ለአንድነት ምክር ቤት አባሎች

ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም (የካቲት 20 ቀን 2001 ዓ.ም.)

ቅንጅትን ያፈረሰው የጥቂት ሰዎች ግለኛና አምባገነናዊ አሰራር በሌላ መልክ በአንድነት ውስጥ ሲከሰት

መግቢያ

አንድ መሰረታዊ ጥያቄ የሚያከራክር ሆኖ አላገኘሁትም፤ያነጋገርኳቸው የአንድነት አባላት ሁሉ ከመድረክ ጋር መቀራረብ፣ መወያየትና መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ትልቁና ዋናው ጥያቄ በአንድነትና በመድረክ መካከል የሚፈጠረው ግንኙነት መዋቅራዊ ነው? ወይስ ተግባራዊ? (structural or functional?) የሚለው ይሆናል።

 

መዋቅራዊ ህልውናን ሊያሳጣ ይችላል፤ ተግባራዊው አስፈላጊ በሆኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ በአቻነትና በነጻነት መመካከርን የሚያመቻች ይሆናል። ከነዚህ ከሁለቱ አማራጮች የትኛውን መንገድ መርጠን ከመድረክ ጋር እንቀራረባለን? በአሁኑ ጊዜ በአንድነት አባሎች መካከል የተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት በለዚህ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ከመሆኑም በላይ የደንብና ሥርዓት ጉዳዮችም አሉበት፤ በደንቡና ሥርዓቱ እንጀምር።

 

አንደኛ፡- የብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥልጣንና ኃላፊነት

 

የአንድነት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 14 የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ምክር ቤት መሆኑን ይደነግጋል።

 

አንቀጽ 14.7 ደግሞ "የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የብሔራዊ ምክር ቤቱን ውሳኔዎችና መመሪያዎች በስራ ላይ ያውላል።" ይላል።

 

አንቀጽ 14.10 "ከመሰልና አቻ ድርጅቶች ጋር ሊኖር የሚገባን የትግል ግንኙነት በተመለከተ የብሔራዊ ምክር ቤቱን ውሳኔና መመሪያ ተግባራዊ ያደርጋል።" ይላል።

 

በነዚህ ሶስት ደንቦች እንደምንገነዘበው የስራ አስፈጻሚው፤ የብሔራዊ ምክር ቤቱን መመሪያ ተከትሎ የሚሰራ እንጂ የፓርቲውን ህልውና በሚነካ ጉዳይ ላይ መወሰን አይችልም።

 

ሁለተኛ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ስልጣንና ኃላፊነት

 

አንቀጽ 11 "ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛው የፓርቲው የስልጣን አካል ነው" ይላል።

 

የብሔራዊ ምክር ቤቱን ስልጣን በተመለከተ ደንቡ በአንቀጽ 11.9 "ከመሰልና አቻ ድርጅቶች ጋር የሚመሰርታቸውን ከህብረት እስከ ውህደት የሚደርሱ የትግል ግንኙነቶችን በተመለከተ ስምምነት ይፈጽማል፤ ይህንንም ለጠቅላላ ጉባኤው ያሳውቃል።" ይላል።

 

እነዚህ ደንቦች ደግሞ በትግል ግንኙነት ጉዳይ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ያለውን ስልጣን በግልጽ ያመለክታል።

 

ሶስተኛ በጥር 30 ቀን 2001 ዓ.ም. የብሔራዊ ምክር ቤት ከመድረክ ጋር ስለሚኖር ግንኙነት የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

 

"መድረኩን በተመለከተ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመድረክ ጋር በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የገለጠውን በማመን የስራ አስፈጻሚውን ሀሳብ ተቀብሏል። አፈጻጸሙን በተመለከተ የስራ አስፈጻሚው (እንደ አስፈላጊነቱ የቴክኒካል ኮሚቴዎችን በመጨመር) የአንድነትን ፖለቲካዊ አላማ መሰረት አድርጎ ግንኙነት እንዲጀምር የተደረሰበትንም ስምምነት ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንዲያጸድቅ። ይህ የምክር ቤቱ መመሪያ የስራ አስፈጻሚው ከመድረክ ጋር ግንኙነት እንዲጀምርና የተደረሰበትንም ስምምነት ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንዲያጸድቅ።" ይላል።

