የ”ነፃነት” - ነገር (ጽዮን ግርማ)
ጽዮን ግርማ
”እናቴ በእግር ብረት አስራ ተማሪ ቤት ከላከችኝ ከዚያች ቀን ጀምሮ፣ አንዲት ነገር እንደተመኘሁ፣ አንድ ነገር ደግሞ እንደጠላሁ አለሁ” አሉኝ አንድ ቀን እንደቀልድ ”ሥልጣን ይወዳሉ?” ብዬ የጠየኳቸው ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም።
እሳቸውም ምክንያታቸውን ጠቅሰው ሊያስረዱኝ የፈለጉት፣ ገና ልጅ እያሉ እናታቸው ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በእግር ብረት አስረው ያለፍላጎታቸው ትምህርት ቤት ስለሰደዷቸው የጠሉት ”ባለሥልጣን” መሆንን ነበር።
እሳቸው ይህን ከነገሩኝ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ይህን አባባላቸውን ደጋግሜ እንዳስብ ያደረገኝን እሳቸው ከጠቀሷቸው ሁለቱ ጉዳዮች አንዱ በተለይ ከዚያች ዕለት ጀምሮ የፈለጉትና የተመኙት ነገር የሁሉም ሰው ልጅ ፍላጎትና ምኞት መሆኑ ነበር።
ፕሮፌሠር ከዚያች ዕለት ጀምሮ የተመኙት አንዲት ነገር ከእግር ብረቱ እስር ተፈትተው ነፃ መውጣትን ነበር። በእርግጥ እናታቸው ያኔውኑ ከእግር ብረቱ ፈትተዋቸዋል፤ እሳቸው ግን እስከአሁኑ ዕድሜያቸው እሳቸውና ሰፊው ህዝብ ከዲሞክራሲና ከነፃነት እንዳልተወዳጁ ስለሚሰማቸው ነፃነታቸውን ከዚያች ቀን ጀምሮ እንደተመኙ አሉ።
አባባላቸውን ደጋግሜ እንዳስብ ያስገደደኝ የሰሞነኛው የአሜሪካ ምርጫ ወሬ ያለ መቀዝቀዝ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም ያሉ ጋዜጦች ሙሉ ዘገባ የአሜሪካ ምርጫ ነው። እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙ ሚዲያዎች፣ ያለማቋረጥ ስለምርጫውና ተያያዥ ጉዳዮች አከታትለው ይዘግባሉ። ምርጫው ካለፈ አንድ ሣምንት ቢያስቆጥርም ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ምርጫ ውጭ የምሰማው አንዳችም ሣምንታዊ ጉዳይ አላገኘሁም።
እኔም ጆሮዬን ለሌሎች የመገናኛ ብዙኀን አውታር ቀስሬ፣ የአሜሪካውን ምርጫ ብሎም የጥቁር አሜሪካውን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መመረጥ እያዳመጥኩ፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን አንዷ ”ሚጢጢዬዋን” ሥፍራ የያዘችው ”እንቢልታ” ጋዜጣም፣ ከምርጫው በኋላ የሚታተመውን ሁለተኛ ሣምንታዊ የዝግጅት ማጠናቀቂያ ጊዜ ደረሰ።
ከመደበኛ ”ኤዲቶሪያል ቡድን” ውጭ ያሉ ዓምደኞቻችን ጽሑፋቸውን አጠናቀው በሚያስገቡበት የመጨረሻ ቀን፣ የሁሉም ጽሑፍ ለእርማት ተዘጋጀ፤ ጽሑፎቹ ከተለያየ ቦታ የመጡና አገላለፃቸው የተለያየ ይሁን እንጂ የሚያወሩት ግን ”ስለ ባራክ ኦባማ” መመረጥ ብቻ ነበር።
ጋዜጠኛው፣ የፓለቲካ ተንታኙና አንድ ቀን ደፍሮ ጽፎ ወይም ተናግሮ የማያውቀው ሁሉ የባራክ ኦባማ መመረጥና የምርጫው ሂደት ሳይሰለቸው ለሣምንታት መነጋገሪያ የማድረጉ ሚስጥር ምን ይኾን? ስል ማሰብ ጀመርኩ።
