አንድ ዕይታ አስራ አንድ አስተያየቶች፤ ስለቀጣይ “ምርጫ” እና ቀጣይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አካሄድ
“ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሳተፍ፤ መግባት አለባቸው” ተክለሚካኤል አበበ
በ2010ም እ.ኤ.አ. ይሁን ከዚህ በኋላ፡ መቼም “ምርጫ” ከተካሄደ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢህአዴግ መንግሥትነት በሚካሄድ ማናቸውም ምርጫ መሳተፍ ይገባቸዋልን? የሚለውን ጥያቄ፡ “አዎ መሳተፍ አለባቸው!” ብቻ ሳይሆን “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሳተፍ፤ መግባት አለባቸው” ማለቴ ብዙዎቻችሁን ሳያስገርም ምናልባትም ይሄ ሰው ምን ነካው? ጤነኛም አይደል እንዴ ሳያሰኛችሁ አይቀርም።
ከምርጫ 2010 ጋር በተያያዘ ለተደረገ ውይይት የቀረበ የመነሻ ሃሳብ
ተክለሚካኤል አበበ (ቫንኩቨር- ካናዳ)
በ2010ም እ.ኤ.አ. ይሁን ከዚህ በኋላ መቼም “ምርጫ” ከተካሄደ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢህአዴግ መንግሥትነት በሚካሄድ ማናቸውም ምርጫ መሳተፍ ይገባቸዋልን? የሚለውን ጥያቄ፤ “አዎ መሳተፍ አለባቸው!” ብቻ ሳይሆን “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሳተፍ፤ መግባት አለባቸው” ማለቴ ብዙዎቻችሁን ሳያስገርም ምናልባትም ይሄ ሰው ምን ነካው? ጤነኛም አይደል እንዴ ሳያሰኛችሁ አይቀርም። ይሄንን ያልኩበትን ምክንያት ከመዘርዘሬ በፊት ለማነሳቸው ዋና ዋና ነጥቦቼ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡልኝና የአድማጮቼን ምናብ ለመሰብሰብ አንድ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን አስቀድሜ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ።
አንደኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ህወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ አድረጓል፣ ወደፊትም ያደርጋል፣ በኢትዮጵያ ውስጥም ነፃ ምርጫን ሊያስተማምኑ የሚችሉ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ማለትም ነፃ ምርጫ ቦርድ ወይንም ነፃ ፍርድ ቤት አሉ ብዬ አላምንም። አሁን ባለው ሁኔታ ነገሮችን ወደፊት ካላሻሻለ በስተቀር ነፃና ተወዳድረን የምናሸንፍበት ወይም የምንሸነፍበት የምርጫ ሥርዓት የለም። ዋናው ትግልም እነዚህን ነፃ ተቋማት መፍጠሩ ነው። ስለዚህ ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ መግባት አለባቸው ስል በሰፊው ዴሞክራሲን ለማምጣት በጠባቡ እነዚህን ነፃ ተቋማት ለመፍጠር በምናደርገው ትግል የተቃዋሚዎች ነፃ እንዳልሆኑ በምናምናቸውም ተቋማት ውስጥ መታገል አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማምንና በሌሎችም ዝቅ ብዬ በምጠቅሳቸው ምክንያቶች እንጂ ነፃ ምርጫን ተስፋ ከማድረግ በመነጨ ምክንያት አይደለም።
