ከዳንዴው ሠርቤሎ

የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ተብሎ መንግሥት ከውጭ ገበያ ገዝቶ ያስገባው ስንዴ፣ በየቀበሌው ኩንታሉ በ350 ብር ሂሳብ እየተሸጠ ነው። ጥያቄው ግን ከዋጋ ማረጋጋት ያልፋል። የማግኘት ወይም የማጣት ጉዳይ ስለሆነ ግማሹ ለክፉ ቀን ያስቀመጠውን ስንቁን እያሟጠጠ ገዝቷል። ግማሹ ደግሞ ተበድሮም ተለቅቶም ሸምቷል። “ምን እንደሚመጣ አይታወቅም” እያለ በሥጋት ምክንያት ባገኘው ዋጋ ከተገኘው ገበያ እየገዛ አስቀምጧል።

 

በየቀበሌው የተቋቋሙ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ለአንድ ሰሞን ስንዴ በማከፋፈል ሥራ ተሠማርተው ሲያግዙ ነበር። ሰሞኑን ግን የስንዴ ዕደላው ጋብ ብሏል። በስንዴው ጥራት ምክንያት ይሁን፣ በገንዘብ እጦት የተነሳ ይሁን ፈላጊው ቀንሷል። በአንዳንድ ቀበሌዎች የዘይት መሸጫ ዋጋው መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፣ ያም ሆኖ ፈላጊ የለውም።

 

ምክር ቤቱ ሲከፈት በሚቀርበው ሪፖርት፣ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እንደሚወስድ መግለጫ መስማት የተለመደ ሆኗል። ስንዴም እየተገዛ እንደሚሠራጭ በተነገረው መሠረት እየገባ ነው። አሁን አነጋጋሪ የሆነው ዐቢይ ችግር የስንዴው ባህሪ ሆኗል። አንዳንድ የቢሮ ሴቶች በኢንተርኔት ድረ-ገጽ እንዴት እንደሚጋገር መረጃ እስከመፈለግ ደርሰዋል ይባላል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ ቋሚ ቀልድ በቅብብሎሽ በከተማው እየተናፈሰ ነው። አንዷ የኮምፒዩተር ኤክስፐርት የስንዴውን ፍሬ መጠን፣ ከለሩን፣ ክብደቱን፣ የአዲሳባን የአየር ሁኔታ (ሙቀቱን ቀዝቃዜውን፣ በዲግሪ ሴልሺየስ) ለክታ የምጣዱን ግለት መጠን እያቀያየረች፣ መረጃውን ለኮምፕዩተሩ ሰጠችና ውጤት ስትጠይቅ፣ ”ጎግል ውስጥ መረጃ የለም” የሚል መልስ አገኘች አሉ እየተባለ ይገለጣል።

 

መቸም ያንን ሁሉ ሚሊዮን ብር በውጭ ምንዛሪ አውጥቶ መንግሥት ግዥውን ሲፈጽም፣ የስንዴውን ጥራት ደረጃ፣ ዳቦ መሆን መቻሉን፣ ፍሬው የሚሠጠውን የዱቄት መጠን፣ የአገልግሎት ዘመኑን፣ የተመረተበትን ዓመት፣ … ሳይፈትሽና ሳያወዳድር ዋጋውን ሳያነፃፅር ይገዛል ለማለት ያስቸግራል። የመንግሥትን የዕቃ ግዥ ሥርዓት የሚያውቁ ይበልጥ ሊዘረዝሩና በአፈፃፀም ሂደት ችግር ከተከሰተ፣ እነማን ሊጠየቁ እንደሚገባቸው የተከበረው ምክር ቤት እንደሚከታተለው አይጠረጠርም።

 

ስንዴው ግን በየቤቱ ማነጋገሩ አልቀረም። ባለፈው ዓመት በዕርዳታ መጥቶ፣ ግማሽ ኩንታሉ በ90 ብር ሂሳብ ለተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ሲሸጥ የነበረው ስንዴ ጥራት ጥሩ ነበር ይባላል። ብዙዎቹ ኮታቸውን ለነጋዴ አየር ባየር እየሸጡ ጨውና በርበሬ መግዣ በማድረግ ትርፉን ሲጠቀሙበት የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ እያስፈጩ ዳቦ ጋግረውት ውጤቱን እንደወደዱት ይመሰክራሉ። አሁን በቅርቡ ተገዝቶ፣ ኩንታሉ በ350 ብር ተመን በመከፋፈል ላይ ያለው ስንዴ ባህሪ ግን ሸማቹን ግራ አጋብቷል።

 

እንደተለመደው ተቦክቶ፣ ሁለት ሦስቴ ኩፍ እስቲል ተጠብቆ ሲደፋ፣ ከምጣድ የሚላቀቀው በዳቦ መልክ ሳይሆን በእንኩሮ መልክ ነው ተባለ። ምን ይደረግ ሲባል ባበሻ እርሾ ተቦክቶ ቢጋገር ልክ ይመጣል ተባለ። ያም አልሆነም። ግማሹ ስንዴው ማሸት አይወድም ይላል። በማሸት ቀርቶ በማሻሻት ሲሞከር እስከናካቴው አትቀስቅሱኝ ብሎ ለሽ አለ።

 

