ዳኛቸው ቢያድግልኝ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ ሳይሆን ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ወንጀል ነው። ፍቅር አያስከብርምና ይኸው ዛሬን ደግሞ ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ ይቅር መባባልን አሳስረን የእስር ቤታችንን አጥር እያጠባበቅን ነው። የፈራን ፈርተን ዳግም ቀና እንዳንል ስንረገጥ ታፋችንን በፈረቃ ለመስጠት ፈቃዳቸውን እየጠበቅን ’የባሰ አታምጣ!’ እንላለን። የመረጥነውን እምቢ ሲሉን ዝም ባልን፣ የመረጥናቸውም ግራ ሲጋቡብን ወደ ’አንድ ሁኑ!’ ማለት ባይቻለን ዛሬ ከቀሳውስቱ ልቆ ምህረትን የለመነ፣ ከጠቢባን ልቆ ፍቅርን የሰበከና በሚፈነጭበት ዕድሜው ብስለትን ያስመለከተ ወንድማችንን ለስድስት ዓመት ሊነጥቁን መወሰናቸውን ነገሩን። እግረ መንገዳቸውንም ’እስቲ የምትሆኑትን እናያለን’ ብለው እንደ ጠገበ ጅብ እያስካኩብን ነው።

 

 

አንበርክከው እያስገበሩ ያሉትን የኢህአዴግ መሪዎች ከጠፉ በጎች መካከል እንደ አንዱ የሚያዩ ዓይኖች አንድም የዋህነት አለያም ፍርሀት መሆን አለበት እንድል ተገደድኩኝ። ሌሎች የሚታያቸው ሦስተኛ ምክንያት ቢኖርም ለጊዜው አልታየኝም። የመጠቀ የማዳቀል ችሎታ ቢኖራችሁ እንኳ ከኢህአዴጎች ኢትዮጵያዊነትን ከእባብ እንቁላል እርግብን አታስፈለፍሉም። ስለዚህ ጊዜ በአገኙ ቁጥር እጅግ አስከፊ በሆነ ቅጣት ሞራላችንን ከስክሰው፣ ሰብዕናችንን ነጥቀው፣ ወደ ጎን እንጂ ወደላይ እንዳናይ ሸብበው፤ ማለትም ዋና ጠላታችንን እንዳናይ እርስ በእርስ አናክሰው ኢትዮጵያ ሀገራችንን ታሪክ ያደርጓታል።

 

እኛም የኢትዮጵያን መፍረስና መበታተን የምንመሰክር የመጨረሻው ትውልድ እንድንሆን ተፈርዶብናል። አርቆ ማሰብ የተሳናቸው አንጎላቸው ከርሳቸው የሆኑ ምስኪን ነብሶች ከየማኅበረሰቡ አሉና የጠላታችንን ሥራ ቀላል ያደርጉታል። ከዚያም በላይ የመኖር ግድና ድህነት እየጠፋ ካለው መተሳሰብና መረዳዳት ጋር ተዳምሮ የመከራ ቀናችንን ያረዝመዋል። ”የፈለገው ቢመጣ ከዚህ የከፋ አይመጣም” እያልን በክፋት ከራሰው ወደበሰበሰው የመሸጋገር ባህላችን የኢትዮጵያን መፍረስ በፀጋ እንድንቀበል ከዚያም የጎጥ መሪዎቻችን ከአዳዲስ የእጅ አዙር ገዢዎቻችን ጋር ደንገላሳ እንዲጋልቡን ወደምንፈቅድበት ደረጃ ላይ እንደርስ ዘንድ ጥርጊያውን እያበጃጀን ነው።

 

የጅምላ ሀገር ሻጮችም ሁኑ ቸርቻሪ ጎጠኞች ምን ያህል አሪፍ ብትሆኑ ክፋትን ሸጣችሁ ፍቅርን፣ እብሪትን አከፋፍላችሁ መቻቻልን፣ ቂምና ብቀላን ሸቅላችሁ ምህረትን፣ ጥላቻን ቸርችራችሁ መተሳሰብን ታተርፉ ዘንድ አይቻላችሁም። ጥላቻ ጥላቻን ይወልዳል፣ ክፋታችሁም መከራን አብዝቶ ይሰጣችኋል እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም። ታሪክ ያስተማረን ይሄንኑ ነው። ዛሬ በሀገራችን የምናየውም ተመሳሳይ ነው። ውሻ በከፈተው ግን ጅብ እየገባ ያሻውን ማድረጉ እውነት ነው። ሊከፋፈሉን ያሰቡ ጅቦች አሰፍስፈዋል።

 

