በኖርዌዩ የውይይት መድረክ ላይ እንዳትሳተፍ ኢህአዲግ ከሀገር እንዳትወጣ ከለከላት

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. June 9, 2009)፦ ከጁን አንድ እስከ ስድስት 2009 እ.ኤ.አ. በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በተደረገው ሦስተኛው ”ዓለም አቀፍ የሃሳብ ነፃነት የውይይት መድረክ” (Global Forum on Freedom of Expression) ላይ ልዩ ቦታ ተሰጥቷት ዋና ተናጋሪ በመሆን ተጋባዥ የነበረችው ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል፤ ከኢትዮጵያ እንዳትወጣ የኢህአዲግ መንግሥት ስለከለከላት በውይይት መድረኩ ላይ ለመገኘት አልቻለችም። በውይይቱ ላይ በጽሑፍ የላከችው ንግግር መልዕክት ለታዳሚዎቹ ተነብቧል።

 

ይህንኑ የጋዜጠኛ ሰርካለምን መልዕክት ያነበበችው ”ተዋንያን ለሰብዓዊ መብት” የተሰኘው ሲቪክ ድርጅት አባል የሆነችው ኖርዌያዊቷ ተዋናይ አሌክሳንድራ ጎርደን ነበረች። ጋዜጠኛ ሰርካለም በዚሁ መልዕክቷ ላይ በእስር ቤት ስለነበረው ሁኔታ በጥቂቱ ገልጻለች። በተለይም ወደ እስር ቤት ስትገባ ነፍሰጡር እንደነበረችና የመጀመሪያ ልጇንም በእስር ቤት እያለች መውለዷን በማውሳት፤ በወሊድ ወቅት የደረሰባትን ችግር፣ የነበረውን ቢሮክራሲ፣ መብት ማጣት፣ ... ለተሰብሳቢው አስረድታለች።

 

በእስር ቤት እያለች የደረሰባትን ስቃይ፣ እንግልትና ቶርቸር በማስታወስ፤ ይህንን የፈፀሙባትን ወገኖች እንዳላዘነችባቸውና ቂም እንዳልቋጠረችባቸው የገለፀችው ጋዜጠኛ ሰርካለም፤ ”... ይልቁንም ፈጣሪ ይቅር እንዲላቸው እፀልይላቸዋለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስም ’የሚሠሩትን አያውቁምና ...’ ይላልና ...” ብላለች።

 

ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የምኒልክ እና የሳተናው ጋዜጦች አሣታሚና ዋና አዘጋጅ የነበረችና ከምርጫ 97 ጋር በተያየዘ ለሁለት ዓመታት ከታሰሩት ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎችና፣ የሲቪክ ማኅበር አባላት ውስጥ አንዷ ነበረች። ባለቤቷ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም መታሰሩ አይዘነጋም። ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሰርካለም፣ እስክንድር እና ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እስከዛሬ ድረስ የፕሬስ ሥራ ፈቃድ ተከልክለው ጋዜጣ ማሣተም እንዳልቻሉ ይታወቃል።

 

ሙሉውን የጋዜጠኛ ሰርካለም መልዕክት ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!