ልጅ ተክሌ - ከካናዳ

የሚሳፈር ይሳፈር፣ የማይሳፈር ይቅር፤ ቀኑ ሲደርስ ግን ሁሉም ይሳፈራል

 

ሀገሬ መግባት እፈልጋለሁ!!

“ሀገሬ መግባት እፈልጋለሁ!! እኔ ሌላ ምንም ዓላማ የለኝም። ወያኔ አትገባም ብሎ ከሶኛል። ወያኔ ከተሰቀለበት የትዕቢትና እብሪት ሰቀላ ተፈጥፍጦ ወርዶ ማየትና በሀገሬ በነፃነት መኖር እፈልጋለሁ።” አለኝ ኤልያስ ክፍሌ፤ ከኤርትራ መልስ አንዳንድ ነገሮችን ስናወጋ። ይኸው ነው ይሄንን ልጅ እንቅልፍ አሳጥቶ ሠላም ነስቶ ከዲሲ አስመራ፤ ከዚህ እዚያ የሚያንከራትተው።

 

ኤልያስ አንዳንድ ጊዜ ያበሳጭ ይሆናል። ”ኤልያስ ተው ሰው አትንካ! የትጥቅ ትግልን ለማራመድ የግድ ብርቱካንን ማውገዝ የለብንም። የለም ሠላማዊ ትግል አያዋጣም፤ የቀረን ትጥቅ ትግል ብቻ ነው ብለህ መከራከር ትችላለህ። ያንተን ክርክር አሳማኝ ለማድረግ ግን እነ ብርቱካን ሚደቅሳን መዘልዘል፣ እነ ዶ/ር ኃይሉን ማዋረድ የለብንም። እነ ዶ/ር መራራን ማበሻቀጥ አያስፈልገንም። እንደዚያ አይነቱ ነገር ትክክል ስላልሆነ ብቻ ሳይሆን ያንን ባደረግክ ቁጥር ፍጥጫው በእኛና በኢህአዲግ መሀከል መሆኑ ይቀርና የትጥቅ ትግል በሚያራምዱ ወገኖችና በሠላማዊ ትግሉ አራማጆች፤ በተለይም ደግሞ በአንድነት ደጋፊዎች መካከል ይሆናል። ተው ሰው አትንካ!”

 

የኢህአዲግ ሥራ ይበቃል፤ የህወሓት ጥፋት

 

ሰዉን የትጥቅ ትግል እንዲቀበል ኢህአዲግ የሚሠራው ሥራ በቂ ነው። ኢህአዲግ የሠላማዊውን ትግል ምህዳር እያጠበበ እያጠበበ ሲመጣ፣ በአራት ዓመት ውስጥ አንድ ሠላማዊ ሰልፍ ሲከለከል፣ በአራት ዓመት ውስጥ ሁለት ህዝባዊ ስብሰባ ሲነፈግ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ የቴሌቭዥ ማስታወቂያ ማሰማት ሳይቻል ሲቀር፣ የሰማኒያ ዓመት አዛውንት ያለፍርድ ሲታሰሩ፣ የአስራ ሰባት ዓመት ወጣቶች በግንባራቸው ተመትተው ሲገደሉ፣ በየዓመቱ በረሃብ የሚቀጠፍ ሰው ቁጥር ሲጨምር፣ በየዓመቱ የሚሰደድ ሰው ቁጥር ሲያሻቅብ፣ የሀገሪቱ መሬት ለዓረብና ሱዳን ሲቸበቸብ፣ የአንድ ብሔር ልጆች እንደ እንቧይ እስኪያብጡ ሲፈነጩብንና ሲወቅጡን፣ ... ይሄ ሁሉ ህዝቡን ወደለየለትና ወደባሰበት የትጥቅ ትግል ያመጣል። ከኢህአዲግ በኩል የሚሠራው ሥራ በቂ ነውና ከኛ በኩል ህዝቡን ወይንም ድርጅቶችን የትጥቅ ትግል እንዲመርጡ የሚያስገድድ ማስፈራሪያና ስድብ፤ አታካራና ጭቅጭቅ አያስፈልግም። ኢህአዲግ ያንን ሥራ በሚገባ እየሠራ ነው። የኛ ሥራ ሌላ ነው።

