ወደራሳችን እንመልከት (ከዳኛቸው ቢያድግልኝ)
የተማርነው ከእውቀት እንድንርቅ አምባገነንነትንም እንድናከብር ነው
ከዳኛቸው ቢያድግልኝ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጤና ይስጥልኝ ወገኖቼ! ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ጉዳይ ይቅርታን ማን ይጠይቅ ይቅርታስ ለምን? በሚል ርዕስ በኢትዮሚድያ (http://ethiomedia.com/accent/sorry.pdf) ላይ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር። ወደራሳችን መልከት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማማመን በጥልቅ ጉዳዩን አውቃለሁ እንደሚል ጠቢብ ሳይሆን እንደ ትውልድ ያገባኛል በሚል እምነት ለውይይት፣ ለትምህርት፣ መንደርደርያ እንዲሆን በማሰብ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥቂት ማለትን ስለመረጥኩ ነው።
ጽሁፉን አስመልክቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን አበረታታችና አስተማሪ የሆኑ አስተታየቶች ሰጥተውኛል በዚህ አጋጣሚ የኢትዮሚድያን አዘጋጅና አስተያየት የሰጡኝን ሁሉ አመሰግናለሁ። አሁንም ልድገመውና በፖለቲካ ሳይንስ፣ በታሪክ ምርምር፣ በፍልስፍና ጥናቶች ወይንም በሀይማኖት ጉዳይ የልምድ እውቀት እንጂ በትምህርት ቤት ውስጥ የተለየ ስልጠና የተሰጠኝ አይደለሁም። ለእኔ እንደሚታየኝ የቸገረን ነገር የድክመታችንን ምንጭ ለማወቅ ያለመቻል ወይም ያወቅን ይህንን ወደ አደባባይ ለማውጣት ያለመድፈራችን ሊሆን ይችላል። በጉዳዩ ተጠበብን የሚሉ ምሁራን መንገድ ማመላከት ላይ አይተጉም ወይንም ጆሮ አልሰጠናቸውም። የሕዝባቸውን የእውቀት አቅም መርምረው አቅሙ በሚችለው ጠቅልለው ማጉረስ ግን ድርሻቸው ነው። የማጠናከሩን ስራ ለመስራት በመጀመርያ መንገዱን (tools and methods) ማሳየትና መሰረታዊ የአቅም ግንባታ አስፈላጊነትን አምነው በዚህ አቅጣጫ ሊሰሩ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ወደራሳችን እንመለከት ዘንድ የማቀርባቸው ሀሳቦች የሚያደሉት ጠንካራው ላይ ሳይሆን ደካማ አድርጎናል ብዬ የማምንባቸው ጉዳዮች ላይ ነው።
ጀግና ነን፣ ኩሩ ነን፣ ከማንም በላይ ነን፣ አዋቂ ነን፣ ትዕግስተኛ ነን፣ ወ.ዘ.ተ. የሚሉን ብዙ አሉ። እኒህ አብዝተን ያልናቸው እርስ በእርስ የምንሞካሽባቸው ጉዳዮች ናቸው። ነገር ግን ይህን ሁሉ ከሆንን የአለም ጭራ እንድንሆን ለምን ፈቀድን? የሚል ጥያቄ ልናነሳም ይገባል። የመሪ ማጣት ልንል እንችል ይሆናል። በአለም አንደኛ የሆነ ሕዝብ በአለም አምሳኛ የሆነ መሪ እንኳ ለመውለድ ለምን አቃተው? የሚመራ ከሌለ መሪ የለምና ለዚህ የተመቸን ሰዎች ብንበዛ ይሆን የመከራ ዘመናችን የበዛው? ስለዚህ መሰረታዊ የሆኑ ችግሮቻችን ምንጮቻቸው ምንድን ናቸው? እንዴት የተሻለ መንገድ እንምረጥ በሚሉ ጉዳዮች ላይ መስራት አለብን ብዬ አምናለሁ። ይህን ያህል ከተንደረደርኩ ወደ ዋናው ጉዳይ ለመሮጥ ይቻለኛል። ከድረገጾች ላይ ርዕሶችን ቀነጫጭበን ለመሄድ ለምንቻኮል ይህ ጽሁፍ አለቅጥ ይበዛል። ለወደፊቱ በጣም አጠር ለማድረግ እንደምሞክር ቃል እየገባሁ ይህንን ግን ታገሱኝ እላለሁ። ጊዜ ለብዙዎቻችን ከወርቅም በላይ መሆንዋን አምናለሁና።
አዎ የተማርነው (Conditioning, Associative learning ከሚለው ጋር ይያያዝልኝ) ከእውቀት እንድንርቅ አምባገነንነትንም እንድናከብር ቢቻልም አምባገነን እንድንሆን ነው። አንዳንዶች ርዕሱን እንደተመለከታችሁ «ምን ይቀባጥራል?» ልትሉ ትችላላችሁ። ግድ የለም ቸኩለን መወሰን ብዙ ጣጣ አምጥቶብናልና ትንሽ ታገሱኝ። በስተመጨረሻ እኔ እንደዚህ አላስብም ነበር ትሉ ይሆናል። እኔን እንደዚህ ያሳሰበኝ ሰው በራሱ መንገድ ጽፎ ቢሆን እንዴት ደስ ባለኝ ነበር። ምነው የኔ ወንድም ይህን ለምን አትጽፍም ብለው። «እኔ ምርጥ ዘር አድላለሁ የጎበዘ ዘርቶ ያባዛው» አለኝ። የተማረ ሰው ነው 22 አመት ተምሮ በስሙ ላይ ቅጥል ገብቶለታል። ለሁለት ምሽቶች ብቻ ነበር ያገኘሁት ነገር ግን እንዳለውም የእውቀት ጫፍ አስጨብጦ ተለይቶኛል። ምስጋናዬ ለእርሱ ይሁን። እንዴት ሆኖ ነው ከእውቀት የራቅነው እንዴትስ ነው አምባ ገነን እንድናከብር የሆንነው? ምስጢር ያካፈለህ ሰው የድንቁርና ዶክተር ነው ወይ እንዳትሉኝ። በጭራሽ አይደለም። እንዲያውም ሰሞኑን ብዙ ሰዎች በድፍረት «...እኔ ዶክተር ብሎ ነገር አይገባኝም...» እያሉ ነው። «...የዶክተሮቹን ነገር ትዉት ከነርሱ ያልተማረው ተሽሏል...» እያሉ ነው።
