PM Abiy Ahmed and activist and journalist Eskinder Nega

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድና አክቲቪስትና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

ዲበኩሉ ቤተማርያም

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ሌት ተቀን እየተንገበገብኩ አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን በጋራ ከማደርገው ትግል በተጨማሪ በግሌም እየታገልኩ ባለኹበት የመከራ ወቅት፣ እርስዎ ድንገት ብቅ ብለው የነፃነት ብርሃን እያበሩ ሲመጡ፤ እልል ብለው ከተቀበልዎት መኻል አንዱ ኾንኩ። ሙሉ ድጋፌንና ክፍት ልቤንም ልሰጥዎ ተገደድኩ። ፈጣሪንም አመሰገንኩ፤ ዕድሜና ጤና እንዲሰጥዎትም ለመንኩ።

እርስዎ ከቀን ወደቀን በሚያደርጉት ልብን በሚያረካና ማንንም በሚያስደስት ተግባርዎት ደስታዬ እጥፍ ድርብ ኾነ። በተስፋ መቁረጥ ተጨማዶ የነበረ ፊቴም ፈካ፤ የወደፊቷን ኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እየተመኘኹ ደስ አለኝ። አሸጋጋሪ መሪ መኾንዎትን አሰብኩ። በርግጥ በዚህ ጉዞዎ ላይ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚገጥምዎ ባውቅም፤ በአመራር ብቃትዎ እንደሚወጡት በሙሉ ልቤ አመንኹ።

በዚህ መኻል የቦንብ ጥቃት ሲሞከርብዎ፤ እኔ ላይ የደረሰ አደጋ ያህል ተሰምቶኝ አዘንኹ። እግዚአብሔር ይመስገን! ከሱም ተረፉ። አሜሪካ ኺደው ሲመለሱም ምን እንደሆኑ ባላውቅም ከሕዝብ እይታ ርቀው ስለነበር የደረሰብዎን ባለመረዳት እንደ ብዙዎቹ ኹሉ አዘንኩ። በዛን ወቅት እውነት ለመናገር እናቶች ሲያለቅሱና ሲጸልዩ ያድሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። አባቶችና ወጣቶችም እንደዚሁ። እንደውም አንድ ስለርስዎ ሐሳብ ያብከነከነው ሰው “አብይ አምሽቶ ከሚገባ ሚስቴ ውጪ ብታድር ይሻለኛል” ብሎም እንደነበር አስታውሳለኹ።

የርስዎ ፈተናም አላልቅ ብሎ እኔም ማሰብ አይጉደልብህ ብሎኝ (ይኽ የኔ ብቻ ሐሳብ ሳይሆን የብዙዎች ነበር)፤ ወታደሮች በሰልፍ ቤተመንግሥት ድረስ መጥተው ከሥልጣን ማውረድ ይኹን መግደል ሊያደርስብዎ ፈለጉ ሲባልም ብዙ ከፋኝ፤ ሆኖም ጥበበኛው መሪ ነዎትና ከንጉሥ ሰለሞን ብልሃት ባልተናነሰ ሁኔታ አብረው ስፖርት ሠርተው፣ ሐሳባቸውን እንዲተነፍሱ አድርገው እንደመለሷቸው ከርስዎ አፍ ስሰማ የተአምር ያህል ሆኖብኝ ተደሰትኹ። አንድ ሰሞን ካገኘሁት ጋር ኹሉ ይሄንኑ ሳወራ ከረምኩ። እውነት ለመናገር በድንገት የተገኘ መሪ ብቻ ሳይሆኑ፤ የግል ዘመዴ ጭምር እየመሰሉኝ ኼዱ። በነገራችን ላይ አሁንም ያ ስሜት አለኝ - የዝመድናው ስሜት …

እያደር ደግሞ ሐሳብ የሚበታትን ነገር ተፈጠረ። ቆሟል ያልነው መፈናቀልና ሞት በአስከፊ ሁኔታ በሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ ደረሰ። ያም ሆኖ እርስዎ ቀርበው ስለሁኔታው ሲናገሩ፤ እኚህ ሰው ፈረደባቸው በዚህ ባልተረጋጋና ጠላትና ወዳጅ በተቀላቀለበት አገር ሥልጣን ይዘው መከራቸው አዩ ብዬ ለርስዎም ጭምር አዘንኹ። ይኽ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰ፤ እርስዎ ከአገር ወጣ ባሉ ቀጥር አዳዲስ አደጋ እየተፈጠረ በመኼዱ፤ እንደሌላው ሰው ሁሉ አማኹዎት፤ ‘ምን አለ ጉዞውን ቀነስ ቢያደሩት፣ ስንት ጠላት እንዳለ ረሱት ወይ?’ ብዬ።

