ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) - ቺካጎ (የኦባማ ከተማ)

ከሀገሬ ተሰድጄ በስደት ከምኖርባት ከቺካጎ ከተማ የወጡ ጥቁር አሜሪካዊው የኢሊኖይ ሴናተር ባራክ ኦባማ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የእኝህ ሰው መመረጥ በአሜሪካን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ያስተጋባ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል። (የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እንኳን በአቅሙ ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን ስለኦባማ ሲዘግብ ነበር)

 

ባራክ ኦባማ ሴናተር ከመባል ይልቅ «ተመራጭ ፕሬዝዳንት» ለመጀመሪያ ጊዜ ሲባሉ፣ ማምሻውን «ትር ትር» ስትል የነበረችው ልቤ በደስታ ተሞልታ እርፍ አለች። «ከአሁን አሁን ኦባማ ይሸነፍ ይሁን?» እያለ በስጋት የኮሰሰውና የተጨማደደው ፊቴም ተፍታታ። ከዓይኖቼም የደስታ እንባ መፍሰስ ጀመረ። በርግጥ በአሜሪካ የጥቁር ህዝብን የሚያኮራ ታሪክ ነው የተሠራው።

 

ጥቂት ደቂቃዎች እንደቆየሁ ለቅሶው የደስታ ብቻ መሆኑ ቀረና የኀዘን እየሆነ መጣ። የተፍታታውና በፈገግታ የተሞላው ፊቴ መጥቆር ጀመረ። የተወለድኩባትና ማንነቴ የሆነችዋን ሀገሬ ኢትዮጵያን አሰብኩ። ድህነቷ፣ ለማኝነቷ፣ የልጆቿ በዘር መከፋፈል፣ የልጆቿ መራብ፣ የልጆቿ በዓለም ዙሪያ ሀገር እንደሌላቸው መበታተንና የልጆቿን መብት መረገጥ ወደ አዕምሮዬ ሲመጣ ውስጤ አዘነ።

 

«መቼ ይሆን የአሜሪካን አይነት በረከት ለኢትዮጵያም የሚመጣው? መቼ ይሆን ለአሜሪካ የዘነበው ለኛም የሚያካፋው? መቼ ይሆን የህዝብ የበላይነት የሚረጋገጠው? መቼ ይሆን በአሜሪካ ነጩ፣ ጥቁር፣ ላቲኖው በአንድ ላይ የአሜሪካን ባንዲራ እያውለበለቡ ሀገራቸውን ለመለወጥ እንደተነሱት እኛም ኢትዮጵያውያን በዘር ላይ የተመሰረተን ኋላ ቀር ፖለቲካችንን ትተን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን እያውለበለብን በአንድነት የምንሰባሰበው? መቼ ይሆን ችግሮቻችንን በጠመንጃ የመፍታት ባህላችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥለን መገዳደላችንንና መጨቋቆናችንን የምናቆመው? መቼ ይሆን ወንጀለኛና ነፈሰ ገዳይ በየአደባባዩ አለፍርሃት ሲንጎራደድ፤ ጥፋት ሳይኖርባቸው ዜጎች ፍርድን በሚያዛቡ ዳኖች በግፍ መንገላታታቸው የሚያቆመው? መቼ ይሆን በከተማና በገጠር የሚኖረው ደሃው ህዝባችን የሚበላው ዳቦ የሚያገኘው? መቼ ይሆን ሀገራችን ለጥቂቶች ገነት ለብዙኀኑ ግን ገሃነም መሆኗ የሚያበቃው? መቼ ይሆን እርቅንና ኢትዮጵያዊነትን በመዝፈናችን፣ ጋዜጦች ላይ ሃሳባችንን በነፃ በመግለጻችንና የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናችን መታሰራችንና መዋከባችን የሚያቆመው? መቼ ይሆን ከውርደትና ከለማኝነት ነፃ የምንወጣው? መቼ ይሆን እንደ ሌሎች ሀገራት ዜጎች ቀና የምንለው? …» እያልኩኝ የሀገሬን ሁኔታ ሳስብ ውስጤ በረዶ ሆነ። ሁሉም ነገር ጨለማ ሆነብኝ።

 

ባራክ ኦባማ በተመረጡ በነጋታው ረዕቡ ጥቅምት 26 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ሌላ ጊዜ ቀኑን ሙሉ ገዢ አጥተው ሱቆቹን የሚያጣብቡ ጋዜጦች ወትሮ ከሚቀመጡበት ቦታ ጠፉ። በመጨረሻ የቺካጎ ጋዜጦችን ባላገኝም በአንድ የስታር ባክስ ቡና መጠጫ ውስጥ የኒውዮርክ ታይምስን አንድ የቀረች ጋዜጣ አግኝቼ ገዛኋት።