በዚህች በእኛው ከተማ (አዲስ አበባ) የምናያቸውና በእጃቸው ቁመት ልክ እስከ አገጫቸው መጽሐፍ ተሽክመው ”የአንባቢ ያለህ” እያሉ የሚለማመኑት የመጻሕፍት አዟሪዎች እጆች ላይ ሳይቀሩ (Dreams From My Father) የሚለውን የባራክ ኦባማን መጽሐፍ ”የለውጥና የታላቅነት ሚስጥር” አዲስ የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ገበያቸውን አድርተዋል።
”የምርጫ አስፈፃሚ ኃላፊ” ያህል ስለአሜሪካ ምርጫና ስለኦባማ ብዙ ነገር የሚያውቀው ጓደኛዬ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ዘጋቢው እስክንድር ፍሬው ስለአሜሪካ ምርጫና ባራክ ኦባማ መመረጥ ሣምንቱን ሙሉ መዘገብና፤ ማድመጥ አለመሰልቸት ምክንያት፤ ”በመላው ዓለም ያለ ህዝብ ከኦባማ ጋር በፍቅር ስለወደቀ ነው” ይላል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ አሜሪካ ብቸኛዋ ልዕለ-ኃያል (Super Power) ሀገር ሆና በመውጣቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳረፍ የምትችለው ተፅዕኖ በሁሉም ዘንድ ስለሚታወቅ ዓለም ሁሉ ወደ አሜሪካ እንዲያተኩር ምክንያት ሆኗል።
ላለፉት ስምንት ዓመታት የዘለቀው የቡሽ አስተዳደር ደግሞ የተከተለው የውጭ ፖሊሲ፣ አብዛኛው ህዝብ ከአሜሪካ የጠበቀውን ተስፋ እንዲያገኝ አላስቻለውም ነበር። እንደ ምሣሌም በመላው ዓለም የተወገዘበት ”ኢራቅ አውዳሚ የጦር መሣሪያ አላት” በማለት የሰው ሀገር እንዲወረር ካደረገ በኋላ ምንም መሣሪያ እንደሌለ በመረጋገጡ የአሜሪካንን ህዝብ ጨምሮ በመላው ዓለም የቡሽ አስተዳደር እንዲወገዝ አድርጎታል።
”እንደኔ አመለካከት ኦባማ ጥቁር ስለኾነ ብቻ አይደለም ዓለም ሁሉ በአሸናፊነቱ ጮቤ የረገጠው፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት በነበረው የቡሽ አስተዳደር መስመሩን የሳተው የዓለም ፖለቲካ ይስተካከላል ብሎ ያመነ የለውጥ መንፈስ የተጠማ ሁሉ ነው፤ ኦባማ ለሁለት ዓመታት ባደረጋቸው የምርጫ ቅስቀሳ ንግግሮች፣ ሁሉም የለውጥ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጎታል” አለኝ ኦባማ ሲያሸንፍ እንደ ምርጫው ተወዳዳሪ ቀኑን ሙሉ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ሲጎርፍለት የዋለው እስክንድር።
ከመስከረም 11 የኒው ዮርክ ጥቃት በኋላ ”ዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻ” በሚል ዘመቻ የጀመረው የቡሽ አስተዳደር፣ ማንኛውም ሀገር ለአሜሪካ የፀረ-ሽብር ዘመቻ አብሮ እስከተሳተፈ ድረስ፣ በሀገሩ ያለው የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር እና ሌሎች ከመብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አሜሪካ ችላ እንድትል አድርጓል።
የዚህ ውጤት ደግሞ የመላውን ዓለም ፖለቲካ መስመር እንዲስት በማድረጉና በሀገራቸው ዲሞክራሲ የጠማቸው በተለይ የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች፣ የለውጡ ንፋስ ተጋሪ የሆኑ ያህል ስለተሰማቸው በሰው ሀገር ምርጫ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆነ። አንዳንዶች እንዲያውም ይህንን የለውጥ ንፋስ ኃይልነት ”መንፈሠ-ኦባማ” እስከማለት ደርሰዋል።
