ያሸንፋል ፍቅሩ

የፍትህ ሚኒስቴር ታኅሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም.፣ በስሙ ያወጣውና በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተደመጠ፣ የተነበበው መግለጫ ለአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2001 ዓ.ም በአገሪቱ ፕሬዝዳንት የተሰጣት ይቅርታ የተነሳው በራሱ በፍትህ ሚኒስቴር ውሳኔ መሆኑን የሚያመለክት ነው። መግለጫው ለይቅርታው መነሳት መሠረት ያደረጋቸውን የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት ዐዋጅ ቁጥር 395/1996 16(253)ንም ጠቅሷል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሊቀመንበርነት የሚመሩት አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ግን ይህን የፍትህ ሚኒስቴር መግለጫ አልተቀበለውም። እንደውም ታኅሳስ 21 ቀን 2001 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት የተሰጠን ይቅርታ አንቀጽ 16 (253) እንደምን ሆኖ ነው ለማንሳት በቂ ምክንያት ተደርጐ የቀረበው በማለት ጠይቆ፣ ድርጊቱን ሕጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው በማለት ገልጿል።

 

ይህ የአንድነት መግለጫ በወጣ በሰዓታት ግዜ ውስጥ፣ የመልስ መልስ የመሠለ ለሕጋዊ ጥያቄ ሕጋዊ ማብራሪያ ሳይሆን የማስፈራሪያ ይዘቱ ያመዘነ መግለጫ ያወጣው የፍትህ ሚኒስቴር አንቀጽ 16 (253) በአንቀጽ 4(3) እና 10(2) ሲተካ ለዚህ የበቃበትን ምክንያት አልገለፀም። ይህም ጉዳዩ ከመነሻው ፖለቲካዊ ነው ለሚሉ ወገኖች የክርክር ማጠናከሪያ ሆናቸው። የሕጉን ሥርዓት በበላይነት የሚመራው የፍትህ ሚኒስቴር እንዴት እንዲህ ዓይነት ተራ የሕግ ስህተት ውስጥ ይወድቃል ሲሉም ይጠይቃሉ።

 

ከዚህም በኋላ ቢሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ፣ ይቅርታው የተነሳው በሕግ አግባብ ነው ከሚል ሾላ በድፍን የሆነ ምላሽ ወጪ፣ አንቀጽ ጠቅሶ፣ ጉዳዩን አብራርቶ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም። እንዲሁም ጥያቄ አታንሱ ዓይነት አገላለፅ ነው የሚቀርበው።

 

የተፈፀመው ድርጊት ሕግን ተከትሎ የሆነ አይደለም ብሎ መጠየቅ ሕጋዊ አካሄድ ነው። ሊበረታታ እንጂ ሊስፈራራ አይገባውም። ተጠያቂው ወገን ማድረግ ያለበትም “በሕግ አግባብ የተፈፀመ ነው” የሚለውን ድርጊት፣ በማስረጃ እያቀረበ ማሳመን ነው። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ወገኖች ግን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢን ጨምሮ ሂደቱ ሕጋዊ አይደለም ስንል ዐዋጁን ዋቢ በማድረግ ነው።

 

ዐዋጅ ቁጥር 395/1996 በብርቱካን ላይ ከተወሰደው ርምጃ አንፃር ሲቃኝ

 

ይህ ዐዋጅ ትርጓሜ በሚለው ክፍሉ አንቀጽ 2(3) “ፍርድ ማለት በወንጀል ጉዳይ በፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተወሰነ ዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት ወይንም የጥንቃቄና ጥበቃ ውሳኔ ነው” ይላል። በአንቀጽ 4 ደግሞ “የይቅርታ ጥያቄ ማለት አንድ ፍርድ በሙሉ ወይንም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣቱ አፈፃፀምና ዓይነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈፀም የሚቀርብ ነው” በማለት ይተረጉማል።

 

ስለ ይቅርታ ጥያቄ አቀራረብ የሚገልፀው የዐዋጁ ክፍል ደግሞ 6 ንዑሳን አንቀጾች ያሉት ሲሆን ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲህ ይላል “በወንጀል ጉዳይ በፍ/ቤት ተከሶ የመጨረሻ ፍርድ የተፈረደበት ማንኛውም ሰው፣ የተወሰነው ፍርድ በሕግ ይቅርታ የሚያስከለክል ካልሆነ በስተቀር የይቅርታ ጥያቄውን ራሱ ወይንም በባለቤቱ፣ በቅርብ ዘመዶቹ በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ማቅረብ ይችላል።”

