ምሕረቱ ዘገዬ

Don Quixote

በወጣትነቴ ካነበብኳቸው ጥቂት መጻሕፍት አንዱ የሰርቫንቴስ ዶን ኪሾት ነው። ይህ ገጸ ባሕርይ - ዶን ኪሾት - በጣም አስቂኝ ነው። ምናቡ የሚፈጥርለትን የጠባብ ዓለም ሕይወት ለመኖር በደራሲው ምናብ የተፈጠረ የሌለውን እንዳለው፣ ያልሆነውን እንደሆነ በመቁጠር ከንፋስና ከበጎች ጋር ሳይቀር “የጦፈ ጦርነት” ውስጥ የሚገባ ገልቱ ሰው ነው። ከነባራዊው ዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ስናየው በምናብ ምሪት ለመኖር ማሰብ ትልቅ ዕብደት ነው። የልቦለዱ ግን ቀላል ነው።

በልቦለድ ዓለም ብዙ ዕብዶችና ወፈፌዎች ይታያሉ - በመጻሕፍትም፣ በትያትርም፣ በፊልምና በመሳሰሉትም ሞልተዋል፤ ያ ዓይነቱ አካሄድ ክልክል ስለሌለው እየሳቅንባቸውና እየሳቁብን እንኖራለን። በገሃዱ ዓለም የምናያቸው ዕብዶችና ወፈፌዎች ግን መቆሚያ መቀመጫ እያሳጡን ጤነኞች ነን የምንለውን ሁሉ ሣንቀር ያሳብዱናል። ዕብድና ዘበናይ ደግሞ በተለይ የፖለቲካውን ልጓም ሲቆጣጠር ተፅዕኖው ዓለምን እስከማሳለፍ ይደርሳል። አሁን የምናየው ዓለማቀፋዊ ክስተት ደግሞ ይህን የሚመስል ነው። የአፍሪካውማ አይወራ! ኢዳሚንን የመሰለ ዕብድ፣ ቦካሣን የመሰለ ዕብድ፣ ጋዳፊን የመሰለ ዕብድ፣ ሙጋቤን የመሰለ የመነቸከ ዕብድ፣ መንግሥቱን የመሰለ ራሱን ከአገር በላይ የሚያፈቅር ወፈፌ፣ መለስን የመሰለ ዕብድና ዘበናይ ... ስም ይቀድሞ ለነገር ባትሉኝ ያህያ ጃሜህን የመሰለ የጋምቢያ ደደብ ወፈፌ፣ ስንቱን ጠቅሰነው... በጥቅሉ አፍሪካ የዕብድ መሪዎች አህጉር ስለመሆኗ የሕዝቧ ዘግናኝ ኑሮ በግልጽ ያመለክታል። በነገራችን ላይ እነዚህን ዕብዶች የተኩ በአስተሳሰብ ከዝንጀሮ የማይሻሉ የአፍሪካ መሪ ተብዬዎች በአዲስ አበባ ተሰብስበው የማይጠግቡ የሰውነት አባሎቻቸውን በዓለማዊ ምግብና የሥጋ ዳንኪራ እያጥለቀለቁ ታላቁን የወቅቱን የምድር ገዢ ሊቀ ሣጥናኤልን በማስደሰት ላይ ይገኛሉ - በአሁኒቷ ቅጽበት። ግን ዘመኑ ቀርቧልና የጨለማው ንጉሥ በቅርቡ መሸነፉ አይቀርም። ያ ነው ተስፋችን። ተስፋችን የጦርነቱ ፍጻሜ መቃረብ ነው። ይህ እውነተኛ ተስፋ ባይኖር ኖሮ ምን ይውጠን እንደነበር አላውቅም።

