ጉዞ ወደ ቃሊቲ፤ በመድረክ “መድረቅ”

አባኪያ - ከሀገረ ካናዳ

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ ያነበብኩት፡ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ “የኤርትራ ጉዳይ” ላይ ከቶም የማይዘነጋኝ አንድ ፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ወይንም ወልደዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ ይመስሉኛል ያን ጊዜ በአውሮፓ ሆኖ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ለሚከራከረው አክሊሉ ሀብተወልድ የተናገሩት አረፍተ ነገር አለ። “አንተ ከዚያ በርታ እኔ ከዚህ እበረታልሀለሁ” አይነት ነገር። በዚህ ሰዓት ብርቱካን ያንን የምትችል መሰለኝ።

 

ያለችበት ሰቆቃ፤ ያም ይመር ይሰለች ይሆናል። በሆነ ተአምር በሆነ ምትሀት እኛን ከሷ እሷን ከኛ የሚያገናኝ መንገድ ቢሰራ፤ ያንን ብቻ የምትል መሰለኝ። “እናንተ ከዚያ በርቱ እኔ ከዚህ እበረታለሁ።” መበርታታችን ግን ገለባውንና ያ የስዊድኑ ወዳጄ “አርቲ ቡርቲ” የሚለውን ጉዳይ እያነሳን ሳይሆን የሚበጀውን፣ የሚያታግለውን፣ የሚያስማማንን፣ ከምንም በላይ ግን ለኢትዮጵያ የሚበጀውን እያነሳን ነው ጎበዝ። የኛ ነገር ሁለት ሳምንት ርስ በርሳችን የሚያባላ ርእስና ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳንወልድ መሰንበት አንችልም። ሁለት ሳምንት። አሁን በእውኑ “መድረክ” ተፈጠረ ብሎ መነታረክ “መድረቅ” እንጂ ሌላ ምን ይባላል? በ”መድረክ” ጉዳይ አንድም ቀን “መድረቅ” የለብንም። ጎበዝ በመድረክና በመድረቅ የሚፈታ ነገር ካለ፤ መልካም ግፉበት። ለጊዜው ግን ብርቱካን ታስራለች። ወደ ቃሊቲ እንመለስ። በዚህ በብርቱካን መታሰር ጉዳይ ላይ እዚህ ካናዳ ያናገርነው አንዱ የፓርላማ አባል እንኩዋን ያለው ያንን ነው።

 

የካናዳው ምክር ቤት አባል “ወ/ት ሚደቅሳ የእስራት ምሳሌ ነች”

 

እኛ ኢትዮጵያዊያን መልስ ያጣንለትን ጥያቄ ያ ካናዳዊው መለሰው። በዚህ በብርቱካ መታሰር ጉዳይ ከካናዳ ም/ቤት ተወካይ ወደ ሌላው ተወካይ ስንመላለስ ስሙን የማልጠቅሰው አንዱ ታላቅ የምክር ቤት አባል ዘንድ ደረስን። ከቢሮው ገባን። ተቀመጥን። የሄድንበትን ጉዳይ ማስረዳት ጀመርን። “ እኛ በካናዳ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ካናዳዊያን ነን፤ የመጣንበትም ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት (ይቅርታ፡ ወያኔ/ኢህአዴግ የሚለውን ቃል ላይረዳው ይችላል ብለን ነው) አንዲት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ መሪ ሴት ያለምንም ፍትሐዊ መሰረት አስሮ ወደ ወህኒ ስለወረወራት፤ ስለወረወራትም ብቻ አይደለም፡ ይህቺን ምስኪን ያንድ ሴት ልጅ እናት አስሮ ሲያበቃ ከሌሎች እስረኞች እንዳትገናኝ፣ ጠበቃዋን ጨምሮ ሌሎች ዘመዶችም እንዳታገኝ ከልክሎ በቆርቆሮ ክፍል አስሯት …”። ሁሉንም ነገርነው።

 

እንደመታደል ሆኖ ይሄ የምክር ቤት ተወካይ ገና ከዚምባብዌ መመለሱ ነበርና የምንለውን ለመረዳት ምንም አልቸገረውም። ትኩረታችን ሁሉ ብርቱካን ላይ በመሆኑ ትንሽ ያልተመቻት አስተዋይ እህታችን ጣልቃ ገባችና፡ “ብርቱካን ብቻ አይደለችም የታሰረችው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ እስረኛ ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች በመላ አገሪቱ ይገኛሉ።” አለችው። ትክክል ናት ትክክል ናት አልን። ያ የገባው ተወካይ እንዲህ አለ። “በጸረ አፓርታይድ ዘመንም ማንዴላ ማንዴላ ይባል እንጂ ማንዴላ ብቻ አይደለም እስር ቤት የነበረው። በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያንም እንጂ። ልክ ናችሁ። ይህቺ ሴት፡ ወ/ት ሚደቅሳም የሰብአዊ መብት ገፈፋ ምሳሌ ነች። She is an embodiment of the human rights violation in Ethiopia. She personifies the human rights abuses” አይነት ነገር አለ።

 

ብርቱካንን ስለማሰብ፤ በነገራችን ላይ ...  

