እኩል ስናለቅስ፡ እናታችን የሞተችብንም እናታቸው ገበያ የሄደችባቸውም
የሪፖርተር ዘገባ፤ ባትወዱትም ስሙት
የማነ ናግሽ፤ የሪፖርተሩ ዘጋቢ የማነ ናግሽ፤ የካቲት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. ህወሓት የተመሰረተበትን 34ኛ ዓመት አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከህወሀት ተወካይ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ተገኝቶ እንዲህ ሲል ዘገበ። በነገራችን ላይ፡ የማነ የሚለውን ስም ስሰማ ድንግጥ እላለሁ። ስመ ሞክሼውን፡ የቀድሞ ወዳጄን ሌላኛውን የማነን ትዝ ስለሚያሰኘኝ ይሆናል። ስለሌላኛው የማነ ሌላ ጊዜ እነግራችኋለሁ።
ወደዚህኛው የማነ ዘገባ ልመልሳችሁ። እናም በዚህ በብሄራዊ ቲያትር በተደረገ ቲያትር (ስብሰባ) ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች "የካቲት 11 በመጣ ቁጥር እንጠይቃለን፤ መልስ ግን የለም፣ ፍትህ የለም፣ ሰው አለአግባብ በፖሊስ ይደበደባል፣ ተራራ እያፈረሰ የሚውል ሕዝብ ተገቢ ዋጋ አይከፈለውም፣ ብልሹ አስተዳደርና ሙስና ሰፍኗል፣ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች በክልሉ የሉም" ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ ይላል ዘገባው። ከመድረክ ሰብሳቢዎች የተሰጠው መልስ "የአንበሳ ድርሻ ፈልጋችሁ ከሆነ ትግሉን ወደኋላ ትመልሱታላችሁ" የሚል ነው። በተሰብሰቢዎቹ የተነሳውና በሰብሳቢዎቹ የተመለሰው ሁለት ነገሮች ገረሙኝ። ወይንም አሳቁኝ። በተወሰነ መልኩም አጠራጠሩኝ። ውስጤ በአብዛኛው የሚነግረኝ ሰዎቹ እያፌዙ እያላገጡብን እንደሆነ ቢሆንም እውነትም እነዚህ ሰዎች እውነታቸውን ይሆን እንዴ ብዬ ራሴን መጠየቄና መጠራጠሬ አልቀረም። የተሰብሳቢዎቹ “በሌሎች ቦታ የሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች በኛ ክልል የሉም” ክስና የሰብሳቢው የአንበሳውን ድርሻ ፈልጋችሁ ከሆነ መልስ እነዚህ ሰዎች ምንም እማያፍሩ “ጉዶች” መሆናቸውን ይጠቁማል። አንደኛ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ስለክልል አንድ ልማት መቆርቆር ሰውነቴ እንጂ አዲስ አበባ ልቤ እዚያው ትግራይ ተቀብሯል የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ሰው ስለትውልድ መንደሩ ማሰብ የለበትም ለማለት አይደለም።በዚህ እነሱ በመቆርቆር ባነሱት መልኩ ማለቴ ነው። ሁለተኛ በጦርነት የተጎዳ ክልል ተብሎ በግላጭና በአደባባይ፣ በአዋጅ ለብዙ አመታት የተደረገለትን ድጎማና ልዩ አስተያየት ሳንዘነጋ የራሱን የኢህአዴግ መንግስትን የበጀት መደልደያ ቅጽ ብንመለከት፤ ለአለፉት 18 አመታት ያገኙትን የአንበሳ ድርሻ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሆኖ ሳለ የጠያቂዎቹም ከሌላው ክልል አነስን የመላሹም የአንበሳውን ድርሻ አትጠብቁ ንግግር በኛ እውቀትና ችሎታ የማፌዝ ጽንፍ ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህን ጥያቄ ህወሓት ማድበስበስ የለበትም።" የስብሰባው ሰብሳቢ አቶ አታክለቲ ግደይም እንዲህ መለሱ "የምትሉት ነገር የትግራይ ሕዝብ ትልቅ መስዋዕትነት ስለከፈለ የተለየ ጥቅም ማግኘት አለበት ከሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከት የመነጨ ነው" ብለዋል፡፡ አስቂኝ። ባንድ በኩል እናታችን የሞተችብንም ገበያ የሄደችባቸውም እኩል ማልቀሳችን ቢሆንም በሌላ በኩል ከነዚህ ሰዎች ጋር በሀሳብ አልተገናኘንም ማለት ነውና የዚህ የትግራይና የትግራይ ተወላጆችን ነገር ደጋግመን እንድናነሳው ግድ ይለናል ማለት ነው። |