ይህ ሊያመን፣ ሊኮሰኩሰንና ሊያኮሰምነን ይገባል። የተማሩ ሰዎች ሕዝባቸውን በደደብ መነጽር እያዪት ነው ወይስ ያልተማርነው ፍርደገምድል ሆነን? በትምህርት ቤት ውስጥ ገብተን ከተማርነው ይልቅ ከአካባቢያችን የቀሰምነው ነገር የህይወት መንገድ እየሆነን እንደመጣ ማወቅና ማመን ስለአቃተን ይሆን? የማኅበረሰባችን ድርና ማግ የሆነው ባህላችን ለዘመኑ የአስተሳሰብ ሸማ አልበጀን ብሎ ይሆን? በፊውዳሊዝም ሪትም የካፒታሊዝም ዳንስ ይዘን ይሆን የእግር አጣጣሉ ግራ ግብት ያለን? በኒህ ጉዳዮች ብዙ መጻፍ አለበት። ይህን በቅጡ ስንረዳ አስመሳይ ዶክተር፣ አሉባልተኛ ኢንጅነር፣ አጨብጫቢ ፕሮፌሰር፣ ቀበኛ ማስተር፣ ጉቦኛ ጠበቃ፣ እብሪተኛ ዳኛ ብናይ አይደንቀንም ማለት ነው። ከተማራት አሜባ በላይ ስለ አሜባዋ ተጠቂ ብዙም የማያውቅ ሀኪም፣ ከሚመረምረው አፈር ውጪ ስለገበሬው ህይወት ጥቂት የማያውቅ ተመራማሪ፣ ከሚያስተምረው ትምህርት ውጪ ስለተማሪው ብዙም የማያውቅ አስተማሪ ሊኖር ግድ እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ይቻለናል። ዶክተር ማለት ሁሉን አዋቂ ማለት አይደለም እኮ። በሰለጠነበት የሙያ ዘርፍ ላቅ የአለ እውቀት የአለው ማለት ነው። በኛው የትርጓሜ ስህተት የዶክትሬት ዲግሪን የውሀ መንገድ ካደረግን ጭርሱኑ ከትምህርት ጋር ጠብ እንጭርና ዶክተሮቻችንን የባዕድ ሲሳይ ማድረግ እንገደዳለን። ማውራት ፖለቲካ ሆኖ በስም ላይ የገባችው ቅጥል እንደማስታዋቂያ ሆና ለስልጣን ደፋ ቀና የሚለውን ደንባራውንም አስተዋዩንም እኩል እያየን መሄዳችን ይበልጥ አደጋ እንዳለው ልናውቅ ይገባል ባይ ነኝ። ወደዋናው ጉዳይ ካልተመለስኩ ደግ አይሆንም።
እንዲህ ልጀምረው፦ ለማወቅ የሚሹ ሁሉ ጥያቄ ይጠይቃሉ «...እሹ ታገኛላችሁ አንኳኩ ይከፈትላችኋል...» እንዳለው ጌታ በቃለ ወንጌሉ። ይቺን ይቺን አልረሳሁም። ሳንጠይቅ የምናውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ይህ የሚሆነው ግን ቀድመው ጠይቀው፣ መርምረው፣ አወዳድረውና አገናዝበው የተረዱ ሰዎች አለማወቃችንን አውቀው፣ ግር እንዳይለን አስበው፣ የመጠየቅ ልምድ እንደሌለን አውቀው ወይም ማወቅ አለማወቃችንን ጠይቀው እንዲህ ነው ስለአሉን ነው። ተመራማሪም «Hypothesis» ወይም «Research question» ይዞ ነው ወደ ጥናቱ የሚሸጋገረውና አዲስ ግኝት የሚያመጣው ወይም ያለን እውነታ የሚያረጋግጠው። የማናውቀውን ንገረና የምትሉ ከሆነ ለማወቅ ጓግታችኋል ማለት ነው። ይህን የምታነቡ ሰዎች በእጅጉ የታደላችሁ ካልሆናችሁ ከዚህ ቀጥሎ የምዘግበውን በራሳችሁ ሕይወት ተሞክሮ ይኖራችሁ ዘንድ እርግጥ ነው። የልጅነቱን ሲነግሩት በትዝታ የሁዋልዮሽ የማይሄድ ማን አለ? እስኪ ደረጃ በደረጃ ከልጅነት እስከ እውቀት ባሉት ዘመናት ከአለማወቃችንና ከፍርሀታችን ምንጮች መካከል እኔ የተረዳሁትን በጋራ እንመርምር።
ሕፃናት ሳለን ይህ ሆኖ አላለፈም?
እንደኛ ያለ አስቸጋሪ ተወልዶ አያውቅም። ጥያቄአችን ማለቂያ የለውም «…ማን፣ እንዴት፣ የት፣ ምን፣ በምን፣ ለምን…» እያልን «አዋቂዎችን» ስናጣድፍ «…ዝም አትልም፣ ዝም አትይም፣ አይቻልም አልኩሽ…» የምንባለው ትዝ አይላችሁም? ያኔ በእያንዳንዱ ቀን ጥያቄ የሚጠይቅ የሚያስቸግር እንደሆነ ነው የምንማረው። ዝም ያለ ጨዋ ነው በቃ! «አዋቂዎች» የምንላቸው ይህን አላውቅም ከሚሉ ይልቅ «…ነውር ነዋ! አልኩሻ ምን ትሆኝ? ነገርኩሃ በቃ!...» ይሉናል። ያልጠየቀ ካላወቀ መጠየቅ ማስቸገር ከሆነ ለማወቅ አልተፈቀደልንም ማለት ነው። ያኔ ሁሉን ነገር በግል መማር እንዳለብን አሜን ብለን መቀበል ግዳችን ነው። የሰው ልጅ ባህርይ እስከ ስድስት ዐመት ባለው ጊዜ ውስጥ ይቀረጻል ይሉናል ሳይኮሎጂስቶች። በዚህ ሁኔታ ካደግን እኛ ምን ያህል እውቀት አጥተን ይሆን? ቁልፍ የሆነውን የመጠየቅ መብት ከተነፈግን የእውቀት ኳሸኮር የብልህነት ሪኬትስ ቢይዘን ምን ይበዛበታል? ከዚህ በላይ ከአካባቢያችን ምን እንማራለን? ቢያንስ አስመሳይነትን።
ለምሳሌ ልጥቀስ። እኛን ከቁም ነገር ሳይቆጥሩ «አዋቂዎች» በሃሜት ሲዘነጣጠሉ እንሰማለን፣ በሃሜት እየተጠቀሰ ያለው ሰው ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ በመረዳት አምርረን እንጠላዋለን። እንደዚያ ሲጨፈጨፍ የነበረን ሰው እናታችን ወይም አባታችን እቅፍ አድርገው እንደናፈቀ ሰው ሲስሙና ለግብዣ ሲንደረደሩ ስንመለከት እንገረማለን። ትምክህተኛ ወንዶች ሴቶችን ሲያኮስሱ ስናይ ወንዶች ከሆንን ትዕቢትን ሴቶች ከሆን ደግሞ አንገት መድፋትን እንማራለን። እናም በትንሿ እግራችን ትልቅ እህታችንን በካልቾ እንመታለን። ወንድነታችንን ለማስረገጥ። ትንሽ የታደልን አሻንጉሊት ቢኖረን ከቤት እቃ የበለጠ እንድንከባከብ ይጠበቅብናል። መተኪያም ስለሌለው ይሆናል ነገር ግን ምርምር፣ ጥያቄ፣ መፍታትና መግጠም እና ለመሳሰሉ ነገሮች መማርያ ይሆን ዘንድ ነበር አሻንጉሊቱ። ቄስ ትምህርት ቤት የነበሩ «torture» ተደረግን ቢሉ ማን ይሞግታቸዋል? እንደ ቤተሰቡ አባል ልጆች በምን ጉዳይ ላይ ተወያይተው ሀሳባቸው ይደመጣል? በምንም። ምንም ስልጠና ያልተደረገለት ሕጻን የቅጣቱ መጠን ከቁጥር በላይ ነው። እናም ሲጠቃለል ቅጣት ማለት ማስተማር ማለት ነው ለወላጆች። ከላይ ያስቀመጥኩት ዝክር ግን በድፍረት ምትክ ፍርሀትን፣ ጠይቆ በማወቅ ምትክ ዝምታን፣ እውነትን በመጋፈጥ ምትክ ማስመሰልን አላስተማረንም ይሆን?
የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤትስ ይህን አይመስልም ነበር?
ነጻነት የሚጀመርበት የመጀመርያው ክፍል ነው ልበል ከቤተሰብ የምንለይበት። ገና ከመነሻው ትምህርት ቤት ያረፈደ ተማሪን የሚያርበደብዱ ዘበኞችን እንፈራለን። ዘግናኝ ድርጊታቸውን በኛ አቅም ልንቋቋም የማንችለው ስለሚሆን እያለቃቀስን እንሄዳለን። ለምን እንደረፈደብን የሚጠይቀን የለም። መከላከያ ወይም ብድር መክፈያችን ስድብ ከሆነ ያንን መለማመድ እንጀምራለን። ትልቅን የማቅለል «ሀ ሁ» ተጀመረ። «ዘቡሌ» ሰደባችሁ የምታውቁ ሳቅ አላላችሁም ይህን ስታነቡ? አስተማሪ በሆነ ባልሆነው ይደበድበን ዘንድ ይቻለዋል። ጥሩ የሚያስተምር፣ ፍቅር የሚያሳይ አስተማሪ ወተት ነው። የሚጋረፍ፣ ከባድ ፈተና የሚፈትን ይፈራል። ጭራሹኑ «የጥበብ መጀመርያው እግዚአብሄርን መፍራት ነው» ብለው ያስተምሩናል። እግዚአብሄርን ማፍቀር ነው፣ ማክበር ነው፣ ማምለክ ነው ቢሉን ፍርሀት ተገቢ ያለመሆኑን ባሰብን ነበር። እግዚአብሄርን መፍራት ነው፣ እናት አባትን መፍራት ነው፣ ታላላቆችን መፍራት ነው፣ አስተማሪዎችን መፍራት ነው። አልፈራም በሉና ሁሉም ጉልበቱን ያሳያችኋል። ያለ ጥፋታችሁ አልተቀጣችሁም? ማን ሰማችሁ? ማንስ አመናችሁ? አስተማሪውን እንደልቡ የጠየቀ አለ? ችግር ነዋ የተናገረ ለፍላፊ ነው፣ የጠየቀ ደደብ ነው፣ የመለሰ ልታይ ልታይ ባይ ነው አለቀ። ዝምታ ወርቅ ነው ሙያም በልብ ነው።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ አዲስ ከአሮጌ እንደሚሻል ልብ የማይሉት «አዋቂዎች» በዚህች ትንሽ እድሜአችሁ ስንት ጊዜ «የዛሬ ልጆች አረ... አረ... ጉድ ነው...» ብለውናል? ጥሩ ነገር ሁሉ የድሮው እንደሆነ ስንት ጊዜ ሰምተናል ማለት ነው? የድሮ ጊዜ ልጆች አፋቸው መብያ እንጂ መናገርያ አልነበረም። አንጎላቸው የነገር ጎተራ «Hard disk or storage device» እንጂ የሚያስብ የሚመረምር አልነበረም። እና እነርሱን አለመሆን ከሰይጣን መወገን ነው «የዛሬ ልጅ» ደግሞ ጠበል ቢግቱትም ያው ነው። ከአሮጌው እሻላለሁ ነው የሚለው። የሚያሳዝነው የኛ አያቶች ወላጆቻችንን እንደዚያ ብለው አሳደጉ እኛም ልጆቻችንን። አትካዱ ብዙዎቻችሁ የዛሬ ልጆች እያላችሁ በእጃችሁ አፋችሁን አልያዛችሁም? ወላጆች ባጠፉ መጠን እንደልጆች የሚገረፉ ቢሆን ኖሮ ያው ቻይና «synthetic» ነገር ሰርታ ካልሸጠችልን በቀር በአገር ላይ አርጩሜና የቆዳ ቀበቶ አይኖሩም ነበር። ልጆችም መልሰን መግረፍ ስለማንችል በማጭበርበር እንሰለጥናለን፣ በመዋሸትና በመስረቅ እንራቀቃለን። ስለዚህ ፍርሀቱ ላይ ሌብነት አጠናን ማለት ነው። እኛም ቀናችን ደርሶ በገረፍን የምንል እንበዛለን በልጅ አስተሳሰብ። ያኔ የአምባገነንነት ችግኝ በኛም ላይ አቆጠቆጠች ማለት ነው።
ሁለተኛ ደረጃ የዘለቃችሁ ይህን ታስታውሱ ይሆን?