 

የነፃነት መንፋሣዊ መዝሙር

በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ምርጫውን አስመልክቶ የተጻፈ የሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን ታሪክ አነበብኩ። ታሪኩ እጅግ ልብ የሚነካና ትምህርት ሰጪ ታሪክ ነበር።

 

ከአርባ ሰባት ዓመታት በፊት እጅ ለእጅ ተያይዘው «መንፈስ ቅዱስ ምረጡ ሲለን እንመርጣለ! ኦ አምላካችን ሆይ! - እንመርጣለን መንፈስ ምረጡ ካለን» እያሉ በመዘመር ነበር ያኔ የሃያ አንድ ዓመትና የሰላሳ አራት ዓመት ወጣቶች የነበሩ፣ ሩታ ማይ ሃሪስና ማሚ ኔልሰን የሚባሉ ጥቁር አሜሪካውያን ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በአሜሪካን ሀገር በጆርጂያ ክፍለ ሀገር አልበኒ በምትባል ከተማ በሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ለመምረጥ የተጓዙት።

 

እግዚአብሔር የሰጣቸውን የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብታቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው የአልበኒ ፖሊስ የምርጫ ካርድን ከመስጠት ይልቅ የዱላና የግፍ በትር አወረደባቸው። ሩታ ማት ሃሪስና ማሚ ኔልሰን ለመብታቸው በመቆማቸው ታሰሩ። ተሰቃዩ። ተንገላቱ። በዚያን ወቅት ዘረኛ ነጮችም በዚያ አካባቢ ኢኮኖሚውን ይቆጣጠሩ ስለነበረ ጥቁሮች እንዲመርጡ ያስተባበሩም የነበሩ የሰብዓዊ መብት ታጋዮችም ከሥራቸው ተባረሩ።

 

ያኔ ጥቁሮች እንኳን ሊመረጡ መምረጥ የማይችሉበት የጨለማ ዘመን ነበር። ያኔ መብት የሚረገጥበትና በደልና ግፍ የበዛበት ዘመን ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን «እግዚአብሔር የሰጠንና የራሳችን የሆነውን ማንም አይነጥቀንም። እኛም ሰዎች ነን። እኛም ሃሳብ አለን። እኛም ድምፃችን ይሰማ» ብለው፣ ድፍረት ወኔ መንፋሣዊ ጽናትና ፈሪሃ እግዚአብሐርን ተሞልተው ዘረኛውን የጆርጂያ አስተዳደር ተጋፈጡ።

 

የኒዎርክ ታይምሱ ዘጋቢ ኬሸን ሳክ እንደዘገበው ሩታ ሃሪስና ማሚ ኔልሰን አሁን ስድሳ ሰባትና ሰማኒያ ዓመት ሆኗቸዋል። ያኔ ይዘምሩት የነበረውን የነፃነት መንፋሣዊ መዝሙር እየዘመሩ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ድምፃቸውን ለመስጠት ወደ አልበኒ ማዘጋጃ ቤት አቀኑ።

 

ያኔ ለመመረጥ በመምጣታቸው ተደብድበውና ቆሳስለው ተመለሱ። አሁን ግን በደስታና በኩራት ድምፃቸውን ሰጡ። ያኔ ጥቁር ስለሆኑ መምረጥ ተከለከሉ። እነርሱ ባላመጡት እግዚአብሔር በሰጣቸው በሰውነታቸው ቀለም ምክንያት በደል ደረሰባቸው። አሁን ግን የነርሱ አይነት ቀለም ያለውን ሰው ለመምረጥ በቁ። ያኔ ጥቁር መሆን ያስደበድብ ነበር። ያኔ ጥቁር መሆን ባርነት ነበር። አሁን ጥቁር አሜሪካዊ የዓለም ኃይል ሀገር የሆነችው የአሜሪካ ፕሬዳንት ለመሆን በቃ። ያኔ ትግሉ ለመምረጥ ነበር። አሁን መመረጥ ተቻለ።

 

