Prof. Mesfin Woldemariamፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም

የኦባማ የምርጫ ዘመቻና የመጨረሻው ውጤት፣ የዓለምን በሙሉ ቀልብ የሳበ ነበር። ለምን? በብዙዎች የመገናኛ ብዙኃን በአሜሪካም ሆነ ከአሜሪካ ውጭ እንደ ምክንያት የሚሰጠው የቆዳው ቀለም መጥቆሩ ነው። በአሜሪካ ታሪክና ባህል ጥቁርነት ከባርነት ጋር ይያያዛል፤ ስለዚህም ኦባማ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ሲወዳደር፣ በስተጀርባው የባርነትን ታሪክ አዝሎ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። ከባርነት መሠረት ተነስቶ ወደ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነት መገስገስ ከፍ ያለ እምነትንና ድፍረትን ስለሚያመለክት ቀልብ የመሳብ ችሎታ አለው።

 

ሆኖም ይህ አመለካከት መጥፎና አደገኛ በርን ይከፍታል፤ ጥቁርነትን ከባርነት ጋር ያቆራኛል። የአውሮፓና የአሜሪካ ባሪያዎች ሁሉ የሄዱት ከአፍሪካ ስለሆነ፣ የአፍሪካ ህዝቦች ሁሉ የባርነት ታሪክ አላቸው የሚል የተሳሳተ መነሻ ካልያዙ በቀር፣ ጥቁርነትና ባርነት የባህሪም ሆነ የታሪክ ግንኙነት የላቸውም። በዚህ የስህተት ወጥመድ ውስጥ ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ እንደፕሮፌሠር ዓለማየሁ ገብረማርያም ያሉ የበሰሉና ጥንቁቅ ምሁራንም የገቡ ይመስለኛል። በጥቁርነትና በባርነት መሀከል የባህሪም ሆነ የታሪክ ቁርኝት የለም፣ ሌላ ቀርቶ ኢትዮጵያ ብቻ ታፈርሰዋለች።

 

ወደ ኦባማ ስንመለስ፣ ኦባማ ጥቁር ነው፤ አባቱ ጥቁር ኬንያዊ ነው፤ ስለዚህም በጥቁረቱ ላይ ክርክር የለም። በተጨማሪም በአባቱ አሜሪካዊ አይደለም አሜሪካዊ ያልሆነው የኦባማ አባት የባርነት ታሪክ የለውም። ኦባማም በጥቁር አባቱ በኩል የባርነትን ታሪክ አልወረሰም፤ ይህም ሊያከራክር አይችልም። የኦባማ እናት ነጭ አሜሪካን ስለሆነች፣ በሷም በኩል የባርነት ታሪክም ሆነ ውርስ የለውም። ስለዚህም ኦባማ በአባቱም ሆነ በእናቱ የባርነት ታሪክ የለውም። ጥቁርነትንና ባርነትን የማቆራኘቱ ዝንባሌ የመጣው፣ ከጥቁር አሜሪካኖች ታሪክ ነው። ጥቁር አሜሪካኖች አሜሪካ የገቡት በባርነት ነው። ”የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ሆነው ተፈጥረዋል” ከሚለውም አዋጅ በኋላ አብዛኛዎቹ ነጭ አሜሪካኖች፣ ጥቁሮችን እንደ ሰው ለመቁጠር አልቻሉም ነበር። ጥቁርና ነጭ በሕግ ተለያይተው የሚኖሩበትን ጊዜ እኔም ደርሼበት አይቼዋለሁ። ከሃምሳ ሁለት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ደቡብ ያየሁትንና የደረሰብኝን ሳስበው፣ ዛሬ አሜሪካ ደቡቡም ጭምር ምን ያህል እንደተለወጠ ስመለከት ያስደንቀኛል።

 