ወንዶች ድምጻቸው አዲስ ቅኝት ያወጣል፣ ሴቶች ከወንዶች እንደሚለዩ በተክለ ሰውነታቸው በግልጽ ማሳየት ይጀምራሉ። ወንዶች ውብትን ማድነቅ ሴቶችም አድናቆትን በጸጋ መቀበል ይጀምራሉ። አስተማሪዎች በፈተናዎቻቸው ክብደት ይመዘናሉ። አደገኛነታቸው በቦንብ ይተረጎማል። የእርሱ/ሷ ፈተና ቦንብ ነው ይባላል። አንዳንዶች ደግሞ በእጅ መንሻ ይታወቃሉ። ውበት ፈተና እንደሚያሳልፍ መማር እንጀምራለን። በልጅነታቸው ሀይለኝነት እንደሚያስከብር የነቁ ወንዶች ደግሞ ማስፈራራት ይጀምራሉ እናም በጉልበታቸው ፈተና ማለፍ እንደሚችሉ ይማራሉ። በጉልበታቸው ፍቅር መግዛት እንዲሚችሉ ይማራሉ እንደ አራዊቱ ማለት ነው። ማኅበራዊ ንቃተ ኅሊና ሲያንስ፣ እውቀት ባብዮሎጂና ኬሚስትሪ ብቻ ሲታቀብ አብረን ውይይት «Reason» ማድረግ አንችልም። የተትረፈረፈ የወጣት ጉልበት አለንና ንግግራችን በጡንቻ ይሆናል። ጡንቻ የሌለን ከራሳችን የከበደ ድንጋይ ይዘን በስድብና በፉከራ ማርበድበድ እንይዛለን። የሽለላ «ሀ ሁ» ደግሞ ጀመርን ማለት ነው። ደጋግ፣ የዋህ፣ ሰው አክባሪና ቅን አሳቢ አስተማሪዎችም ይሁኑ ተማሪዎች ፈሪ፣ ሞኝ፣ ጅል ወይም ምስኪን ተብለው ይፈረጃሉ።
የኒህን መምህራን ትምህርታቸውን ተግቶ የሚያጠና አይበዛም። ቅን ወይም ደግ ተማሪዎችን የሚንቅ እንጂ የሚያደንቅ ጥቂት ነው። መቀለጃዎችም ናቸው። መፍራት እንጂ ማክበር አልተማርንምና የማይፈራውን ለምን እንፍራ? ይህ ሁሉ ሲሆን ወጣቶች ራሳቸውን የሚመዝኑብት፣ ዝንባሌአቸውን የሚገመግሙበት፣ አዲስ ነገሮችን (ከቀለም ትምህርት ውጪ) የሚማሩበት መድረክ የለም። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት (ክርክር) እንዲያደርጉ አይበረታቱም። በስፖርት እንዲታነጹ፣ በስነጽሁፍ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር (ድራማ)፣ በስእል እና በመሳሰሉት ዝንባሌ እንዲኖራቸው አይደረጉም። ስለዚህ አቅምና ተሰጥኦአቸውን በውል አያውቁም፣ ሰብዕናቸው የተሟላ እንዲሆን ትምህርት ቤቶች እድል አይሰጡም ማለት ነው። እንደ አካባቢአቸው ሁሉንም መሞካከራቸው ግን ግድ ነው። ሁሉንም ነገር ግን በድብቅ ሲለሚያደርጉት ወላጆች ወይም አስተማሪዎች ስለ ልጆች ወይም ተማሪዎች የሚያውቁት የሚጠረጥሩትን ብቻ ነው። ገና በእንጭጩ ማስመሰልን ስለተማሩ በወሮበላነት ሊታወቁ የሚገባቸው የጨዋ ተምሳሌት ሆነው ዘመድ ጎረቤት እደጉ ለወግ ለማእረግ ያብቃችሁ ይሏቸዋል። ማስመሰል ብል ነገሮች ትዝ አሉኝ እንዲያው ከመካከላችሁ «Y» ስለተሰነጠቀች ማሰርያ አዋጡ ተብለናል ያላችሁ የላችሁም ሳይማሩ ያስተማሯችሁን? ሙዚየም ሄዳችሁ ካላጠናችሁ ፈተና ይከብዳችኋል ተብለናል ብላችሁ ሲኒማ የገባችሁ የላችሁም እንዴ? የኪስ ገንዘብ የለማ አይፈረድባችሁም። ስለዚህ ቦንብ ፈተና የሚያወጣ አስተማሪ ይፈራል። ትምህርት ቤት የሽንኩርት ቢላም ቢሆን ይዞ የመጣ ይፈራል። አባቱ ጦር ሰራዊት ወይም ባለስልጣን የሆኑ ይፈራል። ታላቅ ወንድም ያለው ወይም ያላት ትፈራለች። የዋሸ፣ የሰረቀና ፌዘኛ የሆነ አራዳ ነው። ክፍል የተማራችሁት ሳይንስ እስከፈተና ድረስ በግቢ ውስጥ በመዋላችሁ የቀሰማችሁት የኑሮ ዘይቤ ደግሞ እስከ መጨረሻው ተከትሎአችሁ ይሄዳሉ። አማርኛችሁን ረቀቅ ለማድረግ ይህንን አልተማራችሁም? ዝምታ ወርቅ ነው፣ ዝም በአለ አፍ ዝንብ አይገባበትም፣ በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ፣ ከአፍ የወጣ አፋፍ እኒህ ተረትና ምሳሌዎች አፋችሁን አይለጉሙም? ፈሪ አያደርጋችሁም? ሀሳባችሁን መግለጽ በመፈለጋችሁ ብትሞቱ «በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ» የሚሉ አይመስላችሁም ቀብራችሁ ላይ? በሌሎቹ ቋንቋዎቻችን ከዚህ ጋር አምሳያ ያላቸው ተረትና ምሳሌዎች አውቄ ቢሆን እንዴት ደስ ባለኝ። የምታውቁ አሳውቁኝ። ገና አንላቀቅም እኮ በግማሽ ቀን ትምህርት ያልሆነላችሁ እንደኔ ትምህርት ጨርሻለው ትላላችሁ። እነ ቀለሜዋዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ። የምሁራን ጎራስ ምን ይመስል ይሆን?
ዩኒቨርሲቲ የፍርሀት ቤተ መቅደስ ነው ይላሉ እውነት ይሆን?