ይህ ዘመን የሚጽፉበትም ሆነ የሚናገሩበት እንዳሆልነ ይገባኛል። ግን የኅሊናን ጫና ባለመቋቋም አንዳንዶቻችን ትንሽ ተንፍሰን ቢወጣልን እያልን በተገኘችዋ አጋጣሚ መተንፈሳችን አልቀረም። አድማጭ ኖረም አልኖረም እንዲህ መናገራችን ለዘመኑ ምሥክር ይሆናልና አይከፋም። እደእውነቱ ከሆነ ዘመኑ ያበቃለት የአጋንንት ዘመን መሆኑን ለመመስከር ኢትዮጵያን ብቻ ሣይሆን መላውን የአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም የዐረብና የእስያ ምድር ማጤን በቂ ነው። ጭምብል ያጠለቁ ዐርባና ሃምሣ አክራሪ ሙስሊሞች ከፊት ለፊታቸው ብርቱካናማ ልብስ የለበሱ ዐርባና ሃምሣ ክርስቲያኖችን አንበርክከው “አላሁዋ ክበር!” በሚል ሰይጣናዊ ዝማሬ በሰላ ቢላዎ አንገታቸውን ሲቀሉ ማየት በራሱ የዘመንን ፍጻሜ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የሚገርመው ግን የፈጣሪ ትግስት መብዛት ነው። ትንቢተ ቃሉ ባይቀድም ኖሮ ብዙዎቻችን በካድነውና የዲያብሎስን ጎራ በተቀላቀልን ነበር። መታገስ ያቃታቸውና ሆዳቸውን ያስቀደሙ ብዙኃን የዓለም ዜጎች የጨለማውን መንግሥት እየተቀበሉና እያስፋፉም መገኘታቸው የወቅቱን ፈታኝነት አረጋጋጭ ነው። ...

ካለፉት ስድሳና ሰባ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የምትባል የጉድ አገር ከምትወልዳቸው “ልጆቿ” መካከል የትኛው ተነስቶ የትኛው እንደሚጣል አልገባህ ብሎኛል - ከልጁና ከእንግዴ ልጁ። “እውነተኛው ልጅ ቢነሳና ቢያድግ ኖሮ አሁን የምንገኝበትን የመሰለ አገራዊ ሥዕል አይኖረንም ነበር” ብዬ የምቆጭባቸው ጊዜያት እየበዙ መጥተዋል። ጠቅልለን የመጥፋታችን ምሥጢር አልገባህ ብሎኝ ተቸግሬያለሁ። “ተያይዘን ጠፍተናል” ቢባል ማጋነን አይደለም። የአጠፋፋችንን ዝርዝር ስለምታውቁት ወደዚያ ገብቶ ብዙ ማውራቱ ጊዜ ማባከን ነው።

እንደማስበው ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ የአይኪዋችን (IQ) መጠን እጅግ እያቆለቆለ መጥቷል ብዬ አምናለሁ። እንዲያውም ሰው ነን ከምንል ከአንዳንዶቻችን ይልቅ እንደዶልፊንና ቺምፓንዚን የመሳሰሉ እንስሳት በኢንተሊጀንስ ሳይበልጡን አይቀሩም። ለምሣሌ አንበሣ ከጠገበ ሚዳቋዎችና ድኩላዎች በፊቱ ቢደንሱ ግድ አይሰጠውም - ምናልባት ይዝናና እንደሆነ እንጂ። ሰው ግን 70 ቢሊዮን ዶላር ይዞ በሀብት በዓለም አንደኛ መሆኑን ካረጋገጠም በኋላ ተጨማሪ ሀብት ለማፍራትና ቁንጮ እንደሆነ ለመዝለቅ ዕንቅፍ አጥቶ ያድራል። ለዚያም ስኬት ወንጀልንና ኃጢኣትን ምንም ሳይፈራ ከሰማይ በታች ያሉ እጅግ የከፉ ነገሮችን ያደርጋል። ግን ግን ዕድሜው ቢበዛ ሰማንያ ያንንም እንደምንም ቢያልፍ ሰው እየጠላውና የፈጠረ አምላኩ እንዲሰበስበው እየጸለየለት ዘልዛላው ዕድሜ 100 ቢደርስ ነው። ከዚያ ሲሞት ወደሚቀርበው የመቃብር ቦታ ተወስዶ እንደ አሮጌ ጣሳ ይጣላል ወይም እንደዬእምነቱ ይቃጠላል። ይህ ነው የሰው ልጅ የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ፤ ለዚችም ሲባል ነው እንግዲህ ይሄ ሁሉ ጦርነት የሚካሄደውና በምቀኝነት አባዜ ተለክፎ አንዱ ሌላውን ሲዘረጥጥ የሚስተዋለው። ማስተዋል እርቆን እንጂ ቆም ብለን ብናጤነው ሁሉም ከንቱ መሆኑን በተረዳን። መጽሐፈ መክብብም ይህን ነው የሚለን። ... ችግሩ ደግሞ ከንቱነት በተማረው ብሶ መገኘቱ ነው።

