ክንፉ አሰፋ

TPLF dialogue

የሙስናውን የመረጃ እጦት ኩምክና ሰምተን ስቀን ሳንጨርስ ሰሞኑን ደግሞ የውይይት ፉገራ አመጡ። ልክ እንደቀበሌ ስብሰባ ተቃዋሚዎችን በአዳራሽ ውስጥ አጉረው ሲያበቁ እነሱ ከመድረክ ሆነው ይቀልዱባቸዋል። የNBC ውን፤ የዴቭድ ሌተርማን 'ሌት ናይት ሾው" (late night show) የሚመስል ነገር በቴሌቭዥን ለቀውብን ነበር። ሁለቱ ባለሥልጣኖች፤ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ መድረክ ላይ ጉብ ብለዋል። በአነስተኛና በጥቃቅን የተደራጁ 21 የፓርቲ መሪዎች ደግሞ እንደ ቲያትር ተመልካች አዳራሹ ውስጥ ተሰይመዋል። እነዚያ ከላይ፣ እነዚህ ከታች ተቀምጠዋል። እነዚያ ይናገራሉ፣ እነዚህ ደግሞ ይሰማሉ። ... ሌላ ምን አማራጭ ሊኖራቸው?

ውይይት ብለውታል። ሌላው አይደለም። አቀማመጣቸው ብቻ የውይይቱን አቅም እና ኃይል ያሳብቃል። በሙስናው የመረጃ እጦትት ኩምክና ስቀን ሳናበቃ ነው ይህንን ፉገራ የለቀቁት። ሲት ኮም ክፍል ሁለት።

አይጋ ፎረም ላይ ስለሁኔታው የጻፉት "ባለሙያ" የአገራችን ችግሮች በውይይት ብቻ እንደሚፈቱ አስምረውበታል። "ይህንን ማን አጣው?" ብሎ ሚጠይቃቸው አልተገኘም እንጂ። በድርድር ሰላምን ለማምጣት መልካም ፈቃዱ ካለ፤ መጀመሪያ በእስር ላይ ያሉትን የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በመፍታት ነበር የሚጀመረው። ከቶውንም የህሊና እስረኞች ለመደራደርያ መቅረብ አልነበረባቸውም። አሁን ግን የምናየው የተገላቢጦሹን ነው። ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ እንዳስቀመጡት "መጀመሪያ የፖለቲካ እስረኞችን ፍቱ!" የምትለው ቅድመ ሁኔታ ለገዥው ፓርቲ የሰጥቶ-መቀበል መደራደርያ ሆና ቀርባለች። ይህ የተቃዋሚዎች የመደራደር አቅም ምን ያህል እንደሆነ የሚለካው አንዱ መስፈሪያ ነው።

ድርድር የምትለዋ ርዕስ እነሱ በችግር በተወጠሩ ቁጥር የሚመዟት አንደኛዋ ካርድ ለመሆንዋ ያለፉ ተመክሮዎች ምስክሮች ናቸው። ዓለም አቀፍ ጫና ሲበዛና የሕዝብ ልብ ሲሸፍት ይመዙዋትና አዘናግተው ሲጨርሱ መልሰው እኪሳቸው ይመልሷታል። እንግሊዞቹ "talks the talk but doesn’t walk the walk" እንደሚሉት ነው። ወሬውን ያወሩታል - ሥራውን አይሠሩትም። በዚህ መንገድ ከሰባት ግዜ በላይ በሕዝብ እና በተቃዋሚዎች ላይ ቀልደዋል።

ድርድር ወይንም ውይይት አንድ ነገር ነው። በድርድሩ ቢቻል የበላይነትን አልያም እኩል ስፍራ መያዝ ሌላ ነገር። በክብ ጠረጴዛ የመቀመጥ እድል ሳይኖራቸው መወያየት ከመሞከር ይልቅ አለማድረጉ ይመረጣል። ጉልበተኛው የጫወታውን ሕግ በሚወስንበት ጫወታ መሳተፍ ከማጅራት መች እጅ ጥምዘዛ የተለየ አይሆንም።

