Ethiopian opposition leaders

በምርጫ ፳፻፯ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች

ሸንቁጥ አየለ

ኢትዮጵያ ተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍም ሆነ ሐሳብ መሰንዘር አጸያፊ ሆኖ የሚገኝበት ወቅት ቢኖር የተጋድሎ ጓዳቸውን እሬሳ እንኳን ሊሰበስቡ በሕይወት ያሉ አመራሮቻቸውን የሚረሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በፍጥነት እየተገነቡ የሚፈርሱበት አገር መሆኑ ነው።

ተቃዋሚ ተብዬ ፓርቲዎች ይሰባሰባሉ እንጅ የሚሰባሰቡት እስከሞት አብረው ሊዘልቁለት በሚማማሉት ግብ እና ራዕይ አይደለም። እናም የተሳሰሩበት አላማ በአንድ ስብሰባ ጭቅችቅ ተረስቶ ፓርቲዎቹ በፍጥነት ይፈርሳሉ። ወይም ደግሞ ወያኔ የሰጠኋችሁን ፈቃድ ነጥቄአችኋለሁ ያላቸው እንደሆነ የመሰረቱትን ፓርቲ አፍርሰው ሌላ አዲስ ፓርቲ ሊመሰርቱ ሽር ጉድ ይላሉ። ወይም ደግሞ ከሌላው ፓርቲ ሄደው ለመቀላቀል ብዙ መተጣጠፍ እና የራሳቸውን የቀድሞ አባላት ማንቋሸሽ እና መዝለፍ ይጀምራሉ። ይሄ እውነታ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን በሚሉት ብቻ ሳይሆን በመሳሪያም ለመታገል በሚነሱት ድርጅቶች የሚስተዋል ነው።

ጠንካራ ተቃዋሚዎችን ወያኔ አንቆ ወደ እስር ቤት ስለወረወራቸው የትግል ጓዶቻቸው ከቶም ግድ አይሰጣቸውም። ስለነዚህ ታጋዮች መከራ ወይም የቤተሰብ ስቃይ ግድም ሳይላቸው አንዱን ፓርቲ ጥለው አንዱ ፓርቲ ላይ ይንጠለጠለጠላሉ።

"እረ ... ምን ግመኛ ነገር ገጠመኝ እሳ?" ይላል የጎጃም ሰው ሲገረም። እውነትም እረ ... ምን ግመኛ ሥነልቦና ነው እንዲህ ጦቢያን የወረራት? ጀግና እንዴት የትግል አጋር ጓዱን እሬሳው ጥሉ ይሸሻል?ጀግና እንዴት መሪውን እና አጋር አባላቱን አስበልቶ የመሰረተውን ፓርቲ በትኖ ወደሌላ ፓርቲ ይሸመጥጣል? ጀግና እንዴት ጓዱ ሲታሰር በእስር ቤት ይረሳዋል? ጀግና እንዴት ጠላት ወያኔ ፓርቲዬን አፍርሶታል እና በቃ እንበታተን ብሎ ይስማማል? ለሕዝብ ሊዋደቅ የተነሳ ጀግና እንዴት ጀግና ጓደኛውን በእስር ቤት ረስቶ ካሁን ብኋላ የምሳተፍበት ፓርቲ ሌላ ስም ስላለው እስር ቤት ስለወደቁት የቀድሞ አጋሮቼ ግድም አይለኝም ይላል?