ሁኔታው ካንዱ ወዳንዱ እየተሸጋገረ የኔም መከረኛ ልብ ከፍ ዝቅ እያለች በሁኔታው ከቅርብ ሰዎቼ ጋር እየተወያየሁ እያለሁ፤ ‘አዲስ አበባ የኛ ናት’ የሚሉ ተጠናክረው ሲመጡ፤ አሁን እኔው ጋ ደረሱ ተውልጄ ያደኩት አዲስ አበባ እኔንና እኔን መሰሎችን የት ድረሱ ሊሉን ነው ብዬ ንድድ አለኝ። በዚህ መኻል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ “አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ናት” በማለት ተነሳ፤ ያደረገውንም አድርጎ ለአዲስ አበባና ለአዲስ አበባ ነዋሪ የብረት መዝጊያ ኾኖ ቆመ። ብራቮ! እስክንድር ወንድ ነው። እንዲህማ አይቀለድብንም! አልኩ። ደስ አለኝ ርቀት ያዘኝ እንጂ ከእስክንድር አጠገብ ባልተለየኹ ነበር።

ይሄን በማያያዝ ዘመዴ በቴለቪዥን መስኮት ብቅ ብለው መናገር ሲጀምሩ፤ አጅሬ አንጀቴን ቅቤ ሊያጠጡት ነው ብዬ እንዳቆበቆብኩ የጭቃ ጅራፍዎን ይዘው መጥተው እርር ድብን አደረጉኝ። ለማን እናገረዋለሁ እንደጨስኩ ውዬ እንደጨስኩ አደርኹ፤ ሰነበትኹም። ስንት ጥፋት ያጠፉ እያሉ፣ ስንቶች እንደፈለጉ ሲቦለትኩ፣ እኚህ ሰውዬ ምን ነክቷቸው ነው? ጦርነት ድረስ እገባለሁ ለማለት የደረሱት? ብዬ ጨስኹኝ። ምን አስደበቀኝ ክፉኛ አናደዱኝ። እንዴ! ሰውዬው ወዴት እየተጓዙ ነው? ብዬ ጥርጣሬም ውልብ አለብኝ። እውን እኚህ ሰው አብይ ናቸው ወይ? እስከማለት ደረስኹ። አፈርኩም፤ ደነገጥኩም። በፊቱኑ እኛ ብለን ነበር የሚሉ ሰዎች አንገታቸውን ቀና ቀና ማድረግ መጀመራቸው ደግሞ ይበልጥ አናደደኝ። ይኼ ኾኖ እያለ ከሳምንት በኋላ ከአቶ ለማ ጋር ተደርበው ማረጋጋት በሚመስል ሁኔታ በደፈናው ይቅርታ ቢያቀርቡም፤ ቅር መሰኜቴን እንዳዘልኩ ቆየኹ።

ይኼን ውጣ ውረድ እያሰብኩ በፊት ያለፉትን ቀናትና አዲስ መጪውንም ግዜ እየመረመርኹ እንዳለኹ፤ ይባስ ብሎ ዝግጅትና እቅድ ባለው ሁኔታ በአማራ ክልል በወሎ፣ በከሚሴ፣ በሽዋና በአጣዬ ሰላማዊ ዜጎችን በከባድና ቀላል መሣሪያ በመግደል፤ የእምነት ቦታዎችን በማቃጠል እጅግ አሳዛኝ፣ አስነዋሪና አስከፊ ጥቃት ተፈጸመ። እንደልማድዎ እርስዎ በአገር አልነበሩም። እንደሌሎች አገር መሪዎች ጉብኝትዎን አቋርጠው ይመጣሉ የሚል ሐሳብ ነበረኝ። ምን በወጣዎትና! በተረጋጋ ሁኔታ ጉቡኝትዎን ፈጽመው ተመለሱ። በዚህ ዐይነት ጉዳይ ላይ የእስራኤል መሪዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በአይሮፕላን ላይ እያሉ እንዲህ ያለ አደጋ ይቅርና አንድ ወታደር ወይም ሲቪል ላይ አደጋ እንደደረሰ ሲሰሙ ጉዞውን አቋርጠው፣ አቅጣጫ ለውጠው እንደሚመለሱ አውቃለኹ።