 

ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው መፈክር ብቻ ነው። ታሪክ ሰሪ ግለሰቦችም ናቸው። ብርቱካን ታሪክ መስራት አለባት። ብርቱካን ታሪክ እየሰራችም ነው። ብርቱካን የታሰሩትን ብቻ የምትወክል ታላቅ ሴት አይደለችም። ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በሚነሱና ወሳኝ በሆኑ የጾታና የብሄር ጉዳዮች በመጪው ዘመን እንደ አስታራቂ ልታገለግል የምትችል ሴትም እንጂ። በብርቱካን ውስጥ ይሄንን አየሁ። ይሄንን እኔ በሷ ውስጥ ያየሁትን እሷም ላታየው ትችላለች። እኔ ግን ተገለጠልኝ። ለምሳሌ፡ ስለብሄርና ስለብርቱካን። ባለፈው ሰሞን አንዱን ወዳጄን ብርቱካን ኦሮምኛ ትናገራለች እንዴ ብዬ ስጠይቀው “በሚገባ፡ በደንብ አድርጋ” ብሎኛል። ይሄ ሰው ጨምሮም፡ “ደበበ እሸቱ ወደ ቫንኩቨር በመጣ ጊዜ ነው ያጫወተኝ ብሎኛል።” ለነገሩ ብርቱካን ብሎ ሚደቅሳ ነው። ሚደቅሳ ብሎ ደግሞ ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ ብሎ ደግሞ ኢትዮጵያ መሆኑን አሁን አሁን ኢትዮጵያዊነት ሽቅብ ሽቅብ የሚላቸው አንዳንድ ዘመን አመጣሽ ኦሮሞዎች ካልሆኑ በስተቀር ማንም አያጣውም። ለነገሩ ሰው ምንም ነኝ ወይም አይደለሁም ማለትም መብቱ ቢሆንም፤ ሰው ስላለና ስላላለ ብቻ የሚሆነው ወይም የማይሆነው ነገር የለም። ስለዚህም የብርቱካን ሚደቅሳ ኦሮምኛ መናገር እውነት ከሆነ፤ የብርቱካንን የወደፊት ፖለቲካዊ ዋጋ በእጥፍ ያሳድገዋል። የብርቱካንን ኢትዮጵያውያንን የመድረስና የመቤዥ አቅም ያጎለብተዋል።

 

በነገራችን ላይ፡ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ በልጦናል። በዚህ ረገድ የተስፋዬ ገብረአብ የቅርብ ጊዜ ትንተናው እንደተጠበቀ ሆኖ ኢህአዴግ በዚህ በብሄሮች ቋንቋ በመግባት ረገድ በልጦናል። ማንም ሰው፡ ማንም ህዝብ በቋንቋው ሲያናግሩት አንጀቱ ስፍስፍ ይላል። ልቡ ስንጥቅ ይላል። በዚያ ላይ ብርቱካን ሴት ነች። የሴት ልጅ ንግግርም የብዙዎችን ልብ ይተረክካል። ትፈታ እንጂ፤ ብርቱካን መናገር አለባት። በኦሮምኛ። ያም ብቻ አይደለም፡ የአንድነትን መርሀ ግብር አላውቀውም። ግን ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ሁለተኛ የስራና የብሄራዊ ቋንቋ እንዲሆን መታገልም አለባት እንጂ። ይሄንን ጽሁፍ መጻፍ ከጀመርኩ በኋላ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በሲያትል ስብሰባው ላይ የኦሮምኛ ቋንቋ ተጨማሪ የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የቅንጅት ምኞትም መርህም እንደነበረ ተናግሯል። ያንን እንገፋበታለን። ምክንያቱም …

 

ያኔ ቢሆን ኖሮ፤ አሁንስ ቢሆን?