በኦባማ ጥቁረት ላይ የሚያተኩሩ ሁሉ የሚረሱት አንድ ዋናና መሠረታዊ ነገር አለ። የአሜሪካ ህዝብ ለውጥን አይፈራም፤ ጊዜውንና ሕጉን ጠብቆ ካልተስማማው፣ ለውጡንም ለመለወጥ ችሎታ እንዳለው በልበ ሙሉነት ያምናል። የአሜሪካን ህዝብ ከአውሮፓም ህዝቦች የሚለየው፣ ለውጥን የመቀበልና አዲስ ነገርን ሳይፈራ ለመሞከር ያለው ትልቅ ችሎታ ነው። በታሪክ፣ በባህልና በሸር፣ በሴራና ጥሎ ማለፍ የውርስ ጭነት ያልተዳከመ፣ አብዛኛውን ጊዜ በአዕምሮና በእውቀት የሚመራ ማኅበረሰብ ነው። ስለዚህም የአሜሪካ ህዝብ በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምሥራቅም፣ በምዕራብ፤ ጥቁሩም፣ ነጩም፣ ወንዱም፣ ሴቱም፣ ሽማግሌውም፣ ወጣቱም በብዛት ኦባማን መምረጡ እኔን አላስደነቀኝም። በሃምሳ ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በዘር ጉዳይ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ተከታትዬ አይቸዋለሁ። የአሜሪካ ህዝብ ከኦባማ የቆዳ ቀለም አልፎና ጠልቆ ችሎታውንና ብቃቱን ተገነዘበ፤ ከቡሽ ጋር አወዳደረው፤ ከማኬን ጋር አወዳደረው፤ በጣም የተሻለ መሆኑ ገባውና መረጠው። እንደተጠበቀው ካልሆነ ከአራት ዓመታት በኋላ ይለውጠዋል።

 

ቡሩክ ኦባማ ለአሜሪካ የፕሬዝዳንትነት ውድድር ለመቅረብ፣ የመጀመሪያው ጥቁር አልነበረም፤ ጄሲ ጃክሰን የሚባለው ካህን ቢያንስ ሁለት ጊዜ የሞከረ ይመስላል። ጄሲ ጃክሰን በጥቁርነቱ ነው ውድድር ውስጥ የገባው። ጥቁር ነኝና ምረጡኝ! ጥቁር አሜሪካኖቹ ከእጅ አይሻል ዶማ አሉት መሰለኝ፤ ነጮቹ አሜሪካኖች በበኩላቸው ”እሱን ተወው!” ያሉት መሰለኝ።

 

ኦባማ ግን ከጥቁርነቱ አልተነሣም፤ ለይቶ ለጥቁር አሜሪካኖችም አልተነሳም፤ በነጮች ላይም አልተነሳም። ኦባማ የተነሳው በእውቀት ከተገነባው ሰውነቱ ነው፤ ከአሜሪካዊ ሰውነቱ ነው የተነሳው፤ ለአሜሪካ ህዝብ በሙሉ ነው፤ ለነጩም ለጥቁሩም፣ ለሌላውም። በምርጫ ዘመቻው ጊዜ ተወዳዳሪዎቹም ሆኑ ጋዜጠኞች ኦባማን በዘር ፖለቲካ ውስጥ ለማስገባት ሞክረው አልሆነላቸውም። ስለዚህም ጥቁር ቆዳው ላይ ሳይሆን ሰውነቱና አዋቂነቱ ላይ ማተኮር ተገደዱ። ተወዳዳሪዎቹ ያልቻሉትም በዚሁ ነው። የሱን የቆዳ መጥቆር ሰርዘው፣ የተወዳዳሪዎቹን የቆዳ መንጣት አብሮ ሰረዘው፤ ሰውና ሰው ተወዳደረ። ቡሩክ ኦባማ አሸነፈ። የጥቁሮችም የነጮችም እንባ ረገፈ፤ በዚህ እንባ የአሜሪካ አሳፋሪ የዘረኛነት ታሪክ ፀዳ፤ ቆዳውን ካለፉ ሁሉም ሰው መሆኑን በድምፅ ብልጫ ወሰኑ፤ ሰውነታቸውን አወቁ፤ የቡሩክ ኦባማ ረድዔት ይህ ነው። ይህ ያልገባቸውና ያልተቀበሉት አሜሪካኖች እንቅልፍ አይወስዳቸውም፤ የቡሩክ ኦባማ ሥጋት ይህ ነው።

 

ቡሩክ ኦባማ ለአሜሪካ ምን ይዞ መጣ? በተሳለና በብሩህ አዕምሮ፣ በተከማቸና በተደላደለ እውቀት፣ በላቀ የመንፈስ ልዕልናና በመንፈሣዊ ወኔ፣ የአሜሪካ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም ህዝቦች በሙሉ የጥቁር ሰውነት እንዲቀበሉ አስገደዳቸው፤ በዘመናችን የጥቁር ህዝብን ስብዕና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ካደረሱት ሁለት ጥቁር ሰዎች ቡሩክ ኦባማ ሁለተኛው ነው፤ አንደኛው ኔልሰን ማንዴላ እንደሆኑ ግልጽ ነው።