ሁለተኛ ተቃዋሚዎች ወደምርጫ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መግባት አለባቸው” ስል አሁን ያለውን የምርጫ ሕግና ጠቅላላ የፖለቲካ ሁኔታ መልካም እንደሆነ ተቀብለው በእኩልነት እንደሚወዳደሩ አምነው ምንም ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያስቀምጡ ይግቡ ማለቴ ሳይሆን፤ ትክክለኛና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ያስቀምጡ፤ በምንም መልኩ ግን አስቀድመው እነዚህ የምናስቀምጣቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ ወደ ምርጫ አንገባም የሚል መደራደሪያ አያስቀምጡ ለማለት ነው። በሌላ አነጋገር። ወደ ምርጫ እንገባለን፤ ወደምርጫ የምነገባው ግን ምርጫው ፍትሃዊ ይሆናል፤ ነፃ የምርጫ ቦርድ አለ ብንበደል የምንከስበትና ፍትህ የሚሰጠን የምንተማመንበት ነፃ ፍርድ ቤት አለ ብለን ሳይሆን እነሱ የሉም ብለን እነሱም አለመኖራቸውን ለዓለም ለማሳየትና እነሱ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥም ይሄንን ሥርዓት ለማሸነፍ አንቦዝንም ብለው ይግቡ ለማለት ነው።
ሦስተኛ ሰዎች የሚያዋጣቸውን የትግል መንገድ የመምረጥ ህዝብም ያንን የትግል ስልት መከተል ወይም አለመከተል መብት አለው። ይሄ ተቃዋሚዎች የሚከተሉትን መንገድ ካልወደደውም ራሱ ህዝቡ ሊያስተምራቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መልስ ሊሰጣቸው ይችላል የሚለው ግምቴም ይታወቅልኝ። ይሄንንም ትንሽ ልሞርደውና በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ ሥርዓቱን የሚረዳ ወይም የሚያግዝ ወይንም የሚደግፍ ሥራ እስካልሠሩ ድረስ ተቃዋሚዎች የመሰላቸውን የትግል መንገድ የመምረጥ መብታቸው የተጠበቀ ነው ከሚል ግምት ተነስቼ ነው። የዚህ ተቃራኒውና ግልባጩ ምንድነው እሱ ተቃዋሚዎች ወይም ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግን ለመጣል የሚታገል ኃይል መከተል ያለበት ወይም ያለባቸው መንገድ አንድ ብቻ ነው ያልን ዕለት በምርጫ የማናምን ሌላ ኢህአዴግን እንሆናለን። ያ ደግሞ እንዲወገድ የምንፈልገውን ችግር እኛም ደገምነው ማለት ነው።
እነዚህን ብዬ የሚቀጥሉትን ደግሞ እላለሁ። ወደ አንደኛው ነጥቤ ላምራ። በዚሀ ሰዓት እንደኔ አስተያየት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ኬንያን እያየ፣ ዙምባቤን እያየ፣ ራሷን ኢትዮጵያን እያየ የኢህአዴግ ትልቁና ዋንኛው ፀሎቱ ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ አንገባም እንዲሉና እንዳይገቡበት ነው። በምንም መልኩ እንደ 2005ቱ ምርጫ የሚያሳጣውና የሚፈታተነው ተወዳዳሪ ፓርቲ እንዳይኖር ለማድረግ የማይሳለው ስለት አይኖርም። ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ቢገቡ ለኢህአዴግ ራስ ምታት ነው። ታዛቢዎች ሊመጡ ነው። መገናኛ ብዙኀንን ሊለቅ ነው። ሊሳጣና ሊተች ነው። በረሃብና በኑሮ ውድነት የተማረረው ህዝብ በሱ ላይ አሁንም በድጋሚ እንዲነሳሳና እንዲያምጽ የሚቀሰቅስ መድረክ እንዲፈቅድ ሊገደድ ነው። ሙስና ሊጋለጥ ነው። ስለዚህ የተቃዋሚዎችን ወደ ምርጫ መግባት ከማንም በላይ የማይፈልገው ራሱ ኢህአዴግ ነው። ስለዚህ ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ አንገባም ቢሉ አትራፊው ኢህአዴግ ነው። ያንን በማለታቸው ተቃዋሚዎችም ይሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያተርፉት ምንም ነገር የለም ብቻ ሳይሆን ይጎዳሉም።