እውነታው ግን ይሄ ነው። እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ሌላው ቀርቶ ጀግኖቹ በእስር ቤት እየተሰቃዩ በሐሰተኛው የወያኔ ፍርድቤት ሲቀርቡ እንኳን ዜናቸውን የሚዘግብላቸው የተቀናጀ የፓርቲዎቻቸው አሰራር የላቸውም። ለምሳሌ ያህል የሰማያዊ፣ የአንድነት፣ የመኢአድ ጀግኖች ዛሬ በእስር ቤት መማቀቃቸው ብቻ ሳይሆን እየደረሰባቸው ያለውን ዜና የቀድሞ ፓርቲዎቻቸው በተቀናጀ ሁኔታ በውስጥ ተነጋግረው እንዲዘገብ የሚያደርጉበት ስልት አልፈጠሩላቸውም። የቀድሞ አጋሮቻቸው ተበታትነዋል፣ ሕጋዊነታ አጥተዋል የሚል የማስመሰያ ሽፋን ግን አይሰራም። ችግሩ ሕጋዊነት ማጣታቸው ላይ አይደለም። ችግሩ ያለው የሞተ ማኅበራዊ እና ሥነልቦናዊ ዝቅጠት ውስጥ ኢትዮጵያውያን መዘፈቃችን ነው።

ጥንታዊያን አባቶቻችን ጦረኛ መሆናቸው ብቻ አልነበረም የሚያስከብራቸው። ከሁሉም የተከበረው ሥነልቦናቸው ግን የጓዳቸውን ሬሳ በጦር ሜዳ ጥለው አለመሸሻቸውም ነው። የጓድህን ሬሳ ጥለህ እንዴት ትሮጣለህ? ወዴትስ የአቋራጭ ድል ፍለጋ ከሌሎች ጓዶች ጋር ለመቀላቀል ትፈረጥጣለህ? መጀመሪያ ቃል የገባህለት ጓድህ፣ አላማህ፣ ፓርቲህ እና እምነትህ ዝም ብሎ የሐሰት ነበር ማለት ነው? ነው ወይስ የትግል ሂደቱ እንዲህ በአቋራጭ አንዴ ከዚህ ሌላ ጊዜ ከዚህ እያቃሰጥህ እና ሄደህ እየተለጠፍህ የሚገኝ መስሎህ ነበር? ታላላቅ አገራት አሜሪካንን፣ እስራኤልን፣ ሩሲያን እና ቻይናን ጨምሮ ጥልቅ እና መሰረታዊ የሆነው የትግል እና የጦር ሜዳ ብሎም የፖለቲካ ትግል መርህ ምን እንደሆነ አታቅም ማለት ነው? በማንኛውም ቦታ ብትሆን የትግል አጋር ሬሳን ጥሎ መሸሽ የለም የሚል ነው። ይሄ የቀደሙ ኢትዮጵያውያን መርህ በማንኛውም ታላላቅ እና ጽኑዓን የአለም ሕዝብ ዘንድ በክብር ወርቅ የተጻፈ መርህ ነው።

ሆኖም በኛ ተቃዋሚዎች ዘንድ ይሄው የሥነልቦና ዝቅጠት በመላው አለም የተበተነው ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ፖለቲከኛም ውስጥ እንደ ጉድ ይስተዋላል። ትናንት እና እደግፋቸዋለሁ ብሎ የተነሳውን ጓዶቹን ፓርቲያቸው ደከም ያለ እንደሆነ፣ ወያኔ ፈቃዳቸውን ነጥቄያቸዋለሁ ያለ እንደሆነ እንደ እሥስት ቆዳውን ቀያይሮ እንደ ሀሳዊ መሲህ መምህር የትምህርት አላማውን ቀላቅሎ እና አምታትቶ አንድም እጥፍጥፍ ይልና አዲስ ፓርቲ ፍለጋ ይኳትናል። አዳዲስ ጉልበት ያላቸው የሚመስሉትን፣ ገንዘብ ያላቸው የሚመስሉትን፣ ሚዲያ ያላቸው የሚመስሉትን ቡድኖች ተከትሎ ይሮጣል። አንድ ሰሞን ሲጮህላቸው እና ሲያሞጋግሳቸው የነበሩ ጀግኖች ፓርቲያቸው ደከም ሲል፣ እስር ቤት ሲወረወሩ፣ አካላቸው ሲጎል፣ ሲራቡ፣ ቤተሰባቸው ሲበተን፣ እና ሞት ሲደርስባቸው ለቅጽበት እንኳን ዘወር ብሎ ላለማዬት ህሊናውን ይደፍናል። እንዴውም "አይ የነሱ መንገድ አያስኬድም። አሁን መደገፍ ያለብን ይሄኛውን ወገን ነው" ብሎ ቁጭ። እናም ትናት ለታጋዮች በግድ ንዘብ ካልላክሁላቸው ይል የነበረ ዲያስፖራ ደጋፊም ይደግፈው የነበረ ፓርቲ ደከም ያለ እንደሆነ፣ ወይም ጀግኖቹ ሲታሰሩ እና ቤተሰባቸው ሲበተን በአላዬሁም ባልሰማሁም ላሽ ይላል። ሌላ እስክስታ እደመቀበት ከበሮ ለመነረት ይሄዳል። ድል ለመስበክ። ስለ ድል ለማንባረቅ። ድል ግን የራሱ ሕግ አለው እንጅ በስክስታ አይመጣም።