 

የዛሬን አያድርገውና፡ ብርቱካን በትልልቅ መድረኮች ለምን ኦሮምኛ እንደማትናገር አልጠየቅኳትም። ለጊዜው ስለታሰረች ይሄንን ጥያቄ በይደር ትቼዋለሁ። እስከዚያው ግን ስለኦሮሞና ኦሮምኛ ቋንቋ ይሄንን እላለሁ። ኦሮሞና ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ውስጥ ካላወቅንበት ወሳኝና ሚዛን አዛቢ፤ ካወቅንበትም አስፈላጊና ሚዛን አርጋቢ ጉዳዮች ናቸው። ላቲኖን በላቲንኛ፤ ክቤኮችን በፈረንሳይኛ ነው ነገሩ። እዚህ ካናዳ እንደዚያ ነው። ፈረንሳይኛ ሌላኛው የካናዳ ብሄራዊ የስራ ቋንቋ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፡ የፈረንሳይኛ ተናጋሪዋ ክቤክ (ኩቤክ) ድምጽ መንግስትን በሚመሰርተው ፓርቲ ላይ ወሳኝ አሉታዊ ወይንም አዎንታዊ ተጽእኖ ስላለው ፈረንሳይኛ ሁለተኛ/ሌላኛው የስራ ቋንቋ ነው። በፈረንሳይኛ ክርክር ይደረጋል፣ በፈረንሳይኛ ቅስቀሳ ይደረጋል፤ በፈረንሳይኛ ይቦተለካል። ብርቱካን ከኢህአዴግ ቀድማ ኦሮምኛን ሁለተኛ የትዮጵያ ቋንቋ ማድረግ አለባት። ኦሮምኛን በደንብ መጠቀም አለባት። ሁለተኛ ስል ሌላኛው ቋንቋ ማለቴ እንጂ፡ በደረጃ ሁለተኛ ማለቴ አይደለም። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እንጂ ኦሮምኛ የአማርኛን ቦታ ለመያዝ ወይም ለማስለቀቅ ምንም አያንሰውም። ኢህአዴግ በሀይልና በጉልበት ብቻ አይደለም የተወሰነውን ህዝብ በራሱ ቋንቋ በማናገርም በልጦናል። ኢትዮጵያዊነት የግድ ኦሮሞነትን ወይንም ሲዳማነትን ወይም በየነ ጴጥሮስን የሚውጥ አማራነት መሆን የለበትም።

 

በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ተጨቁናችሁ ተበድላችሁ እያለ ብዙ ብሄሮችን በቋንቋቸው አናግሯቸዋል። ይሄንን ስል ፊታችሁን ጭፍግግ የምታደርጉ ብዙዎች ትኖራላችሁ። እኛ ተመቸን አልተመቸን አይደለም ነገሩ። እነሱ፤ እነዚያ በቋንቋቸው እንዲናገሩ፣ እንዲማሩና እንዲዳኙ የተደረጉት ተመቻቸው አልተመቻቸው እንጂ። እነሱ አንዳንዶቹ ጥሟቸዋል። የድሮዋ ኢትዮጵያ ብትቀጥል ላያገኙ የሚችሉትን ነገሮች አግኝተዋል። ይሄ ኢህአዴግን ስለመደገፍ ስላለመደገፍም አይደለም። ኢህአዴግን ምንኛ ብንቃወመውም እሱ በበለጠንና ለብዙ ጎሳዎች ወይንም ብሄሮች በሰጣቸው መብት መሰል መብቶች ላይ መነሳት የለብንም። የዛሬ ሀያ ዓመት አካባቢ በኦሮምኛ የሚዳኝ ዳኛ፤ በኦሮምኛ የሚሰራ ማዘጋጃ ቤት ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም። አሁን ያ አለ።

 

ትንሽ የሚያጨፈግግ ነገር ልመርቅላችሁ። የዛሬ ሀያ አምስት ዓመት አካባቢ ያ የኔ ጓደኛ ዲሮ አማርኛው ስለተንተባተበ የአርሲ ነጌሌ ከተማ ከንቲባ ሊሆን አይችልም ነበር። አሁን ከዚያ ነው መነሳት ያለብን። ኢትዮጵያን ሁሉ በአማርኛ ኢትዮጵያዊነት ማሰር አንችልም። ብርቱካን የምታስፈልገን ለዚህ ነው። በኦሮምኛም ጭምር እንጂ። ትፈታ እንጂ፤ ቅንጅትን ማለቴ አንድነትን አንድና ሙሉ ለማድረግ ብርቱካን ኦሮምኛ መናገር አለባት። የኔ ነገር፤ ከየት የት ዘለልኩ ጎበዝ። መጀመሪያ ይሄ በየምናምኑ የምንነታረከውን ነገር አቁመን ብርቱካንን ማስፈታት አለብን። ብርቱካን የእስራታችን ምሳሌ ነችና። እሷ ካልተፈታች መድረክ ብሎ ጦርነት መግጠም ምንም አይፈይድም። መድረቅ ይሆንብናል እንጂ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንደ ድርጅትም እንደ ግለሰብም የሚመቻቸውን ጉዞ መቀየስ መብታቸው ብቻ ሳይሆን ማድረግም አለባቸው። ከተመቸን መደገፍ። ካልተመቸን ልዩነታችንን አስታውቀን ሌላ አማራጭ መፈለግ። እንጂ ብርቱካንን እስር ቤት አስቀምጠን ሌላ አታካራ ውስጥ መግባት አይበጅም።

 

ጥሩ ሰዓት፡ ጥሩ ጊዜ ...