ወደ ምርጫ መግባት ለተቃዋሚዎች ትልቅ ኃይልን፣ ብርታትንና አሁን ያጡትን መድረክ ይሰጣቸዋል። በርግጥ ይሄንን ያልኩት ወይም የምለው ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ቢገቡ ኢህአዴግ በይሉኝታም ይሁን በግድ ለተቃዋሚዎች ትንሽም ብትሆን የመንቀሻቀሻ፣ የመናገሪያ፣ የመከራከሪያ መድረክ ይሰጣቸዋል ብዬ በመገመት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ የለም ምንም መድረክ አልሰጥም ካለ ይሄ የጠቀስኩት ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ላያስኬድ ይችላል። ከሆነና ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ፊት ለፊት በህዝባዊ መድረኮች ወይም በመገናኛ መድረክ ላይ ከተቀመጡ ኢህአዴግን ሙስና የኢህአዴግን ሰው ሠራሽ ረሃብ የኢህአዴግን ሰው-ሠራሽ ሽብር ለማጋለጥና ኢህአዴግ ላይ ለማላገጥ ምርጫ ባይገቡ የማያገኙትን መድረክን ያገኛሉ።
ዞሮ ዞሮ ተቃዋሚዎች ምርጫ ባለመግባታቸው የገቡትም ከምርጫ በመውጣታቸው ኢህአዴግ ምርጫ ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ባለፈው ሚያዝያ ያደረገውን ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈበትን የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ልብ ይሏል። ምርጫውም ተደረገ ኢህአዴግም ይገዛል እኛም የፈየድነው ምንም ነገር የለም። እንደውም ይባስ ብሎ ሦስት ሚሊዮን ተወዳዳሪዎች አቅርቦ አረፈው። በዘጠና ዘጠኝ ከመቶው መሰለኝ ያሸነፈው። ተቃዋሚዎች ምርጫ ቢገቡም ባይገቡም ኢህአዴግ ምርጫውን ያደርጋል። ምናልባት ከፓርላማ ምርጫ ጋር ሲወዳደር የወረዳና የቀበሌ ምርጫ ብዙ ቦታ ላይሰጠው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በላፈው ሚያዝያ በተደረገው የኢህአዴግ ምርጫ ተቃዋሚዎች ላለመሳተፋቸው አጥጋቢ ምክንያት ቢኖርም ከዚያ ተቃዋሚዎች ካልተሳተፉበት ምርጫ ይልቅ ተቃዋሚዎች የተሳተፉበት ምርጫ ነው ከፍተኛውን የህዝብ ስሜት የቀሰቀሰ፣ የዓለምን ምላሽ የቀሰቀሰ፣ የእኛ በውጭ የምንገኘውንም ኢትዮጵያዊያን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ ያንቀሳቀሰ። ስለዚህ በምርጫው ባለመሳተፍ የምናገኘው ምላሽ በምርጫ መሳተፍ ከምናገኘው ምላሽ ወይም ተነሳሽነት የላቀ ነው የሚል ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር፣ በምርጫ መሳተፉ በምርጫ ካለመሳተፉ የበለጠ ውጤታማ ነው።
በዲሞክራሲያዊም ይሁን ዴሞክራሲያዊ ባልሆኑ ሀገሮች ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብንመለከት (ካናዳን፣ ኬንያን፣ አሜሪካን፣ ጋናን፣ ራሷን ኢትዮጵያን ይመለከቷል) ገንዘብ በማዋጣት፣ አባላትን በማደራጀት፣ ቅስቀሳን በማስፋት ረገድ ተቃዋሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱት የምርጫ ሰሞን ነው። ያለፈውን የኢትዮጵያን ምርጫ ብንመለከት ተቃዋሚ ድርጅቶች አብዛኛውን ኃይላቸውንና ገንዘባቸውን እንዲሁም ድርጅቶቻቸውን የማቀናጀት ግንባር የመፍጠር ሥራ ላይ የተሰማሩት በምርጫው ሰሞን አስቀድሞ ባሉ ጥቂት ወራት ውስጥ ነው። ምርጫ ካለና ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ካንቀሳቀሳቸው አባላትን ለመመልመል ገንዘብ ለማሰባሰብ፣ ግንባር ለመፍጠር፣ ሥርዓቱን ለማሳጣት እና ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ትክክለኛውና ወርቃማው አጋጣሚ ምርጫ ነው። ተቃዋሚዎች ምርጫ ውስጥ ካልገቡ ምንም አይነት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ዕድልም ሰበብም አይኖርም። በሠላማዊ መንገድ እዚያው ሀገር ቤት እንታገላለን ብለው የሚንቀሳቀሱትን ድርጅቶች ማለቴ ነው። ከዚያ መለስ እንታገላለን የሚሉ ወይም የምንል ሀገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ጋር የማያገናኝና እኛው እዚሁ ልንወጣው የሚገባን የቤት ሥራ ስላለን ይሄ ጽሑፍ እኛን አይመለከትም።
