አሸናፊ በቀለ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን፣ በዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አመራር ስር በነበረበት ወቅት ”… አመራሮቹ ትክክለኛና ፍትሐዊ ውሳኔ የመስጠት ፍላጎትና ችሎታ የላቸውም፣ የሚያስተላልፉት ውሳኔም ሆነ ትዕዛዝ የተወሰኑ ቡድኖችን ሊጠቅም በሚችል ነው፣ ለሥራ ትኩረት አይሰጡም፣ ክለቦች እርስ በርሳቸው እንዲናቆሩ ያደርጋሉ፣ ለአንድ ክለብ ያዳላሉ፣ አምባገነንነት ይታይባቸዋል፣ …” የሚሉ በርካታ ቅሬታዎች ይነሱበት ነበር።

 

የፌዴሬሽኑ ጉዳይ ወደ ተካረረ አለመግባባት ከተቀየረና ቡድኖቹ የእርስ በርስ ሽኩቻ ከጀመሩ በኋላ፣ አብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ምን እንደሚወስን ግራ ተጋብቶ አስተያየት ከመስጠትና ግፊት ከማድረግ ሲቆጠብ፣ ሌላው በፍርሐት ዝምታን መርጧል። ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ በመገናኛ ብዙኀን አማካኝነት በግልፅ በመውጣት፣ ለጥቂት ጊዜያት ለአዲሱ ፌደሬሽን አመራሮች ድጋፍ ሲሰጡ ቆዩ፣ እኔም ከነሱ እንደ አንዱ ሆንኩ።

 

ጉዳዩ እንደ ሌሎቹ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በሀገር ሕግና በሀገር ሽማግሌ የሚዳኝ ባለመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ አካላትን ጣልቃ ማስገባት የግድ ነበር። እናም ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) አመራ። በዚህም ”ሕግ ተጥሶ ያለአግባብ ከሥልጣን ተነስቻለሁ፣ ሕግ ሊከበር ይገባል” ያሉት ዶ/ር አሸብር፣ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ጽ/ቤት ሄደው ከሰሱ። ፊፋም ሕጋዊ እውቅና ያለውን የዶ/ር አሸብርን አመራር በመደገፍ ፌደሬሽኑ መከተል ያበትን ሮድ ማፕ በመቅረጽ አስታራቂ ሃሳብ ላከ።

 

አዲሱ ፌደሬሽን ይህን ውሳኔ አንዴ ሐሰተኛ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በገንዘብ ኃይል የተወሰነ ነው፣ ጉዳዩን ጠቅላላ ጉባዔው ተወያይቶበት የሚወስነው ነው በማለት መግለጫ እያወጣ ሲሸሸው ቆይቷል።

 

ፊፋ በውሳኔው በዶ/ር አሸብር የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራር ቢሮውን ተረክቦ፣ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና አዲስ ምርጫ እንዲያካሂድ የሚያዝ ቢሆንም፣ አዲሱ ፌደሬሽን ፍቃደኛ ባለመሆኑ በፊፋ የተሰጠው ቀነ ገደብ ተጠናቆ ሀገሪቱ በእግድ ላይ ትገኛለች።

 

አዲሱ ፌደሬሽን ይባስ ብሎ ስለፊፋ በሰጠው ሌላ መግለጫ ”… የሕግ ባለሙያዎቹ ከፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ቀደም ሲል ያስቀመጡትን ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) በመለወጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ወደ ፌደሬሽኑ ቢሮ መመለስ የማይገባቸውና ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ የማስወገድ ድምፅ (ሞሽን ኦፍ ዲስሚሳል) እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን፣ የሕግ ባለሙያዎቹ በ10/10/2000 በላኩት የፋክስ መልዕክት አረጋግጠውልናል” የሚል መግለጫ በሀገራዊው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ቢሰጡም፤ ፊፋ ወዲያውኑ ባወጣው መግለጫ የተቀየረ ሃሳብም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ የወጣ መግለጫ እንደሌለ በማስታወቁ፣ የአዲሱ ፌደሬሽን መግለጫ ውሸትነት አጋልጦ አውጥቷል። ውሸትን ምን አመጣው?