 

ይህ አንቀጽ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን መያዙን ልብ እንበል። የይቅርታ ጥያቄው መቅረብ የሚችለው ከመጨረሻ ፍርድ በኋላ መሆኑንና ጥያቄው በማን እንደሚቀርብ በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን።

 

የይቅርታ ጥያቄ መቼ እንደሚቀርብ ይበልጥ ግልፅ የሚያደርገው፣ ይህን ብቻ የሚገልፀው አንቀጽ 14 (1) ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በማናቸውም ጊዜ ሊቀርብ ይችላል በማለት በማያሻማ ሁኔታ በግልፅ አስፍሯል።

 

ከምርጫ 97 ውጤት ጋር ተያይዞ፣ ለእስር የበቁትና ከ21 ወራት ቆይታ በኋላ በይቅርታ የተፈቱት ወገኖች፣ የይቅርታ ሂደት ወይም አፈፃፀም ግን ከላይ የተጠቀሱትን የዐዋጁን ድንጋጌዎች አንዱንም ያሟላ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ የፍትህ ሚኒስቴርን መግለጫ ራሱን በዋቢነት ጠቅሶ መከራከር ይቻላል። ቀደም ብሎም እንደምናውቀው መግለጫውም አስታውሶ እንዳረጋገጠው፣ የይቅርታ ደብዳቤው የተፈረመው ሰኔ 15፣ ፍርድ የተሰጠው ሐምሌ 9፣ ታሳሪዎቹ ቃሊቲን ለቀው የወጡት ሐምሌ 13 ነው። ይህም የይቅርታው ጥያቄ የቀረበውና ሂደቱ የተጠናቀቀው፣ ከመጨረሻው ፍርድ በፊት ነው ለማለት ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው።

 

እነርሱ በቀጥታ ባይጠይቁም፣ ተጠየቀላቸው ኋላም አምነው በደብዳቤው ላይ ፈረሙ የሚል መከራከሪያ የሚነሳ ከሆነ፣ ለዚህ ምላሽ የሚሰጠው የዐዋጅ አንቀጽ 12(2) ነው። የፍትህ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ይቅርታ ሊደረግላቸው የሚገባቸውን ሰዎች በመምረጥ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉ ይህ አንቀጽ ይገልፃል። የቀድሞ ቅንጅት አመራሮች የፈረሙት ደብዳቤ የተፃፈው በሽማግሌዎች ነው የለም ለጠ/ሚኒስትሩ ነው የሚለውን ሙግት ለጊዜው ትተን፣ ደብዳቤው ለቦርዱ (ኮሚሽኑ) የቀረበው በጠ/ሚኒስትሩ አማካኝነት መሆኑን፣ በወቅቱ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተነገረንን ስናስታውስ፣ ጉዳዩ በዚህኛው አንቀጽም በተገለፀው መሠረት ያልተስተናገደ መሆኑን ያለምንም ጥያቄ መቀበል ይቻላል።

 

ከዚህም ሌላ አንድ የይቅርታ ደብዳቤ ሊያካትታቸው የሚገቡ ገዳዮችን፣ አንቀጽ 13 በአሥራ ሦስት ንዑሣን አንቀጾች ይዘረዝራል። በወቅቱም ሆነ አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተመለከትነውና የተነበበልን፣ እኛም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነበብነው ይቅር ተባዮቹ የፈረሙበት ደብዳቤ ወቅታዊና ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው መልዕክት እንጂ በዐዋጅ ከተጠቀሱት አንድም አልሠፈረበት። ይህም ጉዳዩ ከይቅርታ ዐዋጁ ጋር እየተመሳከረ ያልተፈፀመ ለመሆኑ በቂ ማሳያ ነው።

 

ከዚህ በላይ በመጠኑ ከዐዋጅ አንቀጽ ጋር እየተነፃፀረ የቀረበው ድርጊት የሚያሳየን፣ የሀገር ሽማግሌዎቹም በወቅቱ የገለፁት፣ እኛም በጊዜው ትኩረት ሰጥተን የተከታተልነው ይቅርታ የተፈፀመው 18 ወራት በፈጀ የሽምግልና ሂደት እንደሆነ ነው።

 

ፍትህ ሚኒስቴር የጠቀሳቸው አንቀጾች ከጉዳዩ ጋር ያላቸው አግባብነት

 

ፍትህ ሚኒስቴር በታኅሳስ 20 የመጀመሪያ መግለጫው የጠቀሰው አንቀጽ፣ 16 (2) “የይቅርታ ጥያቄ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ፣ የይቅርታ ውሳኔ በማጭበርበር ወይንም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም” የሚል ነው።