ይሄን ካነሳሁ አይቀር ግን ይሄ ተቃዋሚዎች ምርጫ ውስጥ መግባት አለባቸው ማለት ሌላ የትግል መስክ አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ መጥቀስ እሻለሁ። ወይንም እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በተለምዶ በሠላማዊ ትግል እየተባለ በሚጠራው ስልት የማምን ሆኜ አይደለም። የሀገር ቤቱ ትግል ራሱን በቻለ ማዕቀፍ ውስጥ ነው መቀመጥና መገምገም ያለበት ከሚል እንጂ። አሁንም ለማስተካከል ያህል አንዳቸው ስለአንዳቸው አይመለከታቸውም ወይንም አንዳቸው አንዳቸውን አያግዙም ለማለት ሳይሆን፤ ይሄ ይሁን ያኛው ግን አይሁን ስንል ሁለቱንም በየራሳቸው ተገቢ መሆን አለመሆን እንጂ አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ሊያመጡ ከሚችሉት ስሜት በመነጨ መሆን የለበትም ለማለት ነው።
ምርጫ ውስጥ መግባት በምንም መልኩ ሌላኛውን ከምርጫ መለስ ያለ የትግል እንቅስቃሴ አያግድም። በሌላ የትግል መንገድ የምናምን ሰዎች በምንም መልኩ ምርጫ ውስጥ የሚገቡ ድርጅቶችን እንደ እንቅፋት ልንወስዳቸው አይገባም። ሌላኛውን የትግል ስልት መከተልና ምርጫ ውስጥ መግባት ከቶም መንገድ ላይ የማይጠላለፉና ቢጠላለፉም እንኩዋን ሁለቱንም መንገዶች የሚከተሉትን ሰዎች የሚያጠቃ የጋራ ጠላት የጋራ ጨቋኝ ባለበት ሁኔታ አንዱ ከሌላኛው ሳይቃረኑ የሚሄዱ ስልቶች ናቸው። ሌላ የትግል ስልት የሚከተሉ ሰዎች ሀገር ቤት ያሉትን ድርጅቶች እንደጠላት ወይም እንደምቀኛ ሊያዩ የሚችሉበት ምንም አይነት ምክንያታዊ ግንኙነት የለም።
ምርጫ ኢህአዴግን ለዓለም ኅብረተሰብ የማሳጣቱ አንደኛው መንገድ ነው። ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ተሳጥቷል ትሉኝ ይሆናል። ግን ትግሉም ይሁን የማሳጣቱ ዘመቻ የሚያበቃው ያሸነፍን ዕለት ብቻ ነው። ዙምባብዌንና ሱዳንን እንዲሁም ኬንያን ይመለከቷል። አምና አሳጥተነዋል። ካቻምናም አሳጥተነዋል። በቂ ነው የምንለው ደረጃ ላይ የምንደርሰው ግን የምንፈልገውን ያገኘን ዕለት ብቻ ነው። እስከዚያው ብዙ ሥራ ይቀረናል ማለት ነው። ዓለም ኢህአዴግ ትልልቅ በደሎችን ቢፈጽምም አብሮት ከመብላት ወደኋላ አላለም። ስለዚህ የማሳጣት ትግላችን ማባራት የለበትም ማለት ነው። ያ ደግሞ አንዱ መንገዱ ምርጫ መሳተፍና በራሱ በኢህአዴግ ሜዳ በኢህአዴግ መድረክ ኢህአዴግን ማሳጣት ነው ማለት ነው።
ወደ ምርጫ መግባት አንድ የትግል ስልት ነው እንጂ ብቸኛ ስልት አይደለም። ምርጫ ውስጥ መግባት አለመግባት ራሱ ምርጫ ነው። በምርጫ የምናምን ሰዎች ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ቢገቡ ምርጫቸውም ማክበር አለብን። የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫውን የማያምነበት ከሆነ አያምንበትም ብዬ አምናለሁ፤ ያንን ህዝቡ ለተቃዋሚዎች በተለያየ መንገድ ሊያሳያቸው ይችላል። ስለዚህ መራጩ ህዝቡ ራሱ መልሱን ይስጣቸው እንጂ እኛ ወደ ማውገዝ ልንገባ አይገባም። ተቃዋሚዎች አንሳተፍም ብለው ቢቀሩ እንኩዋን ኢህአዴግ ሌሎች አሻንጉሊት ተቃዋሚዎችን ከመፍጠርና ምርጫው ውጤታማና ዲሞክራሲያዊ ነው ከማለት ወደኋላ አይልም። ይችልበታልም። አድርጎታልም።
