ታሪካዊው የጎንደር ሰልፍ እና እንድምታው
ክንፉ አሰፋ
በሰሞነኛው የአዲስ አቤ ቀልድ ልጀምር። ወጣቱ፣ ሱሪ ለመግዛት ወጥቶ አንድ የልብስ ሱቅ ወስጥ ገባ። ባለ ሱቁ ጠየቀው። “የቻይና ይሁንልህ ወይንስ የአውሮፓ ሱሪ?” ወጣቱም መለሰ። “የለም የለም ... የጎንደሩን ሱሪ ነው የምፈልገው።”
እስረኞችን የማስፈታቱ ሰላማዊ ጥያቄ የእብሪት መልስ ሲያገኝ፤ ጨዋታውም ተቀየረ። “እንዲያውም አናውቅህም። ከህዝብ ጫንቃ ላይ ወረድ” ሲል ነበር የጎንደር ህዝብ ብረትን ሰብሮ ዙፋኑን የነቀነቀው። “ወንዱን በምርቃና ሴቱን በቃና አደንዝዘን ይዘነዋል!” ያሉት ህዝብ ከቶውንም እንዳልተዘናጋ አሳየን ... የመናገር እና ሃሳብን ያለፍርሃት የመግለጽ መብትን ህወሓት ሲፈልግ የሚሰጥ ሲያሻው ደግሞ የሚነፍገው የግል ሀብቱ አድርጎ ለ25 ዓመታት ሰንብቶ ነበር። ይህ መብት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቆ ጎንደር ላይ ተከበረ። በባህርዳር፣ በደሴ፣ በኦሮምያ፣ በመቀሌ ... ላይም ይቀጥላል ...
ከአርባ ዓመት በፊት የቬትናም ህዝብ ባዕዳን ያነገሱትን አሻንጉሊት መንግሥት በኃይል ሲነቀንቀው፤ አሻንጉሊቱ ሥርዓት ለህዝብ እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አልነበረውም። የህዝብ ያልነበረው ይህ መንግሥት ወደ አመሻሹ ላይ ካመሸገበት የአይጥ ጉድጓድ ሆኖ መግለጫ ሰጠ። እንዲህ ሲል፣
“ሥልጣኑን ለህዝብ ለማስረከብ ከንጋት ጀምሮ እየጠበቅኩ ነው። ...“
የሰሜኑ ህዝብም ምላሽ የተጠበቀው ነበር፣ “ይህን ለማድረግ ትንሽ ዘገየህ። ... የሌለህን ሥልጣን እንዴትስ ልታስረክብ ትችላለህ? ...“
ይህ ተላላኪ መንግሥት ወድቆ የነበረው ከህዝባዊው አመጽ እና እንቢተኝነት በፊት መሆኑን አላስተዋለውም። ሥርዓቱ የወደቀው ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ ሲሽረው ነበር። ህዝብ "መንግሥት የለም!" ማለት የጀመረው ለአፋኝ አዋጆች አልንበረከክም ብሎ አደባባይ በወጣ ግዜ ነበር። ይህ መንግሥት የተወገደውም ለዜጋው የመብት ጥያቄ የጥይት ምላሽ በሰጠ ግዜ ነው።
"የዘመናችን ትልቁ ክስተት!" ብሎታል የኩባው ፊደል ካስትሮ።
ባለፈው እሁድ በጎንደር የታየው የህዝብ እንቢተኝነትም የዘመናችን ትልቁ ክስተት ነበር። ህዝብ የተፈጥሮ መብቱን ተነጥቆ በጫንቃው ላይ ተጭኖ የነበረውን ቀንበር ያስወገደበት ክስተት! ሥልጣን የህዝብ እንጂ የጥቂቶች መፈንጫ አለመሆኑ የታየበት ክስተት። በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ወርቃማ አሻራ ጥሎ ያለፈ፤ ለሀገር የፍቅር፣ ለዜጎች የፍትህ እና የሕብረት ሐውልትን የተከለ ክስተት። የማይቻል የሚመስለውን ተራራ ደርምሶ የናደ ኃይል ስለነበር፤ ታሪክ ይህንን ሰልፍ ይዘክረዋል።
ግዙፉ የጎንደር ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጠናቀቀ፣ የህወሓት መገናኛ ብዙኀን የሆነው ፋና ራዲዮ ሲዘግብ፤