እንደ ፈንግል አንድ ምሽት ጠራርጎ የሚያስወጣው ፈተና እስኪመጣ ሁሉም ፈሪ ነው። መምህራኑ ጎራዴና ሰይፍ የያዙ እስኪመስሉ ድረስ ያስፈራሉ። የጥበቃ ሰራተኞች የተማሪውን ደህንነት ከሚጠብቁ ይልቅ ከተማሪ የተጣሉ ይመስላሉ እናም ያስፈራሉ። ፍሬሽ ፍሬሽ እያሉ የሚያንጓጥጡ ይበዛሉ። በምግብና መኖ መካከል ያለ ነገር በሰልፍ ትበላላችሁ። ፍሬሽ መሆን ያስፈራል፣ ትምህርቱ ያስፈራል፤ የምግብ ሰልፉ ያስፈራል፣ የመጻህፍት እጥረቱ ያስፈራል እስቲ የማያስፈራና የሚያበረታታ ልብን የሚያሞቅና ደስ የሚል ነገር ንገሩኝ። ሰቀቀን ነው ሰቆቃ ነው። ክሪስማስን በናንተ ብርታት በፈጣሪም እገዛ እለፉት። ፕሮፌሰር እገሌ ለሁልሽም «F» ሽን አስታቅፍሻለሁ ብለው ይዝታሉ። ያለፉ ተማሪዎችም የሚነግሯችሁ ይህንኑ ነው። ሌላው ፕሮፌሰር ደግሞ «A» ን ለእግዚአብሄር «B» ን ለኔ ሲሆን ለናንተ ከዚያ የተረፈውን ነው ይላሉ። ሽብር ሲነዙ። እንዲህ አይነት አስተማሪዎች ጠመንጃ ቢሰጧቸው አሰልፈው ይረሽናሉ። እውነቴን እኮ ነው ሽብር ፈጣሪ አስተማሪዎች ያርበተብታሉ። ያኔ ፍርሀት በደም ስራችሁ ይሄዳል።
አራተኛ አመት ያሉ ለሶስተኛ አመት ተማሪዎች ፕሮፌሰር እገሌ እኮ ፈተናው አይቻልም። ይረፈርፈዋል ይላሉ አሁን ድረስ ሰውየው ባለፈበት ማለፍ እየፈሩ። ስንት ተማሪ እኮ ተባረረ በእርሱ ምክንያት ይላሉ እነርሱም በሶስተኛ አመት ተማሪዎች ላይ ሽብር ሲነዙ። እዚህ ላይ ነው ያ የእውቀት ዘር አስጨብጦኝ ጠፋ ያልኳችሁ ሰው ትዝ የሚለኝ። ኣንድ ፕሮፌሰር ተማሪውን ሁሉ ከረፈረፈ፣ በዚሀም ምክንያት ከተፈራ፣ እርሱም ይህን አውቆ ሰዉን ሁሉ ቁልቁል ከተመለከተ፣ እናም ሀይ የሚል ከጠፋ የዞረብን ነገር አለ ማለት ነው ነበር ያለን። በምሳሌ ይህንኑ ሲነግረን «... እስቲ አስቡት ፕሮፌሰሩን በገበሬ መስሉትና አያ ሞገሴ እንዴት ያለ ጎበዝ ገበሬ መሰላችሁ እንዲያው የበቆሎ ማሳውን ለመኮትኮት ከወጣ አረም የለ በቆሎ የለ ነቅሎ ነቅሎ ማሳውን አዲስ እርሻ እኮ ነው የሚያስመስለው ....» ማለት እኮ ነው አለን። ሁላችንም መተያየታችንና በትንግርት ይህ ሰው የሚለውን ያውቃል ማለታችን እውነት ነው። እንዲህ ነው እንግዲህ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው እዚህ የደረሱ ተማሪዎች የተሰጣቸው ትምህርት በደረሱበት ደረጃ የሚመጥናቸው ከሆነ፣ መምህሩ በሚገባ ካስተማረ፣ ተማሪዎች መረዳታቸውን ከጠየቀና ያስተማራቸውን ከፈተነ መረፍረፉን ምን አመጣው? እንዲያስ ቢሆን ልፋቱ ከንቱ ሆኖ ተማሪዎቹ በርሱ ትምህርት ሲወድቁ ተንሰቅስቆ ማልቀስ እንጂ ኩራቱና ትምክህቱ ምንኛ ነው? ነገር ግን ፕሮፌሰሩም ተማሪዎቹም ፍርሀትና ጀብድ ተለማምደው ስሊሚመጡ ተማሪዎቹ መውደቃቸውን በፀጋ ይቀበላሉ። መምህሩም እንደ ገዳይ ያቅራራሉ ገዳይ የሚፈራበት ሀገር ስለኖሩ። ፍርሀታችሁ መቼም ቢሆን አይለቃችሁም።
ኖት የሚያወጣበትን መጽሀፍ ለተማሪው የማይናገር አስተማሪ መቀደምን ይፈራል። ተማሪው እንዳይበልጠውም ይሰጋል። ይህ የተሳከረ አመለካከት ይመስለኛል። ተማሪዎች ከአስተማሪዎቻቸው እንዲበልጡ፣ አዳዲስ እውቀት እየጨመሩ ያለውን እንዲያጎለብቱ እንጂ የፈቀዱለትን ብቻ እንዲግጥ ጉልበቱ ላይ ታጥፎ እንደታሰረ አህያ ከተደረጉ ምኑን የእውቀት ቁልፍ ጨበጡ? እንዴትስ ከድሮው የተሻለ ነገር ይፍጠሩ? የመምህር ደስታ ተማሪዎቹ እርሱ ያስጨበጣቸውን እውቀት ይዘው እንዲበልጡት ማድረግ አይደለም ወይ? ከራሱ እንዲበልጡ፣ የተሻሉ እንዲሆኑ የማይጥር አስተማሪ ምኑን ተስፋ ዘራ? ይህን እዚህ ላይ ላብቃ ሌሎች የሚጨምሩት ይኖራልና። እኔም አስራሁለት ክፍል የቆጠርኩት አናንተም አስራ ስድስት የቆጠራችሁቱ ስራ መግባታችን አይቀርም ማስትሬት ዶክትሬት ካላላችሁ በቀር። እስቲ ያንን ደግሞ እንመልከት። ይህን ስመለከት እውነትም እኮ ሁላችንም ዞሮብናል እላለሁ።
በሥራ አለምስ ይህ ልምድ የለንም?