ወደ ምርጫው መግባት ማለት እስከምርጫው ዋዜማ ሃሳብን መለወጥ አይቻልም ማለት አይደለም። ሀገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ባይገቡ አከተመላቸው። ወደ ምርጫ ቢገቡ ግን ኢህአዴግን ለመዋጋት ተጨማሪ ዕድል አገኙ ማለት ነው። እንደ ተወዳዳሪ ከምርጫ ቦርድም ይሁን ከውጭው ዓለም ታዛቢዎች ጋር መገናኘትና መነጋጋገር በየዕለቱም ኢህአዴግን ማሳጣት ይችላሉ። ወደ ምርጫ ባይገቡ ወደ ምርጫ ቢገቡ የሚያገኙትን ዕድል አያገኙም። ተቃዋሚዎች ከምርጫ ውጪ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ምንም አጀንዳ የለም። ተቃዋሚ ድርጅቶች የጽዋ ማኅበራት አይደሉም፣ በየወሩ እየተሰበሰቡ ለመለያየት አይደለም የተደራጁት። ምርጫ ካልገቡ፣ ስብሰባቸው ጽዋ ከመሆን አያልፍም።
እጃቸውን አጣጥፈው ቢቀመጡ ምን እናገኛለን? ምክንያቱም በምርጫ በተገኘ አጋጣሚና ሰበብ ከመንቀሳቀስ ውጪ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ውጪ ሊሠሩ የሚችሉት ነገር አይታየኝም። ተቃዋሚዎች የምርም ይሁን አይሁን በኢህአዴግ ሕገመንግሥት እንወዳደራለን ብለው ፈርመው ሥርዓቱ ባዘዘው ልክ ብቻ ለመንቀሳቀስ የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው። ሰልፍና አመጽ፣ አድማና የመሳሰሉት ሌላ ነገር ተብለዋል። በዚያም ያለኃጢያታቸው እስር ቤት ገብተዋል። ሌላ ነገር መደረግ አለበት ካልን ያንን የምናደርገው ወይም ማድረግ ያለብን እኛ በዚህ የኢህአዴግ ሕገመንግሥት አናምንም የምንልና በሥርዓቱ ላይ ያመጽን ሰዎች እንጂ ሀገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች አይደሉም። እነሱማ መንገዳቸውን መርጠዋል መንገዳቸውም ሥርዓቱ በፈቀደው ቦይ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ነው። ያ መንገድ ተሞክሮ ትንሽም ቢሆን ሠርቷል። ቀደም ሲልም ወደ ምርጫ ሲገባ የተስተካከል ነገር ኖሮ ሳይሆን በዚያችው ኢህአዴግ በፈጠራት ክፍተት ውስጥ ለውጥ እናመጣለን ተብሎ ነው። ስለዚህ ከዚያ የተለየ ነገር የለም።
ሌላው ምክንያቴ ሁሉንም እንቁላላችንን ባንድ ቅርጫት ማስቀመጥ የለብንም ከሚል የመነጨ ነው። በሌላ መንገድ የምንታገል በሌላ መንገድ መታገል እንችላለን። ትግሉን ሁሉ ግን ባንድ ስልት፣ ባንድ ድስት፣ ባንድ መንገድ ውስጥ ልናስገባው አንችልም። በምንም መልኩ አንድ መሆን አንችልም። ምክንያቱም ለዚህች ሀገር ያለን አጀንዳም አንድ አይደለምና። የአረናና የቅንጅት አጀንዳ፣ የኦነግና የኢህአፓ አጀንዳ፣ የኢዴአፓና የሕብረት አጀንዳ አንድ አይደለም። ስለዚህ አንድ አይነት አቋም እንዲወስዱ መጠበቅ የለብንም። ያ ከሆነ በሠላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ሀገር ቤት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የመረጡት ስልትና አጀንዳ ከነዚህ በብዛት ፈሰው ከሚገኙ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ነው። ያንን የነሱን ስልት ከኛ ስልት ጋር በግድ እንደብልቅህ ብንለው የተለያየ ተፈጥሮና የተለያየ ንጥረ ነገር ስላላቸው ዘይትና ውሀ የመደብለቅ ያህል ይሆናል ብቻ ሳይሆን ይሄ ሂደት ሲሰበር ተሰበረ ነው።
