ዶ/ር አበባ ፈቃደ

Prof. Asrat Woldeyes
ፕሮፈሰር አስራት ወልደየስ

ኢትዮጵያ በዓለም ጥንታዊ የሥልጣኔ ባለቤትነት፤ ቀዳሚና ዋና ከሆኑት አገራት ውስጥ አንዷና የመጀመሪያዋ ነች። በወዳጆቾ፣ በተቀናቃኞ፣ በጠላቶቿ ሆነ በራሷ ሊቃውንት በኩል በታሪክና በሳይንስ መዛግብት፤ የሥልጣኔ ቁንጮ የፍጥረታት ሁሉ ምንጭ፤ እጹብ ድንቅ ፣ የጠቢባን አገረ ፣ ቅድስት ምድር መሆኗ ተመስክሮላታል። ለምስራቅም ሆን ለምእራባዊ ሥልጣኔ መሰረት ተበሎ የሚታወቀው የግብጽ ሰልጣኔ ጭምር ምንጭ በመሆን የግብጽ እናት (Egypt the daughter of Ethiopia) ተብላ የተጠራች ኢትዮጵያ መሆኖ አከራካሪ አይደለም። ከጥንቶቹ ሄሮድትስ፣ ሆመር እስክ የቅርብ ጊዜ ሊቃውንት፣ ቼክ አንታ ዲዮፕ፣ ቤን ዮሃነን፣ ጸጋየ ገብረ መድህንን ዋቢ ምስክሮችን ለናሙና ያህል መጥቀስ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር ነች የምትባለው እንደ አገር አመሰራረቷ የዕድሜ ባለጸጋ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዛሬ ለደረሰበት ልዩ ልዩ የሥልጣኔ ዘርፎች ምንጭና መገኛ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረከተች ጭምር ነው። የፍጥረታት የሕይወት መገኛ መሆኗ በልዩ መታደል ያገኘችው የተፍጥሮ ጸጋ ቢሆንም ለሥልጣኔዋ ገለጫ የሆነችው ግን በልጆቿ እውቀት ጥበብና ስራዎች ምክንያትም ነው። ለልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎች መሰረት በመጣል፣ አካላዊ ሆነ መንፈሳዊ ስነ ጥበባትን፣ እምነትና ኃይማኖት፣ ሂሳብና ቁጥር፣ ስነ ጽሁፍና ፊደላትን፣ የእጅ ጥበብና ኪነትን፣ መንግስትና አስተዳደርን፣ የሚታይና የማይታየውን ሰማያዊና ምድራዊ ፍልስፍና ያበረከተች የሥልጣኔ ባለቤት ነች፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ። አገረ እግዝአብሔር የተባለችውም ሰውን ሙሉ ሰው የሚያሰኘውን ዋናና ልዩ ባህርያትን ከፈጣሪዋ ባህሪ ጋራ በማዛመድና በመዋሃድ ለሰብአዊ ማንነትን ትርጉም ከፍተኛ ቦታ የሰጠች አገር ስለነበረች ነው።

ነገር ግን ላለፉት ጥቂት ምዕተ ዓመታት ይህ ያልተበከለው ልዩ ማንነቷ ጎልቶ እውነታው ለሁሉም እንዲታይ አልተደረገም። ይህን የሥልጣኔ ጎዳና እንዳንስትና እውነተኛ ማንነታችነን እንድናውቅም አልሆነም። ያልሆነበትንም ጥቂቶቹን ምክንያቶቹ ጠንቅቆ ማወቅና እውነታውን ህያው በማድረግ ገናና ታሪኳን እንዲያንሰራራ ማድረግ የዛሬና የነገው ትውልድ ተግባርና ኃላፊነት ነው። ምንም እንኳ የዚህ አጭር ጽሁፍ አላማና አቅም ታሪካዊ ትረካን ለማቅረብ ባይሆንም፤ ለዓለም ሥልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገች አገር ኢትዮጵያ ለራሶ ሕዝብ እውነተኛ ማንነቷ እንዳይታወቅ የተፈለገው ለምን ይሆን ብሎ መጠየቅና መጠርጠር ግን እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያ ማነች፣ እኛስ ማን ነን፣ ብለን መመርመር ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለአገር ነጻነትና ለሕዝብ ደህንነት በምናደርገው ትግል፣ ለተጋረጠብን ወቅታዊ ውጥረት መፍቻና ለቀጣይ አስተማማኝ ህልውና መሰረት የሚጥል አስፈላጊ መሳሪያ ይሆነናል። ለወቅታዊ ትግሉ ፍቱንና ወሳኝ ምላሽ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ለዘላቂ የነጻነት መንገድ፣ ፍትህና ርትእ ለማንገስ ትክክለኛውንና ቀጥተኛ አቅጣጫን ይጠቁማናል። የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነው የወያኔ የጎሣ ፖለቲካና የአማራው ጉዳይን በተመለከተ ለምን ልዩ አስቸኮይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ ለማስጨበጥና፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተንቀሳቃሾችንና የምሁራንን የማሰቢያ ሞተርን ለማስነሳትና ከሰመመን ለመቀስቀስ እንዲረዳን ነው። የተድበሰበሱትና የተሸፋፈኑ አገራዊ ሃሳቦችን በድፍረት መኮርኮርና እንደያስፈላጊነቱ በመገላለጥ ስንወያይ የፖለቲካ አመለካከቶቻችን ላይ የእይታ ጥራት ሊሰጠን ይችላል።

