላ ህዝብ፣ የመከራው ዳፋ ዘመናት ያስቆጠረው የአፋር ህዝብ፣ ዕድሜውን ሙሉ በሥርዓቱ ክርን እንደ ጌሾ ሲወቀጥ የኖረው ኦጋዴኑ ከዳር እስከ ዳር ሆ ብሎ ይነሳ ነው የጎንደሮች ጩኸት። ተንበርክከን ከምንሞት ታግለን እንገደል ነው የጩኸቱ መስተጋቦ።

የኛ ሞት የናንተ ሞት መሆኑን፣ የናንተም ሞት የኛ እንደ ሆነ አጢነን ተነሱ እንነሳ ነው የደወሉ ጥሪ። ስንወድቅ እንደ ህዝብ ተባብረን እንውደቅ። ስንነሳም ሆ ብለን በሕብረት እንነሳ ነው የመለከቱ ክተት። እምቢኝ ለመብቴ፣ እምቢኝ ለነፃነቴ፣ ... አልገዛም ብለን እናምጽ ነው የዕምቢልታው እንጉርጉሮ። እንደ ዶሮ አንገታችን እየተጠመዘዘ በተናጥል ከምንሞት እንደ ጀግና መክተን እንውደቅ ነው የክተቱ አዋጅ። እናም ጎንደሮች ታጠቅ ብለው ተነስተዋል።

“ሱሪ አሰፋሁ ብየ ልነሳ ልቀመጥ ልሄድ ከለከልኝ
ቀዶት ቀዶት መጓዝ ይሻላል መሰለኝ፤”

ብሎ የተነሳው የጎንደሮች ትግል ቢያንስ ስድስት ድሎችን ተቀዳጅቷል።

ሀ. በኢትዮጵያ ህዝብ ሥነ ልቦና ለአርባ ዓመት ጎጆ ሠርቶ የኖረውን የፍርሃት ቆፈን የጉም ሽንት አድርጎታል

ለ. የወያኔን አንድ ለአምስት የስለላ መርበብ በጣጥሶ ዋጋ ነስቶታል።

ሐ. የጎንደር ህዝብ ትግል የአማራው ህዝብ የማንነት ጥያቄ መሆኑ ገዝፎ እንዲታይ አድርጎታል።

መ. “በስረና .. በቅልጺምና” የሚለውን የወያኔን ትምክህት ቢከፍቱ ተልባ አድርጎታል።

ሠ. የአገዛዙን የዕድሜ ገመድ ህዝባዊ አመጽ ሊያሳጥረው እንደሚችል አስገንዝቧል።

ረ. የጎንደሮች ትግል ግብአቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ድል መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም ግንዛቤ አስጨብጧል።

ቀጣዩ ትግል ምን ሊሆን ይገባዋል?

የአመጽ እሳቱ ተለኩሷል። አምጹ ቋያ እንዲሆንና ነበልባሉም ወያኔን እንዲለበልበው ህዝብ በያለበት ተቃውሞውን ማብረድ የለበትም። ድርድርና ሽምግልና የወያኔ መሰረታዊ የትጥቅ ማስፈቻ መሣሪያዎች ሆነው ሲያገለግሉ መኖራቸውን ካለፉት ተመክሮዎቹ ትምህርት መውሰድ ብልህነት ነው።

ሀ ብሎ ወያኔ ትግል ሲጀምር ተሃትን እንደራደር በማለት ለድርድር የተቀመጡትን የተሃት መሪዎች ከተኙበት አርዶ ድርጅቱን ደብዛውን ሊያጠፋ ችሏል። ከኢህአፓ ጋርም በጦርነት ላለመፈላለግ ከተዋዋሉ በኋላ፤ በስምምነቱ መሰረት የውሉን ሰነድ ሁለቱም ድርጅቶች ለአባሎቻቸው እንደሚያስረዱ የተስማሙትን ውል ኢህአፓ ተግባራዊ በማደረግ የሠራዊቱን የህሊና ዝግጅት ሲያቀዘቅዝ፤ ወያኔ ግን በተጻራሪው ለጦርነት ሲያዘጋጅ ባጅቶ ኢህአፓ ኃይሎቹን በከፊል ወደ ወሎ ሲልክ ጊዜ ጠብቆ ድንገተኛ ጦርነት በመክፈት ከአሲምባ ማስወጣት ችሏል።

ሥልጣን ከያዘ በኋልም የከፋኝን መሪ ኪዳነ ማርያምን በቄስና በታቦት ተማጽኖ በሽምግልና ካስገባ በኋላ ገድሎታል። ስለዚህ እነ ኮሎኔል ደመቀና ሌሎቹም የኮሚቴ አባላት የኪዳነ ማርያም ዕጣ ፈንታ የነርሱም ዕጣ ፈንታ እንዳይሆን ድርድርና ሽምግልና ብሎ ህዝብ መሞኘት የለበትም።