 

ቡሩክ ኦባማ ለአሜሪካ የሚመርጣቸውን የባለሥልጣኖች ዓይነት፣ በምክትል ፕሬዝዳንቱና በቤተመንግሥቱ አስተዳዳሪ አሳይቷል። ትልቅ መሪ ለመሆን ትልልቅ ሰዎችን የመምረጥ ችሎታ ያስፈልጋል። ትልልቅ ሥራ በትንንሽ ሰዎች አይከናወንምና እያሰቡ የሚያሳስቡ፣ ልበ ሙሉ ሰዎችን መምረጥ የመሪነቱን ብቃት ያረጋግጣል። ይህንን በቅርቡ የምናየው ይሆናል።

 

ቡሩክ ኦባማ አሜሪካን አነቃ፤ እስከ ዛሬ በሀብታሞች እየታመሰ የፖለቲካውን ሥራ በሙሉ ለነሱ ለቅቆ የነበረው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘውና የወጣቱ ክፍል፣ ኅልውናውንና የወደፊት ዕድሉን ለመቀየስ ቆርጦ ተነሣ። ለወትሮው ለምርጫ ዘመቻ የሚያስፈልገው ወጪ ሁልጊዜም ከሀብታሞች የሚገኝ በመሆኑ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ቁጥጥር ነበር። በምርጫ ጊዜ በሀብታሞችና በገንዘባቸው የተነሣ ከምርጫው ጋር የነበረውን ቁርኝት ኦባማ በጠሰው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉት መራጮችና ወጣቶች፣ በትንንሹ እንደአቅማቸው ገንዘብ በማዋጣት፣ ከሀብታሞች ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት እንደሚችሉ አሳየ። አምስት ሀብታሞች በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር ቢያዋጡ፣ አምስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ተራ ሰዎች ሁለት ሁለት ብር ብቻ በማዋጣት፣ የአምስቱን ሀብታሞች ያህል ለማበርከት ይችላሉ። ስለዚህም የጥቂት ሀብታሞችን የገንዘብ ጉልበት፣ በብዙዎች ቆራጥ ተራ ሰዎች ትናንሽ መዋጮ ለመተካት እንደሚችል አረጋገጠ። የኦባማ የምርጫ ዘመቻ በመስከረም ወር ብቻ፣ አንድ መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ ቻለ። በገንዘብ ኃይል በሩን የሚከፍተው የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ ተከፈተ። አንገቱን ደፍቶ የነበረው የአሜሪካ ህዝብ ክፍል ነፍስ ዘራ፤ ለመብቱ ለመቆምና የኦባማን የለውጥ ጥሪ ለመቀበል ”እንችላለን!” ብሎ ተነሳ።

 

የኦባማ የለውጥ ጥሪ እያስተጋባ ሲሄድ የአሜሪካ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ አንድ በአንድ ከኦባማ ጎራ ገቡ። የኬኔዲ ቤተሰቦች፣ የክሊንተን ቤተሰቦች፣ እነኬሪ፣ እነኮሊን ፖውል፣ እነኦፕራ፣ … ሌሎችም ብዙ ታላላቅ ሰዎች የኦባማ ደጋፊዎች ሆኑ። ብዙ ጋዜጣዎችም የኦባማ ደጋፊዎች ሆኑ። ከተቀናቃኝ ቡድኑም (ከሪፐብሊካን ፓርቲ) ተለይተው ወደ ኦባማ የገቡ እንደኮሊን ፖውል (በኢራቅ የመጀመሪያውን ጦርነት (የባህረ-ሠላጤውን ጦርነት) የመሩ ጄኔራልና በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር) ያሉ ሰዎች ነበሩ።

 

ከአሜሪካ ውጭም ቢሆን የቡሩክ ኦባማ ደጋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር የሚያስደንቅ ነው። አሜሪካ ብቻ ሳይሆን ዓለም በሙሉ ተቀብሎታል ለማለት ይቻላል። ቡሩክ ኦባማ የገባበት ዓለም በተለይ በኑሮ ጭንቀት ላይ ነው፤ እግዚአብሔር ይርዳው!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