ዳኛቸው ቢያድግልኝ / ጥር 5 ቀን 2001 ዓ.ም.

ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ!

አንዳንዶቻችን አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን እያልን ዳር በቆምንበት ሰዐት ፈተናችንን እንቀበል ዘንድ ብርታትን፣ በአሸናፊነት እንወጣው ዘንድ ጥበብን አብዝተህ ስጠን ያሉ ፈጥነው እየገሰገሱ ነው።

 

በጭንጫ መሬት ላይ ዘሩን የበተነ ገበሬ ብዙ አላመረትኩም ብሎ ቢያዝን ምሬቱ ከንቱ ነው። ለርሱ የቆሙለትን ጀግኖቹን ያሳፈረ፣ አይዞአችሁ ያላለና የአቅሙን ያላደረገ ተጠቃሁ ወይም ተበደልኩ ብሎ ቢያማርር አደንቋሪው ጩኸቱ ሰሚ አልባ ነው። በዋዛ ፈዛዛ እኔ ዘንድ ካልደረሰ ምን አግብቶኝ የሚል ትውልድ ከበረከተ የነፃነት ቀን መራቁ አይቀርም። አንድ ኅጻን ቆሞ ከመሄዱ በፊት ብዙ ጊዜ ይወድቃል። በዚያ ጨቅላ አእምሮ ውስጥ ግን መውደቅ ስለአለ ከመዳህ በቀር ምርጫ የለኝም ብሎ ዳዴ እንዳለ የሚቀር የለም።

 

ይህን ጽሑፍ የምናነብ በሙሉ የጤና ችግር ከሌለብን በቀር ሺህ ጊዜ ተንደባለንና አፈር ቅመን በመጨረሻ የስበትን ሕግ ተቋቁመን በእግራችን መሄድ ብቻ ሳይሆን መሮጥና መዝለልም ችለናል። ይህንን መለስ ብለን ማየት በምንጀምራቸው አዲስ ጅምሮች ውስጥም መውደቅና መነሳት መኖሩን የግድ ልብ እንድንል ያሳስበናል።

 

የቅርቡ የቅንጅት ታሪክም በእግር ለመቆም የመውተርተርን ሙከራ ያስመለከተ ነበር። ቅንጅትን ጉልበት የሰጠነው ወፌ ቆመች ያልነው እኛው ነን ጉልበቱ እንዳይጠናና እንዲልፈሰፈስ አስተዋጽአ ያደረግንም እኛው ነንና በዚያ እርር ኩምትር ስላልን የወያኔ ጉልበቱ አይዝልም። አሁን ቅንጅት ብዙ እግር አውጥቷል ለሂያጁም ለሚሮጠውም፣ ለሚዘልለውና ዳዴ ለሚለውም ሁሉ ድጋፍ የምንሰጥ እኛው ነን። ሌሎች ድርጅቶችም አዲስ የሚፈጠሩቱም ቢሆን የሕዝብ ድጋፍን ይሻሉ። ወያኔዎች ለጥፋት ምን ያህል እንደሚሄዱ ነጋሪና መስካሪ አያሻንምና እይታችን ምን አቅጣጫ መያዝ እንዳለበት የጋራ የሆነ የድርጅት መርኅ ወይም የሀገር ሕልውና አስፈላጊነቱን ሁላችንም ልብ ልንል ይገባል።

 

ተቧድኖ ለመጋጠም መጀመሪያ ሜዳው፣ ሕግና ሥርዓቱ መኖር አለባቸው። ኳሷ ብቻዋን የምትፈይደው ነገር የለም። ጥሩ የመሀልና የመስመር ዳኛዎች ያስፈልጋሉ። ከሁሉም በላይ ግን ሜዳውና ሕጉ ወሳኝ ናቸው። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ራዕያቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበት የጋራ ሀገርና ሕገመንግስት ከሌላቸው ግን ሳይመሰረቱ ፈርሰዋል ማለት ነው። ሀገርን የማያስቀድሙ ድርጅቶች ከሥልጣን በላይ የሚሹት የለምና ለሕግና ለሀገር ደንታ የላቸውም። በቅርቡ በተደረገው ሙከራ ወያኔን ጥለን እኛም እየተጓተትን ወደቅን፣ ወያኔ ፈጥኖ ስለተነሳ ደረታችን ላይ ተቀምጦ አፍንጫ አፍንጫችንን እያለን ነው። ገና ለሁለተኛ ጊዜም ልንወድቅ እንችላለን። ቆመን ለመሄድ ግን አንችልም ብለን የጠላቶቻችን ጫማ ስር ዳዴ ስንል አንቀርም። ራዕይ የሌላቸውና ተስፋ የቆረጡ የትግሉን መርዘም ሲመለከቱ ዳዴ ለማለት ወስነው ሊሆን ይችላል። እነርሱም ቆመው ለመሄድ መውተርተራቸው ግን አይቀርም። ምናልባት አትነሱም! የሚላቸውን እየጠበቁ ይሆን ይሆናል።