"የጎንደሩ የተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጠናቀቀ። ..." ነበር ያለው። “ጋዜጠኛው” ከምጥ እንደተገላገለች ሴት በረጅም ተነፈሰ። በስፍራው ያልነበረው መገናኛ ብዙኀን በስፍራው የነበረውን ክስተት ሲደሰኩር፣ ለሰላማዊ ሰልፍ ፍቃድ የተከለከለ ህዝብ በራሱ ፈቃድ መውጣቱን፤ በሰልፉም ላይ እነሱ የከለከሉትን ባንዲራ ብቻ መያዙን ጨምሮ አበሰረ።
ይህንን የዜና እወጃ ያዳመጠው የጎንደር ህዝብ “ይህን ለማድረግ ትንሽ ዘገየህ። ...“ ሳይለው አልቀረም። ልክ እንደ አሻንጉሊቱ የቬትናም መንግሥት፣ የህወሓት የአፈና ግዜ ማብቃቱን ያረጋገጡለት ይመስላል። አንድ ሥርዓት መንግሥትነቱ የሚያከትመው ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ ሲረግጠው እና ህዝብም ለሱ አዋጅ ተገዥ አለመሆኑን ሲያሳየው ነው። አላስተዋልነው ይሆናል እንጂ ህወሓት ዕድሜውን ጨርሶ በባከነ ሰዓት እንደሚንገዳገድ “የልማቱ” ተጠቃሚዎች ሳይቀሩ ነግረውን ነበር። እነ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ እና አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) ከማጀታቸው ወጣ ወጣ ብለው ሀገሪቱ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ፣ መንግሥት በሚባለው እና በፓርቲ መሃል እንኳን ልዩነት እንደጠፋባቸው ነግረውናል። ይህ ጉዳይ ጻድቃንን ግራ ካጋባው ሌላው ምን ይበል? ጆቤ የህወሓት ሙስና እና የፍትህ እጦት ካስፈራው ተራው ህዝብ ምን ይሰማው? የሚገርመው ነገር፣ እያየነው ያለው ቀውስ የነ ፃድቃን እና የነ ጆቤ "ሌጋሲ"ም ጭምር መሆኑ ነው።
የጎንደሩ አመጽ ሁለት አበይት ነገሮችን ጥሎልን አልፏል። አንደኛው መተባበር እና መደጋገፍን ማስተማሩ ነው። አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንዲሉ፤ በተለይ የኦሮሞ ወገናችን ደም የሁላችንም ደም ነው ማለታቸው የህወሓትን ከፈፍሎ መግዛት እቅድ የሚያፈርስ መፈክር ነበር። የአኙዋክ መገደል ከአማራው መገደል ተለይቶ አለመታየቱን፣ የሲዳማው ሰቆቃ ... የሁሉም ወገን ሰቆቃ እንደሆነ ... የሚያሳይ ትዕይንት ነበር። በማን አለብኝነት የሚጫኑ አዋጆችን መስበር መቻሉ ደግሞ ሥልጣን ዛሬ በህዝብ እንጂ በአንባገነኖች እጅ አለመሆኑን አሳይቶናል። ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ለመብቱ ፈቃድ እንደማያስፈልገው ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም ጥንት አባቶቹ በአደራ ያስረከቡትን ባንዲራ ይዞ በመውጣቱም የሥርዓቱን ማክተም አሳይቶናል።
የማይነካ የመሰለው ጉልበቱ ሲፈታ፣ የማይሰበር የመሰለው ኃይል ሲሰበር ይህ የመጀመርያው አይደለም። በዘረፉት ሀብት እና በሠራዊታቸው ጉልበት ብቻ እየተማመኑ የገዛ ወገናቸውን ሲበድሉ የኖሩ አንባገነኖች ከቶውንም መቶ ዓመት ሲቆዩ አላየንም። በዓለማችን የተነሱ ብርቱ የሚባሉ አንባገነኖች በህዝብ ኃይል እየተዋረዱ መውደቃቸውን የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።