አይኪዋችን ብቻም ሣይሆን EQ, SQ, PQ (Emotional Quotient, Spiritual Quotient, Physical Quotient) በሚባሉት የልዩ ልዩ ኢንተሊጀንስ ዓይነት መለኪያዎች አንጻር ብንፈተሸ ብዙዎቻችን ወዳቂዎች ነን - “ውዳቂዎች” እንዳላልኩ ግን ይታወቅልኝ። እነዚህ የኢንተሊጀንስ ዓይነቶች በአንድ ዜጋ ውስጥ ተሟልተው በቅጡ እንዳይገኙ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች አንደኛው ድህነት ነው ብዬ አምናለሁ። አሸር ባሸር እየመገብክ ቀጥቅጠህ የምትገዛው ሕዝብ ከአድማስ ማዶ ማሰብ እያቃተው በጓዳ ችግሩ ብቻ ተወጥሮ ቢገኝ አይፈረድበትም፤ መብል መጠጥ ሰውን ሰው እንደሚያደርግ መረዳት ይገባል። አስተሳሰባችን ከአመጋገባችን ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው - ሌሎች ግብኣቶችም ቢኖሩ። ባሕር ወለድ ምግቦችን የሚመገቡ የሩቅ ምሥራቅ ሕዝቦች አእምሯቸው ምጡቅ እንደሆነ የሚነገርላቸው በተፈጥሮ እኛ ከነሱ አንሰን ወይም እነሱ ከኛ በልጠው ሣይሆን ገዢዎቻችን ከአልሚና ከተመጣጠኑ ምግቦች ገድበው እንደከብት ያገኘነውን መናኛ ነገር እያመነዠክን ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ለመኖር ያህል ብቻ እንድንኖር ስላስገደዱንና ያንንም የአእምሮ መቀጨጭ ስላጋጠመን ነው - ድህነት ደግሞ የሁሉም ክፋቶች መባቀያ መሆኑ እያስተዋልን ነው - ምቀኝነቱ፣ ቅናቱ፣ ተንኮሉ፣ ሸፍጡ፣ ዘረኝነቱ፣ ምኑም ምናምም ባብዛኛው ከድህነት አምባ ይፈልቃል። ይህን ዓይነት ሕዝብ ስለወዲያኛው ዓለም ቀርቶ ስለዚህኛው ዓለም እንኳን እንዲያስብ ማድረግ አይቻልም። ይህ ዓይነቱ ሕዝብ የዛሬ እስትንፋሱን ወደነገ ለማሳደር ባለፈ ስለሞራል፣ ስለኃይማኖት፣ ስለባህላዊ ዕሤቶች፣ ስለመልካም ሥነ ምግባር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ማኅበራዊ ወግና ልማድ ... ብትሰብከው በቀላሉ ይገባዋ ተብሎ አይጠበቅም - “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” ይባላል፤ ሆድ ቀላል ይመስለናል እንጂ በዚህች ምድር እጅግ ወሳኝ ነው። ጥቂቶች በሀብትና በሥልጣን እየነገሡ ብዙኃኑ እየጠፋ ያለበት ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሮ በተለይ መፃዒው የአገራችንና የትውልዳችን ዕጣ ፋንታ ዥው ያለ ገደል አፋፍ ላይ ተደቅኖ ትልቅ አደጋ ላይ ነን። የሀብት ክፍፍሉ መረን የለቀቀ በመሆኑና መድሎና መገለሉም ያንኑ ያህል ቅጥ ያጣ በመሆኑ አገራችን ለይቶላት የምትፈነዳበት ጊዜ ተቃርቧል ብንል እንደሟርተኛ ሊያስቆጥረን አይገባም። ያንዣበበብንን አደጋ ሰው ብቻ ሣይሆን ዛፍ ቅጠሉ የሚረዳው ግልጽ ግን ዘግናኝ አደጋ ነው። “የፈሩት መድረሱ፣ የጠሉት መውረሱ” ደግሞ አይቀርም። ...