አስገራሚ ነው። ሰዎች ተቃዋሚ ነን ብለው የሚሰባሰቡበት አላማ እራሱ ግልጽ ሳይሆንላቸው ነው እንደ ወገዝ በመንጋ ተሰባስበው የሚነጉዱት ማለት ነው? መሆኑ ነው። ደግሞ ለመገለባበጥ ፍጥነታቸው። አሁን በርካታ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበሩ ጀግኖች የት ነው የወደቁት? በርካታ የሰማያዊ እና የመኢአድ አመራሮች፣ አባላቶች እና ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞው ፖለቲካ ውስጥ በመሳተፋቸው የደረሰባቸው ሁኔታ መራራ እና አስጨናቂ ቢሆንም በአንድ ወቅት አጋር የነበሯቸው ዛሬ ዘወር ብለው ላያዩዋቸው ሌላ አዲስ ቡድን እየፈለጉ እስክስታ ላይ ናቸው።

ትግል እንደ ወረት ነው የተያዘው። ድል በአቋራጭ ሊገኝ መሆኑ ነው። በአንድ ወቅት ቅንጅት ብለው አብረው የተሰለፉ ሰዎች ዛሬ ተበታትነው ብዙ ጎራ ውስጥ ተሰልፈው በእስር ላይ ስለሚጉላሉ የቀድሞ አጋሮቻቸው ዞር ብለውም ላለማዬት ወስነዋል። የትግል ጓድን ሬሳ ጥሎ መሸሽ ማለት ይሄው ነው። ፓርቲያቸውን እንደሞተ ነገር፣ አላማቸውን እንደ ሞተ ነገር እረስተው በፍጥነት ከፓርቲ ፓርቲ የሚዘሉ ብዙዎች ናቸው።

ዛሬ ሽህ እና ሽህ እስረኛ በመላ አገሪቱ እስር ቤቶች ታስሯል። ሽህ እና ሽህ እስረኛ የታሰረው ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሲዋደቅ ነው። ግን ዛሬ በመላው አለም የተበተነው ኃይል አንድ እንኳን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የፖለቲከኛ እስረኞች ያለ አድሎ እና ማግለል የሚጠይቅ እና የሚያጽናና ብሎም የሞራል አጋርነቱን የሚያሳይ ድርጅት መመስረት አልቻለም። ለምን? በቃ እነዚያ በአንድ ወቅት ትንታግ የነበሩት ታጋዮች ዛሬ ታስረዋላ። ዛሬ እስር ቤት ናቸዋ።