ዛሬ የምናስባቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጀግና ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለሰማዕትነት ያበቃቸው ዋናው ምግባራቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህልውናና በአማራው ሕዝብ ላይ በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የታቀደውና የተቃጣውን የማጥፋትና የማፍረስ ዘመቻን በቆራጥነት እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ተላብሰው በመቋቋማቸውና በማከላከላቸው ነበር። ፕሮፌሰር አስራት ይህን የጀግንነት ታሪካዊ ተግባር እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸውና ውስጣዊ ኃይልና ረዳትም የሆናቸው ኢትዮጵያዊ ባህሪያቸውና መንፈሳዊ እምነታቸው ሲሆን ለእውነትና ለእውቀት ታማኝ የሕዝብ ምሁርና ባለሙያ በመሆናቸውም ጭምር ነው። ያልምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት ነው የማንነት መለያየና ምልክቴ ያለውን የአማራ ሕዝብ ካንዣበበት የመጥፋት አደጋ ለማዳን አጣዳፊ የሰብአዊና የምሁራዊ ግዴታ መሆኑን በማመናቸው፤ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና ለአገራዊ አንድነትና ህልውና ለምናደርገው ትግል፣ ድልን የሚያጎናጽፍ ስልት መሆኑን በማስተዋላቸውም ነው። ማለትም አማራው በታሪክ፣ በአካል በመንፈሳዊና በባህላዊ ማንነትና የኢትጵያዊ የጋራ መገለጫዎችን ከራሱ የማንነት ባህርያት ጋራ በአንድነት መተሳሰሩን ያወቀና የተቀበለ ሕዝብ በመሆኑ፣ ጎሣና ቋንቋ ዘለል አገራዊና የአንድነት ዝንባሌ፣ ማህበራዊና የአብሮነት ስሜትና ፍላጎት፣ ነጻነት ወዳድነትና አርበኝነት የመሳሰሉት ባህርያት ያይሉበታል። በዚሀም ምክንያት የአማራውን ማኅበረሰብ በጎሣና በመንደራዊ ጠባብ ስሜት ውስጥ የተዘፈቁ፣ በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች አስተሳሰብ የተገዙና የተበከሉ የፖለቲካ ሊህቃንና የጎሣ ምሁራን ሁሉ በአሉታዊ እይታ እንዲመለከቱትና በጠላትነት እንዲፈርጁት ተደርጓል።

የአማራው ደህንነት ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር የተወራረሰና የተሳሰረ መሆኑን በጥልቅ በመገንዘባቸው እንዲሁም በማመናቸው ነበር ፕሮፌሰር አስራት፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚቅበዘበዙ ሁሉ እነሱ ይጠፋሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትጠፋም ያሉት። ይህም አባባላ ህያውና ዘላላማዊ ነው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት ወድ ሕይወታቸውን የከፈሉበት ኢትዮጵያዊ ሀቅና መርህ ነው።

አማራው ላይ በይፋ የሚደረገው የማጥፋት ዘመቻና ጥቃት ግልጽ ሆኖ በማያሻማ ሁናቴ መታየቱ ለአማራው ንቃት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የነጻነት ትግልም ስውር በረከት ነው፤ የአማራው መነሳሳት ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ፈር ቀዳጅ ኃይል ሰለሚሆን። ይህን አባባል በአፍ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ጎሣዊ ወይም ጸረ አንድነት ስውር ስሜት ያላቸው የፖለቲካ ሊህቃን ለመቀበል ያዳገታቸዋል። አማራው የጎሣ ድርጅት አይደለሁም ራሴን ከጥፋት የምከላከል፣ ብሔራዊ ታማኝነቴ ለኢትዮጵያዊነቴ ነው ብሎ ሲያረጋግጥም ለመቀበል ያስቸግራቸዋል፤ ለኢትዮጵያዊነቱ ያለው ቁርጠኝነት ይከነክናቸዋል። አማራው ብቻ ማን ኢትዮጵያዊ አደረገው ወዘት የሚል ተልካሻና ብላሹ ክርክር ለመፍጠር ይሞክራሉ። እነዚህ የፖለቲካ ሊህቃን፣ ሌሎች ማኅበረሰቦች ማንነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው በማለት ራሳቸውን እንዲገለጹ ከማበረታት ይልቅ አማራውን ሌሎች ስላልሆኑ ወይም ስላላሉ ለምን ኢትዮጵያዊነትህን ታረጋግጣለህ ተብሎ ሊወቀስ አይገባም ነበር፣ ወቃሾቹ የእውነተኛ ኢትዮጵያዊ አገራዊ አጀንዳ ቢኖራቸው ኖሮ።