በዚያኛው ሰሞን የፕሮፌሰሮችን ውዝግብ በጥሞና ተከታተልኩ። በጣም ገረመኝ። አግራሞት ቢገድል ኖሮ ቀዳሚ ሟች ነበርኩ። “ከዕውቀት አምባ የተገኙ ለሰማይ ለምድር የሚከብዱ ታላቅና ታናሽ ዝኆኖች ሲጣሉ እንዲህ ቅጥአምባራቸው ከጠፋ እኛ ማይምናኑማ እንዴት እንሆን?” ብዬ ለአገሬ የትውልድ ሾተላይ ከልብ አዘንኩ። ፍቅራችንም፣ ጠባችንም የማያምር እኛ ኢትዮጵያውን ብቻ እንደምንሆንም አሰብኩ፤ እንሆን እንዴ ግን? የብዙዎቻችን ፍቅር የወረትና ያንገት በላይ ሲሆን ጠባችንም ለዕርቅ የማያመችና አጥንትን ሰርስሮ የሚገባ ነቀርሣ መሰል ወሬዛ ነው። የመረገማችን ጡዘት ወደር የለውም።

ካነበብኩት አንዲት ጨዋታ አጠር አድርጌ ላቅርብ - የቀድሞ አባቶች ጠባቸው እንዴት ያምር እንደነበር እንድናስታውስ ነው። እነሱ ሲጣሉም ሲፋቀሩም ያምርባቸው ነበር፤ እንደኛ የገረረና ለሰሚም ግራ የሆነ ሻካራ ግንኙነት አልነበራቸውም።

አለቃ ክንፉና አለቃ ልሣኑ ይባላሉ፤ የቤተ ክህነት ሰዎች ናቸው። ተጠፋፍተው ከርመው መንገድ ላይ ይገናኛሉ። በሁለቱ መካል የነገር ቁርሾ አለ፤ ግን አልተዘጋጉም (አልተኳረፉም) ነበርና ሰላምታ መለዋወጥ ጀመሩ።

አለቃ ክንፉ - እንዴት ከረሙ አለቃ ልሣኑ? ለብዙ ጊዜ አልተገናኘንም። በጤናዎ ነው?

አለቃ ልሣኑ - እግዚአብሔር ይመስገን፤ ደኅና ነኝ። ግን ያ ያዳም ጠላት ዘወር ብሎብኝ ትንሽ አመም አድርጎኝ ሰነበተ።

አለቃ ክንፉ - አይይ፣ እንዲያው ልሣኑ ይዘጋና እርሱማ ሁላችንንም እያንገላታን አይደል?

አለቃ ልሣኑ - ኧረ ምን ልሣኑ ብቻ፣ ክንፉም ይርገፍ እንጂ አለቃ!

“ስለዚህ” አልኩ ለራሴ። “ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን እንዴት መፋቀርና መጣላት እንደሚኖርብን ለመረዳትና ሁሉንም በአግባቡ ለማስናተገድ ‹ሀ› ብለን መማር አለብን። ግብረ ገብ መማር አለብን፤ ኃይማኖትን መማር አለብን፤ የቀድሞ የይሉኝታና የጨዋነት ዕሤቶቻችንን መመለስ አለብን፤ራስን ከመቆለል፣ ‹ባላንጣ›ችንን አለስሙና አለግብሩ ስምና ግብር እየሰጠን ከማንኳሰስና ከማዋረድ በዚያም ራሳችንን ለማዋደድ ከመልፋት እንድንድን ትህትናንና ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን መማር ይኖርብናል፤ ያኔ ነው ፈሪሃ እግዚአብሔር አድሮብን ከሰይጣናዊ ትዕቢትና ዕብሪት ነፃ የምንወጣው ...” ብዬ ለራሴ ነገርኩት።

በመሠረቱ ተስፋ መቁረጥ አልወድም። ተስፋዬም እግዚአብሔር እንጂ ሰው ወይም ሀብትና ገንዘብ አይደለም - የኋለኛው ባይኖረኝም። ጠፊ በሆነና ሟች በሆነ ነገር መተማመን አልፈልግም። ይሁን እንጂ የሰሞኑ ሁኔታ እጅጉን ተፈታትኖኝ ነበር። ከፍ ሲል ከጠቀስኩት አሣዛኝ ታሪክ ጀምሮ እስከሌሎች ትናንሽ ዶንኪሾቶች ድረስ በአስተሳሰቤ ላይ ትልቅ ጥላ አጥልተውበት ስሜቴን አደብዝዘውብኝ ነበር። አሁን ሳስበው ደግሞ ከሰው ዱሮውንም ብዙ መጠበቅ እንደማይገባኝ ተረዳሁ።