የትግል አጋሩን እሬሳውን ጥሎ የሚሸሽ ሥነልቦና በኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ውስጥ እንደ ጉድ ይንጽባረቃል። አንዳንድ ነጋዴ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ደግሞ ሁሉንም እስረኞችን እንጠይቃለን፣ እንደግፋለን ብለው ብር ያሰባስቡና ጥቂት ጥቂት ድጋፍ የሚያደርጉት እየመረጡ ነው። እነ እገሌ እኛን ይቃወሙናል፣ እነ እገሌ ከኛ ጋር ተጣልተዋል፣ እነ እገሌ አክራሪዎች ናቸው፣ እነ እገሌ የዚህ ፓርቲ ሰው ናቸው እያሉ እስረኛን ከስረኛ አበላልጠው ድጋፍ የሚሉትን ጥቂት ነገር እነሱን ይደግፉናል ለሚሏቸው በተን በተን ያደርጋሉ። አሳፋሪው ነገር ታዲያ ድጋፉን ሲሰበስቡት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እስረኞች ብለው መሆኑ ነው። ለእከሌ ፓርቲ አባላት ድጋፍ አደርጋለሁ ሳይሉ እና ለሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድጋፍ እናደርጋለን ብለው ጀምረው አጨራረሳቸው ግን ከወያኔ የባሰ ወገንተኛ ሆነው ቁጭ። ለሕዝብ ሪፖርት ሲያቀርቡ ግን ሁሉንም ወገን እንደደገፉ አድርገው ነው። ወያኔስ ኢትዮጵያን በምን አመሳት? የእኔ ወገን ብቻ፣ እኔን የሚደግፈኝ ብቻ ይጠቀም በማለት አይደልም?

እናም ለተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን እና ፓርቲዎቻቸው አንድ ጥብቅ መልዕክት ቢተላለፍላቸው መልካም ነው። የቀደመውን ኢትዮጵያዊ የሥነልቦና እና የማኅበራዊ እሴት አንግባችሁ መታገል ካልቻላችሁ ከቶም እንደማታሸንፉ እወቁት። በቀደመው ኢትዮጵያውያን ሥነልቦና እና ማኅበራዊ እሴት ውስጥ በጦር ሜዳም ይሁን በማንኛውም ተጋድሎ ስፍራ የጓድህን ሬሳ ጥለህ አትሄድም።

በትግል አለም ያላችሁ ወገኖችም ሆናችሁ ወደ ትግል አለም የምትቀላቀሉ ወገኖችም እራሳችሁን አንድ መሰረታዊ ጥያቄ አጥብቃችሁ ጠይቁ። ዛሬ አብሯችሁ ያለው ታጋይ ነገ እሬሳችሁን ጥሎ የሚሸሽ ነው? እናንተስ የአጋራችሁን እሬሳ ጥላችሁ የምትሸሹ ናችሁ? ነው ወይስ በክብር እስከ መጨረሻው የቀብር ስርአቱን እንደ አንድ ታላቅ አርበኛ ታስፈጽሙለታላችሁ? እነዚህን ሶስት የሚመስሉ ግን አንድ መሰረታዊ ጭብጥ ያላቸው ነጥቦች በአስተማማኝ መመልሰ ከቻላችሁ ብቻ የሚከተሉትን ነጥቦች በአንድ መስመር መመለስ ትችላላችሁ ማለት ነው።

የተሳሰራችሁበት የትግል አላማ አንድነት፣ ያስተሳሰራችሁ ድርጅት እውነትኛ የትግል መሳሪያነት፣ የአሸናፊነታችሁ አድማስ እና አብረዋችሁ ያሉት አጋሮቻችሁ በግብ እውነትም የተሳሰሩ መሆናቸውን በአስተማማኝ ማብራራት ትችላላችሁ ማለት ነው። መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃውሞ ውስጥ የሚገባው ለታላቅ አገራዊ መስዋዕትነት እና ሕዝባዊ ተጋድሎ መሆኑን ነው። ይሄ ጉዳይ ደግሞ የጓዱኑ እሬሳ በትግል ሜዳ ጥሎ የሚሮጥ ሥነልቦናን እና ማኅበራዊ እሴትን በአነገበ ስብስብ ውስጥ ከቶም እውን አይሆንም። 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!