ተጽእኖ ፈጣሪን በመፍጠር በተጽእኖ ስር የወደቀ መንጋ እንዳንፈጥር!
የትነበርክ ታደለ (የግል አስተያየት)
ይሄን አገላለጽ በበርካታ አነቃቂ (Inspirational) ዲስኩሮች ላይ እንሰማዋለን። "ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ለማፍራት ..." ወዘተ ሲባል እንሰማለን።
እኔ በግሌ እየቆየሁ ሳስበው ግን ይሄ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን የማፍራት ድካማችን መጨረሻው በጎ እንዳልሆነ ነው የተገነዘብኩት። ጥቂት ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ባፈራን ቁጥር ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ተከታይ መንጋ እንደምናፈራ አስባለሁ።
ለምን በሉኝ በምሳሌ አስረዳለሁ።
ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ማፍራት እጅግ ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከተጽእኖ ፈጣሪዎች ተጽእኖ ነጻ የሆነ ዜጋ ማግኘት ግን እጅግ ከባድ ነገር ነው።
ምሳሌዎቻችን ያው እንደተለመደው ዕድሜ ልካችንን ተጽእኖ ፈጥረውብን አልላቀቃቸው ያልናቸው ምዕራባውያኑ ናቸው። እነዚህ አገራት ኮከቦችን በማፍራት ጉዳይ ላይ ቀን ከለሊት እንደለፉ ነው።
ሚዲያዎቻቸው በየቀኑ ስለኮከቦች ሲለፍፉ ይውላሉ። የኮከቦቻቸው ንግግር፣ ሳቅና ጨዋታ፣ አለባበስና አበላል፣ ሀዘንና ደስታ፣ ኮከቦች የሚለብሷቸው ልብሶች፣ የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ሁሉ እንደ ትልቅ ቁም ነገር ሲተነተን ውሎ ሲተነተን ያድራል። ይህ ብቻ አይደለም። የኮከቦቹ ባህሪ፣ እምነታቸው፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፍላጎታቸው፣ የአደንዛዥ እጽ ሱሳቸው ... ወዘተ ለተከታዩ መንጋ ሲነገረው ይውላል።
እንግዲህ እነዚህ ምዕራባውያን "እኛ በዓለም ላይ ነጻነት ያለንና፣ የፈለግነውን ለማድረግ ወይም ለመምረጥ ፍጹን ነጻ ፍጥረታት ነን፣ ማንም ተጽእኖ አያሳድርብን ..." እያሉ ይነግሩናል። እንደምንመለከትው ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው።
ያው እነሱም የኮከቦቻቸው ተከታዮች ናቸው። ምርጫዎቻቸው ተመርጦላቸው ነው፣ ሃሳባቸው ታስቦላቸው ነው፣ ድርጊቶቻቸው እንኳ ሳይቀር ከተጽእኖ ፈጣሪዎቻቸው የተቀዳ ነው። እነዚህ ኮከቦች ያደረጉት ነገር እንደ ትክክል፣ እውነትና ቢደረግ "ምንም ጣጣ የሌለው" ነገር ነው። ምክንያቱም እነ ተጽእኖ ፈጣሪዎቹ አድርገውታልና ...።
ለዚህ ነው ተጽእኖ ፈጣሪዎች ወይም ከዋክብት ላይ ያጠፋነው ጊዜ በኋላ መንጋውን እንዳያጠፋ ለማለት የተነሳሁት። ተጽእኖ መፍጠር ሳይሆን ተጽእኖ የማይፈጠርበት ዜጋ ለመፍጠር ብንተጋ ራሱን ችሎ የቆመ፣ ነጻ፣ የራሱን መንገድ የሚጓዝ ሙሉ ሰው መፍጠር እንችላለን።
ሰላም!