የማያልቅ መንገድ እና የማይነጋ ጨለማ የለም። በአንጻሩ የማይመሽ ቀን የለም። የብዙዎ አንባገነኖች ችግር በጉልበታቸው ብቻ በመተማመን ዙፋናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ ማሰባቸው ነው። በዚህች ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ለውጥ የሰው ልጅ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው። ዘገምታኛም ይሁን ቅጽበታዊ፣ እኛም በተራችን ለውጥን የምናይበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
ይህ ሊሆን ግድ ነው። ጽዋ እስኪሞላ የሚጨመርለትን ሁሉ ይሸከም እና ከሞላ በኋላ መፍሰሱ ሳይንሳዊም፤ ተፈጥሯዊም ሕግ ነውና፤ ከአቅሙ በላይ ሲሞላ ሁሉም ነገር ይፈስሳል። ከየአቅጣጫው ህዝቡን ገፍተው እዚህ አደረሱት። እነሆም የህዝብን የቁጣ ወላፈን ትላንት በኦሮሞ ወንድሞቻችን፣ ዛሬ ደግሞ በጎንደር አዩት። ነገ በደቡብ፣ ከዚያም በምስራቅ እና በምዕራብ ይቀጥላል። ይህ ቁጣ የመጀመርያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም።
"የዚህን መንግሥት ያህል በህዝብ ክፉኛ የተጠላ ሥርዓት በሕይወት ዘመኔ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም።" ሲሉ አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣን ሲናገሩ አድምጫለሁ። ከውስጣዊ ሰዎች እንደምንሰማው ከሆነ 90 በመቶ የሚሆኑት የኦህዴድ እና የብአዴን አመራር አባላት ከህወሓት ጋር ሆድና ጀርባ ከሆኑ ሰንበትበት ብለዋል፤ የህዝቡ በደል አንገሽግሿቸው ህዝባዊውን አመጽ ለመቀላቀል በመጠባበቅ ላይም ናቸው። በራሱ በአገዛዙ ውስጥ ያሉ ሁለተኛ ረድፈኞች ሳይቀሩ እንደሚመሰክሩት፤ የህወሓት ወንጀል ደርግ ከሠራው ወንጀል እንኳን ሊወዳደር አይችልም። የበደሉን ብዛት እና የዝርፊያውን ግዙፍነት የሚመሰክሩት ሁሉ ይህ ሥርዓት በቅርጽ እንጂ በይዘት ልዩነት እንደሌለ ነው እየመሰከሩ ያሉት። “በአሁን ሰዓት በመንግሥት ስም የሚነግድ የማፍያ ቡድን እንጂ መንግሥት የለም!” ነው ያለው አንድ ከፍተኛ የብአዴን ሰው።
ህዝቡ ይህንን ሥርዓት ለምን አይጥላው? ሁሉም ስለታፈነ ህዝብ ነው የሚናገሩት። አንድ ለአምስት ተጠርንፎ የተያዘ ህዝብ፣ እስከውስጥ ገመናው በኢህአዴግኛ መስፈርት እየተገመገመ የሚሰቃይ ህዝብ፣ ሌት ተቀን በሙስና እንደመዥገር እየተበዘበዘ ያለ ህዝብ። ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል እንኳን ለመጥራት እየተጸየፉ፣ ሀገርን እና ታሪካዊ ባንድራዋን እየጠሉ፣ ... እንዴት ሊቆዩ ይችላሉ?
ለችግሮች ሁሉ መፍትሔያቸው ጠመንጃ ነው። የጎንደሩንም ችግር በጠመንጃ ለመፍታት እየመከሩ ይገኛሉ። በመጀመርያ ከህዝቡ መሣሪያ መንጠቅ። ከዚያም እንደ በኦሮሞ ወጣቶች እንዳደረግነው በአልሞ ተኳሾች አማጺውን መልቀም ይኖርብናል ሲሉ ዶ/ር ደብረጽዮን መናገራቸው እየተሰማ ነው። ከ500 ያላነሱ የኦሮሞ ወገኖቻችንን ጨርሰው ሲያበቁ፤ እርምጃው ተመጣጣኝ እና ፍትሃዊ ነው ሲሉ ቀለዱብን። ለመሆኑ ከአንድ ሰብዓዊ ፍጡር እንደዚህ አይነት ፍጹም አረመኔያዊ ነገር ይሰማል? የጭካኔ ጣርያው የት ድረስ ነው? ...