በጥልቅ አስተውሎ ያለንበትን ሁኔታ ስናጤን፣ ሰፊ ግዛት የነበራት ቅድስት በመባል ትወደስ የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ ምን ሁኔታ ቢገጥማት ነው ለህልውናዋና ለሕዝቧ ደህንነት አስጊ ቀውስ ውስጥ የወደቀችው፣ ለባርነት የተጋለጠችው፣ ለምን ይሆን የአማራው ማኅበረሰብ ለልዩ እልቂትና የዘር ጥፋት ኢላማ የሆነው ብለን መጠየቅ የግድ ነው። በውስጣችን ከተገኙ አሉታዊ የተፈጥሮ ድክመቶች ወይስ በውጭ ጠላቶች የተጠነጠነ ስውር የዘመናት የጥቃት ሴራ ወይስ በራሷ ልጆች ባንዳነትና፣ ጠላትነት ብትጠቃ ነው ዛሬ በዓለም ፊት ደሃና ቆሻሻ ለመባል ያበቃችው? ከጀመረችውስ የሥልጣኔ ጎዳና ባትደናቀፍ፣ የራሷን መንገድ ባትስት ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ አገራችን ምን ልትመስል ትችል ነበር? እንዚህ ጥያቄዎች ለወቅታዊ ችግራችን መፍትሄ ሆነ ለወደፊት ሀልውናና እድገት መልስ ሰጪ ሰለሚሆኑ የተዝረከረኩና የጓጎሉሉትን አስተሳሰቦች በሃቀኛ የፖለቲካ ሊህቃንና የሕዝብ ምሁራን ተፍታቶ ሊብላላ ይገባዋል።

የአማራ ማንነት ኢትዮጵያዊነት፤ ነጻነቱ አሸናፊነቱ

የወያኔ ትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር ዋና መርህና አላማ የኢትዮጵያን ነጻ አገራዊ ግዛታዊ ሉዓላዊነት፣ የሕዝቦን አንድነትና ብሔራዊ ህልውናን ማስደፈረና ማናጋት መሆኑን በህግ ደንግጎ በተግባር እያዋለ ነው። ወያኔ ኢትዮጵያዊ መለያ ቅርሶችን ባህሎች፣ ተቋሟችን ወዘተ በአይነ ጥላቻ የሚመለከት የሚቀናቀን፣ ብሎም ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት በሆኑ ነገሮች ላይ በተለይ የአማራውን ሕዝብ በተመለከተ በልዩ ጠላትነት በመፈረጅ ለመጉዳት ኢላማ ያደረገ ኃይል ነው። ወያኔና ግብረ አበሮቹ ለኢዮጵያዊነቱ ቅድመ ሁኔታን የማይጠይቅ ብሔራዊ ክብሯን የሚያስጠብቅ፣ አብሮነትን የሚሻና የሚወድ፣ የአንድነት ምሰሶ የሆነውን ጀግና የአማራ ማኅበረሰብን ማዳከምና ማጥፋት መላ ኢትዮጵያን ለማጥቃትና ለመበተን ያስችላል በሚል ስሌት ነው የተንቀሳቀሱት አሁንም የሚንቀሳቀሱት።

በአሁኑ ጊዜ የአማራው ማኅበረሰብ ለደረሰበትና ለሚደርስበት ጥቃት ለመመከት ይችል ዘንድ፣ ከማንነቱ የመነጨ ነጻነት ወዳድነቱን፣ የጀግንነት ስሜቱን፣ የሰለጠነ ተክለ ሰውነቱ አርበኝነቱን በጥብቅ ማወቅና ሆኖ መገኘት እጅግ አስፈላጊ ነው። የአማራው ዋናው የማንነት መሰረት ጥንታዊና ውስጣዊ የባህርያት አሻራዎች ውስጥ ጥቂቶቹ አብሮነት፣ ጀግንነትና መንፈሳዊነት ናቸው። እነዚህን ባህርያት የህልውናው መሰረት መሆናቸውን አውቆ በተገባር መተርጎም የተዳፈነውን ማንነቱ እንደገና እንዲያንሰራራ ያደርጋል። በዚህ ውስጣዊ ጉልበት የአማራው ባህርያትንና የማንነት ኃይል በተገባር ሲመነዘር ውጤቱ ኢትዮጵያዊ ሕዝባዊ አሸናፊነት ነው፤ እንደ ድርና ማግ የተሳሰረ ሕዝብ በመሆኑና ስለሚመጋገብ በአማራው ላይ የተሰነዘረው ጥቃት የተዳፈነውን የኢትዮጵያን የጀግንነት መንፈስ ይቀሰቅሳል፣ ተጨባጭም ያደርጋል።

አማራው እንደ አንድ ማኅበረሰብ ቦታና ጊዜ የማይወስነው የራሱ የማንነት መገለጫ የሆኑ ወግና ዘይቤ ባህልና ልምድ ያለው በመላ የኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የሚኖር፣ ከአገራዊ ማንነት ጋር የተሳሰረና፣ ራሱን ከአገር ጋር ያዋሃደ ሕዝብ ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አገሬ ነች፣ ማንም ይህን ማንነቴን አይደፈርም በማለት የሚነሳ የአማራ ራስ አድን ንቅናቄ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቅናቄ መሆኑን በጥብቅ መረዳት የሚያስፈልገው። አስተዳዳራዊ አብሮነትና የማህበራዊ አንድነት መንፈስ የሰረጸው የአማራ ሕዝብ ንቅናቄ፣ ጽንፈኝነት የሰረጸውን፣ በመለያየት ላይ የተመሰረተውን የወያኔ ትግሬ ነጻ አውጪን ሆነ የሌሎችን ተመመሳሳይ አግላይ የጎሣ ፖለቲካ ፍልስፍና ያነገቡትን ጸረ አንድነት አስተሳሰቦች ሁሉ በኢትዮጵያዊ ማንነት መሻር ይችላል።

