La Gare downtown luxury complex design, Addis Ababa

በአዲስ አበባ ለገሀር ሊገነባ የታቀደው ዘመናዊና የተቀናጀ የማሕበረሰብ ልማት አምባ ፕሮጀክት ዲዛይን

ዘ-ጌርሳም

ገና ስምንት ወር ብቻ ነው - ሕፃናት ተወልደው ቁመው የማይሄዱበት ዕድሜ፤ ከድምፅ በቀር ቃላት እንኳን አያወጡም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ተጭኖት ከነበረው የመከራና የግፍ አገዛዝ ቀንበር ራሱን ነፃ ለማድረግ፤ መራራና ፈታኝ መስዋእትነት ከፍሎ ለውጡን ለሚመሩለት ኃይሎች አስረክቧል። ይህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት በየቀኑ የሚያሳያቸውንና የሚያስመዘግባቸውን ለውጦች በአንክሮ ለሚከታተል ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኝ ሆኖ ጥራቱና ፍጥነቱ ደግሞ የበለጠ ያስደምማል።

የዓለም አገሮችና መንግሥታትም ያልተለመደና በማንም አገር ላይ አይተውት የማያውቁት ዐይነት የለውጥ እርምጃ ስለሆነባቸው፤ በአርምሞ እንዲከታተሉ ብቻ አድርጓቸዋል። ታሪክም የዚህ ዐይነት ለውጥ የመዘገበው አልተገኘም።

እውነትም ኢትዮጵያ ታላቅና የሁሉም ነገር መገኛና የታሪክ መነሻ ነች አስብሏቸዋል፤ ከታላቅነት ላይ እጥፍ ድርብ ክብረ ሞገስን አጎናጽፏታል፤ ይህ የሰው ሥራ ሳይሆን የፈጣሪ ገድል ነውም አስብሏል።

ሰላምና ፍቅር በአገር ውስጥ፤

ሰላምና ፍቅር ለጎረቤት አገራት፤

ሰላምና ፍቅር በየአገሩ ተበትነው ለኖሩ ኢትዮጵያውያን፤

ሰላምና ፍቅር ከኢትዮጵያ ለሁሉም ክፍለ ዓለማት፤

የሙሴን ተልኮ በተግባር የደገመ መንፈሳዊ ተልዕኮ የመሰለ ግብዐትና ከፈጣሪ የተላከ የምሕረት ብሥራት አዋጅ።

ሕብረተሰቡ ለውጡን ለሚመሩት ኃይሎች አስረክቦ ቁጭ ማለት ግን በቂ የሚሆን አይደለም፤ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ጣምራ ትግሉን መቀጠል ይጠበቅበታል። እያንዳንዱ ዜጋም የለውጡ አካል የመሆንና የባለቤትነት ስሜትን በሕሊናው ማስረጽ ተገቢ ይሆናል፤ ትግሉ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚና የሥነ ልቦና ጭምር በመሆኑ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲን ለማስፈን ሁለገብ ትግል ያስፈልጋል።

ለውጡ በአሸናፊነት ካስመዘገባቸው ግብዐቶች አንኳሮቹን መጥቀስ ቢያስፈልግ፣

  • የፖለቲካና የሕሊና እስረኞ መፈታት፤
  • ለተፎካካሪ ኃይሎችና ቡድኖች ሰላማዊ የትግል መድረክ መፍጠርና ምኅዳሩን ማስፋት፤
  • ሆድና ጀርባ ሆኖ የቆየውን ሕብረተሰብ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩትን ወገኖች ለመጀመሪያ ጊዜ እጅ ለእጅ አያይዞ በጋራ የጋራ የድል በዓላቸውን እያከበሩ የሰላምና የፍቅር ዜማዎችን አዚሟል፤
  • ለሃያ ዓመታት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦችን እንዲገናኙ አድርጓል፤
  • የአገርና የሕዝብ ሀብት የመዘበሩና ያሸሹ ትልልቅ ዓሣዎችና ድርጅቶቻቸው ሕጋዊ ማረጋገጫ ባለው የክትትል ውጤት ተለይተው በመገናኛ ብዙኃን እንዲታወቁ ተደርጓል፤
  • የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረሱና በሕዝብ ላይ ዘግናኝና ኢሰብአዊ በደል ከፈጸሙት ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ተለይተው ታውቀዋል፤ በርካታዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከነሱ ባላነሰ እንዲያውም በሚበልጥ መልኩ በሕዝብ ላይ ሰቆቃ ያደረሱት ትንንሽ ዓሣዎችም ዕጣ ፈንታቸው የትልልቆቹ ዐይነት እንዲሆን፤ ሕብረተሰቡ በማስረጃ ክትትል እያደረገ በመጠቆም ሕግ ፊት እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት ይጠብቀዋል።

የልማት ትብብርም፣ ወንጀልና ወንጀለኛን መከታተልና መከላከል የመንግሥት ብቻ የሥራ ድርሻ መሆን የለበትም፤ ሕብረተሰቡ ግድግዳና ማገር በመሆን መተባበር ግድ ይለዋል።

ሰሞኑን፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዳግም ለማሳበብና እንደሌሎች አገሮች ዋና ከተሞች የተዋበችና ያሸበረቀች ከተማ ለማድረግ፤ በለገሀር ሊገነባ ለታሰበው ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረት ድንጋይ ማኖራቸው፤ ታላቅ የደስታና የተስፋ ስሜት የሚሰጥ ነው። ይህ ጅምር በየክልሉ ዋና ከተሞችና ሌሎች የገበያና የቱሪዝም ማዕከል በሆኑ አካባቢዎች ተመሳሳይ የግንባታ ሥራ እንዲጀመር አነሳሽነት አለው። በመሆኑም፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከዚህ እሳቤ በመነሣት፤ የበኩላቸውን የዜግነት ግዴታ መወጣት ይገባቸዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃንም የተጋ እንቅስቃሴ፣ የቅስቀሳና የማበረታቻ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የመገናኛ ብዙኃንና የሶሻል ሜዲያ ድረ ገፆችም በዚህ ወቅት ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የሥራ ድርሻ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችም እንደተለመደው ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ለሕዝብ ልዕልናና ለታሪክ ጥሪት የሚሆን ሙያዊ እርሾ ጥለው ማለፍ ግድ ሊላቸው ይገባል።

ዶክተር ዐቢይና ካቢኔያቸው በቁጥር ውስን ከመሆናቸው ባሻገር፤ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት፤ ሕብረተሰቡ ለየክልል አስተዳደሩ አጋዥ በመሆን በየአካባቢው ያሉትን የሥራ ድርሻዎች በትጋት የማከናወን ኃላፊነት ይጠበቅበታል።

የምንገኘው በሽግግር ወቅት በመሆኑ፤ ነገ ዴሞክራሲያዊትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለማየት የሚፈልግ ሁሉ፤ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገዪቱ ኢትዮጵያ መሠረት ለመጣል ከአሁኑ የግንባታ ጡቦችና የተመቻቹ ድንጋዮችን በማቅረብ ጠንካራ ግንብ መገንባት ካልጀመረ፤ ተሠርቶ የሚያልቀው ቤታችን በቀላሉ የሚፈርስና የሚናድ ይሆናል። በመሆኑም በሁሉም መስክ ሕዝብ፣ ባለሀብቶች፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ)፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግሥት በጋር በመተባበር የለውጡና የግንባታው አራማጅ መሆን ይገባቸዋል፤ ”ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ነውና።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!