አንዳንዶች ተገቢ የሆነ ጥያቄ ያነሳሉ። "የተቃዋሚዎች ጡንቻ ከገዥው ፓርቲ የጠነከረ ባለመሆኑ የሚሰጣቸውን መቀበል ግድ ይላቸዋል።" ይላሉ። ይህ ዕይታ ትክክል ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ መሄዱ ግን ፍጹም ስህተትና ሕዝብን መካድ ነው የሚሆነው።

የገዥው ፓርቲ ጸብ ከሕዝብ ጋር ነው። ሕዝብ በጅምላ ይገደላል፣ ሕዝብ በፈረቃ ይታሰራል፣ የሕዝብ ሀብት ይዘረፋል። በዚህ ሁኔታ - ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ ለረጅም መዝለቅ ደግሞ አይቻልም። የውይይቱ አጀንዳ የሕዝብ ጥይቄ ላይ የሚነሳ ሲሆን፤ ለተቃዋሚዎች የሞራል ብቻ ሳይሆን የኃይልም የበላይነት ይሰጣቸዋል። እዚህ ላይ ተቃዋሚ ስል የተገዙትን ወይንም የተቃውሞ አራራ ያላቸውን እንዳልሆነ ግልጽ ይሁን። እርግጥ ነው። ደፋር እና ትክክለኛ የምንላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በእስር ቤት አልያም በስደት ላይ ናቸው።

የቴሌቭዥን ጋዜጠኛው ታዲያ አፉን ሞልቶ "የፓርቲዎች ውይይት" እየተካሄደ እንደሆነ በዜና አወጀ። ይህን ውይይት ልማቱ ካመጣቸው አዳዲስ ፍላጎቶች ጋር በማያያዝ ለመተንተን ግን አልደፈረም።

በአቶ ይልቃል ጌትነት የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ኢሕአዴግ በጠራው የፓርቲዎች "ውይይት" እንዲቀመጥ የተፈቀደለት እስከ ሻይ እረፍት ድረስ ብቻ ነበር። የሰማያዊ ፓርቲ ባህርይ እስከ ሻይ እረፍት ድረስ ተገምግሞ ሲያበቃ፣ ፓርቲው ጽንፈኛ እና ጸረ-ሰላም በመሆኑ ከምድቡ ተሰርዟል። ሌሎች "ነግ በኔ" ብለው መባነን የነበረባቸው በዚህ ግዜ ነበር። እነ አስመላሽ ወልደሥላሴ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በውይይት ብቻ ነው ብለው ሳይጨርሱ ተሳታፊውን ማባረር ሲጀምሩ ጉዳዩ እዚያው ያቆማል።

በፖለቲካ ኩምክና የሚታወቀው የእንግሊዙ ሳሻ ቦራት የተወነበት "The Dictator" የሚለው ፊልም ታወሰኝ። የዋዲያ ሪፐብሊክ መሪ የሆነው አድሚራል ጀነራል አላዲን የሩጫ ውድድር አዘጋጅቶ ሲያበቃ ተሳታፊዎችንም ራሱ መረጠ። ዳኛው ራሱ ጀነራል አላዲን ነው። ጀነራል አላዲን ተወዳዳሪም ነው። ሩጫውን የማስጀመርያ ሽጉጡን አንስቶ ወደሰማይ ተኮሰ። ሩጫ ተጀመረ። ከዚያም ተወዳዳሪዎቹን በሙሉ እግር-እግራቸውን እያለ ጥሎ በውድድሩ አንደኝነቱን አበሰረ።