ኢትዮጵያዊ ምሁራን የአማራውን ሕዝብ አደረጃጀት ሆነ የትግል አነሳስ የጋራ መንፈስ ያለውና፣ ከሌሎች በጎሣዊ አስተሳሰብ ከተደራጁ ጋር ጥልቅ መሰረታዊ የይዘት ልዩነት እንዳለው ማስተዋል፣ ለትግል ስልትም የሚኖረውን ከፍተኛ አስተዋጽኦን ማወቅና ማሳወቅ፣ ኃላፊነትና ግዴታቸው ነው። ነገር ግን በርካታ የፖለቲካ ሊህቃንና ምሁራን፣ በማወቅም ባለማወቅም፣ በምሁራዊ ንዝህላለነት፣ ለወያኔ የጎሣ ፖለቲካ አስተሳሰብ እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ መጠቀሚያ ሰለባ ሆነዋል። በመሆናቸው የአማራውን የፖለቲካ፣ የህልውናና የደህንነት ጉዳዮችን በማድበስበስ የማይወዳደረውን በማወዳደርና የማይንጻጸረውን በማነጻጸር፣ ዱባና ቅልን በመዳባለቅ አሳሳች ክርክርና ንትርኮችን በእቅድ እንዲስፋፋ አድርገዋል። ከሚሰነዘሩት የማደናገሪያ አባባሎች ለምሳሌ ያህል፣ አማራው ከተደራጀ እንደ ሌሎች ጎሰኛ፣ ተገንጣይ፣ የጎሣ የነጻ አውጭ መሆኑ ነው፣ የወያኔን አላማን ይጠቅማል፣ አማራ የሚባል ሕዝብ እኮ የለም፣ ወዘተ የሚሉ ላይ ላዩን እውነት የሚመስሉ ውስጣቸው ግን ጽንፈኛ ማደናገሪያና አሳሳች የሆኑ ሀሳቦችን ያራምዳሉ። በጥሞና ምሁራዊ ውይይትና ክርክር እንዳይደረግባቸውም በልዩ ልዩ የወሬ ወከባ፣ በቅጥረኛ የካድሬወች ፕሮፖጋንዳና ተመሳሳይ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ብዥታን ይፈጥራሉ። በዚህ ምክንያት የማሰብ ስንፍናና የተረጅነትን ስሜት በምሁራዊ ባህል ውስጥ በመፍጠር ጭቆናን የሚያላምዱ አእምሮን የሚሰልቡና፣ አቋምን የሚያማልሉ ሁኔታዎችን በማስፋፋት የትግል ጉልበትን ያንኮላሻሉ፣ ሕዝብን ለበለጠ ጉዳትና ተጠቂነት ያመቻቻሉ።

ጀግንነት ብዙ ግዜ በጦርነት ሜዳ ላይ ወይም በአካላዊ ግጭት ወቅት ብቻ የሚገለጽና የምንጠቀምበት ባህሪያዊ መሳሪያ ይመስለናል። ነገር ግን ጀግንነት በሁሉም የኑሮ መስክ ውስጥ የሚገለጥ ልዩ መለያው ሃቅኝነት፣ ቆራጥነት፣ አልበገሬነትና ፍርሃትን የሚያሸነፍ ድፍረትና በራስ መተማመን የሚያስችል ልዩ ምግባራዊ ባህሪ ነው። ጀግንነት እንደ ጡንቻ የሚጠነክረውና የሚጎለብተው ሲጠቀሙበት ነው ይባላል፣ አለዚያ ይላላል። ጀግንነት የሚፈልቀው ወይም የሚያድገው በምናስባቸው ሃሳቦች ሆነ በምናደርጋቸው ተግባራት ሁሉ በአቸናፊነት መንፈስ በሙሉ ልብ አምኖ ፈር ቀዳጅ ተግባራትን ስናከናውን ነው። ጀግንነት የምንፈልገውን እንድንሆን የሚያስችለን ልዩ ረቂቅ ምግባራዊ ስሜት ነው። ጀግና የማይወደውንና የማይፈልገውን፣ ስብእናውን በማንኛውም መንገድ ለሚዳፈር አመለካከትና ተግባር አይበገርም፣ ለጉልበተኛና ለባለሥልጣናት አያጎበድድም። ጀግንነት ነገሮችን ለመቀየር ወይም ለመለወጥ ከምንጠቀምባቸው የስሜት መሳሪያ አንዱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከተጎጅነትና ከተጠቂ ደካማ ስሜት በውስጣችን ስር እንዳይዝ መከላከያ ውስጣዊ አኩሪና አጎልባቺ ኃይል ነው።

አማራውን ልበ ሙሉ ጀግና የሚያሰኘው አንደኛው ባህሪ አብሮነትንና መንፈሳዊነትን ማለትም መለኮታዊ ረቂቅነቱን ከአካላዊ ሰብአዊነቱ ጋር ያገናዘበና የተረዳ ሕዝብ በመሆኑ ነው። ከአካላዊ ኃይልና ጉልበት ባሻገር ሁሉን የማድረግ ችሎታን የሚያጎናጽፍ ውስጥዊ ረቂቅ ማንነቱ መንፈሳዊ ኃይሉ መሆኑን በማወቁ ለጋራ ሕይወት የሚጠቅሙ ባህልና ፍልስፍና፣ ኃይማኖትና ሰነምግባር ለመፍጠር መሰረት ሆኗል። የራሱን በመስጠት የሌላውን በመቀበልና በማዋሃድ ለኢትዮጵያዊ ርእዮተ ዓለም አቀራረጽ ሆነ ለተለያዩ ባህሎችና የአኗኗር ዘይቤውች መወራረስና ለአገራዊ አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎል። ይህ እንደ ጥበብ የተጠላለፈው የአብሮነት ምልክትነት፣ ዩሉኝታዊ አስተሳሰብ፣ አስተዋይ ልቦና፣ ይቅር ባይ ህሊና፣ ርህራሄን ትህትና፣ እንግዳ ተቀባይነት ወዘተ የአገር መሰረት በሆኑ ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵያዊነትና የአማራ ሕዝብ የጋራ የማንነት እሴቶች ናቸው። ስለለዚህም የአማራው ሕዝብ አብሮነት፣ ጀግንነቱና መንፈሳዊ ረቂቅነቱን የሚገልጽው በግላዊ ጠባብ ውስን ማንነት ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና በአገራዊነት መርህ ላይ በመመርኮዝም ነው።