እየተቀመጡ መቆም

በደቡብ ካሮላይና ክፍለ ሀገር ግሪንስቦሮ ተብላ በምትታወቅ ከተማ በምትገኝ ምግብ ቤት ውስጥ፣ ዮሴፍ ማክኒል የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ የኮሌጅ ተማሪ፣ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ ምግብ ቤት ምግብ አዝዞ ለመመገብ ደፍሮ በወኔ ገባ። የምግብ ቤቱ ባለቤት ምግብ ለዮሴፍ ማክኒል ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ዮሴፍ ማክኒል ግን ተስፋ አልቆረጠም። በነጋታው ሌሎች ሦስት ጓደኞቹን ይዞ ተመልሶ መጣ። አሁን የምግብ ቤቱ ባላቤት ምግብ አላቀርብም አለ። እንደገና መቀመጥ፣ እንደገና ምግብ መከልከል፣ እንደገና መቀመጥ እንደገና ምግብ መከልከል።

 

ትግሉ እየመረረ ፈተናው እያየለ ቢመጣም ጥቁር አሜሪካዊ ተማሪዎቹ ግን የልባቸውን መስኮት ለተስፋ መቁረጥ አልከፈቱም። ዓላማቸው ከግብ ማድረስ ከባድ እንደሆነ ያውቃሉ። ከፊታቸው ትልቅ ተራራ እንዳለ ያውቃሉ። በፊታቸው የዮርዳኖስ ወንዝ ያጓራል። በፊታቸው ጥልቅ ሸለቆ አለ። ነገር ግን የተራራው ርዝመት አላስፈራቸው። የዮርዳኖስ ወንዝ ጩኸት አላስደነገጣቸውም። የሸለቆውም ጥልቀት ልባቸውን አላቀለጠውም።

 

በየቀኑ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ ምግብ ቤት መቀመጣቸውን ቀጠሉበት። በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በየከተሞች ለነፃነት የሚደረግ የመቀመጥ ትግል ተጧጧፈ። በመቀመጥ ለመብት መቆም ተቻለ። ስጋ ተቀመጠ ልብ ግን ቆመ። ክፋት ስትበረታ፣ ትዕግስትም ልቃ በረታች።

 

ያኔ ጥቁር የበታች ነበር። ያኔ ጥቁር ከነጭ እኩል አይቀመጥም ነበር። ያኔ ጥቁር ለነጮች ብቻ በተመደበ ምግብ ቤት አይገባም ነበር። አሁን ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ቤተመንግሥት በ”ነጩ ቤት” (ዋይት ኃውስ) ውስጥ ጥቁር ሊገባ ነው። መግባት ብቻ አይደለም፤ በዚያው በነጩ ቤትም ለአራት ዓመት ምናልባትም ለስምንት ሊኖርበት ነው።

 

ከላይ እንዳየነው የባራክ ኦባማ መመረጥ እንዲሁ የመጣ አይደለም። ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ የትግል ችቦ እያስተላለፉ ከአንድ ትውልድ ያለፈ ትግል በመደረጉ ነው።

 

የጨለመው ይበራል

ያኔ ለጥቁሮች ጨለማ ነበር። አሁን ግን በራላቸው። በእኛም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከነጄነራል መንግሥቱ ንዋይ ጀምሮ (ምናልባትም ከዚያ በፊት) በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል። ነገር ግን የነፃነትና የዲሞክራሲ ጮራ ገና አልፈነጠቀም። በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ሁላችንም የምንጠብቀው ያ ቀን መጣ ብለን ነበር። ወደ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ዞረናል ብለን ገምተን ነበር። ግን እየበራ የነበረው ተመልሶ ጨለመ።

 

አዎ! ዛሬ ጨልሞብናል። ዛሬ አልተመቸን። ዛሬ ተሰደናል። ዛሬ መብታችን እየተረገጠ ነው። ዛሬ በዘራችን ምክንያት ተለይተናል። ነገር ግን በኛ ላይ የሚደረገውን ግፍ ለማስቆም፣ ጥቂቶች የዘረፉንና እግዚአብሔር የሰጠን የኛው የራሳችን የሆነን መብት ለማስመለስ ከተፈለገ የትግሉን ችቦ ተስፋ ቆርጠን መጣል የለብንም። ከመቼውም በበለጠ መነሳትና ሀገራችን እየሄደችበት ያለውን የጥፋት መንገድ ሠላማዊና ህዝባዊ በሆነ ትግል ማስቀየር አለብን።

 