ዛሬ ጧት አንድ ድረገጽ ላይ አንድ ቆየት ያለ ጽሑፍ ደግሜ አነበብኩ። 108 ገደማ የአንባቢ አስተያየት አለው። የጸሐፊውንም የአስተያየተኞቹንም ዶንኪሾታዊ ተፈጥሮ ተገንዝቤ ሳበቃ ዝም ማለት አቃተኝና ይህችን ጦማር ጻፍኩ። በነገራችን ላይ ኤርምያስ ለገሠንና ታደሰ ብሩን የሚነካብኝ ሰው አልወድም - እንዲህ ስልም አላግባቡ ማለቴ እንጂ እንኳን እነሱን - ሰዎቹን - የሁላችንንም ፈጣሪ የሆነውን እግዜሩንም በሃሜትና በስድብ ስንሞልጭ እንውላለንና ለምን ተነኩ ብዬ አላጉመተምትም። ግን ግን ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና ኤርምያስን በእበላ ባይነት ታዴን በዕውቀት ማነስ የሚሳደብ ሰው ሲገጥመኝ ብችል የሕክምና ወጪውን ችዬ ጤንነቱን ለማስመርመር ዝግጁ ነኝ - ያን ባልችል ደግሞ ወደሸንኮራ ጠበል መውሰድ አያቅተኝም። ሰውን መወቀስ ባለበት መውቀስ ተገቢ ነው፤ ለመውቀስ ብቻ መውቀስ ግን ዕብደት ነው። ውይ! ኢትዮጵያ ነፃ ስትወጣ የአብሮነት ሕይወታችን እንዳይቃወስ ሲባል መቅረፍ የሚኖርብን የድንቁርናና የዕብሪት ጭቅቅት ምን ያህል ሸክም እንደሚሆንብን ሳስበው ከአሁኑ በጣም እደነግጣለሁ። ያስፈራል። የስድቡንና የብልግናውን ተዉት - ጊዜያዊ ነው። አለላችሁ እንጂ - የአስተሳሰብና የአመለካከት ብክለት። “እኔ ካንተ እበልጣለሁ፤ እኔ ላንተ አውቅልሃለሁ፤ እኔን የሚስተካከል አገር ወዳድ ቢፈለግ ጭራሽ አይገኝም! ...” የሚልን ሰው እንዴት ወደሰውነቱ ትመልሰዋለህ? ሰው መሆን እኮ - በተለይ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ መሆን እኮ ታላቅ ፈተና ነው - ሊያውም መሆን የሚፈልግ ካለ። ኢትዮጵያዊነት በስንትና ስንት ልመናና ደጅ ጥናት ይገኝ እንዳልነበር ዛሬ ታሪክ ተለውጦ “እንደራደርበት” እየተባልን ነው። ሲነጋ ግን ሁሉም ያፍራል። ቀኑ ቀርቧልና ለዚያ ያብቃን!