ሠላማዊም እንበለው ሌላ ኢህአዴግ የሚፈቅደውን ብቻ መንገድ መከተል የራሱ ጉዳት የሉትም ማለት አይደለም። ጉዳት ይኖረዋል። ግን በሠላማዊ ትግሉም ሰዎች መስዋዕትነት ይከፍላሉ። ስለዚህ ብርቱካን ወይንም መራራ ወይንም ልደቱ ወይንም ኢንጂንየር ኃይሉ በዚህ በመረጥኩት መንገድ ልሙት ካሉና ህዝብም ሊሞት ከተከተላቸው፣ ያ መብታቸው ነው ማለት ነው። በርግጥ ያንን መብታቸውን በቀጥታ የሚቃረን ያለ አይመስለኝም። ካለም ስህተት ነው። ነገር ግን ተቃርኖው የሚመጣው የነሱ የሠላማዊ ትግል ለምሳሌም በምርጫ መሳተፍ ኢህአዴግን ዲሞክራሲያዊ አስመስሎና በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ዲሞክራሲ ያለ አስመስሎ ትርፉ ለኢህአዴግ ብቻ ነው። ያ ደግሞ ሌሎቻችን ኢህአዴግን ለመጣልም ይሁን ለማሳጣት በተለይም በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድ ጫና ለመፍጠር ለምናደርገው ትግል እንቅፋት ይፈጥራል። አሉታዊም ነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ያንን ስጋት መቅረፍ ይቻላል።
ተቃዋሚዎች በሀገር ቤት ተመዝግበን መንቀሳቀስ የምንችልበት ክፍተት አለ፤ በዚያም ተንቀሳቅሰን በምርጫ በመሳተፍ ውጤት እናመጣለን ብለው በመሰናዳት፤ ነገር ግን በምርጫው መሳተፍ ኢህአዴግን ከመጥቀም ውጪ እርባና ቢስና ትርጉም የለሽ መሆኑን አረጋግጠው ከምርጫም ይሁን ከሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን ማግለልና እኛ ኢህአዴግን በዓለም ማኅበረሰብ ፊት ማሳጣት የፈለግንበትን ጫና መፍጠር ይችላሉ። ስለዚህም ወደ ምርጫ መግባት አስፈላጊ ነው ብቻ ሳይሆን የግድ ነው። ወደ ምርጫ መግባት የሚያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ አለ። በትክክል። ዋናው ጥያቄ ግን የቱ ይበልጣል ነው? ወደ ምርጫ በመግባታችን የሚመጣው ጥፋት ወይስ ባለመግባታችን የምናጣው ዕድል? ሁለተኛ ያ ወደ ምርጫ መግባት ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ተቃዋሚዎች በየደረጃው በሚወስዱት እርምጃ መቀነስ እንችላለን።
እንደማሰሪያም ለኔ መጥፎው ተቃዋሚዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባታቸው ሳይሆን፤ ምርጫው ምርጫ እንደማይሆን እያወቁ በምርጫው ውስጥ ቢቆዩና የኢህአዴግ አዳማቂ ቢሆኑ ነው። ምርጫን ምርጫ የሚያሰኘው ድምፅ የሚሰጥበት ዕለት የሚደረግ ሽርጉድ አይደለም። በሌላ አነጋገር ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ሂደት ውስጥ ተቃዋሚዎች አሸነፉ ቢባልም ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ አያደርገውም። ስለዚህ ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ገብተው ሲንቀሳቀሱ በሚያልፉበት ሂደት ውስጥ በሚያጋጥሟቸው አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች ኢህአዴግን ካሳጡና የምትገኘውን ትንሽ መድረክ ተጠቅመው ከላይ የዘረዘርኳቸውን ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ የኢህአዴግን የምርጫ ውጤት ሕጋዊ ለማስመሰል ብቻ ያህል ወይንም ከዚያ የበለጠ ፋይዳ በማይኖረው ሁኔታ ምርጫ ውስጥ ቢቆዩ ለኔ ትልቁ ችግር ያ ነው። ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ በፈቀደላቸው ልክ ብቻ ነው ወይ መንቀሳቀስ ያለባቸው? ከዚያ ባሻገር ትግላቸውን ማሳደግ የለባቸውም ወይ? ይሄ መልሱ ግልጽ ነው። እነሱ ናቸው የሚያውቁት። ሰው አቅሙን የሚያውቀው እሱ ራሱ ነው። ለሴትም እሷ ራሷ። ለእናንተም እናንተ። አመሰግናለሁ!
ቅዳሜ ታኅሳስ 4 ቀን 2001 ዓ.ም. (Saturday, December 13, 2008)