በዚህ ትዕግስት አስጨራሽ ትግል ውስጥ ሠላማዊ ተቃውሞ ሲያሰሙ በጥይት እንደተገደሉት እንደነ ሽብሬ ደሳለኝ ልንገደል እንችላለን። ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ህዝብን በማነጋገራቸው በፖሊስ እንደታሰሩት እንደ እንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ በእንቢልታ ጋዜጣ የሰው ስም በስህተት ተጽፏል በሚል ተራ ክስ እስር ቤት እንደወረዱት ጋዜጠኞች፣ በዜማው ፍቅርንና ኢትዮጵያዊነትን እንዳቀነቀነውና በአሁኑ ሰዓት ፍትህ ተነፍጎት በቃሊቲ እንደሚሰቃየው ወጣት ቴድሮስ ካሳሁን ልንታሰር እንችላለን። «እኛ የምንላችሁን ካልሰማችሁ በልጆቻችሁ ላይ ነው የምትፈርዱት። ሥራ ይኖረናል ለልጆቻችንም እንጀራ አለ ብላችሁ እንዳታስቡ። እኛን ትታችሁ ሌሎችን የምትደግፉ ከሆነ የምትደግፏቸው ለምታርሱበት መሬት ማዳበሪያ ይስጧችሁ» እየተባልን ማስፈራራት ሊደርስብን ይችላል። ከማስፈራራትም አልፎ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠሩ ኃይላት ለመብታችን በመቆማችን ከሥራችን ሊይባርሩን፤ ለእርሻችንም ማዳበሪያ ሊነፍጉን ይችላሉ። አዎን! ኑሮ ሊመርና ሊከበድ በላያችን ላይም ያለው ቀንበር ከምንሸከመው በላይ ሊሆንብን ይችላል።

 

ነገር ግን በራሳችን ከተማመንና በአንድነት ከቆምን መወጣት የማንችለው ፈተና የለም። ጊዜው እያንዳንዳችን ከራሳችን ጋር የምንነጋገርበትና ትልቅ ውሳኔ የምንወስንበት ጊዜ ነው። ጊዜው ሌሎች ሀገራችንን ነፃ አውጥተው እንዲሰጡን ቁጭ ብለን የምንጠብቀበት ሳይሆን፤ እኛው እራሳችን የየድርሻችንን እያበረከትን ሁላችንም የምንፈልገው ለውጥ በኢትዮጵያ እንዲመጣ በአንድነት የምንቀሳቀስበት ጊዜ ነው። ጊዜው «አትምረጡ አትበሉን። እኛ እናውቅላችኋለን አትበሉን። ያልመረጥነው አያስተዳድረንም። የሥልጣን ባለቤትና ወሳኞቹ እኛ ነን፤ የሰጠነውን ድምፅ እንደከዚህ በፊቱ መስረቅ አትችሉም» እያልን ማስተጋባት የምንጀምርበትና ኃይል ያለው ሰፊው ህዝብ ጋር እንደሆነ የምናሳይበት ጊዜ ነው። ጊዜው የነፃነት መዝሙር እየዘመርን አንድነታችንን፣ ነፃነታችንን፣ መብታችንና ክብራችን የምናውጅበት ነው። እግዚአብሔር የሰጠንንና በጥቂቶች የተዘረፈነውን የሰብዓዊ መብታችንን የምናስመልስበት ነው። ጊዜው ከፍርሃትና ከበታችነት ስሜት የምንላቀቅበትና ካቀረቀርንበትም ቀና የምንልበት ነው። ጊዜው ጠዋትና ማታ ገዥውን ፓርቲ ከመራገምና ችግርን ብቻ ከማውራት አልፈን መፍትሔ አምጪዎችና ሥራ ሠሪዎች የምንሆንበት ነው። ጊዜው በእኛና በዕድገታችን፣ በእኛና በአንድነታችን እንዲሁም በእኛና በመብታችን መካከል የቆሙትን «አሁንስ በቃ» የምንልበት ነው።

 

ጊዜው የሚጠብቅብንን ኃላፊነት እያንዳንዳችን ከተወጣን አሜሪካኖች ጥቅምት 25 ያዩትን አይነት ፍስሃ እኛ የማናይበት ምክንያት የለም። እነኦባማ ሀገራቸውን ይህን ያህል ካናወጡ እኛም ከተቀረቀረችበት ወጥመድና ከወደቀችበት ማጥ እንድትወጣ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያን ማናወጥ አያቅተንም።

 

ጥያቄው የመቻልና ያለመቻል አይደለም። በርግጥ በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን። ጥያቄው እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ለውጥ እንዲመጣ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁና ፈቃደኞች ነን ወይ የሚል ነው። ትብብር አንድነት የኢትዮጵያውያን ንቁ ተሳትፎ በሌለበት ለውጥ የማምጣቱን ነገር እንርሳው።

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ይባርካት!


 

ግርማ ካሳ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ቺካጎ (የኦባማ ከተማ)

ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