የሕንድና የሳውዲ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ናቸው

Ethiopia Zare (አርብ ኅዳር 4 ቀን 2002 ዓ.ም. November 13, 2009)፦ በኢትዮጵያ ለእርሻ አገልግሎት ከሚውለው 14 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ለውጭ ባለሀብቶች እንደሚሸጥ የግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።

 

አቶ ኢሳያስ ከበደ የኤጀንሲው ዳይሬክተር ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሕንድና ሳውዲ ዐረቢያ ለእርሻ ኢንቨስትመንት መሬት ጠይቀዋል፤ በዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናር ምክንያት መሬት ለመግዛት ስለተጣደፉ እንሸጥላቸዋለን ብለዋል።

 

ሰሞኑን አዲስ አበባ የገቡት 400 የሚሆኑ የሳውዲ ባለሀብቶች ከዛሬ ጀምሮ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደርጋሉ። አንድ የሳዑዲ ባንክ ኃላፊ ለዓመታት ዘግታን የነበረችው ኢትዮጵያ ከኛ ጋር በመስማማቷ ደስተኛ ነን ብለዋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጭ አዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተገኝቶ እንደታዘበው ሦስት መቶ የሚጠጉት የሸራተን ሆቴል ክፍሎች በሙሉ የተያዙ ሲሆን፤ የአንድ አልጋ ዋጋም 500 ዶላር ደርሷል። እንግዶቹ በሌሎች ሆቴሎችም እንዲያርፉ እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

 

የሳውድ ኢንቨስተሮች ሳውዲ ለኢትዮጵያ በዋለችው ታላቅ ውለታ የመጡ ናቸው፤ በቅርቡ ለግልገል ጊቤ ሁለት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ ፍለጋ ዓለምን የተማለደችው ኢትዮጵያ፤ ሳውዲ ዐረቢያና ቻይና የረዥም ጊዜ ብድር በመስጠታቸው በኢህአዲግ የሰጥቶ መቀበል ፖሊሲ የሳውዲ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ብለውናል ምንጮቻችን።

 

ባለሀብቶቹ ለ30 ዓመታት የሚሆን መሬት የሚፈልጉ ሲሆን፣ ለ5 ዓመታት የኢህአዲግ መንግሥት በነፃ ነው የሰጣቸው። ኢትዮጵያ በስመቲ ሩዝን በማምረት ለሳውዲ ገበያ በሳውዲያውያን ልታቀርብ ነው።

 

ኢንቨስተሮቹ ከሲሸልስ የተባረሩ ናቸው ያሉት ምንጫችን፤ ሲሸልስ ውስጥ ገብቶ በነበረው ድርቅ ህዝቡ በማመጹ ሊባረሩ የቻሉ ናቸው።

 

ኢትዮጵያ እስካሁን ያልተጠቀመችበትን ቦታ ለኢንቨስተሮቹ የምትሰጥ ሲሆን፣ ካልበቃ ከገበሬዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ከገበሬዎቹ ተወስዶ እንደሚሰጣቸው ታውቋል። መሬቱ ለቡና፣ ለጥጥ፣ ድንች፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ለሻይ ቅጠል፣ ፓልም ኦይል፣ ለአበባ፣ ለሩዝና ለመሳሰሉት የሚሆን ነው። እስካሁን ሁለት ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን መሬት ለመሸጥ መዘጋጀቱ ታውቋል።

 

ጉዳዩ ያሳሳባቸው ኢትዮጵውያን መሬትን ለሕንድ፣ ለሳውዲ ዐረቢያና ለቻይና ለረዥም ዓመታት ቆርሶ መሸጥ በሀገሬው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ከባድ እንደሆነና በሌሎች ሀገራት የተከሰተው ችግር ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ለሀገር በቀል ኢንቨስተሮች የበለጠ ሊደረግላቸው ይገባልም ብለዋል።

 

የሳውዲን እንቅስቃሴ ከተቃወሙት አንዱ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ኅዳር 2 ቀን 2002 ዓ.ም. በጠራው ስብሰባ በውጭ ንግድ በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንሰሳት ተዋጽዖ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ከሳውዲ ነጋዴዎች፤ የኢትዮጵያ ንግድ ም/ቤት ከሳውዲ ንግድ ም/ቤት ጋር ግንኙነት እንዲመሰረት አሳስበዋል። አክለውም ባለሀብቶች የኢትዮጵያ የሥጋና አትክልት ወደ ሳውዲ ገበያ ለመግባት ችግር ያለበት ሲሆን፣ ምርቶቻችሁን በጅቡቲ ነጋዴዎች በኩል አቅርቡ እንደሚባሉም ገልጸዋል። ሳውዲዎች ከኢትዮጵያ ይልቅ መንግሥት ከሌላት ሶማሊያ በግ፣ ፍየል እና የቁም እንሰሳት እንዲሁም ሥጋ መግዛት እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

 

ሳውዲ ለኢትዮጵያ ቅርብ በመሆኗና ካላት የኢንዱስትሪ አቅም አንጻር በኢትዮጵያ የተሻለ ተጠቃሚ እንደምትሆንም ተገልጾ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም መንግሥት እንዲያስከብር ጥቆማ ተሰጥቶታል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