 

አብዮተኛው ኤልያስ፤ አብዮታዊ ሃሳቦች

 

ኤልያስ ዘወትር የሚያነሳቸው ሃሳቦች አብዮታዊ፣ ከዘመናቸው የቀደሙ፣ ደፋርና ሰው ለመግባትና ለማንሳት የሚፈራቸው ናቸው። ለምሳሌ አንድ ግዜ ኤልያስ በሌሊት ተነሳና “የግዞት መንግሥት ማቋቋም ያስፈልገናል” አለ። ብዙዎች ተንጫጩ። ይሄ ሰው ምንድነው የሚያወራው? ምንስ ነው የሚናገረው? ብለው ተሳለቁበት። ጥቂቶቻችንን ግን አስደነቀን። አስፈነደቀንም። ወዳጄ ተክሌ የሻው ሰሞኑን “ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የለችም” የሚል አስደንጋጭ ክርክር አምጥቷል።

 

ዐፄ ኃይለሥላሴ በዚያም በዚህም ብለው በመለኮታዊ መቀባት ሥልጣኔን አገኘሁ ብለው ለዓመታት ህዝቡን አሳምነውት ህዝቡም ”ፀሐዩ ንጉሣችን” እያላቸው ኖሩ። ኢህአዲግ ግን የሽፍታ ጭምብሉንና ኮንጎ ጫማውን በሲቪል ልብስ ለውጦ ሥልጣን ላይ ያለ ምንም ሕጋዊ መሰረት የሌለውና በጡንቻውና በዓለም አቀፉ መንግሥታት ችሮታ ብቻ ሥልጣን ላይ የቆየ አገዛዝ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን የሚወክል የግዞት መንግሥት ለማቋቋም መብቱም ችሎታውም አለን። የኤልያስ ሃሳብ ትክክል ነው።

 

የግዞት መንግሥት ለምን? ከነማንስ ጋር?

 

የግዞት መንግሥት ብናቋቁም የሚቀበሉን መንግሥታት አናጣም። ኤርትራ በተማመን ከጎናችን ነች። ሌሎች ከኢህአዲግ ጋር የተጣሉ መንግሥታትም ከጎናችን ናቸው። ኤርትራ ራሷ ልታመጣልን የምትችለው የወዳጅና የአቅም ብዛት የትየለሌ ነው። ብዙ ሰዎች ያለፈውን የጦርነትና የደም መፋሰስ ዓመታት በማሰብ ኤርትራን እንደ መንጸፈ ደይን ይፈሯታል። ብዙ ሰዎች እንደውም ከኃጢያት ይልቅ ኤርትራን ይፈራሉ። እዚህ ጋር ሲዖል፣ እዚያ ጋር ኤርትራ አለች ቢባሉ ወደ ሲዖል የሚመርጡም አሉ። ያ ስህተት ነው። ያለፈ አልፏል። ያለፈውን አንለውጠውም። ዘመን ይለወጣል። ከኤርትራ ጋር ለመሥራትና ለመወዳጀት የሚያስፈልጉን ነገሮች በጣም ኢምንትና ጥቂት ናቸው።

 

አንደኛ ኤርትራ ሀገር መሆኗንና በምንም መልኩ የኤርትራን ሉዓላዊነት እንደማናሰጋ ቃል መግባት። ቃል መስጠት። ሁለተኛ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት ሀገሮች አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፈጥረው በሠላምና በትብብር እንደሚኖሩ መስማማት። እነሱ ባህር አላቸው። እናም ምጣኔ ሀብት። እነሱ ጨው አላቸው። እኛም በርበሬ። ሦስተኛ ታላላቅ ሰዎችና ድርጅቶች ግንባር ፈጥረው በቀጥታ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ልዑካን ልከው መነጋገርና መቀመጫችውን በአስመራ አድርገው የግዞት መንግሥት መቋቋም። አለቀ።