ዶንኪሾታዊነት ምንጩ ራስን አለማወቅ ነው። ዶንኪሾታዊነት መሠረቱ ለራስ የሚሰጥ ብዙውን ጊዜ ከፍ ያለ አንዳንዴም ዝቅ ያለ ግምት ነው። ስለራስ የሚሰጠው ግምት መጠኑን ካለፈ ወደዕብደት ይመራል። ለአብነት ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው አንድ ሰው “ከኔ በላይ ዐዋቂ ላሣር ነው!” ቢል ይህ ሰው በትክክል ዐብዷል። በመጀመሪያ አንድ ሰው ለዚህች ምድር ከአንዲት የአቧራ ብናኝ የማይበልጥ ኢምንት ፍጡር ነው - እኔ ለምሣሌ ከዝምብ የምሻልበትን ነገር እንዳስረዳ በአንድ ፈላስፋ ብጠየቅ መልስ የሚያጥረኝ ይመስለኛል። በምትሰጠን አጭር ሰብዓዊ ዕድሜ እንኳንስ ሌላ ነገር ራሳችንንም በቅጡ ሳናውቅ ነው ከዚህች ምድር የምንሰናበተው። ያን ዓይነቱን ሰው - ከኔ በላይ ዐዋቂ የለም - የሚልን ሰው እስኪ አንድ ነገር ቀድመን እንጠይቀው። ለመሆኑ ስለምንድን ነው የሚያውቀው? ስለሚያውቀው ነገርስ ከየት ጀምሮ እስከየት ድረስ ነው የሚያውቀው? ቀላል የሚመስል ግን ከባድ ጥያቄ ነው። እንዲያው ግን አምስቱ የስሜት ሕዋሣት ምንድን ናቸው? በዳቦ መልክ የመጣን ፈንጂ የሚጎርስ ሰው፣ በወይን ጠጅ መልክ የሚቀርብን መርዝ ጠጥቶ እንደጫጩት የሚፈነገል ሰው፣ በዱቄት መልክ የመጣን ጀሶ በእንጀራነት የሚመገብ ሰው ... ምን ያውቅና ነው በዕውቀቱ ምጥቀት አንዱ ከሌላው እንደሚበልጥ ቆጥሮ የሚንጠባረረው? ቢያውቅስ ሰው ዐወቅህ ይበለው እንጂ ስለራሱ እንዴት ሊመጻደቅ ይቻለዋል? ... ከትምክህት በቶሎ እንውጣ! “ትምክህትሰ ፀሩ ለክርስቶስ” እንዲል መጽሐፉ። እኔ ስለራሴ ከማውቀው ልኬቴ ይልቅ ሰው ስለኔ የሚያውቅልኝ የተሻለ ሚዛናዊነት እንዳው ካልተረዳሁ በስሜት ጡዘት ብዙ እጎዳለሁ - እንደዶን ኪሾት።

የሰው ጥቅስ ወሰድክ አልባልና አንድ ሰው አለማወቁን ባወቀ ማግሥት ለማወቅ መፈለጉንና ለመማር የዕውቀት መግቢያ በሩን መክፈት መጀመሩን እንረዳለን። ከዚያ ውጪ አንድ ወይ ሁለት የቢኤና የማስተርስ ዲግሪ ይቅርና በአንድ ሰው ዕድሜ የሚቻል ከሆነ አንድ ሰው መቶ ፒኤችዲም ቢሸከም - ሸክም ትርፉ እንለው እንደሆነ እንጂ - ምልዑ በኩልሄ - ፍጹም ዐዋቂ - ሊያስብለው አይችልም። በአንድ ጠባብ የትምህርት መስክ ሾልኮ አንድ ዲግሪ መያዝ ለማንም የማይቻል ካለመሆኑም በተጨማሪ ያም ብቻውን ዐዋቂና በሳል ሊያሰኘው አይችልም። (የኛ አገር ጉድ እኮ ተነግሮ አያልቅም - እንዴ፣ አንድ በቅርብ የዶከተረ ሰው መዶክተሩን እንኳን ሳትሰማ በስሙ ብቻ ብትጠራው እኮ ኩርፊያው አይጣል ነው! በዚህች እንኳን ስንቱን ታዘብን። ስለዚህ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ነውና ለይዘት እንጂ ለቅርጽ ብዙም ትኩረት አንስጥ።)

በተሞክሮና በንባብ ዐመልን መግረዝ ተገቢ ነው። እጅግ ብዙ ግርዛት የሚቀረን ዜጎች አለን። ሰው ሲያጨበጭብልን መንግሥተ ሰማይን ሣይቀር የገዛን የሚመስለን፤ ሰዎች ሲስቁልን አካባቢያችንን በሞላ የተቆጣጠርን የሚመስለን፤ በባሌም በቦሌም ብለን ብዙ ገንዘብ ስላካበትን ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ የገዛን የሚመስለን፣ በመማርም ይሁን በግዢ ዲግሪዎችን ስለያዝን የዕውቀት ጫፍ የደረስን የሚመስለን፣ ወዘተ. እጅግ ብዙ ማፈሪያ ዜጎች በየክፍለ ዓለማቱ ተበትነን ሞልተናል። ከዚህ ራሳችንንና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ከፈጠረብን ዶንኪሾታዊ የምናብ ዓለም ካልወጣን ኢትዮጵያ ነፃ አትወጣም፤ ዜጎቿ የተለያዩ የባርነት ቀምበሮች ሥር የሚማቅቁባት አገር እንዴት ነፃ ልትወጣ ትችላለች? አገራችን ነፃ ካልወጣች ደግሞ እኛም በጨለማ መኖራችንን እንቀጥላለን። ብርሃናማ ሕይወት ለመምራት ከጨለማ መውጣት ቀዳሚው እርምጃ ነውና ሳይረፍድብን ራሳችንን እንመርምር። ከጨለማ ስንወጣ የነበርንበት የዘረኝነትና የጎጠኝነት፣ የማይምነትና የአድልዖ አሠራር ጎልቶ ይታየናል። ያኔ የነበርንበትን የጨለማ አዘቅት እየተጠየፍን በአዲስ የብርሃን ሕይወት ውስጥ እንመላለሳለን። ያኔ ታዲያ እዚያ ላይ ሳንሄድ እዚሁ እታች ገነትን መፍጠር እንችላለን። ይቻላልም!