አማራው የመረጠው በኢትዮጵያዊ ማንነት ስሜት የተገነባ ባለቤትነትን ነው፣ እኔም የሁሉ ነኝ ሁሉም የኔ ነው በሚል ሁሉን አቀፍ በሆነው የአብሮነት ስርአተ ማህበርና አንድነት ነው። በሕዝብ ደረጃ አብዛሃኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ወይም ጎሣወች ይህን ስሜት በተለያየ ደረጃና አገላለጽ ይጋራሉ ብየ እገምታለሁ። ሆኖም ግን በጎሣዊና በጸረ አብሮነት ፍልስፍና የሚመሩት የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ወያኔ፣ ሻብያ፣ ኦነግና መሰል ግልጽና ስውር ጎሣዊ ንቅናቄዎች፣ ይህ አማራው ያለውን ኢትዮጵያዊ ስሜት አይጋሩም፣ እንዳውም ተቀናቃኝና ጸር ናቸው። የአማራው ማኅበረሰብ በታሪኩም ሆነ እስክ ዛሬ ለእልቂት እስከ ተዳረገበት ጊዜ ድረስ ጸረ የኢትዮጵያ አንድነት መንፈስ፣ ከኢትዮጵያ መገንጠልን ማቀንቀን ፣ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ወዘተ የሚል የፖለቲካ ሃሳብም ሆነ ምግባር አሳይቷ አያውቅም። እንዳውም እንደ ሌሎች ጎሰኞች ቅድመ ሁኔታን ሳያስቀምጥ ኢትዮጵያን በሁለንተናዋ፣ ከነጥንካሪዋን ሆነ ድክመቷ፣ ከነሃብቷ ሆነ ድህነቷ በመወደዱና ለአገራዊ አንድነት ታማኝ በመሆኑ ጨቋኝ ገዥ፣ ትምክህትኛ፣ ወዘተ በመባል ጎጂ ለሆኑ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆኖል፤ የኃሰት መሰረተ ቢስ ክስ ተመስርቷበታል። ይህ ሃሰት እንዳይጋለጥ የትምህርት ስርአቱን የመረጃ ተቋሟችን ስለ አማራው እውነትን ያዘለ እውቀት እንዳይሰጥባቸው በምትኩ በወያኔ የውሸት ትረካ እንዲጥለቀለቁ ተደርጐል። እንደሚታወቀው በወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያ ታሪክ በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳይሰጥ ተደርጎል፤ ይባስ ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በአማርኛ መናገር የተከለከለና የሚያስቀጣም ሆኖል፣ አስገራሚና አሳሳቢ ለአእምሮ ባርነት የሚዳርግ የወራሪና የቅኝ ገዥ ተግባራት በተዘናጋው ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ነው።

ወያኔና የውጭ ግብረ አባሮች ጭምር ይህንንም የሚያደርጉት ሁሉንም መንገድ በመጠቀም ሲሆን በተለይም የተማረው ክፍልን ስለራስ ማንነት ያለን እውቀት በሀሰት የተበረዘ፣ አእምሮን የሚያደበዝዝ እይታን በማሰራጨት፣ የማሰብ ስንፍና የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ ዋና ዘዴያቸው ነው። የደቡብ አፍሪካ ጀግና ታጋይ ስቲቭ ቢኮ እንዳለው፣ ጠላትህን ለማጥቂያ የሚጠቅም ዋና መሳሪያ የጠላትህን አእምሮን መያዝ ነው ይላል፤ ምን ማለት ነው? ጠላትህ አእምሮህን ከተቆጣጠረ፣ አስተሳሰብህን፣ አመለካከትን ተግባርህን፣ ስሜትህን ስውር ህሊናህን ባጠቃላይ ማንነትህን ተቆጣጠረው ማለት ነው፤ ምግባርህ ለጠላትህ ጠቃሚ ለራስህ ጎጂ ይሆናል። በአማራው ላይ የተቃጣውን አደጋ በተልካሻ ምክንያት መሸፋፈን፣ ጥፋቱንና ወንጀሉን መካድ፣ በግደየለሽነት አሳንሶ ማየት፣ በፍርሀት የተለወሰ መቻቻልና መታገስ የሚሉ ሽፋኖች በመስጠት አእምሮችንን ለእኛ እንዳየሰራ የሚያደርጉ አጋጣሚወችን እንፈጥራለን። እንዲሁም ለሚጎዳው የአማራ ሕዝብ መቆምን፣ መቆርቆርን እንደማይሰፈልግ፣ የማይገባ ምግባር እንዲቆጠር በማድረግ ትግልን የሚያንኮላሽ፣ ለጠላት አገልጋይ የሚያደረግ አሁን የምንገኝበትን ለዘብተኛ የፖለቲካ ሂደትና እውነታ እንዲፈጠር አድርጓል። ስለዚህ ምሁራንና አገር ወዳድ ሊህቃን ለአእምሮ ደህንነትና ነጻነት እንክብካቤ ማድረግን አስፈላጊነት በጥብቅ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የምንከባከበውም የተዘራበትን ውሸት በማጽዳት በእውነት መተካት፣ የሃሳብ ውዥንብርን በማስወገድ፣ አወንታዊ የጠራ ሃሳብና በምሁራዊ የጀግንነት ወኔ አእምሮችንን ሰናስታጥቀውና ንቁ ስናደረገው ነው።