እድሜ እያሻቀበ ይሄዳል ሀላፊነትም እንዲሁ። ሥራ እንደልብ የለምና አንዴ ከተገኘ እያማጡም ይሁን እየተናጡ ቆንጥጠው የሚይዙት ነው። ስለዚህ አለቃ ሁሉም ነገር ነው። የሚያሳዝነው ርህራሄ የአለው፣ ለሰራተኞች መብት የሚተጋ በስራ ውጤት የሚያምን፣ ለስራ ክብር የአለው መሪ ያን ያህል አይከበርም። አምስት ደቂቃ ያረፈደን የሚገላምጡ፣ በሆነው ባልሆነው የሚደነፉ ከሰራተኛው መሀል ጆሮ ጠቢዎቻቸውን አሰልፈው እገሌ ምን አለ የሚሉ ይፈራሉ። አለቆቻቸውም ቢጤዎቻቸው ስለሆኑ መውጫ ቀዳዳ የለምና ለመኖር መፍራት የግድ ይሆናል። እንዲያው ሰራተኞቻቸውን የሚያርበደብዱ አለቆች ሚኒስትሩ ይመጣሉ ሲባል አጥሩን ድንጋዩን ኖራ ሲያስቀቡ አታስታውሱም? ራሳቸው ኖራ ተቀብተው ቢሰለፉ ቅር የማይላቸው ፈሪ አለቆች ፈርተው አላስፈራሯችሁም። ልጆችሽን/ህን ጦም እንዳታሳድር የሚል የነገር ጡጫ አላወላገዳችሁም? ነገራችሁ የፖለቲካ ትርጉም ተሰጥቶት በባለጊዜዎች ቆንጠጥ አልተደረጋችሁም? እናንተስ ብትሆኑ በአለቃነት ምን ሰርታችሁ ነበር? በመስሪያ ቤት የአዛዥነት እድል ያላገኛችሁ የቤት ሰራተኛ ለመቅጠር የታደላችሁ ወንዶችም ሁኑ ሴቶች እንዴት ነው ከሰራተኞቻችሁ ጋር የምትነጋገሩት? ስንት ሰአት ነው የቤት ሰራተኛ የሚሰራው? ምን የስራ ክፍፍልስ አለ? ይህንኑ አይነት ትዕዛዛችሁን መልሶ የሚያዛችሁ የመስሪያ ቤት አለቃን ልትጠሉ እንዴት ይቻላችኋል? ከልጅነት እስከ እውቀት የተመላለሳችሁበት ሕይወት እንዲህ ቢያደርጋችሁ ሊፈረድባችሁ ይቻል ይሆን? ማን አስተማራችሁና።
የሚያሳዝነው እጅግ ከፍ ያለ የትምህርት ደረጃ አለን የሚሉ ሰዎች ይህን እውነት ማየት ያለመቻላቸውና የተሰጣቸው ትምህርት ከዚህ ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለውና ከሰለጠኑበት ትምህርት ውጭ ህይወትን የሚመሩበት መንገድ ያልተቸራቸው መሆኑ ነው። በፊዚክስ ህግ እንኳን «ለምናደርገው ነገር ሁሉ እኩልና ተቃራኒ ድርጊት ይኖራል አይደል የሚባለው? « For each and every action there is equal and opposite reaction» የሚለውን የኒውተን ህግ በእለት ተእለት ህይወትም ያው መሆኑን ማየት የተቸገርን ይመስላል ለማለት ነው። ለዚህም ነው አለቆች ብዙ ጊዜ ተዋርደው እንጂ ተመስግነው ከስልጣን የማይነሱት። ያዋረዱት ሊያዋርዳቸው ግድ እየሆነ ማለት ነው በመልስ ምቱ። የዚያኑ ያህል መልካም ሰዎችን አዋርደው ያወረዱ ከራሱም የተጣላ አምባ ገነን ተሰይሞባቸው ሲላቀሱ ይኖራሉ የዘሩትን ሲያጭዱ። እውቀት በመማር ይገኛል፣ በመወያየት ይጎለብታል። ስህተት ሲነገረን ወይም እኛ ሌሎችን መሳሳታቸውን ስንናገር ሁለቱ ግንኙነቶች ምን ይመስላሉ? እውቀትን በፀጋ የምንቀበል ስንቶቻችን ነን? ከዚያም በላይ በቀጥታስ የምንናገር ስንቶቻችን ነን? በከንቱ ይፈረድብናል እንጂ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ትምህርቶች እንደ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ የቤተሰብ አያያዝ፣ የገንዘብ አያያዝ፣ የማፍቀር ጥበብ፣ የይቅርታና የመማማር ጥበብ እና የመሳሰሉት በትምህርት መልክ አይሰጡም። ስለዚህ ዶክተሩም የጽዳት ሰራተኛውም ስለ ደሞዝ አጠቃቀም የሚያውቁት በልምድ ያዩትን ነው። ዶክተሩም አናጺውም በቤተሰብ አያያዝ በኩል እምብዛም ያልተራራቀ ነገር ቢያደርጉ አይፈረድባቸውም ሁለቱም በልምድ እንጂ በትምህርት በዚህ ጉዳይ ላይ እኩል ናቸውና። ብዙዎቻችንን አካባቢያችንና ቤተሰባችን እንደ ስለት ሊሞርደን ወይም ሊያዶለዱመን ይቻለዋል ማለት ነው። እንዲህም እንደተኖረ ወደ ጡረታው አለም እንዘልቃለን።
በጡረታ ዘመናችንም ይህን እንጠብቃለን
ከእውቀት እንደሸሸን፣ ትሁትና ዝምተኛ እንደሆንን፣ ገዳያችንንም አዳኛችንንም በእኩል አይን አይተን እድሜአችንን ካረዘምን ተከብረን ጡረታ ልንወጣ እንችላለን። ጨዋ፣ ምስኪን፣ ትሁት፣ የዋህ፣ የእግዜር ሰው የሚል ቅጥል ከያቅጣጫው ሊሰጠንም ይችላል። ምክንያቱም የልባችንን ተናግረን አናውቅም፣ ሲበድሉንም እሺ ሲረግጡንም እሺ ካልን ማን ሊጠላን ይችላል? እንዲሁ ራሳችን ከኖርነው ያልኖርነው ካልቆጨን በቀር። በጊዜያችን ፈሪ ወይም ፍርሃታችንን ለማስፈራራት አምባገነን ከነበረን ከፈጣሪያችን ለመታረቅ ወደ ቤተክርስቲያን ማዘውተር ግድ ነው። የመስጊዱን አላውቅምና የምለው የለኝም።