 

ለጊዜው ብዙዎች ወይንም የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄንን ላይደግፈው ይችላል። ግን ራሱን ኢህአዲግንና ሻዕቢያን ጨምሮ ማንም ኃያል ህዝብ በደገፈው መንገድ አይደለም ሥልጣን ላይ የመጣው ወይም የወጣው። ካሸነፍን ህዝብ ሁልግዜም ካሸናፊ ወገን ነው። የዐፄ ምኒልክ እርግማንና ግዝት ልጅ ኢያሱን አልጠቀመም፤ የኃይለሥላሴ ድል አድራጊነት ግን ሥልጣን ላይ አቆያቸው። 50 ዓመታት ግድም። ግማሽ ክፍለ ዘመን። ስለዚህ የምንፈልገው ማሸነፍ ከሆነና በኤርትራ መጓዙ እንዲሁም የግዞት መንግሥት መቋቋሙ ለማሸነፍ ከረዳን ሰዎች ደገፉትም ተቃወሙትም ያንን ለማድረግ ማመንታት የለብንም።

 

ግንቦት ሰባት፣ ግንቦት ሃያ፣ ግንቦት ሰባት

 

”አሁን የወሬ ጊዜ አብቅቷል” ብሏል ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ። አሁን የሥራ ጊዜ ነው። ኢህአዲግ ሥራውን ሠርቷል። እየሠራም ነው። ከግንቦት ሃያ በፊትም በኋላም። የቀረው የኛ ክፍል ነው። የኛ ሥራ። ኢህአዲግን ለመጣል ግንቦት ሰባት የሚጸየፋቸውና የሚያፍራቸው መንገደች ሊኖሩ አይገባም። ዶ/ር ብርሃኑ ጓደኞቹንና የሥራ ባልደረቦቹን ሰብስቦ ወደ አስመራ ቢወርድ፤ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ለሙአመር ጋዳፊ ያደረጉትን ያህል ደማቅ አቀባበል ነው የሚያደርጉለት። ዝርዝሩን መነጋገር ነው። ካለመነጋገር ነው ካለመጠየቅ ደጃዝማችነት ይቀራል። ኢህአዲግ የሠላምና የእፎይታ አገዛዝ መግዛት የለበትም። ህወሓትም ይሁን ልጆቹ እንቅልፍ አጥተው እንቅልፋቸውን እንግሊዝ እንዲተኙ ማድረግ አለብን። እስካሁን ለንደንና ዲሲ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ ሠርተናል።

 

አሁን ደግሞ እዚያው ሜዳ ላይ መውጪያ ጊዜ ነው። ከኤርትራ የተሻለ፣ ከኤርትራ የቀረበ፣ ከኤርትራ የተመቸ ሜዳና መንገድ እንደሌለ ደግሞ ከዚህ ቀደም ጽፌአለሁ። ተራው የግንቦት ሰባት ነው። ከፍተኛ ልዑካን ልኮ ከኤርትራ መንግሥታ ጋር መነጋገርና ከኤርትራ ጋር መሥራት፣ የስደት መንግሥት ማቋቋምና ከዓለም መንግሥታት ጋር መጻጻፍ ለብቸኝነት የቀረበ መንገድ ነው። ደግሞ ኤርትራ የኢትዮጵያ ውለታ አለባት። ኤርትራን እንደ ሀገር የተቀበለቻት ሀገር “ኢትዮጵያ” ነች። ማለቴ ያው ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት እኛን የሚወክለው ሥርዓት ኢህአዲግ ነውና። ስለዚህ ኤርትራም የኛን የስደት መንግሥት ለመቀበልና መቀመጫ ለመስጠት የመጀመሪያዋ የማትሆንበት ምክንያት ምንድነው? ምንም!


 

ልጅ ተክሌ - ከካናዳ (ግንቦት 2001 ዓ.ም. / ግንቦት 2009 እ.ኤ.አ.)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