በጅምላ ሊወስዱ ያሰቡም የዘመኑ ቱጃሮች ተወዳዳሪዎቻቸውን እያስፈራሩ ነው። እያንዳንዳችን ላይ የ‘ታላቅ ቅናሽ’ ምልክቶች ተለጥፈዋል። እኛም ለመሸጥ ዝግጅታችንን አጠናቀናል። ብዙዎቻችን ገና ድሮ ባርነትን ተቀብለን ራሳችንን ለገበያ ካቀረብን ቆይተናል። ገዢ ያገኘን በዓለማቱ ሁሉ ተበትነን እውቀት ጉልበታችንን እያንጠፈጠፍን ነው፣ በዲግሪያችን ታክሲ እየነዳንበት፣ ልጆቻችን እነ ገነትና አልማዝ መሪማና አሚና እየሆኑ በሻሽ ተሸብበው የሸቀጥ መደርደርያ ላያ ከቀረቡ ሰንብተዋል።

 

’የባሰ አታምጣ!’ ማለት ስለለመድን ክፋትን በፀጋ ተቀብለን ሀገር አልባነታችንን መርሳት ጀምረናል። ሌሎቻችን በአፍሪካ ማዕዘናት የገዢ ያለህ ስንል የራሳችንን ዋጋ ለማሳመር ኃይለኛ ማስታወቂያ እየሠራን በየስደት ካምፑ የግፍ ቀን እንቆጥራለን። በበረሀ ጥምና ንዳድ የወደቁ ለራበው ጅብ እራት እየሆኑ የጠፉት ሳይቆጠሩ ማለት ነው። ከክፋት ሁሉ ትልቁ ሀገር አልባነት የመኖር ተስፋ ምልክት ሲሆን ነው።

 

ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ኤርትራ ለኢትዮጵያዊው ከኢትዮጵያ የተሻለ ተስፋ የሚታይባቸው ሀገሮች ከሆኑ ይህ ከቶ ምን ማለት ነው? ትዕግስት ፍርሀት አይደለም ብለን ራሳችንን እናታለው? አልተሸነፍንም ብለን እንዋሽ? ሁሉን አዋቂ ነን ብለን እንሞካሽ? የሚበጀንን መነጋገር ያቃተን፣ መተባበር ያልቻልን ደካሞች ሆነናል ብለን ተማምነን ከወደቅንበት ብንነሳ ነው።

 

ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል፣ መሪም በትግል ሜዳ። ወደ ትግል ሳንገባ ’የመሪ ያለህ!’ ብንል የአቅማቸውን የሞከሩትን ብናብጠለጥል የመሪ ወኔና ብልህነትን እናዶለዱመው እንደሁ እንጂ አንሞርደውም። አንዳችን በሌላኛው ትከሻ የመንጠላጠልና ጊዜ ሲመች አጋፋሪ የመሆን ባህሪያችን ወደ ባህልነት ከተቀየረ፤ ለኛ ክብርና ነፃነት የሚዋደቁትን ’አላወቁበትም’ ወይም ’አርፈው ቁጭ አይሉም ነበር!’ የምንል ከሆነ ስለራሳችን የምንሰጠውን የውሸት ክብር አውልቀን የተሸናፊነትና የመገዛት አዲስ መለያችንን በፀጋ እንቀበለው። ’አይደለም!’ ካልን አደባባይ የምንጮህ እንጩህ፣ የምንጽፍ እንትጋ፣ ገንዘብ ያለን እንስጥ፣ በውስጥ ሆነን የምንታገል እንበርታ፣ ኢትዮጵያ ጀግና ልጆች ተርባ አታውቅም። ወጣቱ በማንኛውም ሰዓት ተዓምር ለመሥራት የሚችል ኃይል ነው።

 

እኛ ለማስተባበር ለማነሳሳት ለትግሉ አዝማች ለመሆን ካልበረታን ማንም እኛን ሊወግን አይመጣም። ሌቦችና ወሽካቶች እኛው በተውንላቸው መድረክ ነው የሚንፏለሉበት። እኛ ኃላፊነት ስንሸሽ እነርሱ እየተረከቡ ነው ዛሬ ፍርክስክሳችን የወጣው። በውል ከተገነዘብነው ያለን ኃይል እንኳን ለኛ ለአፍሪካም ይበቃል። ኢትዮጵያን ለመታደግ እነነሳ! ወደ መቃብርዋ እየተገፋች ያለች እናታችንን እንታደጋት!! ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሊያስተባብረን ሲል ታስሮአል። ሁሉም ነገር ለምክንያት ይሆናልና የታሰረች ሀገራችንን እናስፈታ ዘንድ ስለ ፍቅር በታሰረው ብላቴና ስም አንድ እንሁን!!!

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!! - አሜን!!!


 

ዳኛቸው ቢያድግልኝ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