በጡረታ ዘመናችን ደግሞ አዳዲስ ፍርሀቶችን መለማመድ እንጀምራለን። ትንሽ ጥሪት ሰርተንም ይሁን አምታታን ከያዝን ያቺኑ ሊቀበሉን ሀብታም ገነት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላታል ይሉናል የወርቅ መስቀል የሚይዙት ሳይቀሩ።እናም እንፈራለን። «መርሴዲስና ሐመር» የሚነዱ ፓስተሮች ገነት ከሚገቡ ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ ይቀላታል ብሎ አንድ ወዳጄ አነጋገሩን ያሻሻለው ያለምክንያት አልመሰለኝም። በድርቅ ለተጎዳች ግመል የመርፌ ቀዳዳ መች ይጠባትና። ፈሪ ስለሆንን እውቀትም ስለሚያንሰን በስተእርጅናና እንኳን መጠየቅ አይሆንልንም። ጦርነቱ ቁጣ ነው ይሉናል፣ የመሬት መንቀጥቀጡ፣ ጎርፉ፣ ድርቁ ሁሉ የመጥፊያችን ምልክት ነው ይሉናል። እኛ ፈርተን ያለንን እንቸራለን። እነርሱ ድሀን ቁልቁል የሚመለከት ትላልቅ ሕንጻ ያቆማሉ። ያለአጥቢያው የሞተ ክርስቲያን መቀበርያ እንኳ የለውም። እንደ ከተማው ቦታ የቀብር ቦታዋም የሊዝ ዋጋ ክፉኛ ንራለች። ለዚያውም መቼ ፈነቃቅለው አጥንታችሁ ላይ ሙዚቃ ቤት እንደሚከፍቱ አይታወቅም። የቄስ ኮንትራክተሮች ሀውልት ሲያቆሙ የጎደላቸውን ከአሮጌ ሀውልት የሚዋሱ ይመስል የጎረቤታችሁ ሀውልት ወላልቆ ነው የምታዩት። በሙታችሁ የገባችሁትን ውል እንኳ አያስከብሩላችሁምና እንደፈራችሁ ወደሚፈርሰው ሀውልታችሁ ታመራላችሁ። የመርፌ ቀዳዳዋ ነገር ድሀ ሽቅብ እንዳያይ እንጂ ሀብታም እንዲፈራ አይመስለኝም። ይልቁንም ሀብታም ሲሞት ነው አንደኛ ማዕረግ ፍትሀት የሚደረግለት። ጸሎቱም መማጠኑም እንደ ገንዘቡ መጠን ይበዛል።
እግዜር ይህን ያህል ሞኝ ቢሆን ሰውን ባልፈጠረ እላለሁ አንዳንድ ነገሮች ግር ሲሉኝ። ግን ስለምንፈራ አንጠይቅም። በድሀ ጎጆ መካከል ተቆልለው ቁልቁል የሚመለከቱ ጉልላቶች ሀጢአተኛነታችንን ያስመለክቱናል። በእኒህ ስፍራዎች ቀሳውስቱ የተራበ ሲያበሉ፣ ትምህርት ቤት ከፍተው ሲያስተምሩ፣ ለመዕመናኑ ደህንነት የሀይማኖት መሪ ድርሻ ሲወጡ አናይም። ሀጢአታችንን አገዝፈው ሲሰብኩ እንጂ ብርታታችንን ተመርኩዘው ሲያበረታቱን አይደመጡም። አሁን ተቀይሮ ይሆናል በአጥር ጥግ አልፍ እንደሆን እንጂ ገባ ብዬ ፍርሀቴ ላይ ተስፋ መቁረጥን ልጨምር ፈቅጄ አላውቅም። ቀሳውስቱ እርስ በርስ ሲናከሱ፣ ሲካሰሱ ስሰማ ፈተናው በክርስቲያን ይበዛል ሲሉኝ ፍርሀቴ ያይላል። ነገር ግን እነርሱም እኛን ሆነው ካደጉ እንደኛው ከኖሩ እንደምንስ ልንፈርዳባቸው ይቻለናል? ችግሩ ሁሉም ሰፈር ነው ያለው ለማለት እንጂ ማንንም ለማኮሰስና ለማጣጣል አይደለም። መጠየቅና መማር ሳይሆን መፍራትና መኖር ነውና የተለማመድን እንዲሁ ቆይተን የመልቀቂያ ጊዜ ሲመጣ ከእውቀት እንደራቅን እንደፈራን እንሰናበታለን። እኛ ስንወለድ አለቀስን ሌሎች ስንሞት ያለቅሱልናል። ብድር በምድር ይሏል እንዲህ ነው በኒውተንኛ። ነገር አላብዛና ከታች በማሰፍረው ሀሳብ የድርሻዬን ላጠቃለው።
ማጠቃለያ
እንግዲህ በጥቂት ዘገባ ብዙ ጓዝ የአለውን ሕይወታችንን መፈተሽ አይቻልም። የኔም ከእውቀት አይጣፍም እንደ ትዝብት እንጂ። የችግሮቻችን ምንጮች ምን እንደሆኑ መመርመርና ማግኘት ከቻልን መፍትሄውን እናውቅ ዘንድ ግድ ነው። ብዙ ዘመናት እንኳ ሊፈጅ ቢችል የኛ ትውልድ ፈር ቅድዶ መጪው ትውልድ ተለማምዶት ከዚያ የሚቀጥሉት እንኳ በተስተካከለ መንገድ ቢጓዙ ታላቅ ነገር ነው። እኔ እንደምረዳው ፍርሀትና አምባገነንነት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ። እውቀት የሌለው ሊፈራ ግዱ ነው። እውቀት የምለው ባንዲት መስክ የሚደረግን ስልጠና ቀንጭቤ ሳይሆን የመኖርን፣ ያብሮነትን፣ የመደጋገፍን፣ የመቻቻልን በጠቅላላው የሰብዓዊነት ቁልፍ መያዝን ነው።
አምባገነን ማለት እኮ አላዋቂና ቀንደኛ ፈሪ ማለት ነው። የተቃረነውን ሕይወት የሚቀጥፈው ሌላ ቀን ሊያሸንፈኝ ይችላል ብሎ ስለሚፈራ ነው። የተቃረነውን ለማጥፋት ወደሁዋላ የማይለው ባለው እውቀት ሞግቶ ወደራሱ ስለማያመጣው ነው። አምባገነን እውቀትን አጥብቆ ይፈራል ስለሆነም አዋቂዎችን አጠገቡ ለረጅም ጊዜ አያቆይም። ተጠቅሞባቸው ቶሎ ያጠፋቸዋል። ከቆዩ ስለሚዳፈሩት ንቀትም ስለሚጀምሩ ለዚህ እድል አይሰጥም። ይማሩም አይማሩም እጅግ ፈሪ ሆነው እንኳን እርሱን ፎቶውን ሲያዩ መደንገጥ የሚጀምሩትን ይወዳል። እንዳሻው ሲሰድባቸው የሽልማት ያህል አንገት የሚደፉትን ይሾማል። በፍርሀት ስለሚበልጣቸው ወደ ስልጣኑ አይመጡም ብሎም ያስባል። ከእውቀት ስለሚርቅ፣ በፈሪዎች ስለሚታጀብና ቀና ያሉትን ሁሉ ስለሚቀጥፍ አምባገነን አብዛኛውን ጊዜ ራሱን ጠልፎ ይጥላል። ለዚህ ነው ሰው ሁሉ እኩል ነው የሚሉ ኮሚኒስቶችን እንዲሁም አገር ወዳዶችን ጠራርጎ እርሱን የሚያመልኩ ግብዞችን በዙርያው ሰብስቦ ሲጃጃል ቆራጡ መሪያችን ሀገርን ለእንዲህ ያሉ ባይታወሮች ያስረከበው።