በ"ሥልጣን ወይም ሞት!" መፈክር የሚሄደው ይህ ድርጅት ያዘጋጀው መድረክ ከጅምሩ የሚሸት ነገር አለው። በቅንነት እና በሙሉ ልብ የሚደረጉ ውይይቶች ከአነሳሳቸው ይታወቃል። "ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል" እንዲሉ፣ ይህ በግማሽ ልብ የተጀመረ መድረክ ለአገር ሰላም ታስቦ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ለውይይቱ የተጠሩት "ሰላማዊ መንገድ የመረጡ" ተቃዋሚዎች ብቻ ናቸው ተብሏል። ጉድለቱ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው።

አንዱን ትክክለኛ ልጅ፣ ሌላውን ደግሞ የእንጀራ ልጅ ብሎ የሚመድበው ማን ነው? አንዱን ጠርቶ እንነጋገር እያለ፣ ሌላውን ደግሞ አንተ "ጽንፈኛ" መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ ከሚል አካል ሰላም ይመጣል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ይሆናል። ህወሓት ለውይይት ሲጠራ የራሱ መለኪያ አውጥቶ ለመሆኑ ከአጠራሩ ሂደት እና ከተጋበዙት እድምተኞች ለመረዳት አያዳግትም። በውይይቱ የበላይነትን ይዘው ለመደራደር መስፈርቱን የሚያሟሉትን ከጠራ በራሱ ላይ የሞት ፍርድ እንደፈረደ ይቆጠራል።

እሳት ከሌለ ጭስ አይታይምና ይህ ሾው ያለ ነገር፣ ያለ ግዜውም አልመጣም። የሰሜኑ ችግር እጅግ እየባሰ መጥቷል። ከወደ ምዕራብም ችግር አለ። የአልባሽር ፍቅር ከደቡብ ሱዳን እያላተማቸው ነው። ደቡብ ሱዳን አሁን ያመረረች ይመስላል። ይህ ደግሞ ለአማጽያን ከኤርትራ የተሻለ አማራጭ ሊሆንላቸው ነው። ሰሞኑን ግጭቱ ተካርሮ ዲፕሎማት እስከማባረር ተደረሷል። የካይሮ እጅ ኖርበትም አልኖረበት፣ የጁባው ዲፕሎማሲ የሥርዓቱን ግባዓተ-ቀብር ማፋጠኑ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው።

ብዙዎችን ጥርጣሬ ውስጥ የከተተበት ምክንያት ገዥው ፓርቲ የሚታመን ሥርዓት ባለመሆኑ ብቻ ነው። ለበርካታ ግዜ ሕዝብን እና ተቃዋሚዎችን በሃሰት አዘናግቷል። ከመተማመን በፊት ውይይት ሊኖር አይችልም። ይህ ደግሞ የሚሆነው የሰማዕታት ቤተሰቦች ሲካሱ እስረኞች ሲፈቱ እና ሁሉም ፓርቲዎች ሲጋበዙ ነው። ያለበለዝያ ጠቀሜታው ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ይሆናል።

ታጋባዥ ተቃዋሚዎቹ ለጥቂት ሰዓታት ከገዥው ፓርቲ ጋር ከተመካከሩ እና በባለሥልጣናቱ ከተመከሩ በኋላ እረፍት እንዲወስዱ ተደርገዋል የሚል ዜና ተለቅቋል። ፓርቲዎቹ ከ15 ቀናት እረፍት በኋላ እንደሚመለሱ አይጋ ፎረም ላይ አነበብኩ። ሳባቲካን እረፍት መሆኑ ነው። ለሰዓታት ውሎ የ15 ቀን እረፍት ከተሰጣቸው፣ ለቀናት ቢወያዩ ደግሞ የዓመት እረፍት የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። የዚህ አይነት ውይይት ያልተለመደና እንግዳ ነገር ቢሆንም፤ በገዥው ፓርቲ በኩል ለሚሠሩ ሸፍጦች ግዜ መግዣነት የታሰበም ይመስላል።

የድርድሩ ቀልድ ግን የተበላበት ካርታ ስለሆነ የሚደረደረው ምክንያት ሁሉ ውሃ አያነሳም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