 

ወ/ት ብርቱካን ላይ የቀረበው ክስ ይቅርታ አልጠየኩም ብለሻል የሚል እንጂ ይቅርታውን ያገኘ ሰው በማታለል ወይንም በማጭበርበር ነው የሚል አይደለም። ይቅር ተባዮቹና የቦርዱ ሰዎች የተገናኙት፣ ለደቂቃዎች ይህ ፊርማህ(ሽ) ነው ወይ? ለሚል ጥያቄ ብቻ ከመሆኑ አንፃር፣ የማታለልና የማጭበርበር ጥያቄ ሊነሳ አይችልም። ደብዳቤውንም ከራሳቸው ሃሣብ አፍልቀው፣ ይቅርታ የመጠየቁን ሃሣብ እነርሱው አቅርበው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ሳይሆን የፃፉት በሽማግሌዎች አግባቢነት ተጽፎ በቀረበላቸው ደብዳቤ ላይ ነው የፈረሙት። በመሆኑም በደብዳቤያቸው ላይ ሀሰተኛ ነገር አሥፍረው፣ አሳስተዋል ሊባልም አይችልም።

 

ከዚህም በላይ ደብዳቤው ለቦርዱ የቀረበው፣ የሽማግሌዎች ወደ ጠ/ሚኒስትሩ፣ ከጠ/ሚኒስትሩ ወደ ቦርዱ በተደረገ ቅብብሎሽ በመሆኑ፣ ቦርዱ ይቅር ተባዮችን አታላችሁኛል፣ አጭበርብራችሁኛል በማለት የሚያስነሳ መንገድ የለውም።

 

በፍትህ ሚኒስቴር የመጀመሪያ መግለጫ የተጠቀሰው ሁለተኛው አንቀጽ (16) 3 “በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ፣ ቅድመ ሁኔታው መጣሱ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም የሚለው ነው።” እዚህ ጋር ሁለት ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ይቅርታ አልጠየኩም ብለሻል ማለት እና ቅድመ ሁኔታ ተነስቷል ማለት እንዴት ይገናኛል? ቅድመ ሁኔታ የተባለው ሕገ-መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር፣ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ የመንግሥት የሥልጣን አባላትን ሥልጣን ተቀብሎና አክብሮ መንቀሳቀስ የሚል ነው። እነዚህ በተለይ በይቅርታ ለተፈቱ ሰዎች ብቻ ተለይተው ቅድመ ሁኔታ ሆነው የሚቀመጡ፣ ሌላውን ዜጋ የማይመለከቱ ጉዳዮች ቢሆኑ “ይቅርታ አልጠየኩም ብለሻል” የሚለው ክስ የትኛውን ቅድመ ሁኔታ መጣስ የሚያሳይ ነው?

 

ሁለተኛው ጥያቄ ስለማታለል ወይንም ማጭበርበር የሚገልፅ እና ስለ ቅድመ ሁኔታ መጣስ የሚገልጹ አንቀጾች እንደምን ለአንድ ጉዳይ በአንድ ላይ ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ? የመጀመሪያው ይቅርታውን ለማግኘት ሲባል የሚፈፀም፣ ሁለተኛው ይቅርታው ከተገኘና ተፈፃሚ እየሆነ ባለበት ወቅት የሚፈፀም ነው። ፍትህ ሚኒስቴርን ለትዝብት፣ ሂደቱንም ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው ለመባል ያበቃው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ፍትህ ሚኒስቴርም ይህንኑ ተገንዝቦ ይመስላል በሁለተኛው መግለጫው አንቀጹን የለወጠው።

 

ቅድመ ሁኔታ ተጥሷል የሚል ክስ አልቀረበም ሊቀርብም አይችልም። ከዚህ አንፃር ወ/ት ብርቱካን ልትመሠገን እንጂ ተጠያቂ ልትሆን አትችልም። ላስረዳ። ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ሠላማዊ ትግል ማካሄድ አይቻልም ሲባል፣ የለም ይቻላል እንጂ መቼ በቅጡ ተግባራዊ አደረግነውና ብላ የሞገተች፣ በሠላማዊ ትግል ለውጥ አይመጣም ሲባል ይዘገይ እንደሁ እንጂ ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ ነው ያውም አስተማማኝ ለውጥ በማለት የተከራከረች፤ ኢህአዴግ ጠላታችን ነው ሲባል፣ እኛ የሰው ጠላት የለንም ብላ ኢህአዴግም አቶ መለስም ጠላት አይደሉም ብላ በአደባባይ የተናገረች የሕግ የፖለቲካና የእውነት ሰው ነች።

