መሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን

Stop shouting

በኦሮሚያ ተቀጣጥሎ ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለተዛመተው ሰላማዊ የፍትሕ ይገባኛል ጥያቄ፤ የግድያና የእስራት ምላሽ እየሰጠ ያለውና በቅርቡም ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኀንና ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ የመብት እንጥፍጣፊ እንዳይኖራቸው “በባርነት አዋጁ” የደነገገው የወያኔ ሥርዓት፤ ለሩብ ምዕተ ዓመት ሲሠራ የቆያውንና አሁንም እየሠራ ያለውን ሁሉ ያስተዋለ በሀገራችን የተከሰተውን ስር የሰደደ የፖለቲካ ቀውስ መረዳት አያዳግተውም።

ይህ የጥቂት ሽፍቶች ሥርዓት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ በሚዳክርበትና ሀገራችንን ወደለየለት የጥፋት ጎዳና በፍጥነት እየጋለበ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፤ ኢትዮጵያችን ከልጆቿ የምትጠብቀው አስተውሎት የተሞላበት እርምጃ ብቻ ነው። ኃላፊነት የሚሰማውና ለሀገር ተቆርቋሪ የሆነ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ በፅናት በገዢው ቡድን ላይ የሚደረገውን ጫና ማጠናከርና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚበጀውን በማሰናዳት ሥራ ላይ መጠመድ አለበት። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየሆነ የምናያውም ይህንኑ ነው።

ይሁን እንጂ፤ ምስኪኑ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ከሰው በላው መንጋጋ ለማላቀቅ ክቡር ሕይወቱን እየከፈለና ከወገኑ ጋር ወንድማማችነቱን በደሙ ማኅተም እያረጋገጠ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ከየአቅጣጫው በመሰማት ላይ ያሉ ጎሣ ተኮር የአደረጃጀትና የትግል ቅስቀሳዎች እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ የግፍ በትር ያልተገረፈ፤ ሰብአዊ መብቱ ያልተደፈጠጠ፤ ወንድም፣ እኅት፣ ወላጅ፣ ዘመድ አልያም ጓደኛው በግፍ ያልታሰረበትና ያልተገደለበት፤ እንዲሁም ሀብት ንብረቱን ያልተዘረፈ የኅብረተሰብ ክፍል ፈልጎ ማግኘት ከቶ አይታሰብም። ይህንን ወደር የለሽ ግፍና በደል ጎሣ ተኮር አድርጎ መቀስቀስና ማራገብ ከባድ አደጋ ያጭራል። ይህን ዓይነት ኋላቀር፣ ጠባብ፣ ኃይልን የሚበታትን፣ የጊዜውን ነባራዊ ሁኔታ ፈፅሞ ያላገናዘበና የአገራችንን ችግር የማይፈታ የትግል ስልት፤ ገዢው ቡድን ሕዝብን በመጨፍጨፉ እንዲተጋና ሥልጣኑንም እንዲያራዝም ይሁንታ ከመስጠት አልፎ የአገርንና የሕዝብን አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው።

ሰፊው ኢትዮጵያዊ የሚያሰማው ጩኸትና የሚያካሂደው ትግል፤ አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን በሚያራግቧቸው ሸውራራ መልዕክቶች ሊቀለበሱ አይገባም። ጎሣ ጎሣ የምትለውን ጨዋታ ብቻ መጫወት የሚመርጡ ልሂቃን ለሩብ ምዕተ ዓመት በወያኔ ጥላቻንና መለያየትን ሲሰበክ የኖረው ሕዝብ ከሚያሳየው የአንድነት መንፈስና ትግል ለመማር ቢሞክሩ መልካም ነበር።

አሁን ላይ ሆነን ሊያሳስበንና ሊያወያየን የሚገባው ጉዳይ የእንጀራ ገመዱ በፍጥነት እያጠረ የሚገኘው ይህ ሥርዓት ከተወገደ በኋላ ስለምንረከባት ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ እንጂ፤ ተለያይተን ስለምንበታትናት ሀገር መሆን የለበትም። አገራችንንና ሕዝቧን ሊመጣ ከሚችለው ጥፋት ለማዳን የጎሣ ተኮሩ አስተሳሰብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስና በጋራ ዓላማ መተካት አለበት። በጎሣ አሰላለፍ ወያኔን ታግሎ መጣልና ኢትዮጵያን ከጥፋት ማዳን ፈፅሞ አይቻልም። ይህ ወቅት የተጣመሩትን ኢትዮጵያውያን እጆች ይዘን ሩቅ ለመጓዝ የምናልምበት መሆን ይገባዋል። ወያኔ የዘመተው በኢትዮጵያውያን ሁሉ ላይ እንደመሆኑ፤ ልንዘምትበት የሚገባው ኢትዮጵያውያን ሆነን ነው። ዘረኛው ሥርዓት የተከለብንን የዘረኝነት መርዝ ነቅለን እስካልጣልን ድረስ፤ ይህ አገዛዝ በጭራሽ አይወድቅም፤ ቢወድቅም ውጤቱ አያምርም።

አምላክ ኢትዮጵያችንን ይጠብቅ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