ሌላው ማሸት ይወዳል፤ እስከ አራት ጊዜ ኩፍታ ድረስ መቆየት ያስፈልጋል ይባላል። ሲታሽ ከእጅ አልላቀቅ ብሎ እንደ ሙጫ ያጣብቃል ይላል። የሴቱን ሙያ የተፈታተነው ስንዴ፣ በምግብ ጥናት ኢንስቲትዩት በላቦራቶሪ ተመርምሮ፣ አንድ መፍትሔ ካልተገኘና ለህዝብ ይፋ እስካልተደረገ ድረስ፣ ከቤት ስንዴ እያለ ወደ ዳቦ መጋገሪያ ቤቶች እየሄዱ መሸመት አማራጭ የለውም ይላል ሸማቹ።

 

ዳቦ ቤቶችም በበኩላቸው እንዲህ ያለውን ስንዴ ገዝተን፣ ምን አድርገን ነው ለህዝብ የምናቀርበው ብለው፣ ያገር ውስጥ ስንዴ በውድ ዋጋ እየገዙ ዳቦ መጋገር እንደተገደዱ ይገልፃሉ። እውነታቸውን ነው፤ ደምበኛን ማስቀየም ገበያን ማራቅ ይሆናል።

 

መቸም የስንዴ ዋጋ በዓለም ገበያ ተወደደ እንጂ አቅርቦቱ እንዳልቀነሰ ይነገራል። ስንዴ ከአውስትራሊያ፣ ካሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከኒውዚላንድና ከአውሮፓ ሀገሮች እንደሚመጣ ይታወቃል። ከዚህ በፊትም ቢሆን መጠኑ ይለያይ እንጂ ሀገሪቱ እየሸመተች ስለምታስገባ ጥሩ ስንዴ ከየትኛው ሀገር ገበያ እንደሚገኝ ታውቃለች። 85 በመቶው ህዝባችን ራሱን መግቦ፣ 15 በመቶውን መመገብ ካቃተው፣ መቸስ ምን ይደረጋል አበባና ቡና እያመረትን፣ ከብት እያረባን፣ ጫት እየሸጥን፣ ደኅና ስንዴ ገዝተን ገበያውን ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን መጠባበቂያ የሚሆን እህል በጎተራ ማኖር ኃላፊነታችን ይሆናል። የሚገዛው ስንዴ ግን ጥራቱ ተፈትሾ፣ የሚበላ ዳቦ የሚወጣው መሆኑ ተረጋግጦ መሆን አለበት። ካለበለዚያ አንዴ በእርሾ፣ አንዴ በመታሸት፣ ሌላ ጊዜ በኩፍታ ብዛት ስንሞክር፣ ለተጨማሪ ማገዶና ኢነርጂ ከመዳረጋችን አልፈን የገዛነውን ስንዴ ምን እንደምናደርገው ግራ እንደገባን መቆየታችን ነው።

 

በነገራችን ላይ ስንዴም ቢሆን በአማራጭነት ዳቦ እየጋገርን ከምንጠቀምበት ባሻገር፣ ሌሎች አማራጮችንም ከግንዛቤ ማስገባት ይኖርብናል። በእርግጥ የጤፍ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ዝቅተኛ ገቢ ለሚያገኙ ቤተሰቦች ቢከብድም፣ ጤፍ በባህሪው በርካታ የጎንዮሽ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚታወቅ ይመስለኛል። በቀላሉ መፈጨቱ፣ እንጀራው ከባዶ እንጀራ በበርበሬ መብላት አንስቶ፣ ሲደርቅ ተሰባብሮ ወይም ተወቅጦ በእንፍርፍር መልክ እስከ መብላት ድረስ ማገልገሉ፣ ኤነርጂ ሳይጨርስ በወረቀት ወይም በቅጠል ማገዶ በቀላሉ መብሰሉ፣ ሲፈለግ በገንፎ፣ ሲፈለግ በአጥሚት መልክ ሊጠጣ መቻሉና በይዘቱ ያለው ንጥረ ነገር ምክንያት ተመራጭ ያደርጉታል።

 

ዛሬ ግን ጤፍ የሀብታሞች ብቻ ምግብ ሆነ። አልፎ ተርፎ ወደ ውጭ ሀገር እስከ መላክ መድረሱ ይነገራል። ግማሹ በብስኩት መልክ፣ ሌላው በዳቦ መልክ እያዘጋጀ ይጠቀምበት ጀምሯል ይባላል። የማይጠቅም የሣር ፍሬ እንዳልተባለች ሁሉ የምንጃርና የበቾ፣ የአድአና የጊምቢቾ፣ የጎጃምና የወለንኮሚ ጤፍ በዶላርና በዩሮ ትቸበቸብ ጀምራለች። መሠንበት ደግ ነው።

 

ይሁንና ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ በፓርላማ ውስጥ ተነሳ፣ በንግድ ምክር ቤት ተወሳ ድመት ”ያው በገሌ” እንዳለችው፣ ደሃው ከበይ ተመልካችነት አልወጣም። ውሎ አድሮ ይህ የምግብ እጥረት መንግሥት ለደሃው ህዝብ ምግብን አብስሎ፣ እንደ መጀመሪያ ዕርዳታ ማቅረብ ስለሚገደድ ካሁኑ መዘጋጀት እንዳለበት ይታየናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