 

አራተኛ በየካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር (መድረክ) “በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ” በሚል ርእስ ስር የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ (አንድነት) እንደተቀላቀለ በግልጽ ይናገራል። ከዚህ አልፎ መቀላቀሉን ለማረጋገጥ በመግለጫው ላይ የአንድነት ማህተም አርፎበታል። ይህ ድርጊት በሁለት መንገድ መመሪያውን የጣሰና ስርአትን ያልተከተለ ግለኛና አምባገነናዊ ዝንባሌን የሚያመለክት ነው። በአንድ በኩል ግንኙነት እንዲጀመር የተባለውን አልፎ በመቀላቀል እንዳጠናቀቀው ያሳያል፣ በሌላ በኩል ለምክር ቤቱ አቅርቦ እንዲያጸድቅ የተባለውን መመሪያ አልፎ መግለጫውን በአንድነት ማህተም አጽድቆታል፤ አንድ ሰነድ ላይ ማህተም የሚደረግበት ሲጸድቅ ነው።

 

አምስተኛ የቅልቅሉን ጉዳይ የብሄራዊ ምክር ቤቱ ይቅርና ብሔራዊ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም የሰማውና የተነጋገረበት ቅልቅሉ ከተፈጸመ በኋላ በየካቲት 13 መሆኑ ሌላውና የመጨረሻው የግለኛነትና አምባገነናዊነት ተግባር ነው።

 

ስድስተኛ በአጠቃላይ ከመድረክ ጋር ግንኙነት ሊኖር የሚገባ መሆኑ ለብዙ የአንድነት አባሎች የማያጠራጥር ቢሆንም ብዙ ውይይትና ማጣራት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችም መኖራቸው ይታመናል። ነገር ግን መቀላቀል በሚል የወጣው መግለጫ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሰተውን መመሪያና ውሳኔ የሚጥስና በጣም በጥድፊያ የተደረገ በመሆኑ ከመድረክ ጋር እንዲኖር የሚፈለገውን ግንኙነት የሚያበላሽ ሊሆን ስለሚችልበአስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ያስፈልጋል።ደንብንና መመሪያን በመጣስና ስልታንን በግለኛነት በመጠቀም የሚወሰድ እርምጃ ድርጅቱን የሚጎዳና ኣላማውንም የሚያደፈርስ ይሆናል። የአንድነት ማህተምም በክብር አለመያዙ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥር በቶሎ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው። ግልጥና ተተያቂነት ያለበት አሰራር እንዲለመድ ኃላፊነት የጎደለውን እርምጃ የወሰዱት ሰዎች መጠየቅ አለባቸው። በተጨማሪም አንድነት ለመድረክ ያለውን በጎ የትብብር መንፈስ ማስታወቅና ግንኙነቱን ማደስ ያሻዋል።

 

ሰባተኛ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች አስፈላጊውን ትኩረት ስበው መታረም ያለባቸውን የአሰራር ግድፈቶች መወገዳቸውን የሚያመለክት ተጨባጭ እርምጃ ካልታየ፣ በተያዘው መንገድ ከቀጠልን የአንድነት ህልውና አስጊ ደረጃ ላይ እንደሚደርስና አደራ የጣለብንን ህዝብም የምናሳዝን ይሆናል። በመድረክ ጉዳይ ብዙ የሐሰት መረጃዎች ለምክር ቤቱ እንደቀረቡና ውሳኔውን እንዳዛቡት ይነገራል፣ ይህ የሚያሳዝን ነው፤ መተማመንን ያሳጣናል።

 

እግዚአብሔር ለአደራ የምንበቃ ያድርገን!

 

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