 

ፍትህ ሚኒስቴር በሁለተኛ መግለጫው የጠቀሳቸው አንቀጾች

 

የፍትህ ሚኒስቴር በታኅሳስ 21 ቀን 2001 ሁለተኛው መግለጫው ላይ፣ አንቀጽ 16 በመተው የጠቀሳቸው አንቀጽ 4(3) እና 10(2) ነው። እነዚህም ቢሆኑ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ የሌላቸው መሆኑ ሲታይ፣ ድርጊቱ ከጅምሩ በቅጡ ታስቦበት የተፈፀመ ያለመሆኑን ያጋልጣሉ።

 

አንቀጽ 4 የሚገልፀው የቦርዱን ሥልጣንና ተግባር ሲሆን፣(አንቀጽ 3 ላይ የሠፈረው፣ “በፕሬዝዳንቱ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ የሚሰጣቸው ሰዎች፣ ቅድመ ሁኔታውን አላሟሉም ወይም ጥሰዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ጉዳዩን መርምሮ ለፕሬዝዳንቱ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል” ነው የሚለው።

 

ቦርዱ የውሳኔ ሃሣብ ሊያቀርብ የሚችለው፣ የከሳሽን ክስ ብቻ አዳምጦ ሳይሆን፣ ይቅር ተባዩ ይቅርታው እንደተነሳበት ክስ የቀረበበት መሆኑን አውቆ፣ ምላሽ ሰጥቶ ቦርዱ ግራና ቀኙን መርምሮ መፈፀም እንዳለበት የሚገልጽ፣ ራሱን ችሎ በግልጽ ቋንቋ የሠፈረ አንቀጽ 17 አለ። የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ይቅርታ ለማሠረዝ የሚያበቃ በቂ ምክንያት ከተገኘ፣ ምክንያቱ በግልፅና ይቅርታ የተደረገለት ሰው በሚገባው ቋንቋ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ፣ ለይቅር ተባዩ እንዲደርሰው ይደረጋል ይላል። ቦርዱ ያልፈፀመው ፍትህ ሚኒስቴርም በተደጋጋሚ መግለጫው ሊያነሳው ያልቻለው ይህንን ነው። አንቀጽ 17(2) ደግሞ ደብዳቤው የደረሰው ሰው ምላሽ ለመስጠት ከ20 ቀን ያላነሰ የማግኘት ዕድል እንዳለው ይደነግጋል። ወ/ት ብርቱካን ግን በደብዳቤ ሣይሆን በፖሊስ ነው የተጠየቀችው። ቦርዱ ከሷ የሰማው ምንም ነገር የለም። በፖሊስ የተሰጣትም የ3 ቀን የጊዜ ገደብ ነው። ለመሆኑ ፖሊስን ማስጠንቀቂያ ሰጪ፣ በይቅርታ ጉዳይ ጠርቶ አነጋጋሪ ያደረገው የትኛው ዐዋጅ ይሆን? ቦርዱ ለፕሬዝዳንቱ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በምን ላይ ተመሥርቶ እንዳቀረበ ማስረዳት ይችላል። የዐዋጁ ቁጥር 395/1996 አንቀጽ 17 ባልተሟላበት ሁኔታ፣ ይቅርታን የማንሳት ውሳኔ በምንም ሕጋዊ ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው ፍትህ ሚኒስቴር በሁለት መግለጫው ቀያይሮ ያቀረባቸው አንቀጾች፣ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ቅርበት የላቸውም የሚል መከራከሪያ የሚቀርበው።

 

ክቡር የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንትም ይህን ታላቀ የሕይወት ጉዳይ፣ በታሪክ ሠፍሮ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጉዳይ በፊርማቸው ሲያፀድቁ ሕግን ተከትሎ የተፈፀመ የዐዋጁን ድንጋጌዎች ያሟላ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አይጠበቅባቸው ይሆን? ፍትህ ሚኒስቴር የይቅርታ መነሳቱን ውሳኔ የሰጠው እሱ መሆኑን ከገለፀበት፣ ያለ ዐዋጅ በራሱ ሥልጣን ከሰጠበት ድፍረት አንስቶ፣ በመጠኑ ከዚህ በላይ በንፅፅር የቀረቡት ጉዳዮች የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር፣ ድርጊቱን የፈፀሙት ለሕጉ ሣይሆን ለፖለቲካው የቀረቡ ሰዎች ይሆናሉ የሚል ጥርጣሬ የሚያጭሩ ናቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