ስለትግራይ ካነሳን አይቀር፤ ስለልማት፣ ስለጥፋተኝነት
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ላይ ስለ ትግራይ የተጻፈ አንድ ዜና ትዝ ይለናል:: ያንን እዚህ ይመልከቱ (www.ecadforum.com) በነገራችን ላይ፡ ይሄ ስለትግራይ ህዝብ አይደለም፡ ጎበዝ። ስለ ትግራይ ልሂቃንና ስለ ህወሀት ጀሌዎች እንጂ። ከሕወሐት ጋር ተያይዞ፡ የትግራይና የትግሬዎች ስም በተነሳ ቁጥር የተባለውን ወይም የሚባለውን በቅጡ ሳያደምጡ ብቻ በራሳቸው ግምትና ስጋት ዘለው “ተዉ የትግራይን ህዝብ አብራችሁ አትወንጅሉ” የሚሉ አሉ። አንድ ነገር ርግጥ ነው። ሕወሀት ላደረገው ነገር ሁሉ የትግራይ ህዝብ ሊጠየቅ አይችልም።
ሕወሀት ለትግራይ ህዝብ የሚያደርገውን ማንሳት ግን ምንም ክፋቱ አይታየኝም። በተለይ ደግሞ እንዲህ እንዳሁኑ አይነት ስብሰባ ላይ እንዲህ አንዳለፈው አይነት እሪታ ሲያሰሙ ዝም ብለን ብናልፍ ያጃጃሉን ይመስላቸዋል። ስለዚህ ይሄንን ማለት መረጥን።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ግዜ ጀምሮ ትግራይን ብቻ አለማ ማለት የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ፍትሀዊ ልማት ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም። ወይንም እያንዳንዱ የትግራይ ሰው የዚህ ልማት ተቋዳሽ ሆኗል ማለት አይደለም። ቀድሞውንም ነገር የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ መልኩ መልማቱን፤ ልማቱም ኢፍትሀዊና በሌሎች ክልሎች ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኪሳራ መሆኑን ላያውቀው ይችላል። አያውቀውምም።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ለዚህ በኢህአዴግ ላይ ለሚነሳው ክስ ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ሕወሀት ኢትዮያዊነትን ሳይሆን ትግሬነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚሰራው ኢፍትሀዊ ስራ ማስረጃ እስካለን ድረስ መነሳት አለበት። ወይንም ሕወሀት/ኢህአዴግ የትግራይ ተዋላጆችን በከፍተኛ ሁኔታ እየመለመለ የትግራይ ተወላጆችን ባልነበረና ወደፊትም በፍትሀዊ መንገድ ሊሆን በማይችል መልኩ የሚሰራው በጎ ያልሆነ ስራ ካለ መነሳት አለበት። የትግራይ ህዝብም ይሄንን የማወቅ ግዴታም መብትም አለው። ኢህአዴግ ትግሬነትን መሰረት አድርጎ የሰራው ነገር አለን? ካለ መነሳት አለበት። ልክ የአማራውን የኦሮሞውን እንደምናነሳው።
ትንንሽ ምስክርነቶች
የዚህ ጽሁፍ አቅራቢና ጓደኞቹ በ1990/91/92/93 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቆዩበት ግዜ ህወሀት በት.ል.ማ. በኩል የትግራይ ተወላጆችን በሜጋ አምፊ ቲያትር ሰብስቦ አብልቶና አጠጥቶ እንዲሁም አስጨፍሮ ሲያበቃ ከሌላው ክልል የሚመጡ ተማሪዎች የማያገኙትን አገልግሎት ሲሰጥ የተመለከትን ምስክሮች ነን። እስኪ አስቡት፤ በዚያን ግዜ ባንድ ቤት የምትኖሩት ዜጋ እሱ ከሜጋ መለስ ቢራና ጥብስ ሲያገሳባችሁ ለመጀመሪያ አመት ፈተና የሚያዘጋጁ የትምህርት መሳሪያዎች ሲአገላብጥበቸሁ፤ እናንተ ምን ይሰማችኋል። ደባልነት።