መገናኛ ብዙኀን ላይ እየወጡ በህዝብ ላይ የሚያላግጡት ነገር ደግሞ እጅግ ያሳምማል። ለጥያቄዎች ሁሉ አንድ መልስ ነው ያላቸው። መልሱም "ሻዕቢያ" የሚባል ግዑዝ ነገር። የኦሮሞ ህዝብ ሰቆቃ ይቁም ብለው የተነሱት ወጣቶች በሙሉ “የታጠቁ እና የተደራጁ የሻዕቢያ ቡድኖች ናቸው” ተባልን። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ያነሱት ወገኖች ሁሉ የሻዕቢያ ተላላኪዎች እንደሆኑ ነገሩን። የታገልነው ለነጻነታችን እንጂ ትግሬ ለመሆን አይደለም ያሉት ከራሳቸው ውስጥ ያሉ ታጋዮችም የሻዕቢያ መልዕክተኞች ናቸው። የችግሮቻቸው ሁሉ መንስኤው ሻዕቢያ ነው። ይህ ሊሆን ይችላል። 10 ሰው የሻዕቢያ ተላላኪ ሊሆን ይችላል። 100 ሰውም የሻዕቢያ ተላላኪ ሊሆን ይችላል። 1000 ሰው የሻዕቢያ ተላላኪ ሊሆን ይችላል። አንድ ሚልየን ህዝብ የሻዕቢያ ተላላኪ ከሆነ ግን፤ ከነጻነት ትግሉ ጀርባ ሻዕቢያ እንዳለ ነው እየነገሩን ያሉት።
ፖለቲካን እንደ ማስንቆ እየቃኘ የሚጫወትበትን ህዝብ፣ እነሱ የሚናገሩትን ሁሉ እንደ ስንዴ እየፈለፈለ እንደሚያበጥረው እንኳን አይገነዘቡም።
የምስራቁ ፈላስፋ ኮንፋሽየስ “ትልቁ እውቀት የራስን የድንቁርና መጠን ጠንቅቆ ማወቅ ነው“ ይለናል። ይህንን ሁሉ ህዝብ የሻዕቢያ ተላላኪ ሲሉ በድፍረት መናገራቸው፤ የድንቁርናቸው መጠን ምን ያህል የወረደ መሆኑን ያመላክተናል። “በወልቃይት ጠገዴ ስቃይ እና እስር ይብቃ!“ የሚለው መፈክር የሻዕቢያ ከሆነ፤ ሻዕቢያ ለወልቃይት ህዝብ መብት በመነሳቱ ሊወገዝ ሳይሆን፤ ይልቁንም ሊወደስ ይገባዋል። እንደ ጣዕረ-ሞት እየተከተለ እንቅልፍ የሚነሳቸው ሻዕቢያ “ለሱዳን የተሸጠው ድንበራችን ባስቸኳይ ይመለስ!“ የሚል መልዕክት ይዞ ህዝብን ማሰለፍ ከቻለ፤ ወዳጅ እንጂ ጠላት አይሆንም።
ሁሌም ህዝብን ማታለል የሚችሉ ይመስላቸዋል። ትላንት የተጫወቱበትን ካርታ ሳይቀይሩ ዛሬም ለመጫወት ይሞክራሉ። በኮብል ስቶን፣ በአነስተኛና ጥቃቅን፣ ... ወዘተ የተያዘ ወጣት ሁሉ፣ በደል ያላመረረው፣ ንቀት ያላስቆጣው መሆኑን አሁን ማረጋገጥ ይችላሉ።
ካሁን በኋላ እነሱ ሊያደርጉ የሚችሉት አንድ አስፈሪ ነገር ቢኖር፤ የትግራይን ህዝብ ከወንድሙ የአማራና ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ደም ማቃባት ብቻ ነው። እዚህ ላይ ነው ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ የሚገባው። የትግራይ ህዝብ የዚህ አናሳ ቡድን እዳ ከፋይ መሆን የለበትም። የትግራይ ህዝብም በቡድን-በቡድን ተከፋፍሎ የሚሰቃይ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። የተገመገመ፣ የሚገመግም እና ሌት ተቀን የሚገመግም ቡድን! ይህ ህዝብም ነጻ መውጣት አለበት።