ምሁራዊ ልበ ሙሉነትና ኃላፊነት

በጥልቀት የተመረመረ ሃሳብና ርእዮተ ዓለም ዛሬ ለነጻነታችንና ለህልውናችን በምናደረገው ንቅናቄ ዋናና ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን ማወቅ የግድ አስፈላጊ ነው ብየ አምናለሁ። ሆኖም ጥያቄው ምሁሩ ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶች ለመቋቋም የሚያስችል ፖለቲካዊና ምሁራዊ የጀግንነት ስራን መስራት የሚያስችል ባህሪና አቅም አለው ወይ ከሌለስ ወይም ከተቦረቦረስ እንዴት መገንባትና ማዳበር ይቻላል? ጥያቄው ለጊዜው ሙሉ በሙሉ በዚህ ውይይት ባይመለስም ማንሳቱ ግን አይከፋም።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ስውር ዓላማን ለማሳካት ረቂቅ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያውያንን አእምሮን ለበታችነት ሰሜትና ተገዠነት ሳያውቀው እንዲቀበልና ብሎም ለመቆጣጠር በዘመናዊ የትምህርት ስርአት በኩል እንዲካሄድ ተደርጎል። በዚህ መልክ የተማረው የአገሩን ጉዳይ በራሱ የእይታ መነጸር መመልከት እንዳይችል፣ በዲቃላ አስተሳሰብ፣ በተንኮላሸ ወኔ በተበረዘ እውቀት ማንነቱ የታነጸ፣ የሌሎች ተከታይ በራሱ የማይተማመን፣ ተምሮ ያልተማረ ዘመናዊ ምሁር ሆነ። የኢትዮጵያ ጠላቶችና ባእዳን ያጠነጠኑትን የፖለቲካ መስመር በመከተሉ ለአገሩ ውድቀት ራሱ ተባበረ።

የባእዳን ዲቃላ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም በእኛ አገር ውስጥ ያለው አስፈላጊነት፣ ጠቃሚና ጎጂነቱ እስከ ምን ድረስ መሆን እንዳለበት በጥንቃቄ በአግባቡ ባይጤነም ያስከተለውን የአስተሳሰብ ውዥንብር አሁን ለደረስንበት ውጥንቅት ከፍተኛ አስተዎጽኦ ማድረጉ ግን ግልጽ ነው። ለምሳሌ የብሔር ጥያቄ የሚለውን የፖለቲካ ጽንሰ ሃስብ በኢትዮጵያ ታሪካዊና ተጨባች ፖለቲካዊ ሁኔታቸው ጋር የሚቃረንና የማይስማማ አጥፊ አስተሳሰብ ለመሆኑ ዛሬ አገራችን ያለችበት እውነታ ምስክር ነው። ከሌሎች አገሮች የፖለቲካ ተመክሮዎች በመነሳት፣ የሌሎችን ታሪክና ማንነት የሚያንጸባርቁ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳቦችን በኢትዮጵያ እውነታ ላይ ለማዋል መሞከር ከፍተኛ ስህተትና ምሁራዊ ንዝህላልነት ነው።

በአብዛሃኛው ምሁሩ መፍትሄ ሰጪ መሆን ሲገባው የባሰውን ችግር ፈጣሪ፣ መሪና አመላካች በመሆን ፋንታ ተከታይ አደናጋሪና አደንቋሪ፣ ደፋርና ልበ ሙሉ ከመሆን ይልቅ ፈሪና አጎብዳጅነትን፣ ሆድ አደርነትን የመሳሰሉትን ባህርያት ባለቤትና አንጸባራቂ ሆነ። የእነዚህ ባህርያት መገላጫ ሆኖ አለመገኘት የሚያስከትለው ለራሱ ያለውን ምሁራዊ ተአማኒነት ማጣት ብቻ ሳይሆን አገርንና ሕዝብንም ለጉዳት ማጋለጥ ይሆናል። ንቁና እውነተኛ የሕዝብ ምሁር የራስ ውስጣዊ የማንነት እውቀት ተሟጦ የማያልቅ የይቻላል መንፈስ ምንጭ መሆኑን ያውቃል፣ ሌሎችንም ያሳውቃል። ይህን ካላደረገ ግን አሁን ለምንገኝበት ለዘመነ ድንቁርና በር ይከፍታል፣ ይህም በቀላሉ ለሌሎች ተገዥ መሆንን ያስከትላል። በማወቅም ባለማወቅም ለዚህ የአመለካከት ውዝግብ ሰላብ የሆነው በአብዘሃኛው የተማረው ክፍል ሲሆን፣ ትርፈ ውጤቱ ማለትም የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ ግን ሰፊው ሕዝብ ነው።