በ1992 ዓ.ም. የህወሀት ወታደሮች የትግርኛ ስም ያላቸውን ሰዎች እየነቀሰ እያስቀረ የኦሮሞ ስም ያላቸውን ልጆች ሲደበድብና ሲያስር የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ተመልክቷል። ተመልክቻለሁ። ቀደሞ ባልነበረ መልኩ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሁሉም የንግድ ዘርፍና በመሬት ስጦታ ላይ እንዲሁም በመንግስትና በአበያተ ክርስቲያናት ሳይቀር የስራ እድል ከተከፈተላቸው፤ ነገር አለ ማለት ነው። በወታደር ውስጥ የሚሰሩ ጓደኞቼ ይሄንን የትግራይ ተወላጆችን ታማኝ አድርጎ የሌሎቹን ተቃዋሚ ናቸሁ፣ እንዲህ ናችሁ፣ እያሉ የማፈንና እድገት የመንፈግ ሁኔታ ነግረውኛል። ይሄንን የትግራይ ህዝብ ማወቅ አለበት።
አደጋው ይሄንን ማንሳቱ ሳይሆን ሁላችንም በውስጣችን የዚህ የዘረኛ ስራ ንዴት እየፈላ የለም የትግራይን ህዝብ አትናገሩ እያልን ባንናገረውና ኋላ ላይ ችግሩ የፈነዳ እለት ለት የሚፈጠረው ውጥንቅጥ ነው። ኢህአዴግ በሆነ መልኩ በሀይል ስልጣን ቢያጣ በየአካባቢው የሚገኙ በዘራቸው ምክንያት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ በሀብት የተመነጠቁና ባለጸጋ የሆኑ ሰዎች ያንን ካስተዋሉና በዚያም ከተጎዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን አደጋ አሁን ማንሳት ችግሩን ለመቅረፍ ያግዘናል እንጂ ችግር አያመጣም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ችግሩን ማንሳት የሚያመጣውን መለስተኛ ችግር በማሰብ እንዳናነሳ የምንተዋቸው ወይንም የምናግዳቸው ርእሶች በኋላ ላይ ባለመነገራቸው ሊያመጡ የሚችሉትን ችግር እንዳናስተውል አድርጎናል።
የሆነ ሆኖ፤ እንደ ማሳረጊያ
መቼም ይሄንን መሰረት አድርጎ የተደረገ ጥናት ባይኖርም ብዙዎቻችን በትግሪኛ ተናጋሪዎች አላግባብ መበልጸግና ያልተመጣጠነ እድገት በየአጋጣሚው ከአውሮፕላን ጣቢያ አንስቶ እስከ ቀበሌና ማዘጋጃ በየመንግስት መስሪያ ቤቱም በሚያሳዩት ትእቢት የሞላበት ድርጊት አንጀታችን እንደሚያር በተለያየ አጋጣሚዎች ብሰማም መልሰው ግን እነዚሁ ሰዎች የለም እባካችሁ ይሄንን ነገር ተዉ አታንሱ ሲሉ ይደመጣል። ችግሩ ካለና በምንም መልኩ የማይቀንስ እንዲያውም የሚብስ ከሆነ ችግሩ መነሳት አለበት እንጂ ተደባብሶ መታለፍ የለበትም። መጨነቅ ያለብን ችግሩን በምን መልኩ እናንሳው ነው። በተለይ ደግሞ እንዲህ እንዳሁኑ ተሰብስበው በሰበብ አስባቡ ላለፉት አስራ ስምንት አመታት በግላጭ ያገኙትን አብላጫ ጥቅማ ጥቅምና ብልጽግና ከካዱ ዝም ማለታችን የልብ ልብ ስለሚሰጣቸውና ሀሰት እንዲነግስ ስለሚያደርግ መናገር አለብን።
ባንድ በኩል ይሄ የትግራይ ተወላጆች ያደረጉት ስብሰባ የማስመሰልም ሊሆን ይችላል። ምን ይታወቃል አንዳንድ ሰዎች የትግራይም ህዝብ ከዚህ ስርአት ምንም እንዳልተጠቀመና እንዲያውም በዚህ ስርአት የተከፋ እንደሆነ ለማስመሰል የሚለፍፉቱን ልፈፋ በህዝብ ዘንድ ሰርጾ እንዲገባ ለማድረግ ወይንም የተቀረውነን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥርጣሬ ላይ ለመጣልና የለም እነዚህ ሰዎች እንደና የተገፉ ናቸው የሚለውን ሀሳብ ለማስፈን የሚደረግ ሙከራም ሊሆን ይችላል። እንጂ ምንም የማያጨቃጭቁ፣ በማናቸውም መለኪያ ቢሰፈሩ የትግራይ ህዝብም ይሁን ተወላጆች ላለፉት 18 አመታት ከተቀረው ኢትዮጵያዊም ይሁን እነሱ ቀድመው ከነበሩበት ሁኔታ በተሻለ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ስርአት እንደነገሰ አያጠራጥርም። እንግዲህ ይህቺን ካልኩ ዘንዳ ትርፍ ነገር ሳልናገር የትግራይንና የትግሬ ብሄረሰብ ልሂቃንን ነገር፡ በዚሁ ላሳጥረው። እስካሁን የተናገርኩት እንደ ትርፍ ነገር ካልተወሰደ ማለቴ ነው።
ያው፡ እኔው ነኝ። ከዚህ ከምስራቅ ካናዳ፡ 28 February, 2009