ይሄ በየጎራው ተቧድነን በላም አለኝ በሰማይ የምኞት ዓለም በብዕርም ሆነ በቡጢ የምንዳለቀው ከነዚህን መሰል እንከኖች ነፃ ስላልወጣን ነው። ፊደል መቁጠር ብቻውን ምንም አይደለም፤ የትምም አያደርስም። ደግሞም ፊደል የቆጠረ ማለትም በቅጡ የተማረና የተመራመረ ሰው በዓለም ትልቁን ሥልጣን የያዘበት ጊዜ በበኩሌ አይታወሰኝም። ስለዚህ ተማርን የምትሉ ወገኖች በተለይ ራሳችሁን ከሰቀላችሁበት ማማ አውርዱና አርጅታችሁ ከመሞታችሁ በፊት ለዚህ በቁሙ ለሞተ ሕዝባችን አንድ ነገር ለመሥራት በየፊናችሁ ተሰማሩ - በመጀመሪያ ከራሳችሁ ኅሊና ጋር ታረቁ፤ ቀጥላችሁ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ታረቁ [ለምሣሌ በዘር መቧደን፣ በነገድና በኃይማኖት መሰባሰብ፣ ለገንዘብና ለሥልጣን ፍርፋ ሲባል አቋምን እንደሸሚዝ መለዋወጥ ... ለሕዝብም ለአገርም እንደማይጠቅም ሳይረፍድባችሁ ተረዱ]፣ ሦስተኛም ከሁሉም የአገራችሁ ልጆችና ምሁራን ጋር ታረቁ። የሃሳብ ልዩነት ጤናማ ነው፤ በሃሳብ ልዩነት ይከራከሯል፣ ይሟገቷል፣ በሃሳብ ፍጭትም ወደስምምነት ይደርሷል እንጂ በዱላ ቀረሽ ስድብና በጠበንጃ አይጨራረሱም። ያ ዓይነቱ አካሄድ ከእንስሳም የሚያወርድ እጅግ ኋላ ቀር ነው። እባካችሁ ሰው እንሁን፤ ሰው መሆን ይናፍቀንና ወደሰውነታችን የተፈጥሮ ፀጋ እንመለስ። እንደወያኔ ከኅሊናችን ጋር እንደተጣላን ስለሆድ በሆድ እያሰብን ወደማይቀርልን መቃብር አንውረድ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ፈጽሞ ባይረሳትም ተኝተን መጠበቅ የለብንም። ከዚህም በከፋ የተማረ ሰው ከዘረኝነትና ከወንዝ ልጅነት ርቆ በሰብዓዊነት መሠለፍና ኃይሉን በአንድ አሰባስቦ ለጋራ ማንነት መታገል ሲገባው አሁን በተያዘው ወያኔያዊ መስመር መንጎዱ የማታ ማታ ከናካቴው አገር የሚያሳጣ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የብዙዎች ችግሮቻችን መልስ ወደጤናማ ኅሊና መመለስ ነውና በዚህ ረገድ እንበርታ። ዶንኪሾቶችንም እንወቃቸው፤ ስንችል እንመልሳቸው - ሳንችል እንራቃቸው። መልካም ጅምሮቻችንን ሳያበላሹብንና እንዳያበላሹብን ገለል እናድርጋቸው። ከኔ በጎደለ እግዚአብሔር ይሙላበት። ቻው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!