ወያኔን መሰል፣ ነገር ግን ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ጎሣዊነትንና አገራዊ ስሜትን በእኩል ደረጃ ወይም ጎሣዊነትን አብለጠው የሚመለከቱ ታማኝነትና የማንነት ስሜታችው ዝቅተኝነት፣ አግላይነትና ጠባብነትን የሚያስቀድሙ ንቅናቄወች፣ ለብሔራዊ አንድነት ሆነ ለአማራው ደህንነት መሰናክሎች መሆናቸው ከምን ጊዜ በላይ ዛሬ ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ አገራዊ ህልውናም ሆነ በሕዝብ አንድነት ላይ ቅድመ ሁኔታዎች የሚያስቀመጡ፣ የሚደራደሩ፣ ወያኔን መቃወም ላይ ብቸኛ ትኩረት ይደረግ በሚል ሽፋን አገራዊ ሆነ ስለ አማራው ጉዳይ ተገቢው ትኩረት እንዳይደረግ በተድበሰበሰ የፖለቲካ ሁካታና በገለባ ስሜትዊ እይታ ተዳፈኖና ተሸፋፍኖ እንዲታለፍ ይደረጋል። በአማራው ላይ ያላቸውም ይህ ያልጠራና የተደናገረ እይታ በይዘቱ ከወያኔ የጎሣ ፖለቲካ ፍልስፍና እምብዛም የራቀ አይደለም።

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያዊነት ላይ የጥፋት የንቀትና የራስ ጥላቻ አስተሳሰብ ሰርጎ የገባው በዚሁ በምራብያውያን ዘመናዊ ትምህርትና አመለካከት አማካኝነት ነው። ሙሉ በሙሉ ለጥፋት መሳሪ የሆነው ምሁር ግን ጸረ ኢትዮጵያና ጸር አንድነት የሆነው በብሔረ ሰብና ጎሣዊ አስተሳሰብ የታነጸውና በተገንጣይነት መንፈስ የተሰለፈው ነው። ኢትዮጵያዊነትን ያነገቡ፣ የነቁና የሕዝብ ወገን የሆኑ፣ ለእውነት የቆሙ፣ አገር ወዳድ ጀግና ምሁራንም አሉ። እነዚህ ሃቀኛ ምሁራን ጠላት ወይም ተቀናቃኝህ በሚሰጥህ መርህ መመራት፣ የፈጠረውን መንገድና አማራጭ መቀበል ተሸናፈነትንና ራስ ጎጂነትን እንደሚያስከትል መጠቆም ይኖርባቸዋል። ይህ ቆራጥ የምሁር ከፍል ብዙ ተጋድረቶች ቢኖሩበትም፣ ይህን ችግር ይወጣዋል፣ አመለካከትን በትምህርትና በንቃት መልሶ መቀየርና ማስትካከል ይቻላልና። ይህን በማድረግ ሕብረትሰቡን ከችግር መንጥቆ ለማውጣት የሚሰራና የማይሰራውን ዘዴ ለይቶ በማሳየት፣ እቅድን በመተለም፣ የጊዜንና የቅደም ተከተል ጠቃሚነትን በማስገንዘብ ለለውጥ የሚያመቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።

ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ ማለትም ሰለራስ ምንነት ትክክለኛና የተሞላ እውቀት የሌለው ሕዝብ ሊጠይቅና ሊመራመር የሚሳነው፣ በራሱ የማይተማመን የተዛብ አስተሳሰብ ያለው የተማረ ማኅበረሰብን ይፈጥራል። የግራም ሆነ የቀኝ የባእዳንን የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ፍልስፍና ያለ ጥልቅ ምርምርና ጥብቅ ጥንቃቄ በመቀበል የፖለቲካ ፕሮግራምና የትግል መመሪያ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የራስን አገራዊ አስተሳሰብ መናቅና ማንኮሰሰንም ያስከትላል፣ ይህ ደግሞ በአገር ይሁን በግለሰብ ውሰጠ ህሊናና ስነ ልቦናዊ ተክለ ሰውነት ላይ የዝቅተኛነት ባህርያትንና ሰሜቶች እንዲፈጠሩና እንዲንጸባረቁ ያደረጋል።

እውነተኛ ምሁር ሙያና ችሎታን ለጋራ ማህበራዊ ጥቅም ማዋል ለራስም ጠቃሚታ መሆኑን በመረዳት የሰለጠነ ነው። የመመርመርና የመፈተሽ፣ ችሎታና አቅም ያለው የሕብረትሰብ ክፍል ስለሆነ፣ ከራሱ የማንነት አንጻር በመነሳት ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ የፖለቲካ ስልት ነድፎ፣ አመለካከትን ቀርጾ የወደፊት አቅጣጫ የመስጠት ኃላፊነት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ይጠበቅበታል።

መደምደሚያ፤ “ደካማ ሁሉ እኔ ጠንካራ ነኝ ይበል”