 

እንደኔ አስተሳሰብ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ዋናው ባለቤት የስፖርት ቤተሰቡ እንጂ ግለሰቦች ባለመሆናቸው፣ ፊፋ ያወጣውን ሮድ ማፕ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ፣ አዲሱ አመራር ወንበሩን የያዘው በምርጫ ከሆነ፣ ፊፋም ያዘዘው ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ምርጫ እንዲደረግ ነውና ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ በሚያደርገው ምርጫ ለመመረጥ የሚከለክለው ነገር ሊኖር አይችልም።

 

አዲሱ ፌደሬሽን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ የግልግል ፍርድ ቤት፣ በመሄድ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው። ነገር ግን የፊፋን ውሳኔ ማስቀየር እንደማይችሉ ደግሞ ተደጋገሞ እየተገለፀ ነው።

 

መንግሥት (የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር) በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት፣ ውሳኔ እንዲሰጥ ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢቀርብም፣ አዲሱ ፌደሬሽን ለፍኖተ ካርታው አልሸነፍም በማለቱ ኢትዮጵያ በእግድ ላይ ትገኛለች። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው የሀገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ገብተው ለመዳኘት ቢሞክሩም፣ ከአዲሱ ፌደሬሽን ቀና ምላሽና ፍላጎት ባለማየታቸው ሽምግልናውም አንድ እርምጃ መራመድ አልቻለም።

 

የፌዴሬሽኑ ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ በሆነበት በዚህ ሁኔታ፣ ባለፈው እሁድ ቁጥሩ ለማመን የሚያስቸግር የእግር ኳስ ተመልካች፣ የጊዮርጊስና የቡናን ጨዋታ ለማየት ስታዲየም በገባበት ሰዓት፣ በጨዋታው የተገኘው ውጤት ግልጽ በሆነ ሁኔታ፣ በዳኛው አድሎ የተፈፀመበት መሆኑን የሚወጡት መግለጫዎች መጠቆም ጀመሩ።

 

በዶ/ር አሸብር ጊዜ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች ዛሬም መነሳት ጀመሩ፤ ፌዴሬሽኑ የሁሉም ክለቦች ሳይሆን በአንድ ክንድ ተፅዕኖ ስር የወደቀ ፌደሬሽን ሆኗል። እንዲያውም ተጫዋቾቹ በዕድሜያቸው ዘመን አይተውት የማያውቁት አድሎ እንደተፈፀመባቸው መናገር ጀምረዋል፤ የክለብ መሪነታቸውን ጥለው የሄዱም አሉ።

 

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በግለሰቦች ተፅዕኖ ስር ወድቆና፣ ፊት ለፊት ያፈጠጠ አድሎ የሚፈጸም ከሆነ፤ ድርጊቱ እንደ ተራ ስህተት ተቆጥሮ ሊታለፍ አይገባውም። ነፃና ገለልተኝነትን በሚጠይቁ ህዝባዊ ተቋሞች ላይ፣ የባለሀብቶች ጣልቃ ገብነት ፍትህንና መብትን ይፃረራል። የፌደሬሽን አመራሮች ከክለብ ባለቤቶች እጅ ነፃ መውጣት አለባቸው።

 

አዲሱ ፌደሬሽን ፍላጎቱ የኢትዮጵያ ስፖርት እንዲያድግ ከሆነ ወይ የፊፋን ፍኖተ ካርታ ተቀብሎ ትክክለኛ ምርጫ እንዲደረግ በማድረግ፣ በገለልተኛ አመራር ሀገሪቱን ከቅጣት፤ ክለቦቹንም ከተፅዕኖ አላቆ ነፃ ያውጣቸው። አሊያም ለሀገር ሽማግሌዎች በመገዛት እነሱ የሚወስኑትን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል።

 

ነገር ግን የፊፋንም ውሳኔ አለመቀበልና ከሽማግሌዎቹም ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ አለመሆን፤ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ፍላጎትን ማስቀደም የሚጠቁም ነው። ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጣልቃ ገብቶ፣ በአስቸኳይ መፍትሔ ማበጀት ካልቻለ ከተጠርጣሪነትና ከተጠያቂነት አያመልጥም። ሁሉም ወገን የሕግን የበላይነት ሊገነዘብ ይገባል። ጥፋተኛው ዶ/ር አሸብርም ሆነ አዲሱ ፌደሬሽን ፊፋ ሌሎች ሀገሮችን በሚያስተዳድርበት ሕግ ወስኗል። ዛሬ ሕግ እንዲጣስ ከፈቀድን ነገ ማጣፊያው ይቸግረናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