የድሮ ሚኒስትሮችን በራድዮ ጠርቶ የረሸነ ተጠርቶ ወደ ከርቸሌ ሲወርድ ለርሱ የተሻለ ፍትህ የሚጠብቅ ሁዋላ ምን ማሰብያ ቢኖረው ነው? ለዚህም ነው አምባገነን ሲወድቅ ተተኪው የባሰው የሚሆነው። ምክንያቱም የሚያስቡ አእምሮዎች ወይ ሞተዋል፣ ወይም እጅግ ርቀዋል አለያም ለቀጣዩ ሲሳይ ላለመሆን ተደብቀዋል። ይህን አላየንም በራሳችን ህይወት? ቢመቸን አምባገነን እንድንሆን ነው ያልኩትን በምሳሌ ልጥቀስ። የቀበሌ ዘበኛ፣ የቀበሌ ሊቀመንበር፣ የጸታ አስከባሪ፣ የወጣት ማኅበራት መሪዎች፣ የመስሪያ ቤት የጥበቃ ሰራተኞች ትናንሽ አምባገነኖች አልነበሩም? አሁንስ የወያኔ ካድሬዎች እንደዚያው አይደሉም? አገልግሎት ለመስጠት በየቢሮው የተቀመጡ ሰዎች ባለጉዳዮችን እንዴት ነው የሚያሽቆጠቁጡት? የሚሰሩት ግልጋሎት ደመወዝ እንደሚያስከፍላቸው ሳይሆን እነርሱ ለሌሎች ውለታ የሚያደርጉ ያህል እንዲለመኑ ሲሹ አናይም? ስለዚህ መሰረታዊ ችግር አለብን ማለት ነው። አሁንም የዘመመው የወያኔ ስልጣን ሊገረሰስ ግድ ነው በምን መተካት አለበት የሚለውን ልብ ካላልን፣ ያገባናል ብለን በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ወደ አንድነት ካልመጣን ከመለስ የባሰ ሊመጣ ወይም ጭርሱኑ ኢትዮጵያችን ላትኖርም ትችላለች። ስለዚህ ከመሰረቱ የጠፋ ነገር የለም ትላላችሁ? አስተዳደጋችን፣ ትምህርታችን፣ ባህላችን፣ ወጋችን ሊፈተሽና ሊሻሻል አይገባውም? የድሮው ከዘንድሮው ከተሻለ የሁዋልዮሽ እየሮጥን ነው ማለት ነው እና ለነገ ምን ተስፋ ሊኖረን ነው? ለዚህ ነው በዶክተርና ማንበብና መጻፍን መማር ባልታደለው መካከል በቄስና በወታደሩ መካከል ሰብዓዊነትን አስመልክቶ ልዩነት የሌለው።
እንዲህ ከተነጣጠልንማ እንደ ሕዝብ አንድ የሚያደርገን እኮ ነገር የለም። አስተዋይነት፣ ታታሪነት፣ ታማኝነት፣ አዛኝነት፣ ኩሩነት፣ ወ.ዘ.ተ. ለተማረውና ላልተማረው እኩል በመታደሉ እኮ ነው እንደ አገር ልጆች የሚያስተቃቅፈን። ጉድለት ካለ ለሁላችንም እኩል ጎድሎብናል። የተማረው የማገናዘብ፣ የማወዳደር፣ አቅም አለውና ፈጥኖ ችግሮቹን ሊያውቅ መፍትሄውንም ሊሻ መትጋት ሲኖርበት ከተርመጠመጠ ነው ችግሩ የሚበዛው። አለማወቁን ከሚናገር የሚያውቃትን እየተነተነ ሌሎችን ቁልቁል የሚያይ ያልታጠቀ አምባገነን ሲሆን ነው ሌሎች የጎሪጥ የሚያዩት። ስለዚህ እንደ ሀገር ልጅነታችን የጋራ ችግር የለብንም ትላላችሁ? ብዙ ጥያቄ አበዛሁ አይደል? በልጅነት የተከለከልኩትን ዛሬ ልወጣውና የምችለውን ያህል ልወቅ ብዬ ነው። ምናልባት ጥቂት ሰዎች እንደዚህ አናስብም ነበር፣ ለካስ መሰረታዊ ችግር አለብን ካሉ ሀሳቤን የሚጋሩ አሉ ማለት ነው። መማር ከሌሎች ተነጥሎ ገዝፎ መታየት እየመሰለን ከሕዝባችን የራቅን እንደሆን፣ እንድንከበር፣ እንዲሰገድልን የፈለግን እንደሆን ጭሰኛውን ቁልቁል ከሚያይ ፊውዳል የምንሻለው የፈረንጅ አፍ በማወቃችን ብቻ ሊሆን ይችላልና አውቀናል የምንል አኪያሄዳችንን እንመርምር። ከእውቀት ርቀናል አምባገነንም እንድንሆን ወይም እንድንፈራ ተደርገናል የምንል ካለን መውጫ መንገዱ ሰብዓዊነትን መማር፣ ፍቅር፣ መቻቻልና፣ መከባበር፣ ከሁላችን ጋር ይሆኑ ዘንድ የጨዋታውን ሕግ መማር ማስተማር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው።
አሁን በአለንበት ሁኔታ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራችን በላይ ገዝፎ የሚታየኝ እኛነታችንን ማወቅ መቻል ላይ ነውና ከራሳችን ታርቀን፣ ከወገናችን ተቃቅፈን ከሞት አፋፍ ላይ ያለችውን ውድ ሀገራችንን ከፍ እናድርጋት። የአምባገንኖች መፈንጭያ፣ የከሀዲዎች መቦረቂያ፣ የአስመሳዮች መጠለያ ሆና ልጆችዋ በስደት፣ በእስር ቤት፣ በስራ ፈትነት፣ በረሀብና ጥማት፣ እንዳይንከራተቱና ልጆቻችንም በእኛ ተስፋ እንዳይቆርጡ የትውልድ ድርሻችንን እንወጣ። ኢትዮጵያችን የሰላምና የነጻነት መናኸርያ ትሆንልን ዘንድ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ ያኔ ወደ መንገዱ መጥተናልና እግዚአብሄርም ይረዳናል።
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
መስከረም 2001