”ለለውጥ የተጠማ በጣም በርካታ ህዝብ አለ፣ ሀገሩ ላይ ማየት ያልቻለውን ዲሞክራሲ በአሜሪካ ምርጫ ለማየት መቻሉ፤ ‘ለካ ምርጫ እንዲህ ነው እንዴ?’ በሚል፤ ‘የአሜሪካው የለውጥ ንፋስ እኔንም ሊያገኘኝ ይችላል’ በሚል ተስፋ በደስታ ተውጦ የሚከታተለው በመሆኑ የማይሰለች አጀንዳ የሆነ ይመስለኛል።” አለኝ የተባበሩት መንግሥታት ዜና አገልግሎት (ኢሪን) የዜና ወኪል የሆነው ተስፋለም ወልደየስ።
እንደተስፋለም ያሉ ሌሎች የውጭ ሀገር ዘጋቢዎችም በዚህ ሃሣብ ሳይስማሙ አይቀሩም። ለምሣሌ ቢቢሲ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሰማራቸው ዘጋቢዎች በየሀገራቱ ያለውን የህዝብ ስሜትና የራሣቸውን አስተያየት ሲሰጡ፤ “በአብዛኛው አምባገነን የሆኑ መንግሥታት ባሉባቸው ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች በአባማ መመረጥ ደስተኞች ናቸው” በማለት ከየሀገራቱ ዘግበዋል። ይህን የመሰለውን ስሜት የፈጠረው ደግሞ ኦባማ ለአምባገነን መንግሥታት ፈጽሞ የሚመች የፖለቲካ ፕሮግራምና አቋም የሌላቸው መሆኑ ነው። ”ቡሽ በየሀገራት ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደፈለጋቸው ሲፈተፍቱ አምባገነን የሆኑ መንግሥታትን ጭምር እውቅና ሠጥተዋል” ይላሉ የዓለም አቀፍ የአልቁዱስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ። ”ኦባማ ደግሞ ለእንዲህ አይነቶቹ መንግሥታት አይመቹም” ባይ ናቸው።
ዓለም በኦባማ ምርጫ የተደመመው፣ የተደነቀውና የተደሰተው፣ ከ50 ዓመት በፊት ለነፃነታቸው የታገሉት ጥቁር ህዝቦች ገድል በመጨረሻ ውጤቱ አምሮ፣ በነጮች የሥልጣን ወንበር ላይ ጥቁር ስለተቀመጠ አልነበረም፣ ወይም ነጮች አሁን ደግሞ ቦታውን ጥቁር መያዝ አለበት በሚል በኮታ የመጣ ጥቁር ፕሬዝዳንት ስለሆነም አይደለም፤ የዓለም ህዝብ የነፃነት ትንፋሽ መተንፈስ ፍላጎቱ ብቻ ስለሆነ ነው።
ኦባማ (Change - I have a dream) ሲል ለውጥን ሰብኳል፣ ”ከሃያ ዓመት በፊት የነበረው እና የአሁኑ ፖለቲካ አንድ አይደለም”፤ ሲልም ወደኋላ እያዩ የሚፈጠር የበቀልና የጥላቻን ስሜት እንዳይታወስ በሩን ዘግቷል። በየጊዜው የሰውና የስም ለውጥ እንጂ ትክክለኛ ለውጥ የማያመጣ መሪ የሰለቸው የየሀገሩን ህዝብ ቀልብ ስቧል፣ ለዚህም ነው ያልተሰለቸውና የማይሰለቸው። መነጋገሪያና መተየቢያ የጨበጠ ሁሉ ሣምንቱን ስለኦባማ ፕሬዝዳንትነትና ስለዲሞክራሲያዊው የአሜሪካ ምርጫ መናገር፣ አንባቢም ስለኦባማ ማድመጥ፣ ማየትና ማንበብ ያልሰለቸው፤ እንደ ፕሮፌሠር መስፍን ዕድሜ ልኩን ለመተንፈስ የሚመኘው ”የነፃነት” ትንፋሽ በአሜሪካ ምርጫ ተግባራዊ ኾኖ በመመልከቱ ነው።
ዓለም በሙሉ የለውጥ ናፋቂ ሆኗል። የስም፣ የመልክ፣ የዘር ሐረግ፣ የቀለም፣ የመሪ ለውጥ ሳይሆን፣ የአሠራርና የአተገባበር ለውጥ፤ በለውጡም የዲሞክራሲና የነፃነት ተቋዳሽ መሆን ይፈልጋል።