ድርድርና ሽምግልና ውጤታማ የሚሆኑት ከኃይልና ከጉልበት ጋር ሲጣመሩ ብቻ ነው። ስለሆነም ህዝብ ተፈላጊውን ጉልበትና ኃይል እስኪያካብት ድረስ ለድርድርና ለሽምግልና መንበርከክ የለበትም። ድርድርና ሽምግልና የወያኔ የጊዜ መግዣ መሣሪያዎች ናቸውና ከወዲሁ ነቅቶ ዘብ ሊቆምባቸው ይገባል። ሞኝን ዝንተለት ሲያሞኙት ይኖሯል፤ ብልህን ግን አንዴ ብቻ ያሞኙታል እንዲሉ ህዝብ በወያኔ ድርድርና ሽምግልና እንዳይታለል ብልህነት ይጠበቅበታል።

በአሁኗ ወሳኝ ሰዓት ይታጠቋል እንጂ ትጥቅ አይፈቱም። ይበለኋል እንጂ አይሞኙም። ይበልጧል እንጂ አይበለጡም። የድል ዋስትናው መደራጀት መሆኑንም አይዘነጉም። የጠላትን ምስጢር ለማግኘት የመባዘንን ያክል የራስንም ምስጢር አጥብቆ መቋጠር የግድ ነው። ድል የጅግንነት ብቻ ውጤት አይደለም። ድል ጠላትን የማታለል (art of deceit) የክህሎት ውጤት መሆኑንም ያጤኗል።

መመከት በራሱ ማጥቃት ስለሆነ፤ ህዝብ አልሞትባይ ተጋዳይነቱን የማጥቂያ መሣሪያው አድርጎ ሊገለገልበት ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን ቀዳማይ ጠላቱ ቆዳውን ገልብጦ የለበሰው “ወገኑ” መሆኑን አውቆ የጽዳት ዘመቻውን ከራሱ በራፍ መጀመር አለበት። የውስጥ አርበኛውን ሳያጸዳ ዋነኛውን ጠላቱን ድል መምታት ቀላል እንደማይሆን ሊያጤነው ይገባል። የሚያስጠቃው አሾክሿኪው የራሱ ሰው ስለሆነ፦

“ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው፤”

እንዲሉ ለጠላት ጆሮ እሚጠባውን አራሙቻ መንቀል ለነገ የማይሉት የትግል የቤት ሥራ ነው። ዛሬ ለሆዱ ያደረው ብዙ ስለሆነ ትግሉን ሊያከብደው እንደሚችል ማጤን ያሻል። ከአቅም በላይ የሆነን ጠላት ማቸነፍ የሚቻለው እየሸራረፉ ስስ ብልቱን በመምታት ነው። የጠላት መደላድሉ ደጋፊው መሆኑን አበክሮ መገንዘብ የግድ ነው። ስለሆነም ጠላት የቆመበትን መሬት መናድ ቀዳማይ የትግል ስልት ነው።

በጠላትና በደጋፊው መሃል ክፍተት እንዲኖር የድጋፍ መሰረቱን መሸርሸር የግድ ነው። ይህ ሲሆን ግን ጊዜ ወስዶ አጥንቶ እንጂ በጥርጣሬ ብቻ እርምጃ መውሰድ ወደ ውድቀት ስለሚያመራ መጠንቀቅ ያሻል። ትግርኛ የተናገረ ሁሉም ወያኔ አይደለም። ባንጻሩ ግን የአማራ ወያኔ፣ የኦሮሞ ወያኔ፣ የጉራጌ ወያኔ፣ ... መኖሩ ዘይን ተረፍ ነው። ስለሆነም እነዚህን የጠላት ደጋፊዎች ከህዝብ መነጠል አንዱ የማጥቂያ መሣሪያ ነው።

እናም እኒህን የጠላት ደጋፊዎች ሰላምታ መንሳት፤ በደስታቸውም ሆነ በመከራቸው ተካፋይ አለመሆን። ለንግድ ተቋማቸው ገበያተኛ ባለመሆን ንግዳቸውን ማክሰር። የጠላትን ደጋፊዎች ቤት አለመግዛት። ለነርሱም አለመሸጥ። ትርፍ ቤቶችን ለነርሱ አለማከራየትና የነርሱን ትርፍ ቤቶችም አለመከራየት። በጠቅላላው ደጋፊዎቹን ከጎረቤት እሳት እንዳይጭሩ በማድረግ ማግለል። እነዚህ እርምጃዎች ከመግደል የበለጠ ወጤት ስላላቸው ህዝቡ ሳያሰልስ ሊያዘወትራቸው ይገባል።

እርምጃዎቹ በሀገር ቤት ብቻ ሳይሆን፤ በውጭ ሀገርም መተግበር ይኖርባቸዋል። በተለይ በውጭ ሀገር የሚኖረው ፀረ-ወያኔ ኃይል በያለበት ይህንኑ እርምጃ ከወሰደ፤ ጉዳቱ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ እንደሚሰማቸው አንድና ሁለት የለውም። ስለሆነም ትግብርቱ ይተግበር።

ድል የህዝብ ነው።

አብርሃም በየነ
ሐምሌ 2008

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!