 

እንደውም ኢህአዴግ ብርቱካንን መልካም ሰዓትና ጊዜ ላይ ነው ያሰረልን። ኢህአዴግ ብርቱካንን በማሰር ዓርማ ሰራልን። ቀድሞ በአውራ ጣት ነበር። የአሁኑን ምርጫ ደግሞ በብርቱካን ይሆናል። ተቃዋሚዎችን መምራት ያለበት ከተቃዋሚ መሪዎች የተሻለ ሰው መሆን አለበት። ብርቱካን በእድሜ ከብዙዎቹ የተቃዋሚ መሪዎች ያነሰች ነች። በእውቀትም ከብዙዎች ትተካከላለች ለማለት ይከብዳል። በልምድም እንደዚያው። በዚህ ሁኔታ ያወቁትንና በእኩልነት እልህ ለማስተዳደር የሚያውኩትን ለመምራትና ለመገሰጽ፣ ቢናገር የሚደመጥ፣ ቢያዝ የሚሰማ፣ የሚታዘዙት፣ ቢገስጽ የማያኮርፉት፤ ይልቅስ የሚያፍሩት መሪ ያስፈልጋል። ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ብርቱካን ያ ተሰሚነት አልነበራትም። አንዳንድ ጫፍ ጫፋቸውን የምንሰማቸው የአመራሩ ንትርክም የመነጨው ከዚያ ይመስለኛል።

 

ብርቱካን ልቃ እንድትገኝና እንድትሰማ (ሰ ይጠብቃል) በእስር ቤት ወይንም በጠላትም ላይ ይሁን በወዳጅ ላይ የሞራልና የግርማ የበላይነት በሚያስገኝ ሂደትና ፈተና ውስጥ ማለፍ እንዲኖርባት የግድ ነው። ከዚህ ቀደም እንዳልነው፡ ያልታሰረ ማንዴላ፡ ያልታሰረች ኦንግ ሳን ሱኪ፤ ከኛ እንዳንዱ ናቸው እንጂ ከኛ በሞራል የላቁ አይሆኑም። ሁለት ወዶ አይሆንም። መምራት የፈለገ በሚያማርር ምሬት ውስጥ ያልፍ ዘንድ መልካም ነው። ብርቱካን በዚያ ውስጥ እያለፈች ነው። ብርቱካንም እስካሁን አልተረታችም። አትረታምም። ብርቱካን የምትረታው፤ ያ የተንኮለኞች ጥርቅም ወያኔ እኛ እዚህ ባህር ማዶ፡ “መድረክ” ምናምን እያል መነታረካችንን ያሰማት እንደሆነ ነው። ያ ሞራል ይነካል።

 

ዞሮ ዞሮ ብርቱካን ትፈታለች፤ ስትፈታ ግን ልቃ፣ ሁላችንም የምንከተላት ነጻ አውጪ ትሆናለች። ብርቱካን ጫካ በመግባት አታምንም። ብርቱካን ስለሰላማዊ ትግል የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነች። እነሆ ያ ይሆናል። ብርቱካን ስለእምነቷ እስር ቤት ስትገባ ካጨበጨብንላት ማለቴ ካደነቅናት፤ በተመሳሳዩም “የለም ኢህአዴግን የምናሸንፈው “በምርጫ” ነው ብላ ምርጫን ከመረጠች ምርጫዋን ማድረቅ አለብን። ኢትዮጵያን የሚለውጥ ከሆነ መድረክም ይሁን መብረቅ ብርቱካን የሚከፋት አይመስለኝም። ያልታሰሩት የአንድነት አመራሮች የሚያታግላቸውን መንገድ ለመምረጥ ከኛ የተሻለ ቦታ ላይ ናቸው። ስለዚህ መድረክ ያስኬደናል ካሉ እንተዋቸው። እንያቸው። የግድ እነሱ የሚጓዙበትን መንገድ እኛ ማጽደቅ የለብንም። ብርቱካንም ይሄንን የምትል መሰለኝ። ለጊዜው ግን ብርቱካንን እናስፈታ። አሁን የክርክር ግዜ አይደለም፤ የሰልፍ እንጂ። ሰዎቹ አይከራከሩም፤ ስራቸውን ግን ይሰራሉ። እነሆ ማርች ሁለት ቀን 2009 በያካባቢአችሁ ተሰለፉ። ቫንኩቨር ትሰለፋለች።

 

ተጻፈና ታተመ ብርቱካን በታሰረች በ58ኛው ቀን የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም.፡ 34/35ኛ ዓመት የህወሓት ምስረታ በዓል ሰሞን። 34/35 ዓመት ኖሩ ጎበዝ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