የሕዝብም ሆነ የግለሰብ የዕለት ኑሮና የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወሰነው በዋናነት በአእምሮው በጸነሰው እምነትና በራሱ የአስተሳሰብ እይታ ላይ በተመሰረት ስልትና ሀይል ሲመራ ነው፤ ይህን ማድረግ በራስ መተማመንን ያዳብራል። በራስ ለመተማመን በቅድሚያ ራስን በይዘትም ሆነ በቅርጽ በጥልቅ ሃሳብ ማወቅን ይጠይቃል። ራስን ማወቅ የእውቀት ሁሉ መሰረትና የበላይ ነው። በዚህ መርህ መሰረት ሕይወታችን ሆነ ትግላችን ሲመራ፣ የምንፈለገውን ለመሆንና ለማግኘት ሙሉ ዋስትና ይኖረናል ምክንያቱም የምንመራበት ሃሳብና አስተሳሰብ ከእኛ የመነጨ፣ ከእኛ ማንነትና ጥቅም ጋር የማይቃረንና የማይጣላ ስለሚሆን። ሌላው ደግሞ አንድ ሕብረትሰብ ለረጂም ጊዜ መብቱን ሲገፈፍና ሲጨቆን፣ ከሚደርስበት ጉዳቶች መሀል ነጻነቱን ለማስከበር የሚያስችሉትን ስሜትና ባህርያትን መነፈግ ነው፣ የነበረውን እንዲያጣ ወይ እንዳያዳብር በማደረግ ማለት ነው። በዚህም ምክንያት የጭቆና ዘመኑን ያስረዝማል፣ ይህም የሚሆነው አንደኛው ዘዴና መንገድ ራሱ ስለራሱ አሉታዊ፣ መጥፎና ደካማ ግምት መስጠትን እንዲያዘወትር በህሊናው ውስጥ እንዲሰርጽ በማድረግ ነው። የራስን አቅም መገንቢያና ነጻነትን ማስከበሪይ አንዱ መሳሪያ ተጎጂነት፣ ተጠቂነት፣ አሉታዊና ራስ ከሳሽነትንና ሌሎች ደካማ ስሜቶችን በማሰላሰል የመዋጥ አዝማሚያና ልምድን መፍጠር ነው። ከእንዚህ ጉልበትን ከሚሟጥጡ፣ አቅምን ከሚቦረቡሩ ህሊናን ከሚያናውጡ አስተሳሰብ መራቅ፣ ማስወገድና በምትኩ ስለራስ ቀና መልካምና ጠንካራ አወንታዊ ማንነትን ማጉላትና ማሳደግ፣ የምንፈለገው እውነታ እንዲከሰት ይረዳናል።

በወያኔ የትግሬ ነጻ አውጪ ግንባር የተደገሰለትን ልዩ አደጋ በአጽኖት የተገንዘበ፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስንና ስነ ልቦናዊ ማንነቱን የኃይሉ ምንጭና ማእከል በማደረግ የሚንቀሳቀስ የአማራ ስልታዊ ንቅናቄን ማራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው፣ ይህ ስልትም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፎች መምታት እንድሚባለው ድል አድራጊ ስልት ነው። ሌሎች ማኅበረሰቦች ወይም ጎሣዎች ይህንን ስልታዊ አስተሳሰብና አካሄድ፣ ማለትም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ውስጣዊ የራሳ መሳሪያ ቢያደርጉ ወያኔን በአፋጣኝ በማስወገድ የጋራ የድል ቀንን እናቀርባለን። በአማራው ሕዝብ ላይ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ወንጀል ሲፈጽም ማወገዝ ብቻ ሳይሆን በአስቸኰይ ማስቆም ዛሬ ነገ የማይባል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ፍጹም ግዴታችን ሊሆን ይገባል። ይህ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር፣ ማንም ፍትህ ወዳድ፣ ነጻ ሕዝብ ሁሉ ሊቆረቁረው ይገባል፣ አማራው ለሌሎች የሕዝብ ቅነሳ እቅድ ሰለባና የበግ ጭዳ መሆን የለበትምና።

ኢትዮጵያ በራሷ ሕዝብ የተፈጠረች አገር ስትሆን መልሳ የፈጠራትን ሕዝብም የፈጠረችና የቀረጸች ታላቅ አገር ናት፤ ዛሬ ግን ሕዝቧ ይህን ማንነት ባለማወቁና በመዘንጋቱ ለወያኔና ለተባባሪወች የባርነት ቀንበር ለጊዜው ቢዳረግም ከዚህ ተመክሮ በመነሳት ችግሩን ወደ አሸጋጋሪ የለውጥ መሳሪያትነ በመቀየረ ትንሳኤውን ያረጋግጣል። ውድ አገራችን ኢትዮጵያ ያላችበት መስቀለኛ መንገድ፣ ለብሔራዊ ህልውናዋ ሆነ ለሕዝቧ አንድነትና ደህንነት አደገኛ ቢሆንም በልጆቿ ልዩ ባህሪና ብርታት የተጋርደባትን አደጋ ልትታዳግ እንደምትችል ታሪካዊ ማንነቷ በድጋሚ የሚያረጋግጠው ሀቅ ይሆናል። እንደ ወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ፣ ለባእዳን ያጎበደደ ፣ ራሱን የካደ የውስጥ ጠላት በታሪኳ ውስጥ ባይገጥማትም ለመነሳት የሚያስችላት ልዩ ኃይል ከውስጧ ስለሚፈልቅ በአቸናፊነት ትነሳለች ብየ አምናለሁ። ይህን እምነት እውን ለማድረግ የምንችለው ግን ወያኔን በመጥላት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመውደድ መሆን አለበት በዋናነት። ለአገራችን በምናደርገው የትግል ሂደት ደካማና አሉታዊ ከሆኑ ሁኔታዎች ይልቅ አወንታዊ ባህርያትን፣ ቀናና ጠንካራ የማንነት መገለጫወችን ማጉላት፣ መነሻ መሰረትና የስበት ማእከል ማድረግ ለምንፈለገው ነገር ሁሉ መሳካት ከፍተኛ አወንታዊ ጥቅም ይሰጠናል፣ ስለዚህ “ደካማ ሁሉ እኔ ጠንካራ ነኝ ይበል”።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

አበባ ፈቃደ

ግንቦት 2009

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!