ይንንን ባያደርጉም እንኳን ከመጡ ወዲያ ጠንከር ያለ እርምጃ ወስደው የተጎዳውንም ቤተሰብ፣ ያዘነውንም ሕብረተሰብ እንባውን ያብሳሉ ስል፤ ከመግለጫ በቀር ዝምታን መረጡ። ሕዝብ እያለቀ ስለፍቅርና መግባባት፣ ስለአንድነትና መደመር ቢሰብኩ ሰሚ ያለ አይመስለኝም። በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረና የሰበከ የለም። ኾኖም ቤተ መቅደሱ በሌቦችና በእርግብ ሻጮች ተሞልቶ እንደደረሰ፤ “ቤቴን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” በማለት ጅራፉን ዘርግቶ እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ ቅጥር እንዳባረራቸው ተጽፏል። እርስዎም የወደደዎትና ያከበረዎትን ሕዝብ ከመከራና ስቃይ፣ ከሞትና መፈናቀል ሊታደጉት ይገባል። ይኽ ካልኾነ ግን “መርዶ አታድርጉብኝና …" እንዳሉት ማለት ባይገባዎትም የአጥቂ ኃይል ተጠናክሮ ሕዝብ ከዚህ የበለጠ ጉዳት እንደሚደርስበት የሚታየው ነገር የሚያመላክት ነው።

በአገራችን አንድ አባባል አለ፤ “ባለቤቱን ካልናቁ፣ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚል፤ እውነቴን ልንገርዎት በጥፋት ኃይሎች ተንቀዋል። መናቅ ብቻ አይደለም እኛንም አስንቀውናል። ፀሐፍት አንድ ሰው ወደ አንድ ከፍታ ሲወጣ ትክክለኛ ጠላቶችና ሐሰተኛ ወዳጆች ያፈራል ይላሉ፤ እርስዎም በያዙት ሥልጣን ላይ ሲወጡ ጠላት ማፍራትዎ አይቀሬ ነው። ጠላቶችዎ ግን ባለዎት የሕዝብ ድጋፍ ፍራቻ አድሮባቸው አድፍጠው ቁጭ ብለው ነበር። አጥፊ አመለካከት ያላቸውና ሁኔታውን እየመረመሩ የተቀመጡም ነበሩ፤ በርስዎ ቆራጥና ጠንካራ እምጃ አለመውሰድ እነዚህ ሁሉ ወደጠላትነት ለመቀየር ወይም ተቃዋሚ ለመኾን መንገዱ ምቹ እንዲኾንላቸው በር ከፍተውላቸዋል።

በዚህ ላይ ስንቶች እርስዎን አምነው ሁሉን እርግፍ አድርገው ከጎንዎት እንደቆሙም አይርሱ። እንደ እናትዎ ትንቢትም ሆነ እንደግዚአብሔር ፈቃድ ነግሠዋል። በአጭር ጊዜ እንደሠሩት ሥራና እንደ ተስፋ አብሪነትዎ፤ “ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ያንግስዎ!” የሚባሉ ነዎት፤ ሆኖም ግን ሕዝብ “ያድነኛል፣ ከጠላት የሚከላከልልኝ ንጉሥ አለኝ” የሚለዎት አልኾኑም። መሪ የሕዝብ ባለአደራ፣ መከታና ጋሻ፣ መብራትና መንገድ መሆኑን አያውቁም ለማለት አልደፍርም። እንደወደድንዎትና እንዳከበርንዎት ሁሉ፤ እርስዎም የሚመጣውን አደጋ ከኛ ጋር ሆነው ተከላከሉልን። ይኼ ሁሉ የሕዝብ ድጋፍ እያለዎት የርስዎ ቆራጥነት ከታከለበት እንኳን በየአውራ መንገዱና በየቤታችን ደማችን ሊፈስ ይቅርና፤ ማንም ቀና ብሎ ሊያየን አይችልምና ሕግ ያስከብሩልን።

ይኽ ጽሑፍ የኔ የአንድ ቀና አመለካከት ያለው ዜጋ መልእክት ቢሆንም፤ የኔን ሐሳብ የሚጋሩና ይኽን አመለካከት እንደራሳችው የሚሰማቸው ብዙዎች መሆናቸውን ተረድተው፤ በማስተዋል እንዲያዩልኝ እጠይቃለሁ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!