 

በጎጥ በመደራጀት ነፃነትን እዋጃለሁ ያሉ የገዢዎች ሰለባ መሆናቸውን ተመለከቱ። ሀገር አማን ናት ብለው ድርጅት ፈጥረው እርስ በእርስ የታገሉ ተያይዘው እየወደቁ የጠላታቸው መሳቂያ መሆናቸውን ተመለከቱ። ሃሳብን በነፃነት የመግለጥ ጉዳይ አብቅቶ በነፃነት ማሰብም ወንጀል መሆኑን ሁሉም አስተዋሉ። ነገር ግን የግል ትምክህት ከክብር ጋር እየተምታቱ ተቀራርቦ መነጋገር እንኳ አስቸጋሪ ሆኖ ሰነበተ። እኔ ገና ከጅምሩ ከፖለቲካና ኃይማኖት ጋር ጠብም ዝምድናም የለኝም ብዬ ነበር። ነገር ግን እንኳን በአንድ ርዕስ መጻፍ ይቅርና ሠላምታም ከኃይማኖትና ከፖለቲካ ሊነጠል እንደማይችል ተረዳሁ።

 

“እግዜር ይመስገን” ካልኩኝ ኃይማኖት ነው “ኑሮው ምንም አይል” ብዬ ብመልስ ፖለቲካ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የሀገሩ ጉዳይ ያገባዋል አንድ የሚያደርገውም የሀገሩ ሕልውና ነው። ይህ አልገባ ቢለን እነ ቴዲና ብርቱ መታሰርና እኛን በፍቅር ማስተሳሰር ችለዋል። በዚህም ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ልጆች ወንድ ሴት ሳይሉ እስላም ክርስቲያን ሳይቆጥሩ፣ በጎሳ ወይም በፖለቲካ ድርጅት ሳይከፋፈሉ በዓለም ዙሪያ በአንድ ቀን ባጭር ጊዜ ተደራጅተው ድምጻቸውን ማሰማት ቻሉበት። ይህ የወያኔን ጓዳ የሚያንቀጠቅጥ ነው። ይህ የሆዳሞችን ቤት የሚረብሽ ነው። እጅግ ስለጨከኑብን ልንጨክንባቸው የግድ ነውና ትግሉ ዳር ሳይደርስ ተመልሰን ላለመውደቅ እንደጋገፍ። ፈጥኖ ለመሄድ መቻልን እንጂ ደጋግሞ የመውደቅ ሬከርድን አንስበር። ወያኔን በእግሩ እንዲቆምና ሀገሪቱን ወደ ግል ሱቆቻቸው ለማዞር የሚርመሰመሱ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ልብ እንበል። ወያኔ በእግሩ መሄድ ችሎ ሳይሆን በሆዳም ኢትዮጵያውያንና በውጪ ኃይል ተደግፎ የሚንቀሳቀስ እግር አልባ (ኢትዮጵያዊነት የሌለው) ነው። ወያኔን ስንታገል ምርኩዞቹንም እናስብ ያኔ ደግሞ እንዳይነሳ አድርገን እንጥለዋለን።

 

ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ናት። ችግራችን ብዙ ነው እውቀታችን ግን ከችግራችን በላይ ነው። ኢትዮጵያውያን ተርበናል ነገር ግን ምርት ሊያትረፈርፍ የሚችል ለም መሬት ይዘናል። ኢትዮጵያውያን ተጠምተናል ነገር ግን ሀገራችን ሌሎችን አጥግቦ የሚያሳድር የውሀ ሀብት አላት። ኢትዮጵያውያን በቂ ሕክምና አናገኝም ነገር ግን በዓለም ላይ በየትኛውም ሀገር እውቅ ዶክተሮቻችን ሌሎችን እያገለገሉ ነው። በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አሉ።

 

በንግድና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገራችንን ከተመደበችበት የድሆች ቁንጮነት ለማውጣት የሚችሉ ወገኖቻችን አሉ። ስለዚህ በአለን የተፈጥሮም ይሁን የሰው ሀብት እንመካ፣ በራሳችን እንኩራ፣ ያለን እምቅ ኃይል የአንድነት ተርባይኑን ያዙረውና የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የብልጽግና መብራት ይብራ። እነርሱ ታስረው እኛን እንድንተባበር፣ እንድንከባበርና በዋናው ጠላታችን ላይ እንድናነጣጥር ስላስተሳሰሩን የፍትህና የፍቅር አርማዎች ሲባል በጽናት እንቁም። እስርቤቱንም ሀገሪቱንም ከሞላው ቱሃን፣ ቅማልና ቁንጫ እንላቀቅ። አንድ ቀን ተባብሮ መቆም ይህን ያህል ከሆነ እስከ ነፃነት እጅ ለእጅ እንያያዝ። ራዕያችንን እውን ለማድረግ በመጀመሪያ ቅድስት ሀገራችን ነፃ ትውጣ።

 

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!!

 

ዳኛቸው ቢያድግልኝThis email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